Netsanet: የትግራይ ሕዝብንና የኢትዮጵያ ፓሊስን በኢትዮጵያዊያን ለማስጠላት የሚደረገው ጥረት ከሽፏል!

Donnerstag, 5. Februar 2015

የትግራይ ሕዝብንና የኢትዮጵያ ፓሊስን በኢትዮጵያዊያን ለማስጠላት የሚደረገው ጥረት ከሽፏል!

February 5, 2015
Patriotic Ginbot 7 Movement for Unity and Democracyህወሓት ንፁሀንን ለመደብደብ የሚያበቃ በቂ ክፋት ያለው ልዩ ጦር ሲያሰለጥን ቆይቷል። ይህን ልዩ ጦር የፓሊስን መለያ እያለበሰ ነውረኛ ሥራዎችን እንዲሠራ በማድረግ በአንድ በኩል ንፁሀንን የመጉዳት በሌላ በኩል ደግሞ ፓሊስን በሕዝብ የማስጠላት መንታ ግቦችን ለማሳካት ተጠቅሞበታል። ይህ ልዩ ጦር በአለፉት ጥቂት ሳምንታት ባዶ እጃቸው ለተቃውሞ በወጡ ነብሰ ጡር ሴቶች ላይ ሳይቀር ባሳየው ጭካኔ፣ በሰማያዊ እና በአንድነት ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች ላይ ባደረሰው ድብደባ መጠን እና ባካሄደው የግለሰብ ንብረቶች ዝርፊያ የሥርዓቱ ባህርይ ፈጽሞ ከሰውኛ ተፈጥሮ እየወጣ እንደሆነ አመላካች ነው። በእነዚህ ድብደባዎች ወቅት በትግራይ ተወላጆች ላይ የተለየ ትኩረት በማድረግ ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስባቸው ተደርጓል። በትግራይ ተወላጆች ላይ የተለየ ትኩረት የተደረገው በደብዳቢዎቹ የግል ውሳኔ ሳይሆን ከበላዮቻቸው በተሰጠ ትዕዛዝ ነው ብሎ አርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ያምናል።
በአርበኞች ግንቦት 7: እምነት መሠረት የፓሊስ ከፍተኛ አዛዦች ህወሓቶች ቢሆኑም አብዛኛው የሠራዊቱ አባል በህወሓት ዘረኛና ፋሽስታዊ አገዛዝ የተማረረ፤ የሥርዓቱ መለወጥ የሚፈልግና ሥርዓቱን ለመለወጥ የሚደረገውን ትግል የሚደግፍ ኃይል ነው። ስለሆነም ህወሓት የተለየ ጦር አሰልጥኖ የፓሊስ ልብስ በማልበስ ነውረኛ ወንጀል በማሠራት ፓሊስን ለማስጠላት የሚያደርገው ሴራ ሊጋለጥ ይገባል ብሎ ያምናል። የፓሊስ ሠራዊት አባላትም በስማቸውና በደንብ ልብሳቸው የሚደረገውን ደባ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ እንዲያጋልጡ አርበኞች ግንቦት 7 ያሳስባል።
ህወሓት እንደሚያስበው እና የኢትዮጵያም ሕዝብ እውነት አድርጎ እንዲቀበለው እንደሚፈልገው የትግራይ ሕዝብ በጅምላ የህወሓት አፍቃሪና ደጋፊ አይደለም። እንዲያውም በተፃፃሪው ህወሓት ከትግራይ ተወላጆች ልብ እየተነቀነ ነው። የትግራይ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ትሕዴን/ደምህት) ከትግራይ የበቀለ፤ ህወሓትን በአመጽ ለመፋለም የቆረጠ ኃይል ነው። አርበኞች ግንቦት 7 በትግራይ ውስጥ ብዙ ደጋፊዎች ያሉት መሆኑ የምናውቀው ሀቅ ነው። አረና ትግራይ ህወሓትን በሰላማዊ መንገድ ለመታገል የተነሳ ተሰሚነቱን በከፍተኛ ደረጃ እያደገ የመጣ እና አቶ አብርሀ ደስታን የመሰለ ወጣት ኢትዮጵያዊ የፓለቲካ መሪ ያወጣ ድርጅት ነው። ህወሓት አንድነት ፓርቲ ላይ የመረረ አቋም ከወሰደባቸው ምክንያቶች አንዱ በትግራይ ውስጥ ያለው ተቀባይነት በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ መምጣቱ ነው። ህወሓት የትግራይን ሕዝብ ከተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ በጅምላ ለማጣላት የሚያደርገው ጥረት ማክሸፍ ይኖርብናል ብሎ አርበኞች ግንቦት 7 ያምናል፤ ለዚህም ተግቶ ይሠራል። አርበኞች ግንቦት 7 ከትግራይ የዲሞክራሲ ኃይሎች ጋር በመተባበር ፀረ ህወሓት ትግል በትግራይ ውስጥ መቀጣጠል ይኖርበታል ብሎ ያምናል። በዚህም መሠረት ትግራይ የህወሓት መቀበሪያ የመሆኗ ጊዜ ሩቅ አይደለም።
በዘንድሮው የ2007 የሴራ ምርጫ አማካይነት ተድበስብሰው የመጡ እነዚህ ሁለት ክፋቶች ማለትም ፓሊስን በሕዝብ ማስጠላት እና የትግራይ ተወላጅ የሆኑ የዲሞክራሲ ወገንተኞችን ለይቶ ማጥቃት ከበስተጀርባቸው ያዘሉት እኩይ ዓላማ መጋለጡ መንገዳችን ያጠራልናል ብሎ አርበኞች ግንቦት 7 በጽኑ ያምናል። በአንድነትና በመኢአድ የተፈፀው የድርጅትና የንብረት ዘረፋም የዚሁ ፕሮጀክት አካል መሆኝ ግልጽ ነው፤ ነገ ተመሳሳይ ነገር በሰማያዊ ፓርቲም ላይ ይፈጽም ይሆናል።
በመሆኑ ከ2007 የሴራ ምርጫ ትሩፋቶች በትግራይ ሕዝብና በፓሊስ ሠራዊት ጀርባ የሚደረገው ደባ መጋለጡ ነው። ይህ ድል ጽኑ መሠረት እንዲይዝ ህወሓትንና የትግራይን ሕዝብ የመነጠል እና ፓሊስ የሕዝብ አጋር መሆኑን የማረጋገጥ ሥራዎችን አጠናክረን መሥራት እንዳለብን አርበኞች ግንቦት 7 ያሳስባል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ !

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen