የኢትዮጵያ ሕዝብ ለውትድርና ከፍተኛ ክብር አለው። ውትድርና ከሙያና ሥራ በላይ የነፃነትና የክብር መገለጫ፤ ሀገርን ከባዕድ ወረራ መከላከያ ጋሻ ነው ብሎ ያምናል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ህግና ሥርዓት አክባሪ በመሆኑ ለፓሊስም ከፍተኛ አክብሮት አለው። የፓሊስ ሥራ ወንጀልን መከላከልና ወንጀለኞችን ወደ ፍርድ ማቅረብ መሆኑ በኢትዮጵያ ባህል የተከበረ ቦታና እውቅና አለው።
በህወሓት የአገዛዝ ዘመን ግን ይህ እየተቀየረ ነው። የህወሓት አዛዦች እየመሩት ያለው የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት ሀገርን ከባዕድ ጠላት ከመከላከል ጋር ምንም ዝምድና በሌላቸው ሁለት አበይት ተግባራት ላይ ተጠምዷል። በህወሓት አዛዦች የሚመራው ሠራዊት ዋነኛ ተግባር ለሰብዓዊ መብቶቻቸው መከበር እና ለፍትህ መስፈን የሚታገሉ ዜጎችን ማጥቃት ሆኗል። የጦሩ ሁለተኛው አቢይ ተግባር ደግሞ ለአዛዦች የግል ጥቅም ማካበቻ ገቢዎችን በሚያስገኙ ሥራ ላይ መሠማራት ነው።
የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት ኢትዮጵያዊያንን ማጥቂያ ሠራዊት መሆኑ ሲቪሉን ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የሠራዊቱንም አባላትን ጭምር ለህሊና ወቀሳ የዳረገ ጉዳይ ነው። ሆኖም ግን ይህ በህሊና ወቀሳ ብቻ ሊታለፍ የማይችል ወንጀል ነው። ሠራዊቱ በህወሓት እየታዘዘ የሚዘምተው በገዛ ራሱ ልጆች፣ እህቶች፣ ወንድሞችና ወላጆች፤ በገዛ ራሱ ጥቅሞች እና በገዛ ራሱ ላይ መሆኑ መገንዘብ ይኖርበታል። በገዛ ራሱ ጥቅሞች ላይ የሚዘምት አንድም ህሊና የሌለው አሊያም ነፃነት የተነፈገው ሰው ብቻ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ሠራዊቱ እየተራበና እየታረዘ አለቆቹ የታላላቅ ህንፃዎች ባለቤቶች፣ ባለፋብሪካዎች፣ የባንክና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ባለአክሲኖች የሚሆኑበት ሥርዓት ከዳር ሆኖ የሚመለከት መሆኑ የሚገርም ነው። ሠራዊቱ ቤተሰቦቹን መመገብ አቅቶት እያለ የአዛዦቹ ልጆች ለሽርሽር ዓለምን ይዞራሉ። እንዴት ነው ሠራዊቱ እየደኸየና እየሞተ አዛዦቹ እየከበሩ የሚሄዱት? ይህ አዋራጅ ሁኔታ እንዲያበቃ መታገል የሠራዊቱ ግንባር ቀደም ኃላፊነት ነው። ሠራዊቱ ወይ ባርነትን አሜን ብሎ መቀበል አለበት አለበዚያም እሱም እንደነሱ ሰው መሆኑን ማሳየት መቻል አለበት። በኢትዮጵያ ውስጥ የህወሓት አገዛዝ ወድቆ የሕዝብ ይሁንታ ያገኘ መንግሥት መመሥረቱ በከፍተኛ ሁኔታ ከሚጠቅማቸው የኅብረተብ ክፍሎች ግንባር ቀደሙ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ናቸው። በዚህም ምክንያት የሠራዊቱ አባላት ለሥርዓቱ መውደቅ በግልጽም በስውርም መታገል የዜግነት ብቻ ሳይሆን አዕምሮ ያለው ሰው ሆነው በመፈጠራቸው የተቀበሉት ግዴታ ነው።
ፓሊስን በተመለከተም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ህወሓት የኢትዮጵያን ሕዝብ አፍኖ ለመግዛት የቻለው በዋኛነት የፓሊስን ኃይል ለአፈናው ተግባር የሚጠቀም በመሆኑ ነው። የተቃውሞ ድምጾች በተሰሙ ቁጥር የኢትዮጵያ ፓሊስ በወገኖቹ ላይ የሚያወርደው ዱላ የሚዘገንን ሆኗል። ሰላማዊ ሰልፈኞችን በጥይት መግደልና ማቁሰል፤ አረጋዊያንን፣ ሴቶችንና ሕፃናትን መግደል፣ ማቁሰል፣ መደብደብ በዚህ ተግባር የተሠማሩ ፓሊሶችን በቡድንም በግልም በህግ የሚያስጠይቅ ከባድ ወንጀል ነው። በህወሃት እየተመራ ያለው የኢትዮጵያ ፓሊስ ተግባራት ተበዳዮችን ብቻ ሳይሆን ራሱ ፓሊስንም ጭምር አንገት የሚያስደፋ ተግባር ነው። ለመሆኑ አንድ ተራ የኢትዮጵያ ፓሊስ ባልደረባ ከህወሓት አገዛዝ ምን ተጠቀመ? መልሱ “ምንም” የሚል ነው። ይልቁንስ በህወሓት የአገዛዝ ዘመን ፓሊስ የተናቀና የተዋረደ ሥራ ሆነ። በህወሓት አገዛዝ ፓሊስ እንደሰለጠነ አዳኝ ውሻ “ያዝ” ሲሉት የሚነክስ፣ የሚያደማ፣ የሚቦጭቅ ሆኗል። ይህ ለፓሊስ፣ ወንጀልም ውርደትም ነው። በህወሓት አገዛዝ መገርሰስ እና በምትኩ የህግ የበላይነት የሰፈነበት ሥርዓት መስፈን ፓሊስ ከሁሉ በላይ ተጠቃሚ ነው፤ ሰብዓዊ ክብሩን ያረጋግጥለታልና።
ዛሬ በኢትዮጵያችን ውስጥ የታዘዙትን የሚፈጽሙ የጦርና የፓሊስ ሠራዊት አባላት ስላሉ ነው የህወሓት ሹማምንት ልባቸው ያበጠው። ለማስረጃ ያህል ሰሞኑን የህወሓቱ ሹም አባይ ፀሐዬ የአዲስ አበባ ዙሪያ ገበሬዎች በግዴታ መነሳታቸው የሚቃወሙትን ዜጎችን ሁሉ ”ልክ እናስገባቸዋለን” ብሎ በሸንጎ የዛተው የታዘዘውን የሚፈጽም የጦርና የፓሊስ ሠራዊት መኖሩን ተማምኖ ነው። እስከ መቼ የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊትና ፓሊስ ሕዝብን ማስፈራሪያ መሣሪያ ይሆናል?
አርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ የኢትዮጵያ የመከላከያና የፓሊስ ሠራዊት አባላት ለራሳቸው እና ለወገናቸው የሚበጀው ሥርዓት የቱ እንደሆነ ያውቃሉ ብሎ ያምናል። በዚህም ምክንያት ስብዕናቸውን እያዋረደ እና እያደኸያቸው ያለውን የህወሓት አገዛዝን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በመሆን ይፋለሙታል ብሎ ያምናል። ይህ ውሳኔ ግን ሠራዊቱ በጅምላ ሳይሆን እያንዳንዱ የሠራዊቱ አባል በግሉ የሚወስደው ውሳኔ እንደሆነ አርበኞች ግንቦት 7 ይገነዘባል።
በዚህም መሠረት ተደጋጋሚ ጥሪ እየተደረገለት፤ ጥሪውንም እየሰማ ከህወሓት ጋር ወግኖ ሕዝብን መውጋት የቀጠለ የሠራዊቱ አባል ላደረሰው ጥፋት በግል መጠየቁ የማይቀር መሆኑ ሊገነዘብ ይገባል። በእያንዳንዳንዱ የጦርና ፓሊስ ሠራዊት ባልደረባ ፊት የቀረበው ምርጫ “ለህወሓት ባርነት ታድራለህ ወይስ ራስህንና ሀገርን ነፃ ታወጣለህ” የሚል ነው።
ራስህንና ሀገርህን ነፃ ለማውጣት የመረጥክ የሠራዊቱና የፓሊስ ባልደረባ አሁኑኑ ሕዝባዊ ትግሉን ተቀላቀል። እስከዛሬ የበደልከውን ሕዝብ ለመካስ ምቹ ሁኔታ አለህ። በግልጽ የነፃነት ኃይሎችን እንድትቀላቀል፤ አሊያም አለህበት ሆነህ በውስጥ አርበኝነት እንድትደራጅና ተግባራዊ ሥራ እንድትጀምር መንገዱ ተመቻችቶልሃል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
Keine Kommentare:
Kommentar veröffentlichen