Netsanet: ለነፃነታችን በጋራ ቆመን ታሪካዊ ግዴታችንን የምንወጣበት ጊዜው አሁንና አሁን ነው!

Mittwoch, 19. November 2014

ለነፃነታችን በጋራ ቆመን ታሪካዊ ግዴታችንን የምንወጣበት ጊዜው አሁንና አሁን ነው!

የኢትዮጵያ ህዝብ ፍትህና ነፃነት እንደናፈቀ፤ ሀገራችንም ቅን መሪ እንዳጣች ዘመናት ተቆጠሩ። በየጊዜው የመጡ ገዢዎቿ በህዝቧ መሥዕዋትነትና ታላቅ ተጋድሎ በተገኘ ድል ሥልጣን ላይ ከወጡ በሗላ፤ በህዝብ ፊት ቃል የገቡትን ወደ ገደል ሰደው፤ ዘግናኝ በሆነ ሥርዓታቸው በማፈን ህዝቧን ለከፋ ድህነትና ጉስቁልና ሲዳርጉት፤ አይናችን እያየ ጆሮአችንም እየሰማ፤ አመታት ተቆጥረዋል። የቅርብ ታሪካችን እንደሚመሰክረው፤ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ፆታ፣ እድሜ፣ ሃይማኖት፣ ጎሳና፣ ዘር ሳይለይ ለአለፉት ዘመናት በተለይም በአምባገነኖቹና በጨካኞቹ የደርግና የህወሓት/ኢህአዴግ ስርአቶች እንደ ባእድ ወራሪ በገዛ ልጆቹና ሃገሩ የግፍ ግፍ ሲፈፀምበት፣ ምድሪቱም በደም ጎርፍ ስትታጠብና፣ ሁሉም በሚችለውና በአቅሙ እነዚህን የሰው አውሬዎች ከላዩላይ ለማስወገድ ሲኳትንና በመራራ ትግሉና በውድ ልጆቹ መስዋዕትነት የመጀመሪያውን ጭራቅ አስወግዶ ሁለተኛውን ሰይጣን ሲተካ ሃዘኑ ያልጠናበትና ፈጣሪውን ያላማረረ ኢትዮጵያዊ የለም።
በተለይ የህወሓት/ኢህአዴግ ሥርዓት በህዝብና በሃገር ላይ የሚያደርሰው መከራ፣ ግፍና፣ በደል በመጠንም በአይነትም እጅግ በዝቶ፤ ምን ያህል አስከፊና ልብ የሚሰብር ደረጃ ላይ እንደደረሰ እለት ከለት ስቃዩን እየተቀበለ የሚገኘው ህዝብ በሚገባ ያውቀዋል። በእርግጥም ህዝብ እየተቀበለው ያለውን የስቃይ ብትር መልሶ መላልሶ ማስተጋባት በስቃዩ ላይ ስቃይ መጨመር፤ ቁስሉንም ክፉኛ ማባባስ ሆኗል። ይህ አረመኔ ሥርዓት ላለፉት 23 አመታት በማናለብኝነት የፍትህ ሥርዓቱን በቁሙ ገንዞ፤ የፈለገውን ሲገድልና በድብደባ አካሉን ሲያጎድል፤ ሲሻው ደግሞ ህገመንግስታዊውን ሥርዓት በሃይል ለመናድ ወይንም አመፅ ለማነሳሳት የሚሉ ሃሰት የይምሰል ምክንያቶችን በመደርደርና በማስተጋባት፤ ብሎም እራሱ ያወጣውን ህገመንግስት በሚፃረር መልኩ የፀረ አሸባሪ አዋጅን በማወጅ፤ ሃሳቡን በነፃነት ለመግለፅ የሞከረን ሁሉ አሸባሪ የሚል ተቀፅላ ስም በመስጠት፤ አያሌ ንፁሃን ዜጎችን ዘብጥያ በጨለማ ክፍል እንደ ርካሽ እቃ ሲወረውር ኖሯል። በዚህም ምክንያት ዛሬ በየእስርቤቱ የሚማቅቀውና ከሚወዳት ሃገሩ ህይወቱን ለማትረፍ የተሰደደው ጋዜጠኛ፣ ፖለቲከኛ፣ መምህር፣ ተማሪው፣ ገበሬው፣ ወጣቱ፣ ጎልማሳው፣ አዛውንቱ፤ ምን ያህል አንደደረሰ ቤት ይቁጠረው። ከዚህም ባለፈ የህወሓት/ኢህአዴግ ሥርዓት አያሌ የከተማ ነዋሪን በሊዝ አዋጅና በልማት ስም ከቤት ንብረቱ አፈናቅሎ ሜዳ ላይ በትኗል። አርሶ አደሩ ከአያት ቅድመ አያቱ የወረሰው አንጡረ ሃብቱንና መሬቱን ለህንድ፣ ለአረብ፣ ለቱርክና፣ ለሌሎች ባእዳን ባለሃብቶች በጥሬ ብር በሃራጅ ቸብችቦ፤ እንዲሁም ከተማን በማስፋፋት ስም ብዙሃን ገበሬውን ከነቤተሰቡ መኖሪያ አልባ በማድረግ ለከፋ ችግር አጋልጧል። ይህ ሁሉ ግፍና በደል አልበቃ ብሎት፤ ህዝብ እየተፈፀመበት የሚገኘውን እኩይ ሴራ መረዳትና ማገናዘብ እንዳይችል ለማድረግ፤ በማይፈታ የድህነት አረንቋ ውስጥ ተዘፍቆ ለዘላለም አገልጋይ ሆኖ እንዲኖር፤ የነፃ ገበያ ሥርዓት በሚል ሽፋን ገበያውን በእጃዙር ተቆጣጥሮ የሸቀጥና የምግብ ዋጋን ከአቅም በላይ ከፍ በማድረግ፤ ሃገሪቱን ጥቂቶች በዘረፉት የተትረፈረፈ ሃብት የሚበለፅጉባት ገነት፤ ነገር ግን ከ80% በላይ ህዝብ ከድህነት ወለል በታች ተዘፍቆ ክፉኛ የሚሰቃይባት ሲኦል አድርጓታል።
ዛሬ ጥቂቶቹ ገዢዎቻችን በወር በሚሊዮኖች በሚቆጠር ብር የህዝብን ንብረት ሲመዘብሩና የግላቸውን ሃብት ሲያካብቱ፤ በከተሞች የውሃና የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንኳ በፈረቃ ከሁለት ሳምንት በላይ ጠብቆ ማግኘት አስቸጋሪ ሆኗል፤ የቴሌፎን ጥራቱም ዘቅጦ እየተቆራረጠ፤ በኢትዮጵያ የመኖር ትርጉሙ ህመም፣ ተስፋ ማጣትና፣ ጨለማ ሆኖ ቀጥሏል። ዛሬ የመብትና የነፃነት በሮች በሁሉም አቅጣጫ በማናለብኝነት ተከርችመው፤ መናገር፣ መፃፍና፣ መብትን መጠየቅ በጥብቅ የተከለከሉ አደገኛ ክስተቶች ሆነዋል። ዛሬ በመላው ሃገሪቱ አድርባይነትና ሙሰኝነት ነግሶ፤ ከቀበሌ እስከ ወረዳ፣ ከገጠር እስከ ከተማ ጥቂት ፈላጭ ቆራጮች ህዝባችንን እያንገላቱትና የማይሸከመውን መከራ እየጫኑበት ይገኛሉ። ለዘመናት በብዙሃን ህዝብ ጥረትና መሥዕዋትነት የተገነባችና የኖረች ሃገር በጥቂት ግዴለሽ አምባገነኖች ከምድር እየጠፋች ትገኛለች። ለአመታት ተጠብቆና ተከብሮ የኖረው ማንነታችን ተንቋል። ለዘመናት ከኛጋር የኖረው አብሮነታችንና አንድነታችን እየተበታተነ፣ እየጠፋና፣ እየተገፋ ይገኛል። መለያችን፣ ማንነታችንና፣ ክብራችን የሆነው፣ ከዚህም ባለፈ የበርካታ ሃገራት ህዝቦች የነፃነት ተምሳሌትነቱን በክብር የሚቀበሉት ሰንደቃላማችን ረክሷል። የብዙሃን ውድ ዜጎች ህይወት በደም የተከፈለበት ዳርድንበራችን ተደፍሯል። ዛሬ የኢትዮጵያ ህዝብ ድህነቱና የኑሮ ውድነቱ ክፉኛ ተጭኖት፤ የፍትህ እጦት እያንገላታው፤ ለዘመናት አብሮት የኖረው ፍቅሩና መተሳሰቡ ሲሸረሸርና ሲናድ፤ ዘረኝነቱ ስር ሰዶ በሃገሩ በነፃነት የመዘዋወርና የመኖር የዜግነት መብቱን በመነፈጉ፤ ለዘመናት ከኖረበት ቀዬው ተገፍቶ ተስፋው ሲጨልም፤ በአይኑ እያየ፣ በጆሮው እየሰማና፣ አንጀቱ እያረረ፤ በቁጭት ለውጥን እየናፈቀ ይገኛል።
በአለማችን ታሪክ እንደተመዘገበውና በቅርቡም እንዳየነው አምባገነኖች ፈልገው የህዝብን ጥያቄ ሲመልሱ ታይተው አይታወቁም። ሁላችንም እንደምናውቀው የኢትዮጵያ ህዝብ በተለያዩ የተቃዋሚ ድርጅቶችና ሌሎች ህዝባዊ ስብስቦች አስተባባሪነት፤ በተጠሩ በርካታ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎች ላይ ብሶቱን ሲያሰማና ጥያቄውን ባደባባይ ሲያቀርብ ቆይቷል። ነገር ግን ሀገራችንን የተቆጣጠሩት ጥቂት አምባገነኖች የህዝብን ጥያቄ በአግባቡ ከማስተናገድና ከመመለስ ይልቅ በህዝብ ላይ ያላቸውን ንቀትና ጥላቻ፤ በፈፀሙብን አሰቃቂ ግፎችና አረመኔ ተግባራት በተደጋጋሚ አረጋግጠውልናል። ውድ የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ! ይህ አሳዛኝ ሂደት እስከመቼ ይቀጥላል!? ጥቂቶች እየጫኑብን የሚገኘውን በደልና ግፍ እስከመቼ ችለን በዝምታ እንዘልቃለን!? እስከመቼስ በጣት የሚቆጠሩ ጥቂት ሆዳሞች ሚሊዮኖችን እያፈኑ፤ ሃገርን እየዘረፉና፤ ህዝብን እያሸበሩ በትከሻችን ላይ ተሸክመን እንችለዋለን!? እስከመቼ የውሸት ዲስኩራቸውንና ባዶ የተስፋ ዳቦአቸውን እየተመገብን መኖር ይቻልን ይሆን!? መልሱ የሚገኘው እኛና እኛ ጋር ብቻ ነው! ከእንግዲህ የጥቂቶች ኪስ ማደለቢያ የሆኑትን ባዶ ፎቆች ከሩቁ እያየ የተስፋ ዳቦ የምንመገብበት ጊዜ ማብቃት ይኖርበታል። ይህ ትግል የመኖር ህልውናችንን የምናረጋግጥበትና ሃገራዊ ተስፋችንን የምንገነባበት ወሳኝ ትግል ነው። በመሆኑም እያንዳንዱ አስተዋፆአችን የዜጎች ሰብአዊ መብት የሚከበርባት፤ የህግ የበላይነት የሚረጋገጠባት፤ ፍቅርና ሰላም የሚነግስባት፤ የሁሉም ህዝብ የሆነች ኢትዮጵያን በጋራ ትግል የምናረጋግጥበት፤ የሰላማዊ ትግሉ ወሳኝ ታሪካዊ የዜግነት ድርሻችን ነው። በአንድነት ተባብረን መኖራችንን የምናረጋግጥበት ጊዜው አሁን ነው። በሃገራችን የመኖር ተስፋችንን የምናስመልስበትና የምንገነባበት ጉልበቱም፣ ችሎታውም፣ እውቀቱም፣ ብቃቱም በእጃችን ነውና፤ ለነፃነታችን በአንድነት ቆመን ህዝባዊ የበላይነታችንን በማረጋገጥ ታሪካዊ ግዴታችንን ለመወጣት ሁላችንም ዝግጁ እንሁን።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen