Netsanet: የትናንቱ የ”አይ ኤስ ኤስ” በግብፅ ክርስቲያኖች ላይ የፈፀመው አሰቃቂ ግድያ ከኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካ አንፃር ምን ያመላክተናል?

Dienstag, 17. Februar 2015

የትናንቱ የ”አይ ኤስ ኤስ” በግብፅ ክርስቲያኖች ላይ የፈፀመው አሰቃቂ ግድያ ከኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካ አንፃር ምን ያመላክተናል?

ኢትዮጵያን ከ”አይ ኤስ ኤስ” እና ”ግልገሎቹ” ለማዳን መፍትሄው ምንድነው? (የጉዳያችን ልዩ ማስታወሻ)

‘አይ ኤስ ኤስ’ ባለፈው ዓመት ያወጣው አዲሱ ካርታ
isismap2ትናንት የካቲት 8/2007 ዓም እኩለ ሌሊት ላይ ”ሮይተርስ” በሊብያ በ”አይ ኤስ ኤስ” (ISS) የታገቱት ሃያ አንድ የግብፅ ክርስቲያኖች በአሰቃቂ መንገድ መገደላቸውን፣የአገዳደሉንም ቪድዮ በአሸባሪው ድርጅት መለቀቁን እና የግብፅ ኮፕት ቤተ ክርስቲያንም ድርጊቱ መፈፀሙን ማረጋገጧን ጠቅሶ የዘገበው ዜና ብዙዎቻችንን አሳዝኗል።ይሄው በ ”ሜጫዊ”(ክርስቲያን በመሆናቸው ብቻ በሰይፍ የመቅላት አባዜ) አስተሳሰብ አራማጅነቱ የሚታወቀው ቡድን እንደ ‘አሜባ’ እራሱን እየለጠጠ ከኢራቅ እስከ ሶርያ ከሶርያ እስከ ሊብያ እየተስፋፋ ነው።አለማችን ለአሸባሪ ተግባሮች አዲስ ባትሆንም በእንዲህ አይነት ሕብረ-ብሔራዊ ባህሪ ያለው እና የመካከለኛው ምሥራቅን እና የምስራቅ አፍሪካን ማኅበራዊ እና መልካ-ምድራዊ አቀማመጥ የደም ጎርፍ በማፍሰስ ለመቀየር መነሳቱን በአደባባይ በማወጁ ቡድኑን ከሌሎች አሸባሪዎች ይለየዋል።
ቡድኑ ኢትዮጵያን እና ኤርትራን ሙሉ በሙሉ ባካለለ መልኩ የሰሜን አፍሪካን እና የአውሮፓ ከፊልን ጨምሮ አዲስ ካርታ ማውጣቱን እና የሚታገለውም ከእዚህ አንፃር እንደሆነ በተዳጋጋሚ ይገልፃል።ይህንን አላማውን ለማሳካት በሀገሮች ውስጥ ያሉት ፖለቲካዊ፣ማህበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ሁኔታዎች ለእንቅስቃሴው ግብአትነት እንደሚጠቀምበት የታወቀ ነው።
ከእዚህ በተጨማሪ መገንዘብ ያለብን ቡድኑ ሁለት መሰረታዊ ነገሮችን መሰረት ያደረገ ነው።አንደኛው እና ቀዳሚው ክርስቲያን የተባለ ሰው የሆነ ፍጥረትን መግደል ሲሆን በእዚሁ መስመር የግዛት ስፋቱን ማስፋፋት ነው።እነኝህን ተግባራት የሚፈፅመው ደግሞ የቀደሙ ታሪኮችን በሙሉ በመደምሰስ የእራሱን የ”ሜጫዊ” ወይንም በሰይፍ የመቅላት አባዜ መመርያው ያደርጋል።የእዚህ አይነቱ አስተሳሰብ በግልገል ተከታዮቹ በሀገራችን የፖለቲካ መድረኮች በተለይ በባህር ማዶዎቹ ግልገሎች ላይ መንፀባረቁን ልብ ይሏል።
ከፍተኛ ውድመት ያደረሱት ሁለቱ የውጭ እስላማዊ ፅንፈኛ እንቅስቃሴዎች
ከኢትዮጵያ አንፃር የእዚህ አይነቱ ፅንፈኛ እንቅስቃሴ በሁለት ታሪካዊ ወቅቶች ጎልቶ ወጥቷል።የመጀመርያው በ16ኛው ክ/ዘመን ቱርክ ወደ አፍሪካ የባህር ዳርቻዎች ይዞታዋን ባጠናከረችበት ወቅትሲሆን ሁለተኛው የአረቡ ዓለም የነዳጅ ዘይት ካገኘበት ከ 1960ዎቹ ወዲህ ነው።በሁለቱም ወቅቶች ኢትዮጵያ ላይ እጅግ ከፍተኛ ጉዳቶች ደርሰዋል።እዚህ ላይ ሁለቱም የታሪክ ክስተቶች መነሻ ያደረጉት የውስጥ ፖለቲካዊ ጉዳያችንን በማጦዝ መሆኑን መዘንጋት አይገባም።
ከሁለቱ የታሪክ ክስተቶች ውስጥ የመጀመርያው የቱርክ መንግስት ወደ አፍሪካ የባህር ዳርቻዎች ያሉት ይዞታዎቹን ያጠናከረበት ወቅት ስንመለከት ቱርክ ቀደም ብላ የደቡብ ምስራቃዊ እና ምስራቃዊ አፍሪካን በንግድ እና ህዝቦችን በግድ ወደ እስልምና በመቀየር ተግባር ብትታወቅም በኢትዮጵያ ግን እጇን ያስገባችበት ሂደት ከውስጥ የተነሳውን ቅራኔ በቀጥታ በመደገፍ መሆኑን እንመለከታለን። ይሄውም ከሀገራችን ምስራቃዊ ግዛት የተነሳው በታሪክ ”የግራኝ መሐመድ እንቅስቃሴ” ቱርክ በወታደራዊ፣በቁሳቁስ እና በሞራል ድጋፍ በማድረግ ግንባር ቀደም ነበረች።በወቅቱ ኢትዮጵያ በታሪክ ከደረሰባት የጥፋት መዓት በላይ በቀዳሚነት ክርስቲያኖች ደማቸው እንደ ጎርፍ የወረደበት፣አብያተ ክርስቲያናት እና ቅርሶች የተቃጠሉበት፣’ማኅበራዊ ጀሃድ’ የተፈፀመበት የጥፋት ዘመን ሆኖ አልፏል።በተለይ ከግራኝ መሐመድ ወረራ በኃላ ኢትዮጵያ በሰሜን ምፅዋ ተከትሎ እስከ ቀድሞዋ አፋር እና ኢሳ (የዛሬዋ ጅቡቲ) ድረስ ያለው ከአንድ ሺህ ኪሎሜትሮች በላይ የሆነው ግዛቷ በተለያዩ ለቱርክ ባደሩ ሱልጣኖች እና በቱርኮች በቀጥታ መጠቃት የተባባሰበት ወቅት ነበር።
ሁለተኛው በኢትዮጵያ ላይ ጉዳት ያደረሰ የፅንፈኛ የእስልምና እንቅስቃሴ ከ1950ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ እጁን የከተተው ኃይል ነው።በተለይ ይህንን ወቅት አደገኛ የሚያደረገው በቀጣዩ አስር አመታት ውስጥ የአረቡ ዓለም በነዳጅ ሀብት የተንበሸበሸበት ወቅት ከመሆኑ አንፃር በሀገራት ላይ ተፅኖ የመፍጠር አቅሙ በእጅጉ በማደጉ ነበር።በእዚህ ወቅት ነበር የኤርትራ በፌድሬሽን ከኢትዮጵያ ጋር መዋሃድ በተባበሩት መንግሥታት መፅደቁ እና ያንን ተከትሎ በኤርትራ ሕዝብ እንደራሴዎች ከፍተኛ ጉትጎታ ፌድሬሽኑ መፍረሱ (‘የኤርትራ ጉዳይ” አምባሳደር ዘውዴ ረታ The Eritrean Affair (1941-1963) by Ambassador Zewde Retta) ኤርትራ ከጥንትም አብራ ከነበረችው ኢትዮጵያ ጋር መሃዷን ተከትሎ ”ጀብሃ” በአረብ ሃገራቱ ከፍተኛ የገንዘብ፣የቁሳቁስ እና የሰው ኃይል ድጋፍ ተመሰረተ።በቀጣዮቹ ጊዜያት ”ሻብያ” ጀብሃን ካባረረ በኃላም ሆነ ”ህወሓት” እና ”ሻብያ” በጥምር ከደርግ ጋር ባደረጉት ውግያ የመካከለኛው ምስራቅ አረብ ሃገራት እርዳታ አልተለያቸውም።እዚህ ላይ እርዳታዎቹ ዋና አላማቸው ኤርትራን አረባዊ ሀገር ማድረግ እና ኢትዮጵያን በሂደት በእዚሁ ተፅኖ ስር እንድትወድቅ ማድረግ ነው።
እዚህ ላይ የደርግ አምባገነን ስርዓት ለሕዝብ ተቃውሞ በቂ ምክንያት አልነበረም ለማለት ባልደፍርም ማጉላት የምፈልገው ጉዳይ ግን በማናቸውም የኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የአረብ ሃገራቱ ዘሎ መግባት በተለይ ኢትዮጵያ የውስጥ ቅራኔዋን እንዳትፈታ የራሱን ጥላ አጥልቷል።እዚህ ላይ አቶ ኢሳያስ የኤርትራን ጥያቄ በመገንጠል ደረጃ ማስቀመጥ ከአረብ ሃገራት ለሚገኝ እርዳታ ቅድመ ሁኔታ እንደነበር ብዙዎች ይስማሙበታል።እዚህ ላይ የቀድሞ የህወሓት ሥራ አስፈፃሚ እና የፋይናንስ ክፍል ኃላፊ የነበሩት አቶ ገብረ መድህን አርአያ በጦርነቱ ወቅት ከኢራቁ ሳዳም ሁሴን እና ከሊብያው ጋዳፊ አይሮፕላን ሙሉ መሳርያ እና ቁሳቁስ ይሰጣቸው እንደነበር ኢሳት ቴሌቭዥን ቀርበው መናገራቸውን መጥቀስ ብቻ ይበቃል።
ሆኖም ግን ያለፉት ሃያ አመታት ያሳዩን ጉዳይ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ተለያይተው መኖር የማይችሉ ይልቁንም ጉዳዩን የቅኝ ግዛት ግንኙነት ነበራቸው የሚለው ተረታ ተረት ዘመን በሄደ ቁጥር ሐሰትነቱ ፍንትው ብሎ እየታየ መሆኑን ነው።ለእዚህም ይመስላል አቶ ኢሳያስ ሰሞኑ በኢሳት ቴሌቭዥን ”የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ጉዳይን እንዴት ይመለከቱታል?” ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ጉዳዩን ”ወደ አንዳንድ የታሪክ መፋለሶች” (historical distortion) ደረጃ ለማውረድ የተገደዱት።ለእዚህም ምክንያቶቹ አንድም ካለፈው ታሪክ ከመማር አልያም አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ ህብረት እና አንድነት ብቻ የሚያድነው መሆኑን ከመረዳት ይሆናል።
ከ”አይ ኤስ ኤስ” እና ግልገሎቹ ኢትዮጵያን ለማዳን መፍትሄው ምንድነው?
አሁን ያለው ወቅት ኢትዮጵያውያንም ሆኑ ከመረብ ማዶ ያሉ የኤርትራ ምድር ህዝቦች አዲስ የፖለቲካ ራዕይ መመልከት ያለባቸው ወሳኝ ወቅት ነው።በተለይ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የጎሳ ፖለቲካ ለዓለም አቀፍ ፅንፈኛ እንቅስቃሴ ምቹ የሆነ እና ኢትዮጵያን እንደሀገር ለማስቀጠል ፈፅሞ ፍላጎት እንደሌለው በተለያዩ ድርጊቶቹ ያረጋገጠ ነው።
የህወሓት የፖለቲካ መመርያ፣ጎሳዊ የምጣኔ ሀብት አደረጃጀቱ እና በታሪክ ላይ ያለው የተፋለሰ አስተያየት ሁሉ አሁን በሕይወት ካለነው ዜጎች ብቻ ሳይሆን ከመጪው እና ካለፉት ጋር ሁሉ የተቃረነ ነው።ይህ ሁኔታ ደግሞ ተወደደም ተጠላ ኢትዮጵያን ወደ አንድ አይነት ውስጣዊ ቅራኔ መምራቱ ሳይታለም የተፈታ ነው።ሆኖም ግን ቅራኔው በሕዝብ እና እራሱን በተደጋጋሚ ጊዜ እንዲያርም ዕድል የተሰጠው ህወሓት መካከል መሆኑን መዘንጋት አይገባም።ኢትዮጵያን ለማዳን እና እንደ ”አይ ኤስ ኤስ” እና ግልገሎቹ ለመታደግ አይነት አደጋ ለመታደግ የህዝብ አንድነት፣ኢትዮጵያዊ መንግስት እና ራዕይ ያለው መሪ የፖለቲካ መዋቅር እጅግ ያስፈልጋል።አሁንም ይህንን በህወሓት ስር ባለች ኢትዮጵያ ውስጥ ፈፅሞ አይታሰብም።ለእዚህ ነው ”ኢትዮጵያ በፍጥነት ዲሞክራስያዊት ሀገር መሆኗ ለእራሷ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ቀንድ ብሎም ለመላው አፍሪካ ወሳኝ ነው” ሲል ለአሜሪካ የውጭ ፖሊሲ ግብዓት የተዘጋጀ ጥናታዊ ፊልም አበክሮ ያሳሰበው።
ባጭሩ ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን ከመረብ ማዶ ያሉ ኢትዮጵያውያንም በዓለም አቀፉ የፅንፈኛ እንቅስቃሴ ታልቅ አደጋ ላይ ናቸው።ይህንን አደጋ ለመከላከል የቤት ስራው የሚጀምረው ከውስጥ ነው።መጀመርያ ውስጣችን ያለው የጎሰኛ ስርዓት ከእነ አሰራሩ ሙሉ በሙሉ መነቀስ አለበት።ቀጥሎ ኢትዮጵያ ታሪካዊ፣ፖለቲካዊ፣ማጣኔ ሃብታዊ እና ማህበራዊ ቦታዋ በአግባቡ የሚያስጠብቅላት መንግስት ያስፈልጋታል።ይህንንም ከመረብ ማዶ ያሉትም በአግባቡ ሊገነዘቡት እና ላለፉት 40 ዓመታት በአንዳንድ አረብ ሃገራት የታለሉትባቸውን መንገዶች በሙሉ በውል ሊያጠኑት ይገባል።በኢትዮጵያ ተቃዋሚ ኃይሎች እና አቶ ኢሳያስ መካከል ያለው መናበብም አስፈላጊ ያምያደርገው ከእዚህ ሁሉ አንፃር ነው።ጉዳዩ ከስልታዊ ግንኙነት በዘለለ ታሪካዊ እውነታን ያገናዘበ መሆን እንደሚገባውም የሚሰመርበት ለእዚህ ነው።የምዕራቡ ዓለም በቀዳሚነት የፅንፈኛ እንቅስቃሴ አደጋ የመሆን ዕድል ኢትዮጵያ እንዳላት ይገነዘባል።ለእዚህም ህወሓት ከሕዝቡ ጋር የተጣላ መንግስት ከመሆኑ አንፃር ኢትዮጵያን አይደለም እራሱንም መከላከል የማይችልበት ወቅት እሩቅ አይደለም።ስለዚህ የአንድነት ኃይሎች መጠናከር ብቸኛ መንገድ መሆኑ ከፍተኛ ግንዛቤ ተወስዶበታል።በመሆኑም የአይ ኤስ ኤስን አደጋ ስንመለከት መጀመርያ የቤታችንን ጉዳይ በፍጥነት ማስተካከል እንዳለብን ግንዛቤ እንዳይጎለን።ጉዳዩ ሁሉ ከጊዜ ጋር ነውና።
ጉዳያችን GUDAYACHN
የካቲት 9/2005 ዓም (February 16/2015)

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen