Netsanet: Januar 2016

Samstag, 30. Januar 2016

የህዝባችን እንባ ለማቆም ሁላችንም አምርረን እንታገል !

የህዝባችን እንባ ለማቆም ሁላችንም አምርረን እንታገል !

ኢትዮጵያ አገራችን ከፍተኛ የሆነ የህልውና ስጋት ተደቅኖባታል። ልጆቿ በያቅጣጫው ዋይታቸውን እያሰሙ ነው። የወያኔ የተበላሸ ስርዓት እና የስግብግብነት ተፈጥሮ ተደማምረው ህዝባችንን በቃላት ሊገለጽ በማይቻል ሰቆቃ ውስጥ ከተውታል። ህሊና ይዘው መፈጠራቸው ጥያቄ ውስጥ እስከሚገባ ድረስ፣ ቅልብ የወያኔ ገዳይ ወታደሮች በኦሮሞ እናቶችና ህጻናት ላይ የፈጸሙት ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ በረጅሙ ታሪካችን ያላየነውና ያልሰማነው ነው። ባለፉት መንግስታት ለነጻነታቸው የጮሁ ወጣቶች በስርዓቱ የጸጥታ ሃይሎች መገደላቸው ታሪክ የመዘገበው ሃቅ ነው፣ ነገር ግን ህጻናትና ታዳጊዎች እጅግ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ግንባራቸውንና ደረታቸውን በጥይት እየተመቱ ሲወድቁ ስንመለከት ይህ በታሪካችን የመጀመሪያ ነው። አለም በፍጥነት እየተለወጠ ባለበት በዚህ ዘመን እንዲህ አይነት ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ መወሰዱ ደግሞ የአገዛዙ ቁንጮዎችንና እነሱን ተከትለው ወደ ጥፋት አረንቋ የሚተሙትን ሁሉ ከሰው መፈጠራቸውን እንድንጠይቅ የሚያደርግ ነው። የኦሮሞ ህዝብ በአጋዚ ወታደሮችና በፌደራል ፖሊሶች በግፍ ለተነጠቀው ልጆቹ ድምጹን ከፍ አድርጎ አልቅሷል፤ ቁጭቱን በቻለው መንገድ ሁሉ ሊገልጸው ሞክሯል። ነገር ግን እስካሁኗ ሰአት ድረስ መገደሉ፣ መታሰሩ፣ መሰደዱ፣ መዋረዱ አለቆመም። አገዛዙ ለአንድ ቀን በስልጣን ላይ ውሎ እስካደረ ድረስ ይኸው ግፍ ይቀጥላል።
የወልቃይት ህዝብ እኛ እንደፈለግን እንጅ አንተ እንደፈለክ አትኖርም ተብሎ ተፈርዶበት ያለፉትን 25 ዓመታት በስቃይ አሳልፏል። አሁንም እንደገና ” እኛ እናውቅልሃለን እየተባለ” መከራውን እየበላ ነው። በአካባቢው ያንዣበበው የሞት ደመና እጅግ አደገኛ ነው። እየተረጨ ያለው መርዝ ካልቆመ፣ አካባቢው በአጭር ጊዜ የግጭት አውድማ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው። ዘራፊው የህወሃት ቡድን ግጭትን ከማባበስ በተረፈ ችግሩን የማስቆም ፍላጎት አላሳዬም።
በዚሁ አካባቢ የአንድ አገር ሎጆችን ቅማንትና አማራ እያሉ እርስ በርስ ለመከፋፈልና ለማጋጨት ወያኔ እየዘራው ያለው ይጥፋት ዘር እስካሁን ከደረሰው እልቂት በላይ ሌላ እልቂት ይዞ እየመጣ ነው። የአገር ሰላምና ጸጥታ እናስከብራለን ብለው መሳሪያ የታጠቁ ሃይሎች በሁለቱም ወገን ግጭት ለመቀስቀስ ሲዶልቱ፣ ሲያቅራሩና ሲሸልሉ ውለው እያደሩ ነው። ከዚህ ሁሉ የእልቂት ጀርባ ያሉት ዜጎችን ካላጋጩ ውለው ማደር የማይችሉት የወያኔ መሪዎችና ግብረአበሮቹ ናቸው።
የደቡብ ህዝብም ልጆቹን በሞት እየተነጠቀ ነው። በሺዎች የሚቆጠሩ ልጆቹም በየእስር ቤቱ ታጉረዋል፡፡ ዛሬ ወደ ኮንሶ፣ አርባምንጭ፣ ቁጫ፣ ሃመር ወዘተ ብንሄድ የምንሰማው ዋይታና ለቅሶ ነው።
የሶማሌው ወገናችን በልዩ ሃይል አባላት የዘረ ፍጅት እየተፈጸመበት ነው፤ አፋሩ ፣ ጋምቤላውና ቤንሻንጉሉ ከቀየው እየተፈናቀለ፣ መሬቱን እየተነጠቀ ለሞትና ለዘላለማዊ ድህነት ተዳርጓል።
ይሄ ሁሉ መከራና ግፍ ሳያንስ ከ20 ሚሊዮን በላይ የሚሆነው ህዝባችን በረሃብ እየተጠቃ መሆኑ በሰፊው እየተነገረ ነው። በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍል በተፈጥሮ በሚሳበብ የአየር መዛባት ችግር ምክንያት ባለፈው የምርት ዘመን የተዘራው ሰብል እንዳለ ወድሞአል:: በዚህም የተነሳ በህዝባችን ላይ ያንዣበበው የረሃብ አደጋ እስከዛሬ ካየነው ሁሉ የከፋ እንደሚሆን አለማቀፍ ድርጅቶች እያስጠነቀቁ ነው። ላለፉት 10 አመታት በእጥፍ አሃዝ የኢኮኖሚ እድገት አስመዝግቤያለሁ እያለ ህዝብ ሲያደነቁርና የለጋሽ አገሮችን ቀልብ ለመሳብ ሲባዝን የኖረው ወያኔ ግን በፈጠራ ታሪክ የገነባው ገጽታ እንዳይበላሽበት ረሀቡን ለመደበቅና የጉዳት መጠኑን ለማሳነስ ብዙ ርቀት ተጉዟል። ያም ሆኖ የችግሩ ግዝፈት እያየለ ሲመጣና ተጎጂዎች ከቀያቸው ተፈናቅለው ወደየ አጎራባች ከተሞች መሸሽ ሲጀምሩ ሳይወድ በግድ ለማመን ተገዷል። ። በሰሜን ወሎ፣ በትግራይ፣ በአማራ፣ በአፋር፣ በደቡብና በኦሮምያ በድርቁ ምክንያት በምግብ እጥረት እየተሰቃዩ የሚገኙ እናቶችና ህጻናት ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ቢመጣም፣ ወያኔ ግን እንደ ኢኮኖሚው ሁሉ እዚህም ላይ የቁጥር ጨዋታ በመያዙ አሁንም ተገቢው እርዳታ ለህዝባችን በጊዜ እንዳይደርስ እየተከላከለ ለህዝብ መከራ ደንትቢስነቱንና ጨካኝነቱን እያሳየ ይገኛል።
ወያኔ በህዝባችን ላይ የደገሰው የሞት ድግስ በዚህ ብቻ አያበቃም። የኑሮ ውድነቱ ጣሪያ በመንካቱ ህዝቡ እያንዳንዷን ቀን የሚያሳልፈው በጣርና በጭንቅ ነው፤ ከጥቂት የወያኔ ባለስልጣናትና ሸሪኮቻቸው ውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ ኑሮው ሲኦል ሆኖበታል። ችግሩና መከራው እየከፋ ሲሄድ እንጅ እየቀነሰ ሲሄድ አይታይም። በሚብለጨለጩና የህዝቡን መሰረታዊ የፍጆታ ችግር በማይቀርፉ ስራዎች ላይ በማትኮር ህዝብን በልማት ስም ለመሸንገል ሙከራ ቢደረግም፣ አልተሳካም። ከኑሮ ውድነት በተጨማሪ ስራ አጥነቱ፣ አፈናው ፣ ስደቱ እስርና እንግልቱ፤ ሙስናው፣ የፍትህ እጦቱ ወዘተ የአገራችን ህዝብ ኑሮውን በጉስቁል እንዲገፋ አድርጎታል።
አርበኞች ግንቦት 7 አገራችንና ህዝባችን ከዚህ ሁሉ መከራና ስቃይ መውጣት የሚችለው አገዛዙ የዘረጋው የተበላሸ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ፖሊሲዎች ሲለወጡና ከህዝብ፡በህዝብ ለህዝብ የሚቆም የመንግሥት ሥርዓት በአገራችን እውን መሆን ሲችል ብቻ ነው ብሎ ያምናል:: የወያኔ የሥልጣን ዕድሜ በተራዘመ ቁጥር በህዝባችን ላይ የሚደርሰው በደልና ሰቆቃም እንዲሁ እየተራዘመ ይሄዳል:: ህዝባችን ከሚደርስበት ለቅሶና መከራ እንዲገላገል ሁላችንም በያለንበት አምርረን እንታገል::

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ
አርበኞች ግንቦት7

Donnerstag, 28. Januar 2016

‹‹ማዕከላዊ ነው እንዴ ያለነው?›› (ክፍል ፪) በናትናኤል ፈለቀ (ካለፈው የቀጠለ)

Zone9


‹‹ማዕከላዊ ነው እንዴ ያለነው?›› (ክፍል ፪)

በናትናኤል ፈለቀ

(ካለፈው የቀጠለ)

የማታው የመፀዳጃ ሰዓት አብቅቶ እስረኞችን ቆጥረው በሩን የሚቆልፉት ፖሊሶች መጡ፡፡ ሼህ ጀማል ዘወትር እንደሚያደርጉት የመጡት ፖሊሶችን ሰዓት ጠየቋቸው፡፡ አልፎ አልፎ በቁጣ ተሞልተው ከሚመጡት ፖሊሶች በስተቀር ሰዓት ለመናገር አብዛኞቹ ተባባሪዎች ናቸው፡፡ 12 ሰዓት ከ10 ደቂቃ እንደሆነ የተነገራቸው ሼህ ለመግሪብ ጸሎት የቀረው ግማሽ ሰዓት እንደሆነ ክፍሉ ውስጥ ለነበሩ የእስልምና እምነት ተከታዮች አሳወቁ ኡመድ ለፈረሃን ተረጎመለት፡፡

ደቂቃዎች አልፈው የፀሎት ዝግጅት ላይ እያሉ ከሳይቤሪያ ኮሪደር መግቢያ ላይ የሚንቆጫቀጭ የካቴና ድምፅ በከስክስ ኮቴ ታጅቦ ተሰማ፡፡ ድምፁ ምን ማለት እንደሆነ ክፍሉ ውስጥ ያሉት 14ቱም ይገባቸዋል፡፡ በእስር ለቆዩት ሰዎች ግር ያላቸው ነገር ተቆጥረው በር ከተዘጋ በኋላ በዚህ ፍጥነት ለምርመራ የሚጠራ ሰው መኖሩ ነው፡፡ የካቴናው ድምጽ 7 ቁጥር በር ላይ ሲደርስ ቆመና በሩ ተከፈተ፡፡ ‹‹ፈረሃን ኢብራሂም›› ከውጭ የመጣው ጥሪ አስተጋባ፡፡ ለምርመራ ሲጠራ የመጀመሪያው የሆነው ፈረሃን ምን ማድረግ እንዳለበት ግር ብሎት ተደናበረ፡፡ ተነስቶ ቆመ፡፡ ‹‹ፈረሃን ኢብራሂም እዚህ አይደለም?›› ከውጭ የቆመው ፖሊስ ጠየቀ፡፡ ኡመድ ፈርሃን እንዲወጣ በምልክት ወደበሩ ጠቆመው፡፡ ፈረሃን ኮፍያ ያለውን ሹራብ ደረበና ወጣ፡፡

ውስጥ የቀሩት ሰዎች እርስ በርስ ለምን በዚህ ሰዓት ሊጠራ እንደቻለና ምን ሊከሰት እንደሚችል የራሳቸውን መላምት እየሰጡ ክፍሉን በጫጫታ ሞሉት፡፡ በሼህ ጀማል የተመራው ፀሎት ተጠናቆ ብዙም ሳይቆዩ ወደ 7 ቁጥር እየቀረበ የመጣ የእግር ኮቴ ሰምተው ደግሞ ማን ይሆን ባለተራ ብለው በሰቀቀን በር በሩን ያዩ ጀመር፡፡ በሩ ተከፈተና ፈረሃን ገብቶ በሩ ተዘጋ፡፡ ከሄደ ግፋ ቢል ግማሽ ሰዓት ቢሆነው ነው፡፡ በዚህ ፍጥነት የሚጠናቀቅ የመጀመርያ ምርመራ የለም፡፡ ቢያንስ በምርመራ ወቅት እስኪሰለች ድረስ በተደጋጋሚ የሚጠየቀው የሕይወት ታሪክ ከ30 ደቂቃ በላይ መፍጀት አለበት፡፡

ፈረሃን በተፈጠረው ነገር እንደተገረመ ፊቱ ላይ ያስታውቃል፡፡ ኡመድ ምን እንደተከሰተ ሊጠይቀው ሲል ፈረሃን ቀድሞ ጭንቅላቱን እየነቀነቀ ‹‹እነዚህ ሰዎች የሚደንቁ ናቸው!›› አለ፡፡ ‹‹እንዴት?›› የኡመድ ተጠባቂ ጥያቄ ነበር፡፡ ፈረሃን ጭንቅላቱን መወዝወዙን ሳያቋርጥ፡ ‹‹ኮሪደሩን እንደጨረስን የለበስኩትን ሹራብ አስወልቆ ፊቴ ላይ አሰረው፡፡ በጣም አጥብቆ ስላሰረው እንዳመመኝ እና መተንፈስ እንደተቸገርኩ ብነግረውም ምንም ውጤት አልነበረውም፡፡ ከዛ እየመራ የሆነ ክፍል ውስጥ ከተተኝ፡፡ ስሜን፣ ከየትኛው የሱማሌ ጎሳ እንደሆንኩኝና ለምን ወደኢትዮጵያ እንደመጣሁኝ ጠየቁኝና ጨርሰናል ብለው መለሱኝ፡፡›› ብሎ በእጁ አንጠልጥሎት የገባውን ሹራብ መልበስ ጀመረ፡፡ ‹‹ሲያናግሩህም ፊትህን ሸፍነውህ ነበር?›› ኡመድ ተገርሞ ጥያቄውን ቀጠለ፡፡ ‹‹ኮሪደሩን ስንጨርስ እንዳሰረኝ መልሰውኝ እዛው ስደርስ ነው ከፊቴ ላይ የፈቱልኝ፡፡›› ነገርየው ይበልጥ እንቆቅልሽ የሆነበት ኡመድ ሌላ ጥያቄ አስከተለ ‹‹ስንት ሆነው ነው ያናገሩህ?››፡፡ ‹‹ሁለት ድምፆች መስማቴን እርግጠኛ ነኝ›› አለ ፈረሃን፡፡ ፈረሃን በጥያቄዎቹ መሰላቸቱን ኡመድ ቢረዳም ጉጉቱን ግን ማሸነፍ አልቻለም፤ ‹‹ሊያናግሩ የወሰዱህን ክፍል አቅጣጫ ታስታሰዋለህ?›› ሲል ጠየቀ፡፡ ‹‹ደረጃ ይዘውኝ ስለወጡ ፎቅ ላይ መሆኑን ብቻ ነው የማውቀው፡፡›› ፈረሃን መለሰ፡፡ ኡመድ ማዕከላዊ በቆየባቸው አንድ ወር ከግማሽ ጊዜ ውስጥ እንዲህ ያለ ነገር ሲገጥመው የመጀመሪያው ነው፡፡ በርግጥ እራሱም ወደ 11፡30 አካባቢ አንድ ቀን ተጠርቶ ነበር፡፡ የዛኔ ምርመራ ያደረገበት ምንም የማያውቅ ግን ብዙ የሚያውቅ ለማስመሰል የሚጥር ከደኅንነት መሥሪያ ቤት የመጣ ሰውዬ ነበር፡፡ ሰውየውን አይቶታል፡፡ ለምርመራ ሲወስዱትም ዓይኑን አልሸፈኑትም፡፡ ፈረሃን የነገረውን እየተረጎመ ለሌሎቹ ሲነግራቸው ፈረሃን በመኻል አቋረጠውና ‹‹የአንደኛው ሰውዬ ድምፅ ግን ካረፍኩበት ሆቴል ይዘውኝ ሲመጡ ሲቪል ለብሶ የነበረውን ሰውዬ ድምፅ ይመስላል፡›› አለ፡፡ ሁሉም በሰሙት ነገር ተገርመው እያወሩ እንቅልፍ አንድ በአንድ ጣላቸው፤ ሌንጂሳ እስኪጠራ ድረስ፡፡

በማግስቱ ማክሰኞ ፈረሃን በተመሣሣይ ሰዓት ተወስዶ ሩብ ሰዓት እንኳን የሞላ ምርመራ ሳይወስድ ተመለሰ፡፡ በዚህኛው ምርመራ ደግሞ ሲጠየቅ የነበረው ወደኢትዮጵያ አብሮት የመጣ የሚያውቀው ሰው እንዳለ እና ጢያራ ማረፊያ ተገኝቶ የተቀበለው አስጎብኚን ማን እንዳስተዋወቀው ነበር፡፡ ፈረሃን አዲስ አበባ ዓለም አቀፍ ጢያራ ማረፊያ ከመጣበት ጢያራ ሲወርድ ሰላምታ ከተለዋወጠው አንድ ሴንት ፓውል በመልክ ብቻ ከሚያውቀው ተለቅ ያለ ሱማሌ ውጪ ሌላ የሚያውቀው ሰው በመንገዱ ላይ እንዳላጋጠመው እና አስጎብኚ ያሉት ሰው የእናቱ የወንድም ልጅ እንደሆነ ፊቱን ሸፍነው ለሚመረምሩት ሰዎች አስረድቶ ተመለሰ፡፡

***

እጅግ አስቸጋሪ እና በአደጋ የተሞላ ቢሆንም ሳይቤርያ ያሉ እስረኞች መልዕክት የሚለዋወጡበት ዘዴ አበጅተዋል፡፡ የምርመራ ሂደታቸው ምን እንደደረሰ፣ እየተጠየቁ ያሉት ጥያቄዎች ምን ምን እንደሆኑ እና ከማዕከለዊ ውጭ ስላለ ነገር መረጃ ሲደርሳቸው ሌላ ክፍል ውስጥ ያለ ጓደኛቸው ጋር መልዕክት ይለዋወጣሉ፡፡ እንደዚህ በሚስጥር ካልሆነ በቀር ሁለት የተለያዩ የሳይቤሪያ ክፍሎች ውስጥ ያሉ ታሳሪዎች በፍፁም አይገናኙም፡፡ ይህንን የታዘበው ፈረሃን ኡመድን ውለታ ጠየቀው፡፡ አብረውት ፍርድ ቤት የቀረቡት ሱማሌዎች ያሉበትን ክፍል እና የምርመራቸው ሂደት እንዴት እንደሆነ እንዲያጣራለት ነበር የፈለገው፡፡

ኡመድ ሳይቤሪያ ሌላ ክፍሎች ውስጥ ባሉ አብረውት በታሰሩ ጓደኞቹ በኩል ባደረገው ማጣራት መውሊድ የሚባለው ከፈረሃን ጋር ፍርድ ቤት አብሮ የቀረበው ሱማሌ 3 ቁጥር ውስጥ እንደሚገኝ እና ኢብራሂም የሚባለው ደግሞ 4 ቁጥር ውስጥ እደሚገኝ አወቀ፡፡ ፈረሃን ለሁለቱም በያሉበት የድብቅ መልዕክት ልኮ ያሉበትን አጠቃላይ ሁኔታ እንዲያስረዱት ቢጠይቃቸውም መልስ ግን አልመጣም፡፡ ሁለት ቁጥር ውስጥ ታስሮ የነበረው አብሯቸው ፍርድ ቤት የሄደው ሽማግሌ ግን ‹‹እስካሁን ለምርመራ ወስደውኝ አልወሰዱኝም›› የሚል መልዕክት መለሰ፡፡ ፈረሃን ለሽማግሌው በላከው የመልስ መልስ ሽማግሌው ለምርመራ ከተወሰደና ‹‹ፈርሃንን ታውቀዋለህ ወይ?›› የሚል ጥያቄ ከተነሳበት ‹‹ፈረሃንን አውቀዋለሁ፤ በጣም ጥሩ ባሕሪ ያለው ልጅ ነው፡፡›› እንዲልለት ለመነው፡፡

***

ፋይሰል 8 ቁጥር ካሉት ክፍሎች ውስጥ በስተግራ በኩል ወዳለው የመጀመርያ ክፍል ነበር የተዘዋወረው፡፡ በመጀመርያ የገባ ቀን ጋህነም ውስጥ የከተቱት ነበር የመሰለው፡፡ የክፍሉ አየር መታፈን ሳያንስ የሚተኛበት ፍራሽ ደግሞ የሆነ የሚረብሽ ጠረን ነበረው፡፡ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ መርማሪዎቹ ደግሞ በተከታታይ እየጠሩ ታውቃለህ የሚሉትን እንዲያምንላቸው ልብሱን አስወልቀው ይደበድቡታል፤ የውስጥ እግሩን በኤልክትሪክ ሽቦ ይገርፉታል፡፡ ከዚህ ሻል ያለ ቅጣት በሚቀጣ ቀን እጁን ወደላይ ሰቅሎ ቁጭ ብድግ እንዲሰራ ይገደዳል፡፡

ለብቻው የታሰረበት ክፍል ውስጥ ስለታሰረበት ጉዳይ እንኳን ባይሆን ስለሌላ ተራ ጉዳይ የሚያወያየው ሰው ማጣቱ ጭንቅ ውስጥ ከቶታል፡፡ ሰው ማጣት እንደዚህ ያሰቃየኛል ብሎ አስቦ አያውቅም፡፡ ሌላ ግዜ በራሱ ፍላጎት ብቻውን ሲሆን እንኳን እንደሚያደርገው ቁርዓን እንዳይቀራ፣ ቁርዓን የለውም፡፡ ቢኖረውም ኖሮ በየትኛው ብርሃን ሊያነብ፡፡ የተወለደበትን ቀን አምርሮ ረገመ፡፡

ክፍሉ ውስጥ የሚተኛበት ፍራሽ፣ ለኡዱ ማድረጊያ በላስቲክ ቀድቶ የሚያስቀምጠው ውኃ እና ለመጸዳጃ የሚሆነው ባሊ አለ፡፡ የሚተኛበት ፍራሽ ቁመት ከክፍሉ ርዝመት ስለሚበልጥ በአግድሞሽ ካልሆነ እግሩን ዘርግቶ መተኛት አይችልም፡፡ ፋይሰል የሚያስበውም፣ የሚበላውም፣ የሚጸዳዳውም፣ የሚተኛውም እዚችው ክፍል ውስጥ ነው፡፡

8 ቁጥር አጠገቡ ካሉት ሦስት ክፍሎች ውስጥ አብረውት ፍርድ ቤት ከቀረቡት አምስት ሱማሌዎች መካከል አንዳቸውም እንደሌሉ አረጋግጧል፡፡ ለምን እሱ ላይ እንዲህ ያለ ሰቆቃ እየተፈፀመበት እንደሆነ ለመረዳት ተቸገረ፡፡ የአጎቱ ልጅ በፍርሐት ያልሆነ ነገር ተናግሮ እንደሆን ጠረጠረ፡፡ አብረውት ፍርድ ቤት ከቀረቡት መካከል ብቸኛው የውጭ ሀገር ፓስፖርት ባለቤት አለመሆኑ ለዚህ እንደዳረገው እንዴት ሊጠረጥር ይችላል?

***

በሳምንት አንድ ቀን ተራ ወጥቶላቸው ሳይቤርያ ያሉ ማረፊያ ቤቶች ለግማሽ ቀን ያክል ክፍሉ ውስጥ ባሉ ታሳሪዎች ይጸዳሉ፡፡ ሁሉም እስረኞች ገላቸውን መታጠብ የሚፈቀድላቸውም ክፍላቸውን በሚያጸዱበት ቀን ብቻ ነው፡፡ ረቡዕ ከሰዓት ፋይሰል ያለበትን ክፍል እንዲያጸዳ እና ገላውን እና ልብሶቹን እንዲያጥብ ታዘዘ፡፡ የተባለውን ለመፈፀም የሚተኛበትን ፍራሽ ወደኮሪደሩ ይዞት ሲወጣ ፍራሹ ላይ ያየው ነገር ሆዱን እረበሸው፡፡ ወዲያው ከፍራሹ ይወጣ የነበረው መጥፎ ጠረን ምን እንደሆነ ገባው፡፡ ከሱ በፊት እዛ ክፍል ውስጥ ታስሮ የነበረው ሰው ደም የፍራሹን ራስጌ ቀይ ቀለም አልብሶታል፡፡ እስከዛ ቀን ድረስ ደም ላይ ተኝቶ እንደነበር ሲያስብ የበላው ምሣ እንዳለ ወጣ፡፡

***

2 ቁጥር ውስጥ ያለው ሽማግሌ ለፈረሃን መልዕክቶች መልስ መመለስ አቁሟል፡፡ ፈረሃን በሁኔታው ግራ ተጋብቷል፡፡ በመጀመሪያ ቀን መውሊድ እና ኢብራሂም እንኳን መልዕክት መላክ ባልቻሉበት ግዜ ፈጥኖ መልስ የላከው እሱ ነበር፡፡ ከዛን ግዜ ወዲህ ግን በተገላቢጦሽ ከነመውሊድ ጋር በተደጋጋሚ መልዕክት ሲለዋወጥ ለሽማግሌው የሚልከው መልዕክት ግን የውኃ ሽታ ሆኖ ነው የሚቀረው፡፡ መውሊድ እና ኢብራሂም ከፈረሃን የተለየ ምርመራ አልተደረገላቸውም፡፡ የተለየ ነገር የነበረው መውሊድ ከፈረሃን ጋር የት እንደሚተዋወቅ መጠየቁ ነው፡፡ ሽማግሌው ሰውዬ ግን ለምርመራ ይወሰድ አይወሰድ፣ ስለፈረሃን ጠይቀውት ጭራሽ አላውቀውም ይበል ወይንም ልመናውን ተቀብሎ ስለ‹ጥሩ› ባሕሪው ምስክር ሆኖለት ይሆን ማወቅ አልቻለም፡፡

ሴቷ ወጣት ሱማሌ ደግሞ ሳይቤሪያ ባሉ ማረፊያ ቤቶች ውስጥ ያሉ ታሳሪዎች በቀን ለ10 ደቂቃ የሚፈቀድላቸው የፀሐይ ብርሃን ከሚያገኙበት ቦታ ፊት ለፊት በተለምዶ ጣውላ ቤት በመባል የሚጠራው የሴት እስረኞች እና ጓደኞቻቸው ላይ ምስክር ለመሆን የተስማሙ ወንድ እስረኞች የሚቆዩበት ሕንፃ ላይ ያለ ክፍል ውስጥ ስለሆነ ያለችው ፈረሃን ከሷ ጋር መልዕክት መለዋወጥ አልቻለም፡፡

***

ፍርድ ቤት የቀረቡ ዕለት በሽማግሌው እና በወጣቷ ሴት መካከል ያስተዋለው መቀራረብ የቆየ ትውውቅ እንዳላቸው እንዲጠረጥር አድርጎት ነበር፡፡ ፋይሰል ጥርጣሬው ልክ እንደነበር የገባው ምርመራው ቀሎለት ከብቸኛ ክፍሉ ከ8 ቁጥር ወደ 10 ቁጥር ከተዘዋወረ በኋላ ከሽማግሌው ጋር ባደረገው የመልዕክት ልውውጥ ነበር፡፡ ሽማግሌው የዴንማርክ ነዋሪ ሲሆን ወደኢትዮጵያ የመጣው ሚስት ለማግባት ነበር፡፡ ዕቅዱ ተሳክቶለት ኢትዮጵያ በስደት ላይ የነበረችውን ለግላጋ ወጣት በእጁ አስገብቶ ወደ ዴንማርክ ለመመለስ አዲስ አበባ ሲመጣ ነው ከነሚስቱ ጫጉላቸውን ማዕከላዊ እንዲያሳልፉ የተገደዱት፡፡

ፈረሃን ስለሽማግሌው እዲያጣራለት ባዘዘው መሠረት አንዱ ቀን አመሻሽ ላይ ፋይሰል ለአጎቱ ልጅ መልዕክት ላከ፡፡ መልዕክቱ የሽማግሌውን እና ሴቷን ግንኙነት ካስረዳ በኋላ ሽማግሌው ለምን የፈረሃንን መልዕክት መመለስ እንዳቆመም ያትት ነበር፡፡ ሽማግሌው ከፈረሃን ጋር ግንኙነት ያቋረጠው የመጀመርያ ቀን መልዕክት ሲለዋወጡ ስለባሕሪው እንዲመሰክርለት የጠየቀው ፈረሃን የሆነ ጥፋት አጥፍቶ ለመሸፈን እየሞከረ እንደሆነ ስለተሰማው ነበር፡፡

***

ፈረሃን የሽማግሌውን ታሪክ ለኡመድ አጫውቶት ነበር፡፡ አንድ ቀን ከሰዓት ፀሐይ እየሞቁ ከፊት ለፊታቸው ካለው ጣውላ ቤት አንዱ ክፍል በር ላይ ፔርሙዝ እያጠበች የነበረችውን ሱማሌ እንዲያይ ፈረሃን ለኡመድ ጠቆመው፡፡ ኡመድ ልጅቷን ካያት በኋላ ፈረሃን ምን ሊነግረው እንደፈለገ ጠየቀ፡፡ ፈረሃን ወጣቷ ሱማሌ 2 ቁጥር ያለው ሽማግሌ ሚስት እንደሆነች ነገረው፡፡ 2 ቁጥር ውስጥ የነበረውን ሽማግሌ በደንብ የሚያውቀው ኡመድ በባልና ሚስቱ መኻከል ያለው የዕድሜ ልዩነት ደንቆት ጭንቅላቱን ወዘወዘ፡፡ ኡመድ መገረም የገባው ፈረሃን በእስር ቆይታው አሳክቶ የተናገራት የመጀመርያም የመጨረሻም ዓረፍተ ነገር ወረወረ፡ ‹‹ገንዘብ ካለህ በሰማይ መንገድ አለ፡፡›› ፈረሃን አማርኛ አሳክቶ መናገሩ ለኡመድ ሌላ ግርምት ሆነበት፡፡ በመጀመርያ ስለምን እንዳወሩ እንኳን የማያውቁት የ7 ቁጥር እስረኞች ፈረሃን በሰማይ መንገድ መኖሩን ለመጠቆም የተጠቀመበት የእጅ እንቅስቃሴ እና በአማርኛ በቅጡ ለመግባባት ሳይችል ይህችን ተረት መተረቱ ደንቋቸው እየተሳሳቁ 10 ደቂቃዋ አልቃ ወደክፍላቸው ተመለሱ፡፡

***

በእስር ቆይታው መጀመርያ ላይ ለሁለት ቀናት በድምር አንድ ሰዓት ለማይሞላ ምርመራ ከመወሰዱ ውጭ ሌሎች ክፍሉ ውስጥ ያሉ እስረኞች እየተመላለሱ ሲመረመሩና ሲደበደቡ እሱ ሌላ ምርመራ አልተደረገበትም፡፡ ከሁለት ሳምንት በኋላ በጥዋት ሥሙ ተጠራ፡፡ አብረውት ፍርድ ቤት ከሄዱት ሱማሌዎች ውስጥ ከውጭ ሀገር የመጡት ሦስቱ በተለምዶ ሸራተን ወደሚባለው ምርመራ የጨረሰ ሰው ወደሚቆይበት ማረፊያ ቦታ ተዘዋውረዋል፡፡ ሳይቤሪያ የቀሩት እሱና የአጎቱ ልጅ ፋይሰል ብቻ ነበሩ፡፡ የነመውሊድ ዝውውር በተደረገ ማግስት በጥዋት ሲጠራ እሱም ወደሸራተን ሊሄድ እንደሆነ ገምቶ ነበር ነገር ግን ጥሪው እቃውን እንዲይዝ ትዕዛዝ ባለመጨመሩ ግምቱ የተሳሳተ እንደሆነ ተረዳ፡፡

የጠራው ፖሊስ ሁል ግዜ ምርመራ የሚሄድ ሰው እንደሚደረገው ፈረሀን እጅ ላይ ካቴና አጠለቀለት፡፡ ምርመራ በተደረገለት ሁለት ቀናት ሹራቡን አስወልቆ ፊቱን ያሰረበትን ቦታ ዝም ብሎ ሲያልፈው ‹ዛሬ መርማሪዎቼን ላያቸው ነው፡፡› ሲል አሰበ፡፡ ከ7 ቁጥር ጠርቶ ይዞት የመጣው መለዮ የለበሰ ፖሊስ ለሌላ ሲቪል ለለበሰ ፖሊስ አስረከበው እና ከአዲሱ ሰውዬ ጋር ሆኖ አሮጌ ጣውላ ደረጃዎችን አልፎ አንድ ቢሮ በር ላይ እንዲቆም ታዘዘ፡፡ በሩ ላይ ሲቪል የለበሰው ፖሊስ ፈረሃን እጅ ላይ የነበረውን ካቴና ፈትቶ ወደክፍሉ እንዲገባ በሩን ከፈተለት፡፡ ፈረሃን ክፍሉ ውስጥ ሲገባ የእናቱ ወንድም (የፋይሰል አባት) ከተቀመጡበት ተነስተው ተጠመጠሙበት፡፡ ሁለት ሳምንት የገቡበት ጠፍቷቸው ሲያፈላልጉ ቆይተው ከጎዴ መጥተው ነበር ያገኙት፡፡

ወደማረፊያ ቤት ሲመለስ ዓይኖቹ ቀልተው ፊቱ ፍም መስሎ ነበር፡፡ አጎቱን በማግኘቱ የደስታ እምባ ያነባውን ያክል ያለምክንያት እስር ቤት መወርወሩ ያጠራቀመበት እልህ ላይ የልጆቹ እና ሚስቱ ናፍቆት ተጨምሮበት በአንሶላ ተጠቅልሎ እዬዬውን አቀለጠው፡፡ ክፍሉ ውስጥ የነበሩት እስረኞች ‹‹ምን አግኝተውበት ደበደቡት?›› ሲሉ አንሾካሾኩ፡፡

ምሣ ሰዓት ከመድረሱ በፊት ከቤተሰብ የተቀበሉትን ስንቅ ለእስረኞች የሚያድሉት ፖሊሶች መጥተው የፈረሃን ሥም ተጠራ፡፡ ክፍሉ ውስጥ የነበሩት ሁሉ ጠዋት የተጠራው ቤተሰብ ለማግኘት እንደሆነ ገባቸው፡፡ ኡመድ ፈረሃንን ቀስቅሶ የመጣለትን ምግብ እንዲቀበል አደረገ፡፡ የፈረሃን አጎት ያመጡትን የሱማሌ እንጀራ ከሞፎ እና በሪስ ጋር በሉ፡፡ የሱማሌ እንጀራው ለኡመድ በጣም ስለተመቸው ሁልግዜ አጎቱ ሲመጡ ይዘው እንዲመጡ እንዲጠይቃቸው ፈረሃንን ተለማመጠው፡፡

***

አብረውት 7 ቁጥር ውስጥ የነበሩ እስረኞች ሁሉ በምርመራ ወቅት ተደብድበዋል መባሉን አምኗል፤ ከዝምተኛው መላጣ ሽማግሌ በቀር፡፡ ሰውየው ከአክሱም አካባቢ እንደመጡ ከተነገረው ጀምሮ እንደውም በጥርጣሬ ነው የሚያያቸው፡፡

አንድ ቀን እኝሁ ሽማግሌ ተጠርተው ወጡ፡፡ ግማሽ ቀን ሙሉ ቆይተው ሲመለሱ የሸሚዛቸው ቁልፎች ግማሾቻቸው ተበጥሰው ቀሪዎቹ ደግሞ ተዛንፈው ተቆልፈው ነበር፡፡ እንደተመለሱ ማንንም ሳያናግሩ ወደፍራሻቸው አምርተው ተኙ፡፡ ተደብድበው እንደሆነ ከፈረሃን በስተቀር ሁሉም አምነዋል፡፡ ቆይተው ሲነሱ ኡመድ አግባብቶ ምግብ እንዲበሉ ካደረገ በኋላ ምን እንደተፈጠረ ጠየቃቸው፡፡ የተፈጠረውን ለኡመድ ሲያስረዱት ዓይኖቻቸው እምባ አቅርረው፣ ድምፃቸውን ሲቃ እየተናነቀው እና የሰውነታቸው የደምስሮች ሁሉ ተገታትረው ነበር፡፡ ፈረሃን ሽማግሌው ለኡመድ የነገሩትን እንዲተረጉምለት ወተወተው፡፡ በሐዘን ድባብ ውስጥ ሆኖ ኡመድ ለፈረሃን የሆነውን ነገረው፡፡ እንዲህ ነበር የሆነው፤ አቶ ጎበዛይ ገ/ስላሴ ጭቅጭቅ እና እንግልቱ ሲሰለቻቸው ግዜ የማያውቁትን ‹አውቃለሁ›፣ ያልሰሩትን ‹ሰርቻለሁ› ብለው አምነው ለፖሊስ የተከሳሽነት ቃላቸውን ይሰጣሉ፡፡ ይህ አልበቃ ያለው ፖሊስ ይህንኑ ቃል ፍርድ ቤት ቀርበው ዳኛ ፊት ቃላቸውን እንዲሰጡ ፍርድ ቤት ይወስዷቸዋል፡፡ ፍርድ ቤት ዳኛ ፊት ሲቆሙ ፈፅመኻል ስለተባሉት ወንጀል ምንም የሚያውቁት ነገር እንደሌለና እንደውም ፖሊስ አስገድዶ የተከሳሽነት ቃል እንደተቀበላቸው በመግለጽ ‹‹በሕግ አምላክ ፍረዱኝ›› ብለው ይጮኻሉ፡፡ በነገሩ እጅግ የበገኑት መርማሪዎቹ ከፍርድ ቤት ሲመለሱ በቀጥታ ወደምርመራ ክፍል ወስደው ልብሳቸውን አስወልቀው መሬት ላይ ጥለው እየረጋገጡ ደበደቧቸው፡፡

ፈረሃን በሰማው ነገር ግራ በመጋባት ‹‹ይህማ ሊሆን አይችልም!›› ሲል ድምፁን ከፍ አድርጎ ተናገረ፡፡ በዕድሜ የገፋ ሽማግሌ፤ ለዛውም እንኳን እንዲህ ሊንገላቱ ቀርቶ ጭራሽ ይታሰራሉ ብሎ ከማያስባቸው የትግራይ ተወላጅ ላይ ተፈፀመ የተባለውን ማመን አልቻለም፡፡ ኡመድ ‹‹አንድ ስለአቶ ጎበዛይ የማታቀው ነገር ልጨምርልህ፤ ሕወሓት ከደርግ ጋር ባደረገችው ትግል ውስጥ ለ11 ዓመታት አብረው የታገሉ ሰው ናቸው፡፡ እዚህ አብረውን የነበሩት ቄስ ጎይቶም ወደ 8 ቁጥር ከመቀየራቸው በፊት የውስጥ እግራቸውን ተገርፈዋል፡፡ እዚህ የምታያቸው ሼህ ጀማል የአስም ሕመማቸው እንዲያሰቃያቸው ነው ሽንት ቤት አጠገብ ያለ ክፍል ውስጥ የታሰሩት፡፡ ሌላ ብዙ ልልህ እችላለሁ፤ የማዕከላዊ ግፍ እና ማዋረድ በዕድሜ፣ በፆታ፣ በዘውግ ወይንም በሃይማኖት አባትነት የሚለይ አይደለም›› አለ ንዴቱ እንዳይታወቅበት እየጣረ፡፡

ፈረሃን ኢትዮጵያን እየገዛ ስላለው ስርዓት ያስብ የነበረው እና እራሱ እየመሰከረ ያለው ክፉኛ ተጋጭተው እስካሁን እውነቱን ለመፈለግ ያደረገው ሙከራ ትንሽነት አሳፈረው፡፡

***

ቀኑ መሽቶ እየነጋ 28 ቀን አለፈና የቀጠሮው ቀን ደረሰ፡፡ ብዙዎቹ አብረውት 28 ቀን ያሳለለፉት የ7 ቁጥር እስረኞች የሚለቀቅበት ቀን እንደሆነ ገምተዋል፡፡ ፖሊስ ከዚህ በላይ ፈረሃንን ማቆየት የሚፈልግበት ምክንያት አልታያቸውም፡፡ በ28 ቀን ውስጥ ሁለት ቀን ለዚያውም ተደምሮ አንድ ሰዓት እንኳን የማይሞላ ምርመራ የተደረገበት ሰው ለምን ለተጨማሪ ግዜ ይፈለጋል?

ጠዋት ሲጠበቅ የነበረው የፈረሃን ፍርድ ቤት ጥሪ ሳይመጣ ቀረ፡፡ ምሣ ሰዓት በመድረሱ የሁሉም ተስፋ አደገ፡፡ በቀጠሮው ቀን ፍርድ ቤት ካልተወሰደ፣ ፖሊስ ብቻውን ቀርቦ ምርመራዬን ስለጨረስኩ የግዜ ቀጠሮ መዝገቡ ይዘጋልኝ ብሏል ማለት ነው፡፡ ይህ ከተከሰተ ደግሞ ከሁለት ነገሮች አንዱ ይከተላል ማለት ነው፡፡ የመጀመርያው ከእስር መፈታት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ የክስ ምስረታ ነው፡፡ በአንድ ሰዓት ምርመራ ደግሞ ክስ ሊመሰረት እንደማይችል እና እነዚህን መሳሰሉ ትንተናዎች እየተጨዋወቱ ምሣ ከበሉ በኋላ በድንገት በሩ ተከፈተና ፈረሃን ተጠራ፡፡ ክፍሉ ውስጥ የነበሩት ሰዎች ሁሉ ሲጠበቁት የነበረው የፍቺ ጥሪ ግን አልነበረም፡፡

ፈረሃን ከሄደበት ተመልሶ ሲመጣ እጅግ ተስፋ መቁረጥ ይስተዋልበት ነበር፡፡ ተጨማሪ 28 ቀናት እንደተቀጠረበት ለኡመድ ሲያስረዳው ሁሉም ተደናገጡ፡፡ እየሆነ ያለውን በፍፁም ሊረዱት አልቻሉም፡፡ ‹‹ምን ዓይነት ዳኛ ናት? 28 ቀን ምን ሠራችሁ ብላ ሳትጠይቅ ሌላ 28 ቀን የምትሰጣቸው?›› ሲል ኡመድ አማረረ፡፡

***

ቅዳሜ ግንቦት 30ቀን 2006 ዓ.ም ከሰዓት ፈረሃን ካረፈበት ሆቴል ትንሽ የእግር ጉዞ ለማድረግ ፈልጎ እየወጣ እንዳለ የሆቴሉ የእግዳ መቀበያው ላይ አንድ የሚያውቀው ፊት ያየ መሰለው፡፡ ተጠግቶ ሲያረጋግጥ የሚኖርበት ሴንት ፖውል ሚያውቀው ሱማሌ ወጣት ነበር፡፡ ያረፈበት ሆቴል አዲስ አበባ ውስጥ ሱማሌዎች የሚበዙበት አካባቢ እንደሚገኝ እና ሆቴሉ ውስጥም በብዛት የሚያርፉት የሱማሌ ዲያስፖራዎች እንደሆኑ ፋይሰል ነግሮት ስለነበር በሺዎች ማይል ርቀት የሚያውቀው መውሊድን እዚህ ማግኘቱ ብዙም አልገረመውም፡፡ መውሊድ ፈረሃን ያቀረበለትን ግብዣ ተቀብሎ የአዲስ አበባ ከሰዓት አየር እቀዘፉ የቦሌን አካባቢ ቃኙት፡፡ ከመስቀል አደባባይ እስከ ቦሌ ዓለም አቀፍ ጢያራ ማረፊ ድረስ የተዘረጋው አፍሪቃ ጎዳና የተሠራበት ደረጃና ከጎዳናው ግራና ቀኝ የተሰለፉት ሕንፃዎችን አይተው ግርምታቸውን ተለዋወጡ፡፡ ፈረሃን አብሮት ላለው የሴንት ፖውል ወዳጁ ሌላ የተደመመበት ጉዳይንም አጫውቶት ነበር፡፡ አባቱን ለማስታመም የሚሄድበት ጎዴን ከጅግጅጋ የሚያገናኝ አዲስ የአስፋልት መንገድ በቅርቡ መዘርጋቱን እና ቀድሞ መንገዱ ከሚወስደው ግዜ አሁን በግማሽ እንደቀነሰ በአድናቆት አጫወተው፡፡

በአንፀባራቂ ሕንፃዎቹ መስታወት ውስጥ የድኃ ኢትዮጵያውያን ችጋር አልታያቸውም ነበር፡፡ አዲስ እና አሮጌ መኪኖች እንደፈለጉ የሚፈሱበት ጎዳና ኢትጵያውያን ላይ የተጫነው ጭቆና ማራዘሚያ እንደሆነ አልተገነዘቡም፡፡ ፈረሃን እና መውሊድ እነዚህን ጉዳች ለመረዳት በከባዱ መንገድ መማር ነበረባቸው፡፡ ከዛች አስደሳች ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ በድጋሚ የተገናኙት ሰኞ ዕለት ፍርድ ቤት ቀርበው ፖሊስ በሽብርተኝነት እንደሚጠረጥራቸው የሰሙ ግዜ ነበር፡፡

ሦስተኛ ተጠርጣሪ ሆኖ ችሎት ከጎናቸው የቆመው ኢብራሂም በትውልድ ኬንያዊ ሱማሌ ሲሆን ከሚኖርበት አሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል ፕሬዝዳንት በአሜሪካን ሚኒሶታ ግዛት ተገኝተው ኢትዮጵያ እና ክልላቸው ለኢንቨስትመት ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠራቸውን እና ማንም ሰው ኢንቨስት ለማድረግ ቢመጣ በደስታ እንደሚያስተናግዱት የገቡትን ቃል አምኖ እና አንዳንድ መገናኛ ብዙኃን በየግዜው ስለኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት መመንደግ ሚያወጡት ዘገባ አጓጉቶት ከእናት ሀገሩ ኬንያ ይልቅ በኢትዮጵያ መዕዋለ ነዋዩን ቢያፈስ የተሻለ የትርፍ ሕዳግ እንደሚያገኝ ተማምኖ ነበር፡፡

***

ለሁለተኛ ግዜ ፍርድ ቤት በቀረበ ማግስት መጀመርያ ተጠሪ ፈረሃን ነበር፡፡ ማንም ባልጠበቀው ሁኔታ የማክሰኞ ሐምሌ 1 ቀን 2006 ዓ.ም ጠዋት የመጣው ጥሪ ፈረሃንን ጓዙን ጠቅልሎ እንዲወጣ የሚያዝ ነበር፡፡ ፖሊስ ተጨማሪ 28 ቀን ፈረሃን እና ጓደኞቹ ላይ የጠየቀው ፍርድ ቤቱን ታዛዥነት ለማረጋገጥ ነው እንጂ ሌላ ምክንያት አልነበረውም፡፡ ፍርድ ቤቱም ታዛዥነቱን በሚገባ አረጋግጧል፡፡

በሕመም አልጋ ላይ የወደቁት አባቱን እንዲጎበኝ እንኳን ዕድል ሳይሰጠው ፈረሃን ወደመጣበት ሀገር እራሱ በቆረጠው ትኬት እንዲመለስ ቀጭን ትዕዛዝ ተሰጠው፡፡ የታዘዘውን ከማድረግ ውጪ አማራጭ አልታየውም፡፡ ምንያቱም ይህች በአዲስ ዓይኑ ማየት የጀመራት ኢትዮጵያ ናት፡፡ ፖሊሶች እየጎተቱ ከ7 ቁጥር ሲያስወጡት እምባው ጉንጩ ላይ እየወረደ እንዲህ አለ፤ ‹‹ኡመድ፤ የተበደላችሁትን አልረሳም፡፡ ሁሉንም እንደምናፍቃቸው ንገርልኝ፡፡››

---

ይህ ታሪክ ለአንባቢ ምቾት ሲባል ከተደረገለት ዘይቤያዊ ማስተካከያ በስተቀር እውነተኛ ታሪክ ነው፡፡

---

ተፈፀመ

http://wp.me/p5L3EG-9T

Mittwoch, 27. Januar 2016

የሰላምን በር ጠርቅሞ የዘጋው ወያኔ ነው

የወያኔ አረመኔያዊ ያገዛዝ ስርዓት በህዝባችን ላይ የሚፈጽመው አፈና ግድያና ዝርፊያ በመጠኑም በዘግናኝነቱም ይበልጥ እያገጠጠ ስለመጣ ለወትሮው እንዳላዩ አይተው የሚያልፉትን ምዕራባውያን ለጋሾቹንና ወዳጆቹን ሳይቀር በእጅጉ ማሳስብ ጀምረዋል። ወያኔ ለምዕራባውያን ደህና ሎሌ በመሆን ወንጀሌን እንዳላዩ እንዲያዩልኝ ማድረግ እችላለሁ የሚለው አካሔዱ በውንብድና ተግባሩ ለከት የለሽነትና ዘግናኝነት ምክንያት ሙሉ ለሙሉ እየተሸረሸረበት ነው። ብዙዎቹ ምዕራባውያን ላለፉት ሁለት ወራት በተለይ በኦሮሚያ ውስጥ የሚካሄደውን ጭፍጨፋና አፈና ለማውገዝ የተገደዱበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

አሜሪካንን ጨምሮ የወያኔ ለጋሽ ሀገራት የሆኑት ምዕራባውያን ሰሞኑን በኦሮሞ ወገኖቻችን ላይ ወያኔ የከፈተውን የዕብሪት ጭፍጨፋ፣ እስራትና አፈና አስመልክቶ ችግሩን በውይይትና በስልጡን መንገድ ይፈታ ዘንድ የሚያሳስቡ ግልጽና ባንጻራዊ ደረጃ ሲታዩ ጠንከር ያሉ መግለጫዎችን አውጥተዋል። የደረሰውም ጥፋት ተመርምሮ ጥፋተኛ ወገን እንዲጠየቅ የሚጠይቁና ችግሩም በሰላምና በውይይት እንዲፈታ እየጎተጎቱ ይገኛሉ። ባለፉት በርካታ ዐመታት ምዕብራባውያኑ የወያኔ ጉጅሌ ይህንን አቅጣጫ እንዲከተል ተጽዕኖ የመፍጠር አቅማቸውን ተጠቅመው ያደረጉት በቂ ግፊት እንደሌለ ይታወቃል። የአሜሪካ መንግስትና የአውሮፓ ሕብረት አባል ሀገሮች ዘግይተውም ቢሆን ሀገራችን ውስጥ የተካሄደውንና እየተካሔደ ያለውን ጭፍጨፋ ማውገዛቸውና ወደፊትም በዝርዝር ተመርምሮ ተጠያቂው እንዲታወቅ ያቀረቡትን ሀሳብ እንደ በጎ ጅምር እንመለከተዋለን።

ለሀገራችንና ለህዝባችን እጣ ፋንታ የምንጨነቅና የህዝቡ ጥቃት ያንገፈገፈን የሀገሪቱ ልጆች የችግሩ የመፍትሔ መጀመሪያ ይህ በጉልበቱ ህዝባችን ላይ የተጫነ መንግስት ነኝ ባይ የግፈኞች ጥርቅም በሃይል በሚደረግ ትግል ጭምር መወገድ አለበት ወደሚለው ውሳኔ የደረስነው የሰላም በርና ጭላንጭል ሁሉ በመዘጋቱ እንደሆነ ስንገልጽ ቆይተናል ። ላለፉት ሁለት ወራት በኦሮሞ ወገኖቻችን ላይ የተፈጸመውና ከመቶ ሀምሳ በላይ ወገኖቻችን ያለቁበት ጭፍጨፋ እንዲሁም በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች በሚኖሩ ዜጎቻችን ላይ እየተፈጸመ ያለው ተመሳሳይ ግድያ፣ እስራትና የተቀናቃኝን አድራሻ ደብዛ ማጥፋት እርምጃ የሚያሳየው ይህ ስርዓት የበለጠ ጥፋት ከማድረሱ በፊት በፍጥነት መወገድ ያለበት መሆኑ ላይ ያለን አቋም ለሁሉም ይበልጥ ግልጽ እየሆነ መምጣቱን ነው። እንደ ወያኔ ያለ ከህዝብ የተጣላ የፖለቲካ ሀይል የፖለቲካ ጥቅምን የሚያየው ከራሱ ህልውናና ደህንነት አንጻር እንጂ ከህዝቡ ሰላም ብልጽግናና ነጻነት ወይም ከሀገሪቱ የረጅም ጊዜ እጣ ፋንታ አንጻር አይደለም። የወያኔን ገዥዎች የሚያስጨንቃቸው የህዝቡ ኑሮ ሳይሆን የራሳቸው የዝርፊያ ስርዓት ባግባቡ መጠበቅ አለመጠበቁ ነው። ለዚህ ነው ስርዓታቸውን ለመጠበቅ የነጻነት ጥያቄ ኮሽታ በሰሙ ቁጥር የሚባንኑት። ለዚህ ነው በሰላም መብቱን የጠየቃቸውን ሁሉ መደዳውንና በጭካኔ በጥይት የሚረፈርፉትና የተረፋቸውን እንደ እንስሳ ወህኒ በረት ውስጥ የሚያጉሩት።

አርበኞች ግንቦት 7 የወያኔ ጸረ ህዛብና ጸረ አገር እርምጃ ሊቆም የሚችለው ላለፉት 25 አመታት ወያኔ በመካከላችን የገነባው የመከፋፈልና የልዩነት ግድግዳ ለመናድ ሁላችንም እጅ ለእጅ ተያይዘን በአንዳችን ላይ የሚፈጸመው ጥቃት በሁላችንም ላይ እንደ ተፈጸመ ቆጥረን በጋራ ስንንቀሳቀስ ብቻ ነው ብሎ ያምናል:: ዛሬ በኦሮሚያ ወገኖቻ ላይ እየተፈጸመ ያለው ሰቆቃና ግዲያ ትናንት በጋምቤላ ፤ በኦጋዴን ፤ በአፋር፤ በቤኔሻንጉል ፤ በደቡብና በአማራ ወገኖቻችን ላይ በፈረቃ ሲፈጸም የቆየና እየተፈጸመ ያለ መከራ መሆኑን የማይገነዘብ የለም:: በፈረቃ መገደል፤ በፈረቃ ወህኒ መወርወር ፤ በፈረቃ መፈናቀል፤ በፈረቃ ለስደት መዳረግ የሁላችንም ዕድል ፈንታ ሆኖአል:: ይህንን ስቃይና መከራ ማስቆም ለፍትህና ለነጻነት የቆመ ዜጋ ሁሉ ግዴታ ነው::

ወያኔ የሰላም በሮችን በሙሉ ጠርቅሞ ሲዘጋ ለአገራቸው ጥቅም ሲሉ ዝምታን የመረጡ ምዕራባዊያን የህዝብ ብሶት ገንፍሎ አደባባይ ከወጣና ብዙዎች በአጋዚ ጦር ጨካኝ ግዲያ ህይወታቸውን ከገበሩ ቦኋላ ዘግይተውም ቢሆን መናገር መጀመራቸው መልካም ጅምር ነው:: ነገር ግን በእብሪት የተወጠሩ የወያኔ መሪዎች በባዕዳን አለቆቻቸው ቁጣ ከአቋማቸው ፍንክች ይላሉ ብሎ መጠበቅ መዘናጋት እንዳያስከትል መጠንቀቅ ተገቢ ነው::  ችግሮችን ተነጋግሮ መፍታት ትልቅ አቅምና ችሎታን የሚጠይቅ የዘመናችን ሥልጣኔ ውጤት ነው:: በጠመንጃ ተጸንሶ በጠመንጃ የተወለደው ወያኔ ለእንዲህ አይነት ዕድገትና ሥልጣኔ አልታደለም::

አርበኞች ግንቦት 7 የወያኔ ስርዓት ሊወገድ እንጂ ሊጠገን የማይችል የተበላሸ ስርዐት መሆኑን ይገነዘባል:: በመሆኑም በህዝባችንና በአገራችን ላይ የሚፈጸመውን ወንጀል ለማስቆም የጀመረውን ሁለገብ ትግል የወያኔ አገዛዝ እስኪወገድና ሠላምና ዲሞክራሲ በአገራችን እስኪሰፍን ድረስ አጠናክሮ እንደሚቀጥልበት ለወዳጅም ለጠላትም ያረጋግጣል ::

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ

‹‹ማዕከላዊ ነው እንዴ ያለነው?›› (ክፍል ፩) በናትናኤል ፈለቀ

Zone9

‹‹ማዕከላዊ ነው እንዴ ያለነው?›› (ክፍል ፩)

በናትናኤል ፈለቀ

እራሳቸውን ድንገት ስተው ‹‹ኮማ›› ውስጥ የገቡ ወላጅ አባቱን ለማስታመም እና በቅርቡ ሕይወታቸው ያለፈውን አሳዳጊ ሴት አያቱን እርም ሊያወጣ ከ15 ዓመት በላይ ወደተለያት ሀገሩ እየተመለሰ ነው፡፡ ለጉዞው ቀና ብሎ ያሰበው መንገድ ከሚኖርበት ሴንት ፖውል፣ ሚኒሶታ ወደካናዳዋ ቶሮንቶ አቅንቶ ከዛ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አዲስ አበባ ለመግባት እና በማግስቱ አውቶቢስ ተሳፍሮ አባቱን ወደሚያገኝበት የሱማሌ ክልል ከተማ ጎዴ ማምራትን ነበር፡፡

ወደ ሀገሩ ተመልሶ አባቱን ለማግኘት እጅግ ቸኩሏል፤ ተጨንቋል፡፡ ጭንቀቱን የሚያሳብቀው ገና ከተወለደች ሁለት ሳምንት ያልሞላትን ሁለተኛ ልጁን እና የሦስት ዓመት ወንድ ልጁን አራስ ባለቤቱ ላይ ጥሎ ጉዞውን መጀመሩ ነው፡፡ ነገሮች ሁሉ እንዳቀደው ከሄዱለት በአንድ ወር ግዜ ውስጥ የኢትዮጵያ ቆይታውን አጠናቆ ዜጋዋ አድርጋ ወደተቀበለችው አሜሪካን ይመለሳል፡፡

በኢትዮጵያውያን አቆጣጠር ግንቦት 29 ቀን፣ 2006 ዓ.ም ዕለተ ዓርብ የ31 ዓመቱ ፈረሃን ኢብራሂም አዲስ አበባ ዓለም አቀፍ የጢያራ ማረፊያ ደረሰ፡፡ አብረውት አዲስ አበባ እንዲደርሱ የሸከፋቸው ሻንጣዎች ግን አልደረሱም፡፡ ጉዳዩን ያስረዳቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኞች ጓዙ የሚመጣው በሚቀጥለው በረራ እንደሚሆን፤ ይህ ማለት ደግሞ አዲስ አበባ የሚደርሰው ከሁለት ቀን በኋላ እንደሚሆን አስረዱት፡፡ የዕቅዱ መዛነፍ የመጀመርያ ምዕራፍ ይህ ሆነ፡፡ ነገርየው ብዙም የሚያስጨንቅ ሆኖ አላገኘውም፡፡ በሥራው ምክንያት የብዙ ግዜ የአየር ጉዞ ልምድ ስላለው እንደዚህ ዓይነት አጋጣሚዎች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ ያውቃል፡፡ አባቱን የሚያገኝበት ግዜ መራዘሙ ቢያሳስበውም አዲስ አበባ ውስጥ ሁለት ቀን እንዲቆይ መገደዱ ከተማዋን ዞር ዞር ብሎ ለማየት የሚፈጥርለትን ዕድል በማሰብ ለመፅናናት ሞከረ፡፡

***

ፋይሰል ሜድኮ ባዮ ሜዲካል ኮሌጅ ውስጥ የሁለተኛ ዓመት የፋርማሲ ተማሪ ነው፡፡ የትምህርት ወጪውን የሚሸፍንለት በፎቶ ብቻ የሚያውቀው የአጎቱ ልጅ ከአሜሪካን ሀገር ሲመጣ ተቀብሎ አዲስ አበባ ያለውን መስተንግዶ ጨርሶ ወደጎዴ ለመላክ ያለውን ኃላፊነት እሱ ወስዷል፡፡ የአጎቱ ልጅ ሲያገኘው እንዲኮራበትም በቅርቡ በላከለት ገንዘብ ያሰፋውን ጥቁር ሱፍ ግጥም አድርጎ ለብሶ፣ አበባ ይዞ ቦሌ ዓለም አቀፍ ጢያራ ማረፊያ መንገደኞችን ለመቀበል ከተደረደሩት ሰዎች መኻከል ተገኝቷል፡፡

እሁድ ሰኔ 1 ቀን 2006 ዓ.ም ከቀኑ 12፡30 ገደማ ፋይሰል ፈጽሞ ሊገባው ባልቻለ ሁኔታ እራሱን የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ዘርፍ የተጠርጣሪዎች ማረፊያ ክፍል ቁጥር 9 ውስጥ አግኝቶታል፡፡ ከሱ አስቀድሞ ክፍሉ ውስጥ ነበሩትን ሰዎች ምን እየተፈጠረ እንደሆነ እንዲያስረዱት በሚችላት ትንሽ አማርኛ ተፍጨረጨረ፡፡ ሊገባው የቻለው ነገር ያለበት ቦታ በተለምዶ ማዕከላዊ እየተባለ እንደሚጠራ እና ያሉበት ክፍል የሚገኝበት ሕንፃ በቅዝቃዜው ምክንያት ‹‹ሳይቤርያ›› የሚል ስያሜ እንደተሰጠው

ብቻ ነው፡፡

***

ፈረሃን ለመጀመርያ ጊዜ በዕጁ ያጠለቀውን ካቴና ፈትተው አንድ ደብዛዛ ብርሃን ያለበት ክፍል በር ከፍተው ገፈተሩት፡፡ ከሻንጣው ውስጥ ወደማረፊያ ቤቱ ይዞት እንዲገባ የተፈቀደለትን አንድ ቅያሪ ቱታ እና የጥርስ ብሩሽ እና ሳሙና በቢጫ ፌስታል እንዳንጠለጠለ በሩ አጠገብ ቆሞ የገባበትን ክፍል ይቃኝ ጀመር፡፡ በር ድረስ አጅበው ይዘውት የመጡት ሰማያዊ ቀለም ያለው ሬንጀር የለበሱ ሰዎች በሩን ሲዘጉት የወጣው ድምጽ የክፍሉን ቅኝት አቋርጦ በድንጋጤ ከበሩ አካባቢ እንዲርቅ አስገደደው፡፡

ደቂቃዎች አለፉ፤ ፌስታሉን በዕጁ እንዳንጠለጠለ ቆሟል፡፡ ቀድመው ክፍሉ ውስጥ የነበሩትን ሰዎች ቆጠራቸው፣ 13 ነበሩ፡፡ ‹‹ቁጭ በል›› ብለው ቢጋብዙትም አልገባውም፡፡ በቋንቋ እንዳልተግባቡ ሲረዱ ከመካከላቸው ተኝቶ የነበረ አንድ ልጅ ቀሰቀሱና ‹እንግዳ ተቀበል› አሉት፡፡ ከንቅልፉ የተቀሰቀሰው ልጅ ከፍራሹ ተነስቶ ወደቆመው ሰውዬ አመራና እጁን ለሰላምታ ዘረጋ፡፡ ኡመድ ብሎ እራሱን አስተዋወቀ;; የቆመው ሰውዬ ለሰላምታ የተዘረጋለትን እጅ በቸልታ እየጨበጠ ‹‹ፈረሃን እባላለሁ›› አለ፡፡ ኡመድ ሌላኛውን እጁን ፌስታሉን ለመቀበል እየሰደደ እንግዳውን እንግሊዘኛ መናገር ይችል እንደሆነ ጠየቀ፡፡ ፈረሃን ጭንቅላቱን ላይ ታች ወዝውዞ መለሰለት፡፡ ሊግባባው ሚችል ሰው ማግኘቱ ቢያስደስተውም አሁንም ፈፅሞ ደኅንነት እየተሰማው አይደለም፡፡ ለማየት የሚረዳውን መነጽር ከዓይኑ ላይ አወረደና በእጁ ያዘ፡፡ አንድ ጊዜ እንደገና ክፍሉን ቃኘ፡፡ በኮንክሪት የተሰራ ጣራ እና ግርግዳ፣ ለአየር መውጫና መግቢያ እንዲሁም የኤሌክትሪክ ብርሃን የሚገባበት በፍርግርግ ብረት የተገደበ ከበሩ በስተግራ በኩል ጣራውን ታክኮ ያለ ትንሽ ክፍተት፣ ክፍሉ ውስጥ ባሉ ሰዎች ቁጥር ልክ የሚመስል ጥግ ይዘው የተደረደሩ የውኃ ማሸጊያ ላስቲኮች፣… ከላስቲኮቹ መኻከል አንዳንዶቹ ውስጥ ያለው ፈሳሽ ሽንት ስለመሰለው በመጠየፍ መራቅ ፈለገ፡፡ ኡመድ ተኝቶ ወደነበረበት ፍራሽ ተመለሰና ‹‹ፈረሃን፣ ወደዚህ ና›› ሲል ጋበዘው፡፡ ከላስቲኮቹ መራቅ የፈለገው ፈረሃን በትክክለኛው ሰዓት የመጣለትን ግብዣ ተቀብሎ ጫማውን አወለቀና በፍራሾች ላይ ተረማምዶ ከኡመድ አጠገብ ተቀመጠ፡፡

ክፍሉ ውስጥ ያሉት ሌሎች ሰዎች የኡመድ እና የፈረሃንን ዓይን አፈራርቀው እያዩ ለኡመድ በጥያቄ አጣደፉት፡፡ ኡመድ ወደፈረሃን ዞሮ ‹‹ሱማሌ ትመስላለህ?›› አለው፡፡ ፈረሃን በመስማማት በመስማማት ጭንቅላቱን ነቀነቀ፡፡ ኡመድ አብረውት ከታሰሩ ሶማሌዎች ካስተማሩት የሚያስታውሳትን ሱማልኛ ተናገረ ‹‹ማፊዓንታሃይ?›› ፈረሃን ክፍሉ ውስጥ ከገባ በኋላ ለመጀመሪያ ግዜ ፈገግ ብሎ መልስ ሰጠ – ‹‹ፊዓን›› ሲል፡፡ የሚችለውን ሱማልኛ የጨረሰው ኡመድ በእንግሊዘኛ መናገር ቀጠለ፡፡ ‹‹ከየት ነው የመጣኸው?›› ፈረሃን ጥያቄውን ለመመለስ ጥቂት ሰከንዶች ከወሰደ በኋላ የሚኖረው አሜሪካን ሀገር እደሆነ፣ ለጥቂት ግዜ እረፍት ወደ ኢትዮጵያ እንደመጣ አስረዳ፡፡ ኡመድ ጥያቄውን ቀጥሎ ለምን እንደታሰረ ያውቅ እደሆነ ጠየቀው፡፡ ፈረሃን ግራ መጋባቱን በሚያሳብቅ ሁኔታ ዓይኑን ግራና ቀኝ ካንከባለለ በኋላ ትከሻውን ሰብቆ የሚያውቀው ነገር እንደሌለ ገለፀ፡፡ አብረዋቸው ያሉት ሰዎች ጥያቄዎቻቸውን እያዥጎደጎዱ እንዲያስተረጉምላቸው ቢፈልጉም ከዚህ በላይ ፈረሃንን ማስጨነቅ ያልመረጠው ኡመድ ‹‹አሁን ተረጋግተህ እረፍት አድርግና ጠዋት እናወራለን፡፡ ለሁላችንም የሚበቃ ፍራሽ ስለሌለ ከኔ ጋር ፍራሽ እንጋራለን፡፡ ሽንት መሽናት ከፈለክ ከነዛ ላስቲኮች አንዱን ተጠቀም፡፡›› አለውና አንሶላ አነጠፈለት፡፡ ፈረሃን ‹‹አመሰግናለሁ›› አለና እንደማመንታት ብሎ ማውራት ቀጠለ፡፡ ‹‹ታውቃለህ? መጀመሪያ እዚህ ሲያስገቡኝ የምትደበድቡኝ መስሎኝ ነበር፡፡ እኔ የምኖርበት ሀገር እስር ቤት ውስጥ አዲስ ሰው ሲገባ የቆዩት እስረኞች በድብደባ ነው አቀባበል የሚያደርጉለት፡፡›› ኡመድ ጮክ ብሎ ሳቀ፡፡ ሌሎቹ እስረኞች ምን እንዳሳቀው ለማወቅ ጓግተው ጠየቁት፡፡ ፈረሃን የነገረውን ተረጎመላቸው፡፡ ሁሉም እየተሳሳቁ ፍራሾቻቸውን ማንጠፍ ጀመሩ፡፡ ኡመድ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሌሎች እስር ቤቶች ውስጥም ተመሳሳይ ነገር ሊከሰት እንደሚችል ለፈረሃን አስረዳው፡፡

ፈረሃን ለመተኛት ትንሽ ሲገላበጥ ቆየና የረሳው አንድ ነገር ድንገት ትዝ አለውና ኡመድን ‹‹ፀሎት ማድረግ እችላለሁ?›› ብሎ ጠየቀው፡፡ ኡመድ፤ በክፍሉ ውስጥ የነበሩት የእስልምና ዕምነት ተከታዮች የመግሪብ ፀሎት እንዳደረጉ፣ ትንሽ ከቆየ አብሯቸው የኢሻ ፀሎት ማድረግ እንደሚችል አልያ ግን ብቻውን ቢፀልይ ችግር እንደሌለው እና ቦታ ሊያመቻችለት እንደሚችል ነገረው፡፡ ፈረሃን ቆይቶ በጋራ ፀሎት ማድረጉን መረጠ፡፡

***

ከእንቅልፉ ነቅቶ አይኑን ሲገልጥ ግር ተሰኘ፡፡ ዙሪያውን ሲያይ የማያውቀው ቦታ እራሱን ስላገኘው ተደናገጠ፡፡ ዓይኖቹን አሻቸው፤ የተለወጠ ነገር ግን አልነበረም፡፡ ቀስ ብሎ ለማስታወስ ሞከረ፡፡ ደስ የማይል ስሜት ውስጡን ሲወረው ተሰማው፡፡ ከ17 ሰዓታት በፊት የተፈጠረውን ነገር አስታወሰ፡፡ በህልሙ ቢሆን ምርጫው ነበር፡፡

***

የዘገዩት ሻንጣዎችን ለማምጣት እሁድ ረፋድ ላይ ካረፈበት ሆቴል ታክሲ ተኮናትሮ ወደቦሌ አቀና፡፡ የአየር መንገዱ ሰራተኞች ለተፈጠረው ስህተት እና መጉላላት ይቅርታ ጠይቀው ሻንጣዎቹን አስረክበው ሸኙት፡፡ ወዳረፈበት ሆቴል እየተመለሰ ለፋይሰል የስልክ ጥሪ አደረገና የዘገዩት ሻንጣዎች በእጁ መግባታቸውን ከነገረው በኋላ ወደጎዴ የሚወስደውን የአውቶቢስ ትኬት ለመቁረጥ ሰኞ ጠዋት ለመገናኘት ተቀጣጠሩ፡፡ ፋይሰል ያረፈበት ሆቴል ድረስ መጥቶ አብረው ሄደው ትኬቱን እንደሚገዙ ነበር የተሰማሙት፡፡

የሚያደርገው ስላልነበረው ዕረፍት ለማድረግ አስቦ ጋደም አለ፡፡እንቅልፉ መኻል ላይ ያረፈበት ሆቴል ክፍል በር ሲንኳኳ ሰማ፡፡ የሚጠብቀው እንግዳ አልነበረም፤ ከፋይሰል በስተቀር ያረፈበትን ቦታ የሚያውቅ የቅርብ ሰው የለውም፡፡ ከፋይሰል ጋር ደግሞ ከሰኞ በፊት ሌላ ቀጠሮ አልነበራቸውም፡፡ በሰመመን ሆኖ የሆቴሉ ሰራተኞች ለፅዳት ወይንም ሌላ አገልግሎት መግባት ፈልገው ሊሆን እንደሚችል ገመተ፡፡ ከእንቅልፉ ጨርሶ መንቃት ስላልፈለገ የበሩን ጥሪ ትቶ ወደእንቅልፉ ለመመለስ ሞከረ፡፡ ከቆይታ በኋላ ግን በሩ እንደገና ተንኳኳ፡፡ ይኼው መንኳኳት እንደቀደመው ሊተወው የሚችለው አልነበረም፡፡ በከፍተኛ ድምጽ እና ቶሎ ቶሎ ነበር በሩ የሚደበደበው፡፡ በንዴት ሱሪውን እንኳን ሳያጠልቅ ከአልጋው ወረደና ወደበሩ ሄዶ ከፈተው፡፡ በሩ ላይ ቆመው መከፈቱን ይጠባበቁ የነበሩት ብዛት ያላቸው መሣርያ የታጠቁ ዥንጉርጉር ሰማያዊ መለዮ የለበሱ ሰዎች እና አንድ ሲቪል የለበሰ ሰው ፈረሃንን ገፍትረው ወደክፍሉ ገቡ፡፡ የሚያየውን ማመን ከብዶት ነበር፡፡ የታጠቁት ሰዎች የክፍሉን ጥግ ጥግ ይዘው ቆሙ፡፡ ሲቪል የለበሰው ሰውዬ የፈረሃንን ክንድ ይዞ እንዲቀመጥ ጎተተው፡፡ ሰውየው ቤቱን ዞር ዞር ብሎ ካየ በኋላ ፊት ለፊቱ ተቀመጠ፡፡ ሰውየው በተሰባበረ እንግሊዘኛ ፖሊሶች መሆናቸውን እና ያረፈበትን ክፍል ሊፈትሹ እንደሚፈልጉ ገልፆ ሻንጣዎቹን የት እንዳደረጋቸው ጠየቀው፡፡ ፈረሃን በአገጩ ወደሻንጣዎቹ ጠቆመ፡፡ ሰውየው በተጠንቀቅ ወደቆሙት ወታደሮች ዞሮ በዓይኑ ምልክት ሰጣቸው፡፡ ሁለቱ መሣሪያቸውን ወደጀርባቸው አዙረው አዘሉና ሻንጣዎቹን መበርበር ጀመሩ፡፡ ላፕቶፕ ኮምፒውተሩን፣ ለዘመዶቹ ይዟቸው የመጣው አራት ዘመናዊ ተንቀሳቃሽ ስልክ ቀፎዎች እና ሻንጣው ውስጥ ያገኟቸውን ወረቀቶች በሙሉ ለብቻ ለብቻ ዘረገፏቸው፡፡ ሲቪል የለበሰው ሰውዬ ወረቀቶቹን አለፍ አለፍ እያለ ገረበባቸው እና ወደፈረሃን ዞሮ ‹‹ፓስፖርትህ የት ነው ያለው?›› ሲል ጠየቀው፡፡ ፓስፖርቱን ከሱሪ ኪሱ አውጥቶ ሊሰጠው ከተቀመጠበት ፈረሃን ብድግ ሲል ሰውየው ከፍ ባለ ድምጽ ተቆጥቶ እንዲቀመጥ አዘዘው፡፡ ‹‹ፓስፖርቴ ያለው ሱሪ ኪሴ ውስጥ ነው፡፡›› አለ በድንጋጤ ተውጦ ሱሪው ወዳለበት ቁምሳጥን እየጠቆመ፡፡ ሰውየው እራሱ ሳጥኑን ከፍቶ ሱሪውን ፈተሸ፡፡ ጥቂት የኢትዮጵያ ብሮች፣ ብዛት ያለው የአሜሪካን ዶላር እና የአሜሪካን ዜጋ መሆኑን የሚያረጋግጥ ፓስፖርቱን ካወጣና ሌላ ምንም እንዳልቀረ ካረጋገጠ በኋላ ሱሪውን ለፈረሃን ወረወረለት፡፡ ፈረሃን በተቀመጠበት ሆኖ ታግሎ ሱሪውን አጠለቀ፡፡

ከሻንጣዎቹ የወጡትን ንብረቶቹን ለብቻ አድርገው ሻንጣዎቹን ዘግተው ይዘዋቸው ወጡ፡፡ ሲቪል የለበሰው ሰውዬ እንዲነሳ አዝዞ ወደበሩ በአገጩ ጠቆመው፡፡ ዝም ብሎ ከዚህ በላይ መሄድ ያልፈለገው ፈረሃን ምን እየተካሄደ እንደሆነ ጠየቀ፡፡ ሲቪል ከለበሰው ሰውዬ ‹‹ፖሊሶች ነን›› ከሚል ምላሽ ውጪ ምንም ተጨማሪ መረጃ ማግኘት አልቻለም፡፡ ገፍትረውት ከገቡት ክፍል እየገፉ ይዘውት ወጡ፡፡

***

የረፈሃንን ስልክ ጥሪ ተቀብሎ ለሰኞ ቀጠሮ ከሰጠው በኋላ ፋይሰል ወትሮ እሁድ ከሰዓት እንደሚያደርገው ከጓዶቹ ጋር ኳስ እየተጫወተ ለማሳለፍ ከሚኖርበት ቦሌ ሚካኤል የጋራ መኖርያ ቤቶች አቅራቢያ ወደሚገኘው የእግርኳስ ሜዳ አመራ፡፡ ቀድመውት ከደረሱት ጓደኞቹ ጋር ኳስ እየተጫወቱ ወደማጠናቀቁ ሲቃረቡ ያልተለመደ ሁኔታ አካባቢው ላይ አስተዋለ፡፡ ሁሉም ጓደኞቹ ቆመው ኳሷ ብቻዋን ሜዳው ላይ ተንከባለለች፡፡ አስር የሚደርሱ ፌደራል ፖሊሶች ኳስ መጫወቻ ሜዳውን ከበው እያጠበቡ እየተጠጓቸው ነበር፡፡ የፖሊሶቹ ጣቶች ያነገቡት መሣርያ ቃታ አካባቢ ተሰድሯል፡፡ ፋይሰል አብረውት ኳስ ከሚጫወቱት ጓደኞቹ መካከል አንደኛውን እንደሚፈልጉ ገምቶ ነበር፡፡ የመጡት ፖሊሶች ‹ፌደራሎች› መሆናቸው የመጡበት ጉዳይ ቀላል እናዳልሆነ ጠቁሞታል፡፡ ይህ እያሰላሰለ ለጥቂት ሰከንዶች ከገባበት ሐሳብ ስሙ ሲጠራ ሰምቶ ባነነ፡፡ የከበቧቸውን ፖሊሶች ከኋላ ሆኖ የሚመራው ሲቪል የለበሰ ሰውዬ ነበር ሥሙን የጠራው፡፡ በፍጥነት ነገሩ ሁሉ ተደበላለቀበት፡፡ ስሙ ድጋሚ ሲጠራ መደናገሩ ስላለቀቀው ቆሞ ከማፍጠጥ ውጭ ምንም ማድረግ አልቻለም፡፡ የጓደኞቹ ዓይኖች በሙሉ እሱ ላይ አነጣጠሩ፡፡ ለሦስተኛ ግዜ ስሙ ሲጠራ የሚማርበት ክፍል ውስጥ ጥያቄ ለመመለስ እንደሚያደርገው የግራ እጁን ወደላይ አነሳ፡፡

***

ሊነጋጋ ሲል ያደሩበት ክፍል በር ተከፍቶ በሽንት የተሞሉትን ላስቲኮች እያንጠለጠሉ እየተጣደፉ ሲወጡ ምን እንደተፈጠረ እንዲያስረዳው ፈረሃን ኡመድን ጠየቀ፡፡ በቀን ውስጥ ሽንቱን መሽናት እና ውሃ ለመቅዳት ከሚያገኛቸው ሁለት አጋጣሚዎች አነደኛው መሆኑን፤ ይህ አጋጣሚ ግፋ ቢል ለ20 ደቂቃዎች ብቻ ስለሚቆይ ፈጠን ብሎ ተነስቶ ጉዳዩን እንዲጨርስ ከማሳሰቢያ ጋር ኡመድ መለሰለት፡፡ ፈረሃን ያገኘው መልስ ባይዋጥለትም ማሳሰቢያውን ተቀብሎ ወደመጸዳጃ ቤቱ አመራ የሽንት ሰዓቱ አብቅቶ በሩ ተመል እንደተዘጋ ጉዳዩን እንዲያብራራለት በድጋሚ ኡመድን ጠየቀው፡፡ ኡመድ የተለየ መል አልነበረውም፡፡

ኡመድ እና ጓደኞቹ የፈረሃንን ቁርስ ተቀበሉለት እና አብሯቸው በላ፡፡ ሁሉንም በሥም ተዋወቃቸው፡፡ በዕድሜ፣ በተክለ ሰውነት፣ በፊታቸው ቀለም ይለያያሉ፡፡ ሁሉም እዛው የተዋወቁ እንደሆነ ገብቶታል፡፡ ነገር ግን ከእንቅልፉ ሲባንን ነጭ አንሶላ የመሰለ ልብስ ተከናንበው ቆመው በቃላቸው ሲያነበንቡ የነበሩት ሽማግሌ ሰውዬ ከትግራይ የመጡት ቄስ ጎይቶም፣ ከኡመድ ቀጥሎ ግርግዳውን ታክኮ ያለው ፍራሽ ላይ ለሁለት የተኙት ወጣቶች የጅማና የሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ ምህንድና ተማሪዎቹ ሌንጂሳ እና ቢልሱማ፣ ከራሱ በስተቀኝ በኩል ተኝቶ ያደረው ወጣት የ16 ዓመቱ የቤኒሻንጉል ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ ታጋይ አብዱ፣ ከሱ በተቃራኒው ከቄሱ አጠገብ የተኛው ጎስቋላ ጎልማሳ የቤጊው ገበሬው በሊስ (አስፋው)፣ ከነሌንጂሳ በተቃራኒ ያለውን ፍራሽ የሚጋሩት የጅማው ኢማም ሼህ ጀማል እና ጣሂር፣… ባጠቃላይ ከኤልያስ በስተቀር ሲገባ ከቆጠራቸው 13 ሰዎች ውስጥ 12ቱ በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው በምርመራ ላይ ያሉ መሆናቸው ገና አልገባውም፡፡

ቁርሳቸውን ጨርሰው ሁላቸውም ፍራሾቻቸው ላይ ቁጭ ቁጭ ብለው በዝምታ ተዋጡ፡፡ ማታ ሲቀላቀላቸው በጨዋታ ደምቆ የነበረው ክፍል ለምን በዝምታ እንደተዋጠ አልገባውም፡፡ ምናልባት ወደኋላ እየሞቃቸው ሲሄድ ዝምታው እንደሚጠፋ ገመተ፡፡ በአብዛኞቹ ጭንቅላት ውስጥ ገብቶ ዝምታውን ያሰፈነው ሰኞ ጠዋት መሆኑ ነበር፡፡ እሁድ ቀን ከምርመራ ሚያርፉባት ናት፡፡ ሰኞ ጠዋት ደግሞ ምርመራው የቆመው ምን ጋር እንደነበር እያስታወሱ እንዴት እንደሚቀጥል እና ከግርፋት እና ከእንግልት የሚድኑበት መልስ ምን እንደሆነ የሚያሰላስሉባት ናት፡፡

ፈረሃን ዝምታን ለመስበር ለኡመድ ጥያቄ አነሳ፡፡ ‹‹አሁን ምንድነው የሚሆነው? ምንድን ነው የምሆነው?›› ኡመድ ረጋ ብሎ ለፈረሃን መመለስ ጀመረ ‹‹ዛሬ ምናልባት ፍርድ ቤት ይወስዱህ ይሆናል፡፡ ለምን እዚህ እንዳመጡህ ለፍርድ ቤት ሲያስረዱ ትሰማለህ …›› ፈረሃን ኡመድን አቋረጠውና ‹‹ፍርድ ቤት በእንግሊዘኛ ነው የሚሰራው?›› ሲል ጠየቀው፡፡ ኡመድ ፈገግ ብሎ ‹‹ፍርድ ቤት በእንግሊዘኛ አይሠራም፡፡ ሱማልኛ አስተርጓሚ መጠየቅ ግን ትችላለህ፡፡›› አለው፡፡ ማስረዳቱን ቀጥሎም ‹‹በደረቅ ወንጀል ከሆነ የጠረጠሩህ እስከ 14 ቀን የሚደርስ ቀጠሮ አለበለዚያ በሽብር የሚጠረጥሩህ ከሆነ ደግሞ …›› ፈረሃን በድጋሚ ኡመድን ቋረጠውና ‹‹ይህ ሊሆን አይችልም!›› አለ፡፡ ኡመድ ፈገግ ብሎ ‹‹በጣም ጥሩ›› ብሎ መለሰ፡፡ በልቡ ግን ፈረሃን ፍርድ ቤት ከሄደ የ28 ቀን ቀጠሮ ይዞ እንደሚመጣ ጠንካራ ግምት ነበረው፡፡

ትንሽ እንደተጨዋወቱ ያሉበት ክፍል በር ተከፈተና ኡመድ ተጠራ፡፡ እየተቻኮለ እየወጣ ወደፈረሃን ዞሮ ‹‹ምርመራ መሄዴ ነው፡፡›› አለው፡፡ ብዙም ሳይቆይ ፈረሃንም ተጠርቶ ወጣ፡፡ ለምሣ ሰዓት ጥቂት ግዜ ሲቀረው ፈረሃን ተመልሶ መጣ፡፡ ፊቱ ላይ የመቆጣት ስሜት ይነበብበት ነበር፡፡ ምርመራውን ጨርሶ ከፈረሃን በፊት ወደክፍሉ ተመልሶ የነበረው ኡመድ ‹‹ፈረሃን፤ እንኳን በደህና ተመለስክ፡፡ ፍርድ ቤት ወሰዱህ እንዴ?›› ሲል ጠየቀው፡፡ ተስፋ በቆረጠ የተሰላቸ ድምጽ ‹‹28 ቀን ቀጠሩኝ፡፡›› ብሎ ፍራሹ ላይ በደረቱ ተደፋ፡፡

***

የክፍሉ መቀርቀሪያ በኃይል ተወርውሮ ሲከፈት ያወጣው ድምጽ ሁሉንም ከእንቅልፍ ቀሰቀሳቸው፡፡ በርግጥ ከመካከላቸው ገና ወደበሩ እየቀረበ የነበረውን የእግር ኮቴ እና ሲንቀጫቀጭ የነበረውን የካቴና ድምጽ ሰምተው ከእንቅልፋቸው አስቀድመው የነቁ ነበሩ፡፡ በሩ ተከፍቶ ‹‹ሌንጂሳ አለማየሁ›› የሚል ድምጽ ተጣራ፡፡ ሁሉም ዓይናቸውን ወደሌንጅሳ ወረወሩ፡፡ ‹‹አቤት›› ብሎ ብርድ ልብሱን ከላዩ ላይ እየገፈፈ ተነሳ፡፡ ከመውጣቱ በፊት የመተኛ ሱሪው ላይ ሌላ ሱሪ ደረበ፡፡

ፈረሃን ክፍሉ ውስጥ የቀሩት ሰዎች ሌንጂሳን ያዩ የነበረበት ሁኔታ የሆነ ክፉ ነገር እንዳለ ነግሮታል፡፡ ከእንቅልፍ አስቀስቅሶ የሚያስወስድ አሳሳቢ ነገር ምን ይሆን ሲል አሰበ፡፡ ስንት ሰዓት እንደሆነ ጠየቀ፡፡ ኡመድ በግምት ሶስት ሰዓት አካባቢ እንደሚሆን ሲናገር ፈረሃን ቀና ብሎ የክፍሉን አራት ማዕዘን ግርግዳዎች ቃኘ፡፡ የፈለገውን አላገኘም፡፡ ‹‹እዚህ ምንም ሰው ሰዓት የለውም?›› ሲል ጠየቀ፡፡ ኤልያስ የፈረሃን ጥያቄ ያለአስተርጓሚ ስለገባው ተሰባበረ እንግሊዘኛ ወደማረፊያ ቤት ሰዓት ይዞ መግባት የተከለከለ መሆኑን አስረዳ፡፡ ፈረሃን የበለጠ ግራ በመጋባት ‹‹ታድያ የፀሎት ሰዓት ሲደርስ በምንድን ነው የምናውቀው?›› ኤልያስ ጥያቄውን መረዳት ስላቃተው የኡመድን ዓይን ያይ ጀመር፡፡ የኤልያስ ችግር የተረዳው ኡመድ የፈረሃንን ጥያቄ ተርጉሞ ነገረው፡፡ ‹‹አሃ…›› ኤልያስ መልሱን በእንግሊዘኛ ሲያደረጅ ቆየና ተሰላችቶ ኡመድን በቃ አንተ ንገረው በሚል አኳኻን አይቶት ዝም አለ፡፡ ጠዋት እና ማታ የሚቆጥሯቸው ፖሊሶች ሲመጡ ስንት ሰዓት እንደሆነ እንደሚጠይቋቸው እና ከዛ የቀረውን ግዜ በግምት እንደሚያሟሉት ኡመድ አብራራ፡፡ ፈረሃን ያለበት ቦታ ሲዖልነት ቀስ በቀስ እየገባው ነው፡፡ ቀጥሎ በጠየቃቸው ጥያቄዎች የተረዳው ነገር ደግሞ ለደህንነቱ አብዝቶ እንዲጨነቅ አስገደደው፡፡ ሌንጂሳ እና ጓደኛው ቢልሱማ ከሚማሩበት ዩኒቨርሲቲ በቁጥጥር ስር የዋሉት መንግሥት ሊተገብረው ያቀደውን የአዲስ አበባ እና በዙሪያዋ ያሉ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ዞኖች የተቀናጀ ማስተር ፕላንን በመቃወም የተካሄዱ ሰልፎች ላይ ተሳትፋቹኻል እና ተቃውሞውን አስተባብራቹኻል በሚል ምክንያት ሲሆን በተለይ ሌንጂሳ ጅማ ዩኒቨርስቲ ደጃፍ ላይ በደህንነቶች ከተያዘ በኋላ አዲስ አበባ እስኪመጣ ድረስ የነበረውን 3ቀን እህል የሚባል እንዳልቀመሰ፣ አሁን ያሉበት ቦታ ካመጡት ጀምሮ ደግሞ በየቀኑ ማታ ማታ ተጠርቶ ሌሊቱን ክፉኛ እየተደበደበ በምርመራ እንደሚያጋምስ ነበር የተነገረው፡፡ ምርመራ ተወስዶ መደብደብ ማንም ሰው ላይ ሊከሰት እንደሚችል፣ ክፍሉ ውስጥ ከነበሩት ሰዎች መካከል ጨዋታ ከሚወደው ባለ ደንዳና ሰውነቱ የቡና ነጋዴ ኤልያስ በስተቀር ሁሉም ክፉኛ ድብደባ የደረሰባቸው መሆኑን ኡመድ አንድ በአንድ እየጠቆመ ነገረው፡፡

እንቅልፍ አጥቶ ሲገላበጥ ብዙ ሰዓት አለፈው፡፡

የክፍሉ በር ተከፈተና ሌንጂሳ በፖሊስ ተደግፎ ወደክፍሉ ገባ፡፡ እራሱን ችሎ መራመድ ስላቃተው ቢልሱማ ተነስቶ ድጋፍ ሆኖት ወደፍራሹ አደረሰው፡፡ ሁሉም ድጋሚ ከእንቅልፋቸው ተነስተው በትካዜ ተዋጡ፤ የተከሰተው ለሁሉም ገብቷቸዋል፡፡ ፈረሃን አንድ ነገር ድንገት ጭንቅለቱ ውስጥ አቃጨለ፡፡ አንድ ጓደኛው ከወራት በፊት በአግራሞት አውርቶለት የነበረ ‹‹Human Rights Watch›› የተባለ የመብት ተሟጋች ቡድን ‹‹They Want Confession›› በሚል ርእስ ያወጣው ዘገባ ትዝ አለውና ወደኡመድ ዞሮ ‹‹ማዕከላዊ ነው እንዴ ያለነው?›› ሲል ጠየቀ፡፡

***

ፋይሰል ፍርድ ቤት የተከሰተው ነገር ጭራሽ ግርታውን አብሶበታል፡፡ ከሱ እና ከአጎቱ ልጅ በተጨማሪ አይቷቸው የማያውቃቸው ሶስት ወንድ እና አንድ ወጣት ሴት ሱማሌዎች አብረዋቸው ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡ ሶስቱ ወንድ ሱማሌዎች የሚያመሳስላቸው ነገር እንዳለ ፋይሰል አስተውሏል፡፡ የአነጋገር ዘይቤያቸው ልክ እንዳጎቱ ልጅ ውጭ ሀገር ቆይተው እንደመጡ ያስታውቃል፡፡ 18 ዓመት እንኳን የሞላት የማትመስለው አብራቸው ፍርድ ቤት የቀረበችው ሴት ደግሞ ከአነጋገሯ የኢትዮጵያ ሱማሌ እንዳልሆነች ገብቶታል፡፡

ከፍርድ ቤት እንደተመለሰ ክፍሉ ውስጥ የነበሩት ሰዎች ጥያቄ ያጣድፉት ያዙ፡፡ ፍርድ ቤት የተከሰተውን ለማስረዳት ሞከረ፡፡ ስድስት ሆነው እንደሄዱ፣ ችሎት ውስጥ ለሁለት ከፍለው ሦስት ሦስት አድርገው ይዘዋቸው እንደገቡ፣ እሱን በዕድሜ ሸምገል ካለው ሰውዬ እና ከወጣቷ ጋር ችሎት ፊት እንዳቀረቡት ነገራቸው፡፡ በጥሞና ሲያዳምጡት የነበሩት ሰዎች በምን ወንጀል እደተጠረጠረ ለማወቅ ነበር፡፡ ፋይሰል በረጅሙ ትንፋሽ ወስዶ ‹‹አል ሸባብ ከተባለ ቡድን ተልዕኮ ተቀብለው አዲስ አበባ ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች የሽብር ወንጀል ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ ይዣቸኋለው፡፡›› የሚል ክስ ይዟቸው የሄደው ፖሊስ አንብቦ የ28 ቀን ቀጠሮ እደጠየቀና መነፅራቸውን ዝቅ አድርገው ጥያቄውን የሰሙት አዛውንት ሴት ዳኛ የ28 ቀን ቀጠሮውን መፍቀዳቸውን አስረዳቸው፡፡ ከጠበቁት ብዙም የራቀ ነገር አልነገራቸውም፡፡ ምንም የመደንገጥም ሆነ የመሸሽ ዓይነት ስሜት ስላላየባቸው እረፍት ቢሰማውም ሽብርን የሚያክል ትልቅ ክስ ቀረበብኝ ሲላቸው አለመገረማቸው ግር አሰኝቶት ነበር፡፡ ኋላ ላይ ሲረዳ ግን ማዕከላዊ የገባ ሰው ከሱማሌ ከሆነ አልሸባብ ወይንም ኦብነግ ተብሎ፣ ኦሮሞ ከሆነ ኦነግ፣ ከትግራይ ከሆነ ትሕዴን፣ ሙስሊም ከሆነ አልቃይዳ፣ አማራ ከሆነ አርበኞች ግንባር፣ ጋዜጠኛ ወይንም የፖለቲካ ድርጅት አባል ከሆነ ግንቦት 7 ተብሎ መከሰሱ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

***

ምሣ በልተው እንደጨረሱ በሩ ተከፈተና የፋይሰል ስም ተጠራ፡፡ ‹‹አለሁ›› ሲል ለጥሪው መልስ፡፡ ‹‹ዕቃህን ይዘህ ውጣ›› የሚል ትዕዛዝ ተከተለ፡፡ የተባለው ስላልገባው እንዲደገምለት ‹‹እእ…›› አለ፡፡ በሩ ላይ የቆመው ፖሊስ ቁጣ በተቀላቀለበት ድምጽ ‹‹ዕቃህ ይዘህ ውጣ!›› ሲል ደገመለት፡፡ ከኳስ ጨዋታው መልስ ታጥቦ ሊቀይር ይዞት የነበረውን ልብስ በስስ ፌስታል ይዞ ወጣ፡፡

በር ላይ ቆሞ የነበረው ፖሊስ ካቴና አለመያዙን ሲያስተውል ተስፋ ቢጤ ተሰምቶት ነበር፡፡ ግን የተሰማው የተስፋ ስሜት በፍጥነት ወደተስፋ መቁረጥ ተለወጠ፡፡ ከሰው ጋር አብሮ ይታርሰር ከነበረበት ማረፊያ ቁጥር 9 የወጣው ብቻውን ወደሚታሰርበት ጨለማ ክፍል ቁጥር 8 ለመዘዋወር ነበር፡፡

***

በተለምዶ ሳይቤሪያ ተብሎ የሚጠራው የማዕከላዊ ሕንጻ ቁጥር 84 በረጅም ኮሪደር ለሁለት የተከፈለ ሲሆን የእስረኛ ማቆያ ክፍሎቹ ከኮሪደሩ ግራና ቀኝ የተደረደሩ ናቸው፡፡ ኮሪደሩ ሲጀመር በግራና በቀኝ 2ቁጥር እና 10 ቁጥር ማረፊያ ክፍሎች ፊት ለፊት ተፋጠዋል፡፡ በግራ በኩል ከ2ቁጥር አንስቶ እስከ 6ቁጥር የሚዘልቅ ሲሆን በስተቀኝ በኩል ደግሞ ከ10 ቁጥር ጀምሮ ቁልቁል እየቆጠረ እስከ 7ቁጥር ይሄዳል፡፡ ከ7 ቁጥር ማረፊያ ክፍል ቀጥሎ ደግሞ ዘጠኙ ክፍሎች ውስጥ የሚታሰሩት ሰዎች በየተራ ክፍሎቹ እየተከፈቱ በቀን ሁለት ግዜ (ጠዋት እና ማታ) ቢበዛ ለ20 ደቂቃዎች የሚጠቀሙበት ባለ6 የሽንት ቤት ክፍል እና አንድ መታጠቢያ ክፍል ያለው መጸዳጃ ቤት ይገኛል፡፡

ሳይቤርያ ውስጥ የሚገኙት ክፍሎች በስፋት ካልሆነ በቀር አንድ ዓይነት ናቸው፡፡ ከሁሉም ክፍሎች የሚለየው 8ቁጥር ነው፡፡ ከውጪ በሩ ተዘግቶ ለሚያየው ሰው 8 ቁጥርም ቢሆን ከሌሎቹ የሚለይበት ነገር የለም፡፡ በሩ ተከፍቶ ወደውስጥ ሲገባ ግን በግራና በቀኝ በኩል ሁለት ሁለት የራሳቸው በር ያላቸው ሌላ ከፍሎች ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ክፍሎች ጠንከር ያለ ምርመራ እየተደረገባቸው ላሉ መንፈሰ ጠንካራ ሰዋች የተዘጋጀ ነው፡፡ እነዚህ ክፍሎች ውሰጥ የሚታሰር ሰው በቦታ ጥበት፣ በጨለማ እና ብቸኝነት ይፈተናል፡፡

ይህ ታሪክ ለአንባቢ ምቾት ሲባል ከተደረገለት ዘይቤያዊ ማስተካከያ በስተቀር እውነተኛ ታሪክ ነው፡፡

(ይቀጥላል)

http://wp.me/p5L3EG-9O