Netsanet: ችኩል ቀንድ ይነክሳል! (መስቀሉ አየለ)

Donnerstag, 15. Juni 2017

ችኩል ቀንድ ይነክሳል! (መስቀሉ አየለ)

ችኩል ቀንድ ይነክሳል!
መስቀሉ አየለ

በጉራጌ ዞን የዐማሮች ንብረት ወደመ፤ በሕግ ጥበቃ ስር ያለ ዐማራ በአሰቃቂ ሁኔታ ተጨፍጭፎ ተገድሏል
በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ ግምቱ ከአምስት ሚሊዮን ብር የሆነ የዐማራ ተወላጆች ንብረት ከሰኔ 4 እስከ ሰኔ 6 ቀን 2009 ዓ።ም በቀቤና ብሔረሰብ አባላት መውደሙን ከቦታው ዛሬ ያገኘነው መረጃ አመልክቷል፡፡ የሚል ዜና እራሳቸውን የ አማራ አክቲቪስት ነን በሚሉ ሰውች ተለቆ በመራገብ ላይ ነው። እንደ ዜናው አገላለጥ ሰውየው ይህ ሁሉ የደርስበት አማራ ስለሆነ ብቻ ነው የሚል ሲሆን አቀራረቡም የአማራዎችን ትኩረት በመሳብ ወደ ሌላ ዙር አቅጣጫ የመሳብ ሂደት ነው። እውነቱ ግን ይኽ አይደለም።

እሁድ እለት ሁለት ጎረቤታሞች ይጣላሉ። አንዱ ቀቤና ሲሆን ሌላው አማራ ነው። የጠቡ መነሻ በአንደኛው ግቢ ውስጥ የነበረ የሸንኮራ አገዳ ወሰድክብኝ የሚል ነው። ተሰዳደቡ፤ ተዛዛቱ።  ምሽት ላይ የ8 ወ እርጉዝ የቀቤና ሴት ተመታች፤ ሴትየዋ  ያረገዘችው መንታ ህፃናትን ነበር። ሆስፕታል ተወሰደች፤ እናትና አንዱ ህፃን ሞቱ። አንደኛው ህፃን በህይወት ተወለደ። ዜናው ሰፈሩን ረበሸ። አማራው በጥርጣሬ ታሰረ። የሰፈሩ ሰው እሱ ነው የመታት የሚል እምነት አለው። የተወሰኑ የቀቤና  ወጣቶች ወደ እስር ቤት ሄደው ፓሊሶቹን ደብድበው ሰውየውን ገደሉት፤ ቤቱንም በእሳት አቃጠሉት። አሁን በጉዳዩ የአገር ሽማግሌዎች ገብተውበት በርዷል።

ይህን መረጃ የሰጠ ሰው በሴትየዋና ህፃኑ በቀብር ላይ የተገኘ ሲሆን በተፈጠረው ነገር  ሰውን ሁሉ ያሣዘነ ፤ አማራ ቀቤና ጉራጌ ሳይባል ሰብዓዊነት ያለው ሁሉ በተገኘበት የቀብር ስነ ስርዓቱ ተፈጽሟል።

ለማስታወስ ያህል ቀቤና ጉራጌ ዞን ውስጥ ወልቂጤ ከተማ አካባቢ የሚገኝ እራሱን የቻለ ብሄረሰብ ቢሆንም ከመካከላቸው በጉራጌ ዞን ውስጥ መካለላቸውን የማይወዱ አሉ። በ 1993/94 አካባቢ በወያኔ በተቀነባበረ አሻጥር ቀቤኖች ወልቂጤ የእኛ ስለሆነ ጉራጌ ለቆ ይውጣልን ብለው ከፍተኛ የሆነ ደም መፋሰስ ከመድረሱ በፊት በብልህ ሰዎች ጥረት ነገሩ ተረጋጋ። ወልቂጤ ውስጥ ችግር አለ ከተባለ እንኩዋን ችግሩ ያለው በቀቤና በጉራጌ እንጂ በቀቤና በአማራ ወይም በጉራጌና በአማራ መካከል አይደለም። ቀቤናዎች ወልቂጤ የኛ ነን ይላሉ፤  ወልቂጤ ደግሞ በቀቤና መን ደሮች የተከበበች ከተማ ናት።

ከዚህ ውጭ የተቃጠለ ተጨማሪ የወደመ ንብረት በሌለበት ሁናቴ ነገሩን ጎሳዊ ቅርጽ መስጠቱ ሃላፊነት የጎደለው አካሄድ ነው። ትርፍና ኪሳራውን አስልቶ የማይራመድ፤ ለግላዊ ፍላጎት ሲባል ብቻ በአገር ላይ ቁማር መጫወት አክቲቪስትነት አይደለም። ይልቁንም በጸረ ወያኔ ትግሉ ላይ ወሃ በመቸለስ እንቅፋት መሆን እንጅ።

የወያኔ ማኔፌስቶ ጠላቴ አማራ የሚል ነው። አራት ነጥብ። ይኽ ነገር ወያኔ ገሃነም እስኪገባ ከሰማይ በታች ባለ ትንትኔ አይቀየርም። ለዚህ ተፈጻሚነት ደግሞ ይኽን ህዝብ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ብሄረሰቦች አልፎ ከሱዳን እስከ ሱማሌ ያልገዛለት ጠላት የለም። አላማውም ግልጽ ነው፤ የቁርጡ ቀን ሲመጣ እንደ ገና ዳቦ በሁሉም ማእዘን እሳት አንድዶበት ለመሄድ ነው። የእድሜ ልክ የቤት ስራ ሊሰጠው ነው። ዛሬ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በአማራነታቸው ተቆርቁረው የተነሱ አክቲዚስቶችለዚህ አይነቱ የወያኔ ሴራ ግብአት ላለመሆናቸው ምንም አይነት ማረጋገጫ ሊያመጡ አይችሉም። እነሱም ባቅማቸው ለአማራ ያልገዙለት ጠላት የለምና። ዛሬም የሚራገበው የወልቂጤ ዜና ሌላ ትርጉም የለውም።  ወያኔ እርስበርሳችን ሊያጣልን እሳት ሲጭር ቤንዚን እያርከፈከፍን ባናግዘው ጥሩ ነው።

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen