Netsanet: ይድነቃቸው ከበደ የመከላከያ ምስክሮቹን ዛሬ አስደመጠ ( በፍቃዱ ዘ ሀይሉ)

Donnerstag, 15. Juni 2017

ይድነቃቸው ከበደ የመከላከያ ምስክሮቹን ዛሬ አስደመጠ ( በፍቃዱ ዘ ሀይሉ)

ይድነቃቸው ከበደ የመከላከያ ምስክሮቹን ዛሬ አስደመጠ

(ፍርድ ቤቱ "ጥፋተኛ" ሆኖ ካገኘው "በቀላል እስራት፣ ወይም በመቀጮ፣ ወይም ወንጀሉ ከባድ በሆነ ጊዜ ከሦስት ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት ይቀጣል")

ነሐሴ 28/2008 በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የደረሰውን ቃጠሎ ተከትሎ እስረኞች ወደ ዝዋይ እና ሸዋሮቢት መዘዋወራቸው ተጠቅሶ ጳጉሜ 3/2008 ቀን እስረኞቹ ያሉበትን አድራሻ እንደሚያሳውቁ ከማረሚያ ቤት አስተዳደር ተገልፆ ነበር።


በተጠቀሰው ዕለትም [ጳጉሜ 3/2008] የሚፈልጋቸውን እስረኞችን (ማለትም የሰማያዊ ፓርቲ አባላት የሆኑ እስረኞች የተዘዋወሩበትን) አድራሻ ለማወቅ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የሔደው የሰማያዊ ፓርቲ አባሉ ይድነቃቸው ከበደ፣ ሲመለስ ሲቪል በለበሱ ግለሰቦች ተይዞ መታሰሩ ይታወሳል። ለአንድ ሳምንት በእስር ቆይቶ በ5,000 ሺ ብር ዋስ ከእስር ከወጣ በኋላ በ14/3/20009 የወንጀለኛ ሕግ አንቀፅ 486(ሀ)ን በመተላለፍ፤ «ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት አካባቢ የሕግ ታራሚዎች ቤተሰቦችን "መንግሥት ታራሚዎችን አቃጥሎ ለምን ዝም ብላችሁ ታያላችሁ፣ አትጮሁም ወይ፣ አታለቅሱም ወይ አሁን እኛም መታገል አለብን" በማለት የሐሰት ወሬዎች በማውራት፣ ሕዝብን በመቀስቀስ እና ማነሳሳት ወንጀል» በመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አቃቂ ቃሊቲ ምድብ 1ኛ ወንጀል ችሎት ክስ ቀርቦበታል።

በመሐሉ፣ የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ከታወጀ በኋላ በድጋሚ ታስሮ አዋሽ ሰባት የፌዴራል ፖሊስ ካምፕ "የተሐድሶ ሥልጠና" ወስዶ በታኅሣሥ ወር ከተፈታ በኋላ የቀጠለው ይህ ክሱ፣ ግንቦት 14/2009 ቀን በተሰሙት ሁለት የአቃቤ ሕግ ምስክሮች ተፈፀመ የተባለውን ድርጊት በተመለከተ ተመሳሳይ ያልሆነ (እርስ በርሱ የሚጋጭ) ምስክርነት የሰጡ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ ግን ከክሱ ነፃ ለመውጣት ራሱን መከላከል እንዳለበት ብይን ሰጥቷል።

ዛሬ በነበረው ቀጠሮ ይድነቃቸው ከበደ መከላከያ ምስክሮቹን እና የምስክርነት ቃሉን አሰምቷል። ማረሚያ ቤቱ ባቀረበው ጥሪ መሠረት ወደቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የሔደው የሚፈልገውን እስረኛ አድራሻ ለማወቅ እንደነበረ እና ማረሚያ ቤት ደርሶ እስረኛው የት እንዳለ ካወቀ በኋላ በመመለስ ላይ እያለ በሲቪል ፖሊሶች ተይዞ እንደታሰረ የምስክርነት ቃሉን በሚሰጥበት ጊዜ አስረድቷል።

አንደኛው ምስክር የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ የሽዋስ አሰፋ፣ ከይድነቃቸው ቀደም ብለው ማረሚያ ቤት እንደደረሱ፣  የሚፈልጉትን እስረኛና የተዛወረበትን አድራሻ ለመስማት ተቀምጠው እያሉ ይድነቃቸው ከሌላ ከማያቁት ሰው ጋር እንደመጣ፣ ይድነቃቸው የሚፈልገው እስረኛ አድራሻ ከእርሳቸው ቀድሞ በማወቁ ተሰናብቷቸው እንደሄደ እና በወቅቱ ምንም የተከሰተ ረብሻ እና ሁከት እንዳልነበረ መስክረዋል።

ሁለተኛ ምስክር የሆነው ሀይለመለኮት አሰፋ፣ ከይድነቃቸው ጋር አብሮ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ሔዶ ይድነቃቸው የሚፈልገው እስረኛ የት እንዳለ ካወቀ በኋላ ወደየቤታቸው በመመለስ ላይ እንዳሉ ሲቪል የለበሱ ሰዎች ጠርተውት ትንሽ አናግረውት፣ በፒክአፕ መኪና ይዘውት እንደሄዱ፣ በወቅቱ ፖሊሶች እና ወታደሮች በአካባቢው በርከት ብለው እንደነበረ እና ሁኔታው ሁሉ ሠላም እንደነበረ ተናግሯል።

ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃዎችን ከይድነቃቸው መከላከያ ምስክሮች ጋር አመሳክሮ የጥፋተኝነት ፍርድ ለመስጠት ("ጥፋተኛ" ወይም "ነፃ" ለማለት)  ለሐምሌ 3/20093 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen