Netsanet: እኛ ላይ የምትጮኸው ጠብ-መንጃ ስለሌለን ነው?!!

Montag, 23. Juni 2014

እኛ ላይ የምትጮኸው ጠብ-መንጃ ስለሌለን ነው?!!

Gashaw Mersha

በነገረ-ኢትዮጵያ ጋዜጣ የተስተናደ
ጤና ይስጥልኝ!! እንደምን ሰነበቱልኝ፡፡ ዛሬ ከካሳንቺስ ስድስት ኪሎ በቤተ-መንግስቱ አጥር ስር እያለፍን እናወራለን፡፡ እንቀጥል፡፡ ከካዛንቺስ ስድስት ኪሎ ለመሄድ የታክሲ ሰለፍ ይዣለሁ፡፡ እንደ በረሃ ዘንዶ የተጥመለመለው ሰልፍ የቤተ-መንግስቱን አጥር ታኮ ፊት በር ሊደርስ የጥቂት ምስኪን ተሰላፊዎችን ከኋላ መሆን ብቻ ይጠባበቃል፡፡ ትንሽ ክብዶ(ማካበድ) ስንጨምርበት ደግሞ ከኋላ በተሰለፈውና በቤተ-መንግስቱ ጠባቂ መካከል ያለው ርቀት አንድ መትረየስ አያሥጠምድም፡፡ አንድ ሰዓት ላይ የማልቀርበት ብርቱ ቀጠሮ 6 ኪሎ አካባቢ ይጠብቀኛል፡፡ ሳላረፍድ ለመድረስ 11 ሰዓት ካዛንቺስ ታክሲ መያዣ ደርሸ የመሰለፍ ግዴታየን መወጣት ይኖርብኛል፤ ወይም ይህን ሰልፍ ትቸ የአንድ ሰዓት የእግር ጉዞ በቤተ መንግስት አጥር ስር አንገቴን ደፍቸ ማለፍ ይጠበቅብኛል፡፡በዚህ ቤተ-መንግስት ለሚያልፍ ሰው አንገቱን ደፍቶ ማለፍ ግድ ይለዋል፡፡ ይህን ማድረግ ያልቻለን አስገድደው አንገት የሚያስደፉ ስልጡን ጠባቂዎች እንደ ግሪሳ ወፍ ወረውታል ቤተ-መንግስቱን፡፡ የሆነ ነገር ፈልገው ወይም የሚያሳክክ ነገር ቢገጥምዎት እንኳን ቀና ማለት ውጉዝ ነው፡፡ ይህን ካደረጉ ደግሞ ቁጭ በል ተነስ፤ቁም ሂድ የሚል ግልምጫ ሊከተልዎት ይችላል፡፡ አለፍ ካለና ጥበቃዎቹ እጅና እግራቸውን ማፍታታት ካስፈለጋቸው ደግሞ ጡጫ ነገርም ሊቀምሱ ይችላሉ፡፡ ለምን ብሎ ጥያቄ የለም፡፡ ምክንያቱም ይህ ቤተ-መንግስት ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ ሽር ማለት የሚችል መንግስት እንጅ እንደ እኔ አይነት አመዳም ድሃ አይደለምና፡፡ እድለ ጠማማ ከሆንክ ደግሞ አንዱ የአፍሪካ ነፍሰ ገዳይ አምባገነን መሪ ከቦሌ አየር ማረፊያ እየመጣ ስለሆነ ጀርባህን ሰጥተህ ቁም ልትባል ትችላለህ፡፡ በደርግ ጊዜ ነው አሉ እንዲህ እንዳሁኑ ሊቀመንበሩ ሲያልፉ ፊትህን አዙረህ ቁም ይባል ነበር፡፡ ይህ ድርጊታቸው ስልችት ያላቸው ሴትዮ ‹‹ሰውየውን የሚጠብቁት ከአይን ነው ወይስ ከጥይት›› አሉ ይባላል፡፡ ስለዚህ ይህን አካባቢ ፈጥን ብሎ በታክሲ ላፍ ማለት ይበጃል፡፡
በዚህ ደዲቃዎችን ሳይሆን ሰዓታትን በሚጠይቀው ሰልፍ ላይ የተደረደሩት ምስኪን የሀገሬ ዜጎች ሰማያዊ ታክሲ ላይ ትኩረት አድርገው አይናቸውን ላይ ታች ያቅበዘብዛሉ፡፡ በዚህ ሰልፍ ላይ የሌለ የሰው አይነት የለም፡፡ ከወፍራም እስከ የኔ ቢጤ ሲንብሮ፡ከሰማይ ቅርቡ ሞጋጋ እስከ እንቅፋት የመሰለ ድንክ፡ከምሁራን እስከ መሰረተ-ትምህርት ምሩቅ ብቻ ሁሉንም ሊያስማማ ከሚችለው መመዘኛ ከድህነት ውጭ ሰልፉ የሰው ማህበራዊ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በነገራችን ላይ እንዲህ ታክሲዎች የመስቀል ወፍ በሚሆኑበት አጋጣሚ እንደ እኔ አይነት ቀጫጫዎች ተወዳጅነታቸው ይጨምራል፡፡ ቀጫጫዎችን በአንድ ወንበር እስከ ሶስትና አራት ሰው ለመጫን ስለሚመች፡፡ በመሆኑም እርስዎ ታክሲ ይሳፈራሉ እርስዎን ሌላ ሰው ተሳፍሮዎት ይጓዛሉ፡፡ ለምን ብሎ ጥያቄ የለም ምክንያቱም ይህ ጽሀዩ መንግስታችን ያመጣው ልማት ውጤት ነውና፡፡ በፈረንጅ ሀገር ወፍራም ሰዎች ተጨማሪ ክፍያ ይጠየቃሉ ሲባል ብሰማ መንግስቴን አጥብቄ አመሰገንኩት፡፡ እንዴት ብለው ከጠየቁኝ፤እንዲህ እመልሳለሁ፡፡ ሀገሬ ፍትሀዊነት የሰፈነባት በመሆኗ ወፍራሙም ቀጫጫውም እኩል የታክሲ ታሪፍ ስለሚከፍል፡፡ ደግሞ ኢቲቪ እንዳይማኝ፡፡ ኢቲቪ ከሰማ ግን እንዲህ ነው የሚዘግበው፡፡ ሀገራችን በታክሲ ታሪፍ ፍትሃዊነት በምስራቅ አፍሪካ አንደኛ ናት፤ አክሎም የታክሲ ሰልፈኛው ፈዛዛነት ለጎረቤት ሀገራት ምርጥ ተሞክሮ ሊቀመር የሚችል ነው ሲሉ አንዳንድ የታክሲ አሽከርካሪዎች ተናግረዋል!! ማለቱ አይቀርም ኢቲቪ ነፍሴ፤ ነፍሱ ይጥፋና፡፡ ጎበዝ በስንቱ አንደኛ ሆንን ተብሎ ይዘለቃል፡፡ ሌሎቹ ሀገራ ስራ አቆሙ እንዴ?!! በአንድ ወቅት አቶ መለስ ስለ ፍትሀዊ የገቢ ክፍፍል ሲናገሩ ሀገራችን ኢትዮጵያ ከኖርዌይ ቀጥላ ሁለተኛ ናት ሲሉ ሙድ ይዘው ነበር፡፡ ከደረጃ ጋር በተያያዘ የሆነ ወቅት ላይ ሚስተር ኦባማ የአለም መሪዎችን ሰብስበው ተወያዩ ሲባል የሰማ ካድሬ መሪዎቹ በጉብዝናቸው ነው የተመረጡት ሲል አወራለት፡፡ ጓደኛየ ካድሬውን እንዲህ ጠየቀው ‹‹የመረጣው መስፈርት አንድ ከላይ አንድ ከታች ነው እንዴ››ብሎ ነበር፡፡ በታችኛው መመዘኛ የገባው ማን እንደሆነ መቸም ገምታችኋል፡፡ የእኔ ነገር የተነሳውበትን ነገር ስቸ ወዴት ተሰነቀርኩ፡፡ ወደ ቀደመ ነገሬ ልመለስና ስለ ታክሲ ሰልፌ ላውራ፤ ሰልፍ ሰልፍ ሰልፍ………….ኡፍፍፍፍፍፍ……….
ለምንና እስከ መቸ እንዲህ እንደምንሰለፍ ባይገባኝም፡የወገኔ ድካም ግን እጅጉን ያመኛል፡፡ ተሰላፊው የሰውነቱን ክብደት መሸከም አቅቶት እግሩ የዛለው ወገቡን ይዞ፤የባሰበት እየተቀመጠ፤የቀናው ደግሞ ከጎኑ የተሰለፈችን ኮረዳ እያሽኮረመመ ሰማያዊ ታክሲ ይጠባበቃል፡፡ ኮረዳ አሽኮርማሚው እንኳ ታክሲው ባይመጣም ግድ አይሰጠውም፡፡ በስንት ደቂቃ ልዩነት ብቅ የምትለው ታክሲ ከአስራ አምስት ሰው በላይ ጭና ላፍ ትላለች፡፡ ቀሪዎቹ ሰዎች ሰማያዊ ታክሲ መጠበቃችን እንደቀጠለ ነው፡፡ ፍቅረኛው ‹‹ሰማያዊ ልብስ ለብሸ እመጣለው ያለችው ጎረምሳ በታክሲ ይደነብራል›› እንደሚባው ሰማያዊ ነገር ባየን ቁጥር እናንጋጥጣለን፡፡ እንዲህ ወደ ታክሲው ያንጋጠጥነውን ያክል ወደ ቤተ-መንግስቱ ብናጋጥጥ መና ይወርድልን ነበር አልላችሁም መቸም፡፡ ታዲያ ቤተ-መንግስት ምን የሚወርድ ነገር አለ እንዳላችሁ ገብቶኛል፡፡ ‹‹ሆድ ይፍጀው›› አለ ሰውየው ብየ አልፈዋለው፡፡ በአሁኑ ጊዜ እኮ ስለ ቤተ-መንግስቱ የማይሆን ነገር ማሰብ አሸባሪነት ነው፡፡ ቀድማ የሄደችው ታክሲ የምትመለሰው ሾፌሩና ረዳቱ መቶ ግራም ገለምሶ ካኘኩ በኋላ ነው፡፡ ከስንት ሰዓት በኋላ እንደምንም እየተንፋቀቅን በሀይለ ስላሴ ጊዜ የተገዛች ከርካሳ ታክሲ ላይ ተጭነናል፡፡ መኪናዋ በጣም ከማርጀቷ የተነሳ ግጭት ቢደርስባት ቲታነስ ሊገድለዎት ይችላል፡፡ የብሄራዊ ሙዚየም ድክመት ነው እንጅ ታክሲዋ መገኛዋ እዛ ነበር፡፡ ለማንኛውም ጠጋ በል ከሚል የወያላ ንዝንዝ ለመዳን ስል ጋቢና መሳፈር እወዳለሁ፡፡ በእዛውም ቶሎ ለመድረስ ጋቢና መቀመጥ መፍትሄ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በታክሲ ፈልፍ ያባከንኩትን ጊዜ ያካክስልኛል ብል በአለም የመጀመሪያው ውሸታም አልሆንም፡፡
ሰው እንደ ቲማቲም ግጥግጥ ብሎ ተጭኗል…….ተሳፋሪዎች ጥቅጥቅ ብለው እንደገቡ ሴታ ሴት መሳዩ ሾፌር ገብቶ የመኪናውን ሞተር ቆሰቆሰው፡፡ ሞተሩ ተረክ ብሎ ተነሳ፡፡ በመቀጠል የተወዳጇ አስቴር አወቀ ተስረቅራቂ ድምጽ ከእስፒከሩ ወደ ጆሯችን ፈሰሰ፡፡ ‹‹ወይ ኑሮ ወይ ኑሮ›› ትላለች አስቱ የዛን ዘመን ኑሮ ዳገት ለመተረክ፡፡ የተዘፈነበትን ዘመን ሳይሆን ዛሬን የሚሰብከው የአስቴር ዘፈን ኑሮ እንዴት ከባድ እንደሆነ ለማስረዳ ያጣጥራል፡፡ ዘፈኑ በዚህ ዘመን ተዘፍኖ ቢሆን ምን ሊባል ኑሯል፡፡ ይህ ዘፈን ሲዘፈን የአንድ ኩንታል ጤፍ ዋጋ በአሁኑ የአንድ ምግብ ዋጋ ጋር እኩል ነበር፡፡ አስቱ አሁን ሪሚክስ አድርጋ ብትዘፍነው እንደ ብሄራዊ መዝሙር ሁሉም ሰው ተቀባብሎ ይጫወተው ነበር፡፡በዚህ በሀል አንዱ ተሰፋሪ በኑሮ ይማረር በምን እሱ ያውቃል፤ከሙዚቃው ድምጽ በላይ 11.2% ጮክ ብሎ ሙዚቃውን ቀንሰው ሲል ደነፋ፡፡ እንደ ተንቤን ኮረዳ ሹርባ የተሰራው ሴታሴት ሾፌር ድንገት ወንዳወንድ ሆኖ አልቀንሰውም ሲል መለሰለት፡፡ ቀጠል አድርጎም ተሳፋሪው ላይ የትችት ማዕበል አወረደበት፡፡‹‹ታክሲ ውስጥ ብቻ ነው መብትህ ትዝ የሚልህ?››ከሁለት ሰዓት በላይ ተሰልፈህ ስትቆይ ለምን ብለህ አልጠየቅክም? ወይስ አሁን ነው ሰው መሆንህ የገባህ? በሚሉ ሞጋች ጥያቄዎች ያፋጥጠው ጀመር፡፡ ሁሉም ተሳፋሪ በሾፌሩ መልስ በመገረም ጸጥ አለ፡፡ አሁንም ሾፌሩ መናገሩን ቀጥሎ ‹‹እኛ ላይ የምትጮኸው ጠብ-መንጃ ስለሌለን ነው›› ሲለው የኮረኮሩኝ ያክል አሳቀኝ፡፡ ሌላው ተሳፋሪም አብሮ ሳቀ፡፡ ሰውየውም ሂሱን ውጦ ዝም አለ፡፡ ‹‹ጠብ መንጃ ስለሌለን›› ድንቅ አባባል፡፡ ተናጋሪው ሰውየ ድንገት የተቃዋሚዎች ስብሰባ እንደታደመ ካድሬ ቅስሙ ተሰብሮ ጸጥ አለ፡፡ ወደ ውስጤ አሰብኩ የሹፌሩ ነገር ትክክል ነበር፡፡ ከሁለት ሰዓታት በላይ ታግሶ መሰለፍ የቻለ ሰው እንዴት የሙዚቃ ድምጽ በዛ ብሎ ለመቃወም ወኔ አገኘ፡፡ ያውም ለስለስ ብሎ የተከፈተን ሙዚቃ ካቀነስክ በሚል ጥያቄ፡፡ በነገራችን ላይ ከመጠን በላይ የሚለቀቁ ሙዚቃዎች አግባብ ናቸው የሚል መከራከሪያ የለኝም፡፡
ታክሲዋን ቀና ብየ አየኋት፡ጥቅሶች ተንጠልጥለዋ፡፡ ዙሪያ ገባዋ በአብዮተኛ ጥቅሶች ተሞልታለች ያች ከርካሳ ታክሲ፡፡ ትኩረቴን የሳበችኝ ግን ‹‹መብትህን ከታክሲ ስትወርድም ጠይቅ!!›› የምትለዋ ነች፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ ሾፌሩን አደነቅኩት፡፡ ሳትፈራ ጠይቅ ነው ያለው ሾፌሩ፡፡ የጥበብ መጀመሪያው መጠየቅ ነው!! እንዲል የእኔ ፍልስፍና የመጨረሻው ምዕራፍ፡፡ ትክክል መስሎ ያልተሰማንን ነገር መጠየቅ፤ያላመንበትን