Netsanet: September 2016

Montag, 26. September 2016

«እሱም አላቸው ሂዱ ፥ እነሱም አሉ አንሄድም»( በ ኄኖክ የሺጥላ)

Henoke Yeshetlla
​«እሱም አላቸው ሂዱ ፥ እነሱም አሉ አንሄድም» ነው ያሉት እኛ የልደታ ቤ/ክርስቲያን ቄስ! እኝህ አባት ባንድ ወቅጥ « በኖህ ዘመን » አሉ « አዎ በኖህ ዘመን ልጆቼ ምድር ተጥለቀለቀች ፥ በምድር ላይ የሚኖሩ ነገሮች ሁሉ ተጥለቀለቁ ፥ በግዜው የዋና ፓንት እና መንሳፈፊያ የሰውነት ጓንት አልነበረም ፥ ቀይ መስቀል አልነበረም ፥ ጥሬ ውሃና እና ጥሬ ፍጥረት ብቻ ነበር የነበረው » አሉ ። ቀና ሲሉ አውሮፕላን ሲበር አዩ ። እና ቀጠሉ

አዎ በኖህ ዘመን አሉ « በኖህ ዘመን አውሮፕላኑም ተጥለቀለቀ » ።   የእኝህን አባት ማንነት ሳጣራ ፥ ታጋይ እና ተጋዳላይ የነበሩ ፥ አንድም አይነት የቤተ ክህነት እውቀት የሌላቸው ሰው እንደሆነ ኋላ ላይ ደረስኩበት ።

እና ምን ለማለት ነው ፥ « በመስቀል ዘመን ፥ መስቀል አደባባይ በፌደራል ተጥለቀለቀች ፥ መስቀል አደባባይነቷን ረስታ ፥ ፌደራል አደባባይ ሆነች ፥ በጊዜው ምዕመን አልነበረም ፥ የነበረው ጥሬ  ወታደር  እና እርጥብ  ችቦ ብቻ ነበር ።  ህዝቡንም ውጡና በዓል አክብሩ አሏቸው ፥ ህዝቡም አንወጣም  ይህ የደመራ ችቦ ሳይሆን የደም ደቦ ነው አለ» በኛ  ዘመን ! እየተናቁ መግዛት ግን እንዴት ያስጠላል!   በግድ ውደዱኝ ማለት ግን እንዴት ይሸክካል!? ነገሩ ያራዳ ልጅ ካልሆንክ ይህ አይገባህም ! የገገሞች ህገ መንግስት መግቢያ « አስገድደን ለምንገዛችሁ እና በግድ እንድትወዱን ላስገደድናችሁ ህዝባችን ሆይ » ነው የሚለው ? እኔ እንጃ! ጃ ያስተሰርያል!

ኄኖክ የሺጥላ
http://wp.me/p5L3EG-dl

Sonntag, 25. September 2016

​ስለ አሻጥር እና ሕዝባዊ አሻጥር(በ ዶ/ር ታደሰ ብሩ)

​ስለ አሻጥር እና ሕዝባዊ አሻጥር

Dr Tadesse Biru Kersmo

1. መግቢያ

በሕዝባዊ አሻጥር ላይ በፃፍኳቸው ጥቂት መጣጥፎች “አሻጥር” የሚለው ቃል አሉታዊ ትርጉም ስላለው ሌላ ቃል እንድፈልግለት ጥቂት ወዳጆቼ በግል በላኩልኝ መልዕክቶች ጠይቀውኛል። በዚህም መነሻ ይህንን አጭር ማብራሪያ  መስጠት አስፈላጊ ሆኖ አግኝቸዋለሁ።

2. አሻጥር እና ሕዝባዊ አሻጥር

“አሻጥር”(Sabotage) ማለት ተንኮል፣ ሸር፣ ደባ ማለት ነው፤ አንድን ነገር በስውር ማፍረስ ማለት ነው።  አሻጥር ሁሉ መጥፎ ነገር አይደለም። አንድን አሻጥር “ጥሩ” ወይም “መጥፎ” ከሚያሰኙት ነገሮች ሁለቱ:

1. በማን ላይ ወይም በምን ዓይነት ሰው፣ ድርጅት ወይም አገዛዝ ላይ ነው አሻጥሩ የሚፈፀመው? እና
2. ምን ለማግኘት ነው አሻጭሩ የሚፈፀመው?
ለሚሉ ጥያቄዎች የሚሰጡ መልሶች ናቸው።

ደረጃቸው እና ዓይነታቸው ይለያይ እንጂ ሁሉም መንግሥታት አሻጥር ይሠራሉ። ስውር ተግባራት (Covert Activities or Covert Actions) በመሠረቱ አሻጥሮች ናቸው። ዲሞክራሲያዊ አገሮችም አሻጥሮችን ይሰራሉ፤ ሆኖም ባብዛኛው በሌሎች አገሮች ላይ እንጂ በራሳቸው ዜጎቻቸው ላይ አይደለም። ዲሞክራሲያዊ መንግሥት በዜጎች ላይ አሻጥር ቢፈጽም ዜጎች መንግሥትን በህግ ከሰው ማስቀጣት የሚችሉበት ሥርዓት ተበጅቷል።

አምባገነን መንግሥታት ግን አሻጥር የአገዛዛቸው አንድ ሁነኛ መሣሪያ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ የህወሓትን ያህል አሻጥረኛ ድርጅት ማግኘት ከባድ ነው። የሚከተሉትን ለአብነት እናንሳ:

1. ህወሓት በረሀ በነበረት ጊዜ ከላይ ስንዴ በተን በተን የተደረገባቸው በአሸዋ የተሞሉ ከረጢቶችን ለየዋህ ለጋሾች ሸጧል። ህወሓት አሸዋ ሸጦ ገንዘብ ሰብስቧል።

2. ህወሓት በትግሉ ሜዳ የነበሩትን የመጀመሪያ ዙር ተቀናቃኞቹን ያጠፋው ለእርቅ ጠርተዋቸው አብረው በልተውና ጠጥተው በተኙበት በማረድ እንደሆነ በስፋት ይነገራል።

3. የህወሓት አገዛዝ ፍርድ ቤቶች በአሻጥር የተሞሉ ናቸው። አንዳንዱ አሻጥር ዓይን ያወጣ ቢሆንም አገዛዙ ደንታ  የለውም። ለምሳሌ “በዳኞች ተሟልቶ አለመገኘት” ብቻ ከሁለይ ዓመት በላይ የተጉላሉ የፓለቲካ እስረኞች አሉ።

4. ህወሓት በእርቅ ስም ተቀናቃኞቹን ሲያሞኝ የኖረና አሁንም ለማሞኘት እየሞከረ ያለ ድርጅት ነው። በምርጫ 97 እንዳየነው ታሳሪዎቹ ከእስር ቤት ሳይወጡ በሽማግሌዎች የተደረሰበት ስምምነት ተሰርዞ፤ ለሽማግሌዎቹ የተገባው ቃል ተሰብሮ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ ተከፍቶባቸዋል። ከዚያ ወዲህ እስከዛሬ ድረስ ህወሓት በእርቅና በሽምግልና ስም አሻጥር  እየሠራ ነው።

5. የህወሓት/ኢህአዴግ አገዛዝ ተቀናቃኝ ፓርቲዎችን ለማዳከም በፓርቲዎቹ አመራር መካከል ጥርጣሬ እንዲነግስ ጉባዬዎቻቸውን እየሰለለ ቃለጉባኤዎቻቸውን ከእነሱ አስቀድሞ በጋዜጣ የሚያትም መሰሪ አሻጥረኛ ነው።

6. ህወሓት በተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራር መካከል ቅጥረኞችን ይመለምላል፤ እርስ በርስ ያጋጫል፤ ፓርቲዎቹ በቅራኔ ፈጽሞ  እንዲፈርሱ ወይም እንዲዳከሙ ያደርጋል። አንድነትና መኢአድ ላይ የተፈፀመው ልብ ይሏል ! 

7. የህወሓት/ኢህአዴግ አገዛዝ ምርጫን የሚጠቀመው በአሻጥር መሣሪያቱ ብቻ ነው። በየአምስት ዓመቱ የምርጫ ድግስና ግርግር ይኖራል ውጤቱ ግን አስቀድሞ የታወቀ ነው።

8. የህወሓት አገዛዝ “በህጋዊ መንገድ ታገሉኝ” ይላል፤ ሆኖም እንኳን መታገል የመሰብሰቢያ አዳራሽ ማግኘት ከባድ ነው። የተቃዋሚ ፓርቲዎች በአገዛዙ ከጀርባ በሚደረግ ግፊት የመሰብበሲያ አዳራሽ የሚያከራያቸው የጠፋበት አጋጣሚ ለቁጥር እስከሚያታክት ብዙ ነው። በአንዳንድ አጋጣሚዎች ሆቴሎች “ሀሳባቸውን የሚቀይሩት” ስብሰባው ሊጀመር ደቂቃዎች ሲቀሩት ነው።

9. ከህክምና ስነምግባር ውጭ የወህኒ ቤት ጤና ባለሙያዎች ታሳሪዎች ምን መሆኑ የማያውቁት መርፌ ይወጋሉ። ሲቪል ሰርቪስ አስቂኝ በሆኑ ምክንያት ባለጉዳዮችን ያጉላላል። ለምሳሌ የታዋቂ ሰዎችን የጉዞ ፕሮግራም ለማስተጓጎል በማይረባ ሰበብ ፓስፖርት ይዞ ማቆየት በህወሓት የተለመደ አሠራር ሆኗል።

10. በልማት ስም የሚደረገው አሻጥር ብዛት ተዘርዝሮ  አያልቅም። የኢኮኖሚ የበላይነት ካልተያዘ የፓለቲካ ሥልጣን ብቻውን መያዝ በቂ አይደለም በሚል የተንሸዋረረ ፍልስፍና  መነሻነት አባላቱን ለሀብት ዘረፋ ያሰማራ ድርጅት ህወሓት ነው። ሌላው ቀርቶ  በከተሞች በልማት ስም ቤቶች ሲፈርሱ ሆነ  ተብሎ በክረምት እንዲሆን የሚፈለግበት ምክንያት ከመሰሪ አሻጥረኝነት የተሻለ ገላጭ የለውም።

ከላይ ለአብነት ያህል የተዘረዘሩት የአሻጥር ዓይነቶች አንድ እኩይ ድርጅት በሕዝብና በአገር ላይ የፈፀማቸው አሻጥሮች ናቸው፤ እነዚህን መፀየፍ ተገቢ ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ ተበዳይ በበዳይ ላይ፤ ተጨቋኝ በጨቋኝ ላይ፤ ደካማው በጉልበተኛው ላይ የሚሠራቸው አሻጥሮች አሉ። የጀርመንን ፋሺዝምን ከጣሉት ነገሮች አንዱ በራሱ በናዚ ፓርቲ ውስጥ የነበሩ ቅን ዜጎች አሻጥር በመሥራት ሥርዓቱን ማሽመድመዳቸው ነው።  ለአብነት ያህል ኦስካር ሽንድለር (Oskar Schindler) መጥቀስ ይበቃል። ይህ ሰው  የናዚ ፓርቲ አባልና ሰላይ ነበር። ሆኖም አለቆቹ ያዘዙትን ሳይሆን ቅን ህሊናው ያዘዘውን አሻጥር በመሥራት የነፃነት ታጋዮችን መርዳት ጀመረ፤ በሱ የግል ትብብር የ 1200 ሰዎችን ሕይወት ታደገ። ከጦርነቱ በኋላ ኦስካር በርካታ የክብር ስሞችና ሽልማቶች የተሰጠው  በመልካም አርዓያነቱ የሚጠቀስ ሰው ሆነ። እንዲህ ዓይነቱን አሻጥር መልካም አሻጥር (Civic Sabotage) ይባላል።
መልካም አሻጥር በማኅበረሰብ ደረጃም ይደረጋል። በአሜሪካና ቬትናም ጦርነት አሜሪካን ግራ ያጋባትና በኋላም ለአሳፋሪ ሽንፈት የዳረጋት የቬትናሞች የጋራ (የደቦ) የተቀነባበረና የተቀናጀ አሻጥር ነው። እንዲህ ዓይነቱን አሻጥር “ሕዝባዊ አሻጥር” ብለን መጥራት እንችላለን።

ሕዝባዊ አሻጥር ለኢትዮጵያዊያን አዲስ ነገር አይደለም።  በጣሊያን ወረራዎች ጊዜ ከፊት ለጠላት እየሳቁ ከጀርባ መውጋት  የተለመደ ነበር። በሁለተኛው የወረራ ወቅት ደግሞ በፋሺስት መሥሪያ ቤት እና በባለስልጣኖቹ መኖሪያ ቤት ተቀጥሮ ሚስጥር መስረቅና ለወገን ማሳለፍ አንድ የአርበኝነት ዘርፍ ነበር፤ መጠሪያ ስሙም “የውስጥ አርበኛ” ነበር። የውስጥ አርበኛ፣ አርበኛ ነው !!! እንዲያውም  የውስጥ አርበኛ ከበረሀ አርበኛ የበለጠ የሚከበርበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል። ዶክተር ፍቅሬ ማርቆስ ገድሌ "የአኩሪ ገድላት ባለቤት" በሚለው መጽሐቸው ያወደሷቸው ወ/ሮ ሸዋረገድ ገድሌ አሻጥረኛ ናቸው። ሆኖም ግን የእሳቸው አሻጥር ዓላማ ሀገርን ከወራሪ ለመታደግና አርበኞችን ለመርዳት በመሆኑ ወ/ሮ ሸዋረገድ የሚወደዱ፣ የሚከበሩ፣ የሚወደሱ አሻጥረኛ ናቸው። የወ/ሮ ሸዋረገድ አሻጥር ሕዝባዊ አሻጥር ነው።  ወይዘሮ ሸዋረገድ በዚህ የሕዝባዊ አሻጥር እንቅስቃሴአቸው ከአስራ ሁለት ጊዜ በላይ መታሰራቸውን፣ በተለይም በግራዚያኒ ሕይወት ላይ በተቃጣው የቦንብ ዉርወራ ተሳትፈሻል ተብለው ከፍተኝ የሆነ ድብደባ እንደደረሰባቸው፣ በኋላ ላይ የተለወጠ የሞት ፍርድ እንደተፈረደባቸውና በእስር ከሌሎች አርበኞች ጋር በጣሊያኗ የአዚናራ ደሴት ላይ ታስረው እንደነበርም ከታሪካቸው እንረዳለን። በጠላት ወረራ ዘመን የውስጥ አርበኛ (ሕዝባዊ አሻጥረኛ) መሆን ከነፃነት በኋላ የሚያስከብር ጀብድ ሆኖ በመገኘቱ ባንዶች ሳይቀሩ ዘመዶቻቸውን እያስመሰከሩ ተሸልመውበታል። ይህም ማለት በሕዝባዊ አሻጥር ላይ አሻጥር ተሰርቶበታል። ይህ ሀቅ “የውስጥ አርበኛ” ድርብ ትርጉም እንዲይዝ፤  Civic Sabotage ወይም Covert Activities “የውስጥ አርበኛ” በሚለው የተለመደ አጠራር እንዳንጠቀም የተወሰነ ተጽዕኖ አድርጓል።

በመጨረሻም፤ “እምተኝነትና” እና “አመጽ” አሉታዊ ስሜት የሚሰጡ ቃላት ቢሆንም እንኳን “ሕዝባዊ እምቢተኝነት” እና “ሕዝባዊ አመጽ” የሚሉ ጽንሰ ሀሳቦች ተቀባይነት እያገኙ መምጣታቸውን በማጤን Civic Sabotage ን ወይም ለመልካም ዓላማ የሚፈፀም ስውር ተግባራትን (Covert Activities) “ሕዝባዊ አሻጥር” ብለን ብንተረጉመው የተሻለ ነው የሚል እምነት አለኝ።

3. ማጠቃለያ

ሁለገብ ትግል ዘርፈ ብዙ ነው: ሕዝባዊ እምቢተኝነት፣ ሕዝባዊ አመጽ፣ ሕዝባዊ አሻጥር፣ ...  በሁለገብ የትግል ስትራቴጄ እያንዳንዱ ዜጋ ለትግሉ የሚያበረክተው አስተዋጽዖ አለ። ሕዝባዊ አሻጥር የሁለገብ ትግል አንድ የትግል ስልት ነው። በማናቸውም ምክንያት የመሣሪያ ትግል ለማይወዱ ሕዝባዊ አሻጥር ተመራጭ የትግል ስልታቸው ሊሆን ይገባል። “የጨዋ” ወይም አንዳንዴ እንደሚባለው “የሰለጠነ” ፓለቲካ በማድረግ ፋሽስታዊ ሥርዓትን ከስልጣን ማስወገድ ይቻላል የሚል ሰው ራሱን እያሞኘ ያለ ሰው ነው።

በአፋኝ ሥርዓት ላይ አሻጥር መሥራት ከሥነምግባር አኳያ ተቀባይነት ያለው መልካም ሥራ ነው - ሲቪክ ነው። ይልቁንስ አስነዋሪ የሚሆነው ከአፋኝ ሥርዓት ጋር መተባበር ወይም “እኔ ምን አገባኝ” ብሎ መቀመጥ ነው፤ ይህ አስነዋሪ ብቻ ሳይሆን ወንጀልም ነው።  በህወሓት አገዛዝ ተዘርዝሮ የማያልቅ ግፍ እየተፈፀመብን “እኔ ምን ማድረግ እችላለሁ” እያሉ ዝም ብሎ መቀጥቀጥ ፈጽሞ ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም።

ሕዝባዊ አሻጥር የትግሉን ኪሳራ በመቀነስ ረገድ ያለው አስተዋጽዖ ከፍተኛ ነው። እያንዳንዱ የአጋዚና የፌደራል ፓሊስ በሰው ላይ ሳይሆን አየር ላይ ቢተኩስ፤ እያንዳንዱ የህወሓት ሰላይ እጁ ውስጥ የገቡ ሚስጢሮችን ለነፃነት ታጋዮች ቢያቀብል፤ እያንዳንዱ የመንግሥት ጋዜጠኛ ዜናዎችን ለነፃው ሚዲያ ቢያቀብል፤ እያንዳንዳ ታይፒስት የህወሓት ሹማምንት ቃለጉባኤዎችን ለነፃነት ኃይሎች ብታቀብል፤ እያንዳንዱ ሠራተኛ በሥራው ላይ ቢለግም፤ እያንዳንዱ መምህር ስለነፃነት፣ ስለሰብዓዊ መብቶችና ስለፍትህ ቢያስተምር፣ ....  ህወሓት እንዴት አድርጎ መግዛት ይችላል?

ሕዝባዊ ተግባራት በቡድን ቢደረጉ ሕዝባዊነታቸው ይጎላል፤ ሆኖም ግን ሕዝባዊ ተግባራት በአንድ ግለሰብም ይፈፀማሉ። የሕዝባዊ አሻጥር ተግባራትም እንደዚሁ ናቸው፤ በቡድን ቢሰሩ መልካም ነው ሆኖም በአንድ ግለሰብም ተግባራዊ ሊደረጉ የሚችሉ በርካታ የሕዝባዊ አሻጥር ተግባራት አሉ። እያንዳንዳችን አካባቢያችን እንመልከትና በህወሓት አገዛዝ ላይ መስራት ስለምንችለው አሻጥር እናስብ፤ ተግባራዊ እናድረገው።

በአፋኝ ሥርዓት ላይ የሚደረግ አሻጥር የጽድቅ ሥራ ነው፤ መልካም ሥራ ነው፤ ሕዝባዊ ነው። 

ጊዜው የሕዝባዊ አሻጥር ነው !!!