Netsanet: Juli 2017

Montag, 10. Juli 2017

አርበኝነት

አርበኝነት

አርበኝነት ማለት ለወገኑ የተሻለ ህይወትና ጊዜዉን ጉልበቱን እዉቀቱን ገንዘቡን  ንብረቱንና ክቡር ህይወቱን መስዋትነት ለመክፈል የተዘጋጀ ሰዉ ወይም የህብረተስብ ክፍል ማለት ነዉ።

ከዚህም በመነሳት ዛሬ ላይ እየተካሄደ ባለዉ የአርበኝነት ትግል አላማችን እንዲሳካ እራአያችን እንድያብብ የምንሻ ሁሉ የግድ ያለዉን ነባራዊ ሁኔታ ማጤንና መገንዘብ ያስፈልጋል።  የአርበኝነት አላማ ደግሞ ዉጤታማ የሚሆነዉ በእቅድ የሚመራ በተግባር የሚታይና በድርጊት የሚገለጽ  የጥርት ዉጤት ሲሆን ነዉ።
በመሆኑም ድሮ አርበኛ አባቶቻችን በአዋጅ ተሰባስበዉ በራሶችና በደጃዝማቾች የጦር አጋፋሬዎች እየተመሩ ለሃገራቸዉ በነበራችዉ ጥልቅ የሃገራዊ የፍቅር ስሜት አርበኝነትን ተላብስዉ በባዶ እግራቸዉ ወንዝና ሽነተረሩን አቋርጠዉ ዳገት ቁልቁልቱን ወጥተዉ ወርደዉ ከጦርነቱ አዉድማ ሲደርሱ ነጋሪት እየተጎሰመ እንቢልታዉ እየተንፋ ንጉስ ከፈረስ ሳይወርዱ በጦርነተ መሃል ዉስጥ ሆነዉ አዋጅ እያስነገሩ የፊዉታራሬ ጦር ግባ ተብለሃል፥ የቀኝ አዝማች ጦር ግባ ተብለሃል፥የግራዝማች ጦር ግባ ተብለሃል በሚል የአዉደ ዉጊያ የእዝ ሰንሰለት ጊዜዉ በፈቀደዉ የጦርነት ስልት ነበር  በጦር በጎራዴ ተዋግተዉ ደማቸዉን አፍሰዉ ሃገራችን ኢትዮጵያን ከወራሪ  ቅኝ ገዥዎች ያዳኗት።
ዛሬ ላይ ደግሞ ሃገር በቀል ወራሬ የወያኔን ቡድን ለማስወገድ የአርበኞች ግንቦት 7 አርበኛ ታጋዮች በሁለገብ የትግል ስልት ከገጠር እስከ ከተማ ሁሉንም የሃገራችነን ክፍል ባከለለ የህዝባዊ እንቢተኝነትና የህዝባዊ አመጽ እንዲጎለብት በማድረግ በቁርጠኝነት በምታገል ላይ ናቸዉ።
እንድሁም አርበኛ ታጋዮቻችን ከነጻነት ሃይሎችና ከህዝቡ ጋር በመሆን የሽምቅ ዉጊያ በማካሄድ ትግሉ ወደ ላቀ ደረጃ እንድሸጋገር ከፍተኛ ተጋድሎ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
ስለሆነም የአርበኞች ግንቦት 7 አርበኛ ታጋዮች እንዳ አባቶቻችን የአርበኝነትን  መንፈስ ተላብሰዉ መስዋእትነት በመክፈል ደማችዉን አፍሰዋል።
በአሁኑ ስአትም ደም ገብረዉ ሃገራችንን ከጥፋት ለመታደግ የቆረጡ የህዝብ ልጆች ከአገዛዙ ታጣቂ ሃይሎች ጋር እየተፋለሙ ናቸዉ።
በሌላ በኩል ግን ወያኔን ለማስወገድ ራሱ ወያኔ በመጣበት የትግል ስልት እና ኢህአፓና ኢድዩ የትጓዙበትን የትግል መንገድ የተከተለ አይደለም ምክኔያቱም ዘመኑ ያለፈበት የትግል መንገድ በመሆኑ።
ወይም እንዳባቶቻችን የደጃዝማች ጦር በቀኝ በኩል ግባ ተብለሃል የፊዉታራሪ ጦር በግራ በኩል ግባ ተብለሃል በሚል በአዋጅ የሚደረግ ጦርነት አይደለም ዘመኑ የቴክኖሎጅ ዘመን ነዉ።ስለዚህ አሁን ያለዉ የአርበኝነት ትግል የወቅቱን ነባራዊ ሁኔታን ባገገናዘበ በስልትና ሚስጥር በመጠበቅ የሚደረግ የአርበኝነት ትግል ነዉ ።
