Netsanet: ሰማያዊ የምርጫ ቦርድ የፓርቲዎች ሚዲያ አጠቃቀም ድልድል ፍትሃዊ አለመሆኑን አስታወቀ

Montag, 2. Februar 2015

ሰማያዊ የምርጫ ቦርድ የፓርቲዎች ሚዲያ አጠቃቀም ድልድል ፍትሃዊ አለመሆኑን አስታወቀ

ሰማያዊ ፓርቲ የምርጫ ቦርድ ያወጣው ረቂቅ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ውድድር የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ሰዓት አጠቃቀም ድልድል ፍትሃዊና በእኩልነት ላይ የተመሰረተ አለመሆኑን አስታወቀ፡፡
ዛሬ ጥር 25 ቀን 2007 ዓ.ም የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሀገር አቀፍ ፓርቲዎችን በረቂቅ የሰዓት ድልድሉ ላይ ጊዮን ሆቴል ጋብዞ ውይይት አድርጓል፡፡ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢብኮ) ኃላፊዎች ረቂቁን ለውይይት ያቀረቡ ሲሆን፣ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ እና ሌሎች ኃላፊዎችም በውይይቱ ተገኝተዋል፡፡
የኢብኮ ኃላፊዎች ባቀረቡት የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚዲያ አጠቃቀም ረቂቅ ድልድል መሰረት 55 ፐርሰንት በፓርላማ መቀመጫ ወንበር ላላቸው ፓርቲዎች፣ 20 ፐርሰንት ፓርቲዎቹ በሚያቀርቧቸው ዕጩዎች ብዛት እንዲሁም ቀሪ 25 ፐርሰንቱ ለሁሉም ፓርቲዎች በዕኩል የሚከፋፈል እንደሆነ ተገልጹዋል፡፡
ሰማያዊ ፓርቲን በመወከል በውይይቱ ላይ የተገኙት የፓርቲው የህግ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ይድነቃቸው ከበደ ለነገረ ኢትዮጵያ እንደገለጹት፣ ረቂቅ የሚዲያ አጠቃቀሙ ድልድል ሲወጣ እንደ መስፈርት የተጠቀሙባቸው ነጥቦች ችግር ያሉባቸው ናቸው፡፡
‹‹በእኛ እምነት መስፈርቱም ልክ አይደለም፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ የሚዲያ ሰዓት አጠቃቀም ድልድል ሲወጣ ሁለት መስፈርቶች በቂና ትክክለኛ ናቸው ብሎ ያምናል፡፡ እነዚህ ነጥቦች በሚቀርቡ እጩዎች ብዛት እና በእኩልነት የሚከፋፈል የድልድል መስፈርት መሆን አለባቸው›› ብለዋል አቶ ይድነቃቸው፡፡
በእርግጥ ረቂቁን ያቀረበው ኢብኮ እንደ መመዘኛ መስፈርት የተጠቀመው ‹‹እኩልነትና ፍትሃዊነት›› የሚሉ መርሆዎችን ነው፡፡ ‹‹ኢብኮ በቃላት ደረጃ የገለጻቸው ‹ፍትሃዊነትና እኩልነት› በተግባር ረቂቅ ድልድሉ ላይ አልታዩም፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ በእኩልነትና ፍትሃዊነት መርሆዎች ላይ ችግር የለበትም፡፡ መርሁን መሰረት አድርጎ ወጣ የተባለው የሚዲያ ድልድል መጠን ግን በትክክል መርሁን የተከተለ አይደለም፡፡ ስለሆነም ለውጥ ሊደረግበት ይገባል›› ብለዋል አቶ ይድነቃቸው፡፡
አቶ ይድነቃቸው የሰዓት አጠቃቀም ድልድሉ ላይ ስንወያይ ነጻ ሚዲያ በሌለበት፣ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት በተገደበበት፣ ጋዜጠኞች በታሰሩበትና በተሰደዱበት፣ አማራጭ የሚዲያ ተቋማት በሌሉበት በዚህ አጣብቂኝ ወቅት ላይ በህዝብ ሀብት በሚተዳደሩ ሚዲያዎች ላይ የፍትሃዊነት ችግር ይዘን መወያያታችን አሳዛኝ ነው ብለዋል፡፡ ‹‹ሳንሱር በህገ-መንግስቱ ተነስቷል፤ ይሁን እንጂ ኢብኮ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለያዩ ጊዜያት ለህዝብ የሚያስተላልፏቸው አማራጭ ሀሳቦችና ፖሊሲዎቻቸውን በቆርጦ ቀጥል ሲያዛባ እናስተውላለን፤ ይህ ሁኔታ መወገድ ያለበት ነው፡፡››
በውይይቱ ላይ ኢህአዴግ የድልድሉ መስፈርት ላይ እንደሚስማማ በመግለጽ፣ በፐርሰንቱ የተቀመጠው መጠን ላይ ግን መሻሻል እንዲደረግ እንደሚፈልግ መግለጹ ታውቋል፡፡

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen