Netsanet: ጦማሪያኑን እና ጋዜጠኞቹን በተመለከተ ችሎቱ ለፖሊስ ጠንካራ ትዕዛዝ አስተላለፈ

Donnerstag, 19. Juni 2014

ጦማሪያኑን እና ጋዜጠኞቹን በተመለከተ ችሎቱ ለፖሊስ ጠንካራ ትዕዛዝ አስተላለፈ

June 18/2014

በ አሸናፊ ደምሴ

በቁጥጥር ስር ከዋሉ ባለፈው ቅዳሜ (ሰኔ 7 ቀን 2006 ዓ.ም) 50ኛ ቀናቸውን በእሰር ያሳለፉት ስድስቱ ጦማሪያንና ጋዜጠኞች ለአራተኛ ጊዜ የ28 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ተፈቅዶባቸዋል። ለአራተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት የቀረቡት ከዞን 9 ጦማሪያን መካከል ዘላለም ክብረት፣ ናትናኤል ፈለቀና አጥናፉ ብርሃኔ ሲሆኑ፤ ጋዜጠኞቹ ደግሞ ተስፋለም ወልደየስ፣ ኤዶም ካሳዬ እና አስማማው ወ/ጊዮርጊስ ናቸው። በዕለቱ ችሎቱ መርማሪ ፖሊስ የሚያቀርባቸውን ተደጋጋሚ ምክንያት አጠንክሮ በመፈተሽ በቀጣይ ቀጠሮ ፈፅሟቸው ሊመጣ የሚገቡ አራት ተግባራትን በግልፅ በማስቀመጥ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
zone 9999

በፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 1ኛ ወንጀለ ችሎት በዕለቱ የቀረቡት ጦማሪያንና ጋዜጠኞች ፖሊስ የመሰረተባቸውን የሽብርተኝነት ክስ በተመለከተ የደረሰበትን ማስረጃዎች ለፍርድ ቤቱ ለማሰማት ነበር። በችሎቱ ጥበት ምክንያት አንዳችም የውጪ ሰው ወደ ውስጥ ሳይዘልቅ የተከናወነው ችሎቱ በብዙዎች ዘንድ “የዝግ ችሎት ነው ወይ?” የሚያሰኝ ጥያቄን ቢያስነሳም ለጦማሪያኑና ጋዜጠኞቹ በጥብቅና የቆሙት ጠበቃ አመሃ መኮንን ግን ችሎቱ ጠባብ በመሆኑ ነው የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። በዕለቱ በግቢው ውስጥ በርካታ ቁጥር ያላቸው ጋዜጠኞች ዲፕሎማቶችና የታሳሪዎቹ ወዳጅ ዘመዶች ተገኝተው ነበር።

