Netsanet: አዲዮስ ምርጫ… አዲዮስ ሰላማዊ ትግል!!!

Freitag, 27. Februar 2015

አዲዮስ ምርጫ… አዲዮስ ሰላማዊ ትግል!!!

February 27, 2015
Tilahun Zaga | fikireyohanis@yahoo.com
በዓጼው ዘመን የነበሩ ደራስያን አብዛኛዎቹ በቀኝ እጃቸው ብዕር በግራ እጃቸው ስልጣን የጨበጡ ናቸው፣ በዚህም መሰረት የዘመኑ ሹም የሰራው ብቻ ሳይሆን በሩቁ በማንኪያ የነካው ወጥ ሁሉ ይጣፍጥለታል፣ ወጡ እንዳይጎረና ዙሪያውን ከበው የሚያማስሉ ብዙ ሊቄዎች ስላሉ ነው፣ የዚያ ሁሉ ወጥ አማሳይ እጅ ያረፈበት ወጥ ደግሞ በየትኛውም መመዘኛ ሲታይ ላይጣፍጥ አይችልም
ከዚህ በተቃራኒው ግን አንድ ነበልባል ብዕር በቀኝ እጁ የጨበጠ ግራ እጁ ግን ባዶ የሆነ የብዕር ሰው በስራዎቹ እሳት ጫሪ፣ አነጋጋሪ፣ የአብዮትን ማዕበል የሚቀሰቅሱና በዓጼው ቢባል በደርጉ በብዕሩ የተቀመጡበትን ወንበር አንቀጥቃጭ ጉበኛው አቤ ነበር፣ አቤ በቀኝ እጁ የያዘው ብዕር ብቻ ነው
አቤ በዚያን ዘመን የግሽ ዓባይ ጎርፍ ከገጠር አምጥቶ ከቀለጠው ከተማ የዶለው ብቸኛ ፍጡር ነው፣ ብዕሩ በገነተ- ልዑል ግቢ ገብቶ ያልተሟሸ ይልቁንም በደረቅ የገጠር ቅኔ ቤት ተስሎ የወጣ፣ ቃላቱም ቱባ አገራዊና ሸካራ ለባለስልጣናቱም ጎርባጣ እንጂ ቤተ መንግስታዊ ለስላሳ አልነበሩም
ይህን ጽሁፍ ከላይ ለጠቀስኩት ርዕስ ማስተካከያ ደርዝ እንዲሆን አንድ ጸሃፊ ስለ አቤ ጉበኛው ከጻፉት መጣጥፍ የተዋስኩት ሲሆን በርዕሱ እንዲሁም በመግቢያው ላይ በጨረፍታ ለማሳየት እንደሞከርኩት የአምባገነኖች የዘመን ፍጻሜ ሲቃረብ ብዕረኞች የመድፈኞች ያህል ይገናሉ፣ ጋዜጠኞች የታንከኞች ያህል ያስተጋባሉ፣ ጸሃፊዎች የሮኬት ተኳሾች ያህል አቧራውን ያስነሱታል
እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ በሃገራችን ብቻ ሳይሆን በአብዛኛው ተራማጅ በሚባሉ ክፍለ ዓለማት ባሉ ህዝቦች ዘንድ የተሞገሰ እንቅስቃሴ ነበር፣ እንቅስቃሴው ተራማጅ ብቻ ሳይሆን የሶሻሊስት ርዕዮት አቀንቃኝ ነበር፥ ከብዙ የህቡዕና አንዳንዴም የግልጽ ተቃውሞ እንቅስቃሴዎች በኋላ የዓጼውን ስርዓት ስር ከስር ቦርቡሮ የጣለው ይህ የተማሪዎች አብዮት እንደሆነ ይታመናል፥ ይህን የተማሪዎች አመጽ ተከትሎ ከገዥው ስርዓት ይሰጡ የነበሩ መልሶች ለምላሹም ይሰጡ የነበሩት አጸፋዊ መልሶች እና ጉልበት ላይ ብቻ ያተኮሩ የዓጼው ባለሟሎች እርምጃዎች ተማሪውን ወደእልህና ቁጭት የገፉ ናቸው
ይልቁንም ህቡዕ የነበሩ የእንቅስቃሴው አራማጆች በገሃድ እየወጡ ስርዓቱን መቃወማቸው የየዩኒቨርሲቲዎች ዓመጽ፣ የአውሮፕላን ጠለፋዎች፣ የመሬት ላራሹ ድምጾችና ሌሎችም፥ ዓጼውን ያደናበሩ በእውር ድንብር ይወሰዱ የነበሩ ግብታዊ እርምጃዎችም ትግሉን ከፍ ወዳለ ደረጃ ያሳደጉ ነበሩ
የዓጼው ስርዓት የመጨረሻው መጨረሻ ሲቀርብም ሁኔታውና ሂደቱ ያስፈራቸው ባለጊዜዎች በተለያዩ ጊዜያት ጠቋሚ ጽሁፎችን ያሰፈሩበት ሁኔታ እንደነበር ታሪክን ያስታውሷል፥ በዓጼው ስርዓት ገዥ ወንበር ላይ የነበሩት ጄነራል አቢይ አበበ በ19 መቶ 55 ለህትመት በበቃች አነስተኛ መድብላቸው አውቀን እንታረም ሲሉ የስርዓቱን ማብቃት የጠቆሙ ቢሆንም የዓጼው አገዛዝ ከገባበት ቀውስ ለመውጣት የሞከረበት አጋጣሚ እምብዛም ነበር
ጄነራል አቢይ በመጽሃፋቸው መግቢያ የህይወትን ምሬትና ጣፋጭነት በብዙ ከተነተኑ በኋላ፣ ድካማችን ለሃገራችንና ለመጪው ትውልድ ነው የሚል ሞልቶ ይሆናል . . . ሲሉ ይቀጥላሉ ይህን መናገር የሚገባው በአንድ የትውልድ ዘመን አብሮት ላለው ጓደኛው የሚያስብ አእምሮ ያለው ሰው መሆን አለበት፣ እንደሚታየው ከሆነ ድካማችን ለየግል ፍላጎታችን ሆኖ የድካማችንን ፍሬ በልቶ መሞት ብቻ ነው፣ ሞታችንም ቅጣታችን ነው እስከዚያው ድረስ ግን ግንብ በሌለው . . . ዘበኛ በማይጠብቀው ክፍት ወህኒ ቤት ውስጥ ሆነን እንደልባችን እየተቀናጣን፣ ለምኞታችን እየተገዛን ምንም የሚደርስብን አይመስለንም፣ ጊዜው በደረሰ ጊዜ ግን አይተነው የማናውቀው የብረት አጥር በዙሪያችን እንደነበረ ይከሰትልናል . . . ትልቁም የብረት በር እፊታችን ተደቅኖ ይታየናል፣ ያን ጊዜ መንጥቆ የሚያስወጣንም ዘበኛ ይገለጣል በአጠገባችንም ይንጎራደዳል፣ እንደከብት ስናግድ እና ስንታገድ የኖርንባትና ለማዳዎቹ አውሬዎች የሰባንባት መሬት ተራዋን ልትበላንና ሰብታም ሌላውን ለመመገብ አፏን ከፍታ ትቀበለናለች፣ ከዚህ የሚያድነን የለም. . ተመልሰን ልንወጣ አንችልምና የኛም ተራ በዚሁ ይወሰናል ሲሉ ጽሁፋቸውን መጪውን የህዝብ የቁጣ ዘመን በማሳሰብ ይቀጥላሉ
ሆኖም ግን ይህንና ሌሎች ህዝባዊ ጥያቄዎችን መመለስ ያልቻለው የዓጼው ስርዓት ጊዜው ደርሶ በ66ቱ የመረረ አመጽ ሲደረመስ፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ከሚታወቁትና በደርግ ወደ እስር ከተጋዙት እንዲሁም በጅምላ ከተረሸኑት 60ዎቹ ሚኒስቴሮች ውስጥ አስቀድመው አውቀን እንታረም ብለው የተናገሩት ጄነራል አቢይ አበበ አንዱ ናቸው
ከዚህ ትምህርት ያልወሰደው ደርግም በመጨረሻዎቹ የስልጣን ማገባደጃ ዘመኑ ቀድሞም ቢሆን ለዓይን ሙሉ ያልነበሩ ጸሃፍትን እያደነ መረሸን፣ እያፈነ መሰወር ስራዬ ብሎ ተያያዘው
እልም ባለ አጠቃላይ ሃገር አቀፍ ቀውስ ውስጥ የተዘፈቀው የደርግ መንግስት የወንበዴዎች ሃይልና ሴራ ማየል፣ የየጦር ክፍል አዛዦች መከፋፈል እንዲሁም ሃገሪቱ የተዘፈቀችበት ቅጥ ያጣ ሶሺዮ-ኢኮኖሚካል ቀውስ፣ ሃገሪቱን አልፎም ቀጠናውን ሙሉ በሙሉ የጦር አውድማ ያደረገ ነበር
እዚም እዚያም ሃገራዊ ግዳጆች፣ እዚም እዚያም አፈሳና የወጣቶች ትርምስ፣ እዚም እዚያም የጦርነት ድምጽና የግደል ተጋደል ዘመቻዎች ብዛት የደርጉ መንግስት የለት ተቀን የቤት ስራዎች ሆነው የነበዓሉ ግርማ “ኦሮማይ“ በወቅቱ ያለሰሚ ቢዳፈንም ውለው አድረው ግን በባለስልጣናቱ ጆሮዎች ላይ ማቃጨላቸው አልቀረም፣ የሆነው ሆኖ ግን በመጨረሻው መጨረሻ የሆነው ለዓጼው በተማሰው የጠለቀ ጉድጓድ መግባት ነበር፣ ከ1960ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ በከፍተኛ ትጋት በከፍተኛ ትጋት የተማሰው ጉድጓድ አሁንም የሞላ አይመስልም፣ ምናልባትም አሁን ያሉትን ዘረኝነት ያሳበዳቸውን ጎርሶ የሚደፈን ከሆነ ጊዜ የሚያሳየን ይሆናል
አሁንም ከነዚህ ስርዓቶች ያልተማረው ህወሃት/ኢህአዴግ በመጨረሻው መጨረሻ ሰዓት እንኳ የሚጮሁትን የጣር ድምጾች፣ የሚያቃጭሉትን የማንቂያ ደወሎች ባለመስማት በየዕለቱ እየከፋ የሄደ ስርዓት መሆኑን እያሳየን ነው
የሰላና የተባ ብዕር ያላቸው ጸሃፊያን የእስር ቤት ግዞት፣ የነጻነት ጠያቂ ዜጎች የጅምላ ግድያ እና ሌሎች ሃገራዊ ስቃዮች ያላነቁት ህወሃት/ኢህአዴግ ህዝባዊ እንቅስቃሴዎችንና የመብት ጥያቄዎችን በሃይል ለመደፍጠጥ እየሄደበት ያለው መንገድ፣ ሩቅ የማይወስድና ምሪቱም ወደማይቀረው የተማሰ ጉድጓድ መሆኑን የተረዳው አይመስልም
በሃገራችን የተንሰራፋውን ጭቆና፣ የመብት ጥሰትና፣ ፍትህ አልባነትን ስንመለከት የህዝብ አብዮት ለመከሰቱ ምንም ጥርጥር እንዳይኖረን ያደርጋል፣ እንዲህ አይነቱ በገነገነ እምቅ የቁስል ስሜት የሚቀሰቀስ አብዮት ውጤቱ ምን ሊመስል እንደሚችል ሰሚ ጆሮ ካላቸው ሩቅ ዘመን ሳይሄዱ እነጋዳፊና ሙባረክ ላይ የሆነውን ማየት ይቻላል
አዲዮስ ምርጫ፣ አዲዮስ ሰላማዊ ትግል
የነጻነት መንገዶችን ሁሉ ቀርቅቦ የዘጋው ህወሃት/ኢህአዴግ፣ ምናልባትም ትንሽ ቀዳዳ ካገኘን ብለው በሃገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ህልውናቸው የመጨረሻው የገደል ጫፍ ላይ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ እንደ አንድነት ያሉ በሰላማዊ የትግል ስልት የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሻሞ. . .ሻሞ ተወርውረው ለታማኞች መሰጠታቸውና ህልውናቸው መክሰሙን ስናይ ሌሎችም ባለሳምንቶች መኖራቸውን ለመናገር ነቢይ መሆንን አይጠይቅም፣ የነጻነት መንገዶች ሲዘጉ የአመጽ መንገዶች ወለል ብለው እንደሚከፈቱ አለማወቅ፣ ታሪክን ብቻ ሳይሆን ለነባራዊና ተጨባጭ ኩነቶች ዓይኖችን ማሳወር ነው፣ ስለዚህም አዲዮስ ምርጫ፣ አዲዮስ ሰላማዊ ትግል!!!

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen