አቤንኤዘር ጀምበሩ ((አዲስ አበባ)
ጥር 11/07 ዓም ቦታው አፍንጮ በር፣ ከዩሀንስ፣ ከጊዬርጊስ እና ቀጨኔ መድሃኒያለም ታቦቶች ለከተራ ወደ ጃንሜዳ ሲተሙ የሚጋጠሙበት ቦታ። እልልታው ፣ጭፈራው፣ መዝሙሩ ፣ የሐገር ባህል ልብስ፣ ዱላ ፣ሸንኮራ ፣ጠጠር መጣያ ከሌለው ህዝብ ጋር አብረው ሽኝቱን አድምቀውታል ። ከሁሉ ከሁሉ ድምጽ ግን ከጀርባዬ የቆሙ እናት ጮሆ ውስጥ ድረስ ዘልቆ ተሰማኝ ። መቼ ነው ምልጃ እና አግዚኦታ የሚያልቀው? “አምላኬ ወጣቶችን ጠብቅ፣ ምርጫውን በሰላም አጠናቀው ፣ደም መፍሰስን አንተ በቃ በል ፣ ልጆቻችንን ጠብቅ፣ ተለመነን … ” ፣ ሁሉ አንቅስቃሴ ፣ ሁሉ አዲስ ነገር ፣ ሁሉ አዲስ ሐሳብ የስጋት ምንጭ እንደምን ይሆናል? ስጋትን ወደ መልካም አጋጣሚነት መቀየር አይቻልም?
የቤታችን በር በአማካኝ ሶስት ጊዜ ትንኳኳለች፣ ሰሞኑን አህዟን በእጥፍ አሳድጋ ስድስት ጊዜ መንኳኳት ጀምራለች። ምክንያት ብትሉ ያካባቢያችን ምርጫ አስፈፃሚዎች “ካርድ ወሰዳችሁ፣ ውሰዱ ፣ማን አልወሰደም ፣ መቼ ተወሰደ …” እያሉ ይመጣሉ። ለመምረጥ ካለኝ ጉጉት ሳይሆን መልካም ዜጋነቴን ለማስመስከር ወደ ምርጫ ጣቢያ ሄድኩ ። አሁንም እንደ ጥንቱ ቁራጭ ካርድ ፣ መዝገብ ፣ እስክሪፕቶ የሃገራችን የምርጫ ቴክኖሎጂ? ምርጫው ሲመጣ ደግሞ ባምስት አመት የሚራገፉ ቀዳዳዎች የበዙበት የሸራ ኮሮጆ። በቢሊዬን ህዝብ ያላት ሕንድን ጨምሮ ብዙ የአፍሪካን ሐገራት የምርጫ ቴክኖሎጂን ምርጫን ለማቀላጠፍ ሲጠቀሙ ፣ እኛ ሐገር ስማችንን እንኳን በኮምፒውተር መመዝገብ እንደምን ተሳናቸው?ስራ አጥተው የተቀመጡ ባለ ዲግሪ ወጣቶች ድንጋይ ፍለጡ እየተባለ ፣የትምህርት ደረጃቸው በአብዛኛው ከሁለተኛ ደረጃ ያልዘለሉ የሰፈር ፊትአውራሪዎች ለምን ዋና ተዋንያን ሆኑ? ካርድ ለመውሰድ በሄድኩበት ወቅት በአካባቢያችን የማውቃቸው እናቶች ፣ ፕሮፌሽናል ያልሆኑ የመንግስት ሰራተኞች፣ የቀበሌ ሰራተኞች ተሰብስበዋል (በእርግጥ አንዳንዶቹን አይቼያቸው ስለማላውቅ ማን እንደሆኑ አላውቅም) ። ከመሃላቸው አንዷ ቡና ታፈላለች። በወቅቱ ቦታው ስደርስ የሞቀ ሰላምታ ሰጥተው በፍጥነት አስተናገዱኝ፣ ስወጣ ገለፃ እንደተሰጠብኝ እገምታለሁ ።
የሰሞኗ የአዲሳቤዎች ቀልድ ታዲያ ቀልቤን ስባዋለች። የኢትዮጵያ ፣ የራሺያና የአሜሪካ ልኡካን ስለ ምርጫ ውጤት ልምድ ሲለዋወጡ፣ የራሽያው ልኡክ “እኛ ሐገር ምርጫ በተደረገ በአንድ ቀን ውስጥ ውጤቱ ይታወቃል” አለ። አሜሪካዊው ለጠቅ አድርጎ “ይህማ ዘግይቷል የኛ ከ3–6 ሰአት ውስጥ ” አለ። የኛው ቀበል አድርጎ “የኛ ከሁላችሁም የተሻለ ነው፣ ውጤቱ ከምርጫው በፊት ነው የሚታወቀው ” ብሎ አረፈው (lol)። እናም አሁን ላይ ምርጫው በሰላም ይለቅ ሲባል በቅንፍ ገዥው ፓርቲ ያለግርግር ያሸንፍ እንደማለት ይመስለኛል። እንደሚያሸንፉ የተማመኑት ገዥዎቻችን የቀጣይ አምስት አመት እቅድ መንደፍ ይዘዋል። የተበላ አቁብ ማለት ይህ አይደል ታዲያ?
እናም እላለሁ መንግስት በአንፃራዊ የተሻሉትን ተቃዋሚዎች ተከፋፈሉ እያለ ጊዜ እየገዛባቸው እንደሆነ ይሰማኛል። ችግራቸውም ጊዜው ሲደርስ ይፈታል።ግን በፊት ያልነበረ ክፍፍል ከየት መጣ?፣ የእጩ ማቅረቢያ ጊዜ ለምን ተራዘመ? ከኋላው የፓለቲካ ቁማር መኖሩ አያጠራጥርም። ምርጫው ጥቂት ወራቶች ቀርተውት እንኳን እኛ አዲሳቤዎች በሙሉ አፋችን የተቃዋሚ ፓርቲ ስም አንጠራም (በእርግጥ እነሱም የት እንዳሉ አይታወቅም) ፣ ብንጠራም ግራ ቀኛችንን አይተን ነው። ክርክር የለም፣ የሐሳብ ልውውጥ የለም፣ አማራጭ የለም፣ አዋጪ መንገዶች ዝርዝር የለም። ያለው ስጋት እና የምርጫ ቦርድ ሪፓርቶች። እውን ይሄ የማን ሌጋሲ ይሆን?
Keine Kommentare:
Kommentar veröffentlichen