ይህን ተከትሎ በትጨባጭ የአርበኞች ግንቦት 7 አርበኛ ታጋዮች በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አንድነትን ለማምጣትና ዴሞክራሲን ለማስፈን ለሃገራችን ኢትዮጽያ በጎ ራእይን በመሰነቅ  የወያኔን አገዛዝ ለማስወገድ በሁሉም መስክ ትግሉን እያቀጣጠሉ ይገኛሉ።
 ነገር ግን አንዳድ ወገኖች ከራሳቸዉ የግል ጥቅም በመነሳት እና አሁን ያለዉን ነባራዊ ሁኔታ በጥልቀት ባለመረዳት እንድሁም በግንዛቤ እጥረት አራንባና ቆቦ በሆነ አስተሳሰብበ በአዉሮፓና  በአሜሪካ  ካለ የፕረስ ነጻነት ጋር በማመሳሰል እቅዳችን ይሕ ነዉ፥አሁን እንደዚህ እየሰራን ነዉ ፥ወደፊት እንደዚያ ልናደርግ ነዉ የሚል ሪፖርት ወይም ጋዜጣዊ መግለጫ እንድሰጥ የሚፈልጉ የመኖራቸዉን ያክል፥ በሌላ በኩል ደግሞ የሽምቅ ዉጊያ ሚስጥራዊነቱ ተጠብቆ የሚከናወን በመሆኑ አንዳድ ብሄር ተኮር ፖለቲከኞች ለራሳቸዉ የፖለቲካ ስካራ ለግባትነት ለመጠቀም በማሰብ ሆን ብለዉ በተግባር እየተከናወነ ያለዉን ስራ ትቢያ እያለበሱ  ምንም ስራ እንዳልተሰራ በደካማ ጎን በመፈረጅ የወሬ ቋታቸዉን ሲያራግቡ ይስተዋላሉ።
 በጥቅሉ  እነዚህ ግለሰቦች አብሮ ከመታገልና የስናፍጭ ቅንጣት ታክል ለትግሉ አስተዋጽኦ ከማድረግ ይልቅ ችግሮችን እየፈለጉ በስራ ላይ የሚከሰቱትን ጥቃቅን ስህተቶችን ነቅሶ በማወጣት የሚያናፍሱት ወሪ የአርበኝነት ትግሉን ወደኋላ   የሚጎትት እና የወያኔን የአገዛዝ እድሜ ሊያራዝም በሚያስችል በተሳሳተ መንገድ እየተጓዙ መሆናቸዉ ግልጽ ሆኖ እየታየ ነዉ።
ሃግርን ለምዳን በሚደረገዉ የሞት ሽረት ትግል ዉስጥ ሚና በሌለዉ ለግል ጥቅም አንጋጦ በወሬ ብቻ እራስን ከፍ አድርጎ እንደ ታጋይ በመቁጠር የሚመጣ ለዉጥ የለም ከገደል ማሚቶነት ማስተጋባት የዘለለ ሊሆን የሚችል አይደለም ።
በአንጻሩ ግን ለፖለቲካ ግባትነት ያገለግላል ከሚል መነሻነት አማራ ኦሮሞ በማለት ልዩነትን በማስፋት ትርፍን አስቦ የግል ፍላጎትን ለማሟላት የሚደርግ ሩጫ የወያኔን እድሜ ከማራዘሙም በላይ በህብረተሰቡ መካከል ቅራኒን አስፍቶ ዘመን የማይሽረዉን ጠባሳ ይተክላል ።ስለሆነም በህዝብ ደም ለመነገድ ማሰቡ ሊቆም ይገባዋል። 
የዚህ አይነት አመለካከት ያላቸዉ ግለሰቦች ሊያዉቁት የሚገባዉ መሬት ላይ ያለዉ እዉነታ በርበኞች ግንቦት7 ድርጅት ጥላ ስር የትሰባሰቡ በሃገር ዉስጥም በዉጭም ያሉ አርበኛ ታጋዮች በእንቅስቃሴአቸዉ በተግባር እያከናወኑት ያለዉ የአርበኝነት ትግል አንዱን አገዛዝ አስወግዶ ሌላዉን አገዛዝ ለመተካት አይደለም  ምክኒያቱም በትግሉ ሂደት ዉስጥ ሁሉንም እይነት ፈተና በመቀበልና መስዋእትነት እየተከፈለ ያለዉ ሃግራችን ኢትዮጽያ ከገባችበት የአሮንቃ ማጥ ዉስጥ ለማዉጣት ሲባል ብቻና ብቻ ነዉ።
ስለሆነም ክቡር ህይወትን ከመገበር በላይ ሌላ ምስክርነት የሚስፈልገዉ አይደለም ።
ይልቁንም እንደኔ እምነት የሚሻለዉ መንገድ ሁላችንም ግለሰባዊ ጥቅምን ወደ ጎን በመተዉ እንደ ሃገር በጅምላ የደረሰብንን መከራና ስቃይ ዋየታና እሮሮ ለማስቆም በአንድነት ላይ ቁመን በጋራ ተባብረን በአርበኝነት በመታገል ወራሪ የህዉሃትን ቡድን ለማስወገድ ቅድሚያ ልንሰጠዉ የሚገባ ተግባር ሊሆን ይገባዋል።

ባንዳነት ጌጥ የሆነላቸው (መስቀሉ አየለ)

ባንዳነት ጌጥ የሆነላቸው (መስቀሉ አየለ)
መስቀሉ አየለ
ቡልጋሪያ የምትባል የምስራቅ አውሮፓ ክፍል አለች። ለአራት መቶ አመት ያህል በቱርክ የእሳት ሰንሰለት ተጠፍንጋ የኖረች አገር ናት። የኦቶማን ቱርክን ጦር ቀጥቅጦ ወደ መቃብር የገፋላት የሩሲያ ጦር ነበር። ቡልጋዎች ይህን የነጻነት ቀን በያመቱ ሲያከብሩ የክብር እንግዳው የሚመጣው ከሩሲያ ነበር። ባለፈው አመት ግን ይኽ አልሆነም። በሶፊያ፣ ቡልጋሪያ የሚገኘው የ አሜሪካን አምባሳደር ተቆጣ አሉ፤ ተቆጥቶም አልቀረም ይልቁንም የክብር እንግዳው ከቱርክ መሆን አለበት ብሎ ቀጭን ትእዛዛ ያስተላለፈው ለአገሪቱ ፕሬዝዳንት ነበር።በጌታና የሎሌ ግንኙነት ወቅት ፕሮቶኮል ትርጉም የለውም።Unpatriotic act
የናዚ ጀርመን ጦር አውሮፓን እንዳይወር በወቅቱ የነበሩት መራሄ መንግስትታ ለሂትለር እጅ መንሻ የመስዋእት ጠቦት አድርገው የሰጡት ፖላንድን ነበር። ክፋቱ ሂትለር እርሷን በልቶ አለማቆሙ ነው እንጂ። ፖላንድን ከናዚ ጦር ነጻ ለማውጣት ስድስት መቶ አምሳ ሺህ የሩሲያ ጦር ነበር ያለቀው። በታሪኩ አሰቃቂ በተባለለት አስቸጋሪ የበረዶ ላይ ከበባ ዋጋ ለከፈሉትና ድፍን አውሮፓን ከናዚዝምና ከፋሽዝም ለታደጉት የሩሲያ ወታደሮች መታሰቢያ በፖላንድ ዋርሳው የቆሙትን ሃውልቶች ዛሬ ከአሜሪካ በላይ አሜሪካዊነት በሚሰማቸው የፖላንድ መሪዎች መፈራረስ በመጀመራቸው የሩሲያ መንግስት የወታደሮቹን አጽም በክብር ወደ አገሩ መልሶ ለማሳረፍ ቃል ገብቷል።ዛሬ ፖላንድ ማለት በምስራቅ አውሮፓ ውስጥ ያለች አንዱዋ የአሜሪካን ላፕዶግ መሆኗን በብዙ አጋጣሚ እያስመሰከረች ያለችበት ሁኔታ ነው ያለው።

