Netsanet: በምርጫ ሥም የነጻነት ትግሉን ማዘናጋት አይቻልም!!

Mittwoch, 5. November 2014

በምርጫ ሥም የነጻነት ትግሉን ማዘናጋት አይቻልም!!


የ‹‹ነጻነት ለፍትሃዊ ምርጫ›› ህዝባዊ ትግል ፕሮግራም የመጀመሪያ ዙር እንቅስቃሴ በፓርቲዎች ትብብር በህዳር ወር ይጀመራል!

ከኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ትብብር የተሰጠ መግለጫ

ጥቅምት 12 ቀን 2007 ዓ.ም ትብብር የመሰረትን ዘጠኝ ፓርቲዎች ስለምስረታችን በሰጠነው መግለጫ የስምምነታችን ‹‹ … ዘላቂ ግብ ማንም ተጎጂ የማይሆንበትና ሁላችንም ተጠቃሚ የምንሆንበትን አቅጣጫ የተከተለ እንደመሆኑ ገዢው ፓርቲ/መንግስት እኔ ከሥልጣን ከለቀቅሁ በቀጣይ በሚመጣው ለውጥ አገር ትበታተናለች በማለት ህዝብን ከሚያስፈራራበት፣ ካድሬዎቹን ፣መከላከያ ሠራዊቱንና የፀጥታና ደህንነት ኃይሉን ተቃዋሚዎች ካሸነፉ አንድም ለወህኒ ካነሰም ‹‹ለልመናና የጎዳና ተዳዳሪነት›› ትዳረጋላችሁ… በሚል ሽብር ከሚነዛበት ፕሮፖጋንዳና አካሄድ እንዲመለስና እንዲታረም ዕድል የሚሠጥ›› መሆኑን ፣ ለትብበሩ አባላት ‹‹ ከምንም እና ከማንም በላይ ቀዳሚው አገርና ህዝብ ›› መሆኑንና በህዝባዊ ሠላማዊ ትግል በምትገነባው ሉዓላዊነቷ የተከበረ ዲሞክራሲዊት ኢትዮጵያ ‹‹ በሁለት ጽንፎች የተወጠረው የአገራችን የአሸናፊ-ተሸናፊ የጠቅላይ ሥልጣን ፖለቲካ ልምድ እንደሚቀየርና በከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ በህዝቦች መካከል ያለውን አብሮነት ለመበጣጠስ የተዘራውን አጥፊ ዘር ማድረቅ፣ የተሰራጨውን መርዝ ማርከስ ›› መቻሉን መግለጻችን ይታወሳል፡፡ 

አካሄዳችንን በሚመለከትም ‹‹…ለጋራ ዓላማችን እውን መሆን ያለፈው አካሄዳችን የትም እንዳላደረሰንና እንደማያደርሰን ከውድቀታችን ልምድ ቀስመን በአዲስ አስተሳሰብና የአመራርና አሰራር ሥርዓት ለማይቀረው ሥር ነቀል ሁለንተናዊ ለውጥ በግልጽነት በተጠያቂነት መርህ በጽናት ለመታገልና ለማታገል የደረስንበትን ስምምነት ስናበስር ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚመጣውን አገራዊና ህዝባዊ ኃላፊነት በመገንዘብ ›› መሆኑን ገልጸን ለዓላማችን ማስፈጸሚያ ተመጋጋቢና ተደጋጋፊ የአጭርና የረጅም ጊዜ የዕቅድ አቅጣጫ ማስቀመጠችንንም ገልጸን ነበር፡፡ የዛሬው መግለጫችን ዓላማም ባስቀመጥነው የአጭር ጊዜ ዕቅድ - ምርጫ 2007 ላይ ትኩረት ያደረገና ‹‹ ነጻነት ለፍትሃዊ ምርጫ›› በሚል ፕሮግራም በተከታታይ የሚካሄደውን ህዝባዊ ሠላማዊ ትግል የመጀመሪያውን ዙር የአንድ ወር እንቅስቃሴ መርሀ-ግብር ከባለቤቱ ዘንድ ማድረስ ነው፡፡ 

በዚህ መግለጫ በአገራችን ነባራዊና ተጨባጭ ኢኮኖሚያዊ፣ፖለቲካዊና ማኅበራዊ እውነታዎች ዝርዝር ውስጥ ለመግባት አይሞከርም ፣ በየቤታችን የዕለት ተዕለት ኑሮ የሚታየውን ፣በአራቱም የአገሪቷ አቅጣጫዎች በህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ሥቃይና የሰላምና ፀጥታ ፣የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት… ላይ የደረሰውንና የፈጠረውን ሥጋት ማንሳት ‹‹ ቀባሪን የማርዳት›› ሙከራ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ትኩረታችን በምርጫና በመጪው ምርጫ 2007 ላይ ይሆናል፡፡

ሁላችንም እንደምናውቀው በመጪው ግንቦት ወር አምስተኛው አገራዊና ክልላዊ ምርጫ ይካሄዳል ተብሎ ስለሚጠበቅ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ያዘጋጀውን የጊዜ ሰሌዳ እንደተለመደው ለማወያየት በሚል ለማሳወቅ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ስብሰባ መጥራቱ ይታወሳል፡፡ ከዚህ ስብሰባ አስቀድሞ የዚህ ትብብር አባላትን ጨምሮ አስራ ሁለት ፓርቲዎች ለቦርዱ ጥቅምት 5 ቀን 2005 

‹‹ 1ኛ/ ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ዛሬ ያቀረብናቸው ጥያቄዎቻችን እንዲመለሱ፤

2ኛ/ ገዢውን ፓርቲና አጋሮቹን ጨምሮ ሁሉም ህጋዊ ፓርቲዎች በጋራ ተገናኝተው በምርጫና የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ ላይ የሚወያዩበት የጋራ መድረክ እንዲዘጋጅ ›› 

የሚሉ የጋራ ጥያቄዎችን በማቅረብ ‹‹የእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ማለት ለሠላማዊ የሥልጣን ሽግግር / የነጻ፣ ፍትሃዊና ተኣማኒና አሳታፊ የምርጫ ውድድር ሥርዓት/ ሠላማዊ ትግል/ ዕድል ከመስጠትና የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ከማረጋገጥ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው፡፡ ማለትም በሌሎች አምባገነን መንግስታትና ሥርዓቶች በጦር መሣሪያ ኃይልና በደህንነት አቅም በመመካት በሥልጣን ላይ ለመቆየት ያሳዩትን እምቢተኝነትና ማንአለብኝነት ተከትሎ የተከሰቱ ህዝባዊ እምቢተኝነትና በውጤታቸውም የተከተሉ ቀውሶችን በጋራ በመከላከል ከአሸናፊ/ተሸናፊ ጠቅላይ የፖለቲካ ሥልጣን አስተሳሰብ በመውጣት ለዲሞክርሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረት የመጣልና ለዘላቂ ሠላምና ልማት ዋስትና መስጠት ማለት ነው፡፡ በዚህ ማንም ተጎጂ አይሆንም፡፡›› ብለን ሌላው አማራጭ ደግሞ ‹‹በተቃራኒው እነዚህ ጥያቄዎች ባልተመለሱበት የሚደረግ የምርጫ ተሳትፎ ለኢህገመንግስታዊነትና ኢዲሞክራሲያዊነት ዕውቅና በመስጠት አገሪቷንና ህዝብን ወደባሰ አዘቅት መወርወር በመሆኑ በታሪክና ትውልድ ፊት የሚያስጠይቅ ይሆናል፤በዚህ ማንም ተጠቃሚ አይሆንም፣ በዚህ መተባበርም ከተጠያቂነት አያተርፍም፡፡›› ብለን የእኛ ምርጫ የመጀመሪያው በመሆኑ ቦርዱ ‹‹ ከምርጫ የጊዜ ሰሌዳ በፊት ባለበት አገራዊና ህዝባዊ ኃላፊነት መሠረት ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጠውና ተገቢ ምላሽ በመስጠት ሚዛናዊነቱን. ከወገንተኝነት የጸዳ፣ በምርጫ ህጉ በተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት መሰረት የሚሰራ መሆኑን እንዲያረጋግጥ በድጋሚ አበክረን እንጠይቃለን፡፡›› በማለት አሳውቀናል፡፡ 

ከዚህ በተጨማሪም በስብሰባው ወቅት ( እዚህ ላይ ይህ ዓይነቱ ስብሰባ በ2005 አዳማ ላይ ስለምርጫ 2005 የጊዜ ሰሌዳ ፓርቲዎች በአንድ ላይ ተሰብስበን 33ቱ ‹‹ከጊዜ ሠሌዳው በፊት የፖለቲካ ምህዳሩ ይስተካከል›› የሚል ፔቲሽን ከተፈራረሙ በኋላ ባለው ጊዜ ቦርዱ ፓርቲዎችን በሦስት ቦታ በመከፋፈል እንጂ በአንድ ላይ የማይጠራ መሆኑን ያጤኑኣል) በሦስቱም የስብሰባ ቦታዎች የተገኙ ከኢህአዴግና አጋሮቹ እንዲሁም የኢህአዴግ ቀለብ የሚሰፈርላቸው የ‹‹ስለት›› ልጅ የሆኑ ለአጃቢነት የታጩ ፓርቲዎች በቀር ሁሉም የተቃውሞ ጎራ ፓርቲዎች በተመሳሳይና ተደጋጋፊ መንገድ ከላይ የቀረቡትን ጥያቄዎች የሚያጠናክሩ ተጨባጭ ማሳያዎችን በማቅረብ፣በማብራራትና የጥያቄዎቹን ምክንያታዊነትና ባልተመለሱበት ሊፈጠር የሚችለውን ችግር ለቦርዱ በዝርዝር አስረድተዋል፡፡ ቦርዱም እነዚህን ጥያቄዎች በዝርዝር እየመዘገበ መሆኑን በኦዲዮ ቪዥዋል መሳሪያዎችም እየተቀረጹ መሆናቸውን በመግለጽ ለቦርዱ ስብሰባ ቀርበው መልስ እንደሚሰጣቸውና መፍትሄ እንደሚበጅላቸው፣ይህንንም ተገናኝተን እንደምንነጋገር ቃል ገብቶ ስብሰባዎቹ ተጠናቀው ነበር፡፡ 

በተገባው ቃል መሰረት የሚሰጠውን መልስና የሚበጀውን መፍትሄ በመጠባበቅ ላይ እያለን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አመራሮች በጥያቄኣችን ላይ ያነሳነውን ለገዢው ፓርቲ ያላቸውን ‹‹ ወገናዊነትና የጉዳይ ፈጻሚነት ሚና›› ፍንትው አድርጎ በሚያሳይ መልኩ የጊዜ ሰሌዳውን ማጽደቅ ብቻ ሣይሆን በምርጫ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ የተመሰረቱትን ጥያቄዎቻችንን የቢሮ ጥያቄዎችና አስተዳደራዊ ጉዳዮች በማስመሰል አሳንሶ በማቅረብ ፕሮፖጋንዳ በመስራት በለመደው መንገድ ለመቀጠል መወሰኑን አውጀዋል፡፡ በዚህም ሳያበቃ በትብብር በጋራ ለመስራት በምናደርገው ግንኙነትና በተፈራረምነው ስምምነት መሰረት በቀጣይ ለምንቀሳቀሰውም ቦርዱ በህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር (ከዚህ በፊት ተመሳሳይ መግለጫ ይሰጡ የነበሩት የኢህአዴግ አባልና የደብረ ብርሃን ከተማ ዕጩ የምርጫ ተወዳዳሪ የነበሩ መሆኑን እያስታወስን) በኩል ‹‹ በዚህ ትብብር አማካይነት ነገ ወደ ሥራ ሲገቡ ችግር ቢያጋጥማቸው ቦርዱ ሊቆምላቸው የሚችልበት የሥራ አግባብ የለም ››፣ በዚህም ተጠያቂ ‹‹ እንደግለሰብም ሆነ እንደፓርቲ ራሳቸው ነው የሚሆኑት›› የሚፈጠረው ችግርም ‹‹ከህግ ማክበር ጋር ›› የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል በመግለጽ (ሪፖርተር ጥቅምት 29 ቀን 2007) ለማን መሆኑን ባናውቅም (ለኢህአዴግ ይህን መምከር ስድብ ይሆናልና) በማስፈራሪያ መልዕክት የታጀበ የወንጀል ክስ ኃሳብና ጥሪ አስተላልፏል፡፡ 

ከላይ የገለጽናቸው ሁሉ በጋራ ትግላችን ላይ ለማሳረፍ የተፈለገውን የፖለቲካ ጫናና አንድምታውን የመረመረው የትብብሩ አስተባባሪ ኮሚቴ ‹‹ ጽድቁ ቀርቶ በወጉ በኮነነኝ ›› እንዲሉ በህገ መንግስቱና በምርጫ አዋጁ የተቀመጠው መብታችን መጣስ/መጨፍለቅ፣ ቦርዱም ሆነ በሥሩ ያሉት መዋቅሮች ነጻና ገለልተኛ ያለመሆን፣ የምርጫ ሜዳው (የተፎካካሪ ፓርቲዎች በእኩል በህዝብ ውስጥ የመንቀሳቀስ መብት፣የአማራጭ ኃሳብ ማራመጃ ሚዲያ ፣ የመራጩ ህዝብ ዲሞክራሲዊ መብትና ሳይሸማቀቅ በነጻ የመምረጥ መብት፣ የምርጫ አስተዳደሩ፣…) በሚመለከት ለምናቀርባቸው ጥያቄዎች መልስ የማይሰጥ፣ቦርድ በህግ ‹‹ጥፋት›› ለሆነ ድርጊት ከለላ ሊሰጠን እና መከታ ሊሆነን መከጀሉ (መቼ፣ለማን፣እንዴት፣ተደርጎ እንደነበር በጥያቄ ታልፎ) ምጸት መሆኑን ተረድቷል፡፡ የቦርዱም አካሄድ ከተለመደውና በድህረ ምርጫ 2002 ግምገማ ከደረስነው ድምዳሜ ‹‹የፖለቲካ ምህዳሩ ጠቧል›› ከሚለው አልፎ ‹‹ ተዘግቷል›› ወደሚል ድምዳሜ የሚያሸጋግር ሆኖ መገኘቱን በተጨባጭ አረጋግጠናል፡፡ ዛሬ ላይ የእምነት ነጻነት ጠያቂዎች፣ጋዜጠኞች፣ጦማሪያን፣የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና አባላት፣ አልፎም ከገዢው ፓርቲ የተለየ ኃሳብ ያላቸው ዜጎች በአፋኝ ህጎች በፈጠራ ወንጀል ተከሰው የት እንደሚገኙ ከእኛ አልፎ የዓለም ህዝብ ያውቀዋል፤ አንድም በወህኒ ያሊያም በስደት፡፡

ስለዚህ ነጻነት በሌለበት ፍትሃዊ ምርጫ የማይታሰብ በመሆኑ የተዘጋውን በር ለማስከፈት ትግሉን የ ‹‹ ነጻነት ለፍትሃዊ ምርጫ›› በሚል የፕሮግራም መርህ ለመግፋት ወስኖ የመጀመሪያውን ዙር እንቅስቃሴ በአዲስ አበባ ከተማ ለማድረግ የአንድ ወር ዕቅድ አዘጋጅቶኣል፡፡ በዕቅድ ዝግጅቱ የፕሮግራሙ የአፈጻጸም ስልት ፣የጊዜ ሰሌዳ፣ የቦታ ሽፋን፣የፋይናንስ ምንጭ፣ ዓላማዎች፣ትኩረት የሚደረግባቸው ጉዳዮችና መንግስታዊና የህዝብ ክፍሎች፣ዋና ዋና ተግባራት ፣በተጨማሪም በታሳቢነት በአፈጻጸም ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮች/ደንቃራዎችና ሥጋቶች እንዲሁም ለፕሮግራሙን ስኬት አጋዢ ሁኔታዎች እንዲካተቱ ተደርጓል፡፡ 

በዚህ መሠረት ይህ ዙር የሚያተኩርባቸው ዋና ዋና ተግባራትም--
1. በየቤተ እምነቱ ጸሎት ፕሮግራም እንዲደረግ ጥሪ ማድረግና አባላት እንደየእምነታቸው ተሳትፎ ማድረግ፤
2. በምርጫ ዙሪያ የፓናል ውይይቶችን ማድረግ፤
3. የአደባባይ ህዝባዊ ስብሰባዎችን ማድረግ፤
4. ለመንግሥታዊ ተቋማት ደብዳቤ ማስገባት፤
5. የተቃውሞ ድምጽ ማሰማት፤
6. የህዝብ ተሳትፎ ማበረታታትና ድጋፍ ማሰባሰብ፤ ናቸው፡፡

እዚህ ላይ ሊታወቅ የሚገባው አቢይ ጉዳይ ይህን ዕቅድ ስናዘጋጅ ነጻነታችንና መብታችን ከገዢው ፓርቲ ለምነን የምናገኘው ሣይሆን በእያንዳንዳችን እጅ ውስጥ መሆኑንና በማመን እኛ የዕቅዱ አስተባባሪዎች እንጂ የጉዳዩ ዋነኛ ባለቤት፣ የዕቅዱ ፈጻሚና ዋና ተዋናይ እያንዳንዱ/ዷ ኢትዮጵያዊ/ት ዜጋ ነው/ናት በሚል ሙሉ እምነት ላይ ቆመን መሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ ለዚህ ዕቅድ ተፈጻሚነት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ/ት በጋራ/በትብብር ከጀመርነው ሠላማዊ ትግል ጎን በመቆም ነጻነት በሌለበት ፍትሃዊ ምርጫ አይኖርምና በምርጫ ሥም ሠላማዊ የነጻነት ትግሉን ማዘናጋት ያብቃ// ማለትና ለዕቅዱ ተፈጻሚነት የነቃ ተሳትፎ ማድረግ ራስን ከባርነት ነጻ የማውጣት፣አገርን ከጥፋት የመታደግ የዜግነት ግዴታ መሆኑ ግልጽ እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡ 

በመጨረሻም ከላይ በገለጽናቸው ተጨባጭ ሁኔታዎች ውስጥ የሚደረግ ምርጫ ገዢው ፓርቲ በጉዳይ ፈጻሚው የምርጫ ቦርድ በኩል በተለመደው መንገድ በምርጫ ሥም ለመሥራት የተያያዘውን ቧልት ራቁቱን በማስቀረት ለ ነጻ፣ፍትሃዊ፣ ተኣማኒና አሳታፊ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ የምርጫ ሜዳውን እንዲያስተካክል በሠላማዊ ትግል አዎንታዊ ተጽዕኖ ለማሳረፍ በእኛ በኩል አስፈላጊውን መስዋዕትነት ሁሉ ለመክፈልና እስከ መጨረሻው በጽናት ለመቆም የተዘጋጀን መሆኑን እያረጋገጥን ፡-

1ኛ/ የችግሩ ገፈት ቀማሽና የጉዳዩ ቀዳሚና ዋነኛ ባለቤት የሆናችሁ በአገር ቤት ያላችሁ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ አገራችን ከገባችበት ፈተና ህዝባችን ከሚደርስበት ሥቃይ ለማውጣት የራሳችን የዜግነት ክብር ባለቤት ለመሆን ያለን ምርጫ በጽናትና ቆራጥነት የተባበረና የተቀናጀ ሠላማዊ ትግል ስለሆነ ለዚህ ፕሮግራም ስኬት ሁለንተናዊ የፋይናንስ ፣የማቴሪያል፣የጊዜና ጉልበት፣ የዕውቀትና ሙያ፣ የትግል አስተዋጽኦ (በማድረግ የዜግነት ግዴታችሁን እንድትወጡ) እንድታደርጉና እንቅስቃሴኣችንን በመከታተል የአመራርና አፈጻጸም እገዛችሁ እንዳይለየን ፤

2ኛ/ ከአገዛዝ ሥርዓቶች ጋር የተያያዙ የተለያዩ ችግሮችና ፈተናዎች ለስደት የተዳረጋችሁ፣በውጪ ለመኖር የተገደዳችሁ ባላችሁበት ሆናችሁ የአገራችሁ ጉዳይ እንቅልፍ የሚነሳችሁ ኢትዮጵያዊ የዲያስፖራ አባላት በሙሉ ከላይ የእናንተ ተሳትፎ ከትብብርና ድጋፍ ያለፈ አገራዊ ኃላፊነት የመወጣት ነውና በአገር ቤት ላሉት ካቀረብነው በተጨማሪ ድምጹ ለታፈነውና የሰቆቃ ህይወት ለሚገፋው ወገናችሁ ድምጽ ሆናችሁ የዲፕሎማሲውን ትግል በኃላፊነት ስሜት እንድታከናውኑ፤

3ኛ/በትብብሩ ያልታቀፋችሁ በተለይም በሂደቱ ከጅምሩ እስከ መጨረሻው ተሳትፋችሁ በተለያየ ምክንያት የስምምነቱን ሰነድ ያልፈረማችሁም ሆነ የአገርና ህዝብን ጉዳይ ከፓርቲ ጥቅምና ዓላማ በላይ ስለሆነ በጋራ ለመሥራት ዝግጅቱና ቁርጠኝነቱ ያላችሁ ሌሎች ሠላማዊ የተቃውሞ ፖለቲካ ፓርቲዎች ከጋራ ትግሉ እንድትቀላቀሉ እና/ወይም የፕሮግራሙ አካል እንድትሆኑ፤

4ኛ/ የዓለም አቀፉና የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት መንግስታት ተለዋዋጭና ኃላፊ፣ ህዝብ ግን ቋሚ ነውና በግንኙነታችሁ የህዝብ ለህዝብ ዘላቂ ጥቅምንና ታሪካዊና ፖለቲካ አንድምታን ከግምት እንድታስገቡ፤ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡ 

በተቀናጀ የጋራ አመራር የተባበረ ህዝባዊ ሠላማዊ ትግል በእኩልነት ላይ የተመሠረተች ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እንገነባለን// 

ጥቅምት 25/2007፣ አዲስ አበባ

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen