በኤልያስ ገብሩ ጎዳና
‹‹ይህ ሽልማት የእኔ ብቻ አይደለም፡፡ የእናንተም ነው፡፡ …››
‹‹በእስር ላይ የምትገኙ ጋዜጠኞች እና ጦማሪያኖች የእኔ ጀግኖች ናችሁ››ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ
‹‹አሁን ደስተኛ ነኝ››
‹‹እስክንድርን ምግብ ማብሰል እያለማመድኩት ነው››አቶ አንዷለም አራጌ
ከትናንት በስትያ ሰኔ 03 ቀን 2006 ዓ.ም ከቀኑ 6፡00 ሰዓት ላይ ከቅርብ ጓደኛዬ እና የሙያ ባልደረባዬ ጋዜጠኛ አናንያ ሶሪ ጋር ወደቃሊቲ ማረሚያ ቤት [እስር ቤትም ነው] አምርተን ነበር- ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋንና የአንድነት ፓርቲ ጸሐፊ የሆኑትን አቶ አንዷለም አራጌን ለመጠየቅ፡፡ የተለመደውን የፖሊስ ፍተሻ አልፈን ወደ ውስጥ ስንዘልቅ የሰማያዊ ፓርቲ የድርጅት ጉዳይ ኃላፈ አቶ ብርሃኑ ተ/ያሬድ ፣ አቶ ሳሙኤል የተባሉ አባልና የ‹‹ነገረ ኢትዮጵያ›› ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው እስክንድርን ሊጠይቁ ቀድመውን ደርሰው ነበር፡፡
…እስክንድርን እና አንዷለምን አስጠራናቸው፡፡ ሁለቱም ሲያዩን ደስ አላቸው፡፡ በተለይ በተለይ የእስክንድር ፈገግታ በጣም ደማቅ ነበር፡፡ ተከፋፍለን ከሁለቱም ጋር ሃሳቦችን መለዋወጥ ጀመርን፡፡
እስክንድር በዓለም የጋዜጠኞች እና የዜና አታሚዎች ማኅበር የዓመቱ የወርቅ ብዕር የ “pen Golden of freedom 2014″ ተሸላሚ በመሆኑ ‹‹እንኳን ደስ ያለህ›› አልኩት፡፡ ‹‹አመሰግናለሁ፡፡ ትናንት አንድ ልጅ ሊጠይኝ መጥቶ ነግሮኛል›› ካለን በኋላ ደግመን ስለሽልማቱ በጋራ ሃሳብ መለዋወጥ ቀጠልን፡፡ እስክንድር ሽልማቱ አዲስ መሆኑን አላወቀም ነበር፡፡
በመሆኑም ስለሽልማቱ ሁኔታ፣ ማን እንደሸለመው፣ ሽልማቱ የት እንደተደረገ፣ ሽልማቱን ማን እንደተቀበለለት [ሽልማቱን የተቀበለው በኢትዮጵያ በሽብርተኝነት ክስ ወንጀለኛ ተብሎ ከባልደረባው ፎቶ አንሺ ጋር 11 ዓመታት ከተፈረደበት በኋላ በይቅርታ የተለቀቀው ስዊድናዊ ጋዜጠኛ ማርቲን ሽብዬ ነበር]፣ የሽልማት ሥነ-ሥርዓቱ ምን እንደሚመሰል፣ በሽልማቱ እነማን እንደተገኙ …ያወቅነውን ሁሉ ነገርነው፡፡
‹‹ይህንን አላዋኩኝም፣ ሰርካለም (ባለቤቱ) ለምን በቦታው አልተገኘችም?›› በማለት ጠየቀንና በድጋሚ ደስ ብሎት ጣቶቹን በሽቦ ውስጥ አሾልኮ ጨበጠን፡፡ ወዲያው ይህቺን መልዕክት ተናገረ፡-
‹‹ይህ ሽልማት የእኔ ብቻ አይደለም፡፡ የእናንተም ነው፡፡ የኢትዮጵያዊ ጋዜጠኞች ነው፡፡ ሁላችንንም ይመለከተናል፡፡ ለሁላንችም ይገባናል፡፡ ይሄንን ሽልማት የምመለከተው ሐሳብን በነጻነት ከመግለጽ የመብት ጥሰት አኳያ ብቻ አይደለም፡፡ ለሌሎች የዜጎች መብቶች ሲሉ ለታገሉ እና እየታገሉ ላሉ ፖለቲከኞች፣ የሕሊና እስረኞችም ጭምር ነው፡፡ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ከሌሎች ከተነፈጉ መብቶች ተለይቶ የሚታይ አይደለም፡፡ ሁሉንም መብቶች እናገኛቸዋለን፣ ወይም እናጣቸዋለን፡፡ ለዚህ ደግሞ ጸንተን እንታገል፣ ትግላችን ግን ሰላማዊ ብቻ መሆን አለበት፡፡ …››
እስክንድር ደስ ብሎት ሃሳቡን መናገሩን ቀጥሏል፡፡ እኔ ለተወሰኑ ቀናት በማዕከላዊ መታሰሬን ሰምቶ ስለነበረም ‹‹ማዕከላዊ እያለህ የታሰሩትን ጋዜጠኞች እና ጦማሪያኖች ለማግኘት ችለህ ነበር?›› ብሎ ጠየቀኝ፡፡ እነሱን በአካል ማግኘት አለመቻሌን ነገር ግን ከእነሱ ጋር ታሥረው የነበሩ ሌሎች ተጠርጣሪ ዜጎችን አግኝቼ በእስር ስላሉበት ሁኔታ መጠየቄን ነገርኩት፡፡
የታሰሩት ጋዜጠኞች እና ጦማሪያኖችን ቤተሰብ ማግኘት እችል እንደሆነና ከቻልኩም በእነሱ በኩል መልዕክቱ ይደርስለት ዘንድ በድጋሚ ጥያቄያዊ ሃሳቡን አቀረበልኝ፡፡ የተወሰኑ የእስረኛ ቤተሰቦችን ማግኘት እንደምችል አስረዳሁት፡፡
‹‹የታሰራችሁ ጋዜጠኞች እና ጦማሪያኖች የእኔ ጀግኖች ናችሁ፡፡ አከብራችኋላሁ፡፡›› ብለህ ንገርልኝ አለኝ – ደጋግሞ፡፡ …
በዕለቱ ከሰዓታት በፊት ሰናይት ታከለ የምትባል ወዳጄም እስክንድርን ልጠይቀው ቃሊቲ እንደምሄድ በነገርኳት ጊዜ ‹‹እንደማከብረው እና እንደማደንቀው ንገርልኝ›› ያለችኝን መልዕክት ለእስክንድር አደረስኩላት፡፡
እሱ ግን ሳቅ እያለ ‹‹ተሳስተሻል! …ተሳስተሻል! …ተሳስተሻል›› ብለህ ንገራት አለኝ፡፡ ‹‹ለምን?›› አልኩት፡፡ ‹‹ገና ምን ሰርቼ?›› በማለት በዚያ ትሁት አንደበቱ መለሰልኝ፡፡ በእውነት መልሱ አስደመመን፡፡ ዋይ እስክንድር፣ ፍጹም የተለየ ታላቅ ሰው!!!
እስክንድርን እናናግረው የነበርን ጠያቂዎች ወደ አንዷለም አራጌ ዞርን፡፡ አንዷለም ጋር የነበሩት ደግሞ ወደ እስክንድር፡፡
አንዷለም የስፖርት ቲ-ሸርት ከቁምጣ ጋር ለብሷል፡፡ ጥቁር መነጽር አድርጓል፡፡ ረጋ ብሎ ፈገግ በማለት ‹‹ምን አዲስ ነገር አለ?›› በማለት ጨዋታ ጀመረ፡፡ አንዷለም የእስክንድርን ሽልማት ሰምቶ ኖሮ፣ ‹‹አሁን ከምሳ በኋላ ጣፋጭ የለውዝ ሻይ እሱን እና ጓደኞቻችንን በመጋበዝ ‹እንኳን ደስ ያልህ!› በማለት ሰርፕራይዝ አደርገዋለሁ፡፡ ምግብ ማብሰል እያለማመድኩት ነው፡፡ ብዙ ጊዜ እኔ ነኝ ሰርቼ የማበላው፡፡ በልጅነቱ በበርገር ያደገ ልጅ አሁን ሽንኩርት እና ቲማቲም መክተፍ ችሏል …›› በማለት በቀልድ ነገረን፡፡
‹እነማን ከእናንተ ጋር አሉ? በአንድ ክፍል ውስጥስ ስንት ናችሁ? ጊዜያችሁንስ እንዴት ነው የምትጠቀሙበት?›› የሚል ጥያቄ አቀረብንለት፡፡
‹‹ለረዥም ጊዜ፣ በጣም አስቸጋሪ ክፍል ውስጥ፣ መሬት ላይ ስንከባለል ነበር በእስር ያሳለፍሉት፡፡ አሁን አቶ ስዬ አብርሃ ታስሮ በነበረበት ጥሩ በሚባል ክፍል ውስጥ ለአምስት ታስረን እንገኛለን፡፡ አቶ መላኩ ተፈራ፣ አቶ መላኩ ፈንታ ና አንድ ባለሃብት አብረውን ናቸው፡፡ አሁን አልጋ ላይ መተኛት ጀምሬአለሁ፡፡ ይሄ ለእኔ እንደ አዲስ ሕይወት ነው፡፡ አሁን ደስተኛ ነኝ፡፡ …ጊዜያችንን በጥሩ ሁኔታ ከፋፍለን እየተጠቀምንበት ነው፡፡ እናነባለን፣ እንወያያለን፣ የምንፈልጋቸውን መጽሐፍት ግን በምንፈልገው ጊዜ አናገኝም፣ በዚህ በኩል መጠነኛ ችግር አለ፡፡ በተረፈ ደህና ነኝ፡፡ እኔ ተስፈኛ ነኝ፡፡ እናንተም በተሰማራችሁበት ዘርፍ የምትችሉትን ሁሉ ለሀገራችሁ ለውጥ መታገል አለባችሁ…››
ከሁለቱም ጋር የነበረንን የ30 ደቂቃ ቆይታ ሳንጠግብ ‹‹በቃችሁ›› የሚለው የፖሊስ ድምጽ ተሰማ፡፡ ‹‹እናመሰግናለን፣ በቃ ሂዱ›› ሲል አንዷለም በእርጋታ ተናግሮ በሽቦ ስር አሾልኮ እጆቻችንን ጨበጠን፡፡
እስክንድር ደግሞ ‹‹‹ሲመቻችሁ ብቻ መጥታችሁ ጠይቁን፣ ሥራ እንዳይበደል!፡፡ ሥራችሁን ሥሩ›› በማለት ለእኛም ያለውን አሳቢነት ከምክሩ ጋር ደጋግሞ ገለጸልን – ሁሉንም ሰላም በሉልኝ በማለት፡፡ እንግዲህ እስክንድርን የምትሉ ሁሉ ሰላምታውን በእኔ በኩል አድርሻለሁ፡፡
Keine Kommentare:
Kommentar veröffentlichen