በኛም አገር ለአገራቸው በጎ የዋሉ፤ ለማንነታቸው ዋጋ የሰጡና እራሳቸውን የተቀደሰ መስዋእት አድርገው ህዝባቸውን የታደጉ አባቶቻችን አጽመ እርስታቸው የሚያርፈው አዲስ አበባ በሚገኘው ዮሴፍ ቤተክርስቲያን እንደነበረ ይታወቃል። አርከበ እቁባይ የተባለ የባንዳ ልጅ የመናገሻውን ቢሮ በያዘ ሰሞን “የኒህን የነፍጠኞች ምናምንቴ አውጥተኽ ጣልልኝ!” ብሎ ባዘዘው መሰረት የዚያ ሁሉ የአርበኛ አጽም ነበር ድፍን አዲሳቤ በኣይኑ ብረት ቆሞ እያየ በቡልዶዘር ተጠራርጎ የፈረሰው። ከላይ በሌሎች አገሮች ተሞክሮ እንዳየነው ባንዳ ሁሉ ስነ ባህሪያቸው አንድ ነው። ሰሞኑንም የፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ፣ መልአከ ብርሃናት አድማሱ ጀንበሬና ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤን አጽም አንሡ መባላችን ያው ከላይ በፖላንድ ካየነው እውነት ልዩነት የለውም። እንዲህ በማንነቱ የሚሸማቀቅ፣ የገዛ ታሪኩን የሚያዋርድና ገንዘብ ባየበት ሁሉ እንደ ሴተኛ አዳሪ የሚገለፍጥ የወያኔ አይነት ባህሪ ለምን የምእራባውያንን ልቦና እንደሚያማልል ግልጽ ነው። ዘመኑ የባንዳ ነው።

Sonntag, 2. Juli 2017

የአዲስ አበባ ከተማን ህዝብ ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብት የሚጥስ አዋጅ አጥብቀን እንቃወማለን!!! (ከሰማያዊ ፓርቲ ብሔራዊ ሸንጎ የተሰጠ መግለጫ)

የአዲስ አበባ ከተማን ህዝብ ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብት የሚጥስ አዋጅ አጥብቀን እንቃወማለን!!!

    ከሰማያዊ ፓርቲ ብሔራዊ ሸንጎ የተሰጠ መግለጫ
ህወሀት/ኢህአዴግ በ100 ፐርሰንት አሸንፊያለሁ ብሎ ባወጀ ማግስት በመላ ሀገራችን በሁሉም አቅጣጫ እንደየአካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ የነፃነት፣ የእኩልነትና የዴሞክራሲ ጥያቄን በማንገብ የኢትዮጵያ ህዝብ የህይወት መስዋዕትነት እየከፈለ ነው፡፡አገዛዙ ይህንን መሰረታዊ የለውጥ ጥያቄ ለማዳፈን ሲል ለማመን በሚከብድ ሁኔታ አስተዳድረዋለሁ በሚለው ህዝብ ላይ ግድያ፣ የጅምላ እስር እና ማፈናቀል ዋነኛ ተግባሩ አድርጎታል፡፡ በዚህ የአገዛዙ ኢ-ሰብዓዊ እርምጃም ቢሆን የኢትዮጵያን ህዝብ የለውጥ ጥያቄ ማስቆም ባለመቻሉ በድንጋጤና ባልታሰበበት ሁኔታ የኢትዮጵያን ህዝብ ለመከፋፈል እና በጥርጣሬ እንዲተያይ ለማድረግ አዲስ ረቂቅ አዋጅ ይዞ ብቅ ብሏል፡፡
ይህ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ተረቀቀ የተባለው አዋጅ በጥድፊያ የወጣ፣ግልፅነት የጎደለው፣ህገ መንግስቱን የጣሰ፣በመረጃና በጥናት ላይ ያልተመረኮዘ፣አጠቃላይ የዴሞክሰራሲ መርሆና ከህገ መንግስቱ አንቀፅ 49 አላማ ጋር በእጅጉ የተቃረነና ህዝብን ከህዝብ በማጋጨት አገዛዙ የተነሳበትን የፖለቲካ ትኩሳት ለማብረድ በማሰብ የተቀነባበረ ግልብ ሴራ ነው፡፡
አገዛዙ በተቆጣጠራቸው መገናኛ ብዙሃን እንደተገለፀው በዚህ አዋጅ የማርቀቅ ሂደት ላይ የተሳተፉት አካለት የኦሮሚያ ክልል መንግስት፣ኦህዴድ፣የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች እንደሆኑ ተገልፅዋል፡፡ይህ ከሆነ ደግሞ አዲስ አበባን ከሚያስተዳድሩትም ሆነ በፌደራል ፓርላማ 100 ፐርሰንት አሸንፊያለሁ ያለው ኢህአዴግና አጋሮቹ ውስጥ እንደ ድርጅት ኦህዴድ ብቻ መሳተፉና ሌሎች ማለትም ብአዴን፣ደህዴንና ህወሃት እንዳይሳተፉ መደረጋቸው በድርጅቱም ውስጥ ታስቦበትና ሙሉ ስምምነት ተደርሶበት የተዘጋጀ ረቂቅ አለመሆኑን እና ተራ የፖለቲካ ሸቀጥ መሆኑን ግልፅ ማሳያ ነው፡፡በዚሁ መግለጫ ላይ አንደተገለፀው በአዲስ አበባ ማስተር ፕላን መስፋፋት ለተፈናቀሉና ወደፊትም ለሚፈናቀሉ ሰዎች ካሳ የሚከፈለው ለኦሮሞ ብሄር ተወላጅ አርሶ አደሮች እንደሆነ ተገልጧል፡፡ይህም ማለት በዚህ አዋጅ መሰረት በአዲስ አበባ ማስተር ፕላን መስፋፋት ምክንያት ለሚፈናቀሉ ኦሮሞ ያልሆኑ ኢትዮጵያውያን አርሶ አደሮች ካሳ የማግኘት መብት የላቸውም ማለት ነው፡፡ ይህ አገላለፅ የዜጎችን ተዘዋውሮ የመስራትና ሀብት የማፍራት ህገ መንግስታዊ መብት የሚነጥቅ በመሆኑ ረቂቅ አዋጁ ተቀባይነት የለውም፡፡
የህገ መንግስቱ አንቀፅ 49/5 ዓላማ የአገልግሎት አቅርቦትን፣የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምናን እና የጋራ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን አፈፃፀም የተመለከተ ሲሆን ይህ ተረቀቀ የተባለው አዋጅ ግን ከዚህ አንቀፅ በተቃራኒው ተለጥጦ የአዲስ አበባን ህዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር ህገ መንግስታዊ መብት በመንጠቅ ኦሮሞነትን በላዩ ላይ በመጫንና ተገዶ እንዲቀበል በማድረግ ኦሮሞ ያልሆነው የአዲስ አበባ ህዝብ በገዛ ሀገሩ ባይታወርነት እና እንግድነት እንዲሰማው የሚያደርግ ጨቋኝ አዋጅ ነው፡፡
በዚህ ተረቀቀ በተባለው አዋጅ በአዲስ አበባ የሚኖሩ የኦሮሚያ ክልል መንግስት ሰራተኞች ተመዝግበው ቤት የማግኘት መብት እንዲከበርላቸው ይደነግጋል፡፡ በመሰረቱ የኦሮሚያ ከልላዊ መንግስት ዋና ከተማ አዳማ መሆኗን በ1994 ዓ.ም የተሸሻለው የክልሉ ህገ መንግስት አንቀፅ 6 ይደነግጋል፡፡ይህ ሆኖ እያለ ህወሃት/ ኢህአዴግ በ1997 ዓ.ም በተካሄደው ምርጫ አዲስ አበባ ከተማ ላይ በደረሰበት አስደንጋጭ ሽንፈት ምክንያት የወቅቱ የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ መለስ ዜናዊ በምርጫው ማግስት የኦሮሚያ ክልልን ህገ መንግስት በመጣስ በፖለቲካ ውሳኔ የአዳማ ከተማ የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማነት መብትን በመንጠቅና ወደ ህዝብ የመቅረብ መሰረታዊ የፌደራሊዝም ፅንሰ ሃሳብ በመጣስ ወደ አዲስ አበባ እንዲዛወር አድርገዋል፡፡ይህ ውሳኔ የክልሉን ህገ መንግስት ያላከበረ ስለሆነ ሊፀድቅም ሊፈፀምም አይገባም፡፡
በፌደራሉ ህገ መንግስት መሰረት 9 ክልሎችና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች እንዳሉ ሲታወቅ አዲስ አበባ በዚህ ህገ መንግስት በአንቀፅ 49/2  መሰረት ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብትና የራሱን የስራ ቋንቋ የመወሰን መብቱ የአዲስ አበባ ህዝብ እና የሚወክላቸው አካላት ብቻ መሆኑ በግልፅ ተደንግጓል፡፡ይህንን ህገ መንግስታዊ መብት በመጣስ የአዲስ አበባ አስተዳድርን የስራ ቋንቋ የሚወስን አዋጅ በፌደራል መንግስት ማውጣት በራሱ በህገ መንግሰቱ አንቀፅ 9 መሰረት ተቀባይነት የለውም፡፡ከዚህም በተጨማሪ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኦሮሞኛን የስራ ቋንቋ ማድረግ አዲስ አበባ ተወልደው ያደጉ ኦሮሞ ያልሆኑ ኢትዮጵያውያንን ከስራ እድል በማግለል ኦሮሞ ለሆኑ ኢትዮጵያውያን ቅድሚያ ለመስጠት በማስመሰል በዜጎች መካከል አላስፈላጊ የጥቅም ግጭት እንዲፈጠር የሚያደርግና በህዝብ መካከል ያለውን መስተጋብር የሚንድ መርዘኛ አዋጅ በመሆኑ በፍፁም ተቀባይነት የለውም፡፡    
ከላይ በገለፅናቸው ማሳያ ነጥቦች መሰረት ይህ ተረቀቀ የተባለው አዋጅ የህግም ሆነ የሞራል መሰረት የሌለው ስለሆነ በአስቸኳይ አንዲቆምና የኦሮሚያ ክልል መንግስትም የአዳማን የክልል ርዕሰ ከተማነት ህገ መንግስታዊ መብትን በማክበር አሰተዳደሩን ወደ አዳማ እንዲያዛውርና የአዳማ ከተማ በክልሉ ህገ መንግስት የተሰጠውን የክልል ከተማነት መብት ተከብሮ ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚገኙ የኢኮኖሚ፣የፖለቲካ እና የማህበራዊ እድገት ተፈፃሚ እንዲሆን በአፅንዖት እንጠይቃለን፡፡በመጨረሻም ረቂቅ አዋጁ ህወሀት/ኢህአዴግ የኢትዮጵያን መሰረታዊ የህዝብ ጥያዌ ለመመለስ አቅምም ሆነ ፍላጎት እንደሌለው በግልፅ የሚያሳይ ከመሆኑም ባሻገር ለስልጣኔ ይጠቅመኛል  ያለውን ሁሉ በህዝብ ላይ ከመፈም ወደኋል እንደማይል ከድርጊቱ ተገንዝበናል፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይም የአዲስ አበባ ህዝብ ይህንን ተረቀቀ የተባለውን ከፋፋይና መርዘኛ ረቂቅ አዋጅ ውድቅ እንዲሆን ጥቃቅን ልዩነቶችን በማሶገድ መሰረታዊ ለሆነው ለኢትዮጵያ ህዝብ ነፃነት፣እኩልነትና ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር አውን መሆን ላይ በማተኮር በአንድነት ትግሉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
 
                                ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!
                                ሰኔ 25 ቀን 2009 ዓ.ም