ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ
መልካም የጉዞ ፍታት ለካራቱሪ: በኢትዮጵያ የካሩቱሪ አሟሟ አስከሬን ምርመራ
በምዕራብ ኢትዮጵያ በምትገኘው በጋምቤላ ክልል ካሩቱሪ እየተባለ ከሚጠራው ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል የውጭ የግብርና ልማት ድርጅት ጋር የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ
ቡድን ስብስብ ባደረገው ስምምነት መሰረት ሲተገበር የቆየው የመሬት ቅርምት የመድረክ ላይ ተውኔት ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚጠቅም እና በእውነትም ለዕድገት የእራሱን ድርሻ ሊያበረክት የሚችል ቢሆን ኖሮ እጅግ በጣም ጥሩ ነገር ነበር፡፡ ሆኖም ግን በተግባር እየሆነ ያለው ነገር በሸፍጥ እና በመሬት ዘረፋ ላይ ያተኮረ ዕኩይ ምግባር በመሆኑ ለኢትዮጵያ ህዝብ እጅግ በጣም አስከፊ እና ጎጅ በመሆን አስጠያፊ ጥቁር ጠባሳ ጥሎ አልፏል፡፡
ባለፈው ወር “የኢትዮጵያ ሳራማ የረግረግ ቦታ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት/Ethiopian Meadows Plc“፣ “በኢትዮጵያ የጋምቤላ አረንጓዴ ሸለቆ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት/Gambella Green Valley Plc“ እና “በኢትዮጵያ የካሩቱሪ የግብርና ምርት ውጤቶች አምራች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት/Karuturi Agro Products Plc (Ethiopia)“ እየተባሉ የሚጠሩትን የግል የርሻ ንግድ ድርጅቶች አካትቶ በመያዝ ጋምቤላ እየተባለ የሚጠራውን የኢትዮጵያ የግዛት ክልል ለም መሬት በመዝረፍ ሲንቀሳቀስ የቆየው ካሩቱሪ ዓለም አቀፍ የህንድ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት/Karuturi Global, Ltd ምንም ዓይነት የመድረክ ላይ ትወና ሳይደረግና የፕሮፓጋንዳ ጥሩንባ ሳይነፋ በድብቅ እና በሚስጥር የሞቱ መርዶ ይፋ ተደርጓል፡፡
በግብርና ልማት ስራዎች ላይ የተሰማራው ካሩቱሪ እየተባለ የሚጠራው የህንድ የግብርና የንግድ ድርጅት ከመጠን በላይ በተጋነነ መልኩ “በኢትዮጵያ፣ በኬንያ እና በህንድ የጽጌረዳ አበባዎችን የሚያመርት እና ወደ ውጭ የሚልክ ታላቅ ዓለም አቀፍ ድርጀት ነው እየተባለ ይነገርለታል፡፡ እ.ኤ.አ በ2008 ካሩቱሪ በምዕራብ ኢትዮጵያ በጋምቤላ ክልል 300,000 ሄክታር መሬት እጅግ በጣም ርከሽ በሆነ ኪራይ ወሰደ፡፡ የመሬት ኪራዩ ከፍተኛ የሆነ የፕሮፓጋንዳ/ቅስቀሳ ጫጫታ የበዛበት ወይም ደግሞ አስቸጋሪ የሆነ የማሳመኛ የክርክር ጭብጥ የተደረገበት በመሆን ከዓለም ከፍተኛ የሆነ የምግብ እህል አምራች ድርጀት ተብሎ ለካራቱሪ የመሰረት ድንጋዩን በመጣል ታዋቂነቱን አበሰረ፡፡ የካራቱሪ የጽጌረዳ ምርት ግን በተደሰኮረለት መጠን ሳይጓዝ ቀርቶ በመጨረሻ የጋምቤላ ክልል “የአበባ አስከሬን” መሆኑ በይፋ ተረጋገጠ፡፡
እ.ኤ.አ በ2011 የጋርዲያን ጋዜጣ የመጀመሪያ የዓይን መክፈቻ የሆነውን ዘገባውን ባወጣ ጊዜ ጋምቤላ በምዕራብ እንግሊዝ የምትገኘውን ከጥንታዊቷ የዌልስ (የሚተረክለት ንጉስ አርተር እና የካሜሎት ግዛታቸውን የሚያህል መሬት) ግዛት ጋር እኩል የሚሆን የመሬት ስፋት ያለው መሆኑን ይፋ አድርጎ ነበር፡፡ እንግዲህ ካሩቱሪ አብዛኛውን የጋምቤላን ክልል መሬት ለ99 ዓመታት በኪራይ የሚወስደው ከሆነ በትክክለኛ እና እውነታን በተላበሰ መልኩ እንዲሁም ይፋ በሆነ መልኩ የመሬት የባለቤትነት ይዞታን ከማረጋገጥ አንጻር ጋምቤላ “የካሩቱሪ ቅኝ ” ተብላ መሰየም ይኖርባታል በማለት ግልጽ አድርጌ ነበር፡፡
ካሩቱሪ እራሱን ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ህወሀት) እያለ ከሚጠራው ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ጋር የመሬት ነጠቃ እና ቅርምት ስምምነቱን ከፈጸመ በኋላ ወያኔ የካሩቱሪን ስምምነት በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን ለሚያፈስሱ የሁሉም የውጭ መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች ሁሉ ብቸኛ ተምሳሌት አድርጎ በማቅረብ በብቸኝነት በተቆጣጠራቸው የመገናኛ ብዙሀን ሌት ከቀን ፕሮፓጋንዳውን መልቀቅ ጀመረ፡፡ እ.ኤ.አ በ2011 አሁን በህይወት የሌለው የወያኔ መሪ መለስ ዜናዊ የእራሱን ባዶ ስብዕና ከፍ ከፍ በሚያደርግ መልኩ እየተመጻደቀ ኢትዮጵያ በምግብ እህል እራሷን እንደምትችል ታዕምራዊ የሆነ መፍትሄ ማግኘቱን በይፋ ደሰኮረ፡፡ በዘመናችን አስጨናቂ ሆኖ ለዘለቀው ለኤች አይቪ ኤድስ ፈዋሽ መድኃኒት የተገኘለትን ያህል ነበር ቡራ ከረዩ ሲል የከረመው፡፡ ለዘመናት በኢትዮጵያ ምድር ላይ ሲያንዣብብ እና በጥቁር ፈረስ ላይ ሆኖ የምጽዓት ቀንን ሲጠብቅ ለቆየው አሰቃቂ የረኃብ መቅሰፍት የመለስ የሚስጥር መሳሪያ ካሩቱሪ ሆኖ ተገኘ፡፡ መለስ እንዲህ በማለት የውሸት ዲስኩሩን በድፍረት በማሰማት አምባርቆ ነበር፣ “በአምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያ ምንም ዓይነት የምግብ እህል እርዳታ አትፈልግም፡፡“
በአጭሩ እ.ኤ.አ በ1991 መለስ በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠ በኋላ ኢትዮጵያውያን/ት በቀን ሶስት ጊዜ ምግብ የሚበሉ ከሆነ የእርሱ መንግስት ስኬት በዚያ የሚለካ መሆኑን በይፋ ተናግሮ ነበር፡፡ የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት/ኮንግረስ የውጭ እርዳታ አጽዳቂ ኮሚቴ ሰነድ አባሪ 2 እ.ኤ.አ በ2015 ያወጣው ዘገባ እንዲህ ይላል፣ “ኢትዮጵያ በዓመት በነፍስ ወከፍ 471 የአሜሪካ ዶላር ሀገራዊ ገቢ (Gross Domestic Product/GDP) በማግኘት እና የአሜሪካንን የምግብ እና አስቸኳይ እርዳታ ከሚቀበሉ የመጀመሪያዎቹ ሀገሮች አንዷ በመሆን አስከፊ የምግብ ዋስትና እና በምግብ ንጥረ ነገር እጦት ከሚሰቃዩ በዓለም ካሉ ሀገሮች መካከል የመጨረሻዋ ደኃ ሀገር ሆና ትዘልቃለች፡፡“ እንግዲህ እንደዚህ ያለ ሁኔታ በተንሰራፋበት ከባቢ አየር ውስጥ ነው የምግብ እህል እርዳታ አያስፈልጋትም እየተባለ በመለስ ሲደሰኮር የቆየው!
ለካቱሪ ስለተሰጠው ስለ300,000ው የጋምቤላ የመሬት ኪራይ (በእርግጥ ስጦታ ቢባል ይሻል ነበር) ጉዳይ እስከ አሁን ድረስ ምላሽ ያላገኙ በርካታ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ይኸ በተለየ መልኩ የሚያስደንቅ ሊሆን አይችልም፡፡ የድብቅነት ባህሪ የተጠናወተው የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አመራር (በጫካ በነበረበት ጊዜም እንኳ ቢሆን) ምንም ዓይነት ግልጽነት ወይም ደግሞ ተጠያቂነት በሌለው ሁኔታ ሁልጊዜ የጨለማ አካሄድ ድርጊትን ነው ሲከተል የቆየው፡፡ ለወያኔ ሁሉም ነገር የመንግስት ሚስጥር ነው፡፡ መለስ ከሞተ ከሶስት ዓመታት በኋላ እንኳ የሞቱ መንስኤ ምን እንደሆነ እንዳይታወቅ እስከ አሁን ድረስ ከፍተኛ ሚስጥር ሆኖ ተይዞ ይገኛል፡፡ በወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ውስጥ በመንግስት ላይ መንግስት በማቋቋም ሚስጥራዊ ምርምር የሚያደርግ ተቋም ያለበት የዕኩይ ምግባር አራማጅ ድርጅት ነው፡፡ በወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ዋና ስብስብ የዉስጥ አመራር ያሉት በዓለም ዉስጥ ካሉ ውስጥ እጅግ በጣም አጭበርባሪ፣ ሸፍጠኛ፣ ጮሌ አታላይ፣ ተከታታይ ደባ ሰሪ፣ ጠማማ፣ ማቋረጫ የሌለው ክፋት፣ አውዳሚ፣ ሰይጣናዊ፣ ስውር ደባ እና መሬት ላይ በየትኛውም ቦታ የሚገኙ የማካቬሊያን ዓይነት የፖለቲካ አሰራሮች የሚተገብሩ ጭራቆች ናቸው፡፡
ከዋናዎቹ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አባላት ውጭ ያሉ ጥቂት አመራሮች ከካሩቱሪ ጋር የተፈጸመውን ስምምነት ወይም ደግሞ ከሌሎች የመካከለኛው የዓረብ እና የኢስያ ሀገሮች መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች ጋር የተደረጉትን ስምምነቶች ፍንጭ ሊያውቁ ይችሉ ይሆናል፡፡ ይህንን የመሰለ ድብቅነት ከግንዛቤ በመውሰድ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ሁልጊዜ ቢያንስ ሁለት ስምምነቶችን የሚያካሂድ መሆኑ መሰረታዊ ጭብጥ ያለው ይመስላል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አንደኛው ለህዝብ ፍጆታ ሲባል ላይ ላዩን ለሽፋን የሚያደርገው አስመሳይ ስምምነት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ምንም ዓይነት የማስመሰያነት ድርጊት የሌለበት እና ከጠረጴዛ ስር ሰው ሳያየው የተደረገ ስምምነት ነው፡፡ ከዚህ አንጻር መለስ እና የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ድርሻቸውን (ኪስ የሚሞላ ጉርሻቸዉን) አግኝተዋል የሚል ግምት አለኝ፡፡ ስለዚህ ስለሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ልማት፣ ዕድገት፣ ሰላም እና ፍቅር ደንታቸው አይደለም!
እውነት ለመናገር በመጀመሪያ ደረጃ በካሩቱሪ “የመሬት ኪራይ ስምምነት” ላይ የነበረኝ እንቆቅልሽ ጮሌዎቹ አታላዮች፣ አጭበርባሪዎች የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የጓዳ ዱለታ አራማጆች ካሩቱሪ ጋምቤላ ላይ መዋዕለ ንዋዩን እንዲያፈስ አታለውት ይሆን የሚል ጥያቄ ነበረኝ ። ወይም ደግሞ ካሩቱሪ በስግብግብነት ምንም ዓይነት ግንዛቤ ሳይኖረው እና ሳያጣራ ወደ ጋምቤላ ክልል ዘው ብሎ በመግባት ገንዘቡን እና ጊዜውን ያባከነ እርባናየለሽ ፕሮጀክት ነውን? ማንኛውም የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ተወካይ የሆነ ሁሉ ከውጭ መዋዕለ ንዋይ አፍሳሽ ጋር ስለማንኛውም የመሬት ኪራይ ስምምነት ትክከለኛና ሕጋዊ ውል ሊፈጽም ይችላል ብሎ ማመን ይቻላልን?
እውነታው ተፍረጥርጦ ሲታይ ግን የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ እና አሁን በህይወት የሌለው መሪው በአንክሮ ሲፈተሹ የጥንት የግሪክ አስመሳይ እና የቅጥፈት አማልዕክት ተመልሶ የመወለድ ዓይነት ተምሳሌቶች ናቸው፡፡ እነዚህ የዕኩይ ምግባር አራማጆች የአጭበርባሪነት፣ የቀጣፊነት እና የውሸት መረጃ ጌቶች ናቸው፡፡ እንደዚህ ያሉ አይን አውጣ ቀጣፊዎች ናቸው፣ እናም ባለፉት አስርት ዓመታት ጊዜ ውስጥ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ታዕምራዊ እና አስደናቂ በሆነ መልኩ በየዓመቱ በአማካይ በ11 በመቶ የምጣኔ ሀብት ዕድገት አስመዝግቧል በማለት የዓለምን ህዝብ ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ እንዲታለል ያደረጉ ፈጣጣ ቀጣፊዎች ናቸው፡፡ (“የዓለም ባንክ እና የኢትዮጵያ የዕድገት እና ትራንስፎረማሽን ዕቅድ“ በሚል ርዕስ ባቀረብኩት ትችቴ ላይ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ (የቅጥፈት የድንፋታ አጋሮቹ የዓለም ባንክን፣ የዓለም አቀፉን የገንዘብ ድርጅት፣ የዩናይት ስቴትስ አሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት መምሪያ እና የልማት ዕገዛ ቡድን የዓለም አቀፍ የድህነት ወትዋች አቃጣሪዎችን ጨምሮ) ሁሉም ኢትዮጵያ ባለፉት አስርት ዓመታት ውስጥ በየዓመቱ በአማካይ በ11 በመቶ የምጣኔ ሀብት ዕድገት አስመግባለች የሚለው ድፍረት የተሞላበት ነጭ ውሸት፣ ተራ ቅጥፈት እና የቁጥር ጨዋታ (የቁጥር ቅጥፈት) መሆኑን ከጥርጣሬ በላይ በሆነ መልኩ ያረጋገጥኩ መሆኔን ግልጽ አድርጌ ነበር፡፡)
ያም ሆነ ይህ ስለ ኢትዮጵያ መሬት ኪራይ (ስጦታ ቢባል ይሻላል) ስለሚታወቀውም ሆነ ስለማይታወቀው ጉዳይ ካሩቱሪንን ጨምሮ ደሳለኝ ራህማቶ የተባሉት የኢትዮጵያ ልሂቅ እና በገጠር መሬት ላይ እውቅ የሆኑ ተመራማሪ እ.ኤ.አ በ2011 “መሬት ለመዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች፡ መጠነ ሰፊ የመሬት ዝውውር በኢትዮጵያ/LAND TO INVESTORS: Large Scale Land Transfers in Ethiopia“ በሚል ርዕስ ባቀረቡት ትችት በርካታ ጉዳዮችን አንስተው ነበር፡፡ ደሳለኝ እንዲህ የሚል የመከራከሪያ ጭብጥ አቅርበው ነበር፣ “የግብርና እና የገጠር ልማት ሚኒስቴር/Ministry of Agriculture and Rural Development(MoARD) እና የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ባለስልጣን የተባሉት መንግስታዊ ድርጅቶች ከመዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች ጋር የስምምነት ውል የመፈጸም ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል፡፡ የኮንትራት ስምምነት ሰነዶቹ ቀላል እና መዋዕለ ንዋይ በሚፈስስባቸው ፕሮጀክቶች ላይ አስቸጋሪ የሆነ ግዴታን የሚጥሉ አይደሉም፡፡ መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች ምን ዓይነት ሰብሎችን ማምረት እንደሚፈልጉ እና በየትኛው ገበያ ወስደው መሸጥ እንዳለባቸው መዋዕለ ንዋያቸውን በሚያፈስሱበት ሀገር ምንም ዓይነት ጣልቃገብነት ሳይደረግባቸው መፈጸም እንደሚችሉ በሰነዱ ላይ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች ያመረቷቸውን ምርቶች ለአካባቢው ወይም ደግሞ ለሀገር አቀፍ ገበያዎች ማቅረብ እንዳለባቸው የሚያስገድድ ሁኔታ ሳይኖር ይልቁንም ምርቶቹን ለውጭ ሀገር ገበያ ማቅረብ እንዲችሉ የሚያበረታቱ ናቸው፡፡ የሀገሪቱን የምግብ ዋስትና ፍላጎት ከማሳካት አንጻር የተደረገ ስምምነት የለም፡፡ የፕሮጀክት ኃላፊዎች/Project managers ለማህበረሰቡ መሰረታዊ አገልግሎቶችን የማቅረብ ወይም ደግሞ በእነዚህ ዘርፎች ላይ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ የስምምነት ግዴታ የለባቸውም… “
ለፕሮጀክቶቹ የተደረጉ የአካባቢ ስነምህዳር የጉዳት ትንታኔ ጥናቶች/impact assessment አሉ ቢባልም እንኳ የውሸት እና በጣም ጥቂት ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት መሬቱ ሁልጊዜ አደገኛ ለሆነ የአፈር መሸርሸር እና ለአፈር መከላት አደጋዎች በመጋፈጥ ከፍተኛ የሆነ የአካባቢውን የተፈጥሮ ሀብት ውድመት ያስከትላል፡፡ (አጽንኦ ታክሎበታል፡፡)
የካሩቱሪ ከመጠን ያለፉ ጥረቶች፣
በጋምቤላ በ99 ዓመታት በተገባው የመሬት ኪራይ ውል በደሳለኝ ዕይታ መሰረት ካሩቱሪ የሚጠበቁበት ዝርዝር ነገሮች ምንድን ናቸው? የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ሁሉንም ነገር ደብቅ ስለሚያደርግ እውነታዎችን ለማረጋገጥ የምችልባቸው እውነታዎቸ የሉም፡፡ ሆኖም ግን ከብዙ ትንታኔዎች እና ጥናቶች በመነሳት በካሩቱሪ ላይ የዋህነት የተንሰራፈበት፣ ምኞት የተንጸባረቀበት፣ ስግብግብነት የታጨቀበት፣ እና ደባ የተሸረበበት ሁኔታ ለመኖሩ ሊያረጋግጡ የሚችሉ የተጋጥሞ መረጃዎች ተገኝተዋል፡፡
ካሩቱሪ እ.ኤ.አ በ2008 ከጋምቤላ ክልል በርካሽ የኪራይ መጠን መሬት ሲያገኝ ከአምላክ በወርቃማ ሳህን ላይ ምግብ እንደመና የወረደለት ነበር የመሰለው፡፡ በኢትዮጵያ የካሩቱሪ ኃላፊ የሆኑት ካርምጅት ሴክሆን እንዲህ በማለት ገለጻ አድርገው ነበር፣ “መሬቱን አላየንም፡፡ እነርሱ ሰጡን፣ እኛ ደግሞ ተቀበልናቸው፡፡ በእውነት እንደዚህ ነው የሆነው፡፡ መሬቱን የማየት አጋጣሚ እንኳ አላገኘንም (በድል አድራጊነት እንደ ጅብ በመሽከምከም ሳቁን ለቀቀው)፡፡ መሬቱን አደሉን፡፡ የሆነው የኸ ነው፡፡ በጣም ቆንጆ የሆነ ለም መሬት ነው፡፡ በዚያው ላይ ደግሞ ዋጋው ርካሽ ነው፡፡ በእርግጥም በጣም ርካሽ ነው፡፡ በህንድ ውስጥ እንደዚህ ያለ መሬት በፍጹም የለንም፡፡“
የሴክሆን የደስታ ቅዠት የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በኢትዮጵያ እጅግ በጣም ውድ የሆነውን ለም መሬት በጣም ርካሽ በሆነ ዋጋ ለካሩቱሪ የሰጠው መሆኑን እና ካሩቱሪም በተሰጠው መሬት ላይ የፈለገውን ነገር ማድረግ የሚችል የመሆኑን እውነታ ያረጋግጣል፡፡ በዚህ ታላቅ የሆነ የሎተሪ ቲኬት ባለዕድልነትን በመያዝ አንድ ሰው በዚህ መሬት ላይ ምን ማድረግ ነው የሚጠበቅበት?!
ካሩቱሪ በዓይኑ ሳያይ ያገኘውን መሬት ከተቀበለ በኋላ ስለአዋጭነቱ፣ ስለትርፍ ኪሳራው፣ ስለዕዳውና ስለአጠቃላይ ሁኔታው “ተገቢ የሆነ ጥንቃቄ” በተሞላበት ሁኔታ ማሰላሰል መጀመሩን ሊገልጹ የሚችሉ የተገጣጥሞሽ መረጃዎች አሉ፡፡ (“ተገቢ የሆነ ጥንቃቄ” ለሚለው ሀረግ እንግዳ ለሆናችሁ አንባቢዎቼ ሀረጉ አንድ ገዥ ወይም ደግሞ መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ የተዘጋጀ ባለሀብት ስለአንድ የንግድ ባህሪ ስላለው ፕሮጀክቱ ስለሀብት፣ ዕዳ፣ ወዘተ አዋጭነት ጥልቅ እና አሳማኝ በሆነ መልኩ የማሰላሰል የማጥናትና የማሰብ ሂደት ነው፡፡)
እ.ኤ.አ በ2009 ካሩቱሪ ጋምቤላ ክልል በተሰጠው የኪራይ መሬት (ነጻ ስጦታ) ላይ የመሰረተ ልማት የማሻሻያ ስራዎችን መስራት ጀመረ፡፡ ከባሮ ወንዝ (በአካባቢው የአኟክ ኗሪ ማህበረሰቦች ኡፔኖ እየተባለ በሚጠራው ወንዝ) እና ከገባሮቹ ከአልዌሮ እና ጂካዎ ወንዞች ላይ የሚነሱትን የጎርፍ አደጋዎች ለመቀልበስ ካሩቱሪ የጎርፍ መቀልበሻ ቦዮችን (የወንዞቹን የተፈጥሮ የፍሰት አቅጣጫ ለመቀልበስ) እና ሌሎችን የግንባታ ስራዎች ሲገነባ ቆይቷል፡፡ ገና ከመጀመሪያው ጀምሮ የካሩቱሪ የንግድ ስትራቴጅዎች ነገሮችን ሁሉ ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ማየት ጀምሮ ነበር፡፡ ርካሽ የሆኑ የማምረቻ መሳሪያዎችን ከህንድ ወደ ኢትዮጵያ አስገባለሁ የሚል ዕቅድ ነበረው፡፡ ሆኖም ግን የህንድ የማምረቻ መሳሪያዎች በጣም ትልቅ ለሆነ የግብርና የንግድ እርሻ ሊያገለግሉ እንደማይችሉ ወዲያውኑ አስልቶ በማረጋገጥ ውሳኔ አሳለፈ፡፡ እ.ኤ.አ በ2010 ካሩቱሪ በአሜሪካ የግብርና መሳሪያዎች አምራች ከሆነው ጆን ዲሬ ከተባለው ድርጅት ለማስመጣት ትዕዛዝ ሰጠ፡፡
ካሩቱሪ የእራሱን የሰለጠነ የሰው ኃይል ሊያሟላ የሚችል ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ የመረጠ አይመስልም፡፡ ሆኖም ግን እ.ኤ.አ በ2009 የመጨረሻዎቹ ወራት አካባቢ የሰለጠነ የሰው ኃይል እንደ ጋምቤላ ባለ እሩቅ ቦታ ያውም በጣም ጥቂት በሆኑ ዘመናዊ አገልግሎቶች የችግሩን ውስብስብነት የበለጠ የተወሳሰበ ያደርገዋል፡፡ የችግሩ ውስብስብነት ጉዳይ እንዳለ ሆኖ ከህንድ ሀገር ወደ ጋምቤላ የሚመጡት የቴክኒክ ባለሙያዎች እገዛ እንደዚህ ያለ ታላቅ የግብርና የንግድ ፕሮጀክት ድርጅትን ለመምራት ልምድ የለውም፡፡ እንደዚህ ያሉት የዕቀቅድ ኪሳራዎች ወዲያውኑ ሳይውሉ ሳያድሩ ወጭን በማናር፣ የስራ ፕሮግራምን በማዘግየት፣ የስራ ማስኬጃ ወጭዎችን በከፍተኛ ሁኔታ በማናር እና ገቢን በመቀነስ ግልጽ የሆነ ችግርን ይፋ አደረጉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከአካባቢው የሚገኙትን የሰለጠነ ጉልበት የሌላቸውን ሰራተኞች በዘመናዊ የግብርና ቴክኒክ በማሰልጠን ብቁ ለማድረግ በሚደረገው ጥረትም የእራሱ የሆኑ ችግሮች ነበሩበት፡፡ ችግሮች በችግሮች ላይ እየተደራረቡ በካሩቱሪ ላይ የችግሮች ሁሉ ቁልሎች ተፈጠሩ፡፡
እ.ኤ.አ መጋቢት 2011 “ኢትዮጵያ፡ ለሽያጭ የቀረበች ሀገር“ በሚል ርዕስ በወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ እና በካሩቱሪ ድርጅት መካከል ስለተደረገው ስምምነት ለመጀመሪያ ጊዜ ትችት አቅርቤ ነበር፡፡ በቀደምቶቻቸው ተጠብቆ የኖረውን የጋምቤላ ህዝቦችን ለም መሬት የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ከወገኖቻችን ላይ እየነጠቀ ለውጭ ሀገር ዜጋ አሳልፎ መስጠቱን ማመን አቅቶኝ ነበር፡፡ የካሩቱሪ የመሬት ኪራይ ውል መሬቱን ለማግኘት ለተዋዋለው ኩባንያ የዘመናችን ምርጥ ውል ተብሎ ሊጠራ እንደሚችል ምንም ዓይነት ጥያቄ ሊያስነሳ አይችልም፡፡ “በሳምንት በ150 ፓውንድ ወይም ደግሞ 245 የአሜሪካ ዶላር ከ2,500 ካሬ ኪሎ ሜትር በላይ ስፋት ያለው ያልተነካ ድንግል ለም መሬት ይህም ማለት በእንግሊዝ ሀገር ከምትገኘው ከዶርሴት ግዛት ጋር እኩል የሆነ መሬት ለ50 ዓመታት ከግብር ነጻ በሆነ መልኩ ልታገኝ ትችላለህ፡፡ እንግዲህ እንዲህ ባለ ሁኔታ ነው የጋርዲያኑ ጆን ቪዳል አዲስ የተቋቋመውን እኔ ካሩቱሪ ቅኝ ግዛት እያልኩ የምጠራውን ድርጅት ተወካይ በደስታ ተውጦ እንደ ጅብ የሚያሽካካውን ካርምጅት ሴክሆንን በቪዲዮ በመቅረጽ ለዕይታ እንዲበቃ ያደረገው፡፡
ሴክሆን የካሩቱሪን ሊታመን የማይችል ዕድል ማግኘት አስመልክቶ ለቪዳል ገለጻ በሚያደርግበት ጊዜ እራሱን በደስታ ሲቃ ውስጥ ሆኖ የሚናገር መሆኑን የሚያስተውል አይመስልም ነበር፡፡ “መሬቱ ምንም ዓይነት ነገር ሊበቅልበት የማይችል ነገር የለም፡፡ ለመጀመር ያህል 20,000 ሄክታር ለፓልም ዘይት፣ 15,000 ሄክታር ለሸንኮራ አገዳ እና 40,000 ሄክታር ለሩዝ፣ ለምግብ ዘይት እና ለጥጥ ምርት እርሻ የሚውል ይሆናል፡፡ የውኃ ማጠራቀሚያ፣ የጎርፍ መቀልበሻ እና መንገዶችን ለ15,000 በከተማ ለሚኖሩ ህዝቦች የግንባታ ስራ እናካሂዳለን፡፡ ይህ የመጀመሪያው የፕሮጀክት ምዕራፍ ነው፡፡ በሶስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ 300,000 ሄክታር መሬትን በ60,000 ሰራተኞች እናለማለን፡፡ እዚህ ያለውን የሀገሪቱን ህዝብ እንመግባለን…“ (ካሩቱሪ እዚህ ያለውን የሀገሪቱን ህዝብ እንመግባለን ያለውን ባዶ የማጭበርበር ጉራ መሰረት በማድረግ ነው እንግዲህ መለስ በአምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያ በምግብ እህል እራሷን ትችላለች በማለት ያወጀው፡፡ ሰማይ ቅርቡ ተግባር እሩቁ የሆነው ባለራዕይ መሪ!)
እ.ኤ.አ ኦክቶበር 2011 ካሩቱሪ እንዲህ ከሚለው የአሌክሳንደር የግጥም ስንኝ የመጀመሪያውን ምርጥ ትምህርት ወስዷል፡፡
በጠባብ ጎዳና ሞኞች ሲንጋጉበት፣
ከላይ ታች እያሉ ሲንፈላሰሱበት፣
ለጊዚያዊ ጥቅም ሲርመሰመሱበት፣
ሳሩን ተመልክተው አደጋን በመፍራት፤
ይህን እና ያንን አመዛዝነው በውነት፣
አማልዕክት ፈሪዎች ታቀቡ ከድርጊት፡፡
እምነተቢስ እምነት በኃይል ተጀቡኖ፣
ደግ እና ክፉውን ሳይመረምር አምኖ፣
መድረሻውን ሳያይ መነሻውን ይዞ፣
በቁንጽል መረጃ እውነታን ፐውዞ፣
ሰክም ሰከም ሲል አዕምሮው ደንዝዞ፣
ጥቅምን ለማሳደድ በሸፍጥ ተመርኩዞ፣
ሩጫን ተማምኖ ማሰብን ሰርዞ፣
ሁሉም ገደል ገብቶ በቅዠት ተናዞ፣
ሲያነባ ይኖራል እንደ ባህር አዞ፡፡
እ.ኤ.አ በጥ ቅምጥ 2011 ካሩቱሪ የባሮን (ኡፔኖን) ወንዝ እና የገባር ወንዞችን መብረቃዊ ማዕበል በመጋፈጥ የተሰሩትን የጎርፍ መከላከያ ግንባታዎች በጎርፍ በማጥለቅለቅ እና የካሩቱሪን 80 ኪ/ሜ ርዝመት ያለውን የጎርፍ መቀልበሻ እንዳለ እንዲሰጥም በማድረግ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል፡፡ ቅጽበታዊ በሆነ መልኩ ካሩቱሪ 50,000 ሜትሪክ ቶን የሚሆን የበቆሎ ሰብሉን ለምልክት እንኳ ሳያስቀር አደገኛው ጎርፍ ሙጥጥ ጥርግ አድርጎ ዶግ አመድ በማድረግ አውድሞበታል፡፡
የካሩቱሪ ዋና ስራ አስፈጻሚ የሆነው ሳይ ራማክሪሽና ካሩቱሪ የተባለው የእርሱ ኩባንያ 15 ሚሊዮን ዶላር ግምት ያለው ንብረት በጎርፉ ምክንያት እንደወደመበት ይፋ አድርጓል፡፡ በዚያ በደረሰው አሰቃቂ ውድመት ምክንያት የማይሰማ በድን መሆኑን እንዲህ በማለት ገልጾ ነበር፣ “የዚህ ዓይነት የጎርፍ አደጋ እስከ አሁን ድረስ ከዚህ በፊት ተከስቶ አይተን አናውቅም፡፡ ይህ አገር ምድሩን የሚያጥለቀልቅ እብድ የጎርፍ ውኃ ነው፡፡ ድንቄም እብድ ለመሆኑ ማን ነው እብዱ ጃል“!? እብዱ የባሮ ወንዝ ነው ወይስ ካሩቱሪ? ካሩቱሪ ከተፈናጠጠበት ፈረስ ላይ ወርዶ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ውይይት ቢያደርግ ኖሮ አብዛኛው ለማልማት ሲል ተረክቦት የነበረው መሬት ሁሉ በጎርፍ ከሚጥለቀለቀው አካባቢ መሆኑን ይገነዘብ ነበር፡፡ ለዚህም ነው የአካባቢው ማህበረሰብ ያንን መሬት አብዛኛውን ጊዜ ለእንስሳት ግጦሽ እና ለአደን ተግባራት ያውለው የነበረው፡፡ ይህንን ያህል ነው እንግዲህ ስለካሩቱሪ የጥንቃቄ ሂደት፡፡ እ.ኤ.አ በ2011 በጋምቤላ የተከሰተው የጎርፍ መጥለቅለቅ አደጋ ለካሩቱሪ የመጥፎ ዕድል ምልክት ነበር፡፡
እ.ኤ.አ ሚያዝያ 2013 ካሩቱሪ በኬንያ መንግስት በ11 ሚሊዮን ዶላር የግብር ማጭበርበር ክስ ከፍተኛ ቅጣት ተጥሎበታል፡፡ ለአነስተኛ አርሶ አደሮች እርዳታ የሚያደርገው ዴቭሊን ኩዬክ ግሬን/Devlin Kuyek of GRAIN የተባለው ለትርፍ ያልቆመ ድርጅት የሚከተለውን ምልከታ አከናውኗል፣ “የግብር ማጭበርበር ብቻ አይደለም የተፈጸመው፣ ሆኖም ግን ካሩቱሪ የሰብአዊ መብትን በመደፍጠጥ፣ ደካማ የሆነ የጉልበት ስራዎችን በማሰራት፣ የአካባቢ ስነምህዳር ውድመት አደጋን፣ወዘተ…በማስከተል ጨምር ክስ ተመስርቶበታል፡፡ የዓለም ባንክ ቡድን ካሩቱሪ በኢትዮጵያ ለሚያደርገው የልማት እንቅስቃሴ እንኳ የፖለቲካ አለመረጋጋት አደጋ ዋስትና አልሰጠውም፡፡“
እ.ኤ.አ ሰኔ 2013 በጋምቤላ የሚገኘው የካሩቱሪ ፕሮጀክት እጅግ በጣም ከፍተኛ በሆኑ ችግሮች ተተብትቦ የሚገኝ መሆኑ ግልጽ ሆኖ ነበር፡፡ በዚያው ዓመት ካሩቱሪ ከተከራየው ጠቅላላ መሬት ውስጥ 5 በመቶውን ብቻ ነበር ማልማት የቻለው፡፡ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ካሩቱሪ የያዘውን የኪራይ መሬት የይዞታ መጠን እንዲቀንስ አስፈራርቶት ነበር፡፡ ኩባንያው ከፍተኛ የሆነ ዕዳን አጠራቅሟል፣ እናም የመስሪያ ሀብት/ካፒታል የማግኝት ችግር ላይ ወድቆ ነበር፡፡ ታላላቅ መዋለዕለ ንዋይ አፍሳሾች በአስተዳደሩ እና በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ እያደጉ በሚመጡት በፖለቲካው ችግሮች ላይ ከፍተኛ የሆነ የማማረር ችግር ይታያል፡፡ ሌሎች መዋዕለ ንዋያቸውን በጋምቤላ ላይ ለማፍሰስ ቃል ገብተው የነበሩ ባለሀብቶች ወደዚያ በተከሰተው ማጭበርበሪያና ፍልምያ ከህዝብ ጋር ፊታቸውን እንደማያዞሩ ግልጽ አድርገዋል፡፡
ካሩቱሪ የወንጀል ድርጊቶችን ፈጽሟል በሚል በጋምቤላ ባለስልጣኖች ምርመራ ተካሄደበት፡፡ የመሬት ልማት ዕቅዱ እና የካሩቱሪ የእርሻ ማልማት ልምዶች በአካባቢው ስነምህዳር እና የስነህዝብ ሁኔታዎች እንዲሁም በየብስ እና በውኃ አካላት ላይ ግበልጽ የሚታይ ጉዳትን አስከትለዋል፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ በመንደር ምስረታ የተፈናቀሉ ማህበረሰቦች በሰብሎቻቸው ላይ እና በግጦሽ መሬቶቸ ላይ ስለደረሰው ጉዳት በተደጋጋሚ ሲያማርሩ ይደመጣሉ፡፡ የአካባቢው ኗሪዎች የጋራ በሆኑት የግጦሽ መሬቶች ላይ እና ለእንስሶቻቸው በሚውለው ውኃ ውሱንነት ላይ የመረረ ቅሬታ አሰሙ ፡፡ የአካባቢው ኗሪዎች ካሩቱሪ ቃል በገባው የውል ስምምነት መሰረት የማህበረሰብ ዘመናዊ አገልግሎቶችን እንዲያቀርብላቸው እና መልካም ነገሮችን እንዲሰራላቸው እና የአካባቢውም የአኗኗር ባህሎች እንዲከበሩላቸው ጠየቀው ምንም መልስ አላገኙም ።
የጋምቤላ ቀደምት ህዝቦች መኖሪያ የነበረው ገነት በአሁኑ ጊዜ ወደ ገሀነም የቅዠት መኖሪያ በካሩቱሪ አማካኘት ተቀየረ፡፡
በካሩቱሪ ፕሮጀክት ተቀጥረው የነበሩት ጥቂት የሆኑ ሰራተኞች ለስራቸው ተመጣጣንኝ ለሆነ ምንዳ እና ለተሻለ የስራ ሁኔታ ነበር ሲታገሉ የቆዩት፡፡ ካሩቱሪ ለሰራተኞቹ ስለሚከፍለው ምንዳ በሚመለከት ዓለም አቀፍ የመሬት ህብረት/International Land Coalition የተባለ ዓለም አቀፍ ድርጅት ያጠናው ጥናት ዘገባ ውጤት እንዲህ ይላል፣ “በኢትዮጵያ በባኮ እርሻ ልማት (ከጋምቤላ በስተሰሜን ምስራቅ አቅጣጫ በሚገኘው ሌላው የእርሻ ልማት ድርጅት) ተቀጥረው በመስራት ላይ የሚገኙት የቀን ሰራተኞች በቀን 10 የኢትዮጵያ ብር (0.50 የአሜሪካ ሳንቲም ) ይከፈላቸዋል፡፡ ይህም በሀገሪቱ በእንሰት እርሻ ልማት ተቀጥረው የሚሰሩት የቀን ሰራተኞች ከሚያገኙት 20 ብር (1 የአሜሪካ ዶላር ጋር ሲነጻጸር በግማሽ ያነሰ ሆኖ ይገኛል፡፡ የካሩቱሪ ድርጅት የጥበቃ አባሎች መሳሪያ የታጠቁ ከሆነ በወር 300 ብር (15 ዶላር) የሚከፈላቸው ሲሀን መሳሪያ ያልታጠቁ ከሆነ ደግሞ በወር 200 ብር ደመወዝ (10 ዶላር) ይከፈላቸዋል፡፡ ካሩቱሪ ከዚህ በተጨማሪ በጣም አንገብጋቢ በሆኑ የስራ መደቦች ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ የእርሻ ልማት ሰራተኞችን ከህንድ ሀገር በማምጣት ቀጥሮ ሲያሰራ መቆየቱ ተረጋግጧል፡፡
ታላላቆቹ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች እና የአካባቢ ስነምህዳር ጥበቃ ቡድኖች በጋምቤላ በተካሄዱት የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ ወንጀሎች ላይ ምዘና እና ግምገማ madreg jemeru፡፡ እ.ኤ.አ በ2012 ሂዩማን ራይትስ ዎች የተባለው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ‘ሞትን ተቀምጦ መጠበቅ፡ በኢትዮጵያ በጋምቤላ ክልል የግዳጅ የመንደር ምስረታ ፕሮግራም/Waiting Here for Death’ Forced Displacement and Villagization in Ethiopia’s Gambella’ በሚል ርዕስ እንዲህ የሚል ዘገባ አውጥቶ ነበር፣ “በጋምቤላ ክልል ምዕራባዊ ግዛት የመንደር ምስረታ ፕሮግራም በሚል ሰበብ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ቀደምቶቻቸው ይኖሩባቸው ከነበሩበት ቀያቸው በግዳጅ ተፈናቅለዋል፡፡“ እ.ኤ.አ በ2012 ኦክላንድ ኢንስቲትዩት የተባለው ዓለም አቀፍ ድርጅት “በጋምቤላ ክልል በቋሚ ኗሪ ማህበረሰቦች ላይ በመሬት ማልማት ሰበብ የሚደረግ የሰብአዊ መብት ረገጣ ያልተሰሙ ድምጾች/UNHEARD VOICES OF THE HUMAN RIGHTS IMPACT OF LAND INVESTMENT ON INDIGENOUS COMMUNITIES IN GAMBELLA“ በሚል ርዕስ በጋምቤላ ክልል ከመሬት ማልማት እና ከመንደር ሰፈራ ፕሮግራሞች ጋር በተያያዘ መልኩ በሰዎች ላይ ሲፈጸሙ የቆዩትን የሰብአዊ መብት ረገጣዎች አጠቃላይ ሁኔታ አመላክቷል፡፡
እ.ኤ.አ ጥቅምት 2014 የባህላዊ ቅርስ ጥበቃ/Cultural Survival የተባለው ዓለም አቀፍ ድርጅት እንዲህ የሚል ዘገባ አቅርቧል፣ “በኢትዮጵያ በጋምቤላ ክልል የቋሚ ኗሪ ህዝቦች ሞት፣ ንብረትን ማጣት እና ከዚህ አስከፊ የሆነ ችግር ውስጥ ለመውጣት የሚደረግ ዘለቄታዊ ትግል“ በሚል ርዕስ ባወጣው ዘገባ መሰረት “የመንደር ምስረታ ፕሮግራም ከህወሀት በፊትም ችግር የነበረበት ነበር“ በማለት ዘገባውን ግልጽ አድርጓል፡፡ እ.ኤ.አ በ1986 የባህላዊ ቅርስ ጥበቃ/Cultural Survival የተባለው ዓለም አቀፍ ድርጅት በሩብ ዓመቱ ያወጣው ዘገባ እንዲህ የሚል ነበር፣ “የኢትዮጵያ መንግስት 17,553 አባወራዎችን/የቤተሰብ ኃላፊዎችን ከትግራይ በማንሳት እስከዚያ ድረስ ሰፈራ ወዳልተካሄደባቸው የጋምቤላ ክልል ድንግል እና ለም መሬቶች እየወሰደ በማስፈር እና ከዚያ ሌላ እንደዚያ ያለ ቋሚ ማህበረሰቦች የሚኖሩባቸው እንደ አኟክ ያሉ ማህበረሰቦች እንዳልነበሩ መንግስት ምስክርነቱን ሰጥቷል“ ብሎ ነበር፡፡
ካሩቱሪ በጋምቤላ ሲያካሂድ ከነበረው ፕሮጀክቱ ጋር በተያያዘ መልኩ ሁሉንም የሚካሄዱበትን የሰብአዊ መብት ረገጣ ውንጀላዎች አልፈጸምኩም በማለት ሲያስተባብል ቆይቷል፡፡ በእርሱ ፕሮጀክት እና በወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የሰፈራ መንደር ፕሮግራም መካከል ምንም ዓይነት ግኑኘት የለም በማለት ሲያስተባብል ቆይቷል፡፡ ካሩቱሪ ይቀርቡበት የነበሩትን ክሶች ፍጹም መሰረተቢስ እና የምዕራቡ ዓለም ጭፍን የጥላቻ መገለጫዎች ናቸው በማለት ምላሽ ሲሰጥ ቆይቷል፡፡
እ.ኤ.አ ሚያዝያ 2014 የእንግሊዝ ዓለም አቀፍ የልማት መምሪያ እና የዓለም ባንክ በጋምቤላ ህዝቦች ላይ መጠነሰፊ የሆነ ጉዳት ላደረሱ ፕሮጀክቶች የገንዘብ እርዳታ እንዲያደርጉ የህግ ተጠያቂነት ወይም ደግሞ ውስጣዊ ድርጅታዊ ምርመራ መደረግ ተጀመረ፡፡ እ.ኤ.አ መስከረም 24/2012 በተጻፈ ደብዳቤ ስማቸው ያልተጠቀሰ የአኟክ ብሄረሰብ ተወላጅ የሆኑ በጋምቤላ የኢትዮጵያ መሰረታዊ አገልግሎቶች ጥበቃ ፕሮጀክት/Basic Services Project (PBS) በሚል የዓለም ባንክ በሚሰጠው የገንዘብ እርዳታ ህዝቡ በከፍተኛ ደረጃ የጉዳት ሰለባ መሆኑን በመግለጽ ይህንን አስመልክቶ በጉዳዩ ላይ ምርመራ እንዲካሄድ ጥያቄ አቅርቦ ነበር፡፡ በዚህም መሰረት የምርመራ ቡድን እንዲቋቋም ተደርጎ እ.ኤ.አ ጥቅምት 2014 የዓለም ባንክ የምርመራ ቡድን/Inspection Panel አስተማማኝነት ያለው ዘገባ በማቅረብ በድረ ገጽ እንዲለቀቅ ተደረገ፡፡ በጥናት ቡድኑ ዘገባ መሰረት የዓለም ባንክ አውቆም ይሁን ሳያውቅ በፕሮጅክቱ አማካይነት በጋምቤላ ህዝቦች ኗሪ ማህበረሰብ ላይ ጉዳት ያደረሰ መሆኑን በግልጽ አመላክቷል፡፡
እ.ኤ.አ ጥር 2015 ካሩቱሪ ፕሮጀክቱን መዝጋቱን ይፋ አደረገ፡፡ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የግብርና ኢንቨስትመንት እና የመሬት አስተዳደር ኤጀንሲ ዳይሬክተር የሆኑትን አበራ ሙላትን ሪፖረተር ጋዜጣ ጠቅሶ እንደዘገበው ካሩቱሪ ውስጣዊ አስተዳደሩን ተከትሎ ለኪሳራ ተዳርጓል በማለት ይፋ አድርጓል፡፡ በዚሁም ተመሳሳይ ዘገባ መሰረት የካሩቱሪ ዋና ስራ አስፈጻሚ/Chief Executive Officer የሆኑት ራም ካሬቱሪ እንዲህ የሚል ዘገባ አሰምተዋል፣ “15 ሚሊዮን ዶላር ሊያወጣ የሚችል ዋጋ ያላቸው የማምረቻ መሳሪያዎች ድርጅቱ ያለበትን ዕዳ ለመክፈል በሚል በመሸጥ ላይ ናቸው፡፡ ካሩቱሪ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ከዳሽን እና ከዘመን ባንኮች ብድር የወሰደ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ኩባንያው ያለበት ብድር ከ170 ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑን እና ዋና ስራ አስፈጻሚው ይህንን ዕዳ በዚህ ወር መጨረሻ ከፍሎ ለማጠናቀቅ እና ከዕዳ ነጻ ለመሆን እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡“
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የመሬት ማጭበርበር የቁማር ጨዋታ፣
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ለካሩቱሪ ያደረገው የመሬት ኪራይ (ነጻ ስጦታ) እ.ኤ.አ በ1960ዎች እና 70ዎቹ በዩናይትድ ስቴትስ በተለይም በፍሎሪዳ ግዛት ሲደረግ የነበረውን የመሬት ማጭበርበር ዘረፋ አስታወሰኝ፡፡ በዚያን ጊዜ የመሬት አጭበርባሪዎች በጣም ውብ የሆኑ የደን መሬቶችን በጣም ጥቂት በሆኑ ዶላሮች በጸሐያማዋ ፍሎሪዳ ለመኖሪያ ቤት ህንጻ ግንባታ መስሪያነት ማስታወቂያዎችን ያወጡባቸው ነበር፡፡ ከአካባቢያዊ ስነምህዳር አንጻር በማየት ጠንከር ያለ ገለጻ ያደርጉ ነበር፡፡ ያ የተዋበ እና ድንቅ የደን መሬት በእርግጥ ረግረጋማ መሬት ነበር፡፡ ፍሎሪዳ የገዙትን ያንን የተዋበ መሬት ወይም ደግሞ ገና ወደፊት ለመግዛት ዕቅድ ያላቸው ገዥዎች ለማየት በሚሄዱበት ጊዜ ሻጮቻቸው በዓይኖቻቸው አተኩረው በመመልከት የጉዳቱ ሰለባ ለሆኑ ሰዎች የእናንተ ንብረት ከዚያ ከምታዩት ጫካ አድማስ አለፍ ብሎ ነው ይሏቸው ነበር፡፡ እነዚህ የጉዳት ሰለባዎች መንገዶችን እንሚሰሩላቸው፣ መሰረታዊ አገልግሎቶችን እንደሚያቀርቡላቸው እና በቅርቡም የልማት ቦታዎች ግንባታ እንደሚጀመር ያረጋግጡላቸው ነበር፡፡ ሆኖም ግን ስምምነቶቹ ከጠረጴዛው ላይ ያሉ ስለሆነ ዛሬውኑ መፈረም እንዳለባቸው ይገልጹለቸው ነበር፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች እነዚያን እረግረጋማ መሬቶች በስልክ ግንኙነት በማደረግ ገዟቸው እናም ለምንም ነገር የማይጠቅም ኢንቨስትመንት ነው በማለት ገንዘቡን በቸክ ገቢ ያደርጉላቸው ነበር፡፡ ሁሉም ከስረው ቀሩ።
እንደዚሁም ደግሞ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ዓይነ ሰፊ በሆኑ የዲስፖራ መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች እና በወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አማካይነት የመሬት ልማት እየተባለ እየተሰጣቸው የማጭበርበር እና የዘረፋ ስራ ሲካሄድ ተመልክቻለሁ፡፡ አንዱ ዋና የማጭበርበር ዘዴ ግዥው በሚፈጸምበት ጊዜ በአሜሪካ ዶላር ገንዘብ (በሀገሬው ገንዘብ አይፈቀድም) የተወሰነ ክፍያ መክፈል እና ቀሪውን ደግሞ በቀጣይነት ለመክፈል ስምምነት ማድረግ ነው፡፡ የዚህ ዓይነት ስምምነት ሰለባ የሆኑት አስቀድመው የከፈሉት ገንዘብ ሳይመለስ እና ቃል የተገባላቸውም የኮንዶሚኒየም ቤት ግንባታ ሳይገነባ ከስረው ይቀራሉ፡፡
ሌላው የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያንን/ትን ለማታለል የሚጠቀሙበት እና ለማመን የሚያስቸግረው ዘዴ የመኖሪያ ቤት ልማት ፕሮጀክት በሚል በአዲስ አበባ ከተማ ቦታ ለማግኘት ሲባል የኮንዶም የግንባታ ስራ ለመጀመር አስቀድሞ በአሜሪካ ዶላር ክፍያ እንዲፈጽሙ ይደረጋሉ፡፡ የግንባታ ስራው ለመጠናቀቅ ትንሽ ሲቀረው አጭበርባሪዎቹ መሬት አዳዮች ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾችን መጠኑ ከፍ ያለ ገንዘብ (የኮንትራት ስምምነቱን ሶስት ጊዜ ያህል በመጨመር) እንዲከፍሉ ወይም ካልሆነ ደግሞ ይህንን በመጀመሪያ ያስገቡትን ገንዘብ መልሰው እንዲወስዱ ይነግሯቸዋል፡፡ የመሬት ዘረፋው አጭበርባሪዎች በዲያስፖራው የተሰጣቸውን የመጀመሪያውን ክፍያ ለግንባታ ካዋሉ በኋላ ለመጠናቀቅ ትንሽ የቀረውን የኮንዶሚኒየም ግንባታ ቤት በአሁኑ ጊዜ የቤት ገበያ ዋጋ እየጨመረ ስለሆነ በከፍተኛ ዋጋ ለሌላ ሊሸጡት ይችላሉ ፡፡ የመጀመሪያዎቹ መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች ያልተጠናቀቀውን የኮንዶሚኒየም ቤት የንብረት ባለቤትነት ጥያቄ በሚያቀርቡበት ጊዜ አጭበርባሪ ዘራፊዎቹ ፈቃደኛ ባለመሆን ይቃወማሉ፡፡ መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች ጉዳዩን ወደ ህግ በመውሰድ አሸናፊ ቢሆኑም አጭበርባሪ ዘራፊዎቹ ይግባኝ ይጠይቁ እና በሌላ ዳኛ እንዲታይ በማድረግ እነርሱ በሚፈልጉት መልኩ እንዲሻር እና ለእነርሱ በሚጠቅም መልኩ እንዲወሰንላቸው ያደርጋሉ፡፡ ምን ዓይነት አጭበርባሪነት ነው እባካችሁ! በወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የቤት ልማት ግንባታ ሰበብ የሚጭበረበሩ የዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን/ት የተሰበረ ልብ እንዴት የሚያሳዝን ሁኔታ ነው!
የከተማ የቤት ልማት የማጭበርበር ድርጊቶች “የናይጀሪያ 419 ማጭበርበር” እየተባለ የሚጠራውን አስታወሰኝ፡፡ (እ.ኤ.አ በ1990ዎቹ የመጨረሻዎቹ እና በ2000ዎቹ የመጀመሪያ ወራት አካባቢ የጫካውን ዳክየ ማሳደድ በሚል በምንም ዓይነት መልኩ ሊደረስበት የማይችልን በፋክስ ማሽን የተከናወነን የገንዘብ ማጭበርበር ጉዳይ አስመልክቶ ጥቂት ደንበኞቸን በመወከል ጉዳዩን ይዠው ነበር፡፡) አጭበርባሪዎቹ መንግስታዊ በሆነው በናይጀሪያ ብሄራዊ ፔትሮሊየም ኮርፖሬሽን ዳይሬክተር ስም የተጻፈ ደብዳቤ በማስመሰል በፋክስ እንዲላክ ያደርጋሉ፣ ወይም ደግሞ በናይጀሪያ ልዑል፣ ጀኔራል ወይም ለአዕምሮ የበላቤትነት ከፍያ ገቢ እንዲደረግ በሚል በማጭበርበር ብዙ ገንዘብ (አብዛኛውን ጊዜ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ) ከናይጀሪያ እንዲወጣ ይደረጋል፡፡ የገንዘብ ዝውውሩ ከተጠናቀቀ በኋላ የማጭበርበር ድርጊት የተፈጸመበት የጉዳት ሰለባ ከተላከው ገንዝብ ውስጥ የተወሰነ መቶኛ ድርሻ እንደሚሰጠው ይነገረዋል፡፡ አንድ ዋና ማነቆ የሆነ ቸግር አለ፡፡ ይኸውም የጉዳት ሰለባው ለማስፈጸሚያ ሂደቱ በሚል በርካታ የሆነ በሺዎች የሚቆጠር ገንዘብ እንዲልክ ይጠየቃል፡፡ ወዲያውኑ አጭበርባሪዎች ገንዘቡን እንዳገኙ እራሳቸውን በመሰወር የውኃ ሽታ ይሆናሉ፡፡ ይህም ማለት በአዲስ አበባ ከተማ በኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ ላይ እንደሚደረገው የማጭበርበር ስራ ማለት ነው!
ካሩቱሪ እንደ ፈሎሪዳ ዓይነት የመሬት ማጭበርበር ድርጊት ተፈጽሞበት እንደሆነ እስከ አሁን ድረስ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ በሁሉም ዘንድ አካባቢው የጎርፍ ጥቃት ያለበት መሆኑ እየታወቀ አንድ ኩባንያ እንዴት በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በማውጣት ለኪሳራ እንደተዳረገ ለእኔ ሊታሰብ የማይችል አስቸጋሪ ጉዳይ ነው፡፡ ካሩቱሪ የስነ ምህዳር (የአካባቢ ጉዳትን ጨምሮ) ዝርዝር ጥናት አላካሄደምን? ካሩቱሪ ከአካባቢው ማህበረሰብ መሪዎች እና ከህዝቡ ጋር ውይይት አላደረግምን? ምናልባትም አድርጎ ሊሆን ይችላል፣ ሆኖም ግን በሰከነ እና ጥንቃቄን በተላበሰ መልኩ ሳይሆን የጥናቱን ውጤት ወደ ጎን በመተው በችኮላ ወደ ስራው ገብቶበት ሊሆን ይችላልን? ካሩቱሪ የአካባቢ ጥናት አካሂዶ ቢሆን ኖሮ የጥናት ውጤቱ ሊሰጠው የሚችለው መረጃ ያ አካባቢ ለፕሮጀክቱ ሊሆን የሚችለው ለግጦሽ እና ለአደን እንጅ በየጊዜው የሚከሰት የጎርፍ አደጋ የሚከሰትበት አካባቢ በመሆኑ ምክንያት ለሰብል ልማት ሊውል አይችልም የሚል ይሆን ነበር፡፡ ካሩቱሪ የሰራቸው አነስተኛ የጎርፍ መቀልበሻዎች፣ የመስኖ መፋሰሻዎች እና ቦዮች ኃይለኛውን እና ታላቁን የባሮን (ኡፔኖን) ወንዝ እና የገባሮቹን ጎርፍ ሊከላከል ይችላል ተብሎ ይታሰባልን? ምናልባትም በጣም ላልገረም እችላለሁ፡፡ በፍሎሪዳ የመሬት ማጭበርበር የተሳተፉ የመሬት ባለቤት አታላዮችም የአካባቢውን ረግራጋማ ቦታዎች ሁሉ በሙሉ አንጠፍጥፈን ለልማት ስራ እናውለዋለን የሚል ዓላማ ሲያራምዱ ነበር፡፡ በረግራጋማ ቦታ እና በጎርፍ አካባቢ መካከል ጉልህ የሆነ ልዩነት ይኖራልን? የሰርከስ ታላቅ ባለሙያ የሆነው ፒ.ተ. ባርነም በአንድ ወቅት እንዲህ ብሎ ነበር፣ “በእያንዳንዷ ደቂቃ የሚወለድ ሞኝ ሞልቷል“፡፡
የጋምቤላ ህዝቦች እና ሌሎች አናሳ ብሄረሰቦች ከቀደምቶቻቸው የተረከቧቸውን መሬቶች ደህንነት ለመጠበቅ የአጋር ጓደኞቻቸውን ሙሉ ድጋፍ ይሻሉ፣
እ.ኤ.አ እስከ 2006 ድረስ ስለጋምቤላ ወይም ደግሞ እዚያ አካባቢ ስለሚኖሩት ህዝቦች ብዙም ነገር አላውቅም ነበር፡፡ ታዋቂው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የሆነው ሂዩማን ራይትስ ዎች “በጋምቤላ ክልል በሰው ልጆች ላይ የተፈጸመ ወንጀል/Crimes Against Humanity in Gambella Region“ በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ ታህሳስ 2003 በመለስ ዜናዊ እና በእርሱ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በተቀነባበረ ሴራ በምዕራብ ጋምቤላ የአኟክ ህዝቦች ላይ የጅምላ ግድያ እልቂት፣ አስገድዶ መድፈር እና ማሰቃየት እስከፈጸሙበት ጊዜ ድረስ ስለአካባቢው ብዙም አላውቅም ነበር፡፡ በእርግጥ እ.ኤ.አ በ2005 በኢትዮጵያ ተካሂዶ በነበረው ሀገር አቀፍ ምርጫ የተከሰተውን ውዝግብ ተከትሎ መለስ ዜናዊ በማን አለብኝነት እና በአረመኔነት እኩይ ምግባሩ በሰላማዊ መንገድ ቅሬታቸውን ለመግለጽ ወደ አደባባይ በወጡ ንጹሀን ዜጎች ላይ የጥይት እሩምታ እንዲከፈት አድርጎ ሮጠው ያልጠገቡ እምቦቃቅላ ህጻናተን እና ሌሎቹን ወገኖቼን ሁሉ በአደባባይ ማስጨረስ ከጀመረ በኋላ ነው ፍላጎት ያደረብኝ እና ወደ ኢትዮጵያ ፖለቲካ ዘው ብየ በመግባት ነገሮችን ሁሉ መከታተል የጀመርኩት፡፡ ያ የመለስ አሰቃቂ የንጹሀን ዜጎች እልቂት የጣለው ጠባሳ በህይወቴ ላይ ልዩ የሆነ አጋጣሚን በመፍጠር በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ላይ ሙሉ በሙሉ እንድገባ እና የዜግነት ድርሻዬን እንድወጣ አድርጎኛል፡፡
በጋምቤላ ህዝቦች ላይ ስለተፈጸመው የሰብአዊ መብት ወንጀል ለመጀመሪያ ጊዜ እ.ኤ.አ በመስከረም 2006 ነው ሙሉ ለሙሉ ግንዛቤ ያገኘሁት፡፡ ኦባንግ ሜቶ የተባሉት የኢትዮጵያ ወጣት የሰብአዊ መብት ተሟጋች እና የጋምቤላ የአኟክ ህዝቦች የፍትህ ምክር ቤት ዳይሬክተር/Anuak People’s Justice Council Director “በዴሞክራሲ ላይ የተፈጸመ ክህደት/Betrayal of Democracy“ በሚል ርዕስ አዘጋጅተውት በነበረው ዘገባ ላይ በካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ ሎስ አንጀለስ/University of California, Los Angeles (UCLA) በመገኘት ንግግር እንዳደርግ በተጋበዝኩበት ወቅት መለስ በጋምቤላ ህዝቦች ላይ የፈጸመው እልቂት ገና ትኩስ ነበር፡፡ ኦባንግ ያንን ዘጋቢ ሰነድ በካናዳ ከሚገኘው ከሳስካቸዋን ዩኒቨርስቲ/University of Saskachewan ጋር በመተባበር ነው አዘጋጅተውት የነበረው፡፡ ኦባንግ “ያ ዘጋቢ ሰነድ በመንግስት ዴሞክራሲ አለ እየተባለ በሚሰበክባት ሀገር እንደዚህ ያለ አሰቃቂ የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ በኢትዮጵያ ተንሰራፍቶ እንዳለ እና በአሁኑ ጊዜም በአኟክ ማህበረሰብ እና በሌሎች ህዝቦች ላይም ቀጥሎ እንዳለ መረጃ የሚያቀርብ ሰነድ ነው” በማለት ነበር ገለጻቸውን ያደረጉት፡፡
ከኦባንግ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ፊት ለፊት የተገናኘነው እ..ኤ.አ በ2006 የጸደይ ወቅት ኤች. አር 4423 (የኢትዮጵያ የ2005 የማጠናከሪያ ድንጋጌ)/H.R. 4423 (Ethiopia Consolidation Act) የሚለው ሰነድ በዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ጉዳዮች ንኡስ ኮሚቴ ተዘጋጅቶ በተጠናቀቀበት ጊዜ ነበር፡፡ ያንን ዕለት በንኡስ ኮሚቴው የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ ሆኘ በካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ ሎስ አንጀለስ ላይ ያደረግሁትን ንግግር አስታወስኩ፡፡ ኦባንግ የምስክርነት ቃላቸውን በሚሰጡበት ወቅት ከመነጋገሪያው ጀርባ ሆኘ በአጽንኦ እመለከት ነበር፡፡ ኦባንግ በታላቅ ስቃይ ላይ ያሉ ይመስሉ ነበር፡፡ እንዲህ ሲሉ አዳምጥ ነበር፣ “በዛሬው ዕለት ስለአኟክ ወገኖቻችን እናገራለሁ፡፡ እኔ የአኟክ ማህበረሰብ ተወላጅ ነኝ፡፡ ጋምቤላ ነው ተወልጀ ያደግሁት፡፡ ስሜታዊነትን በተላበሰ መልኩ ንግግር የማደርግ ከሆነ እባካችሁን ችግሬን ተገንዝባችሁ ይቅርታ እንድታደርጉልኝ እጠይቃለሁ፡፡“
ኦባንግ በርካታ ኢትዮጵያውያን/ት በታደሙበት ቦታ ንግግር ወደሚደረግበት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ፈጠን ብለው በመሄድ እንዲህ በማለት ንግግራቸውን ቀጠሉ፣ “አሁን ንግግር በማደርገበት ጊዜ ዛሬ አብዛኞቻችሁ የእኔን ፊት በመመልከት ኢትዮጵያዊ እንዳልሆንኩ አድርጋችሁ ልትገምቱ ትችላላችሁ፡፡ ለጥቂት ኢትዮጵያውያን/ት ጀርመን ልመስል እችላለሁ፡፡ በዛሬው ዕለት እንኳ ልገለል እችላለሁ፡፡ አኟክ የምትለዋን ቃል የተነፈሷት ብቸኛው ሰው ሊቀመንበር ስሚዝ ናቸው፡፡“ የኦባንግ ንግግሮች እየሞቀ እንዳሚሄድ የቦንብ ባሩድ እኔም እየሞቀኝ መጣ፡፡ ኦባንግ ስለምን ይናገሩ እንደነበር በእርግጠኝነት አውቅ ነበር፣ ሆኖም ግን እንደዚህ ያለውን የቤት ዉስጥ ጉድ በመድረክ አደባባይ የዩኤስ የተለያዩ ግዛቶች የምክር ቤት አባላት በጥንቃቄ እየመዘገቡ በሚይዙበት ሁኔታ አያለሁ የሚል የስነ ልቦና ዝግጅት አልነበረኝም፡፡
ኦባንግ እውነታውን አፍርጠው እና አፍረጥርጠው እንደዚያ ባለ ግልጽ እና ድፍረትን በተላበሰ መልኩ ያቀርቡታል የሚል ግምት አልነበረኝም፡፡ አይበገሬው ኦባንግ እውነተኛ የአርበኝነት ወኔን እና በእራስ መተማመንን በተላበሰ መልኩ ንግግራቸውን እንዲህ በማለት ቀጠሉ፣ “አኟኮች የኢትዮጵያ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ዜጎች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያውያን/ት ይህንን እውነታ የመቀበል ግዴታ አለባችሁ፡፡“ ይህንን በምሰማበት ጊዜ ጭንቅላቴን ዝቅ በማድረግ ብቻ ኃፍረትን በተከናነበ መልኩ መሬት መሬቱን መመልከት ጀመርኩ፡፡ ኦባንግ እውነታውን አፍርጠው እንደተናገሩ አሳምሬ አውቃለሁ፣ ሆኖም ግን ይህንን አውንታ በአደባባይ በምስለ ትዕይንት/ኤግዚቢሽን ከሌሎች ኢትዮጵያውያን/ት ጋር በኃፍረት አንገታችንን ደፍተን እናየዋለን የሚል ግምት አልነበረኝም፡፡ ኦባንግ ስለአኟክ ህዝቦች እልቂት በማውሳት ለእነርሱ የሚጠቅም አንድ ነገር መደረግ እንዳለበት እንዲህ በማለት የተማጽዕኖ ንግግራቸውን ቀጠሉ፣ “በጣም አናሳ የሆንን ብሄረሰብ ነን፡፡ የአኟክ ህዝብ ብዛት ከ100,000 አይበልጥም፡፡ ይህም እኔን ጨምሮ ቢሆን ነው፡፡“ በአኟክ ህዝቦች ላይ የተፈጸመውን እልቂት የአሜሪካ ህዝብ እንዲገነዘበው እዚህ በአሜሪካ ምክር ቤት አባላት/የኮንግረስ አባላት ፊት ቆሜ ለፍትህ እና ለርትዕ ስል ጩኸቴን በማሰማት ላይ እገኛለሁ በማለት ተናግረዋል፡፡ ኦባንግ እዚህ የመጣሁት ወገኖቼ በኢትዮጵያ መንግስት በመወረር ተጨማሪ ሰቆቃ እንዳይፈጸምባቸው የሰይጣናዊ አካሄዱን ለማስቆም እና ለእነዚህ ምስኪን ወገኖቼ የአሜሪካ የምክር ቤት አባላት እገዛ በእጅጉ እንደሚያስፈልጋቸው በማመን ነው በማለት አጽንኦ በመስጠት ንግግራቸውን ቀጥለዋል፡፡ ንግግራቸውን በመቀጠል 1,600 የሚሆኑ ወንድሞቻቸቸው፣ እህቶቻቸው፣ ዘመዶቻቸው፣ ጓደኞቻቸው እና ጎረቤቶቻቸው በኢትዮጵያ መንግስት ታጣቂ ኃይሎች ተገድለዋል፣ እንዲያልቁም ተደርገዋል ብለዋል፡፡ ሌሎች በሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖች ደግሞ በኡሁኑ ጊዜ በመጠለያ ውስጥ ሆነው እርዳታ ጠባቂ ናቸው፡፡ በዚያ የጩኸት ማሰሚያ የስብስባ አዳራሽ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ በወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የዘር ማጽዳት ወረራ በአደገኛ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ አስቸኳይ እርዳታ እንዲደረግላቸው እዚያ በመገኘት እየጮኹላቸው ያሉት ብቸኛው ኢትዮጵያዊ ኦባንግ ብቻ ነበሩ፡፡ ቪቫ ኦባንግ! ኢትዮጵያዊው ጀግና የሰብአዊ መብት ተሟጋች!
ኦባንግ ስለአኟክ ህዝቦች ተስፋየለሽ የጨለማ ህይወት እንዲህ በማለት ተናግረዋል፣ “በአሁኑ ጊዜ የአኟክ ህዝቦች ተስፋ የላቸውም፡፡ እናም የዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ደንታቢስ በመሆን ማድረግ ያለበትን የሞራል ግዴታ ባለመወጣቱ በፈተናው ወድቋል፡፡“
በዚያ ዕለት በዚያ የመሰብሰቢያ አዳራሽ በመገኘት ለፍትህ እና ርትዕ ሲባል በዩኤስ አሜሪካ የምክር ቤት አባላት ፊት ፍቅርን በተላበሰ መልኩ በጽናት ቆሞ ለህዝቦቹ የተናገረ ከኦባንግ ውጭ ማንም አልነበረም፡፡ በምስል ትዕይንት ማሳያው ጀርባ ተቀምጨ እራሴን በህፍረት ማቅ ውስጥ ተወሽቆ አገኘሁት፡፡
እውነታው ተግልጦ እና ተፍረጥርጦ ሲታይ ግን እራሳቸውን ኢትዮጵያዊ/ት አድርገው የሚቆጥሩ በርካታ ናቸው፣ ሆኖም ግን የአኟክን ወይ ደግሞ ሌሎችን በቋሚነት ሰፍረው የሚኖሩትን አናሳ ብሄረሰቦች በደቡብ ኢትዮጵያ የኦሞ ማህበረሰብ ህዝቦችን ጨምሮ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ/ት መሆናቸውን ያለመቀበል ሁኔታ ይታያል፡፡ አናሳ ማህበረሰቦችን በተመለከተ በአሁኑ ጊዜ እንኳ የተሳሳተ እንዲያውም በእጅጉ የከፋ ነገር አለ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ስለእነዚህ አናሳ ማህበረሰብ የጎሳ ቡድን ወገኖቻችን ደንታ የሌለን ስንቶቻችን እንዳለን ቤት ይቁጠረው፡፡ ያ ዕልቂት ከተፈጸመበት ከአስር ዓመታት በኋላም እራሴን በታላቅ ኃፍረት ውስጥ ተደብቆ አገኘሁት፡፡ የኢትዮጵያን ቅርስ እና ኩራት እወዳለሁ የሚል ኢትዮጵያዊ/ት ሁሉ የጋምቤላን ወይም ደግሞ የአሞን ህዝቦች ወንድምነት እና እህትነት ሙሉ በሙሉ በማይቀበሉት ወገኖቻችን ላይ ልናፍር ይገባል፡፡ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በአሜሪካ በፍሎሪዳ ግዛት እንደተደረገው የመሬት ማጭበርበር ዝርፊያ ቅሌት ሁሉ በጋምቤላ ክልል ቀደምቶቻችን ለዘመናት ሰፍረውበት የኖሩትን ለም እና ድንግል መሬት በማጭበርበር እና በመሸጥ ባደረጉት ቅሌት ሊያፍሩ ይገባል፡፡ የጋምቤላ ህዝቦች በመንደር ሰፈራ ፕሮግራም እና በተፈጸመባቸው የግድያ እልቂት የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ሊያፍር ይገባል…
በወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ እና በእነርሱ የድብቅ የጥቅም ተጋሪ የሸፍጥ ኢንቨስትመንት ዘራፊዎች (በቅርቡ ለእንግሊዝኛ ቋንቋ ዘራፊዎችን ከኢንቨስትመንት ጋር ለማቆራኘት የተጠቀምኩበት) በጋምቤላ ወይም ደግሞ በኦሞ ህዝቦች ወገኖቻችን ላይ የሚፈጸመውን የመሬት ነጠቃ እና የግድያ እልቂት ስናይ ማልቀስ፣ መጮህ እና እሪ ማለት አለብን፡፡ በምንም ዓይነት ሁኔታ ዝም ማለት የለብንም፡፡ ደግመን ደጋግመን እሪ እንበል፡፡
እንደ ጋምቤላ ህዝቦች ሁሉ በአሁኑ ጊዜ በደቡብ ኢትዮጵያ በኦሞ ወንዝ ሸለቆ የሚኖሩ ወገኖቻችንም እንደዚሁ የአካባቢ ስነምህዳር አደጋ ተጋፍጦባቸው ይገኛሉ፡፡ ይህ የከፋ ችግር፣ ወገኖቻችንን ለረኃብ፣ በቋሚነት ከሚኖሩበት ቦታ የመፈናቀል እና ለግጭት መንስኤ መሆን ብቻ አይደለም አሳሳቢ ሆኖ የሚገኘው፣ ሆኖም ግን እነዚህ ህዝቦች ለዘመናት ሲኖሩበት የነበረው የአካባቢ ስነምህዳር በአጠቃላይ እንዲወድም ተደርጎ ህይወት ያለው ነገር ሁሉ በአጠቃላይ እንዲጠፋ የሚደረግበት ክስተት ሊመጣ እንደሚችል ልናስተውል ይገባል፡፡
የዓለም አቀፍ ወንዞች/International Rivers የተባለው ዓለም አቀፍ ድርጅት ባለፈው ሳምንት ባወጣው ዘገባ መሰረት የጊቤ 3ን ግድብ ለመሙላት በሚል ምክንያት የሚደረገው እንቅስቃሴ በታችኛው የኦሞ ሸለቆ በሚኖሩ ህዝቦች እና በአካባቢው ስነምህዳር ላይ አስከፊ የሆነ ጉዳትን ሊያመጣ እንደሚችል አስጠንቅቆ ነበር፡፡ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የአካባቢውን ስነምህዳር በጠራራ ጸሐይ በማውደም እና በኦሞ ህዝቦች ላይ ኢሰብአዊ የሆኑ ጭራቃዊ ድርጊቶችን በመፈጸም ሰብአዊ መብቶቻቸው ሲደፈጠጡ አይኖቻችንን መጨፈን፣ ጆሮዎቻችንን መድፈን እና ከንፈሮቻችንን መምጠጥ ዋጋ የለውም፡፡ መናገር አለብን፡፡ ድምጻችንን ከፍ አድርገን መጮህ አለብን!
በጋምቤላ ለተፈጸመው የዘር ማጥፋት እና በህዝቦች ላይ ለተፈጸመው የሰብአዊ መብት ረገጣ ወንጀል ኃላፊነቱን የሚወስደው ማን ነው?
በተባበሩት መንግስታት የሮም ስምምነትን በመተላለፍ በጋምቤላ ህዝቦች ላይ የዘር ማጥፋት እና የሰብአዊ መብት ረገጣ ወንጀሎች መፈጸማቸውን ከምንም ጥርጣሬ በላይ ማረጋገጥ ችያለሁ፡፡ የሮም ስምምነት አንቀጽ 15 የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ዋና አቃቤ ህግ የሰብአዊ መብት ረገጣ ወንጀል ተፈጽሟል የሚል ጥርጣሬ ካለ (በICC ዋና አቃቢ ህግ ውሳኔ መሰረት) በተገኘው መረጃ መሰረት ክስ በመመስረት ሰብአዊ መብት ረጋጮችን ወደ ፍትህ አካሉ ማቅረብ እና ምርመራውን መቀጠል እንደሚቻል በግልጽ አስቀምጧል፡፡
በሮም ስምምነት አንቀጽ 6 (c) ሆን ተብሎ ታስቦበት እና ተመክሮበት የሰዎችን ህይወት ለማጥፋት እና የአንድን ማህበረሰብ ኢላማ አድርጎ ለሚፈጸም የዘር ማጥፋት ወንጀል ማረጋገጫ ይፈልጋል፡፡ በአንቀጽ 6 (b) በህዝቦች ላይ ሆን ብሎ የአካል ወይም ደግሞ የመንፈስ ጉዳት ያደረሰ ከሆነ ክስ የመመስረት እና የማጣራት ስራ ሊከናወን ይችላል ይላል፡፡
በአንቀጽ 7 (1) (d) ስር ማጋዝን ወይም ደግሞ ህዝብን ከፍላጎቱ ውጭ አስገድዶ ማስፈር እንደሁም ሌሎችም ኢሰብአዊ የሆኑ ድርጊቶች በአንቀጽ 7 (1) (k) ስር በግልጽ ተቀምጠዋል፡፡
የኢትዮጵያ ህገ መንግስት በአንቀጽ 28 “በሰው ልጆች ላይ ስለሚደርሱ የሰብአዊ መብት ረገጣዎች“ ስለሰብአዊ መብቶች ረገጣ በዓለም አቀፍ ስምምነቶች መሰረት ኢትዮጵያ ያጸደቀችው እና በሌሎችም ህጎች ላይ የተካተቱትን በግልጽ መመልከት ይቻላል… የዘር ማጽዳት ወንጀል በህግ አካሉ ሊታለፍ የሚችል ጉዳይ አይደለም…የኢትዮጵያ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ አንቀጽ 269 እንዲህ ይላል፣ “ማንም በጦርነትም ሆነ በሰላም ጊዜ ሆን ብሎ ሙሉ ለሙሉ ወይም ደግሞ በከፊል ለማጥፋት በብሄር፣ ብሄረሰብ፣ በጎሳ፣ በዘር፣ በዜግነት፣ በቀለም፣ በኃይማኖት ወይም የፖለቲካ ቡድን ሆን በሎ ካደራጀ፣ ትዕዛዝ ከሰጠ፣ ወይም ደግሞ (a) ግድያ ለመፈጸም፣ የአካል ጉዳት ለማድረስ ወይም ደግሞ በየትኛውም መልኩ አስከፊ የሆነ የአካልም ሆነ አዕምሯዊ ጉዳት ካደረሰ ወይም እንዲጠፋ ከተደረገ… ከ5 እስከ 25 ዓመታት ወይም ደግሞ ከዚህ ለበለጡ ጉዳዮች እስከ እድሜ ልክ እስራት ወይም እስከ ሞት ሊያስቀጡ ይችላሉ፡፡ (አጽንኦ ተሰጥቷል)፡፡“
ከቅርብ ጊዜ በፊት በአደናጋሪ ንግግሩ የሚታወቀው አሻንጉሊቱ ኃይለማርያም ደሳለኝ እንዲህ የሚል ንግግር አሰምቶ ነበር፣ “ያሉን ተቋማት፣ ህጎች እና ደንቦች እንከንየለሽ ናቸው፡፡ ህጉ አይደለም አስቸጋሪ ሆኖ የሚገኘው፣ ሆኖም ግን ዋናው ችግሩ ያለው ከአፈጻጸሙ ላይ ነው፡፡” ከኃይለማርያም ፍልስፍና በመዋስ በኢትዮጵያ የህገ መንግስቱ እና የህግ ሂደቶች ሁሉ ለምርመራ እና የዘር ማጽዳት እና ሌሎችን በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለመዳኘት የሚያስችሉ እንከንየለሽ ናቸው፡፡ ህጉ በእራሱ አይደለም ችግር የሚፈጥረው ሆኖም ግን ዋናው ችግር እነዚህን በባዶ ተጽፈው ያሉትን ህጎች ከመፈጸሙ ላይ ነው፡፡ ታዲያ ነገሩ ሁሉ እንደዚህ ከሆነ እነዚህን እንከንየለሽ ህጎች ማን እና ምንድን ነው በአግባቡ እንዳይፈጽሙ የሚያደርገው?!?
ካሩቱሪ በክስረት እሳት ላይ፣
እ.ኤ.አ ጥቀምት 2011 “ካሩቱሪ በእሳት አደጋ ላይ?” በሚል ርዕስ የጋምቤላ ህዝቦችን ቅሬታ በማንሳት ጩኸቴን ያሰማሁ መሆኔን እና በካሩቱሪ እና በድብቁ የዓለም ባንክ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ገንዘብ ለልማት ተብሎ ቢፈስስም እየታዩ ያሉት በጣም ጥቂት የሆኑ የስራ ዕድሎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ክሊኒኮች ወይም ለመጠጥ አገልግሎት የሚውል ጥቂት የውኃ ፋሲሊቲዎች ብቻ ናቸው፡፡ በዕለቱ መጨረሻ የጋምቤላ ህዝቦች በረዥም የጊዜ አድማስ የደን ውድመት (ደኖችን በማቃጠል መሬትን ለእርሻ ማዘጋጀት)፣ የብዝሀ ህይወት መመናመን፣ የአካባቢ ዝርያዎች መጥፋት እና በአረም እና በተባይ ማጥፊያ መድኃኒቶች ርጭት እንዲሁም በሰፊ ታላላቅ የንግድ እርሻዎች ምክንያት የአካባቢ ብክለት መፈጠሩን በማስመልከት የክርክር ጭብጤን አቅርቤ ነበር፡፡
ባቀረብኩት ትችት ላይ ስለካሩቱሪ ውስን የሆኑ የመፍትሄ ሀሳቦችን ሰንዝሬ ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከእርሻው ጋር በተያያዘ መልኩ ያለውን የመሬት ማግኛ ዘዴ እና የባለቤትነት መብት እርግፍ አድርጎ መተው እና በቀጥታ ከጋምቤላ ገበሬዎች ጋር በመስማማት እና በመግባባት የቀድሞውን አሰራር በዚህ መተካት፡፡ በጋምቤላ ላሉ ገበሬዎች ስልጠና መስጠት እና የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑ የእነርሱን እውቀት በአግባቡ መጠቀም፡፡ በዚህ ዓይነት መልኩ በመስራት ካሩቱሪ የምግብ እህል እና ሌሎችን የግብርና ምርት ውጤቶችን በማምረት ለኢትዮጵያ ገበያዎች በማቅረብ ትርፋማ መሆን ይችላል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በረዥም ዕቅድ የአካባቢውን ስነምህዳር እና የግብርና ምራታማነቱን በመጠበቅ ዘላቂነት ያለው ልማትን ለማምጣት ያስችላል፡፡ ካሩቱሪ የጋምቤላን ፕሮጀክት ኃላፊነት የተንጸባረቀበት፣ ጥንቃቄ የተሞላበት እና ትርፋማ ኢንቨስትመንት ዋና የአፍሪካ ሞዴል አድርጎ ማሳየት እና በሌሎች የአፍሪካ ሀገሮችም በተመሳሳይ መልኩ እየሰራ የሚጠቀምበት ማድረግ ይችል ነበር፡፡
ትችቴን ለማጠቃለል ያህል በደቡብ አሜሪካ ግዛቶች እየተጋዙ አስከፊ በሆነ ሁኔታ በጥጥ እና በትምባሆ ሰብሎች ላይ የእርሻ ስራ ላይ የጉልበት ስራ እንዲሰሩ ይገደዱ በነበሩት የአፍሪካ ባሮች የተቋጠሩትን እንዲህ የሚሉትን ጥቂት የሙዚቃ ስንኞች አስታወሰኝ፡፡
አምላክ ለኖህ ብሎ በሰጠው ምልክት፣
በተንቆጠቆጠው በሰባት ቀለማት፣
በቀስተ ደመና ታምር ባጠላበት፣
እራሱን ለማዳን ከማዕበሉ መቅሰፍት፣
ትዕዛዙን ፈጸመ ህይወት ለማቆየት፣
በዚህች ምስኪን ምድር ዘርን ለመተካት፡፡
ኖህ ለአምላክ ሲገዛ ትዛዙን ሲፈጽም፣
ያ ሁሉ መከራ ከጎኑ ሲል እልም፣
የውኃው ማዕበል ብን ብሎ ሲያከትም፣
በቀጣይነትም እሳት አልነበረም፡፡
ኖህ በሰላም ኖረ ዘርንም ተክቶ፣
በሁሉም አህጉር አህዛብን ዘርቶ፣
እኩይ ምግባራትን እብሪትን አጥፍቶ፡፡
እ.ኤ.አ በ2015 የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ያቀረበው መረጃ ታማኝነት ያለው ከሆነ ካሩቱሪ የ170 ሚሊዮን ብር እዳን ከማሳየት በስተቀር ሊያሳይ የሚችለው ምንም ዓይነት ነገር በእጁ ላይ የለውም፡፡
ቃል ተገብቶለት የነበረው በአስር ሺዎች ሄክታር የሚቆጠረው የፓልም ዘይት፣ የሸንኮራ አገዳ፣ የሩዝ፣ የምግብ ዘይት፣ የበቆሎ እና የጥጥ ሰብል ምርት የት አለ? እንደዚሁም 60,000 ሰራተኞች የት አሉ? እነዚህ ሰራተኞች ሌላ በየትም ሳይሆን በወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ መሪዎች የቅዠት ምናብ ውስጥ ይገኛሉ፡፡
አምላክ እ.ኤ.አ በ2011 ለካሩቱሪ በባሮ (ኡፔኖ) ወንዝ ላይ የቀስተደመና ምልክት ሰጥቶት ነበር፡፡ ካሩቱሪ ግን በተሰጠው ምልክት እራሱን ለማዳን አልተጠቀመበትም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ካሩቱሪ በኪሳራ እሳት ላይ እየተለበለበ ይገኛል፡፡
ሌሎችም እንደዚሁ የመንደር ምስረታ እና በህዝቡ ላይ እልቂትን የሚያዘንቡ የሰብአዊ መብ ደፍጣጭ አምባገነኖች ምንም ነገር ሳይሳካላቸው ጉምን ዘግነው እንደሚቀሩ ልተነብይላቸው እወዳለሁ፡፡
ቻው፣ ቻው፣ ካሩቱሪያውያን/ት! ሄሎ! ከኢትዮጵያ ከጋምቤላ እንኳን በደህና ወደ ሀገራችሁ ተመለሳችሁ! እንኳን በጤና ወጣችሁ! ጤና ካለ ገንዘብ ይገኛልና! መጀመሪያ ለጤናችሁ!
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
የካቲት 17 ቀን 2007 ዓ.ም