ፍርድ ቤቱ የማዕከላዊ ፖሊስ በታሳሪዎቹ ላይ ካለፈው ቀጠሮ መልስ አገኘዋቸው የሚላቸውን መረጃዎችና ሰራዋቸው የሚላቸውን ተግባራት በተመለከተ ለፍርድ ቤቱ ሲያስረዳ፤ በከፊል ሰነዶችን ማስተርጐሙን፤ በከፊል የባንክ ማስረጃዎችን ማግኘቱንና በከፊል የቴክኒክ ማስረጃዎችን ስለማሰባሰቡ ቢገልፅም በደፈናው ግን “ብዙ ስራ ሰርተናል፤ ብዙ ስራም ይቀረናል” ሲል ለፍርድ ቤቱ ማስታወቁን ጠበቃው ከችሎት መልስ ተናግረዋል።
በዚህም ጉዳይ ላይ ፍርድ ቤቱ ማስረጃዎች ሲቀርቡ፤ በጥቅል መቅረብ እንደሌለባቸውና በዝርዝር እንዲቀርብለት ትዕዛዝ የሰጠ ሲሆን፤ ከዚህ በኋላም ጥቅል ማስረጃን ማድመጥ እንደማይፈልግ አስታውቋል። ፖሊስ ለስራው መጓተት አሁንም እንደቀደመው ጊዜ ካቀረባቸው ምክንያቶች ውስጥ የምስክሮችን ቃል ስለአለመቀበሉ፤ ተባባሪዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል መቸገሩንና ወደ ክልል ሀገር ሄደውብኛል በሚል አባሎቹን ልኮ በቁጥጥር ስር ለማዋል እየተከታተለ መሆኑን ከመግለፁም በተጨማሪ አሁንም ሰነዶችን አስተርጉመን አልጨረስንም ሲል አብራርቷል።
የተከሳሽ ጠበቆች በበኩላቸው ለፍርድ ቤቱ ሲያስረዱ ለአራተኛ ጊዜ በጊዜ ቀጠሮ ፍርድ ቤት መቅረባቸውን አስታውሰው፤ የቱንም ያህል ውስብስብ ወንጀል ቢሆን ተጠርጣሪዎቹ እጃቸው ከተያዘበት ጊዜ ጀምሮ ያለው 50 ቀናት በቂ ናቸው የሚል መከራከሪያ አሰምተዋል። ጠበቃው አክለውም ይህ የሚያሳየው ፖሊስ ከመነሻው አንድም ማስረጃ ሳይሰበስብ ልጆቹን የያዛቸው መሆኑና ይህም ሕግን የጣሰ ተግባር ነው ሲሉ አስረድተዋል። ሌላው በጠበቆች በኩል የቀረበው አቤቱታ ፖሊስ በተደጋጋሚ የሚያነሳቸው ተመሳሳይ ምክንያቶች በመሆናቸው የቀረቡትን ምክንያቶች ውድቅ አድርጐ ተጠርጣሪዎቹን በዋስ እንዲለቅ፤ አልያም ፍርድ ቤቱ ሕጋዊ ምክንያት አለኝ ብሎ የሚያምን ከሆነ ይህ የመጨረሻ የጊዜ ቀጠሮ ይሁንልን ሲሉ ስለመጠየቃቸው ጠበቃው ተናግረዋል።
የግራ ቀኙን ኀሳብ ያዳመጠው ፍርድ ቤቱም፤ ፖሊስ በተደጋጋሚ ከሚያነሳቸው ምክንያቶች ውስጥ አራት ጉዳዮችን በመምረጥ በቀጣዩ ቀጠሮ እልባት ሰጥቷቸው እንዲመጣ ትዕዛዝ የሰጠ ሲሆን፤ እነዚህ አራት ተግባራትም ተባባሪዎቻቸውን አልያዝንም፣ የምስክሮችን ቃል አልተቀበልንም፣ ሰነዶች ተተርጉመው አልመጡልኝምና ከሽብርተኝነት ጋር በተያያዘ በባንክ የተላከላቸውን ገንዘብ በተመለከተ ደብዳቤ ጽፈን ምላሽ እየተጠባበቅን ነው የሚሉትን ጉዳዮች በተመለከተ ከዚህ በኋላ ለጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ ምክንያት ሆነው ሊቀርቡ እንደማይችሉ በመግለፅ ትዕዛዝ የሰጠ ሲሆን፤ ይሁን እንጂ ፍርድ ቤቱ የጊዜ ቀጠሮውን የመጨረሻ ነው እንዳላለ ጠበቃው ተናግረዋል።
በሌላም በኩል የተጠርጣሪዎቹ ቤተሰብ እንዳይጠይቃቸው መሰናክል መኖሩንና፤ በተለይም ጋዜጠኛ አስማማው ወ/ጊዮርጊስ የወገብ ሕመም ያለበት መሆኑን በመግለፅ ወንበር ወደክፍሉ እንዲገባለት መጠየቁን ነገር ግን አሁንም ድረስ አለመፈፀሙን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል። ፍርድ ቤቱም በበኩሉ መርማሪ ፖሊሶቹ በዚህ ላይ ምላሽ እንዲሰጡ ያዘዙ ሲሆን፤ የተጠርጣሪዎቹን ቤተሰብ መጐብኘትን በተመለከተ ከተደራራቢ ስራና ከአስተደደር ጋር የተያያዘ መሆኑን በመጥቀስ የመከልከል ደረጃ ግን አልተደረሰም ሲል የተፈጠሩት ክፍተቶች እንደሚያሻሽሉ አስረድቷል። የጋዜጠኛ አስማማው ወ/ጊዮርጊስን ጥያቄ በተመለከተ ፍርድ ቤቱ በጤና ጉዳይ ላይ ምንም አይነት ድርድር የለም በሚል የሰጠውን ትዕዛዝ ለመፈፀም እንደሚቻል አሳውቀዋል።
የፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ፖሊስ የጠየቀውና ተጨማሪ 28 ቀናት የምርመራ ጊዜ በመፍቀድ ለሐምሌ 5 ቀን 2006 ዓ.ም እንዲቀርቡ አዟል።
ምንጭ፦ ሰንደቅ ጋዜጣ

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen