Netsanet: ማን ይንገርልን – ማን ይመስክርልን (ጸጋዬ ገብረ መድኅን አርአያ)

Samstag, 14. Juni 2014

ማን ይንገርልን – ማን ይመስክርልን (ጸጋዬ ገብረ መድኅን አርአያ)

June 14, 2014

ጸጋዬ ገብረ መድኅን አርአያ
እንደ ልጄ የምቆጥረውና ከበኩር ልጄ ከዩሐንስ ጋር ያደገው ሳምሶን በሕክምና ኮሌጅ ይማር በነበረበት ዘመን በምሽቱ ሰዓት ላይ የ‹‹ፈገግታ ጊዜ›› በምንለው ግማሽ ሰዓት ያጫውተን ነበር፡፡ አዎን ሕይወት ውጥርጥር ባለበትና ጭንቀት ከቀበሌ ከሚወረወር ቀስት፣ ጭንቀት ከየካድሬውና ከየፖለቲካው ኅቡዕ ድርጅት ከሚወረወር ሌላ ቀስት፣ ጭንቀት፣ ከመስሪያ ቤት ጭንቀት፣ ከበላይ አካል ጭንቀት፣ ከበታች አካል ጭንቀት፣ ጭንቀት —- አንድ የድሮ ማስታወቂያ ሚኒስትር እንዳሉት ከላይ ከመሳፍንቱና ከመኳንንቱ በሚለቀቅብህ እሳት፣ ከታች ከሕዝቡና ከሠራተኛው ከሚነድድብህ እሳት የገና ዳቦ ትሆናለህ፡፡ ስለዚህ ‹‹በታይም አውት›› (ፋታ ልበለው) መልክ ከሳሚዬ ጋር የማደርገው የግማሽ ሰዓት ውይይት (ጨዋታ) ለእኔ “ማሳጅ” ነበር፡፡ መታሻ!Tsegaye Gebremedihn Ethiopian writer latest Amharic article
እንደ ወትሮው የዛሬው ወጋችን በክፍል ውስጥ ስለነበረው አጋጣሚ ነበር፡፡ በዚያው ዕለት በሕክምናው ኮሌጁ የመጀመሪያው ሰዓታት (ሦስት) አስተማሪው ዶክተር አሥራት ወልደየስ ነበሩ፡፡ “ዛሬ የማስተምራችሁ ስለ ጦር ሜዳ አነስተኛ የቀድዶ ሕክምና ነው” ይላሉ፡፡ አከታትለውም የጦር ሜዳውን “ሰገሌ እንበለው” ይላሉ፡፡ ይቀጥላሉ፡፡ ተፋላሚዎች በወሎው ጦር በኩል “ንጉሥ ሚካኤል” —- ይሉና ቆም ብለው ይመለከቱ ጀመር፡፡ እንዳጋጣሚ ከፊት ለፊት የተቀመጠውን አንዱን ተማሪ “ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስን ታውቃቸዋለህ? ብለው ይጠይቁታል፡፡ “አንተዋወቅም” ይላል፡፡ ሁለተኛው ጊዜ ሳይፈጅ ወደ መርካቶ ሲኬድ መግቢያው ላይ ድልድይ ያላቸው ሰውዬ ናቸው” ይላቸዋል፡፡ ሦስተኛው በሙሉ የአዋቂነት ኩሩ ስሜት ‹‹የአጤ ኃይለሥላሴ ቅድመ አያት ናቸው፡፡ ከአያቴ ጋር በጣም ይተዋወቁ ነበር›› አለ፡፡ ሌላው የፕሮፌሰር አሥራትን ከፍተኛ የአገር ፍቅር ስሜት የበለጠ ለማጋጋል ፈለገና ይልቁንም እሳቸው በዛሬው ፕሮግራማቸው ስለጦር ሜዳ ሕክምና ለማስተማር የተዘጋጁ መሆናቸውን ስለተናገሩ “ኢትዮጵያ ከእንግሊዞች ጋር በተዋጋች ጊዜ የጦር መሪ የነበሩት አጭር፣ ፉንጋ ሰው ነበሩ፡፡ አጤ ኃይለ ሥላሴ ሠላሳ ዓመታት አሠሩአቸው” ይላል፡፡ ፕሮፌሰሩ ትንሽ ይደንቃቸውና “ኢትዮጵያ ከእንግሊዞች ጋር የተዋጋችው ትራፋልጋር ላይ ነበር ወይስ ወተርሉ ላይ ነበር?” ብለው ይጠይቃሉ፡፡ አራዳው ተማሪ “የለም ሰገሌና አንኮበር ላይ ነበር” ይላቸዋል፡፡ (በነገራችን ላይ እንግሊዞች በወተርሉና በትራፋልጋር ላይ ጦርነት የገጠሙት ከፈረንሳዩ መሪ ከናፖሊዮን በናፖርት ጋር ነበር፡፡) ፕሮፌሰሩ ቀልዱንም ሞክረውት ጥርሳቸው ሊላቀቅ አልቻለም፡፡ በጎጃም ቅኔ ቤት የሚወራ ጨዋታ ነበር፡፡ በጎንጅ የሚታወቁ አንድ የቅኔ መምህር ነበሩ ይባላል፡፡ እንደአጋጣሚ ሆኖ ጥርሶቻቸው ሽግናም ነበሩ፡፡ አንድ ቀን አንድ ወዳጃቸው ሰውን ሁሉ በጨዋታው ሲያስቅ ውሎአል፡፡ መምህር ሞገሴ ግን አንድም ጊዜ ፈገግ ሲሉ አልታዩም፡፡ ወደማታ ላይ ሰውየው “አባ ሞገሴ አንድ ደቂቃ እንኳ ሲስቁ አላየሁዎትም›› ይላቸዋል፡፡ ጥርሰ ሽግናሙ መምህርም ‹‹መቼ የምስቅበት ጥርስ ስጠኝና?” አሉ ይባላል፡፡ ለመሆኑስ በዚህ አገር ከማስለቀስ አልፎ የሚያስቅ ነገር ከወዴት መጥቶ! አባ ሞገሴ ጨርሰውታል፡፡ መቼ ለፈገግታ ታደልን፡፡
ሳምሶን (ከብዙ ዓመታት በፊት ጀምሮ ዶክተር) እንዳጫወተኝ ዶክተር አሥራት ወረቀቶታቸውን ሰበሰቡና፣ በጥቁር ሰሌዳው ላይ የጻፉትንም አንዳንድ የህክምና ዓይነቶች ጠራረጉና “በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ካሉ ተማሪዎች ጋር አገርን በተመለከተ መነጋገር የሚያስቸግር አይመስለኝም ነበር፡፡ በተለይም ሀብተ ጊዮርጊስን ከማያውቅ የዩኒቨርሰቲ ተማሪ ጋር ምን ጉዳይ አለኝ?” በማለት ክፍሉን ጥለው ወጡ፡፡ ከዚያ ወደ ቢሮአቸው ሄደው በትካዜ ባሕር ይሰጥማሉ፡፡ ያለፉትን ዘመናት ጦርነቶች፣ የጦር አገዛዦቹን ከነጀብዱዎቻቸው፣ በድል ጊዜ የነበረውን ሽለላና ፉከራ፣ የዘመቻ ባህልና የጦርነት መንፈስ አንብበዋል፤ ሰምተዋል፡፡ ፋሽስት ኢጣልያ አገራችንን በወረረችበት ዘመን የነበረውን ውጣ ውረድ፣ ማን ከማን ጋር እንደቆመ፤ ስለጀግንነትና ስለክህደት ሰምተዋል፡፡ ተከታትለዋል፡፡ ሲናገሩ ኖረዋል፡፡ እያደር አገሪቱን የጀግና ድርቅ እንደመታት፣ የእምነት ድቀት እንደወረደባት ብዙ የሚናገሩና ቁጭታቸውም የማይገታ መሆኑን ሰው ሁሉ የሚያውቅላቸው ናቸው፡፡ ስለዚህ ከክፍል ገብተው “ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስን ታውቃላችሁ አይደል?” ሲሉ የተሰጧቸው (እዚህ ላይ ያልተጠቀሱም አሉ) መልሶች አስደነቁአቸው፡፡ በእንግሊዝ አገር ይማሩ በነበረበት ጊዜ ኢትዮጵያውያን እንደ ብርቅ ሕዝብ፣ እንደ ሰማያዊ ተዋጊ ኋይላት፣ የጥቁር ሕዝብ እንቁና እግዚአብሔር ለራሱ መከበርያ አድርጎ —– የፈጠረው ተደርጎ በብዙዎች ይታይ እንደ ነበር አስታወሱ፡፡ የአድዋው ጀግና መሪ የወቅቱን የአውሮፓ ኃያል መንግሥት ያንኮታኮተበትንና ጥቁሩን ሕዝብ እንዳኮራው ሁሉ ተፈሪ መኮንን ወደ ሥልጣን ሲመጡ ‹‹ይኸ ደግሞ ለእኛ ሁሉ የተወለደልን ነፃ አውጫችን ነው›› ብለው እንደ አዳኝና የአርነታቸው ምልክት አድርገው እንደ ተቀበሉአቸው አሰቡ፡፡ ራስ ተፈሪን እንደ አምላክ እንደሚያዩአቸውም አሰቡ፡፡ አድዋን እንደገና፣ ተድአሊን፣ ጉዳጉዲን በአእምሮአቸው አሰሱ፡፡ አጼ ኃይለሥላሴን የሚያደንቁአቸውን ያህል በእነ በላይ ዘለቀ፣ በእነ አቶ ፈጠነ፣ በአፈንጉሥ ታከለ—– በእነ ልጅ እያሱና በአባታቸው በንጉስ ሚካኤል ሞት የነበራቸው ቅሬታ ትዝ አላቸው፡፡ አጼ ኃይለሥላሴ ይቺን አገር ያስከበሩአት መሪ መሆናቸውን እያሰላሰሉ ደግሞ አወዳደቃቸውን፣ አሟሟታቸውንና አብሮአቸውም የሦስት ሺህ ዓመት የዙፋን አገዛዝ ምዕራፍ መዘጋቱን በአእምሮአቸው አወጡ አወረዱ፡፡ ሳያስቡት እንባ ወርዶአቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ታላቅነትና የሕዝብዋ አንድነት ግዙፍ ታሪክ እየወደቀ ይሆን? ብለውም መጨነቅ ያዙ፡፡
ይህ ትውልድ በዚህ ዓይነት ውጣ ውረድ ውስጥ አላለፈም፡፡ ወይም ያንን ዘመን በታሪክ ቅብብሎሽም አላወቀውም፡፡ በአንድ ወቅት እንደ ገለጡልኝ “ጀግና ስንፈልግ ባጀን” የሚለውን የእኔን የጦቢያ መጣጥፍ ካነበቡ በኋላ በአካል የሚያውቁአቸውን ቀኝ ጌታ ዩፍታሔ ንጉሤን አስታወሱ፡፡ ከዚያ በኋላ ቀኑን ሙሉ ተበጥብጠው ውለዋል፡፡ “ስማ! አሉኝ” አቤት አልሁ፡፡ “የሼክስፒየርን ሐምሌት አንብበሃል” አሉኝ፡፡ አዎን ብዙና ዋነኛ ስንኞቹ አሁንም በአእምሮዬ ውስጥ ቀርተዋል፡፡ በቃሌ ነበር የማንበለብላቸው አልኋቸው፡፡ ያነሱብኝ ሐምሌት ከመቃብር ቆፋሪው ሰውዬ ጋር ያደረገውን ንግግር ነበር፡፡ በቁም የሞቱ፤ ሞተው ያልተቀበሩ፤ ሞተውም አለን የሚሉ፤ አለንም የሚሉ ምውታን! ዶክተሩ ቀኝ ጌታ ዮፍታሔን ያነሱበት ምክንያት ገብቶኛል፡፡ ዩፍታሔን እንደ ሼክስፒየሩ መስፍን (ልዑል ሐምሌት) በመቃብር ሥፍራ የሚባዝን ፍጡር አድርገው ነበር ያዩአቸው፡፡ አዎን ከሐምሌት የሚለዩት ዩፍታሔ ከሙታን መካከል ሕያዋንን የሚፈልጉ በመሆናቸው ነው፡፡ ዮፍታሔ ጀግና ናፈቃቸውና “ዓይኔን ሰው አማረው” አሉ፡፡ ባበደ ቅኔ
‹‹አጥንቱን ልቁጠረው መቃብር ቆፍሬ
ጎበናን ከጋላ አሉላን ከትግሬ
ስመኝ አድሬአለሁ ትናንትና ዛሬ ——
“ዓይኔን ሰው አማረው” አሉ?
የአገር ናፍቆት፣ የጀግና ረሃብ፣ የታሪክ ምርምር ፣ የእኔነት ፍለጋ አንድ ሕዝብ ከከፍተኛ ብሔራዊ ውድቀት ላይ በሚገኝበት ሰዓት የሚያጋጥም አባዜ ነው፡፡ የታሪክ ክፍተት፣ የእኔነትና የጋራ አገር ሳይታሰብ ከትልቅ እንቆቅልሽ ውስጥ መውደቅ፣ ወደማይታወቅ፣ ጉዞውም ወዳልለየ አቅጣጫ ይወስደዋል፡፡ ይህንን ወቅት ያሰላስሉአል፡፡ በነገራችን ላይ በብዙዎች መጣጥፎቼ ውስጥ ሐምሌትን ሳልጠቃቅስ አልቀረሁም፡፡
በቅን የኢትዮጵያ ልጅነት ከሚታወቁት ዶክተር ጋር የምር ንግግር ነበረኝ፡፡ ባለፈው መጣጥፌ (ጅብ ቲበላህ በልተኸው ተቀደሰ) ላይ ለማመልከት እንደሞከርሁትም በመላው አማራ ሕዝብ ድርጅት ምክትላቸው ከነበሩት (በኋላ የቅንጅት ሊቀመንበር) ከአቶ ኃይሉ ሻውልም ጋር ስለዚህ አገር የጉዞ አቅጣጫ ቀን ከሌት የምንወያይባቸው ጊዜያት ነበሩ፡፡ ዋናው ጉዳይ አንደኛ የመጣውን አደጋ መመለስ ነው፡፡ ሁለተኛ ኢትዮጵያን በተመለከተ እዚህ ስንደርስ የተቀረጸውን ታሪክ ማቃናት ነው፡፡ ሦስተኛ በየትም አገር በማንኛውም ዘመን ብቅ የሚል ሥነ መንግሥት አለ፡፡ በእኛ እምነት በዚህ ወቅት የመጣብን ሥነ መንግሥት ጤና ጉዳይ አጠያያቂ ከመሆኑ ላይ ነው፡፡ ከሥርዓቱ ጋር ሊግባባ የሚችል ማን ጤነኛ ሰው አለ? ምን እናድርግ? ከዜሮ መነሳት ሳያስፈልገን አይቀርም፡፡
የትናንቲቱ ኢትዮጵያ የዛሬውና የነገይቱ ኢትዮጵያ መሠረት ናት፡፡ የዛሬ ኢትዮጵያውያንም በትናንቲቱ ኢትዮጵያ መሥራቾችና የመሠረት ድንጋይ አቀባዮች ትከሻ ላይ የቆምን ነን፡፡ ይህን በመካድ አዲስ ታሪክ እንመሰርታለን ለሚሉ አጥፊ ኃይላት ሶማሌዎች አንድ አባባል አላቸው፡፡ “አዲስ ጫማ ከመግዛትህ በፊት አሮጌውን አትጣለው” ይላሉ፡፡ የወደፊቱን ተስፋ ሊያሳጡን የሚፈልጉት የዚህ መንግሥት ባለቤቶች የትናንት ደሆችና የዛሬ ውርስ የሌለው ሕዝብ አድርገው ፈርደውብናል፡፡ የሚያሳዝነው ለዚህ ሁሉ ሴራ የራሳቸው ትረካ፣ አዲስ ታሪክና ድርሰት ይዘው ሲቀርቡ የቅጥፈታቸው ሰለባ አለመታጣቱ ነው፡፡ አንድን ሕዝብ የጋራ ታሪክ አልባ ማድረግ፣ መነሻና መድረሻ የሌለው —— መሠረትና መንደርደሪያ አልባ ማድረግ በቀላል ቋንቋ የሚገለጥ ኃጢአት አይመስለኝም፡፡ በአንድ ሐረግ ለመግለጥም ሁላችንም እየተገረፍን እንደ ከብት ወደ ቄራ እየተወሰድን ነው፡፡ በጉልበት የምንጋተው መርዝ! ከዚህ ቀደም በተጠቀምሁበት ቋንቋ እንደገና እመለስበታለሁ፡፡ ለእነዚህ ነፍሳት እግዜሩም ሌላ ገሐነም ማዘጋጀት አለበት፡፡
በመጀመሪያዎቹ አንቀጾች ለማመልከት እንደ ሞከርሁት የቅርቡንም ሆን የጥንቱን የኢትዮጵያ ታሪክ እኛም ከሰባው ዓመት ባሻገር የዘለልነው እምብዛም ክትትል በማጣት በተጨማሪም ወደ ሥልጣን እርካብ ላይ የወጣ ሁሉ ፀሐይ ብርሃንዋ መስጠት የጀመረችው በእነሱ አገዛዝ ጀምሮ መሆንዋን ለማስረገጥ ብዙ ትርምስ ሲፈጠር ኖርዋል፡፡ እውነት ነገር ይነገር፡፡ በአጼ ኃይለሥላሴም ዘመን ቢሆን የምኒልክም፣ የቴዎድሮስም፣ የዩሐንስም ታሪክ ጉልህ ሆኖ እንዳይወጣ ይፈለግ እንደነበረ ምስክር ነኝ፡፡ የዚህም ምክንያት በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመንና ታሪክ ላይ ምንም ጉዳይ ወይም ግለሰብ ጥላውን እንዳይጥል ስለሚፈለግ ነበር፡፡ በዘመናቸውም የነበሩትን አርበኞች ሁሉ ታሪክ ለቅመን በንጉሠ ነገሥቱ ትከሻ ላይ በመቆለል እውነተኞቹ አርበኞች ሳይታወቁ፣ ታሪካቸውን፣ በአፍ በመቀባበል እንጂ ተነግሮ ሳንጠግበው ሰዎቹ ወይ ተገድለዋል፡፡ በገመድ ተንጠልጥለዋል ወይም የእርሳስ ሲሳይ ሆነዋል፡፡
ያለፉትን መንግሥታት በመጠኑና ምናልባትም ይበዘባቸዋል በማይባል ሁኔታ ጀግንነትና ጀግናን ባለማክበር የተሰለፉትን አገር ሻጮችንና ለአገር ክብርና ሰማዕትነት የቆሙትን ወገኖቻችንን ሲገድሉና ሲያስገድሉ የኖሩትን ስንተች በጅተናል፡፡ አዝናለሁ፡፡ በባንዳነትና በአገር ጠላትነት የቆሙትን በየጊዜው ስናሳቅል (እኔን ጨምሮ) የቆየነውን ያህል ለዛሬውና ተረካቢው ስለ ጦርነቶታችን፣ ስለ መሪዎቻችን በጎ በጎ ምንባብ አቅርበን የምናውቅ አይመስለኝም፡፡ በዚህ የተነሳ እንደምትከታተሉት ሁሉ ውሸት ይነግሥ ዘንድ፣ የፈጠራ ታሪክ ተአማኒነት ያገኝ ዘንድ አስተዋጽኦ አድርገናል፡፡ የእውነት አለመነገር ለቅጥፈት ተቀባይነት አስተማማኝ ሁኔታዎችን አስገኝቷል፡፡
ውሸትን የመሰለ ጨካኝ ነገር የለም፡፡ ውሸት ደግሞ ሰው ሳይሆን ባሕርይ ነውና ያንን ገፋ አድርግን ካየነው እንደ ዋሾ ሰው ጨካኝ የለም ለማለት ይቻላል፡፡ ትንሽ ዕድሜህ ገፋ ሲልና በመሠረቱም በቤተሰብ በሚሰጥ ትምህርትና ግብረ ገብነት ተኮትኩተህ ካደግህ ተራራ የሚያካክለው የወያኔዎች ቅጥፈት ያሳብድሃል፡፡ ቀደም ሲል እንዳልሁት ደግሞ ይቺ አገር ከምንም ምንም የበለጠ ሀብትዋና ኩራትዋ የዘመናት ጀግንነትና ለአንድነትዋ የተከፈለው መስዋዕትነት ሆኖ ሳለ ያለንን አውቀን ያለማሳወቁ ጎዳን፡፡ ጎድቶናል፡፡ ሌላው ቀርቶ ልጆቻችን እንኳ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን እየተመለከቱ “የፕሮፓጋንዳውን እውነት” ወደ ማመኑ አዘንብለዋል ባይ ነኝ፡፡ በተለይም መንግሥት ይዋሻል ብሎ ለማመን የማይፈልገው የዋሕ ሁሉ ደህና የፕሮፓጋንዳ ሰለባ ሆኖአል ባይ ነኝ፡፡ የማላስባቸው ሰዎች ሳይቀሩ እኔን አዋቂ አድርገው “ጋሽ ጸጋዬ ይኸ ቴሌቪዥን ላይ የሚቀርበው የምኒልክ ጭካኔ ምን ያህል እውነት ነው?” ብለው ይጠይቁኛል፡፡ እንደአጋጣሚ ደግሞ መኪናዬ ውስጥ በተለዋዋጩ የአየር ጠባይ የወየበች መጽሐፍ አለችኝ፡፡ Who will tell the people? የምትል፡፡ ለሕዝቡ ምን እንንገረው? የሚሉ ፋይዳዎችን የሚነካካ ነው፡፡ አዎን ለሕዝባችን —— በተለይም ለአዲሱ ትውልድ ምን እንንገረው? የእነማን ልጅ መሆኑን ——- በምን መሠረት ላይ የበቀለ መሆኑን እንዴትና በማን ይነገረው? አዎን ሰሞኑን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ላይ ምኒልክንና የአድዋ ጦርነትን ምኒልክንና አርሲን ——- በጠቅላላውም ምኒልክንና የታሪክ ዘመኑን በተመለከተ የሚቀርበው ፕሮግራም ደሙን ያላፈላው ሰው ያለ አይመስለኝም፡፡ የፈጠራ ድርሳንና በአሁኑ ጊዜ ደግሞ እየሰጠመ የሚገኘውን የወያኔ መርከብ ለማዳን ሲባል የተፈበረከው ቅጥፈት መልስ የሚገባው አይመስለኝም፡፡ በእኔ በኩል ውሸትን ማስተባበል ሥራዬ ነው ብዬ አላውቅም፡፡ እውነትን በእውነቱና በሐቀኛ ቅርጹና መልኩ ማሳየት እርግጥ የአደጋ ጊዜ ግዴታ ይሆናል፡፡ አለዚያ ለፈጠራ ድርሳን ሁሉ እንደ አስተባባይና ተቃዋሚ ሆኖ መጮህ ተገቢ አይደለም፡፡
ፋሽስቶችና ናዚዎች አብረው የሚጓዙባቸው የጋራ ባሕሪያት አሉአቸው፡፡ ይኸውም በተደጋጋሚነትና በአሰልቺነት የሚቀርበው የቅጥፈት ፕሮፓጋንዳ ነው፡፡ የደገምሁት ካልሆነ በቀር ሙስሊኒ ራሱ “ማይክሮፎኑን” ከያዘ የሕዝብን ቀልብና ልብ መማረክ ዕዳው ገብስ ነበር፡፡ (ለእኔ ተውልኝ ነበር የሚለው) በዚህም የተነሣ የኢጣልያ ጎረምሶች ለእሱ ፕሮፓጋንዳ፣ የጀርመን ወጣቶች ከሒትለር ለምትወጣ አንዲት ቃል ተገዥ ሆኑ፡፡ ሕዝቦቻቸውም ወደ እልቂትና አገሮቻቸውም ወደ ፍጹም ውድመት መሩ፡፡
ሁላችሁም ልትስማሙኝ እንደምትችሉ አምናለሁ፡፡ በአንዲት ነጥብ ላይ ማለቴ ነው፡፡ ወያኔ በመጣበት እግር መውጣት ሳይሆን መጽሐፋችን እንደሚለው “በታላቅ መንቃቃት” የሚያልፍበት “የታላቁ መልአክ” እንቢልታ ከሚጮኽበት ደረጃ ላይ ደርሶአል፡፡ ይኸን ራሱም አላወቀውም አይባልም፡፡ ከሁለት ባላ ላይ ተንጠልጥሎ ሁለት አደጋ በማድረስ “የመጣው ይምጣ” ላይ ይገኛል፡፡ የጨረሳቸውን የኦሮሚያ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎች ፈለግ ተከትለው አመጹን የሚያፋፍሙ ወጣቶችን ጥያቄዎች ለማስተኛት ኦሮምኛ የሚናገሩ የመንደሩን ሰዎች የቴሌቪዥን እንግዶች እያደረገ ነው፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ በማድረግ “የምኒልክ ሐውልት በፊንፊኔ መቆም ይገባዋል ወይ? የናዚ ሐውልት በለንደን እንዲቆም ይፈቀዳል ወይ?” በማሰኘት የዛሬን ጥያቄ በሌለ ታሪክ ሊለውጠው እየሞከረ ነው፡፡ በሌላም በኩል በአማራውና በኦሮሞው መካከል ያለውን የማያረጅና የማይፈርስ ድልድይ ለማቃጠልና ደም ለማፋሰስ እየሞከረ ነው፡፡ እውን ለዚህ ዓይነቱ ተለማማጅ ፕሮፓጋንዳ የምንፈታ ተራ ሕዝብ ነን?
በዚያን ሰሞን የአንድ ፖለቲካ ፓርቲ መሪ ለሆነ ወዳጄ ስልክ ደውዬለት ነበር፡፡ “ምን እየተፈጠረ ነው?” አልሁትና “እባክህ በአገር ሽማግሌ ጠፍቶአል የማይባል ነገር የለም፡፡ የማይሰማ ታሪክ፣ የማይሰደብ ጀግና፣ ስለኢትዮጵያ አንድነት የማይነገር ተረት የለም” አለኝ፡፡ በዚህ መጣጥፍ ላቀርበው ላሰብሁት አሳብ ተጨማሪ ግፊት ፈጠረብኝ፡፡ የሽማግሌ ከአገር (በአገር) መጥፋት፣ የታሪክ ምስክሮች ከአገር (በአገር) አለመኖር፣ ሕሊና ያላቸው ሰዎች ወጣ ብለው ለመናገር ያለ መቻል (ጥቂቶችን በማኅበራዊ ድረ ገጽ ብናነብብም) በአገር ላይ እየደረሰ ያለውን አደጋ ምን ያህል ጎድቶታል? ብዙ ብዙ እንደሚባለውም አንድ አገር ላይ ሕሊና ቢሶች ከሚያደርሱባት አደጋ ይልቅ ተከናንበው የተኙ የእውነት ምስክሮች በዝምታቸው የሚያደርሱት አደጋ መቶ እጥፍ ነው፡፡
“ሽማግሌ ዜጋ ጠፋ” አለኝ ወዳጄ፡፡ ወያኔ እንደ መጣች ታሪክ መዘበራረቅና የጥላቻን ዘር መበተን እንደ ጀመረች “ኢትዮጵያን በትክክለኛ ቅርጽዋና ይዘትዋ የሚያውቁአት አረጋይ ዜጎች ነበሩ፡፡ በሚኒስትርነት፣ በአምባሳደርነት፣ ሕዝብን በማስተባበርና በጦር ሜዳም ውሎ የታወቁ አባቶች ነበሩ፡፡ እነዚህ አባቶች ሁኔታው ሁሉ አገርን የሚያዋርዱና ቀስ በቀስም የእያንዳንዱን ዜጋ ሕልውና የሚጻረሩ መሆኑን በመረዳት ባለቀ ዕድሜያቸው ላይ “የኢትዮጵያዊነት ማኅበር” አቋቁመው ነበር፡፡ እነዚህም አቶ ሐዲስ ዓለማየሁ፣ ቢትወደድ ዘውዴ ገብረሕይወት፣ ደጃዝማች ዶክተር ዘውዴ ገብረሥላሴ፣ ልጅ ሚካኤል እምሩ፣ ደጃዝማች ወልደሰማያት ገብረ ወልድ ፊታውራሪ ገብረሕይወት፣ አቶ በለጠ ገብረጻድቅና ዋናው ጸሐፊ አቶ ሳሙኤል ዓለማየሁ ነበሩ፡፡ የፖለቲካ ሥልጣንን አይተውትና ጠግበውት በመጨረሻ ዘመናቸው ላይ የነበሩትን እነዚህን አባቶችና ሁለት ሦስት ወጣትነት ያላቸው ቅን ዜጎችን ለማየት ያስደነገጣቸው ወያኔዎች ይኸ አጀንዳ ይፈርስ ዘንድ ያልጣሩት መስክ አልነበረም፡፡ በዚህም በስደቱ ዓለም ተመሳሳይ ጥረቶች መደረጋቸውን አውቃለሁ፡፡ ልብ በሉልኝና አረቡ ዲታስ አሜሪካ ድረስ መረቡን ዘርግቶ ወጣቶቻችንን ለመከፋፈል የሚያደርገውን ትከታተሉት የለም እንዴ? በስፖርቱ ስም!
“የሽማግሌ” ሚና ምንድን ነው? ታሪክ ሲዛባ፣ ሕግና የታወቀው ሥርዓት ሲናጋ፣ በሕዝብ መካከል ሰላም ሲታጣ መምከር፣ መገሰጽ፣ ማስተማር ነው፡፡ ይኸ ነበር ባህላችን! በዛሬው የእብደት ዘመን ግን እንደምከታተለው በእርግጥ የሽማግሌ ሚና ሊጫወቱ የሚገባቸውና በዚያ ሰልፍም ከመጀመሪያው ረድፍ መገኘት የሚኖርባቸው አንዳንድ ግለሰቦች ከአጥፊዎች ጋር ማኅበር በመጣጣት ላይ መሆናቸውን ተገንዝቤአለሁ፡፡ ይኸ የሚያስታውሰን ፈረንጆች “ንጉሡ ራቁታቸውን ናቸው” የሚሉትን ይትበሐል ነው፡፡ እንደሚባለው የንጉሡ ባለሟሎች በዓይነቱ፣ በጥራቱና በረቂቅነቱ እስከዛሬ የማይታወቅ ልብስ እየተሰራልህ ነው ብለው አእምሮውን አስተውታል፡፡ በመጨረሻም “በዓይን የማይታየውን ልብስ ለብሰሃል” ብለው በዙሪያው እየተሽከረከሩ በወደል ወደሉ ቋንቋ ያደንቁት ጀመረ፡፡ በፊቱ እየተንበረከኩም “ንጉሣችን ለዘላለም ይኑር! ዓይን አይቶት የማያውቀውን ረቂቅ ልብስ ለብሶ ለሕዝብ ይታይ ዘንድ ወደ አደባባይ ይወጣል” ብለው ከፊት ለፊቱ መሮጥ ይይዛሉ፡፡ ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ ያጨበጭባል፡፡ ሆታው ሌላ ነበር፡፡ ሁሉም አጨብጫቢ ነው፡፡ “ሆ” ባይ ነው፡፡ በመካከሉ አንዲት ትንሽ ልጅ ——– አእምሮዋ በቅጥፈትና በማጭበርበር ኃጢአት ያልተበከለ-ከአባትዋ ትከሻ ላይ እንደታዘለች “ንጉሡ ራቁቱን ነው፡፡ ንጉሡ ራቁቱን ነው” አለች ይባላል፡፡ ታዲያን እንደ የእውነት ምስክሮችና የአገሪቱ ሕሊናዎች አድርገን የምንመለከታቸው (በእኛም አገር ዛሬ) ሰዎች ራቁቱን ያለውን ንጉሥ ሲያቆላጵሱት እየሰማን ነው፡፡
የአድዋ ጦርነትና የምኒልክ ዘመን በሰባትና ስምንት ሺ ዓመት የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ እንደ “ትናንት” ማታ የሚታይ ይመስለኛል፡፡ እኔ አንድ ትሁት ኢትዮጵያ ዜጋ ደግሞ የተወለድሁት ፋሺስት ኢጣሊያ ከተባረረች በኋላ ሲሆን በምኒልክ ዘመን ሁነኛ ሥፍራ የነበራቸው ሰዎችን ለማወቅና ለማነጋገር ዕድል ገጥሞኛል፡፡ እንዲያውም የአክስቴ ባለቤት (የእናቴ ታናሽ እህት) ልጅ ደስታ ምትኬ የእቴጌ ጣይቱ የአክስት ልጅና ጸሐፊያቸውም ነበሩ፡፡ በተደጋጋሚ በመጣጥፎቼ የጠቀቀስኋቸውን ጋዜጠኛና ከንቲባ ደስታ ምትኬ፣ ፊታውራሪ ተክለሐዋርያት ተክለማርያም (ዋየሕ) ደጃዝማች ከበደ ተሰማን፣ ፊታውራሪ እማኙ ይመርን ሌሎችንም አውቃለሁ፡፡ እንደማምነውም ዛሬም ጭምር በዚያ ዘመን የኖሩ ከአምስት እስከ አሥር ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ (ሰሞኑን ባለ 139 ዓመት ዕድሜ ኢትዮጵያዊ ብቅ አሉ ልበል?)
የምኒልክ ዘመን ወደ ኋላ ብዙ የዘመን ርቀት ሄደን በብዙ ውጣ ውረድ ታሪኩን የምንፈለፍልበት ጣጣ ያለው አይደለም፡፡ የኢትዮጵያን ዕድሜ በምኒልክ ዘመን ሲወስኑት የኖሩት ወያኔ ገዥዎቻችን ግን መረጃው ያላረጀውን፣ ብል በልቶ ያላፈጀውን ቁልጭ ያለ ታሪክ በፈጠራ ድርሳን ለምን እንደ ለሰኑት፣ የፈጠራ ታሪክ ደራሲ (እነ ተስፋየ ገብረአብ) ለምን እንደሾሙብን ግልጽ ነው፡፡ በ20ኛው ክፍለ ዘመን በታላቅና ታሪካዊ ሁኔታ የተመሰረተውን አንድነት በ21ኛው ክፍለ ዘመን መግቢያ ላይ ለማፍረስ ያገኙት ስልት ይኸ ብቻ ስለሆነ ነው፡፡
ለሕዝባችን ስለዚያ ዘመን ማን ይናገር? ማን የሕዝብ ሕሊና ሆኖ ይመስክር? ታሪክ ምን ይላል? ከመጠነኛ ንባቤ፣ ባለፉት ዘመናት በምኒልክ ዘመን ከነበሩ አዛውንትና አዋቂዎች ወግና ምስክርነት በመነሣት ያቅሜን ትንሽ “እውነት” ብተነፍስ ዛሬ ማታ ጥሩ እንቅልፍ የምተኛ ይመስለኛል፡፡ በቻይናዎቹ የታኦ ፍልስፍና እንደሚነገረው “ማለዳ ላይ ታኦ አንብበህ ማታ ላይ ብትሞት ደስ ይበልህ፡፡ የጽድቅ መንገድ ይኸ ነውና” ይላል፡፡
እምዬ ምኒልክ – ትንሽ ስለ ምኒልክ ስብእና
ስለ ልደታቸው፣ ስለ ትምህርታቸው፣ በአጤ ቴዎድሮስ ተወስደው እንደ አባት እንዳሳደጉአቸውና ልጃቸውን እንደዳሩላቸው ከመቅደላ አምልጠው እንዴት ወደ ሸዋ እንደ ተመለሱ ማውሳት ዝርዝርና መጽሐፍ የሚወጣው ይመስለኛል፡፡ ይልቁንም ስለ መንግሥት አመራር ስታይላቸው፣ ስለሕዝባዊነታቸውና ስለ “አረብ ዘመቻቸው” ብቻ ብናወራስ?
ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት የተባሉበት ጊዜና የአጤ ዩሐንስ መንግሥት ማክተሚያ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጭካኔ ይልቅ ርህራሄና ፍቅር የተራበበት ዘመን ነበር፡፡ አጼ ቴዎድሮስን በነበራቸው ታላቅ ብሔራዊ ራእይ እስከ ወዲያኛው የምናከብራቸውን ያህል ወደ መጨረሻው ላይ ጭካኔያቸው ዳር ድንበር አጥቶ ነበር፡፡ በኋላም አጼ ዩሐንስ ጎጃምን በነቂስ አቃጥለው ቀጣሁት ብለዋል፡፡ “እስላም የሆንህ እስከ ሦስት ወር ድረስ ክርስቲያን ሆነህ ካልጠበቅኸኝ ማርያምን በሕይወትህ ቆርጠህ ጠብቀኝ” ስላሉ የወሎ፣ የሸዋ ሙስሊሞች በበኩላቸው ጎራዴ መሳል ጀምረው ነበር ይባላል፡፡ እስካሁን ስላም ጠፍቷል፡፡ ከዚህ ሁሉ በኋላ ምኒልክ “ሁሉም በእምነቱ ይተዳደር፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ልጄ ነው ብለው በአዋጅም በግንባርም ለሕዝባቸው በመግለጣቸው “እምዬ ምኒልክ” ሊባሉ ችለዋል፡፡
እውነት ይነገር! ምኒልክ ከመቅደላ አምልጠው ወደ ሸዋ ሲጓዙ በዛብህ አባደክር የተባለ ባላንጣቸው ብዙ ሠራዊት አደራጅቶ ሥልጣን አልለቅቅም ብሎ አፍቀራ (መንዝ) ላይ መሽጎ አስቸግሮ ነበር፡፡ ይሁንና ምኒልክ ጋደሎ እንደ ደረሱ የሱባ፣ የጥሙጋ፣ የአርጤማና የከረዮ ኦሮሞ ባላባቶች በደስታና በእልልታ ተቀብለው ንጉሥነታቸውን አውጀው ታላቅ ግብዣ አደረጉላቸው፡፡ በዚያ ግብዣም ላይ ምኒልክ (ያን ጊዜ ደጃዝማች) በተራቀቀ ኦሮምኛ ንግግር አድርገው ለባላባቶቹ ልዩ ልዩ ሽልማቶች ሰጥተዋቸዋል፡፡ (በነገራችን ላይ አጤ ምኒልክ ብቻ ሳይሆኑ አባታቸው ንጉሥ ኃይለ መለኮት፣ አያታቸው ንጉስ ሳህለ ሥላሴና የእሳቸውን አባት አዝማች ወሰን ሰገድ የተራቀቀ ኦሮምኛ ይናገሩና እድገታቸውና ክፍላቸውም ከኦሮሞዎች ጋር መሆኑ በጹሑፍም በቃልም የተረጋገጠ ነው፡፡
ምኒልክ በአባታቸው ዙፋን ላይ ለመቀመጥ ወደ ሸዋ በመጡ ጊዜ በባላንጣነትና በሥልጣን አላስረክብም መልክ አምጾ የነበረው በዙ አባደክር ኃይል ጠርቀምቀም ያለ ነበር፡፡ ይሁንና ከአባደክር ሠራዊት መካከል በርከት ያሉት በየጊዜው እጃቸውን ለምኒልክ በመስጠት ከሠራዊቱ ጋር ተቀላቅለዋል፡፡ አንደኛውም የበዙ አባደክር ወታደር ጎበና ዳጬ (አባጥጉ) ነበሩ፡፡ እኒህ የወታደርነት ቁመናና ግርማ ሞገስ የነበራቸው የበዙ አባደክር ወታደር ለምኒልክ ከገቡ በኋላ በፍጥነት የቤተ መንግሥቱ ባለሟል ሆኑ፡፡ ታሪካቸው እንደሚለው ደግሞ በዙ አባደክር እጁን ሰጥቶ ምህረት ጠይቆ ሲገባ ከጎበና ጋር ሲገናኙ ተቃቅፈው ተላቀሱ፡፡ (በነገራችን ላይ እንደ አስተማሪያችን ልናያቸው እንደ እውነት ምስክር ልንቀበላቸው የምንወድደው ክቡር ኦቦ ቡልቻ ስለምኒልክና ጎበና ግንኙነት የሚናገሩት ታሪክ ከየትኛውም የዘመኑ ፋብሪካ የወጣ መሆኑ አልገባኝም፡፡ የምኒልክና የታላቁ ጎበና ዳጨ ግንኙነት ይህን ሲመስል ከበዛብህ ጋር ሆነው ምኒልክን የወጉ በሙሉ ምሕረት መቀበላቸው እውነት ነው፡፡ በዛብህ ግን መላልሶ ምሕረት እየጠየቀ በመሐሉ እየሸፈተ ጥፋት በማድረሱ፣ ወዲህም ምኒልክን በግብዣ ላይ ለመግደል ሽጉጥ ስለተገኘበት፣ በተጨማሪም ስለ ሥልጣን አያያዝ ከሰዎች ጋር የተላላከው ደብዳቤ ስለተያዘበት መሳፍንቱና መኳንንቱ የሞት ፍርድ ፈረዱበት፡፡ ያን ጊዜ ነው እናት አይዋጁ የተባለች የዘመኑ የቡልጋ አዝማሪ (እንደ ዶክተር ሥርግው አገላለጥ)
“ጋላም አርፈህ ተኛ አውልቅ ጀልዶህን
ያማራውም ጎበዝ ፍታ ኮርቻህን
በእሳት አቃጠሉት የሚያባንንህን
“አንተም ጨካኝ ነበርህ ጨካኝ አዘዘብህ
እንደ ገና ዳቦ እሳት ነደደብህ”
አለች ይባላል፡፡ (እሳት ነደደብህ የተባለው በጥይት ሲደበደብ ከጥይቱ ጋር የሚበተነው አረር ልብሱ ላይ አርፎ እሳት ስለተያያዘ አካሉ በተጨማሪም በእሳት ስለተለበለበ ነው፡፡)
ምኒልክ ለበዛብህ ተደጋጋሚ ምሕረት ሰጥተው በሰላም ይኖር ዘንድ ያሳዩትን ፍቅር በመጣስ እስከ ግድያ ሙከራ መድረሱ የተጠቀሰውን ፍርድ መስጠት ግዴታ ሆኗአል፡፡ አለዚያ አጎታቸው ኃይለ ሚካኤል ሣኅለ ሥላሴ ከባለቤታቸው ከወ/ሮ ባፈና ጋር አድማ አቀነባብሮ በሕይወታቸው ላይ ሲነሳ ምኒልክ የግድያ ትዕዛዝ ወይም በወቅቱ ይደረግ እንደነበረው ንብረት አልቀሙም፡፡ ስለዚህ የምኒልክን ደግነት፣ አዛኝነትና ርኅራሄ የተመለከተው ሰው ሁሉ “እምዬ ምኒልክ” ይላቸው ገባ፡፡
ስለባለቤታቸው ስለ ባፈና ትንሽ ነገር እንጨምርበት፡፡ ወይዘሮ ባፈና ምኒልክን ሲያገቡ ብዙ ልጆች የነበሩአቸውና በዕድሜም ረገድ ምኒልክን በብዙ የሚበልጡአቸው ነበሩ፡፡ (እቴጌ መነን አፄ ኃይለ ሥላሴን ስድስት ዓመት ይበልጡአቸው ነበር – የራስ እምሩን ማስታወሻ ያነብቡአል) ወይዘሮ ባፈና ከምኒልክ ልጅ ለመውለድ ስላልቻሉ አንዲት ልጃቸውን ከሣኅለ ሥላሴ ልጆች ለአንደኛው በመዳር ይህንን ክፍተት ለመሙላት ይሞክራሉ፡፡ ስለዚህ ኃይለ ሚካኤል የተባለውን ያልተሟላ ጤንነት ያለውን የሣኅለ ሥላሴ ልጅ አግባብተው ምኒልክን ለመገልበጥ ሞከሩ፡፡ ምኒልክ ይህን ሁሉ ይከታተሉ ነበር፡፡ በዚህ አድማ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑትን ሁሉ አስሮ መቅጣት የተለመደ በሆነ ነበር፡፡ ዳሩ ግን አጎታቸውንም ሚስታቸውንም አልቀጡአቸውም፡፡ ይልቁንም ባለቤታቸው ወይዘሮ ባፈና ከአፈንጉሳቸው ጋር እንደሚማግጡ ያወቁ ስለነበረ ሁለቱንም ከእልፍኝ አስጠርተው “ሁለታችሁን ልድራችሁ ነው” ማለታቸው በጽሑፍ ጭምር ተረጋግጦአል፡፡ በመጨረሻውም ለባፈና መተዳደሪያ የሚሆን መሬትና ሀብት ሰጥተው ከአፈንጉሥ በዳኔ ጋር አጋቡአቸው፡፡ የምኒልክ አርቆ አሳቢነትና ሰብዓዊነት ይህን መሳይ ነበር፡፡
እንደሚባለው አጼ ምኒልክ አፈንጉሥ በዳኔንና ባፈናን ፊት ለፊት ባነጋገሩበት ጊዜ “ሁለታችሁን ልድራችሁ ነው” ሲሉ ታማኝ አገልጋያቸው የነበሩት አፈንጉሣቸው “እንዴት ሲደረግ ጌታዬ ምኒልክ የገባበትን ጭን እኔ የምደፍረው” ሲሉ “ወስላቴ በምስጢር ስታደርገው ግን መቼ እንዲህ አልህ” በማለት አፊዘው ራሳቸው ደግሰው አጋቡአቸው ይባላል፡፡ አፈንጉሥ በዳኔ ለምኒልክ በሥራ በኩል እጅግ ታማኛቸውና በተሰማሩበት ኋላፊነት እንከን ያልነበራቸው ሰው እንደሆኑ ይወሳል፡፡
ስለ ምኒልክ ሰብዓዊነትና አርቆ ተመልካችነት ብዙ ማስረጃዎች አሉ፡፡ አንዱም በጦር ሜዳ ያሳዩት የነበረው ምሕረትና ርህራሄ ነው፡፡ እንደሚነገረው በራስ ጎበና የሚመራውን የሸዋ ጦር የጎጃም ጦር መሪ ራስ ደረሶ በየጊዜው ለፍልሚያ ሲፈታተኑት ቆይተው በኋላ እምባቦ ላይ ንጉሦቹ በተገኙበት ትልቅ ጦርነት ተካሂዶ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ቆስለው ተማረኩ፡፡ በዚህን ጊዜ ንጉሥ ምኒልክ የንጉሥ ተክለ ሃይማኖትን ቁስል እየጠረጉ ፋሻ እያሰሩላቸው ጠቦት እያሳረዱ እንዳከሙአቸውና እቴጌ ጣይቱም ታላቅ እንክብካቤ እንዳደረጉላቸው ዜና መዋዕሉ ያወሳል፡፡ ይኸ ብቻ አይደለም፡፡ አጼ ሚኒልክ ከንጉሥ ተክለሃይማኖት ጋር የነበራቸው ቅራኔ በከፋና በወለጋ ግዛቶች ምክንያት ነበር፡፡ በኋላ ግን ከፋን መልሰው እንደ መረቁላቸው ታውቋል፡፡ (ለንጉስ ተክለሃይማኖት የንግሥናን ማዕረግ ንጉሠ ነገሥት ዩሐንስ ሲሰጡአቸው ንጉሠ ጎጃም ወከፋ ብለው ነበር) ንጉስ ተክለሃይማኖት በኋለኛው ዘመን ለወዳጆቻቸው “እባካችሁ ስለምኒልክ አንድም ክፉ ነገር እንዳትነግሩኝ፡፡ የምኒልክን ሞት ሳልሰማ መሞትን እመኛለሁ፡፡ ይሉ ነበር፡፡
በሌሎች መጣጥፎች ላይ እንዳመለከትሁት ምኒልክ ከአድዋ ጦርነት በኋላ የኢጣልያንን ምርኮኞች እያከሙና እያሳከሙ፣ እያስታመሙና እየቀለቡ ባሳዩአቸው እንክብካቤ አለም ዓቀፍ ክብርና ዝና ተቀናጅተዋል፡፡ ይኸ የሰብዓዊነት ማስረጃ በፈንጆቹ በኩል “ከአፍሪካ የማይታኝና የማይታሰብ ሥልጡን መሪ” ተብለው ተደንቀዋል፡፡ (ከተማረኩት የኢጣልያ ሠራዊት መሪዎች መካከል ጄኔራሎች፣ ኮሎኔሎች፣ ማጆሮችና ቲኒንቲዎች በብዛት ይገኙ ነበር፡፡
አጼ ምኒልክ ከሕዝብ ጋር የነበራቸው ትብብርና ፍቅር እጅግ ድንቅ እንደነበር የሚያስረዳ ሌላ ጉዳይ አለ፡፡ እንደሚባለው ንጉሠ ነገሥቱ በየሳምንቱ በበቅሎአቸው አዲስ ዓለም (55 ኪሎ ሜትር ርቀት) እየሄዱ አስቀድሰው ይመለሳሉ፡፡ ይህን ሁሉ ርቀት አብረዋቸው መሣሪያ ይዘው የሚከተሉአቸው በርካታ ሰዎች ደግሞ ነበሩ፡፡ ታዲያ መኪና መጣና ምኒልክም መንዳት በመቻላቸው በአራዳ ጊዮርጊስ የተሰበሰቡ የዘወትር አጃቢዎቻቸውን “እናንተም አርፋችሁ ጠብቁኝ፡፡ በአውቶሞቢል ሄጄ እመለሳለሁ” ብለው ተሰናብተዋቸው መንገዳቸውን ይሄዳሉ፡፡ እነዚያ አዎች ከአራዳ ጊዮርጊስ ሳይለዩ ሲጠብቁ ቆይተው ምኒልክ ሲመለሱ አገኙአቸው፡፡ ሰዎቹ አኩርፈዋቸዋል፡፡ ምኒልክ ቢለማመጡ ቢለማመጡ ሰዎቹ ይቅርታ ማለት አልሆነላቸውም፡፡ ከሕዝቡ ጋር የነበራቸው ግንኙነት የአባትና የልጅ ዝምድና ስለሆነ “እንግዲህ ካሳዘናችሁኝ ሰልሜ ታርፋላችሁ” አሉ ይባላል፡፡ ይኸ በዘመኑ እጅግ ከባድ አነጋገር መሆኑ ነው፡፡ እግረ መንገዳችውን መቀለዳቸው ነው፡፡
ቀደም ሲል እንደ ገለጥሁት ጎበና ለአጼ ምኒልክ የገቡት ከአባደክር ብዙ ሠራዊት ሲሆን ጎበዝና ደፋር ተዋጊ በመሆናቸው ከደጃዝማችም በላይ ራስ ተብለዋል፡፡ ራስ ጎበና ይህን ሹመት ያገኙት በአንድ ቀን ለእሳቸውና ለዳርጌ ሳህለ ሥላሴ በተሰጠው ሹመት ነው፡፡ ከንጉሥ ሳህለ ሥላሴ ልጅና ከራሳቸው ከምኒልክ አጎት (መስፍን) ቀድመው ራስ መባላቸው ድፍን ኢትዮጵያን ያስደነቀ ሹመትና የምኒልክ ፍትሐዊነት መሆኑ ሲወሳ ኖሯል፡፡ እንዲያውም አጼ ምኒልክ ስለ ጎበና ሲያነሱ “ጎበና ጎበና የእኔ – አንተ የጦር ንጉሥ ያገር ንጉሥ እኔ” ይሉ ነበር ይባላል፡፡ በፍቅር፣ በአክብሮትና በአድናቆት! ታዲያ የራስ ጎበና ልጅ ደጃች ወዳጆ የምኒልክን ልጅ ወይዘሮን ሸዋረጋን አግብተው ልጅ እንደ ወለዱ ይነገራል፡፡ ወጣቶቹ ለምን እንደ ተፋቱና የተወለደውም ልጅ ዕጣ ፋንታ ምን እንደሆነ አላውቅም፡፡
የአረብ ዘመቻውና የኅብረቱ መሠረት
ከዚች አጭር መጣጥፍ ምን ዓይነት ውጤት እንደሚገኝ አላውቅም፡፡ አጀማመሬም ረጅሙን የምኒልክ ታሪክ በአጭሩ ለማስረዳት እችላለሁ ብዬ አይደለም፡፡ በታሪካችን ውስጥ በዚህ ጽሕፈት አማካይነት ምን ያህል ርቀት እንደምንሮጥ ለማየት ብቻ ነው፡፡ እስካሁን የሞከርሁት ምኒልክ የሚለው ስም ከዘመኑ በፊት የተከሰተ፤ ሰውየው ከዘመኑ በፊት የነቃ፣ ሥልጡን፣ በተፈጥሮው ሩኅሩህና ሰብዓዊ መሆኑን ለማመልከት ነው፡፡ ዝርዝር ማስረጃውንና ታሪኩን ማንበልበል ቀላል ነው፡፡ እኔም እንዲሁ በአእምሮዬ ውስጥ ከመዘገብኋቸው ዓበይት ነጥቦች መካከል ትዝ የሚሉኝን ብቻ ነው ለዛሬ ያቀረብኩት፡፡ አለዚያ የምኒልክን ሰብዓዊነት በሚመለከት የፈረንጆችንም የኢትዮጵያውያንም ምስክርነት በሰፊው መዘርዘር ቀላል ነው፡፡ እሸት እሸት የሆኑ መረጃዎች አሉ፡፡
አጼ ምኒሊክ ቀደም ሲል ንጉሰ ነገስት ብለው ማሕተም አሳትመው ከአጼ ዮሐንስ ጋር በመጠነኛ ፍጥጫ ላይ ቆይተው ነበር። አጼ ዮሐንስ ምንም እንኩዋን የነጋሲነት ትውልድ ባይኖርባቸውም ጄነራል ናፒዮር በአጼ ቴዎድሮስ ላይ በነበረው ተልእኮ ተባባሪና ደጋፊ ስለሆኑ በርከት ያለ መሳሪያ መሸለማቸው ይታወቃል። እንግሊዞች ለዚህ ተልእኮአቸው ምኒልክም እንዲተባበሩ ቢጠይቋቸው ትብብር ሳያሳዩ ቀርተው ከመሳሪያ እርዳታው ተካፋይ አልሆኑም። ይልቁንም ምኒልክ ቴዎድሮስን እንደአባት ያዩአቸው ስለነበረ ከሴራው አልተሳተፉም። ራስ ጎበና ሁኔታውን ለመሰለል ሞክረው እንደነበረና ከእንግሊዞች ጋር ግን አለመገናኘታቸው ይወሳል። ለማንኛውም ንጉስ ምኒልክ አጼ ዮሃንስን በንጉሠ ነገስትነት በተቀበሉ ጊዜ በተስማሙት መሰረት ተበታትነው የኖሩትን የምእራብ ኢትዮጵያ ግዛቶች ወደ ውህደቱ በማስገባቱ ረገድ በሚያካሄዱት ዘመቻ አንዳች ተቃውሞና ጣልቃ ገብነት እንዳያስገቡ ንጉሠ ነገስቱ ተስማምተውላቸዋል። በሰሜኑ በኩል ውህደቱን በማምጣቱ ረገድ አጼ ቴዎድሮስ ስራውን በአብዛኛው ጨርሰውታል። ስለዚህ በምኒልክ በኩል በራስ ጎበና አዛዥነት በጉድሩና በአዋሽ ወንዝ አካባቢ የነበሩት ቀድሞም በአምሃየስ ፣ በአስፋወሰንና በሳህለስላሴ ዘመን በኅብረቱ ውስጥ ገብተው የነበሩትን ኦሮሞዎች በማስተባበር አንድነቱ የበለጠ ስር እንዲሰዽድ አድርገዋል። በሚቀጥለው ርምጃ የግቤ፣የጎጀብና የዴዴሳ አካባቢ ስፍራዎች በራስ ጎበና ልጅ በደጃዝማች ወዳጆ አማካይነት በውይይትና በድርድር ብቻ የውህደቱ ተሳታፊዎች ሆነዋል።
የጎበና “የአረብ እንቅስቃሴ” የተጀመረው በ1860-1870 ድረስ ባሉት አመታት ነው።በእነዚህም አስር አመታት የሊበንን ነዋሪዎች፣ በሙገር ጅረት አካባቢ ነዋሪዎች ከዚያም ጊቤን ተሻግረው ነዋሪዎቹን እያሳመኑና እያስተባበሩ በፈቃዳቸው ያለ ደም መፍሰስ ከውህደቱ ተሳታፊዎች ለመሆን ተስማምተዋል:: ከነዚህም መካከል የጅማው አባ ጅፋር ይገኛሉ:: የአባ ጅፋር እናት ህብረቱ ለሁሉም ጥቅም እንደሆነ በማወቅ ለልጃቸው በሰላም እንዲገቡ ምክር እንደሰጧቸው ገልጠዋል::
ከዚህ በኋላ ሁለተኛው የራስ ጎበና ውህደቱን የማጠናከር ተግባር የተከናወነውበ 1870 – 1880 ነበር፡፡ በዚህ ዘመቻ ጎበና አባ ጥጉ የሌቃ ነቀምቴና የሌቃ ቄለሞን ባላባቶች (መሪዎች) ኩምሳ ሞረዳና ጆቴ ቱሉን አንዲት ጥይት ሳትተኮስና በሰላም የአንድነቱ አቋም አባላት አድርገዋቸዋል:: የአጼ ምኒልክ የክርስትና ልጅ የሆኑት ደጅ አዝማች ገብረ እግዚአብሄር ሞረዳ (የሌቃ ነቀምቴው) እና የሌቃ ቄለሙ ደጅ አዝማች ጆቴ ቱሉ ከጦር ሚኒስትሩ ከራስ ጎበና፣ ከኢሊባቡር ገዥ ከራስ ተሰማ ናደው ጋር በመመካከር የኢትዮጵያ ዳር ድንበር እስከ ነጭ አባይ መሆኑን በማመን ዛሬ ኡ ጋንዳ እስከሚባለው አገር ድረስ ሄዶ የሚያቀና የጦር አስኳል ልከው ነበር:: ይሁንና አስመራ ላይ አንድ ችግር ተፈጠረ:: ጣሊያኖች ከህንድ ሀገር ያስመጡአቸው ላሞች በሽተኞች ሆነው ተገኙና ከዚያ የጀመረ የከብት በሽታ ወደ ኢትዮጵያ ተዛመተ:: “ ክፉ ቀን ” በተባለው በዚህ በሽታ እስከ ኢሉባቦር፣ ወለጋ፣ ሲዳሞና ከፋ ድረስ አያሌ ሺህ ህዝብና ከብት አለቀ፡፡ ሠራዊቱም የዘመቻ ተግባሩን ማቋረጥ ግዴታው ሆነ:: (የአረብ ዘመቻ ማለት የምእራብ ዘመቻ ማለት ነው፡፡ ቃሉ ግዕዝ ነው) ለነጭ ዓባይ ማስገበሩ ንቅናቄ የተመረጡት የጦር አዛዥ ከራስ ተሰማ ሠራዊት ፊታውራሪ ኀይሌ የሚባሉ ሲሆኑ ስምንት መቶ ወታደሮች ይዘው ዘምተው ነበር፡፡ እርሳቸው እንደ ምንም ብለው ከስፍራው ደርሰው የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከሶባት ጅረት በስተግራ ሰቀሉ፡፡ እጅግ የሚጋረፈውን ንዳድ ለጠባቂ ለመተው አላስቻላቸውምና እርሳቸውም ሰው ሳያስቀሩ ወደ ጎሬ ተመለሱ፡፡ እንደሚባለው ከጥቂት ቀናት በኋላ ቢቸነር በሚባለው የጦር አዛዥ ሰራዊቱን አስከትሎ ከስፍራው ሲደርስ የኢትዮጵያን ይዞታ ለማስከበር ሰው ስላላገኘ ሰንደቅ አላማውን አውርዶ የግብጽን ሰንደቅ አላማ ሰቀለ፡፡ (ተክለ ጻድቅን፣ ብላቴን ጌታ ኅሩይን፣ ሥርግው ሀብለ ሥላሴን፣ ጸሐፌ ትእዛዝ ገብረ ሥላሴን ወዘተ ወዘተ ያነብቡአል)
ዘመቻው በንዳድ፣ በሰውና በከብት እልቂት ብዙ ችግር ስላደረሰ እንደታሰበው እስከ ነጭ አባይ መፍለቂያ ሊሳካ ባይችልም በዚያው አቅጣጫ የሼህ ሆጀሌ ግዛት ቤኒሻንጉልና(ቤላ ሻንጉል) እና ቦረና ወደውህደቱ እንዲገቡ ራስ መኮንን ወልደሚካኤል ጉዲሳና ፊታአውራሪ ሃብተጊዮርጊስ ዲነግዴ የቦረና፣ የጅባትና ጫጫ ገዢ ብዙ ደክመው ተሳክቶላቸዋል። ከነሱም እኩል የወለጋ ባላባቶች ደጃዝማች ጆቴና ደጃዝማች ገብረግዚአብሄር ተሳታፊዎች ሆነዋል። (በነገራችን ላይ ሼህ ሆጀሌ እስከ እድሜያቸው ፍጻሜ ድረስ ጽኑ የሆነ ኢትዮጵያዊ ስሜት እንደነበራቸው ይነገርላቸዋል፡፡)
“በአረቡ ዘመቻ” ውህደቱን በመቃወም ጦርነት የከፈተው የከፋው ንጉስ ጋኪ ሼሮኮ ነው። ጋኪ ሼሮኮ ከአጼ ሰርጸ ድንግል በቀጥታ የትውልድ ሃረግ የሚመዝዝና በማንም ስር ለመሆን አልፈልግም የሚል ነበር።እርሱም ከራስ ወልደጊዮርጊስ ጋር ተዋግቶ ተማረከ። ጦርነቱ አንዳለቀ ግን የከፋ ሴቶች ባሎቻችንን እኛ ባልደገፍነው ጦርነት ውስጥ ማግዶ አስጨረሳቸው በማለት ከስሰው መሰቀል አለበት የሚል አቤቱታ አቀረቡ። አጼ ምኒልክ ግን ጋኪ ሼሮኮን ወደ አንኮበር በመውሰድ በእንክብካቤ አቆዩት ይባላል፡፡
ስለ አርሲ ምን የምንለው አለ? በሳህለ ስላሴና በንጉስ ሃይለመለኮት (የምኒልክ አባት) ጊዜ ጥቂት ኦሮሞዎች መሸፈታቸው ይነገራል። ይሁንና በአዝማች ሰይፉና በራስ ዳርጌ አማካይነት ወዲያው ሰላም መመስረቱ ይወሳል።ራስ ዳርጌ በቅርብ በህዝቡ ዘንድ ባገኙት እውቅና፣ መልካም ስነምግባርና ሃይማኖተኛነት እዚያ በገዢነት ተመድበዋል፡፡ አርሲ ከኢትዮጵያ ክፍላተ ሃገር ጠበብ ያለችና የህዝቡም ብዛት እስካሁን አንድ ሚሊዮን ስላለሆነ የራስ ዳርጌ ወራሾች እነ ራስ ካሳ ሃይሉ ብዙ የሰላሌ ተወላጆችን ወደዚያ በመውሰድ አስፍረዋቸዋል።
እንደ በቆጂ፣ ትንሳኤ ብርሃንና ጢቾ ባሉት ከተማዎችም ብዙሃኑ ነዋሪ ጉራጌ፣ አማራ፣ ትግሬ፣ ከምባታና ኦሮሞ ነው። የምኒልክ ጸሐፌ ትዕዛዞች ባቆዩን መዘክሮች መሰረት አጼ ምኒልክ ወደ አርሲ የሄዱት በጦርነትና ለጦርነት ሳይሆን የሃረሪው መሪ አሚር አብዱላሂ አልገብርም ብሏል በተባለ ጊዜ ወደዚያ ሲዘልቁ ነበር። የጨለንቆ ጦርነት እየተባለ በሚጠቀሰው ዘመቻ ደግሞ ሃሮልድ ማርከስ እንደገለጸው የአሚሩ አመጽ ያለቀው በአስራአምስት ደቂቃ ነው። ይህም በአለም ታሪክ ያልታየና ያልታወቀ ነው። አሚሩ ሁለት ሚስቶቹን ይዞ ሲጠፋ ወዲያው በከተማው ሰላም ነገሰ። ተስፋዬ ገብረአብና ቀደም ብሎም ወዳጄና የድሮ ተማሪዬ ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ እንዳሉት ሳይሆን በጨለንቆው ዘመቻ አንድም የኦሮሞ ተወላጅ ተሳትፎ አልነበረውም፡፡ እናት አይዋጁ የምትባል (ስርጕው ሃብተ ስላሴ እንደሚሉት)የቡልጋ የኪነት እመቤት(አዝማሪ) ከገጠመቻቸው ሁለት አናቅጽ ባቀርብላችሁ
ጎበና ጎበና ጎበና ፈረሱን አማን ቢያስነሳው
ዓባይ ላይ ገታው
ጎበና ፈረሱን ፋሌ ላይ ቢያስነሳው
አረብ አገር ገታው
ጎበና ፈረሱን ቼቼ ቢለው
ሱዳን ላይ ገታው
የመዳኒት ጥቂት ይበቃል እያለች
እጅጋየሁ አድያም አንድ ወልዳ መከነች
(እጅጋየሁ አድያም ሰገድ የአጼ ምኒልክ እናት ናቸው።)
የታላቅ ብሄራዊ ቤተሰብ ምስረታ
ጥንታዊት ኢትዮጵያ (“ወያኔዎች አጠራሩን ከፈቀዱልኝ”) ጥቁር አፍሪካን፣ አለዚያም እስከ ነጭ አባይና_ቤናድር (ሞቃዲሾ) የመንና ሐድራሞትን (የማውቀው አካባቢ ነው) ማጠቃለሉ ቀርቶ የአሁኑን ቅርጽ የያዘው በ19 ክፍለ ዘመን ፍጻሜና በሐያኛው ክፍለ ዘመን መግቢያ ላይ ነው። እስካሁንም ይህን አንድነት የፈታው አንዳች ሃይል አልነበረም። የኢትዮጵያ ታሪክ በአጠቃላይና ይልቁንም የምኒልክን ዘመን ታሪክ በመከታተል የታወቁት ዶክተር ሃሮልድ ማርክስ በአንድ ጽሁፋቸው ላይ እንደገለጹት አጼ ሚኒልክ ኢትዮጵያን አንድ በማድረጉ ረገድ “አንድ ታላቅ ብሄራዊ ቤተሰብ” መስርተዋል። የዚህ “ብሄራዊ ቤተሰብ” ስርዓት ደግሞ በግዴታ ወይም በማስፈራት የመጣ አይደለም። በተፈጥሮ መጣ ይሉናል was not the outcome of coercion,it was what came naturally, አዎን እንደተባለውም የሸዋ ነገስታት በአብዛኛው ከምኒልክ ወደኋላ የምንቆጥራቸው ሁሉ ኦሮምኛ ስለሚናገሩ፣ በጋብቻ ከኦሮሞዎች ጋር በመተሳሰራቸውና ለሎችንም በዚህ ረገድ ስላደፋፈሩቸው ወዲህም የሞጋሳ (የጡት ልጅነት) ስርአት ስለተዘረጋ “አንድ ብሄራዊ ቤተሰብ” ሊመሰረት ችሎአል።
በሌሎች መጣጥፎቼ ያነሳኋቸውን ነጥቦች ላለመደጋገም እየሞከርሁ ነኝ። ከመቶ አመት በፊት ተበጣጥሶና በጎሳ መሪዎችና የክፍለ ሃገራት ወቅታዊ ገዢዎች _ዘመነ መሳፍንት _ተበታትኖ የኖረ አገር ወደ ህብረት የመጣበት ዘመንና ያንን ያስፈጸሙ የታሪክ ከዋክብት በአባትነት ሊከበሩ፣ በጀግንነት ሊዘከሩ ሲገባ ዛሬ ላይ የሚጨፈጨፉት ለምንድነው? የታሪክ ክብርና የብሄራዊ አላማ ጉዳይ እንደዘመኑ ገዢዎች ቅኝት ነው። ወዳጆቼና ወገኖቼ ለመሆኑ በህልማችሁም በቅዠታችሁም አገር የሚሸጥ መንግስት ይመጣል —- ይኖራል ብላችሁ አስባችሁ ታውቃላችሁ? ለመሆኑ ሕዝብን ከህዝብ ለማጫረስ የሚፈልግ መንግስት ይኖራል ብላችሁ አምናችሁ ታውቃላችሁ? ለመሆኑ በሕልምም ሆነ በቅዠት መንግስት ከህዝብ ይቀማል፣ ይሰርቃል፣ ደም ያፈሳል፣ ቀምቶ ራሱን፣ ያበለጽጋል የሚል ወሬ ብትሰሙ ታምናላችሁን በሌላ አለም ማለቴ ነበር። ለመሆኑ ትልቁ ሌባ የመንግስት መሪ መለስ ነው ብሎ ጉግል (Google) ሲገልጥላችሁ ምን ተሰማችሁ? (ሶስት ቢሊዮን ዶላርስ)
በእኔ በኩል የርስበርሱ ጭፍጭፍ መሰናዶ እያስፈራኝ ነው፡፡ “የምኒልክ ሃውልት ይፍረስ” የቴሌቪዥን ጥሪ! “በኦሮሞ ጥያቄ ስም”! የወያኔ የጦር አዋጅ ነው። ከዚያው ከሰፈራቸው “ወያኔ” ከአስራአምስት ከማይበልጡት ሴረኛና ጠንቀኛ ማእከላዊ ገዢዎቻችን የሚገላግለንና ለእኛም ጋር የሚታረቅ ሽምብራ የሚያክል ወያኔ የለም? ኢትዮጵያን የሚያድን! ትግሬውንም የሚያድን?
በነገራችን ላይ የአጼ ምኒልክ ዘመን የኦሮሞ ልጆች ከትልልቁ የመንግስት ሃላፊነት፣የጦር አበጋዝነትና አስተዳደር ስራ ላይ የወሳኝነትን ሃላፊነት የተቀዳጁበት ነበር። ለመሆኑ ወያኔ የኢትዮጵያን ህዝብ ከታሪካዊ የአገር አንድነት ተጋድሎ፣ውጤትና ታሪካዊ በረከት ሊያለያይ ይችላልን? ወያኔኮ ሺህ አመት የመግዛት ዕድል ቢኖረው አንዲት ትምህርት ላለመካፈል ጭንቅላቱን አውቆ የዘጋ የክፋት ሁሉ ምንጭ ነው፡፡ መሄድ ያለበት።

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen