
አንድነት የዘመነ የበኩር ልጅ ነው። እድሜውም 3 አመት ከአራት ወር ነው። ሲበዛ ያሳዝናል ። አባቱ ዘመነ፣ ከበርካታ ታሳሪዎች ጋር ወደ ፍርድ ቤት ሲገባ አባቱን ያየው አንድነት፣ ከእጄ አምልጦ ወደ አባቱ ሮጠ። አባቱን ግን አላገኘም። አባቱን ለማቀፍ የሮጠው ልጅ፣ ከፓሊሱ አልፎ አባቱን ሊያቅፍ አልቻለም። ቀድሞም ይህ ህጻን አይኑ እያየ አባቱን እየደበደቡ የወሰዱት ፓሊሶች ነበሩና የማይጋፋው ጉልበተኛ እንደገጠመው አውቋል።
ያችን ቅጽበት ሁሌ የምረሳው አይደለም። አንድነት አራዳን በጩኸት አቀለጣት። ዘመነን ለማየት የጓጓው አይናችን ዘመነን እረሳ። ተሸነፍን። እንባችን ግድቡን ጥሶ ፈሰሰ። አንዳንድ የመኢአድ አባላት በህጻኑ አንድነት ልባቸው ተነክቶ ድምጻቸው ከፍ ብሎ እስኪሰማ አለቀሱ። በግቢው የነበሩ ባለጉዳዮችም ሲያለቅሱ ተመልክቻለሁ ። እንዴት ልብ ይነካል ።
ዘመነ ምን ተሰምቶት ይሆን ? በዚህ ክስተት መሀል ዘመነን ባይኔ ፈለኩት። ሌሎች ያለቅሳሉ ። ዘመነ ግን ከአይኑ የሚፈስ እንባ የለም የሆነውን አይቷል። እንዴት አንጀቱ ቻለው ? ዘመነ ልጁን እንዴት እንደሚወደው አውቃለሁ ። ዛሬ እንዴት ቻለው? ምን አልባት እንባን ያላየሁት ወደ ውስጥ እያለቀሰ ይሆን ?
Keine Kommentare:
Kommentar veröffentlichen