በማንኛውም አገር ቢሆን ድምፅ የሌለው፤ ነጻ የሆነ የዜና አገልግሎት የማያገኝ፤ ተቆርቋሪ የፖለቲካ ወይንም የማህበረሰብ ወይንም የሲቪክ ድርጅት፤ ወይንም በነጻነት የሚንቀሳቀስ የመገናኛ ብዙሃን አገልግሎች የሌለው ሕዝብ መብት የለውም። መብቱ በመንግሥት የተከለከለ ግለሰብ ሆነ ቡድን፤ ማህበረሰብ ሆነ ሕብረተሰብ ዘላቂነትና ፍትሃዊነት ያለው እድገት አይጎናፀፍም። ህወሓት ለሃያ አራት ዓመታት በበላይነት ሲገዛት የቆየች ኢትዮጵያ ፍትህ፤ ነጻነት፤ ሰብአዊ መብት፤ በሕግ ፊት የሁሉም እትዮጱያዊያን እኩልነት የማይስተናገድባት፤ ፍፁም አምባገነናዊ ስርዓት የሰፈነባት ሃገር ሆናለች። የህወሓት መስራቾች ስሌት መስራቾቹ ለሃያ ዓምስት ዓመታት፤ እነሱ ተንከባክበውና አስለጥነው፤ ልክ በፋብሪካ እንደተመረቱ “እቃዎች” የእነሱን ርእዮት፤ የፖለቲካና የኢኮኖሚ የበላይነት መስመር የሚከተሉ ተተኪዎቻቸው ዛሬ ሰላማዊ ሕዝብ ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅደው መሰረት ሰላማዊ ሰልፍ ሲያደርግ በጅማል በዱላ እየደበደቡት ነው። ዲፕሎማቶችና ሌሎች ታዛቢዎች እያዩ፤ ባልቴት፤ ወጣት፤ ወንድ፤ ሴት፤ የክርስትና ወይንም የእስልምና ተከታይ፤ ኦሮሞ፤ ጉራጌ፤ አማራ፤ ትግሬ፤ ሳይለዩ እያሳደዱት፤ “እንደ እንሰሳ” በዱላ እየደበደቡት፤ እያፈኑትና እያሰሩት ነው። ድብደባውና ጭካኔው የአፍሪካ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ፤ ከቤተክርስቲያን ተሳልመው ሰልፉን የደገፉ የሰባ ዓመት እናት የሚደበድብ ፖሊስ አገልጋይነቱ ለሕዝብ ሳይሆን ለገዢው ፓርቲ የቆመ መሆኑ የአፍሪካን ብቻ ሳይሆን የዓለምን ሕዝብ ትዝብት ሸምቷል። ኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች መረገጫ መዲና መሆኗ ዙሮ ዙሮ ገዢውን ፓርቲ እንደሚያጋልጠው መገመት አያስቸግርም። በሰላም፤ ለሰላም፤ ለፍትህ፤ ለዲሞክራሲ የሚታገሉ የአንድነት፤ የሰማያዊና የመኢዓድ መሪዎችን፤ አባላትንና ደጋፊዎችን ሲደበደቡ ማየት “ወራሪ” እንጅ ለሃገርና ለሕዝብ የቆመ ገዢ ፓርቲ ነው ለማለት አይቻልም። ተከታታይ የሆነው ጭካኔ የሚያሳየው ህወሓት በራእዩና ፕሮግራሙ እንዳስቀመጠው ለሚቀጥሉት መቶ ዓመታት በኃይልና በጭካኔ ለመግዛት መወሰኑን ነው። ለዚህ የሚያዋጣው አገዛዙ ያስመረረው ምላተ ሕዝብ (አብዛኛው ማለት ነው)፤ ቆርጦና ደፍሮ አገር አቀፍ በሆነ ደረጃ መነሳት ይኖርበታል። በውጭና በውስጥ የሚገኘው ፍትህ ፈላጊ አብሮ ተባብሮ መስራት ግዴታው ሆኗል። ገዢው ፓርቲ የሚፈልገው በተናጥል የሚደረግ ትግልን ነው። ትግሉ የመኖር ያለመኖር፤ ማለትም የህልውና ስለሆነ አብሮ ተያይዞ መነሳት የውቅቱ መሪ ጥያቄ ነው።
የዚህ ጽሁፍ መሰረተ ሃሳብና ክርክር ሰብአዊ መብቶች ካልተከበሩ እንደልብ ለመንቀሳቀስ፤ አቤቱታ ለማቅረብ፤ የግል ድርጅት ለማቋቋም፤ ኑሮን ለማሻሻል የሚደረግ ጥረት ከምኞትና ከህልም አያልፍም የሚል ነው። ይኼን መብት ስኬታማ ለማድረግ የሚችለው ሕዝቡ ለራሱ ህይዎት መሻሻል፤ ወጣቱ ትውልድ ከስደት ይልቅ በሃገሬ ሰርቸ የመኖር መብቴን አስጠብቃለሁ ብሎ ሲነሳ ብቻ ነው። በተለይ በኑሮ ውድነት፤ ጥሮ ግሮ አዳሪና በድህነት የሚሰቃየው ክፍል እና ተምሮ ለስደት የተዳረገው ወጣቱ ትውልድ ለራሱ ሲል ደፍሮ መብቱን ማስከበር ግዴታ ይሆኗል። ማንም የውጭ መንግሥት ሊደርስለት አይችልም።
በቅርቡ በኢትዮጵያ ላለፍቱ ሃያ አራት ዓመታት በአንድ የአናሳ ጎሳ ቡድን ፓርቲ የበላይነት ሲገዛና ሲዳኝ በቆየው “እድገታዊ መንግሥት” ላይ በተለያዩ እውቅና ባላቸው የሰብአዊ መብቶች ተቆርቋሪና ለጋስ ተቋሞች የቀረቡ ዘገባዎች ትኩረት የሰጡት ለመብቶች መረገጥና መታፈን የኢትዮጵያ “ፈጣን” እድገት የጥቂቶች ጥቅም አገልጋይ መሆኑን፤ ዘላቂነትና ፍትሃዊነት ያለው የልማት መሰረት አለመመስረቱን ነው። ይኼን ተከታታይና እየባሰ የመጣ የመብቶች መረገጥና እድገት የጥቂቶች ሃብት መሰብሰቢያ የሆነ ክስተት አሳሳቢ ያደረጉት ሁለት አንኳር ጉዳዮች አሉ። አንዱ መጭው አጠቃላይ ምርጫና የፖለቲካው ምህዳር
(ምድር)ፍጹም በሆነ ደረጃ መዘጋቱ ሲሆን፤ ሁለተኛው ከብዙ ቢሊዮን ዶላር እርዳታ፤ የስደተኛው የገንዘብ ድጋፍ (ሬምታንስ የሚባለው)፤ የውጭ የካፒታል ፈሰስ፤ የመንግሥት ብድርና ብዙ ሚሊዮን ሄክታር ለም መሬትና ወንዝ ለውጭ አትራፊዎች መለገስ በኋላ ኢትዮጵያ አሁንም ድሃና ኋላ ቀር ከሆኑ አገርች መካከል አንዷ ሆና መገኘቷ ነው።
“እውነትና ጭስ መውጫ አያጣም” እንዲሉ፤ የእውነተኛ እድገት መለኪያው የአብዛኛው ሕዝብ ህይዎት መሻሻሉ፤ የአገር ሉአላዊነት መከበሩ፤ የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃብት ለኢትዮጵያዊያን አገልጋይ መሆኑ፤ የስራ እድል መፈጠሩ ወዘተ ናቸው። ህወሓት በቅርቡ አራት ብሄራዊ ፖሊሲዎች እንዳልተሳኩለት አምኗል።
አንድ፤ ህወሓት ፈቅዶና አመቻችቶ የኢትዮጵያን የባህር በር መዝጋቱ፤ ኤርትራን ከእናት አገር ማስገንጠሉ፤ በታሪኩ የተያያዘውን ሕዝብ መለያየቱ፤ ሁለት፤ የመንግስቱ ኃይለማሪያምና ከዚያ በፊት ተከታታይ መንግሥታት ለድርቅ፤ ለረሃብ፤ ለስደት፤ ለድህነት፤ ለሕዝብ መፍለስ ኃላፊዎች ናቸው ብሎ ካጥላላና ኢትዮጵያ ከርሃብ፤ ከምግብ እጥረት በአጭር ጊዜ ውስጥ “ነጻ” ትወጣለች ያለው ምኞች ስኬታማ አለመሆኑ፤ ዛሬ “ኢትዮጵያ በዓለም በተከታታይ የምግብ እርዳታ ጥገኛ ከሆኑ አገሮች የመጀመሪያውን ደረጃ ይዛ” መገኘቷ። ፍፁም ርሃብ (ፋሚን) አለ ተብሎ የማይነገረው ከውጭ በሚገኝ የምግብ እርዳታና መንግሥት በሚሸምተው ምግብ ድጎማ ነው።
ሶስት፤ “ልማታዊው መንግሥት” የኢትዮጵያን መሰረታዊ የኢኮኖሚ ችግሮች ለመወጣት አለመቻሉ፤ ዘላቂነትና ፍትሃዊነት ያለው የልማት መሰረት አለመጣሉ፤ የሃገሪቱ ዘመናዊ የኢንዱስትሪና የምርት ክፍሎች/ምሰሶዎች በውጭ ኢንቬስተሮች መያዛቸው፤ የኢትዮጵያ የግል ክፍሉ ጫጩት መሆኑ፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ ስርጭት የሚያመለክት የግል ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አለመመስረቱ፤ ጉቦ፤ በጎሳ የተመሰረተ አድልዎ፤ ሙስና፤ ከሃገር ተሰርቆ የሚሸሸው የውጭ ምንዛሬ ከፍተኛና አሳሳቢ መሆኑ፤ ወጣቱ ትውልድ ተምሮ ለስደት መዳረጉ፤ የገቢና የኑሮ ልዩነቶች አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሳቸው።
አራት፤ የወታደራዊው ሶሻሊስት መንግሥት ፀር-ዲሞክራሲ፤ ፀረ-ሕዝብ፤ ፀረ-ሰብአዊ መብት ወዘተ ነው ብሎ የምኒልክ ቤተ መንግሥት የገባው ህወሓት ዲሞክራሳዊ ስርዓት በመገንባት ፋንታ፤ ራሱ ፍፁም የሆነ አምባገነናዊ ስርዓት መመስረቱ፤ ሰብአዊ መብቶችን ፍፁም በሆነ ደረጃ ማፈኑ፤ ለእውነተኛ ሽብርተኞችና ለኢትዮጵያ ጠላቶች ሴራ ምክንያት መሆኑ። እነዚህን በቀጥታም ባይሆን በአጠቃላይ ያመነ ይመስላል። አምኖ ግን ራሱን ለመለወጥ አልተዘጋጀም፤ አልፈቀደም። ጨካኝነቱ ብሷል።
ያላመናቸውና ያልተቀበላቸው ብዙ የፖሊሲ ጥያቂቆች አሉ። ለምሳሌ፤ አንድ፤ የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ሃብት–ለም መሬትና ወንዝ–በገፍ ለውጭ አገር ኢንቬስተሮች ማስተላለፉ፤ ነዋሪዎችን ከቀያቸው በገፍና በግፍ ማስወጣቱ፤ ሰላምና እርጋታን ማደፍረሱ። ሁለት፤ “ከፋፍለህ ግዛው” የሚለውን የቅኝ ገዢዎች ፈለግ ተከትሎ ሕዝብን ከሕዝብ ማናከሱ፤ የዘር ማፅዳት ዘመቻ በቀጥታም ሆነ በድብቅ ማካሄዱ። ሶስት፤ በቋንቋ የተመሰረተ ፌደራሊዝም ዘርግቶ አዲስ “የመሳፍንት ዘመንን” የሚያስታውስ ጥቂቶችን ብቻ የሚያገለግል አስተዳደርና ኢኮኖሚ መመስረቱ። የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ከመቸውም በበለጠ ደረጃ በጎሳ ተከፋፍላለች። ለዚህ በሃላፊነት የሚጠየቀው ህወሓት ነው።
የማይካዱ ክስተቶች ብዙ ናቸው። የሕዝብ ለሕዝብ ሰንሰለት ተበጥሷል፤ የዘመናዊ ኢኮኖሚና የማህበረሰብ ግንኙነት (economic and social cohesion) አልተመሰረተም። የሃገር ፍቅር ወድሟል። ከመቶ ዓመታት በላይ የቆዩ ብሄራዊ ተቋሞች ፈርሰዋል። ሆነ ተብሎ።
ለኢኮኖሚው መዛባት ዋና ዋቢ ሆኖ የምናገኘው የተባበሩት መንግሥታት ተቋም አንክታድ (UNCTAD) ያቀረበው ዘገባ ነው። አትኩረን ስናነበው፤ ኢትዮጵያ ስር ነቀል የሆነ፤ የመላውን ሕብረተሰብ ኑሮ የሚያሻሽል፤ አገሪቱን ወደ ዘላቂና ፍትሃዊ ልማት የሚያሸጋግር የእድገት መንገድ ወይንም እቅድ አትከተልም የሚል ነው። የኢትዮጵያ መሰረታዊ ችግር ተፈጥሮ፤ እምቅ የተፈጥሮ ሃብት አለመኖር ወይንም የሕዝብ ስንፍና አይደለም። የስርዓት ማነቆነት ነው። በቅርቡ ዓለም ባንክ ያቀረበው ዘገባ ፍፁም ድህነት እንደቀነሰ ያሳያል። እድገት አለ በሚባልበት የብዙ ቢሊዮን ዶላር እርዳታ ድጋፍ በአገኘ አገር ፍፁም ድህነት መቀነሱ አያስደንቅም። ይኼን የፈጠራ ማስረጃ ይዘን ወደ ዋናው ችግር እንሂድ። አነጋጋሪ መሆን ያለበት፤ ወደ ባሰ ድህነት የገባውና የሚገባው ሕዝብ ብዛት፤ ጥልቀትና ስፋት ነው። መንግሥት የሚሰጠውን ማስረጃ ብቻ ብንቀበል፤ ሰላስ ሰባት ሚሊዮን (በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጊዜ የነበረውን ሕዝብ ቁጥር የሚበልጥ) ኢትዮጵያዊያን ፍፁም ድሃ ወይንም ወደ ፍፁም ድህነት የሚገቡ ናቸው። “Thirty-seven (37) million Ethiopians (almost a third of the population) remain either poor or vulnerable to falling into poverty. The very poorest in Ethiopia have become even poorer…The potential for migration (structural) and non-agriculture growth has been largely missed.” ዓንክታድ ያለውም ይኼን ነው። ይህ መዋቅራዊ ድህነት የፖሊሲ ለውጥ ከሌለ ሊቀየር አይችልም። ድሃ ሆኖ የተወለደ ህፃን ድሃ ይሆናል ማለት ነው። ዓለም ባንክ ማነቆዎቹ ምን እንደሆኑ አልገለፀም፤ ፖለቲካ ነክ ስለሆኑ።
የችግሩን ገፅታ በምሳሌ እንየው።
የሁለት ድሃ እናቶችን ኑሮ እናስብ፤ አንዷ በገጠር ሌላዋ በከተማ የሚኖሩ፤ በስደት የሚኖር፤ ከመቶ እስከ አንድ መቶ አምሳ ዶላር በዓመት አምስት ጊዜ የሚልክ/የምትልክ ልጅ የሌላቸው የገቢ ድሃ እናቶች ኑሮን ማለቴ ነው። በከተማ አምስት ወይንም ስድስት ልጆች የምታስተዳድር የቤት ሰራተኛ ወይንም መሸታ በመሸጥ የምትኖር፤ ወይንም የቢሮ ፅዳት ስራ ወይንም ሌላ ዝቅተኛ ገቢ ያላት እናት ልጆቿን በቀን ሶስት ምግብ ለመመገብ አትችልም። እንደሚባለው ከሆነ፤ የቤተሰቡ አባላት ምግብ በመፈራረቅ ይበላሉ፤ ህይዎታቸው አለ፤ ኑሯቸው ግን አሰቃቂ ነው። በተለይ የቤት ኪራይ የሚከፍሉ ከሆነ። ለዚህ ቤተሰብ ንፁህ ውሃ፤ መፀዳጃ፤ መብራት፤ የጤናና የትምህርት አገልግሎልት፤ መጓጓዣ ህልም ነው። ልጆቹ ለመማር ካልቻሉ ደግሞ መዋቅራዊ ወደ ሆነ፤ ከትውልድ ወደ ትውልድ ወደሚተላለፍ ድህነት ገቡ ማለት ነው። በአዲስ አበባ ብቻ እስከ አንድ ሚሊዮን የሚገመት ሕዝብ–እናቶች፤ ሺማግሌዎች፤ እናት የሌላቸው ህጻናት፤ ወጣት ወንድና ሴቶች በመንገድና በጠለላ ይኖራሉ፡፡ ይሕ በ November 8, 2012 በአንድ የውጭ አገር ታዛቢ ተቀርጾ የተላለፈ ቢዲዮ የድህነትን አሰቃቂ ገጽታ ያሳያል። እድገት በጦፈባት አዲስ አበባ፤ አንድ ሚሊዮን ሕዝብ ማለት የአዲስ አበባ ሕዝብ አንድ አስረኛ ማለት ነው። የሰዎቹ በጠለላ መኖር ብቻ አይደለም አሰቃቂነቱ። እናቶችና ወጣቶች ኮራ በተባለው አካባቢ የሚጣለውን ቆሻሻ ምግብ እየለቀሙ መብላታቸው ጭምር ነው። ለበሺታ የሚዳርገው የቆሻሻ መሰብሰቢያ አይጥ፤ ልዩ ልዩ ተባዮች ተሰማርተውበታል። በተላላፊ በሺታዎች መበከል አይቀሬ ነው። በጠለላ ተጨናንቀው የሚኖሩት ኢትዮጵዊያን የአባለ ዘርእ በሺታ፤ ኤች አይ ቢ አኤድስ፤ የተስቦ በሺታ፤ ቲቪ ወዘተ ያሰቃያቸዋል። አዲስ ባለሃብቶች “ለቃተኛ” ምግብ በሚሰለፉባት አዲስ አበባ እነዚህን ድሃዎች ዞር ብሎ የሚያያቸው የለም። ሰብእነታቸው ሙሉ በሙሉ ተገፏል ለማለት እንችላለን። ይኼ ብዙ ሕዝብ ጤናው ከመታወኩ ሌላ ልጆቹና የልጅ ልጆቹ ወደ ፍፁም ድህነት ገብተዋል ማለት ነው። በዚህ ሁኔታ ተወልደው የሚያድጉት ወጣቶች እንደሌላው ወደ ውጭ ለመሰደድም ተስፋ አይኖራቸውም። ከጥቂቶች በስተቀር።
ከላይ የተጠቀሰችው እናትና በጠለላ የሚኖሩ የተወሰኑ እናቶች ልጆች አማራጭ ስለሌላቸው ወደ ውጭ ይሰደዳሉ። የድሃ አናት ሴት ልጇ “በዚህ አይነት ኑሮ አልኖርም፤ እድሌ ያውጣኝ፤ ወደ አረብ አገሮች ወይንም ወደ ማላዊ እሰደዳለሁ” ብትል እናቷ ልታቆማት አትችልም። በገጠር የምትኖረው ስድስት ልጆች የምታስተዳድር እናት የተሻለ ኑሮ ትኖራለች። ልጆቿ ከቆሻሻ ምግብ አውጥተው አይበሉም። የእርሷ ችግር ለየት ያለ ነው። ቤተሰቧ አንድ ሄክታር መሬት አለው እንበል። የእርሻው ስራ ለራሳቸው ምግብ በቂ ነው፤ ቅጠላ ቅጠል፤ ድንች ወዘተ በጓሮ ያመርታሉ፤ ስለዚህ ራሳቸውን ችለዋል የሚለውን እንቀበል። ይህ ቤተሰብ ገቢው ከፍ ስላለ ጥራ ጥሬ ወይንም በግ ሽጦ ልብስ፤ ጫማ፤ የተሻለ የእርሻ መሳሪያ ወዘተ ለመግዛት እናት ወደ ገበያ ብቅ ስትል ከገቢዋ ጋር ተመጣጣኝ የሚሆን የአገር ውስጥ ሆነ የውጭ እቃ ለመግዛት አልቻለችም፡፡ “እግዚዖ፤ ምን ጉድ መጣ፤ እድገት አለ እያሉ እንዴት ምርት ለማቅረብ አልቻሉም” ብላ ራሷን ከመጠየቅ አታልፍም። በአገር ውስጥ የሚመረተው ከፍላጎት ጋር አልተመጣጠነም ማለት ነው። የከተማ ነዋሪዋ በቂ ምግብ የላትም፤ የገጠሯ ለኑሮዋ መሻሻል የሚያስፈልጋትን ለመሸመት አልቻለችም። መዋቅሩ አልተለወጠም የሚባልበት መሰረታዊ ምክንያት ከምርት ጋር፤ ከእርሻ ዘመናዊነት ጋር፤ ከአቅርቦት ጋር፤ ከኢንዱስትሪ መስፋፋት ጋር፤ ከስራ እድል ጋር፤ ከኑሮ መሻሻል ጋር የተያያዘ ባለመሆኑ ነው። “መንገዱ እኮ ምግብ አይሆነኝም” ያለውን ኢትዮጵያዊ በአእምሯችን እንቅረፀው። በልቶ ማደር የሰብአዊ መብት ነው። የቀድሞው የብራዚል ፕሬዝደንት ዳ ሲልቫ የተናገሩት ትዝ ይለኛል። “ርሃብ ከማንኛውም አሰቃቂ እልቂት የባሰ ነው፤ ርሃብን፤ ድህነትን ማጥፋትና ዘላቂነትና ፍትሃዊነት ያለው የልማት እቅድ መከተል ለሰላም ወሳኝ ነው” ያሉት። መዋቅራዊ ለውጥ ከዚህ ተለይቶ አይታይም።
ኡኑክታድ እድገት ያሳየችው ኢትዮጵያ እድገቷን ተጠቅማ መዋቅራዊ ለውጥ አልመሰረተችም ሲል በፍጥነት ካደጉ፤ ለምሳሌ ከምስራቅ ኤዝያና ፓሲፊክ ሃገሮች ጋር በማነጻፀር ነው። እነዚህ አገሮች ዘመናዊነትና ሃብታምነትን የተጎናፀፉት ሁለገብ የሆነ፤ አንዱ ሌላውን የሚደግፍ፤ በሕዝብ ተሳትፎ፤ ደህንነትና የኑሮ መሻሻል የተመሰረተ የልማት መንገድ በመከተላቸው ነው። አገር ወለድ የሆነ። መንግሥቶቻቸው ለሃገራቸው ተቆርቋሪነትና ሃላፊነት፤ ለመላው ሕዝባቸው ፍቅር ያሳዩ፤ ከሁሉ በላይ አገሮቻቸውና ህብረተሰቦቻቸው ከድህነትና ከኋላ ቀርነት መጥቀው የምእራብ አገሮች ከደረሱበት ለመድረስ ቀን ከሌት የሰሩ ናቸው። የተፈጥሮ ሃብታቸውንና ሃገራቸውን እንደ ተራ ሸቀጥ አልነገዱበትም። ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ ምሳሌ ናቸው።
እንደ ደቡብ ኮሪያ ድሃና ኋላ ቀር የነበሩ አገሮች የውጭ ብድር ተጠቅመው፤ ግን በአብዛኛው በራሳቸው ጥረትና በመንግስቶቻቸው አገር ወዳድ አመራር፤ ደቡብ ኮሪያን በሃያ አምስት ዓመታት ከበለፀጉ አገሮች አንዷ እንድትሆን አድርገዋል። ደቡብ ኮሪያ ከእርዳታ ነጻ የሆነችው ከሃያ እስከ ሃያ አምስት አመታት በሚገመት የጊዜ ገደብ ነው። የውጭ እርዳታ ጥገኝንትን እንደሚያስከትል የተረዱ መሪዎች ነበሩ። በፍጥነት አስደናቂ የልማት ውጤት ስኬታማ ያደረገችው በአገር ወዳድ መሪዎቿ፤ ዘመናዊ ከፓርቲ ቁጥጥር ውጭና ብሄራዊ በሆኑ ተቋሞቿ፤ በሰለጠኑ የመንግሥት ሰራተኞቿ አገልግሎትና መላውን ሕዝቧን አሳታፊ በሆኑ ህጎችና መመሪያዎች ነው። ለዘላቂና ፍትሃዊ ልማት የሃገር ፍቅር ሚና አለው፤ ተቋሞች ሚና አላቸው፤ የህግ የበላይነት ሚና አለው፤ ሃላፊነትና ግልፅነት ሚና አላቸው። ደቡብ ኮሪያ፤ ቻይና፤ ቬትናምና ሌሎች አሳይተዋል። አምባገነን መንግሥታት ቢኖሯቸውም አገር ወዳድነታቸው አያከራክርም። ከሁሉም በላይ ቅድሚያ የተሰጠው ኮሪያን በፍጥነት ማሳደግና የኮሪያን ሕዝብ ከድህነት፤ ከርሃብ፤ ከስራ አጥነት፤ ከድንቁርና፤ ከበሽታ ወዘተ ነጻ ማውጣት ነበር። ሴቶች፤ ወጣቶችና የገጠሩ ሕዝብ የእድገቱ ሙሉ ተሳታፊ ነበሩ። በዚህ ስሌት ይሆን ለሃገርና ለመላው ሕዝብ ፍቅር አለኝ ለማለት የማይችለው፤ አሁንም ራሱን የ “ትግራይ ነጻ አውጭ ግንባር” ብሎ የሚጠራው ህወሓት ተጨማሪ አምስት ዓመታት መግዛት አለብኝ እያለ አፈናውን ያባባሰው። ለምን ይሆን ብሎ መጠየቅ ሞኝነት ቢመስልም፤ ጥያቄውን ማቅረብ ተገቢ ነው። ከጅምሩ፤ ህወሓት ለኢትዮጵያ ታላቅና ረጂም ታሪክ ግምትና እውቅና አልሰጠም፤ የኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅሞችና ሉአላዊነት ደምስሧል፤ ሕዝቦቿ እየተወያዩና እየተናበቡ አብረው ችግሮችን መፍታትና ተቻችሎ መኖርን መመሪያቸው እንዳያደርጉ በተግባር አሳይቷል፤ የደርግን መንግሥት ጨካኝነት፤ ኢሰብአዊነትና ፀረ-ዲሞክራሳዊነት በማስተጋባት፤ “ህወሓት/ኢህአዴግ አዲስ የዲሞክራሲ ምእራፍ ይዤ መጥቻለሁ፤ የምስራች ለኢትዮጵያ ሕዝብ” ብሎ ስልጣኑን ካመቻቸ በኋላ ከደርግ ያላነሰ ፀረ ዲሞክራሲ፤ ፀረ-ሕዝብ ሆኗል። ሕዝቡ ዲሞክራሳዊ ስርዓትን ለመገንባት ያለውን ምኞትና ተስፋ የውሃ ሺታ አድርጎታል። ያለፉትን መንግሥታት እየወነጀለ ጠባብና ጎሰኛ አድሏዊነትን የመንግሥት መመሪያ አድርጓል። በጥላቻና በቂም በቀል የተመራበት መርህ ታላቋን ትግራይ መመስረት የሚል፤ ለዚህ እንዲጠቅም የጎንደርንና የወሎን መሬቶች በኃይል ነጥቆ ወደ ትግራይ ክልል አጠቃሏል። የትግራይን ወሰን ከሱዳን ጋር ኃይል ተጠቅሞ ዘርግቷል። በታሪኩ ኢትዮጵያዊ የሆነውን የትግራይን ሕዝብ ከሌሎቹ ወንድሞቹና እህቶቹ ለመለየት ሞክሯል። ጥላቻንና ቂም በቀልነትን አንግቦ “ኦሮሞውን አማራው ተመልሶ ስልጣን ሊይዝ ነው፤ ተጠንቀቅ፤ አማራውን ኦሮሞው ስልጣን ከያዘ ወዮልህ፤ እልቂት ይከተላል፤ ትግሬውን፤ አማራውም ሆነ ኦሮሞ ስልጣን ከያዘ ትግሬዎችን በያሉበት ይጨፈጭፋል፤ የሩዋንዳ አይነት እልቂት አይቀርም” ወዘተ የሚል ቡድን ነው። ይኼ ለብሄራዊ እድገትና ሰላም ፀር ነው።
ይኼ ሁሉ በድምሩ ለመብቶች መገፈፍና ለኢትዮጵያ ሕዝብ መከፋፈል አስተዋፆ አድርጓል። ሕዝብ ለሕዝብ አለመተማመን የጠቀመው ለዚህ ቡድን ነው። “ከፋፍለህ ግዛው” የቡድኑን አምባገነን ስርዓት አራዝሞለታል፤ ለሰብአዊ መብቶች መታፈን መሰረት ሆኗል። ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና “ተባበሩ ወይንም ተሰባበሩ” ሲል ይኼን አይቶ ይመስለኛል። በምን ላይ እንተባበር? የሚለው የአንዳንድ ተቃዋሚ ክፍሎች ትርጉም የለሽ ጥያቄ ከተመለሰ ቆይቷል። ፈቃደኛነት፤ መተማመን ወዘተ ስለሌለ መተባበር የሚለውን ቃል ሰምተን እንዳልሰማን እያለፍነው ነው። እድል እያመለጠን ነው። ቢያንስ፤ በኢትዮጵያ ሉአላዊነትና ግዛታዊ አንድነት–አገርን በማዳን፤ በሰብአዊ መብቶች መከበር፤ ሕዝብን ከመገረፍ በማዳን፤ በሕግ የበላይነት፤ ለሕዝብ ታዛዢ የሆነ መንግሥት በመመስረት፤ በነጻና ፍትሃዊ ምርጫ፤ በፀረሙስና፤ በፀረየመሬት ነጠቃ ወዘተ ለመስማማትና አብሮ ለመስራት ይቻላል። መተባበር ከሌለ በተናጠል የፖለቲካ ጩኸቱ ዋጋ ቢስ ነው፤ የትም አያደርስም። ከአርባ ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከተቃዋሚው ክፍል የሚጠብቀው መጠላልፍን አይደለም። መተባበርን፤ መተሳሰብን፤ ለጋራ ዓላማዎች መቆምን ወዘተ ነው። “ለመተባበር የሚያስችሉ ሁኔታዎች የሉም፤ በተናጠል የምንታገለው ለዚህ ነው” የሚሉ ግለሰቦችና ቡድኖች የሚያገለግሉት ራሳቸውንና ገዢውን ፓርቲ ነው ለማለት ከምንደፍርበት ጊዜ ደርሰናል። ህወሓት በበላይነት የሚመራው ስርዓት አገሪቱን ለማስተዳደር፤ አንድነቷን ለመጠበቅ፤ የህዝቧን ሕይዎት ለማሻሻል ከማይችልበት ደረጃ ላይ እንደ ደረሰ ብዙ ተመልካቾች ይናገራሉ። አስተዳደር ፍፁም ተበላሽቷል። የሕዝብ አመፅ በየቦታው ብቅ ብቅ ማለት ጀምሯል። በሰራዊቱ ውስጥ ሹክቻው ተስፋፍቷል ወዘተ። ስለሆነም ነባራዊ ሁኔታው በፍጥነት እየተለወጠ ነው። ለዚህ ጠንካራ ድርጅትና መተባበር ወሳኝ ነው። አንዱ ሲነሳ ሌላው መነሳት፤ አንዱ ሲደበደብ አለሁልህ ማለት ወዘተ አስፈላጊ ነው።
በብዙ ተመልካቾች ዘገባ ተጨማሪ አምስት ዓመታት ሆነ አስር ቢገዛ ህወሓት የኢትዮጵያን መሰረታዊ ችግሮች በጋራ ለመፍታት የሚቻለው የኢትዮጵያ ሕዝብ የስልጣኑ ባለቤት ሲሆን ብቻ ነው። ባለፉት ሃያ አራት ዓመታት ሊፈቱ ያልቻሉ የፖሊሲና መዋቅራዊ የሆኑ የማህበረሰብ ችግሮች፤ ለምሳሌ የስራ እድል አለመኖር፤ የኑሮ ውድነት፤ የመጠለያ እጥረት፤ ጉቦ፤ አድልዎ፤ ሙስና፤ የመሬት ነጠቃ፤ ከህግ ውጭ ከአገር የሚወጣው ብዙ ቢሊዮን ዶላር፤ የኢትዮጵያዊነት መታወቂያ ቅርሶች መውደም፤ ወዘተ፤ወዘተ በህወሓት/ኢህአዴግ መሪዎች አርቆ አስተዋይነት ይፈታሉ ብሎ ማሰብ አይቻልም። ለጠባብ ቡድን ጥቅም የቆመ አገዛዝ ጥቅሙን የሚያስተናግደው የፖለቲካና የኢኮኖሚ የበላይነትን በመያዝ ብቻ ነው። እርግጥ፤ የአሁኑን የአምስት ዓመት እቅድ አሻሽለናል፤ በስራ እድል ፈጠራ፤ በእርሻና በኢንዱስትሪ ልማት ላይ ወዘተ ትኩረት እናደርጋለን ወዘተ ሊል ይችላል። ይህ መሰረታዊ ለውጥ አያመጣም፤ የመቆያ ዘዴ ነው። መሰረታዊ ለውጥ ከሕዝብ መብቶችና ስልጣን ጋር የተያያዘ ነው። የሚተካው ነገር የለም።
ዛሬ ፍጹም በሆነ ደረጃና ከድሮው በባሰ ሁኔታ የሰብአዊ መብቶች መረገጥ የሚያሳየው ገዢው ፓርቲ የሃብት ጥቅም ያጎናፀፈውን የብቸኛነት የፖለቲካ ስልጣን ለማንም አሳልፎ እንደማይሰጥ ነው። የፍራቻው መንስኤ ይኼው ነው ለማለት ያደፋፍራል። ለፍርሃት መልሱ ደግሞ አፈና ነው። ህወሓት የሚፈራውና የሚሰጋበት አበይት ነገር አለ ማለት ነው። እመርታዊ የሆነ መላውን መቶ ሚሊዮን ሕዝብ የሚያገለግል የልማት መሰረት ከጣለ ህወሓት/ኢህአዴግ የሰብአዊ መብቶችን መከበርና የተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ተሳትፎ የሚፈራበት ምክንያት የለም፤ ለምን ይፈራል? የሃሳብ ልዩነቶችን ለምን ይፈራል? የአብዛኛውን ኢትዮጵያ ሕዝብ ህይዎት ካሻሻለ፤ ለወጣቱ ትውልድ የስራ እድል ከፈጠረ፤ የአስተዳደር አግልግሎቱ ቀልጣፋና ከጉቦና ከአድልዎ ነጻ ከሆነ ሕዝቡ ያምነዋል ማለት ነው። ካመነው ይመርጠዋል ማለት ነው። ያለምንም ማጭበርበር። ሁኔታው ከዚህ የተለየ ነው። አፈናው በስርዓቱ ውስጥ ያለውን ፍራቻ ያመለክታል። “ከፈራን እኮ ኢትዮጵያን እንደ ኤርትራ ለማድረግ እንችል ነበር” የሚል አነጋገር ይሰማል። ኢትዮጵያ እንደ ኤርትራ ብትሆን ኖሮ ለጋሶች ለልማታና ለምግብ ድጎማ ወደ አርባ ቢሊዮን ዶላር፤ ለልማት ድጎማ ብቻ በዓመት አራት ቢሊዮን ዶላር አይለግሱም ነበር። ባይለግሱ ኖሮ አዲስ ስርዓት ወለድ ሚሊዪኔሮች አይፈጠሩም ነበር። ጀኔራሎች የሚያከራዩት ሰማይ ጠቀስ ፎቅና የመኖሪያ ቪላዎች ለመስራት አይችሉም ነበር። ወዘተ. ወዘተ. አፈናው ይኼ ሁሉ እንዳይታወቅ ጭምር ነው።
የነጻ ተቋሞች ፍፁም መደምሰስ
ህወሓት ትኩረት ያደረገው ተፎካካሪ/ተወዳዳሪ በሆኑ፤ ለሕብረተሰቡ ነጻነት፤ መብትና ፍትህ በቆሙ ህብረ ብሄር የፖለቲካ ፓርቲዎችና የነጻ መገናኛ ብዙሃን ላይ ነው። ሁለቱን ክፍሎች ያያቸውና የፈረደባቸው እንደ ተወዳዳሪና አማራጭ ሰጭ ሳይሆን እንደ ጠላት ነው። ሕብረ-ብሄር የፖለቲካ ድርጅቶች፤ በተለይ አንድነት፤ መኢአድና ሰማያዊ በሕዝብ በኩል ተሰሚነትና ታማኝነት ስለተቀዳጁ ለገዢው ፓርቲ አስጊ ናቸው ከሚል ድምዳሜ ላይ የደረሰ ይመስላል። ስለሆነም፤ እነዚህን ተቀናቃኞች የመንግሥት ስልጣንና ገንዘብ ተጠቅሞ፤ የሕጋዊ ሽፋን–የምርጫ ቦርድ፤ ፍርድ ቤቶች፤ ፖሊስ–(the veneer of legality, for example, the political machine of the Election Board) ተጠቅሞ ማዳከም፤ ማግለል፤ ቢቻል ዋጋ ቢስ ማዳረግ የመንግሥት ስራ ሆኗል። ዓላማው እነዚህ ተቀናቃኞች በምርጫው እንዳይሳተፉ ለማድረግ ነው። ፈቃድ የሚሰጣቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ለገዢው ፓርቲ ታማኝ የሆኑት ብቻ ይሆናሉ ማለት ነው። ከሆነ፤ ገዢው ፓርቲ የዛሬ አምስ ዓመስት ካገኘው የበለጠ ወይንም ያላነሰ ድምፅ አገኘሁ ብሎ የበላይነቱን ይቀጥላል ማለት ነው። የአውሮፓ የጋራ ማህበር እንዳለፈው ወደ ኢትዮጵያ የምርጫ ተመልካቾች ወይንም ታዛቢዎች አልክም ብሎ የወሰነበት ምክንያት በነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ሂደት ምንም እምነት ስለሌለው ነው። አግባብ ያለው አቋም። አሜሪካም ይኼን መንገድ መከተል አለባት።
ህወሓት ሌላ ትኩረት የሰጠው ተቋም በነጻነት የሚንቀሳቀሱ መገናኛ ብዙሃንን ማጥፋት ነው። ነጻ የሆኑ ጋዜጠኞችን ለምን በጅምላ አሰረ ወይንም ከሃገር እንዲወጡ አስገደደ፤ ወይንም ራሳቸውን እንዲያግቡ (Self-censorship) አስገደደ? የፖለቲካ ውድድር አማራጮችን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ለማቅረብ የሚደረገው ጥረት የህወሓትን የበላዮች ለምን አስፈራቸው? ወዘተ. ወዘተ. ህወሓት/ኢህአዴግ በነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ተወዳድሮ ቢያሸንፍ የሕዝብን ልብ ሊማርክ፤ የዓለምን ሕዝብ አክብሮት ሊቀዳጅ ይችላል። ይኼ ከሆነ ሽብርተኞች ቀዳዳና ቦታ አያገኙም። ሕዝቡ መግቢያ ይነሳቸዋል። የገዢው ፓርቲ እምነት በጠበንጃ ሳይሆን በሕዝብ መብት ላይ የተመሰረተ ቢሆን ሰላምና እርጋታ አስተማማኝ ይሆናሉ፤ አሁን አይደሉም። የነጻነታቸውን መብት ተጠቅመው የሚንቀሳቀሱ ጋዜጠኞችና ተወዳዳሪ ፓርቲዎች ተመሳሳይ የሆነ አቋም አላቸው። ሰብአዊ መብቶች፤ ፍትህ፤ የሕዝብ ድምፅ ይከበሩ ወዘተ የሚል። ስለሆነም፤ እንደ ጠላት ተቆጥረዋል። ህወሓት ተወዳዳሪ ጠላቱ ነው።
ህወሓት የተወዳዳሪ ፓርቲዎች አባላትንና መሪዎችን፤ ነጻነታቸውን ጠብቀው ለሕዝብ የሚያገለግሉ ጋዜጠኞችን፤ ብሎገሮችን፤ የማህበረሰብ ድርጂት መሪዎችን ወዘተ እያሰረ፤ እያሳደደ፤ እያስፈራራ፤ እያባበለ፤ ሰርጎ ገብቶ እየከፋፈለ ተቃዋሚ—ተወዳዳሪ ብሎም አይጠራቸውም– የለም ይላል። የፖለቲካ ምድሩ (ምህዳሩ) ዝግ ከሆነ፤ መናገር፤ መሰብሰብ፤ ሕዝብን ማነጋገር፤ ሰላማዊ ሰልፍ ማካሄድ ወንጀል ከሆነ ተቃዋሚ ወይንም ተወዳዳሪ ፓርቲ ሊኖር አይችልም። እያፈኑና እያሳደዱ ተወዳዳሪ የለም ማለት ለህሊና ተቀባይነት የሌለው አጭበርባሪነት ነው። የማይካደው ህወሓት ተቃዋሚውን የሚያየው በጥላቻና በጥርጣሬ መነፅር ነው። እንደ ጠላት። በዚህ ፓርቲ ስሌት ጠላትን መወንጀል፤ ማሳደድ፤ በድብቅ መግደል፤ መደብደብ፤ ማዋረድ፤ ማሰር፤ መንቀሳቀሻ ማሳጣት፤ ወንጅሎ ቤተስብና ወዳጅን መከታተል፤ አስፈላጊ ሲሆን ንብረትን መቀማት መሆኑ ለሰላም፤ ለእርጋታ፤ ለዘላቂና ፍትሃዊ እድገት ማነቆ ሆኗል። አማራጩ አሁንም በጥላቻ ፖለቲክ አዙሪኝ መጓዝ አይመስለኝም። ለህወሓት/ኢህአዴግም አይበጅም። የሚበጀው በሰከነ አእምሮ፤ አገሪቱን ከመበታተን አደጋ ለማውጣት የሚያስችል፤ ሁሉንም ዜጎች የፖለቲካው ስልጣንና የእድገቱ ተካፋይ የሚያደርግ፤ ሙስናን የሚቆጣጠር፤ የጠፋውን ግዙፍ ሃብት ተከታትሎ ለማስመለስ የሚያስችል፤ በጎሳ የተመሰረት አድልዎን የሚያስወግድ፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በሕግ ፊት እኩለነት እንዳላቸው የሚያስተጋባ፤ የፖለቲካ ተወዳዳሪነት ጠላትነት ሳይሆን ለሃገሪቱና ለሕብረተሰቡ ፍትህ-ርትህ ወሳኝ መሆናቸውን የሚያስተጋባ ባህልና ልምድ፤ ኢትዮጵያዊያን በመፈላለግ፤ በመወያየት ችግሮቻቸውን በእርቅና በሰላም ለመፍትት የማመቻቸት ብቃት እንዳላቸው የሚያመልክት፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ የስልጣኑ ባለቤት መሆኑን የሚያንፀባርቅ አገዛዝ ለመመስረት እንደሚችሉ የሚያሳይ፤ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ለዚህ ዲሞክራሳዊ ስርአት ወሳኝ መሆኑን ተቀብሎ አዲስ የፖለቲካ ምእራፍ መክፈት ነው። አዲስ ለሕዝብ ተገዢና ተጠሪ የሆነ አገዛዝ ይመስረት ማለት እንዳለፈው ለመወነጃጅል፤ ለቂም በቀልነት መሆን የለበትም። ፍትህ እንዲሰፍን፤ ሕብረተሰቡ ከአስቃቂ የኑሮ ችግር መጥቆ እንዲወጣ፤ አገሪቱ እንዳትፈራርስ፤ የውጭ ጠላቶችና ሽብርተኞች መግቢያ ቀዳዳ እንዳይኖራቸው ነው። ይኼ በምኞት አይመጣም። የሰብአዊ መብቶች መከበር ለዚህ የተቀደስ አቅጣጫ ወሳኝ ነው።
ሰብአዊ መብቶች ነገ ሳይሆን ዛሬ ካልተከበሩ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ በምንም አይታሰብም። እንዲያውም እድሉ አምልጧል ለማለት ያስደፍራል። በህወሓት ስሌት አሸናፊው በቅድሚያ ተወስኗል። የፖለቲካ አካልና መሳሪያ የሆነው የምርጫ ቦርድ ዋና ስራው ተወዳዳሪ የሆኑ፤ በተለይ እንደ አንድነት፤ መኢአድ፤ ሰማያዊና ሌሎች ህብረ ብሄር የፖለቲካ ፓርቲዎች በረባ ባልረባው ተወጥረው፤ ለምርጫው ዝግጅት እንዳያደርጉ፤ አቤቱታ አቅራቢ እንዲሆኑ አስገድዷቸዋል። የምርጫ ቦርድ፤ የህወሓት ካድሬዎች፤ የፖሊስ፤ ደህንነትና ፍርድ ቤቶች ተቆራኝተው የምርጫ ቦርድ የገዢው ፓርቲ፤ በተለይ የህወሓት መሳሪያ መሆኑ በኢትዮጵያ ሕዝብ በኩል አመኔታ እንደሌለው ካሳየ ቆይቷል። የውጭ የሰብአዊ መብቶች ተቋሞችና መንግሥታት ይህ ሁኔታ በጣም አደገኛ መሆኑን በተደጋጋሚ ተናግረዋል። እነዚህ ድርጅቶች በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ የሚያቀርቡት ሂስ የራሳቸው ፈጠራ አይደለም። በተጨማሪ፤ አንዳንድ መንግሥታትን ያሳሰባቸውም ከራሳቸው ጥቅም ጋር ሲመለከቱት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈጠር የእርስ በርስ ግጭት ሰላምና እርጋታ ለሌበት ለመላዉ የአፍሪካ ቀንድ አደገኛ መሆኑን ስላወቁት ነው። በተጨማሪም፤ የውጭ ኢንቬስተሮች ቀስ በቀስ የሰብአዊ መብቶች መረገጥ አደገኛ መሆኑን እየተረዱ ናቸው። የራሳቸው ሕዝብ እየጮኸባቸው ነው። የሰብአዊ መብት ተቋሞች የሚያስመሰግን አስተዋፅዖ አድርገዋል። በቅርቡ የጀርመኑ የግል ድርጂት ችቦ (Tchibo)፤ የቱርኩ Ayka Investment፤ የስዊድኑ H&M በኦሞ ሸለቆ የሚመረት ጥጥ ለጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ስራቸው አንጠቀምም ብለው አስታውቀዋል። ለምን? የኦሞ ሸለቆ ልማት የሚካሄደው ነዋሪውን ሕዝብ ከመሬቱ አስገድዶ በማስወጣት ነው።
የመሬት ነጠቃ የሚባለው በኢትዮጵያ ስር የሰደደው የገዢው ፓርቲ የልማት አካል መብቶችን አፍኗል። ልክ ጋምቤላ እንደሚደረገው የመሬት ነጠቃ የኦሞ ሸለቆን ነዋሪ ሕዝብ አግልሎታል፤ መድረሻ አሳጥቶታል፤ኑሮውን አፍሮሶበታል። ለጭቁን ሕዝቦች ቆሜያአለሁ የሚለው ህወሓት በኢትዮጵያ ዜጎች ላይ ያካሄደውና የሚያካሂደው በደል ይዘገንናል። ከቡድኑ ጥቅም በላይ አሻግሮ ለማየት አልቻለም። ነዋሪዎች ከመሬታቸው ተገደው እየፈለሱ ከድህነት ወደ ፍፁም ድህነትና ስደት እንዲሸጋገሩ ተደርጓል።
ይኼ የሚካሄደው በልማት ስም ነው፤ ልማቱ የሚያገልግለው የኦሞ ሸለቆን ነዋሪዎች ሳይሆን የገዢውን ፓርቲና አጋሮቹን ነው። የእነዚህ ወገኖቻችን መብት ከተገፈፈ የራሳችንም መብት ተገፈፈ ማለት ነው። ህወሓት ይኼን የሚያደርገው ዓለም የተቀበለውን ሕግና መመሪያ ጥሶ ነው። አከራካሪው የህወሓት መብቶችን ማፈኑ ብቻ አይደለም፤ የውጭ እርዳታ ሰጭዎች ተባባሪነት መኖሩ ጭምር ነው።
በ January 19, 2015, Guardian ያወጣው ዘገባ የመሬት ነጠቃን አደጋ ያሳያል። ዓለም ባንክና የእንግሊዝ መንግሥት የእርዳታ ክፍል ለአዲስ መንደሮች ግንባታ የሰጡት ድጋፍ ሰብአዊ መብቶችን የጣሰ መሆኑን አስምሮበታል። የዓለም ባንክ የውስጥ ቁጥጥር ክፍል ባንኩ የሰጠው እርዳታ “በቁጥጥር፤ በዖዲት፤ በባንኩ የውስጥ ደንብ” ስላልተደገፈ እርዳታው “የኢትዮጵያ መንግሥት የፖለቲካ መሳሪያ ሆኗል” የሚል ትችት ነው። በዚህ የተነሳ “ብዙ ሺህ ኢትዮጵያዊያን ከመሬታቸው በኃይል ተወግደው ለድህነት ተዳርገዋል፤ ብዙዎች ተሰደዋል፤ ኑሩቸው ተናግቷል።” ጥልቀት ያለው ጥናት ያደረገው ዖክላንድ ኢንስቲቱት “ዓለም ባንክ ራሱን አልገሰፀም” ብሏል። በማንኛውም የእርዳታ ክፍል ዓለም ባንክ ራሱን ስህተት ሰርቻለሁ ብሎ አያውቅም። አኑራዳህ ሚታል፤ የተቋሙ መስራችና ፕሬዝደንት እንዲህ ብላለች። “Along the World Bank and other donors, DFID (UK) support constitutes not only financial support but a nod of approval for the Ethiopian regime to bring about economic development for the few at the expense of basic human rights and livelihoods of its economically and politically most marginalized ethnic groups.” ለህወሓት መንግሥት የሚሰጠው ማንኛውም እርዳታ ነጻ የሆነ ቁጥጥር የለውም፤ ገንዘቡ የሚሰጠው ለገዢው ፓርቲ ነው። ማስረጃው የሚመጣው ከራሱ ነው። የድሃው ቁጥር ብዛት በትክክል አይታወቅም። እድገቱ ለማን እንደጠቀመ ይታወቃል፤ ማንን እንደጎዳ ይታወቃል። ዓለም አቀፍ ሁሉን ዓቀፍ ተቋም የሚመራው ዴቪድ ፕሬድ እንዳለው “ዓለም ባንክ ኢትዮጵያዊያን ከቀያቸው በኃይል እንዲባረሩ አድርጓል…ሰብአዊ መብቶች እንደተገፈፉ አይቶ እንዳላየ ዝም ይላል። The Bank today just does not want to see human rights violations, much less accept that it bears some responsibility when it finances those violations.” ባጭሩ፤ አበዳሪዎችና ለጋሶች ለሰብአዊ መብቶች መገፈፍ ሃላፊነት አለባቸው። ለህወሓት የሚለግሱት የማፈኛ መሳሪያ ሆኗል።
ዓለም ቸል ያለው አፈና
ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የተቀበላቸውን የማህበረሰብና የፖለቲካ መብት ህግ፤ ደንብና መመሪያ ፈርማለች (The International Covenant on Civil and Political Rights (ICCPR). አንቀፅ አስራ ዘጠኝ እንዲህ ይላል። “ማንኛውም ግለሰብ የማንም እጅ (የመንግሥት ወይንም ሌላ) ሳይገባበት የራሱን ነጻ ሃሳብ/አስተሳሰብ ለመናገር ይችላል፤ ማንም ግለሰብ የመናገር፤ ራሱን የመግለፅ መብቱ የተጠበቀ ነው፤ ይህ መብት ዜና የመፈለግ፤ የመቀበልና የማስተላለፍ መብትን ይጨምራል፤ ዜናው ገደብ የለውም፤ ወሰን የለውም፤ በቃል፤ በጽሁፍ፤ በመፅህፍ፤ በመፅሄት፤ በስእል፤ በሙዚቃና በሌላ የመገናኛ ዘዴ ሊገለጽ ይችላል።” እነዚህ መብቶች በአብዛኛው ዓለም የተከበሩ ናቸው። ህወሓት እነዚህን መብቶች በምንም አይቀበልም፤ እንዲያውም “ሺሙጥ” የመሰሉ ወይንም ውስጠ ወይራ የሆኑ የህወሓትን መሪዎች የሚመለክቱ ነገሮች ሲወሩ ወይንም ሲነገሩ፤ ወይንም ሲጻፉ፤ “የግለሰብ ክብር ነክታችኋል” ብሎ ይከሳል። የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ኮሚቴ ያወጣውን መመሪያ ዋጋ አልሰጠውም ማለት ነው። “States have the responsibility to ensure that defamation laws must be crafted with care to ensure that they do not serve, in practice, to stifle freedom of expression… መንግሥታት መጠንቀቅ ያለባቸው የግለሰብ ክብር የሚነኩ ህጎችን ሲያወጡ፤ ህጉን የፖለቲካ መሳሪያ አድርገው የሰብአዊ መብቶችን እናዳያፍኑ ነው” ይላል። ህወሓት ያወጣው የፀረ-ሽብርተኛ ሕግ የሚያገለግለው ሰብአዊ መብቶችን ለማፈን ሆኗል። ማንኛውም ተቃውሞ ወንጀለኛነት ሆኗል። ማንም ተቃዋሚ ግለሰብ በዚህ ሕግ ሊከሰስ፤ ሊፈረድበት ይቻላል ማለት ነው። ሕጉ የገዢው ፓርቲ የፖለቲካ መሳሪያ መሆኑ ምንም አያከራክርም። የህወሓት መንግሥት ዓለም አቀፍ ህጎችን አክብሮ አያውቅም። ራሱ ከሳሺ፤ ራሱ ማስረጃ አቅራቢ፤ ራሱ ዳኛና ፈራጂ፤ ራሱ አሳሪ ነው።
የታወቀው የሰብአዊ መብት ጠበቃ ድርጂት (Human Rights Watch) በቅርቡ ባወጣው “Journalism is not a crime: violations of media freedom in Ethiopia, January 22, 2015, እንዲህ ይላል “የኢትዮጵያ መንግሥት በነጻነት (ከመንግሥት ቁጥጥር ውጭ) የሚንቀሳቀሰውን የመገናኛ ብዙሃን ፍጹም በሆነና በረቀቀ መንገድ አውድሞታል። ስለሆነም የፖለቲካና የመናገር፤ የመጻፍና የማሳተም ነጻነት ምህዳር (ምድር) ጨለማ ሆኗል።” ይኼ ሰርዓት ወለድ ውድመት “የመጣው ከመጭው ምርጫ በፊት ነው። ባለፈው ዓመት ብቻ ስድስት በግል ባለቤትነት ይካሄዱ የነበሩ ማተሚያዎችና የሚያበረክቷቸው ጽሁፎች ተዘግተዋል። ገዢው ፓርቲ እየተከታተለና እያስፈራራ አላሰራቸው ስላለ። ሃያ ሁለት ጋዜጠኞች፤ ብሎገሮች (የኢንተርኔት ጋዜጠኞች) እና አሳታሚዎች በወንጀለኛነት ተከሰዋል። ከሰላሳ በላይ የሚሆኑ ጋዜጠኞች ከመያዛቸውና ከመታሰራቸው በፊት ከሃገር ወጥተዋል።” ይሕ ተቋም ከዚህ ድምዳሜ ላይ የደረሰው በብዙ ማስረጃ ነው። ከ May 2013 እስከ December 2014 ባለው ጊዜ ውስጥ ሰባ የሚንቀሳቀሱና በስደት ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞችን አነጋግሯል። አስራ ዘጠኝ ጋዜጠኞች እንደታሰሩ፤ ስድሳዎቹ እንደተሰደዱ አረጋግጧል። ይኼን ማስረጃ በመጠቀም በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከኢራን ጋር “ከፍተኛውን የጋዜጠኞች እስር ቤት መሆን ዝና አስመክራለች” ይላል። በነገራችን ላይ፤ ኢትዮጵያ የጋዤጠኞች ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ተወዳዳሪዎችም እስር ቤት ናት። የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቢያንስ አራት መቶ የፖለቲካ እስረኞች እንዳሉ ተቀብሏል። ቁጥሩ ከዚህ በላይ መሆኑን አምኔስቲ ኢንተርናሺናል ባወጣው ዘገባ ተመልክተናል፤ ለምሳሌ አምስት ሺህ የኦሮሞ ብሄረሰብ አባላት መታሰራቸውን። በየጎራው የታሰሩት የፖለቲካ እስረኞች ከስሌቱ መግባት አለባቸው።
ከመንግሥት ቁጥጥር የሆነ (ነጻ) ሜዲያ የሚባለው ለሰብአዊ መብቶች መከበር፤ ለነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ሂደት ወሳኝ ነው። ያልተበረዘ፤ ያልተደለዘ ዜና ለሕዝብ ተሳትፎ ቁልፍ ነው። በመንግሥት ቁጥጥር የተያዘው መገናኛ ብዙሃን ለሕዝብ የሚያቀርበው ዜና የገዢውን ፓርቲ ታላቅነት፤ የልማትን አስደናቂነትና ህይወት ለዋጭነት፤ የተቃዋሚውን ኃይል ደካማነት፤ የነጻ ጋዤጠኞችን አክራሪነት፤ ሽብር ቀስቃሽነት፤ ፀረ- ሕገ መንግሥትነት ወዘተ ነው። ልክ እንደ ምርጫ ቦርዱ የገዢው ፓርቲ አገልጋይ ነው። የመንግሥት ጋዜጠኛ እድገትና የደሞዝ ጭማሬ ከፈለገ ለህወሓት ታዛዢ መሆን ግዴታው ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ አስተምሮና አሰልጥኖ ሊያገለግሉት የሚችሉ ጋዜጠኛች በእስር ቤት ወይንም በስደት እንዲኖሩ ከተገደዱ የህወሓት የጨለማ አገዛዝ ይቀጥላል ማለት ነው። የሂውማን ራይትስ ዋች ምክትል ሃላፊ እንዲህ በማለት እውነቱን አስቀምጣዋለች። “የኢትዮጵያ ከመንግሥት ቁጥጥር ውጭ የሆነ መገናኛ ለመጭው ምርጫ ቁልፍ የሆነ ሚና ሊጫወት ይችል ነበር፤ ሆኖም የኢትዮጵያ መንግሥት መንግሥትን የማይደግፉ ጋዜጠኞች አንድ ሃተታ ቢያቀርቡ የሚከተለው ውጤት እስር ቤት እንደሚሆን ያውቃሉ።” ተወዳዳሪ ፓርቲዎችም የገጠማቸው ችግር ተመሳሳይ ነው። እንደ ልብ ለመንቀሳቀስ፤ ለመሰብሰብ፤ ሕዝብን ለመቀስቀስ አለመቻል። “ነጻ የሆነ ድምፅን በፀረ-ሽብርተኛነትና ሌላ የተፈጠረ ምክንያት ማፈን ኢትዮጵያ የነጻ ሃሳብ ሲኦል እንድትሆን አድርጓታል። Ethiopia’s government has systematically assaulted the country’s independent voices, treating the media as a threat rather than as a valued source of information and analysis….Muzzling independent voices through trumped-up criminal charges and harassment is making Ethiopia one of the world’s biggest jailers of journalists.” በተመሳሳይ፤ የህወሓት መንግሥት ተወዳዳሪ የፖለቲካ መሪዎችንና አባላትን እያሳደደ፤ የፈጠራ ማስረጃ እየተጠቀመ አስሯል፤ እንዲሰደዱ አድርጓል። የሚፈልገው ግልፅ ነው። ለኢትዮጵያና ለመላው ሕዝቧ ተቆርቋሪ፤ ተሟጋች፤ ታጋይ እንዳይኖር ለማድረግ። የኢትዮጵያዊያን በገፍ መሰደድ ለህወሓት በገንዘብ የማይገዛው ክፍተት ፈጥሮለታል። ተቆርቋሪ ከሌለ አምባገነናዊነት፤ ድርጂታዊ ምዝበራ ወዘተ ይቀጥላል። የሩቅ አቤቱታ ብቻውን አገርን አይታደግም። ስደተኛው ቢያንስ ለሃገሩ፤ ለወገኑ፤ ለክብሩና ለህሊናው ሲል አገር ቤት የሚንቀሳቀሱትን፤ የታሰሩትን፤ የተሰደዱትን ወገኖቹን መርዳት አለበት፤ ቢያንስ በውጭ ድምፁን ማሰማት አለበት፤ አለበለዚያ የታሪክ ተጠያቂ መሆኑ የማይቀር ነው፤ በሃገሩ ሕዝብ መናቁ የማይቀር ነው፤ “ለራሱ ጥቅም ቋሚ” መባሉ የማይቀር ነው። አገሪቱ ከፈረሰች የሰራውን ቤት ሊጠቀምበት አይችልም። አደጋው እስከዚህ ደርሷል።
የህወሓት መንግሥት የማስፈራሪይ ዱላው ብዙ ነው። ለምሳሌ፤ ስራ ለማግኘት፤ የመሬት ምሪት ፈቃድ ለማግኘት ወዘተ የፈለገ ግለሰብ ለህወሓት ታማኝ መሆን ግዴታው። በአንዳንድ ታዛቢዎች አነጋገር፤ የግል ጥቅምን ለማስተናገድ “ወያኔ መሆን” አስፈላጊ ነው፤ ራስን ለጥቅም መለወጥ ማለት ነው። “ወያኔ ያልሆነ ወይንም የወያኔን ዓላማ ያልተቀበለ በመንግሥት መስሪያ ቤት ሊቀጠር አይችልም” የሚሉ ብዙ ናቸው። “አልሆንም፤ ከጥቅሜ ነጻነቴን፤ ክብሬን፤ ህሊናየን፤ አገሬን፤ ወገኔን እመርጣለሁ” ያሉ ግለሰቦች በሰላም ለመኖር አይችሉም።” ጋዜጠኞች በተለይ። የሚፅፉት ነገር ህወሓትን የሚገስፅ ከሆነ የጻፉት ይቃጠላል። ህወሓት በአንድ ወቅት ብቻ አርባ ሺህ እትሞችን አቃጥሏል፤ ፀሃፊዎችን በወንጀለኛነት ከሷቸዋል፤ አስሯቸዋል። በጋዜጠኞች የደረሰው ፍዳ በማህበረሰብ ድርጂቶች ላይ ተፈጽሟል። The Charities and Societies Proclamation of 2009 is a prime example of a blunt political instrument that decimated civil society in Ethiopia. የመንግሥት ያልሆኑ አገልግሎት የሚሰጡ የማህበረሰብ ድርጅቶች ተደምስሰዋል። በምትካቸው ለህወሓት የሚያገለግሉ ድርጅቶች ተቋቁመዋል። ከላይ በተጠቀሰው ድርጂት አባባል “Unfortunately, what little space there was for independent coverage and political expression and analysis of news and political events has shrunk even further in 2014.” ኢትዮጵያዊያን ልዩ ልዩ ሰላማዊ አማራጮችን ለማስተናገድ ያላቸው እድል ተዘግቷል። ይኼ የህወሓት ጭፍን አፈና ለእድገትና ልማት ማነቆ መሆኑን አሳይቻለሁ። ሂውማን ራይትስ ዋች እንደደመደመው፤ “የኢትዮጵያ መሪዎች ማስተዋል ያለባቸው ህያውና ነጻ የሆነ የመገናኛ ብዙሃን፤ ጎልማሳና ነጻ የሆነ የማህበረሰብ እንቅስቃሴና ተወዳዳሪ የፖለቲካ ድርጅት (ድርጅቶች) ለሃገሪቱ እድገትና ልማት ወሳኝ ናቸው።” የሰብአዊ መብቶች መከበር የፖለቲካ ስልጣን ከመካፈል በላይ ነው፤ ለእድገትና ልማት፤ ለሳልማ እርጋታ፤ አብሮ ለመኖርና አብሮ ለማደግ ወሳኝ ነው።
ምን ይደረግ?
ሒውማን ራይትስ ዋች የሰብአዊ መብቶች መታፈን አደጋ በትንተና ብቻ አልተወም፤ ለውጦችን ሰንዝሯል፤
የህወሓት መንግሥት የተጠየቀው
1. በጋዜጠኞች፤ የኢንተርኔት ፀሃፊዎች (ብሎገርስ) ላይ የቀረበው ክስ ይነሳ፤ የታሰሩት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ይፈቱ፤
2. የፀረ-ሽብርተኛው ሕግ ይወገድ፤ የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት ይከበር፤ ይኼን የሚያግቡ መመሪያዎች ይነሱ፤
3. የወንጀለናነት አንቀፅ ስድስት መቶ አስራ ሶስት፤ በተለይ፤ ማዋረድ (ዲፌሜሽን) የሚለው አከራካሪ ሕግ ይነሳ፤
4. መንግሥት በመገናኛ ብዙሃን–ሬዲዮ፤ ቴሌቪዢን፤ ማተሚያ ቤት–ያለው ድርሻ ይቀነስ፤
10
5. የጋዜጣ፤ የሬዲዮ፤ የህትመትና ሌሎች ስርጪቶች ደንቦች ከፖለቲካ ቁጥጥር ውጭ ይሁኑ፤ 6. የኢትዮጵያ ዜና ማስራጫ ድርጅት አመራር ይለወጥ፤ ነጻ ብሄራዊ አገልግሎት ይስጥ፤
7. ገዢው ፓርቲ በነጻ የአገር ውስጥና የውጭ ጋዜጠኞች እንቅስቃሴ ላይ የሚያደርገውን መከታተል፤ አፈና ያቁም፤
8. መንግሥት በድህረ ገጾች፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ ጋዤጠኞች፤ ብሎገሮች ላይ የሚያደርገውን አፈና ያቁም፤ እንዳይደገም ለኢትዮጵያዊያንና ለዓለም ሕዝብ ቃል ይግባ፤
9. በውጭ ሬዲዮ፤ ቴሌቪዢንና ሌሎች መገናኛ ብዙሃን ላይ የሚደረገው ገደባ ይቁም፤ መንግሥት ይኼን እንዳያደርግ ቃል ይግባ
10. መንግሥት እስካሁን እምቢ ያለውን የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ካውንስል ልዩ ፀሃፊ ወይንም ራፖርተር ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጣ ይጋብዝ፤ የመብቶችን ጉዳይ በሚመለከት እንደልቡ እንዲንቀሳቀስ ቃል ይግባ። ዘገባውን በይፋ ያውጣ።
ለጋስ ድርጅቶች፤ ተቋማትና መንግሥታት፤ የአውሮፓ የጋራ ማህበርና አሜሪካ
1. በይፋና በግል የታሰሩ ጋዜጠኞች፤ ብሎገሮችና የፖለቲካ ተቃዋሚ እስረኞች እንዲፈቱ መወትወት፤
2. የፖለቲካ ፍርድ አሰጣጥን፤ ሂደትን በቅርብ መከታተል፤ የዓለም ሕግ እንዳይጣስ ማሳሰብ፤
3. እስር ቤቶች ለታዛቢዎች ክፍት እንዲሆኑ ማሳሰብ፤ መከታተል፤ ተግባራዊ እንዲሆኑ ጫና ማድረግ፤
4. በይፋ ሆነ በግል ለመንግሥት ባለስልጣናት የመናገርና ሌሎች መብቶች መታፈን ለልማት፤ ለሰላም፤ ለደህንነት፤ ለእርጋታ ማነቆ መሆናችውን በግልፅ መናገር፤
5. ከመንግሥት ቁጥጥር ውጭ ለሆኑ መገናኛ ብዙሃን፤ የማህበረሰብ ድርጅቶች የአቅም ግንባታ ድጋፍ መስጠት፤
6. ከመንግሥት ቁጥጥጥር ውጭ የሆኑ ጋዜጦች፤ መፃህፍት፤ የማሳተሚያ ተቋሞችን የመጠቀም መብታቸው እንዲከበር ጫና ማድረግ።
ለትንተናውና ለቀረቡት የለውጥ ሃሳቦች የረዱ ሂደቶች፤ ትንተናዎች
1. የመገናኛ ብዙሃኑን መስክ ወይንም ሜዳ መፈተሽ፤
2. ገዢው ፓርቲ በሚዲያው ላይ ያደረገውን አፈናና ማፈራረስ መመርመር፤
3. ከህግ ውጭ ማሳደድ፤ መክሠስ፤ መደብደብ፤ ማሰር እንዴት እንደሚካሄድ ማስረጃ መሰብሰብ፤
4. መረጃ የሚሰጡ ግለሰቦችን መሰብሰብ፤ ማነጋገር፤ ሰላዮች ለፖሊስ፤ ለደህንነት የሚሰጡት የፈጠራ መረጃ እንዴት እንደሚሰበሰብ መፈተሽ፤ ማመሳከር፤
5. የተቃዋሚ ፓርቲዎች የህወሓት አፈ ቀላጤ ናችው የሚሏቸውን እንዴት እንደሚያስፈራሩ፤ ለምን እንደሚያስፈራሩ መገምገም፤
6. የመገናኛ ብዙሃን ህጎች፤ ደንቦችና መመሪያዎች ምን ያህል የፖለቲካና የጎሰኛነት መሳሪያ እንደሆኑ ማመዛዘን፤
7. ህወሓት ለማስፈራሪያና ለማቫበያ የሚጠቅምባቸውን መሳሪያዎች መመርመር፤ ለምሳሌ፤ አንድ ቃሉን የሰጠ ጋዜጠኛ የፖለቲካውን ማቫበያ እንዲህ ሲል ገልጾታል። የፓርቲው አባል ከሆነክ “የተሻለ ስራና ደሞዝ ይከፈልሃል።” ታማኝነት ለስራ ማለት ነው።
8. የግል መገናኛ ብዙሃንን ገንዘብና ትርፍ መፈተሽ፤ ህወሓት አትራፊ የሆነው ሰው ወይንም ተቋም “ተጨማሪ ቀረጥ መክፈል አለብህ፤ ካልከፈልክ ተቋምህ ይዘጋል” ብሎ ያስፈራራል፤ ካፒታልም ከየት እንዳገኘ ይጠይቃል። ይኼን መፈተሽ።
9. የዜና ምንጮችን የማፈን ዘዴዎችን መመርመር፤ ህወሓት “ማን ከየት ዜና እንዳገኘ ይከታተላል።”
10. ህወሓት ጋዜጠኞች እውነቱን እንዳይፅፉ ራሳቸውን እንዲያግቡ ያስገድዳቸዋል (Self-censosrhip). “If you are a journalist, you censor everything you do. If you don’t, you become a prisoner or flee.”
11. ህወሓት ከውጭ የሚሰራጩ የሬዲዮ፤ የቴሌቪዢንና የድህረገፅ ትንተናዎችና ሃሳቦችን በተከታታይ ያግባል፤ እነዚህ እንዴት እንደሚታገቡ መመርመር፤
12. ህወሓት በሶሻል (ማህበረሰብ) የሚተላለፉ ዜናዎችን፤ ትችቶችን ይከታተላል፤ ክትትሉ በምን ዘዴ እንደሚካሄድ መመርመር፤ ማስረጃ መሰብሰብ፤
13. ጋርዲያን እንዳለው በሃገር ቤትና በውጭ በየዓመቱ ብዙ መቶ ሚሊዮን ዶላር ወይንም በብዙ መቶዎች የሚታሰብ ብር ፈሰስ እያደረገ ስለላ ስለሚያካሂድ ይኼ በሰብአዊ መብቶችን ላይ ያለውን ጫና መመርመር፤ ማስረጃ መሰብሰብ የሚሉ ናቸው።
ለመጨመር የምፈልገው የካናዳ መንግሥትና የአውሮፓ የጋራ ማህበር ለህወሓት መንግሥት ያቀርቧቸውን ከላይ ያልተጠቀሱትን ነው።
1. የፖለቲካ ምህዳሩ በአስቸኳ መከፈት አለበት የሚል፤
2. የፖለቲካ እስረኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ይፈቱ የሚል፤
3. የመንግሥት ሜዲያ ለሁሉም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ይለቀቅ የሚል፤
4. የምርጫ ቦርዱ የገዢው ፓርቲ መሳሪያ መሆኑ አቁሞ በዓለም በተለመደው መንገድ አድሏዊ የሆነ ስራ እንዳይሰራ፤ ሁሉንም ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ያገልግል የሚል፤
5. ፖሊስ፤ መከላከያና ፍርድ ቤቶች በምርጫ ሂደት ጣልቃ ገብተው የፓርቲው አገልጋይ መሆናቸውን እንዲያቆሙ የሚል፤
6. ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ከተካሄደ የአገር ውስጥና የውጭ ታዛቢዎች ያለምንም ገደብ ለመንቀሳቀስ እንዲችሉ የሚል ይገኙበታል።
መደምደሚያ
የኢትዮጵያ ሕዝብ እድለኛ ከሆነ መብቶቹ እንዲከበሩ ከተፈለገ፤ ህወሓት ከላይ የውጭ ታዛቢዎች ያቀረቧቸውን ምክሮች ሰምቶ ለሰብአዊ መብቶች መከበር አስፈላጊነትና ተቀዳሚነት ትኩረት ይሰጥ ነበር። ራሱ የሶቨሪን ቦንድ ፕሮጀክት ለዓለም ገበያ ሲያቀርብ እንዳሳሰበው፤ መጭው ምርጫ ነጻና ፍትሃዊ ካልሆነ ለማንም የማይጠቅም፤ የእርስ በእርስ ግጭት ሊነሳ ይችላል። ይኼን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆነ የዓለም ሕዝብ፤ በተለይ ተደማጭነት ያላቸው አበዳሪ ድርጅቶችና የገዢው ፓርቲ ወዳጅ መንግሥታት በፍጥነት ሊያስቡበት ይገባል። ዛሬ ህወሓት የሚያደርገው ጭካኔ ለሃገሪቱና ለመላው ሕዝቧ በጣም አደገኛ ነው። ለጋስ ድርጅቶችና የምእራብ መንግሥታት፤ በተለይ አሜሪካና እንግሊዝ ለራሳቸው ዘላቂ ጥቅም ሲሉ የኢትዮጵያን ሕዝብ የፍትህ፤ የነጻነት፤ የሕግ የበላይነት፤ የዲሚክራሲ ጥያቄዎች መደገፍ ግዴታቸው ነው። ሂውማን ራይትስ ዋች ለኢትዮጵያ ሕዝብ መብቶች መከበር የተቀደሰና ታሪክ የመዘገው አስተዋፆ አድርጓል። ይኼን እንደ ተራ ጉዳይ ማየት የለባቸውም።
መጭው ምርጫ አራት ወራት ብቻ ቀርቶታል። “ተአምር” ካልመጣ በስተቀር፤ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች (በምርጫ የሚያምኑ የፖለቲካ ድርጅቶች) የደረሰባቸውን አፈና፤ ማሳደድ፤ እስራት ወዘተ ተወጥተው በምርጫው ለመሳተፍ በጣም አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል። ቅድመ ሁኔታዎቹ አመች አይደሉም። አፈናው ከመቸውም በበለጠ ደረጃ በመካሄድ ላይ ነው። ስለሆነም፤ ባለው “ጨለማ” በሆነ የፖለቲካ፤ የመገናኛ ብዙሃን፤ የማህበረሰብና ሌሎች የሰብአዊ መብቶች ፍፁም በሆነ አፈና ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ የማይታሰብ ነው።
ተወዳዳሪ ፓርቲዎች ሌላ ቀርቶ ሕገ መንግሥቱ የሚፈቅደውን የሰላማዊ ሰልፍ መብት ተጠቅመው ለመንቀሳቅስ አልቻሉም። እንዲያውም ሰልፉ ከመካሄዱ በፊት የተቃዋሚ ፓርቲዎች መሪዎችንና አባላትን ማፈን፤ በዱላ መደብደብና ማሰር የባሰ ሆኗል። ህወሓት ተጠላፊ ድርጅቶችን እየፈጠረ የሚያደርገውን ሴራ የኢትዮጵያ ሕዝብ ያውቀዋል። ሆኖም፤ ሕዝቡን ንቆታል ለማለት ያስደፍራል። ይኼ ህብረ ሕዝብ የሆኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ለማዳከምና ለማፍረስ የሚደረግ ሴራ መሆኑ ግልፅ ነው። እነዚህ ተወዳዳሪዎች አገር አቀፍ የሆነ ተደማጭነት ባይኖራቸው ህወሓት የምርጫ ቦርዱን እየተጠቀመ፤ የተቀጥላ ድርጅቶች እየፈጠረና ሰርጎ እየገባ ሊያፈራርሳቸው ባልወሰነም ነበር።
የምርጫ ቦርዱ ዓለም የሚቀበለውን መመሪያ አይከተልም፤ የህወሓት አገልጋይና የተወዳዳሪ/ተቃዋሚ ድርጅቶች አፍራሽ ክንድ ሆኗል። የሚሰራው ህወሓት የሚሰጠውን ፍፃሜ ላይ ማድረስ ነው። ምርጫው ሳይካሄድ እንደዚህ ከሆነ በሰላም የሚደረገው “ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ” ፍጹም ቀልድና ጨዋታ ሆኗል ማለት ነው። ለሃገሪቱ አደገኛ የሚሆነው የሰላሙ አማራጭ ዝግ ከሆነ፤ የመግቢያ ቀዳዳ ለሚፈልጉ ለኢትዮጵያ ጠላት መንግሥታት ክፍተት ይፈጥራል። ዙሮ ዙሮ የሰብአዊ መብቶች መከበር የሚያገለግለው የተቃዋሚውን ኃይልና የኢትዮጵያን ሕዝብ ብቻ አይደለም። ህወሓት/ኢህአዴግን ጭምር ነው።
January 26, 2015