January 13, 2015
በኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባርና የግንቦት 7፣ ለፍትህ፣ ዴሞክራሲና የነጻነት፣ ንቅናቄ መሀል የተደረገውን ውህደት በተመለከተ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ፣
በዛሬው ዕለት፣ ጥር 2 ቀን 2007 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባርና የግንቦት 7፣ ለፍትህ ለዴሞክራሲና የነጻነት፣ ንቅናቄ፣ ድርጅቶች፣ ተዋህደን “አርበኞች ግንቦት 7፣ ለአንድነትና ዴሞክራሲ፣ ንቅናቄ”፣ በሚባል ሥም መጠራት መጀመራችንን ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ስናበስር፣ እጅግ ከፍተኛ ደስታ ይሰማናል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ባለፉት በርካታ አስርተ አመታት፣ለፍትህ፣ ለእኩልነት፣ ለነጻነት፣ መብትና አንድነት፣ ከፍተኛ ትግል ሲያካሂድ ቆይቷል። በአደረገውም ትግል እጅግ ከፍተኛ መስዕዋትነት ከፍሏል። ለከፈለው ከፍተኛ ዋጋ የሚመጥን ግን ምንም ዓይነት ውጤት አላገኘም። እንዲያውም ከጊዜ ወደ ጊዜ የመብት ረገጣው፣ አድሎው፣ ማስፈራራቱና ማዋከቡ ተጠናክረው መቀጠል ብቻ ሳይሆን፣ ሀገራችን ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ልትቀጥል የማያስችል ከፍተኛ የመበታተን አደጋ አንጃቦባት ትገኛለች ።
በሀገራችን ላይ ላንጃበበው ከፍተኛ የመበታተን አደጋ ምክንያት የሆነው በሥልጣን ላይ ያለው የወያኔ የአምባገነን ቡድን ነው። ይህ ዘረኛ አምባገነን ቡድን በሀገራችን ታሪክ በሥልጣን ላይ ከመጡ የገዥ ሃይሎች ጋር ሲወዳደር ሀገርን ለከፍተኛ አደጋ በማጋለጥ፣ ሕዝቧን በማወረድ፣ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ዕኩይ ሃይል መሆኑን በበርካታ ተግባራቶቹ ያለ ምንም ጥርጣሬ አረጋግጧል።
በሌላ በኩል ለቀድሞቹም ሆነ ለዛሬው ዘረኛው የወያኔ አምባገነን ገዥ በሕዝብና በሀገር ላይ በደል እየፈጸመ በሥልጣን መቆየት የቻለበት ምክንያት፣ በተቃዋሚነት የሕዝቡን ትግል ለመምራት የተንቀሳቀስን ድርጅቶች፣ የተቋቋምንበት ዓላማ መለያዬት ብቻ ሳይሆን፣ አንድ ዓይነት ዓላማ ያለንም ብንሆን፣ ከድርጅቶቻችን ጠባብ ፍላጎቶችና ስሜቶች ባለፈ፣ የሀገርና የሕዝብን ጉዳይ በማስቀደም በጋራ መሰባሰብና መታገል ስላቃተን ነው። በዚህም ድርጊታችን የራሳችንን ብቻ ሳይሆን የወገናችንንም የመከራ ዘመን እያራዘምን እንገኛለን ።
ይህ ሁኔታ በተለያዩ ተቃዋሚ ድርጅቶች መሀል ከፍተኛ ጥርጣሬና ፍርሀት ከመፍጠሩ የተነሳ በምንም ዓይነት ሁኔታ፣ ተቃዋሚ ድርጅቶች በጋራ በሀገርና በሕዝብ ደረጃ ትርጉም ያለው ስራ መስራት አይችሉም፣ የሚለው አመለካከት የበላይነት እንዲያገኝ አድርጎታል።
በዛሬው ጥር 2 ቀን 2007 ዓ.ም ወደ ውህደት የመጣነው፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባርና የግንቦት 7፣ ለፍትህ፣፡ ለነጻነትና ለዲሞክራሲ ንቅናቄ፣ መዋሃድ መወሰናችንን ፣ ስንገልጽ በተናጠል ከሚደረጉ በጋራ የሚደረጉ የትግል ጥረቶች ውጤታማ ይሆናሉ በሚል ብቻ ሳይሆን፣ የተቃዋሚ ድርጅቶች፣ በምንም ዓይነት ሁኔታ በሀገርና በሕዝብ ደረጃ ትርጉም ያለው ሥራ በጋራ መስራት አይቻሉም የሚለውን፣ አስከፊ ተመክሮና አመለካካት ለመስበርም ነው።
በእኛ እምነት ከትናናሽ ድርጅቶች ዙሪያ ከሚሽከረከሩ ሀሳቦችና ስሜቶች ለመውጣትና ሀገራዊና ሕዝባዊ የሆነው ጉዳይ ለማስቀደም የወሰነ ማንኛውም ድርጅት፣ አርበኞችና ግንቦት7፣ የደረሱበት የውህደት ውሳኔ ወይም በሌሎች በጋራ ሊያሰሩ በሚችሉ ስምምነቶች አብሮ ለመስራት መወሰን የማይችልበት ምንም ምክንያት አይታየንም። በወያኔ አድሎ ስርዓት የተንገፈገፈና ትግሉን ለመቀላቀል የቆረጠ ማንኛውም ዜጋ፣ የተገኘውን አጋጣሚ በመጠቀም ትግሉን መቀላቀል ይችላል፣ የኢትዮያ ሕዝብ በአንድነት የተነሳ ቀን ደግሞ፣ የወያኔ ግብዓተ መሬት ይፈጸማል፣ ብለን ከልብ እናምናለን።
ይህም በመሆኑ፣
ለተቃዋሚ ድርጅቶች፣
ዛሬ በአርበኞችና በግንቦት 7፣ የተጀመረው ጉዞ ውጤታማ በመሆን ሀገራዊና ታሪካዊ ትርጉም እንዲኖረው፣ ሌሎችም በተግባር የምትንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ድርጅቶች፣ ወያኔን የማስወገድንና ብሎም ሀገር የማረጋጋቱን ሀላፊነት በጋራ እንድንወጣ የሚያስችል መቀራረብ እንድናደርግ ፣ በውህደት በመሰረትነው፣ በአርበኞች ግንቦት 7፣ ለአንድነትና ዴሞክራሲ፣ ንቅናቄ፣ ሥም፣ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
ለወታደራዊና የፖሊስ ሠራዊት አባላት፣
የወያኔ ዘረኛና አምባገነን ቡድን ዕድሜን ለማሳጠርና ሁላችንንም በእኩልነት የምታስተናግድ ሀገር እንድትኖር ፣ በየቦታው የሚደረገውን ትግል፣ የሰሞኑን ቆራጥ የዓየር ሃይል መኮንንኖች ያሳዩትን ዓርያነት በመከተልና በተገኘው አጋጣሚና ሁኔታ በመጠቀም፣ እንድትቀላቀሉ በውህደቱ ድርጅት፣ በአርበኞች ግንቦት 7፣ ለአንድነትና ዴሞክራሲ፣ ንቅናቄ፣ ሥም፣ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
የተከበርከው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ፣
በረጅም ታሪክህ አይተሄው ለማታውቀው፣ ውርደት፣ ክፋት፣ የመከፋፈልና የመጋጨት አደጋ፣ የመብት እረገጣና አፈና፣ ሀገርና ሕዝብን የማራከስና የመሸጥ፣ ዕኩይ ተግባር፣ የተጠናወተው ወያኔ እና የግብር አበሮቹን፣ ጠራርጎ ለማስወገድ በተጀመረው የጋራ ትግል ውስጥ በቀጥታ እንድትሳተፍም ሆነ በምትችለው ሁሉ እርዳታ እንድታደርግ፣ በዛሬው ጥር 2 ቀን 2007 ዓ.ም የአርበኞችና የግንቦት 7 ውህደት በወለደው፣ በአርበኞች ግንቦት 7፣ ለአንድነትና ዴሞክራሲ፣ ንቅናቄ ሥም፣ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
ድል ለኢዮጵያ ሕዝብ!!!
አርበኞች ግንቦት 7፣ ለአንድነትና ዴሞክራሲ፣ ንቅናቄ፣
ጥር 2 ቀን 2007 ዓ.ም
(የውህደቱን መግለጫ በPDF ለማንበብ ከዚህ ላይ ይጫኑ)
Keine Kommentare:
Kommentar veröffentlichen