Netsanet: ጊዜው የሕዝባዊ አሻጥር ነው !!!by (patriotic ginbot 7: dept of civic disobedience)

Montag, 12. Juni 2017

ጊዜው የሕዝባዊ አሻጥር ነው !!!by (patriotic ginbot 7: dept of civic disobedience)

​ጊዜው የሕዝባዊ አሻጥር ነው !!!by (patriotic ginbot 7: dept of civic disobedience)
ጊዜው የሕዝባዊ አሻጥር ነው !!!
አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ “ሴፍ ሀውስ” እያሉ የሚያቆላምጧቸው ከ50 በላይ ድብቅ የማሰቃያ ቦታዎች አሉ። ከፊሎቹ የምድር ውስጥ ዋሻዎች አሏቸው። ብዙዎቹ መሀል ከተማ ውስጥ ሲገኙ ጥቂቶቹ በከተማው ዳርቻዎች ይገኛሉ።  በማዕከላዊና በሌሎች እስር ቤቶች ውስጥም የማሰቃያ ቦታዎች ያሉ ቢሆንም ወገኖቻችን ከፍተኛ ፍዳ እንዲደርስባቸው የሚደረገው በእነዚህ ከእይታ በተሰወሩ የማሰቃያ ቦታዎች ነው።  በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ዋዜማ በናዚ ፋሽስቶች ይፈፀሙ ከነበሩ ሰቆቃዎችን የባሱ አስነዋሪና ኢሰብዓዊ ግፎች በእነዚህ የማሰቃያ ቦታዎች ውስጥ ይፈፀማሉ።  

ልብስን አስወልቆ ራቁት መግረፍ፤ እግርን አስሮ መዘቅዘቅ፤ በተገመደ የፕላስቲክ ቀበቶና የኤሌክትሪክ ገመድ መግረፍ፤ ጭንቅላትን በቀዘቀዘ ውሃ ውስጥ መንከር፤ በተራቆተ ገላ ላይ የተለኮሰ ሲጋራ መተርኮስ፤ በፊት ላይ መትፋት፤ በኤሌክትሪክ ንዝረት መጥበስ፤ በቆሻሻ ማጠራቀሚያ ገንዳ ውስጥ መክተት፤ ጥፍርና ፀጉርን መንቀል፤ በሽንት ቤት ዝቃጭና ውሃ በተሞላ ክፍል ውስጥ ማስገባት፤ እንቅልፍ መከልከል፤ ምግብ፣ መጠጥና ህክምና መከልከል፤  የወንዶች ሽንት መሽኚያ አካልን በሲባጎ አጥብቆ በማሰር ማሰቃየት፤ በወንድ ተመርማሪዎችን የዘር ፍሬዎችን በፒንሳ መጨፍለቅ፤  በወንድ ተመርማሪዎች የዘር ፍሬ ላይ ባዕድ እቃዎችን ማንጠልጠል፤ በሴት ተመርማሪዎች ማህፀን ዉስጥ ባዕድ ነገር ከቶ ማሰቃየት፤ የሴት ተመርማሪዎችን ጡትን በብረት መምታት፤ ሴት ተመርማሪዎችን በቡድን አስገድዶ መድፈር እና ከእነዚህ የባሱ ክፋቶች በእነዚህ የማሰቃያ ቦታዎች በወገኖቻችን ላይ ይደርሳል።
የህወሓት ፋሽስቶች የማሰቃያ ቦታዎቻቸው ከሕዝብ ዓይንና ጆሮ የተሰወሩ ይመስላቸዋል። እነሱ “ሴፍ ሀውስ” ብለው ስለጠሯቸው በእርግጥ “ሴፍ” የሆኑላቸው ይመስላቸዋል። ይህ እውነት አለመሆኑ ግን በተጨባጭ እንዲያዩ ተደርጓል።
እጅግ የመረረ ሰቆቃ ከሚፈፀምባቸው ቦታዎች አንዱ በመሀል ከተማ የቀድሞ ናዝሬት አውቶቡስ ተራ አጠገብ የሚገኘው የፌደራል ፓሊስ ካምፕና የመሣሪያ ግምጃ  ቤት ነው። የብዙ ምርጥ ወገኖቻችን እምባና ደም እዚህ ግቢ ውስጥ በግፍ ፈሷል። በርካታ ወገኖቻችን እዚህ ግቢ ውስጥ በተደረባቸው ሰቆቃ ሳቢያ ለዘላቂ የአካልና የስነልቦና ጉዳት ተዳርገዋል። ዓይኖቻቸው ታስረው ስለሚወሰዱ አብዛኛዎቹ ተጎጂዎች ቦታውን ለይተው አያውቁም። ይህ ማለት ግን ከሕዝብ ዓይና ጆሮ ተሰውሯል ማለት አይደለም። ከሕዝብ ዓይና ጆሮ ያልተሰወረ ነገር ደግሞ ከአርበኞች ግንቦት 7 የተሰወረ አይደለም።  ስለሆነም ቅዳሜ ሰኔ 3 ቀን 2009 ዓ.ም በዚህ ተቋም ላይ የተጠና እርምጃ ተወሰደ፤ በውጤቱም የማሰቃያ ቦታው ብቻ ሳይሆን የፈደራል ፓሊስ የመሣሪያ ማከማቻ መጋዘኖችም በእሳት ጋይተዋል። መላው የአዲስ አበባ ሕዝብ ለሰዓታት የቆየውን ቆጠሎ በዓይኖቹ ተመልክቷል።
የሰኔ 3ቱ እርምጃ ከዚህ በፊት ስለሕዝባዊ አሻጥር የተሰጡ ገለፃዎችን የሚያጠናክር ነው። በመሠረቱ አሻጥር” ማለት ተንኮል፣ ሸር፣ ደባ ማለት ነው፤ አንድን ነገር በስውር ማፍረስ ማለት ነው። ይሁን እንጂ አሻጥር ሁሉ መጥፎ ነገር አይደለም። አንድን አሻጥር “ጥሩ” ወይም “መጥፎ” መሆኑ የሚወሰነው “በማን ላይ ወይም በምን ዓይነት ሰው፣ ድርጅት ወይም አገዛዝ ላይ ነው አሻጥሩ የተፈፀመው?”  እና “ምን ለማግኘት ነው አሻጭሩ የተፈፀመው?” የሚሉት ጥያቄዎች ሲመለሱ ነው።  ተበዳይ በበዳይ ላይ፤ ተጨቋኝ በጨቋኝ ላይ፤ የተገረፈው በገራፊው ላይ የሚያደርጋቸው የአሻጥር ሥራዎች ከሥነምግባር አንፃር ተቀባይነት ያላቸው ተግባራት ናቸው።
ሕዝባዊ አሻጥር፤  ገራፊና ዘራፊ የሆነ አምባገነን አገዛዝን ለማዳከም የሚደረግ፤ ከሥነ ምግባር አንፃር ከፍተኛ ተቀባይነት ያለው፤ ጠላትን በስውር የማዳከሚያ ዘዴ ነው። ሰኔ 3 ቀን 2009 ዓም በአዲስ አበባ ከተማ የተፈፀመው ይህ ነው። እዚያ ግቢ ውስጥ ይደረግ ስለነበረው ሰቆቃ መረጃ የሌላቸው ወገኖች እንኳን ሳይቀር የፌደራል ፓሊስ የመሣሪያ ግምጃ ቤት መቃጠል ለነዋሪው የፈጠረለት የደስታ ስሜት ቃላት ሊገልጹት ከሚችሉት በላይ ነው።
ከዚህ ተግባራዊ እምርጃ የምንቀስማቸው ትምህርቶች አሉ።  ይህ ክስተት ከፍተኛ ውጤት የሚያስገኙ የሕዝባዊ አሻጥር ተግባራት በጥቂት ሰዎች – በአንድ ሴል – ተግባራዊ ሊሆኑ እንደሚችሉ በተግባር የተረጋገጠበት ነው። ይህ ክስተት ከፍተኛ ውጤት የሚያስገኙ የሕዝባዊ አሻጥር ተግባራት በአነስተኛ ወጪ ተግባራዊ ሊደረጉ የሚችሉ መሆኑን የታየበት ነው።  በመጨረሻም ይህ ተግባራዊ እርምጃ የህቡዕ አደረጃጀት ጥንካሬና ውጤታማነት ያሳየ ነው።
© patriotic ginbot 7: dept of civic disobedience
https://netsanetlegna.wordpress.com/2017/06/12/%e2%80%8b%e1%8c%8a%e1%8b%9c%e1%8b%8d-%e1%8b%a8%e1%88%95%e1%8b%9d%e1%89%a3%e1%8b%8a-%e1%8a%a0%e1%88%bb%e1%8c%a5%e1%88%ad-%e1%8a%90%e1%8b%8d-%ef%bc%81%ef%bc%81%ef%bc%81by-patriotic-ginbot-7-dept-of-ci/

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen