Netsanet: ጦማርያኑና ጋዜጠኞቹ ሰብሳቢ ዳኛው ላይ ያቀረቡት አቤቱታ ውድቅ ተደረገ

Donnerstag, 5. Februar 2015

ጦማርያኑና ጋዜጠኞቹ ሰብሳቢ ዳኛው ላይ ያቀረቡት አቤቱታ ውድቅ ተደረገ



በላይ ማናዬ

በእነ ሶልያና ሽመልስ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ የሚገኙት የዞን ዘጠኝ ጦማርያን እና ጋዜጠኞች ሰብሳቢ ዳኛው የተፋጠነ ፍትህ የማግኘት መብታችንን አላስከበሩልንም በሚል ከችሎት እንዲነሱ የጠየቁበት አቤቱታ ውድቅ ተደረገ፡፡ 
ዛሬ ጥር 28 ቀን 2007 ዓ.ም ለ19ኛ ጊዜ የፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት የቀረቡት ጦማርያኑና ጋዜጠኞቹ ጥር 26 ቀን 2007 ዓ.ም በጽሑፍ ያቀረቡት አቤቱታ በፍርድ ቤቱ ውድቅ ተደርጓል፡፡ 
ፍርድ ቤቱ የተከሳሾችን አቤቱታ በንባብ ያሰማ ሲሆን፣ አቤቱታውን ሁለቱ ቀሪ ዳኞች (ሰብሳቢ ዳኛው በሌሉበት) እንደመረመሩት በመግለጽ ብይናቸውን በንባብ አሰምተዋል፡፡ በብይኑ መሰረትም ተከሳሾች ሰብሳቢ ዳኛው ከችሎት ይነሱልን የሚለውን አቤቱታ ፍርድ ቤቱ አልተቀበለውም፡፡ 
ተከሳሾች አቤቱታውን ምክንያት ላይ ተመርኩዘው ቢያቀርቡም፣ ውሳኔዎቹ የተሰጡት በሦስቱ ዳኞች መሆኑን በመግለጽና የቀረቡት ቅሬታዎች በማስረጃ ያልተደገፉ ናቸው በሚል ሰብሳቢ ዳኛው ላይ የተነሳው አቤቱታ ተቀባይነት የሌለው ነው ብሏል ፍርድ ቤቱ፡፡
ስለሆነም ሁለቱ ዳኞች ብይኑን አሰምተው ሲጨርሱ ችሎቱ ሰብሳቢ ዳኛው ባሉበት እንደሚቀጥል በመግለጽ ተሟልተው እንደገና ለመግባት ሁለቱ ዳኞች ከችሎት ወጥተዋል፡፡ በመቀጠልም ሰብሳቢ ዳኛውን ይዘው ተመልሰው በችሎት እንደገና ተሰይመዋል፡፡ 
ከአጭር ቆይታ በኋላ ሦስቱም ዳኞች እንደገና መሰየማቸውን ተከትሎ ተከሳሾች የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ ይደረጋሉ የሚል ግምት የነበር ቢሆንም ሰብሳቢ ዳኛው ‹‹ሁለቱ ዳኞች በእኔ ላይ የቀረበውን አቤቱታ መርምረው በችሎት እንድቆይ ብይን ቢሰጡትም፣ በግሌ እንዲህ አይነት ቅሬታ እየቀረበብኝ እያለ የምሰጠው ውሳኔ አመኔታን ስለማያገኝ በግሌ ከዚህ ችሎት መነሳት እንደምፈልግ ማመልከቻ አስገብቻለሁ፡፡ ስለሆነም ተከሳሾች አዲስ ዳኛ ሲመደብላቸው ቃላቸውን ቢሰጡ ይሻላል›› በማለታቸው ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጥ ተወስኗል፡፡
በዚህ መሰረትም በአዲስ ሰብሳቢ ዳኛ ተከሳሾች የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ በሚል ለየካቲት 11 ቀን 2007 ዓ.ም ጠዋት ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡ 
በሌላ በኩል 7ኛ ተከሳሽ የሆነው ጦማሪ አቤል ዋበላ በትናንትናው ዕለት ከፍርድ ቤት ወደ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት በመኪና ሲመለስ ጀምሮ በማረሚያ ቤት ፖሊስ የመብት ጥሰት እንደተፈጸመበት አቤቱታ አቅርቧል፡፡
አቤል በፖሊስ ከፍተኛ ዛቻና ማስፈራሪያ እንደተፈጸመበትና ማታ ላይም በሰንሰለት ታስሮ እንዳደረ ለችሎቱ አስረድቷል፡፡ በተጨማሪም አቤል በማዕከላዊ ምርመራ በነበረበት ወቅት በደረሰበት ድብደባ ጆሮው በመጎዳቱ የጆሮ ማዳመጫ ያደረገውን እንደነጠቁት አስረድቷል፡፡ ፍርድ ቤቱም አቤቱታው በጽሑፍ እንዲቀርብና በሚቀጥለው ቀጠሮ ማረሚያ ቤቱ መልስ እንዲሰጥበት ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen