January 7, 2015
በህወሓት ሙሉ ቁጥጥር ስር የሚገኘው የፌደራል ፓሊስ በእሁድ ታህሣሥ 28 ቀን 2007 ዓ.ም. የቴሌቪዥን ፕሮግራሙ በግፍ እስር ላይ የሚገኘውን የግንቦት 7 ዋና ፀሐፊን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን አቅርቦት ነበር። ይህ የ10 ደቂቃዎች ምስል ለቁጥር በሚያታክት ብዛት ተቆራርጦ የተቀጣጠለ በመሆኑ አቶ አንዳርጋቸው ምን ተጠይቆ ምን እንደመለሰ ማወቅ አይቻልም። ስለሆነም በንግግሩ ይዘት ላይ አስተያየት መስጠት ይናገረው አይናገረው በአልታወቀ ጉዳይ ማብራሪያ መስጠት ይሆናል። ስለዚህም፣ በንግግሩ ይዘት ላይ ጊዜ ከማጥፋት ህወሓት አንዳርጋቸው ጽጌን አሁን ማቅረብ ለምን እንደፈለገ መተንተን ይበልጥ ጠቀሜታ አለው ብሎ ግንቦት 7 ያምናል።
አሁን ህወሓት በውስጥም በውጭም ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ የገባበት ጊዜ ነው፤ በራሱ በድርጅቱ ውስጥም ሰላም የለም። ህወሓት የትግራይ ክልል ሙሉ በሙሉ በቁጥጥሩ ስር እንደሆነ አድርጎ በመቁጠር መላዋን ኢትዮጵያን ለመዝረፍና ለማጥቃት እንደ መንደርደሪያ፤ በሌላኛው የኢትዮጵያ ክፍል ተቃውሞ ሲበዛበት ደግሞ እንደ መደበቂያ ዋሻ ሲጠቀምበት የነበረው ጊዜ አብቅቶ የትግራይ ሕዝብ በህወሓት ላይ ማመጹ በግልጽ በተግባር እየታየ ነው። በርካታ የትግራይ ልጆች በህወሓት ላይ ነፍጥ አንስተዋል፤ ከፊሎቹ ደግሞ በሰላማዊ ትግል ህወሓትን ማስወገድ ይቻላል ብለው በክልላቸውም ከክልላቸውም ውጭ ከህወሓት ጋር ፍልሚያ ገጥመዋል። ህወሓት መሠረቴ ነው ከሚለው የትግራይ ክልል ፈጽሞ ሊነቀል የሚችል መሆኑ ግልጽ ምልክቶች እየታዩ ነው። የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ትህዴን) ከትግራይና ከተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያገናኘው የአማርኛና የትግርኛ የቴሌቪዥን ፕሮግራም መጀመሩ የህወሓት ሹማምንትን ናላ ያዞረ እርምጃ ሆኗል።
የህወሓት ሌላው መተማመኛው የጦር ሠራዊቱ ነበር። ህወሓት፣ የኢትዮጵያን መከላከያ ጦር ሠራዊት ዘረኛ በሆነ መንገድ አደራጅቶ፤ ከፍተኛ አመራሩን በታማኝ አባላቱ ሞልቶ ተደላድሎ የተቀመጠ መስሎ ታይቶ ነበር። አሁን ግን ይህም ምስል አሳሳች እንደሆነ ግልጽ እየሆነ መጥቷል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት የኢትዮጵያ ጠላት የሆነውን ህወሓትን የማገልገል ፍላጎት የሌላቸው መሆኑን፤ እንዲያውም ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን በመቆም የህወሓትን ውድቀት ለማፋጠን ያላቸውን ጉጉት በግልጽ እያሳዩ ነው። አየር ኃይል ውስጥ ያለው ተቃውሞ ገሀድ የወጣ ዜና ሆኗል። እንደ አየር ኃይል ገሀድ የወጣ ዜና አይሁን እንጂ በሌሎችም የሠራዊቱ ክንፎች ያለው አመጽ ተመሳሳይ የጡዘት ደረጃ ላይ ደርሷል።
ብአዴን እና ኦህዴድ ውስጥ ለአገራቸው ለኢትዮጵያ፣ እንወክለዋለን ለሚሉት ሕዝብ እና ለራሳቸው ክብር ያላቸው አባላት ብቅ ብቅ እያሉ ነው። ብአዴንንና ኦህዴድ እንደ ድሮ ፍጽም ታማኝ አገልጋዮች የመሆናቸው ጊዜ እያበቃ ነው። ደኢህዴንም ቢሆን ሙሉ በሙሉ የሚታመን አይደለም። ጊዜው ለህወሓት እጅግ የመክፋቱ ምልክት ደግሞ እራሱ ህወሓት ውስጥም ስምምነት የሌለ መሆኑ ነው። ህወሓት ይይዘው ይጨብጠው ጠፍቶታል።
ለዓመታት የዘለቀው የሙስሊም ወገኖቻችን ተቃውሞ እረፍት ነስቶት እያለ በባህርዳር የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ወገኖቻችን ተቃውሞ ተጨመረበት። የአምቦውን ተቃውሞ አዳፈንኩ ሲል የጎንደር ተቀሰቀሰበት። ለጉራና ለሀብት ዘረፋ ሲል ያስጀመረው የአባይ ግድብ፣ ጥበቃው ብቻ እንኳን ፋታ የሚነሳ ሥራ ሆነበት። ጋምቤላ፣ አፋርና፣ ሶማሊ የግጭት ቀጠናዎች ከሆኑ ዓመታት አስቆጠሩ።
ከላይ የተዘረዘሩት ጉምጉምታዎች፣ ተቃውሞዎችና አመጾች ተቀናጅተው የመጡ ዕለት መድረሻ እንደሚያጣ የተገነዘበው ህወሓት ትኩረት ማስቀየሻ መፈለጉ ግድ ነበር። በግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ እምነት በአሁኑ ሰዓት የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ወደ ሚዲያ መቅረብ ምክንያቱ ይህ ነው። አንዳርጋቸውን ወደሚዲያ በማቅረብ ትኩረትን የማስቀየስ ስትራቴጂ!
የፊልሙ ማጀቢያዎች የነበሩት የሂውማን ራይትስ ዎች ሪፓርት፣ ስለእንግሊዝ ጋዜጣ የተነገረው፣ አሜሪካ ስለምትፈጽመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተዘከረው፣ ወዘተ … ወዘተ የሚያመላክቱት አንድ አቢይ ሀቅ አለ። ይህም ኢትዮጵያዊያን ፀሐይና ብርድ ሳይበግራቸው “እኔ አንዳርጋቸው ጽጌ ነኝ” እያሉ በእንግሊዝ መንግሥት የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት፣ በእንግሊዝ ኤምባሲዎች እና በአውሮፓ ኅብረት ሲያደርጓቸው የቆዩ ተቃውሞዎች ውጤታማ መሆናቸው ነው። በውጭ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን የፈጠሩት ጫና ወያኔን ወደ ተከላካይነት አውርዶት “እኔ ንፁህ፣ አሜሪካ ርኩስ” እንዲል አድርጎታል። ወያኔ፣ ስለንፅህና ምስክርነትት ይሰጥልኛል ብሎ ተስፋ ያደረገው ደግሞ ራሱ ነፃነቱን ገፎ እስረኛው ያደረገው ሰው መሆኑ ጥረቱ እንደምን ውል አልባ እንደሆነበት ያሳያል። ንፅህናን ነፃ ባልሆነ ሰው ማስመስከር ምን የሚሉት ፈሊጥ ነው? ይህ ክስተት፣ የኢትዮጵያዊያን ዘርፈ ብዙ ተቃውሞ የወያኔን የመከላከል አቅም ማዳከሙን በግልጽ ያሳያል። ይህ ለኢትዮጵያዊያን ትልቅ ብሥራት ነው።
ከላይ የተዘረዘሩት ምክንያቶች ህወሓት አንዳርጋቸውን ወደሚዲያ ለማቅረብ ምክንያት ይሁኑ እንጂ የአንዳርጋቸው ለሶስተኛ ጊዜ በወያኔ ቴሌቬዥን መታየት በኢትዮጵያዊያን ላይ የፈጠረው ስሜት ህወሓት ከጠበቀው ፈጽሞ የተለየ ነው።
ኢትዮጵያዊያን አንዳርጋቸውን ሲያዩ የሚታያቸው ጽናት፣ አርበኝነትና አልበገር ባይነት ነው። የአንዳርጋቸው ምስል በታየ ቁጥር ኢትዮጵያዊያን ፀጉራቸው ይቆማል፤ ደማቸው ይፈላል። ወያኔዎች አንዳርጋቸውን የፈለጉትን ቢያናግሩት ችግር የለም። ለጊዜው በእጃቸው ውስጥ ስለሆነ ያላለውን ያለ ሊያስመስሉ እንደሚችሉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ያውቃል። ወደፊት ደግሞ ሊናገር ያልፈለገውን ያናግሩት ይሆናል። ይህ ሁሉ የሚያመጣው ለውጥ የለም። አንዳርጋቸው ስለወያኔ ምንነትና ማንነት ማንም ሳያስገድደዉ በነፃነት አገር ዉስጥ በግልጽ ተናግሯል፣ አሁንም ወያኔዎች እራሳቸዉ በሰሩት ፊልም ዉስጥ እነሱ በማይገባቸው መንገድ ለኢትዮጵያን ሕዝብ ተናግሯል። እንኳንስ እነሱ እሱም ራሱ በማይገባው መንገድ አንዳርጋቸው ኢትዮጵያዊያን ልብ ውስጥ ገብቷል። አንዳርጋቸውን ስናይ በህወሓት ፋሽስታዊ መዳፍ ውስጥ የወደቁብንን ጀግኖቻችንን ሁሉ ያስታውሰናል። በአስር ሺዎች ይቆጠራሉ። የአንዳርጋቸው ምስል ለግላጋ ወጣቶች፣ በሳል አዛውንት፣ ምርጥ ወንድሞችና እህቶች በወያኔ እስር ቤቶች ፍዳቸውን እያዩ መሆኑን ያስታውሰናል። ምስሉ ብቻውን ያናግረናል፣ ያነቃናል፣ ያነሳሳናል!!!
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ አንዳርጋቸው ጽጌን፣ በርካታ ጀግኖቻችንን፣እራሳችንንና አገራችንን ከወያኔ እስር ነፃ ለማውጣት ክንዳችንን እናበርታ፤ ሁላችንም “እኔም አንዳርጋቸው ጽጌ ነን” እንበል፤ ሁላችንም አንዳርጋቸው ጽጌን እንሁን ይላል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
Keine Kommentare:
Kommentar veröffentlichen