“ዓረብ ስፕሪንግ” እየተባለ ስለሚነገረው ህዝባዊ አብዮት ብዙ ተብሏል። ያ ህዝባዊ አመፅ ለውጥ አምጥቷል።ማን ይነካኛል ብሎ ዜጎቹን መከራ ሲያበላ የነበረው የቱኒዚያው ቤኒ ዓሊ ዛሬ የተረሳ ግለሰብ ሁኗል። እኔ ከሌለው ይህች አገር ትጠፋለች ሲል የነበረው ጋዳፊ ከተደበቀበት የአይጥ ጉድጓድ ውስጥ ተጎትቶ ወጥቶ እንደ ውሻ ተቀጥቅጦ ሙቷል። ሆስኒ ሙባረክም እንዲሁ ተርስቶ ቀርቷል። የየመንም አምባገነን አገር ጥሎ ሂዷል።በሶሪያም አምባገነኖች ከእንግዲህ ተረጋግተው ህዝባቸው ላይ የሚያላግጡበት ዘመን አብቅቷል።
በቱኒዚያዊው ሙሃመድ ቦዛዚ መስዋዕትነት የተጀመረው ህዝባዊ ዓመፅ ብዙ የዓረብ አገራትን አዳርሷል። ይህ ህዝባዊ አመፅ ከዓረቡ ዓለም ባሻገር ወደ ጥቁር ህዝቦች ተሽጋግሯል። ቡርኪና ፋሶዎች ለ27 ዓመት ስልጣኑን ሙጥኝ ብሎ የኖረውን ብሌስ ኮምፓዖሬን ከተቆናጠጠው የስልጣን ወንበር ላይ አባረውታል።
ብሌስ ኮምፓዖሬ የገዛ ወገኑን ሠላም እያሳጣ በጎሬቤት አገሮች ዋና አስታራቂ፤ የሠላም ሰው መስሎ ለመታየት ይኳትን ነበር። አሜርካኖች ቁልፍ ወዳጃችን ይሉትም ነበር። የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም በጎረቤት አገሮች መረጋጋት ዋና ተዋኒያኒ እያለ ያሞጋግሰው ነበር። ብሌስ ኮምፓዖሬ የራሱ እያረረበት፤ የጎሬበቱን እያማሰለ የአሜሪካኖችንና የአውሮፓዊያንን ቀልብ ይዞ ድፍን ሃያ ሰባት ዓመት በስልጣን ተንጠላጥሎ ኑሯል።
የቡርኪናው ብሌስ ኮምፓዖሬ 27 ዓመት ስልጣን ላይ ሲቆይ እንደ ህወሃት ከገዛ ህዝቡ ድምፅ ይልቅ የሌሎችን ድምፅ መስማት ይመርጥ ነበር። ህዝቡ ነፃ ምርጫ ይደረግ፤ ዜጎች በመረጡት መሪ ይመሩ፤ አገር አይታመስ ቢሉት ሊሠማ አልወደደም። ከዚህ ከወገኑ ድምፅ ይልቅ ከባህር ማዶ “ቁልፍ ወዳጃችን” ለሚለው ድምፅ ይገዛ ነበር። በጎረቤት አገሮች ውስጥ አስታራቂ እና ሽማግሌ እኔ ነኝ ብሎ ራሱን በመሾም ላይ ታች እያለ ሌሎችን ለማስደሰት ይንከላወስ ነበር።ይህ ግን ክብር አልሆነለትም።
አልቃይዳና ቦኩ ሃራምን የመሰሉ አሸባሪ ኃይሎች በተነሱ ግዜ ለብሌስ ኮምፓዖሬ ሰርግና ምላሽ ሆነለት። አሸባሪነትን ለመዋጋት የአሜሪካኖች ምርጥ ወዳጅ ለመሆን በቃ። የአየር ክልሉንም ለአሜሪካን የስለላ አውሮፕላኖች እንደልብ ፈቀደ።አሜሪካኖችም በወቅቱ ወዳጅ ብለው የጠሩትን ግለሰብ የሚፈፀመውን ኢ-ዲሞክራሲያዊ ሁኔታ እና የሚፈፀመውን ሰብዓዊ መብት ጥሰት አይተው እንዳላዩ ሆነው ልክ ለህወሃት እንደሚያደርጉት የገንዘብና ሌሎች እርዳታዎችን መለገሳቸውን ቀጥለው ነበር። አሸባሪ ተብለው የተፈረጁ ኃይሎች በየቦታው የመፈጠራቸው ሁኔታ ለህወሃቶችም የተመቻቸ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው የሚካድ አይደለም።
ኮምፓዖሬ በመፈንቀለ መንግስት ስልጣን ከጨበጠ በኋላ ምርጫ በተካሄደ ቁጥር እርሱና ፓርቲው ምርጫ አካሂደን አሸንፈናል እያሉ ለ27 ዓመት በስልጣን ቆይተዋል። በሌላ መልኩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ምርጫው የተጭበረበረ እንደሆነ ቢናገሩም ሰሚ ሳያገኙ ኑረው ነበር። ግዜው ደርሶ የህዝብ ቁጣ ገንፍሎ ከፍርሃት በላይ ሆነና ኮምፓዖሬ ሃያ ሰባት ዓመት ሙሉ ከተዘባነነበት ቤተ-መንግስት ሾልኮ ለሰደት ተዳረገ።
ህወሃቶች ይሄንና ከዚህ ቀደም የታየውን የህዝብ ቁጣ አይተዋል። ከዚህ ዓይነቱ የህዝብ ቁጣ የሚቀስሙት ትምህርት ይኖራል ብለን አንጠብቅም። በፈርዖን ትዕቢት ድንኳን ተጠልለው የሚኖሩ ኃይሎች የህዝብ ቁጣ ገንፍሎ መቃብር እስከ ሚጨምራቸው ድረስ ይማራሉ ብሎ መጠበቅ ከንቱ ምኞት ነው።ዛሬ ሁሉ በእጃቸው፤ ሁሉ በደጃቸው ፤ሚድያው የእነርሱ፤ የመረጃ መረቡ ከአገር ደህንነት ይልቅ የእነርሱን እድሜ ለማራዘም የሚሰራ ሆኖ እንደሚቀጥል አምነዋል። የአገሪቷ አጠቃላይ ሃብትም በእጃቸን ነው። መከላከያ ኃይሉም እኛን ከመጠበቅ ውጪ ሌላ ተልዕኮ የለውም ብለዋል።ይሄን ሁሉ በእጃችን ይዘን ማነው የሚነካን? የትኛውስ ህዝብ ነው የሚነሳብን ብለው ልባቸውን እንደ አለት ማደንደንን መርጠዋል። የህዝብ አመፅ ተነስቶ አገር ከመታመሱ በፊት ለሁሉም በእኩል ደረጃ ሊጠቅም የሚችል ምን በጎ ነገር እንሥራ ብለው ለማሰብ ምንም ፍላጎት የላቸውም። እንዲያውም የህዝብ አመፅ ቢነሳ ውጤቱን ስለማታውቁት “ከማታውቁት መላክ፤የምታውቁት ሴይጣን ይሻላችኋል” ለማለት እየዳዳቸው እንደሆነ እያየን ነው።
ህወሃቶች ትውልድ፤ ወገን፤ አገር የሚባል ቋንቋ እንደማያውቁ በተግባር አሳይተውናል።የህወሃቶች አገራቸው ድርጅታቸው እንጂ ኢትዮጵያ አይደለችም።እነርሱ አገር ሲሉ እነርሱን እንጂ ሌላውን እንደማይጨመር መልሰው መላልሰው ነግረውናል። ”እኛ ከሌለን ኢትዮጵያ ትበተናለች” የሚለው መፈክር ምንጩ ህወሃቶች አገርና ትውልድ የሚል ቋንቋ በውስጣቸው የሌለ መሆኑን ይገልጥልናል። ይሄ መፈክራችሁ ቅዥት ነው፤ ተው ከዚህ ቅዥታችሁ ወጥታችሁ ወደ ገሃዱ ዓለም ተመለሱ፤ በገሃዱ ዓለም አገር እና የተቆጣ ትልቅ ህዝብ አለ። ይህ አገርና ህዝብ ከእናንተ በላይ ነው ብሎ ሊመክራቸው የሚሞክር ከተገኘ አሸባሪነት ተለጥፎበት ጠላት ይባላል።
ለብሌስ ኮምፓዖሬ የአልቃይድና የቦኩ ሃራም መፈጠር ሰርግና ምላሽ የሆነውን ያህል አሸባሪነት ለህወሃቶች የመኖሪያቸው ድንኳን ሁኗቸዋል። አሸባሪነትን ለመዋጋት በሚል ኮምፓዖሬ ለአሜሪካኖች ብርቱ ወዳጅ እንደ ነበረው ሁሉ ህወሃቶችም አሸባሪነትን ለመዋጋት በሚል ሽፋን ለአሜሪካኖች ወዳጅ ለመሆን በቅተዋል። አሜሪካኖችም የህወሃትን ሥም ከአሸባሪነት መዝገብ ሳይፍቁ፤ ህወሃቶች የሚፈፅሙትን ወንጀል እያወቁ እንዳላወቁ፤ አይተው እንዳላዩ ሁነው እርዳታቸውን ሳያቋርጡ እሰከ ዛሬ አሉ። ይህ ለህወሃቶች ባዶ ድፍረት እና የትዕቢታቸውም ምንጭ ሁኗቸው የተሻለ ሃሳብ አለኝ የሚለውን ሁሉ አሸባሪ እያሉ ነው። ህወሃቶችን የሚያሸብራቸው ብዙ ነው። የነፃነት ጥያቄ ያነሳ ያሸብራቸዋል። እኛ ከህወሃት አናንስም፤ህወሃትም ከእኛ አይበልጥም የሚል ከተነሳም ያሸብራቸዋል። እኔ ህወሃትን አልመርጥም የሚል ድምፅ ከተሰማም አሸባሪ ነው። ይሄ የሚያሳየን ህወሃት ኃጢአቱ የሚያሳድደው እና ጥላው የሚያስበረግገው ድርጅት ወደ መሆን መሸጋገሩን ነው። ህወሃቶች በሰሙት ድምፅ ሁሉ እየበረገጉ አገሪቷን እያመሱ እንደማይዘልቋት እኛ ልናስታውሳቸው እንወዳለን።
ህወሃቶች ከህዝቡ ድምፅ ይልቅ የሌሎችን ድምፅ መስማት ከነ ልጅ ልጆቻችን አገሪቷን ለመበዝበዝ ይረዳናል የሚል የደንቆሮ ዕምነት አላቸው። በየጎረቤት አገር ውስጥ ዘው ብለው እየገቡ ራሳቸውን የሠላም መለእክተኛ አድርገው ለዓለም ህዝብ ለማሳየት ይኳትናሉ። እኛ ከሌለን ምስራቅ አፍሪካ በአክራሪ ኃይማኖተኞች ትጠለቀለቃለች፤የአሸባሪዎችም መናኽሪያ ትሆናለች ኢትዮጵያም ትበተናለች እያሉም የሌሎችን ቀልብ ለመያዝ ደጅ ይጠናሉ።ከአሜሪካንና ከአውሮፓዊያን እጅ ለሚወረወርላቸው ምናምን ሲሉ ሳይላኩ ይሄዳሉ፤ ሳይጠሩ ከተፍ ይላሉ። ህወሃቶች ይህን ተላላኪነትንና አደር ባይነት እንደ ሥራ ይቆጥሩታል።ሥራ በመሆኑም ሶማሊያ ዘው ብለው ገብተው የእኛን ልጆች አስከሬን በመቋዲሾ ጎዳና ላይ አስጎትተው መሳለቂያ እንዲሆን አድርገዋል። ህወሃቶች ሶማሊያ ዘው ብለው በመግባታቸው ኢትዮጵያ እንደ አገር ስትጎዳ በግል ደረጃ ግን የህወሃት ጄኔራሎችና ባለሟሎቻቸው በተገኘው የደም ገንዘብ ስም አጠራሩን እንኳ የማያውቁትን አልኮሆል እየተጎነጩ ተዘባነውበታል። ባለ ሃብትም ለመሆን በቅተዋል።
እነዚህ ቡድኖች በህዝቡ እና በአጠቃላይ አገሪቷ ላይ የሚፈፅሙት ክህደት በየትም አገር ታይቶ የሚታወቅ አይደለም።ብሌስ ኮምፓዖሬና ፓርቲው ከህወሃቶች ጋር ሲነፃፀሩ እንደ መልዓክና ሴይጣን ናቸው። ህወሃቶች ከሰው አብራክ የተፈጠሩ አይመስሉም። የስግብግብነታቸው ወሰን ማጣት፤ ምንም አገራዊ ራዕይ የሌላቸው መሆን፤ ርህራሄ የሌላቸው ፍፁም ጨካኞች መሆናቸው፤ ከእውነት ጋር የማይተዋወቁ ውሸትን የኑሯቸው ድንኳን ማደረጋቸው ሲታይ ህወሃትን የሚመስል ክፉ በየትም ዓለም አለ ለማለት ይቸግራል። የኢትዮጵያ ህዝብ በህወሃቶች የደረሰበትን ብዙ መከራ ተሸክሞ ለብዙ ዘመን ኑሯል። ብዙ ዜጎች አገር አልባ ሁነው ተንክራታች ሁነው ቀርተዋል። ብዙ እናቶች እንባቸውን በመዳፋቸው የሚያፍሱ ሁነው ቀርተዋል። ይህ ግን የሚያበቃበት ግዜ እሩቅ አይደለም።
ህወሃቶች ሆይ ስሙ !
ነገ እንደ ዛሬ አይሆንላችሁም። አንድ የዋህ አምባ ገነን ገዢ ሊፈፀመው የሚችለውን ድርጊት ለፈፀመው ለብሌስ ኮምፓዖሬ ዛሬ እንደ ትላንትና እንዳልሆነለት ተመልከቱ። እናንተ እያደረሳችሁ ያላችሁት በደል እና እየፈፀማችሁ ያላችሁት የአገር ክህደት ምሳሌ የማይገኝለት ነው። የእናንተ ምርጫ ከሰላም ይልቅ ደም መፋሰስ፤ አብሮ ከመኖር ይልቅ መለየት፤ ለወገንና ለአገር ከማሰብ ይልቅ ለግል ጥቅም ብቻ መሯሯጥ ሁኗል። በዚህ ምርጫችሁ የተቆጣ ህዝብ እንደ ተደፋነ እሳት ውስጥ ውስጡን እየጨሰ መሆኑን ለማስተዋል ትዕቢታችሁ ሂሊናችሁን ጋርዶታል። ትዕቢታችሁ ወሰን ከማጣቱ የተነሳ እዚህም እዚያም እየተነሱ ያሉትን ብዙ የብሶት ድምፆችን ለማፈን ብዙ ንፁሃን ዜጎችን ትገድላላችሁ፤ታስራላችሁ፤ ታንገላታላችሁ፤ ታዋርዳላችሁ። እናንተን ሸሽቶ ወደ ጎሬቤት አገር የሚሰደደውን ሳይቀር በቅጥረኛ ነፍሰ ገዳዮች ታስገድላላችሁ፤ እያሳፈናችሁ ትወስዳላችሁ።የምትፈፅሙት ግፉ ፅዋውን ሞልቷል።
እኩይ ዲርጊታችሁ እያሳደዳችሁ የገዛ ጥላችሁ እንኳ እያሸበራችሁ ለአገራቸው በጎ ራዕይ ያላቸውን ጥሩ ዜጎች በሙሉ አሸባሪ እያላችሁ እንደምትከሱ ዓለም ሁሉ ዓይኑን ከፍቶ እየታዘበ ነው። በእኩይ ዲሪጊቶቻችሁ ምክንያት ከመሸበራችሁ የተነሳ ሁሉንም ድምፅ ለማፈን የምታጠፉት የአገር ሃብት ነፃነትን፤ እኩልነትን፤ ፍትህንና በእውነት ሊሠራ የሚችል ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ቢውል ኑሮ በእውነት ሠላም አግኝታችሁ መኖር በቻላችሁ ነበር። እናንተ ግን የጨለማውን መንገድ መርጣችኋልና እርሱን እንደምታገኙ ቅንጣት ታክል ጥርጣሬ አይግባችሁ።
አዎን በምርጫችሁ መሠረት በሚገባችሁ ቋንቋ የሚያናግራችሁ ትውልድ የአያቶቹን የነፃነት ጋሻና ጦር አንስቶ ተሠማርቷል። አይናችሁ እያየ፤ጆሯችሁም እየሰማ ወጣቶች ከመላዋ ኢትዮጵያ ተሰባስበው አያቶቻቸው በኩራት በቆሙበት ተራራ ላይ አንገታቸውን ቀና አድርገው እየተመላለሱበት ነው። ህወሃትን የመሠለ ዘረኛ፤ ሌባ እና አደረ ባይ ቡድን ኢትዮጵያን የመሰለች ትልቅ አገር ሲያዋርድ አይተን ዝም ብንል እርግማን ይሁንብን ያሉ የኢትዮጵያ ልጆች ዝናራቸውን ታጥቀው ተነስተዋል። እናቶችም ወገባቸውን በገመድ ታጥቀው ወጣቶቹን እየመረቁ ወደ ጀግኖቹ መንደር እየሸኙ ነው። የተቀሩትም ሳያቅማሙ የኃላ ደጀን ሁነው ቁመዋል። እንግዲህ ኢትዮጵያን የሚያዋርዱ፤ አገሪቷን የሚዘርፉ፤ ንፁሃን ዜጎችን የሚያሰቃዩ ወየውላቸው።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !!
Keine Kommentare:
Kommentar veröffentlichen