ላለማድረግ እንቢ ማለትን መለማመድ ይጠበቅብናል፡፡ እኛ ኢትዮጵያዊያን ስንባል ትልቁ ችግራችን ክፉ ቀንን ታግሎ ከማሸነፍ ይልቅ ችግሩን መለማመድ ይቀለናል፡፡ ልመደው ሆዴ የዘወት እንጉርጎሯችን ነው፡፡ ‹‹ክፉ ቀንን እና ቅዝምዝምን ጎንበስ ብሎ ማሳለፍ ነው›› ስንል እንተርታለን፡፡ ‹‹ቀን ሲያልፍ ተናገር ወንዝ ሲጎድል ተሻገር›› እንላለን፡፡ በአባቶቻችን ተረት የምንኖር በተረት እንኳን እራሳችንን ያልቻልን ምስኪኖች፡፡ ‹‹ቻለው ሆዴ ልመደው በዘዴ››ን በአደባባይ የምዘፍን………
የተንዘላዘለውን ሰልፍ ለማስቀረት ከምንዘይደው ይልቅ የምንለምድበትን ዘዴ እንፈጥራለን፡፡ ኑሮ ማለት ሰልፍ እስኪመስለን ድረስ ለዳቦ እንሰለፋለን፡ለታክሲ ሰልፍ፡ሲያስለቅሰን ለኖረ ሰው የሀዘን ሰልፍ፡ለሰልፋችን መንስኤ የሆነን አምባገነን ለመቅበር ሰልፍ፡በአጠቃላይ ኑኗችን ሰልፍ የሆንን ድንጉጦች….!! በኢትዮጵያ ሰማይ ስር ከእድገት በህብረት ዘመቻው ሰልፍ ቀጥሎ ረጅሙ ሰልፍ የታክሲ ሰልፍ ሳይሆን አይቀርም፡፡ የዚህ ሁሉ ሰልፋችን መንስዔ የሆነውን መንግስት እንፈረዋለን፡፡ ከፍርሀታችን የተነሳም መንግስትን ለማማረር እንኳ በራችን በደንብ መዘጋቱን እርግጠኛ የምንሆን ስንቶቻቻን ነን?፡፡ እንዚህን ሰልፎች አንድ ቀን አንዱ ወፈፌ መፎክር ያስያዛቸው እለት ምን ሊሆን እንደሚችል መገመቱ ከባድ አይሆንም፡፡ ‹‹መንግስት ባቡሩ ሲያልቅ ችግሩ ይቀረፋል እስከዚያው ድረስ ባቡሩን መስላችሁ ተሰለፉ›› እያለ ጥሩምባውን ይነፋል፡፡ ድሃ በህልሙ ቅቤ ባይበላ ኖሮ እከክ ይበጣጥሰው ነበር እንዳሉት አይነት ነው፡፡እኔ የምጠቀመው የስድስት ኪሎ ታክሲ ስለሆነ ችግሬ አይቀረፍምና ዝም አልልም፡፡ ወይም እንደተባለው ተስፋ ማድረግ ይቻላል፡፡ ለነገሩ ዝም ባንልስ ምን እናመጣለን፡፡ እኛ ጠብ-ምጃ የለን ማን ይፈራናል፡፡ ከታክሲው በሰላም ወርጃለው፤የቀጠርኩት ወዳጀም ከፊት ለፊቴ ይታየኛል፡፡ የሾፌሩ ድምጽ ግን አሁንም ይከተለኛል፡፡ ‹‹እኛ ጠብ-መንጃ ስለሌለን ነው የምትጮኸው››?!! ትልቅ አባባል!!
ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል!!

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen