አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ በምርጫ ቦርድ አማካይነት እየደረሰበት ያለውን በደል ለሕዝብ ለማሰማት ጥር 17 ቀን 2007 ዓም በአዲስ አበባ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ጂንካና ሸዋ ሮቢት የተቃውሞ ሰልፎችን ጠርቶ ነበር። በተለይ በአዲስ አበባው ሰልፍ ላይ የተገኙ ወገኖቻችን ለህወሓት ፍጹም ታማኝ በሆነው የፓሊስ ክፍል ያለርህራሄ መደብደባቸው እና የተቃውሞ ሰልፉም በጉልበት መበተኑ ነፃነትና ፍትህ ናፋቂውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ያሳዘነ ብቻ ሳይሆነ ያስቆጨ ጉዳይ ነው። በመላው ዓለም በሚደረጉ የተቃውሞ ሰልፎች ላይ የተለመደውን ድንጋይ ውርወራ እንኳን ሳይከጅሉ፤ የፓሊሶችን ሰብዓዊ ርህራሄ ለማግኘት “ፓሊስ የኛ ነው” እያሉ እየዘመሩ በፓሊስ ተደበደቡ። ሴቶችና አዛውንት ብቻ ሳይሆን ተላላፊ መንገደኞች እንኳን ከፓሊስ ዱላ አላመለጡም። ከሁሉም በላይ የሚዘገንነው ደግሞ የ 7 ወራት ነብሰ ጡር ሴትም በፓሊስ መመታትዋና ሆዷ መረገጡ ነው። ይህ እኩይ ተግባር የሚፈጥረው ቁጭት በህወሓት ላይ ብቻ አያበቃም። ትዝብቱ ለፓሊስም ተርፏል። ይህ የጭካኔ ተግባር ለፍትህና ለነፃነት በሚደረገው ትግል የሕዝብ አጋር ይሆናል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት የፓሊስ ሠራዊትን የሚያዋርድ ነው። ደካማ እናቶችን፣ አረጋዊያንን፣ ባዶ እጃቸውን ተቃውሞ እያሰሙ ያሉትን ወጣቶችንና ነፍሰጡሮችን በጭካኔ መደብደብ ለራሱና ለሥራው ክብር ለሚሰማው ፓሊስ ውርደት ነው፤ የሞት ሞት ነው። የኢትዮጵያ የፓሊስ ሠራዊት አባላት ተግባራቸው ያሳፍራቸዋል፣ ይቆጫቸዋል፤ ቁጭታቸውንም ይህን ትዕዛዝ በሰጡ አለቆቻቸው ላይ በግልም ሆነ በተደራጀ መንገድ በሚወስዱት እርምጃ እናያለን ብሎ የኢትዮጵያ ሕዝብ ተስፋ ያደርጋል።
የጥር 17 ቀን 2007ቱ ሽብር በአንድ ወቅት የተፈጠረ፤ በአንድነት ፓርቲ ላይ ብቻ ያነጣጠረ፣ የተናጠል ክስተት ሳይሆን ህወሓት ደግሞ ደጋግሞ ሲፈጽመው የነበረ ነው። ከዚህ በፊት በሙስሊም ወገኖቻችን ላይ ፈጽሞታል። የአዲስ አበባ ከተማ ማስተር ፕላንን በተቃወሙ የተለያዩ ዩንቨርስቲዎች ተማሪዎች በተለይም በአምቦ ላይ የብዙዎችን ሕይወት የቀጠፈ ሽብር ነዝቷል። በቅርቡ ደግሞ በሰማያዊ ፓርቲ አባላት ላይ ተመሳሳይ አረመናዊ ድርጊት ፈጽሟል።
አርበኞች ግንቦት 7: ለአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ፣ የህወሓት ታጣቂዎች በወገኖቻችን ላይ ያደረሱትን ድብደባ፣ ህገወጥ እስር፣ እና የተቃውሞ ሰልፍ ክልከላን አጥብቆ ይቃወማል። አርበኞች ግንቦት 7፣ በወገኖቻችን ላይ የደረሰው ህመም ህመሙ፣ ቁስላቸው ቁስሉ ነው።
ባለፉት ሃያ ሶስት ተከታታይ ዓመታት፣ በአምቦ፣ በጅማና በኦሮሚያ የተለያዩ ከተሞችና ገጠሮች፣ በባህዳር፣በጎንደርና በበርካታ የአማራ ከተሞችና ገጠሮች፣ በጋምቤላ፣ በሶማሊ፣ በአፋር፤ በአጠቃላይ በመላው ኢትዮጵያ በየአስፋልቱ፣ በየሜዳውና በየጥሻው በህወሓትና ተላላኪዎቻቸው የፈሰሰው የኢትዮጵያውያን ደም በከንቱ ፈሶ መቅረት የለበትም ብሎ አርበኞች ግንቦት 7 በጽኑ ያምናል። አርበኞች ግንቦት 7 ከሌሎች መሰል ድርጅቶች ጋር በመተባበር የህወሓትን እድሜ በማሳጠር የእናቶቻችን እምባ ሊያብስ ዝግጁ ነው። አርበኞች ግንቦት 7 ኢትዮጵዊያን እንደከብት እየተደበደቡ ወደ ማጎሪያ የሚያጋዙበት እና በጠገቡ ሰላዮችና ፓሊሶች እየታነቁ የሚታረዱበት ጊዜ ማብቃት አለበት ይላል።
የቱን ያህል ቢለመንም ሆነ ቢወገዝ ህወሓት ለነፃ፣ ፍትሃዊና ተዓማኒን ምርጫ ዝግጁ ሊሆን ቀርቶ በምርጫ የሚወዳደሩት ፓርቲዎች እነማን እንደሆኑና እነማን በእጩ ተወዳደሪነት መቅረብ እንዳለባቸው ሳይቀር የሚወስን ዓይን አውጣ አጭበርባሪ ድርጅት ነው። ይህንን ከዚህ በፊት አይተነዋል፤ አሁንም በአንድነትና በመኢአድ ላይ እየተደገመ ነው። ህወሓት፣ በየአምስቱ ዓመታቱ በሚያደርጋቸው የሴራ ምርጫዎች በሚቀጥሉት አርባና ከዚያም በላይ ለሆኑ ዓመታት በሥልጣን ላይ የሚቆይበትን ስልት ቀይሶ የሚንቀሳቀስ፤ ኢትዮጵያን ለብዙ ዓመታት ለመግዛት ማድረግ የሚችለውን ክፋት ሁሉ ከማድረግ የማይመለስ አገር በቀል ቅኝ ገዥ ነው። ህወሓት የዘረጋው ሥርዓት ህገ-አልባነት፣ ፀረ-ሕዝብነት እና አምባገንነት ለማጋለጥ በሚል ርህራሄን በማያውቁ የሥርዓቱ አገልጋዮች ፊት ባዶ እጅ መጋፈጥ የሚፈጥረው የሞራል የበላይነትና የመንፈስ ጀግንነት ባያጠራጥርም የሚያስከፍለው ዋጋ ከሚገኘው ውጤት ጋር ማመዛዘን ግን እጅግ ተገቢ የሆነ የማይታለፍ ሥራ ነው ብሎ አርበኞች ግንቦት 7 ያምናል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ከህወሓት የሴራ ምርጫ ፋይዳ ያለው ውጤት ይገኛል ብሎ አይጠብቅም። ከምርጫው የሚፈልገው ውጤት አንድ ነገር ብቻ ነው፤ እሱም የመንግሥት ለውጥ ነው። ምርጫው በምርጫነቱ ወደ መንግሥት ለውጥ አያደርስም፤ ወደ መንግሥት ለውጥ ወደሚያመራ ሕዝባዊ አብዮት ሊያሸጋግር ግን ይችላል። ይህም ቢሆን የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ በተለይም የሠራዊቱን ዓይነትና አደራጀጀት እግምት ውስጥ ባስገባ ሁኔታ መታቀድ ይኖርበታል።
አርበኞች ግንቦት 7 የራሱን ጥናት አድርጎ ለኛ አገር ተጨባጭ ሁኔታ እና ህወሓትን ለመሰለ ጠላት የሚመጥን የትግል ስልት ሁሉንም የትግል ስልቶች እንደሁኔታው ያዳቀለ – ሁለገብ – መሆን ይኖርበታል ብሎ ወስኖ ለተግባራዊነቱ እየተንቀሳቀሰ ነው። ሁለገብ የትግል ስልት ሕዝባዊ ተቃውሞን፣ ሕዝባዊ እምቢተኝነትንና ሕዝባዊ አመጽን እንደወቅቱ ተጨባጭ ሁኔታ ማፈራረቅና ማደባለቅን ይፈልጋል። ሰላማዊ ትግል በተለይም ሕዝባዊ እምቢተኝነት ሲባል ደግሞ ህወሓት ያወጣቸው አፋኝ ህጎች እያከበሩ የሚደረግ አለመሆኑም የኢትዮጵያ ሕዝብ ይረዳል። ሁለገብ ትግል በተቻለ መጠን የወገን ኃይል ራሱን ፈጽሞ መከላከል በማይችልበት ሁኔታ እንዳይገኝ ለማድረግ ይጥራል። በአርበኞች ግንቦት 7 እምነት ሁለገብ የትግል ስልት ሰፊ ተቀባይነት የሚያገኝበት ወቅት ደርሷል። ከዚህ በፊት “የሰላም በሮች ሲዘጉ የአመጽ በሮች ይከፈታሉ” ተብሎ በአንድ ታዋቂ ኢትዮጵያዊ ታጋይ የተነገረው “የሰላም በሮች ሲዘጉ የሁለገብ ትግል ስልት በሮች ይከፈታሉ” በሚል እንዲሻሻልና በዚህ ወለል ብሎ በተከፈተው በር ሁላችንም እንድንገባ አርበኞች ግንቦት 7 ያሳስባል። በሁለገብ የትግል ስልት በሰላማዊ መንገድ የሚደረጉ የትግል ዓይነቶች አሉ፤ በሌላም መንገድ የሚደረጉ አሉ። ስለሆነም በሁለገብ ትግል እያንዳንዳችን እንደየዝንባሌዓችንና እንደየችሎታዎቻችን አስተዋጽኦ ልናበረክት የምንችልበት ሰፊ እድል ይከፍትልናል።
ስለሆነም፣ በዚህ አጋጣሚ አርበኞች ግንቦት 7፣ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ለጦር ሠራዊትና ፓሊስ አባላት ወገናዊ ጥሪ ያደርጋል።
በህወሓት ዘረኛ አገዛዝ በሚደርስብን ውርደት፣ እንግልት፣ ስደት፣ ሥራ አጥነትና ድህነት የተማረራችሁ እና እኩልነቷ የተረጋገጠ፣ የበለፀገች ኢትዮጵያን ማየት የምትመኙ ሁሉ የሁለገብ የትግል ስልትን አዋጪነት እንድታጤኑ የዚሁ ስልት አካል ሆናችሁ እንድትታገሉ አርበኞች ግንቦት 7 ጥሪ ያደርጋል።
የኢትዮጵያ የጦርና የፓሊስ ሠራዊት አባላት በግል ከሚደርስባችሁ ግፍ በተጨማሪ የገዛ ራሳችሁን ወገኖች መግደላችሁ፣ ማቁሰላችሁ፣ ማድማታችሁና መደብደባችሁ የህሊና እረፍት ሊነሳችሁ ይገባል። ህሊናችሁ እረፍት የሚያገኘው የሥርዓቱ እድሜ ሲያጥር መሆኑን በመገንዘብ ለገዛ ራሳችሁ ክብር፣ ለወገናችሁና ለአገራችሁ ስትሉ ፋሽስቱን ወያኔ ከድታችሁ ከአርበኞች ግንቦት 7 ኃይል ጋር ተቀላቀሉ።
እነዚህን ጥሪዎች ተግባራዊ ካደረግን ወገኖቻችን መሠረታዊ መብቶቻቸውን በመጠየቃቸው በመወደስ ፋንታ በፓሊስ ዱላ ሲደበደቡ የማናይበት ዘመን ይመጣል። ይህ ካልሆነ ግን “ውሀና መብራት አጣን” ብሎ አቤቱታ ማሰማት እንኳን በጥይት የሚያስገድልበት ቀን ይመጣል። ያ ከመሆኑ በፊት እንወስን፤ ራሳችንና አገራችን ከህወሓት ዘረኛ አገዛዝ ነፃ እናውጣ።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
Keine Kommentare:
Kommentar veröffentlichen