ጥቅምት ፳፭ (ሃያ አምት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የቀድሞው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባዔ የአሁኑ የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ( ሰመጉ) ባወጣው 132ኛ ልዩ መግለጫ በክልሉ በመንገሽና ጎደሬ ወረዳዎች ተፈጥሮ በነበረው ግጭት የተገደሉ የ60 ሰዎች ስም ዝርዝር ይፋ አድርጓል።
በሪፖርቱ እንደቀረበው 27 የአማራ፣ 27 የመዠንገር፣ 2 የከፋና 4 የኦሮሞ ተወላጆች ተገድለዋል። እንዲሁም 16 የአማራና 6 የመዠንገር ተወላጆች የአካል ጉዳት ሲደርስባቸው፣ 36 የአማራ ተወላጆች ተፈናቅለዋል። 4 የአማራ ተወላጆችም የደረሱበት አለመታወቁ በሪፖርቱ ተጠቅሷል።
ከተገደሉት ሰዎች መካከል የመዠንገር ተወላጅ የሆኑት የዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ ፀጋዬ ጌታሁን ሲገኙበት፣ መካሻ መንግስቱ የተባሉ ሰው ደግሞ እስከነባለቤታቸው ተገድለዋል።
ሰመጉ በግጭቱ መነሻ ዙሪያ የተናገረው ነገር ባይኖርም፣ በተለያዩ አካባቢዎች የብሄረሰቦች ግችት እየተስፋፋ ቢመጣም መንግስት ይህን አሳሳቢ ጉዳይ በዘላቂነት ለመፍታት እያደረገ ያለው ጥረት ከችግሩ ክብደትና እየደረሰ ካለው ጉዳት አንጻር ሲታይ ጨርሶ የሚመጣጠን አይደለም ብሎአል።
በመንግስት በኩልተመሳሳይ ግጭቶች እንዳይፈጠሩ ዘላቂ መፍትሄ ማበጀት ለነገ የማይባል አንገብጋቢ ጉዳይ ነው የሚለው ሰመጉ፣ በመዠንገር ዞን ለተፈጠረው ሰብአዊ እልቂትና መንስኤ የሆኑ ምክንያቶችንና ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ግልሰቦችንና ቡድኖችን አጣርቶ አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድም ጠይቋል።
ሰመጉ ባወጣው መግለጫ ላይ መንግስት የሰጠው አስተያየት የለም። መኢአድ የተገደሉ ዜጎችን ቁጥር በመቶዎች የሚቆጠር ነው ይላል::
ኢሳት በበኩሉ ምንጮችን ዋቢ በማድረግ ከ50 በላይ ዜጎች መገደላቸውን ዘግቦ ነበር።
Keine Kommentare:
Kommentar veröffentlichen