Netsanet: Februar 2017

Dienstag, 28. Februar 2017

​ታላቁ ጃጋማ ኬሎ—ጸረ ፋሽስቱ የኢትዮጵያ ጀግኖች ምልክትከአቻምየለህ ታምሩ

​ታላቁ ጃጋማ ኬሎ—ጸረ ፋሽስቱ የኢትዮጵያ ጀግኖች ምልክት
ከአቻምየለህ ታምሩ
ጀግናው ሌፍተናት ጄኔራል ጃገማ ኬሎ ጥር 21 ቀን 1913 ዓ.ም. በጅባትና ሜጫ አውራጃ በደንቢ ዮብዲ ወረዳ ዮብዶ በሚባል ቦታ ተወለዱ። ለቤተሰባቸው የመጨረሻ ልጅ ቢሆኑም ከሁሉም ጎበዝና ብርቱ ነበሩና አባታቸው የቤተሰቡ አለቃ አደረጓቸው። ስማቸውንም ያገኙት ብርቱ መሆናቸውን አባታቸው በማወቃቸው ገና ሳይወለዱ ለወላጅ እናታቸው ‹‹ጥር 21 ቀን ትወልጃለሽ ስሙንም ጃጋማ ብየዋለሁ›› በማለት ነበር ጃገማ የሚለውን መጠሪያ የሰጧቸው። “ጃገማ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል የአባታቸው የፈረስ ስም ሲሆን፤ የአማርኛ ፍቺው ሀይለኛ ማለት ነው። ሌፍተናት ጄኔራል ጃገማ እሲኪወለዱ ድረስ የፈረሳቸውን ስም የሚሰጡት ሁነኛ ልጅ ያላገኙት አባታቸው፤ በልጃቸው በጃገማ ይኮሩ ነበር።
ጀግናው የኦሮሞ ልጅ ሌፍተናት ጄኔራል ጃገማ ኬሎ ለአገራቸው ነጻነት ሲሉ ከፋሽስት ጥሊያን ጋር ሲፋለሙ የደሙ፣ ዳር ድንበር ለማስከበር የወደቁ፣ ሕይወታቸውን ሙሉ ለወገናቸው ክብር የገበሩና የቆሰሉ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ ናቸው።
ፋሽሽት ጣሊያን ኢትዮጵያን በግፍ በወረረበት ዘመን ጀነራል ጀጋማ በ15 ዓመታቸው ሸፈቱ ። በአፍላው የወጣትነት ጊዜያቸው የ3500 አርበኞች አለቃ ነበሩ ። በምዕራብ ሸዋ የነበረውን የፋሽስት ጦር ሰቅዘው የያዙት ጀግናው ጃጋማ ኬሎ፤ አምስት አመት ሙሉ በጀግንነት ሲጋደሉ ከማሸነፍ በቀር አንዴም ቢሆን ተማርከውም ሆነ ተሸንፈው አያውቁም ነበር። በተለያዩ የጦር ውሎዎች ላይ ባደረጉት ተጋድሎ በጠላት ላይ ከፍተኛ ጀብዱን ከመቀዳጀት ባሻገር፤ በርካታ የጥሊያን የጦር አዝማቾችን ማርከው ለጨካኝ ፋሽስቶች የኢትዮጵያውያንን ርህራሔ አሳይተዋል። የማረኳቸውን በርካታ የጥሊያን ጀኔራሎችም ለእንግሊዝ አስረክበዋል።
ሌፍተናት ጄኔራል ጃገማ ኬሎ ከሸዋ እስከ ጅማ በመዝመት « ጃጋማን ጥሩት» እየተባሉ በርካታ አስቸጋሪ የፋሽስት ምሽጎችን ሰብረዋል። ከነደጃዝማች ገረሱ ዱኪ፣ ወይዘሮ ሸዋረገድ ገድሌ ጋር በመሆን የኢትዮጵያ አርበኞች እስከ መጨረሻው በመምራት ጥሊያንን ቁም ቁምጥ ነስተው ከኢትዮጵያ ምድር ጠራርገው አስወጥተውታል። ከዚህም ባሻገር ሶማሊያ ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት የኢትዮጵያን ዳር ድንበር በማስጠበቅ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ወደር የማይገኝላቸው የአገር ባለውለታ ናቸው። ሌፍተናት ጄኔራል ጃገማ ኬሎ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግስት የስምንቱ ጠቅላይ ግዛቶች የሰራዊት ኃላፊም ነበሩ።
የጀግኖቿን ውለታ ቅርጥፍ አድርጋ የምትበላ አገር ሆና ነው እንጅ፤ታላቁ ጀኔራል ጃጋማ ኬሎ ከነ ዊንተን ቸርችል እና ቻርለስ ደጎል እኩል ሃውልት የሚቆምላቸው የአፍሪካ ጸረ ፋሽስት የሁለተኛው የአለም ጦርነት ጀግና ነበሩ።
የበጋው መብረቅ በሚል የሚታወቁት መልከ መልካሙ ሌፍተናት ጄኔራል ጃገማ ኬሎ ዛሬ የ95 ዓመቱ እድሜ ባለፀጋ ናቸው። እኒህ አርበኛ ከአውሮፕላን ሳይቀር ወድቀው ከሞት ጋር ተጋፍተው ለታምር የተረፉ፤ ሆለታ የጦር ትምህርት ቤትና አሜሪካን አገር ድረስ ተጉዘው ዘመናዊ የጦር ትምህርት የተማሩና በሺዎች የሚቆጠሩ ያገራቸውን ልጆች ያስተማሩ አገር ወዳጅ ጀግና ናቸው።
ስመጥሩ ጀግና ጄኔራል ጃጋማ ኬሎ ስለአገራቸው ምን እንደሚያስቡ በአንድ ወቅት ተጠይቀው፤ የቀኝ ጌታ ዮፍታሔን ግጥም በማውሳት. . .
አገሬ ኢትዮጵያ ውዲቱ ውዲቱ፣
በሶስቱ ቀለማት የተሸለምሽቱ፣
ላንቺ የማይረዳ ካለ በህይወቱ፣
በረከትሽን ይንሳው እስከ እለተ ሞቱ። ነበር ያሉት።
ከሸዋ እስከ ጅማ ዘምተው በማረኩትና ባሸነፉት ጥሊያን ልክ፤ምሽግና የመሳሪያ ግምጃ ቤት ሰብረው ተከታዮቻቸውን ባስታጥቁት ቁጥር እንዲህ ተብሎ ይገጠምላቸው ነበር. . .
ገዳይ በልጅነቱ፣
ዶቃ ሳይወጣ ባንገቱ፤
ጃጌ ጃጋማቸው፣
እንደገጠመ የሚፈጃቸው፤
አባት እናቱ ከኦሮሞ፣
ግዳዩን አስቆጠረ ከምሮ ከምሮ፤
ጄኔራል ጃጋማ ኬሎ የማረኩትን ነጭ የጥሊያን ወታደር መቶ ብር ሸጠዋል። ከእሳቸው መቶ ብር የገዛው ደግሞ ጥሊያኑን 5000 ብር ሽጦታል። ጄኔራል ጃጋማ ፈረንጅ ወይንም ነጭ የሸጡ ብቸኛው ጥቁር አፍሪካዊ ጀግና ይመስሉኛል።
ጄኔራል ጃጋማ ኬሎ የሚያህል ወደር የለሽ ኢትዮጵያዊ አርበኛ የከሀዲ ጥርቅም ሁሉ ሊያሳንሳቸው ቢሞክሩም ታሪክና ትውልድ ግን ውለታቸውን ሲዘክር ዝንታለም ይኖራል። ክብር ለአገራዊ ቅርሳችን ለጀግናው ሌፍተናት ጄኔራል ጃገማ ኬሎ!http://wp.me/p5L3EG-fd

Sonntag, 26. Februar 2017

ዶ/ር መረራ የኦሮሚያን ብጥብጥ በማባባስና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመጣስ ክስ ተመሠረተባቸው


  • በክሱ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋና አቶ ጀዋር መሐመድ ተካተዋል
የአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ ባደረገላቸው ጥሪ ቤልጂየም ብራሰልስ ደርሰው ሲመለሱ  ከመስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ የሆነውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በመጣስ ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙት ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረውን ብጥብጥና ሁከት ሲያባብሱ እንደነበር የሚገልጽ ክስ ሐሙስ የካቲት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. እንደ ተመሠረተባቸው ሪፖርተር ዘግቧል፡፡
የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1ሀናለ)፣ 38(1)ን፣ 27(1)ን እና አንቀጽ 238 (1 እና 2)ን ተላልፈዋል ተብለው የመጀመሪያ ክስ የተመሠረተባቸው ዶ/ር መረራ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋና አቶ ጀዋር መሐመድ ናቸው፡፡ በፌዴራልና በክልል ሕገ መንግሥት የተቋቋመን ሥርዓት በሕገወጥ መንገድ ለማፍረስ መንቀሳቀሳቸውን፣ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የመሠረተው ክስ ያስረዳል፡፡
የፖለቲካ፣ የሃይማኖት ወይም የአይዲዮሎጂ ዓላማን ለማራመድ፣ በመንግሥት ላይ ጫና ለመፍጠርና ኅብረተሰቡን ለማስፈራራት፣ ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ የሁከትና የብጥብጥ ጥሪ በማስተላለፍ በአንዳንድ የአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ኅብረተሰቡ ወደ ሁከትና ብጥብጥ እንዲገባ ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ባቀረበው ክስ ገልጿል ሲል ፡፡ዓቃቤ ሕግ በክሱ እንዳብራራው ዶ/ር መረራ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አመራርነትን እንደ ሽፋን ተጠቅመው፣ የአዲስ አበባ ከተማና የፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን የጋራ ማስተር ፕላን ተቃውሞን እንደ መነሻ በማድረግ ሁከትና ብጥብጥ በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች እንዲቀጥል አድርገዋል፡፡
በ2006 ዓ.ም. ለኦፌኮ አባላት የሥራ ክፍፍል በማድረግ በመንግሥትና በሕዝብ ተቋማት መንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት ላይ የንብረት ውድመት እንዲደርስ ማድረጋቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡ በኢንቨስትመንት ላይ በተሰማሩ ባለሀብቶች ንብረቶች ላይም ውድመት መድረሱንም አክሏል፡፡ በሰውም ላይ ከባድ የአካል መጉደልና ሞት መከሰቱንም ጠቁሟል፡፡
ዶ/ር መረራ በ2008 ዓ.ም. በአንዳንድ የኦሮሚያ ከተሞች በተለይም በምዕራብ ሸዋ ዞን አምቦ አካባቢ የሚገኙ ፕሮጀክቶችን ማለትም የአምቦ-ካራ የመንገድ ግንባታን በመቆራረጥ፣ ካምፕ በማቃጠል፣ በተሽከርካሪዎችና በማሽነሪዎች ላይ የ2,957,661 ብር ንብረት እንዲወድም ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡
በቡራዩ ከተማም በ42,598,204 ብር ንብረቶች ላይ ጉዳትና ውድመት ማድረሳቸውንም አክሏል፡፡ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ወሊሶ፣ አመያ፣ ጎሮ፣ ቶሌ፣ ኢሉ፣ ቀርሳ፣ ወንጪ ወረዳዎችና ቀበሌ መስተዳድር የግለሰቦች መኖሪያ ቤቶችንና በኢንቨስትመንት የተሰማሩ ኢንቨስተሮችን የተለያዩ ንብረቶች ጉዳት በማድረስና በማውደም የ17,352,482 ብር ጉዳት እንዲደርስ ምክንያት መሆናቸውንም ክሱ ያብራራል፡፡
ሐምሌ 28 ቀን 2008 ዓ.ም. በኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ (OMN) ዶ/ር መረራ ባስተላለፉት የሁከት ጥሪ ሐምሌ 30 ቀን 2008 ዓ.ም. በመላ ኦሮሚያ ሕዝባዊ ተቃውሞ ለማካሄድ መታሰቡን በመግለጽና የሁከቱ ተካፋዮች እንዲሳተፉ ጥሪ ማቅረባቸውንም ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡
ዶ/ር መረራ ለዚሁ መገናኛ ብዙኃን መስከረም 24 ቀን 2009 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ኢሬቻ በዓል ላይ የተከሰተውን አደጋ አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፣ የመንግሥት ታጣቂዎች በኦሮሚያ ሕዝብ ላይ በወሰዱት ግድያ 678 ሰዎችን እንደተገደሉ በመግለጽ ባስተላለፉት ጥሪ በክልሉ አንዳንድ ከተሞች ሁከትና ብጥብጡ እንዲቀጥል ማድረጋቸውን ክሱ ያብራራል፡፡
በተነሳውም ብጥብጥና ሁከት የሰላማዊ ሰዎች ሕይወት መጥፋቱን፣ ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን በመንግሥትና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ላይ፣ እንዲሁም በኢንቨስትመንት ላይ በተሰማሩ ባለሀብቶች ንብረቶች ላይ ጥቃት እንዲደርስና እንዲወድሙ ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡
በኦሮሚያ ክልል በኢሉአባቦራ፣ በምዕራብ ሸዋ፣ በምሥራቅ ሸዋ፣ በባሌ፣ በሰበታ ከተማ፣ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ፣ በአርሲ፣ በምዕራብ አርሲ ዞን በመንግሥት ንብረት ላይ የ215,468,309 ብር ውድመት እንዲደርስ ማድረጋቸውንም ገልጿል፡፡ ዶ/ር መረራ መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት ንብረት ላይ የ1,168,293,498 ብር ንብረት እንዲወድም ምክንያት መሆናቸውንም በክሱ አብራርቷል፡፡
ሌላው ዶ/ር መረራ በቁጥጥር ሥር ውለው የታሰሩበት ምክንያት መስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም. የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በመጣስ ተብለው ነው፡፡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት ከተፈረጀው የአርበኞች ግንቦት ሰባት ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ጋር በብራሰልስ በመገናኘታቸው ዓቃቤ ሕግ ክስ መሥርቶባቸዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ አዋጁን ለማስፈጸም በወጣው መመርያ በሽብርተኝነት ከተፈረጁ ድርጅቶች ጋር መገናኘት የተከለከለ መሆኑ ተገልጾ እያለ፣ ዶ/ር መረራ መመርያውን ጥሰው በመገናኘታቸውና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 01/2009 አንቀጽ 12(1)ን በመተላለፋቸው መሆኑን ክሱ ያብራራል፡፡
ዶ/ር መረራ ኅዳር 2 ቀን 2009 ዓ.ም. ከፕሮፌሰር ብርሃኑ ጋር በብራሰልስ የኦኤምኤን ሠራተኞችና የኦነግ አባላትና ደጋፊዎች ባዘጋጁት የስብሰባ መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች ስለነበረው ሁከትና ብጥብጥ በመግለጻቸው፣ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር የተያያዙ ግዴታዎችን የመተላለፍ ወንጀል በመፈጸም ክስ ዓቃቤ ሕግ አቅርቦባቸዋል፡፡
ዶ/ር መረራ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 486(ለ)ን በመተላለፍ በ2006 ዓ.ም የኢትዮጵያና ናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድኖች በአዲስ አበባ ስታዲየም በሚያደርጉት ጨዋታ የአልሸባብ አባላት የአጥፍቶ ማጥፋት ወንጀል ለመፈጸም ባለመቻላቸውና የታጠቁት ፈንጂ ፈንድቶ መሞታቸው እየታወቀ እሳቸው ግን ‹‹አሸባሪዎቹ አፈነዱ የተባለው የውሸትና የመንግሥት ድራማ ነው›› በማለት ሕዝቡ በመንግሥት ላይ እምነት እንዳይኖረው አድርገዋል ሲል ዓቃቤ ሕግ የሐሰት ወሬዎችን የማውራት ወንጀል ክስ መሥርቶባቸዋል፡፡
ከዶ/ር መረራ ጋር በአንደኛ ክስ ተካተው ክስ የተመሠረተባቸው ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋና አቶ ጀዋር መሐመድ ናቸው፡፡ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በህቡዕ አባላትን በመመልመል እንዲንቀሳቀሱ በማድረግ ሁከቱ እንዲቀጥል በኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን (ኢሳት) በተለይ በ2009 ዓ.ም. የሁከት ጥሪ ማድረጋቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ አርሶ አደር ከእንግዲህ ግብርና የማዳበሪያ ዕዳ አይከፍልም፤›› በማለት አርሶ አደሩ በመንግሥት ላይ እንዲያምፅና ለፍትሕ ሥርዓቱ እንዳይገዛ የሁከት ጥሪ ማቅረባቸውንም አክሏል፡፡
እሳቸውም ሆኑ ድርጅቱ አርበኞች ግንቦት ሰባት እስከ መጨረሻው የደም ጠብታ ድረስ እንደሚታገሉ በመግለጽና በሰላማዊ መንገድ መታገል ሞኝነት መሆኑን በመስበክ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የሚገኘው ሕዝብ መሣሪያውን እየወለወለ ወደ በረሃ እንዲገባም በኢሳት ቴሌቪዥን ንግግር በማድረግ ሁከቱና ረብሻው በመላ አገሪቱ እንዲስፋፋ ጥሪ ማቅረባቸውንም ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሯል፡፡
ፕሮፌሰሩ በተለያዩ ጊዜያት በአገር ውስጥ በህቡዕ የሚንቀሳቀሱ ባሉበት ጥቃት እንዲያደርሱ በመንገር ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ የሽብር ቡድን አባላትም ተመሳሳይ ተግባር እንዲፈጽሙ ትዕዛዝ መስጠታቸውንም ክሱ ያብራራል፡፡
አቶ ጀዋር መሐመድም የአዲስ አበባ ከተማና የፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የጋራ ማስተር ፕላንን ለሁከት መቀስቀሻ ምክንያት በማድረግ፣ በአገር ውስጥ ለሚገኙ የኦነግ የሽብር ቡድን አባላት ጥሪ ሲያቀርቡ እንደነበር የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡ በኦሮሚያ ክልል የነበረውን ብጥብጥና ሁከት በኦኤምኤን በማስተላለፍ ሁከትና ብጥብጡ እንዲቀጥል ጥሪ ሲያደርጉ እንደነበር በክሱ ተጠቅሷል፡፡
ከወቅቱ ሁኔታ ጋር ተያይዞ ነጋዴዎች ለሕዝቡ የተለያዩ ቁሳቁሶችን እንዳይሸጡ እንዳያቀርቡና እንዳይገዙ የትራንስፖርት አቅርቦት እንዳይኖር በማለት የሁከት ጥሪ መግለጫዎችን ሲያስተላልፉ እንደነበር በክሱ ተብራርቷል፡፡ አቶ ጀዋር ከላይ በዶ/ር መረራ ክስ ላይ የተገለጹ የንብረት ውድመቶች (በገንዘብ የተገለጹት) እንዲደርሱ ምክንያት መሆናቸውንም ክሱ ይጠቁማል፡፡
በመሆኑም ሦስቱም ተከሳሾች በፈጸሙት በሕገ መንግሥቱና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለማስወገድ ሙከራ ወንጀል መከሰሳቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡ ዓቃቤ ሕግ የጠቀሰውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 238 (1 እና 2)ን ተላልፈው ፈጽመውታል የተባለው ወንጀል በሰውና በሰነድ ማስረጃዎች ከተረጋገጠ፣ ከሦስት ዓመታት እስከ ሞት ሊያስቀጣቸው እንደሚችል ሕጉ ይገልጻል፡፡
በክሱ ውስጥ በሁለተኛ ክስ ላይ የተካተቱት ድርጅቶች ደግሞ የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን (ኢሳት) እና ኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ (ኦኤምኤን) ናቸው፡፡ ድርጅቶቹ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1)ሀ እና ለ፣ 38፣ 34 (1)እና የሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 5 (1) ለን በመተላለፍ፣ ዶ/ር መረራ፣ ፕሮፌሰር ብርሃኑና አቶ ጀዋር ደግሞ ‹‹ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በሁከትና ብጥብጥ እናስወግዳለን፤›› በማለት ያቀረቡትን ጥሪ በማስተላለፍ ድጋፍ ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡
መገናኛ ብዙኃኑ በተለያዩ ጊዜያት ያስተላለፉትን ጥሪ ዓቃቤ ሕግ በዝርዝር በክሱ አካቶ አብራርቷል፡፡ በአጠቃላይ ድርጅቶቹ የኦነግና የአርበኞች ግንቦት ሰባት ልሳን በመሆንና ሚዲያንና ሙያን ሽፋን በማድረግ፣ ሦስቱ ግለሰቦች የሚያስተላልፉትን የብጥብጥ ጥሪ በመቀበልና የሽብር ቡድን ድጋፍ በማድረግ በዋና ወንጀል ላይ ተካፋይ በመሆናቸው፣ የሽብር ተግባር ወንጀል ክስ እንደተመሠረተባቸው ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡
ክሱ የቀረበለት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ለዶ/ር መረራ ጉዲና ክሱን በመስጠት ለማንበብና ተከሳሹ በጠበቃ ተወክለው እንዲቀርቡ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ከስድስት ዓመታት በፊት ክስ ተመሥርቶባቸው በሌሉበት በሞት እንዲቀጡ ፍርድ መሰጠቱ ይታወሳል፡፡

Dienstag, 21. Februar 2017

በኢትዮጵያዊነትና በኢትዮጵያ ሀገራዊ ኣንድነት ላይ የተቃጣው ጦርነትና የአርበኞች ግንቦት 7 ሀገር ኣድን ትግል | ነዓምን ዘለቀ

ራሱን ህዝባዊ ወይኔ ሃርነት ትግራይ  በማለት  በሚጠራው የጸረ-ኢትዮጵያ መሰሪዎች አምባገነናዊ አገዛዝ ላለፉት ሃያ አምስት አመታት  የዘለቀ  ስቃይ እና ጥቃት ኢላማዎች የነበሩት የኢትዮጵያ አንድነትና ኢትዮያዊነት ብቻ ሳይሆኑ  የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችም በተናጠል እና በየተራ ግፍ እና ስቃይ ሲቀበሉ ቆይተዋል  አሁንም በከፋ መልኩ ስቃዩ ቀጥሏል።
ጸረ ኢትዮጵያዊው ሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ በተደራጀ መልኩ  የጥፋት ሰይፉን በዋናነት የመዘዘበት  ኢትዮጵያዊነት ደግሞ አንዳንዶች እንደሚያምኑት የብሄር ብሄረስቦች ማለትም የኦሮሞው፣የአማራው  የትግሬውየሶማሌው የሲዳማው፣የጉራጌው ፣ የአፋሩ፣የከምባታው  እንዲሁም የሌሎች ብሄረሰቦች  ድምር ማንነት ብቻ ሳይሆን  ኢትዮጵያዊነት ከብሄሮች ድምር (The sum of its parts)በላይ ነው።  ኢትዮጵያዊነት ለዘመናት የተገነባ ማንነት ነው። የየትኛውም ብሄር ወይም ነገድ ባህልና ቋንቋ ብቻውን ኢትዮጵያዊነትን አይገልጸውም፣ አይበቃውም፣  አይተረጉመውም።
ኢትዮጵያዊነት ሚሊዮኖች በጋራ የምንጋራው ውስጣዊ ማነትታችን ነው። ስነ-ልቦናዊም ህሊናዊ ባህሪያት ያሉት  ልንገልጸው ከምንችለው በላይ ረቂቅ ነው ፡፡ ለዘመናት የተገነባውና ሚሊዮንኖች በጋራ የሚጋሩት ይህ ማነንታችን መሰረታችን ከሆነው ብሄር ማንነት በላይ ሁለመናችንን የሚገዛን  መንፈስ  ነው።ድሃ ብንሆንም በጨቋኝ ስርዓቶች ወስጥ ብናልፍም  የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎችን አሳፍሮ  በደም የተከበረው፣በማህበራዊ ትስስር የተገመደው ኢትዮጵያዊ ማንነታችን ያረካናል፣ ያጠግበናል።
ከሁለት ብሄር  እና ከዚያ በላይ ቤተሰብ የተገኙ ሚሊዮኖች  ኢትዮጵያዊነትን በብሄር አጥር እንደማናቆመው  ህያው ማሳያዎች ናቸው። በአዲስ አበባ፡ በአዳማ ፣በደሴ፡ በሃረር፣ በድሬዳዋ፣ በጎንደር፣ በባህር ዳር፡ ጅማ፣ አዋሳ  በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ዋና ዋና ከተሞች  ተወልደው ያደጉ ሚሊዮን ከተሜዎች  (Cosmopolitans) በመሆናቸው ራሳቸውን ከተወለዱበት ብሄር/ዘውግ ማነንት ጋር የሚያቆራኙበት ሁኔታ ባለመኖሩም፣ ማንነታቸው ኢትዮጵያዊነት ነው።
ዘውግ ሳይለይ ከሁሉም ማህበረስቦች መሰረታቸው  የሆነ እንዲሁም  ከእያንዳንዱ የዘውግ ማህበረስብ የተወለዱ/ወይንም መሰረታቸው የሆኑ ሚልዮኖች በቀዳሚነት  የማንነታቸው መገለጫ ያደርጉት ኢትዮጵያዊነት በሂደት በህልቆ መሳፍርት ውስብስብ የረጅም ዘመናት ታሪካችንን የሚመግቡ ብዙ የታሪክ  ጅረቶች የተገነባ ነው። ኢትዮጵያዊነት ረጅም የዘመናት ጉዞ ውጤት ነው። ውድቅት፣ ማንሰራራት፣ መነሳት፣ መስፋትና መጥበብ በተፈራረቁባት ጥንታዊት  የሆንችው ኢትዮጵያ   ምድር ደቡብ የነበረው ማህበረስብ ወደ ሰሜን ሲፈልስ፡ የሰሜኑ  ህዝብ ወደ ድቡብ ሂዶ ሲሰፍር ፡ ምስራቅ የነበረው ወደ ምእራብ ፣ ከመሃል ወደ ደቡብ ፣ከደቡብ ወድ ምስራቅ፣ ከሰሜን ወደ መሃል  ወዘተ፡ ለስራ፣ ለግጦሽ፣ ለግብርና፣ ለንግድ ልውውጥ፣ የቋንቋና የባህል መወራረሶች፡ በመዋለድ፡ በመዛመድ፡ በግጭትም ሆነ በሰላም  ማህበረስቦችን ያገናኘ፣ ያስተሳስረ ፡ በረጅም ዘመናት ግንኙነቶች ውርርሶች የተገመደ ፣ የተገነባም   ሀገራዊና ብሄራዊ ማንነት ነው ኢትጵያዊነት ።
ኢትዮጵያዊነት ዛሬ በምትገኘው ኢትዮጵያ ድንበር ውስጥ የሚገኙ ልዩ ልዩ ማህበርሰቦች ሀገራዊ መጠሪያ ብቻ ሳይሆን  በብዙ ሚልዮኖች የሚቆጠሩ  የኢትዮጳያ ልጆች  የህልውናቸው፣ የማንነታቸው መገለጻጫ ነው።  ኢትዮጵያዊነት በልዩ ልዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ሚልዮኖችን ያስተሳሰረ ማንነት ነው።
ኢትዮጵያዊነት በጸረ-ኢትዮጵያዊ የትግራይ ነጻ አውጭ አገዛዝና በተባባሪዎቹ በተቃጣበት የሰነልቦና የታሪክ ክህደት፣ የታሪክ ብረዛ፣ የባህልና የሞራል ሽርሸራ፣ ጦርነት  ብዙ ቢደማም፣  ብዙ ቢቆስልም ማንም ምድራዊ ሀይል ሊበጣጥሰው ያልቻለ ውስብስብ እና ረቂቀ ሆኖ ቀጥሏል። አሁንም  ለህልውናው እየተጋደለ ሲሆን፣ኝ በአንጻሩ የኢትዮጵያዊነት ጠላቶቹ እየተዳከሙ የመጡበት ውቅት ላይ  እንገኛለን።
የዚህ ትውልድ አባቶች፣ አያቶች ፣ቅድም አያቶች የሰሩዋቸው ታሪኮች በረጂም ዘመናት ሂደት የተገነባው የኢትዮጵያዊ ማንነት ግንባታ አካል ብቻ ሳይሆኑ እነዚህ አያት ፣ ቅድማያቶቻችን ደማቸውን አፍሰሰው ፣አጥንታቸውን ከስክሰው፣ ህይወታቸውን ገብረው ኢትዮጵያዊነትን አለምልመውታል። በአለም ታሪክ በብቸኝነት የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎችን ተቋቁማ፣ ሀገራዊ ነጻነትዋን ጠብቃ የኖረች ኢትዮጵያ የምትባለውን ወብ አገር አውርሰውን አልፈዋል። የአውሮፓ ወራሪ  ጣልያኖች ላይ በኢትዮጵያውያን መስዋእትነት የተገኘው ታላቁ የአድዋ ድል የዚህ ትውልድ  ቅድመ አያቶች መስዋአትነት ስለከፈሉ፣ ህይወት ሰለገበሩለት ነበር።  በባርነትና በቅኝ ተጘዥነት ሲማቅቁ ለነበሩ በአለም ዙሪያ ለሚገኙ የጥቁርና የአፍሪካ  ህዝቦች ትልቅ የሞራልና የስነልቦና መነቃቃትን የፈጠረው አንጸባራቂው የአድዋ ድል የአማራ፡ የኦሮሞ፡ የወላይታ ፡የትግሬ፡ የጉራጌ የከንባታና ሌሎች የጦር ኣበጋዞችና ከእነዚህ ማህበረስቦች የሄዱ ሰራዊቶች ለኢትዮጵያ አንድነትና ነጻነት ኢትዮጵያዊነትን በመገንባት የጋራ መስዋትንነት የተከፈለበት የድል ታሪክ እንጂ የአንድ ብቸኛ ዘውግ ወይንም ብሄር ብቻ የተገኘ ድል አይደለም። በኣድዋ ከዘመቱት የኢትዮጵያ የሰራዊት ኣባላት መካከል የዚህ ጸሃፊ በኣባቱ በኩል ቅደመ ኣያቱ የሆኑትንና ከትውልድ ቀዬቸው ከጌጃ ፡ ሸዋ  ተነስተው ከራስ መኮንን ጉዲሳ ሰራዊት ጋር በመዝመት ሀረርጌ  የሰፈሩትን የሸዋ ኦሮሞ  ኣቶ  ጃቶ ወለገራን ይጨምራል።
በሁለተኛውና 5 አመታት የቆየው የጣልያን ፋሽቶች የወራራ ዘመን በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ከአራቱም ማዕዘን ያሳዩት  የአርበኝነት  ተጋድሎ፡ አኩሪ ጀግንነት ኣና  መስዋእትነት  ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ነጻነትና አንድነት የተደረገ፣ ለኢትዮጵያዊነት  የተከፈለ ዋጋ ነበር። ራስ አበበ አረጋይ በቸሬ በሸዋ ፣ኮ/ል አብዲሳ አጋ በጣልያን በረሃዎች፡ እንዲሁም ከወጣቱ ኣርበኛ ደጃዝማች አብቹ አስከ ደጃዝማች በላይ ዘለቀ በጎጃም ፣ ከራስ አሞራው ውብነህ በጎንደር አስከ ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ፡ ከልጅ ሀይለማርያም ማሞ አስከ ሻለቃ በቀለ ወያ ፣ከጀ/ል ጃጋማ ኬሎ በሸዋ አስከ ኡመር ሰመተር የኢትዮጵያ አርበኞች የጀግነት ታሪክ ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ነጻነት በኢትዮጳዊት የጋራ ብሄራዊ ማንነት ስር የሚገኝ ታሪክ እንጂ የአንድ ዘውግ ወይንም የአንድ ነገድ ቋንቋ ተናጋሪዎች ብቻ ሊሆን አይችልም።
እነዚህ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ አርበኞ ያፈሰሱት ደም፡ የከስከሱት አጥንት ፡ የገበሩት ኣይተኬ የህይወት መስዋእትነት  የጋራች የሆነውን ኢትዮጵያውነትን ለማለምለም ግዙፍ አሰተዋጾ አድርጓል። በኣምስቱ ኣመት የፋሽስት የጣሊያን ወረራ ዘመን መስዋእትነት ከከፈሉትና ከኣርበኝነት ትግሉ በሁዋላ በህይወት ከተረፉት ኣርበኞች መካከል የዚህ ጸሃፊ በእናቱ እናት በኩል የወንድ ቅድመ ኣያቱ ባላምበራስ እሻግሬ ተሰማ በፋሽስቶች ጋር በተደርግው የኣርበኝነት ተጋድሎ የተሰዉ ፡ ባላንበራስ ደምሴ ተሰማ ታላቅ ወንድማችው እንደዚሁ የተስው፡ እናም በህይወት የተረፉትን ፊታውራሪ ተገኔ ተሰማ፡ ቀኛዛች ጥላሁን ተስማን ፡ “አጥሬ ተሰማ የባህር አዞ ጠላቱን ገዳይ ኣናዞ ኣናዞ” ተብሎ የተገጠመላቸውን ሻምበል ኣጥሬ ተሰማን ፡ የኣርበኝነት ገድላቸ የተጻፈላቸውንና ከመሰረታቸው ከሰሜን ሸዋ ኣማራ የሆኑትን ስባቱን ወንድማማች የባሌና የሀረር ኣርበኞች ይጨምራል።
ከሰባት ወራት በፊት ጀግናው የጎንደር ህዝብ  በጎንደር ከተማ ላይ ባቀጣጠለው ታላቅ ህዝባዊ የእቢተኝነት ተቃውሞ ሰልፍ የወያኔው መንጋ ለ25 ኣመታት የኦሮሞና የአማራን ነገዶች ለመነጣጠል ያንሰራፋውን የከፋፍለህ ግዛ ሴራ የበጣጠሰ ብቻ ሳይሆን፣ በአማራው ህዝብ ዘንድ የሚገኘውን ከአንድ ብሄር በላይ የሆነውን፤ ከሌሎቹ ብሄሮች ጋር የሚጋራውን ኢትዮጵያዊነት ያረጋገጠ ጭምር ነው፣ የወያኔ ስርአት በዘርጋው ክልላዊነት ለሃያ አምስት አመታት ሲሰብክ የኖረውን ብሄርተኝነትንም ሰብሮ የወጣ፣  መቋቋም የሚችል (Resilient)  ክስተት ሆኖም አይተናል።
ላለፉት 25 አመታት የተሰበከውን የኢትዮጰያን  የመቶ አመት ታሪክ ተረትነትም አጋልጧል። የአክሱም ሀውልት ለወላይታው   ምኑም  አይደለም በማለት  ለብዙ ዘመናት የተገነባውን ኢትዮጵያዊነትን በማሳነስ፡ በማንኳሰስ  ዓመታት ያስቆጠሩት የትግራይ ነጻ አውጪ ነን ባዮች ዛሬ  የኢትዮጵያዊነት፣ ሀገራዊ ማንነት ካባ በማጥለቅ እንደለመዱት ህዝብን ለማጭበርበር እየሞከሩ ይገኛሉ።
እነዚሁ በጭካኔ የተካኑ መሰሪ ወያኔዎች ላለፉት 25 አመታት እንዳደርጉት ሁሉ አሁንም ኢትዮጵያና ህዝቦችዋ፣ ዜጎቹዋን ከዳር እስከዳር በጭካኔያዊ አርምጃዎቻቸው የማጥቃትና የማድማት ተግባራቸው ተጠናክሮ እንደቀጠለ ሁላችንም በየእለቱ የሚያመንና  የሚያንገበግበን እውነታ ቢሆንም፣  ኢትዮጵያውያንን በጅምላ እየፈጁ፣ ከዚያው 40 ዓመት ካረጁበት  የዘር ከረጢታቸውም ሳይወጡ የኢትዮጵያዊነት ሰባኪ  ሆነው ብቅ ብለዋል።  ።
በቅርቡም ኢትዮጵያዊነትንና ኢትዮጵያውያንን ቤት አልባዎች በሚል  ከጥበትና የከድንቁርና ብቻ በሚመንጭ ድፍረት የተናገሩም ሰምተናል፡፡ ኢትዮጵያዊነት  ሁሉ ቤቱ ነው፡ የኢትዮጵያዊነት  ቤት ከሀረር እስከ ጎንደር  ፡ ከእንድብር እስከ ኢሉባቡር፣ ከጂማ እስከ መተማ ፣ ከወሎ እስከ ያቤሎ፡ ከወላቃይት አስከ ወልቂጤ ከኦሮሞ የቅደመ ኣያቴ ትውልድ ቦታ ከጌጃ፡ ሸዋ እስከ ጅጅጋ፡ ሀረር፡ ኣማራ ቅድሜ ኣያቶቼ መሰረታቸው ከሆነው ከቡልጋ ፡ ሸዋ እስከ ባሌ ጎባ  የኢትዮያውያና የኢትዮጵያዊነት ቤቱ ነው። ይህን  መብት የሚነቀንቅ ምድራዊ ሃይል አይኖርም። አራቱም የሀገሪቱማእዘናት  የኢትዮጵያዊነት ቤቶች ናቸው።
በዚህ ረጅም ዘመና ሂደት እንደማንኛውም ሌሎች ሀገሮች ታሪክ ታሪካችን ብዙ በጎ ጎኖች የነበሩት ቢሆንም  አሉታዊ ጎኖችም ነበሩት ፣ ታሪካችን አልጋ በአልጋ አልነበረም፡፡ በእነዚህ አሉታዊ የታሪካችን ጎኖች ሳቢያ ኢትዮጵያዊነት ሁሉም የቋንቋና የባህል ማህበረሰቦች  በእኩልነት የኔም ነው የሚሉት፣ ባለቤትነት፣ ባለድርሻነት የሚሰማቸው የእድገት ደረጃ አልደረሰም ለማለት ይቻላል።  ምክነያቱም አድጎ ለምልሞ  አላለቀም ፣ ሂደት ነው።  ሁሉም አገሮች የተጓዙበት ሂደት የተለየ አይደም። ከእንግሊዝ ኣስከ ቻይና ከሩስያ እስከ ህንድ ገና ኣላለቁም። የሁለት መቶ ኣመት ታሪክ ያላት ዲሞክራሲያዊ ሰረት ከባርሪያ ኣሳዳሪ ኢኮኖሚ ጋር ተጣምሮ፣ የጡቁሮች፡ የሴቶችና ከኣንግሎ ሳክስን ውጭ የነበሩ ማህበረሰኖች ሲብደሉ የነበሩባት ሃያልዋ አሜሪካም ፡ የጎደሉ መብቶች፡ ነጻነችን በህገ መንግስታዊ አርምጃዎችና በህዝብ ትግል እያስተካከልች መጥታለች። ሂደቱዋን ግን ኣልጨረስችም።
ከላይ እንደተጠቀሱትና እንዳልተጠቀሱትን  የኣለም ሀገሮችና ህዝቦች የኛም ሂደት ወደ ሚቀጥለው እድገቱ የሚሸጋገረው ወያኔዎች እንደሞከሩት ኣሁንም በሁልም ጎራ የሚገኙ ጽንፈጮች እንደሚሞክሩት ያለፈውን በማፍረስ ወይንም በብሄር  ማንነቶች ብቻ እንዲተካ፣ እንዲሳሳ በማድረግ ሳይሆን ሁሉን አቃፊ ሁሉንም የቁዋንቋና ባህል ማህበረሰቦች እኩልት፡ የሚረጋገጥበት፣ አሳታፊ የሆነ ዲሞክራስያዊ  የፓለቲካ ስርአት  እውን ማደረግ ስንችል ነው። በቀላል ቋንቋ ኢትዮጵያ የሁሉም የጋራ እናት እንጂ እንጀራ እናት ያለመሆንዋን የሚያረጋግጡ ሁኔታዎች መፍጠር ሲቻል ነው።
እስካሁን ይህን ማድረግ አልቻልንም,። በጥቁሩ ዓለም  ብቸኛው ሀገራዊ ነጻነት የነበራትን ሃገር ለህዝቧ፣ ለማህበርስቦቿ እኩልነት፣  ነጻነት የሰፈነባት ሀገር  ማድረግ ይገባናል።በዚህም ነው  ኢትዮጵያዊነትን ወደ ሚቀጥለው የእድገት ደረጃ ማሸጋገር የሚቻለው።
ኢትዮጵያዊነት ወደ ሚቅጥለው የእድገት ደረጃ ሊሸጋገር የሚችል ሁሉን አሰባሳቢ፣ ሁሉን አቃፊና አሳታፊ ዲሞክራሲ የፖለቲካ ስርአት በትግላችን መመስረት ሲቻል ብቻ ነው። ይህን ማድረግ ካልተቻለ እስከአሁን የነበው የጋራ ብሄራዊ ማንነት — ኢትዮጳያዊነት– እንዲሁም የኢትዮጵያ ሀገራዊ አንድነትም አደጋ ላይ ሊወድቁ ይችላሉ ። በዚህ ትውልድ ኢትዮጵያዊያን  ፊት የተደቀነው ትልቁ ፈተናም  የጋራ ቤታችን የሆነችው ኢትዮጵያን  የተጋረጠባት  አደጋ ነው፡፡ዛሬ ላይ የምንገኝ የዚህ ትውልድ ኢትዮጵያውያንም  እረፍት የነሳን ፣ እንቅልፍ ያሳጣን ይህ በኢትዮጵያ ሀገራዊ አንድነትና በኢትዮጵያዊነት ላይ የተቃጣው አደጋ ነው::
ስለዚህ ነው የጋራ ትግላችን ዋና ተልእኮ ይህን  አደጋ መመከትንና  መቀልበስ  ይሆናል።የሀገር  አደጋውን ልንቋቋም የምንችለው፣ ለኢትዮጵያ ሀገራዊ አንድነት፣ ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ማንነት ልምላሜና መጠናከር ዋስትና የሚሆነው ‘ ለሁሉም እኩል የሆነች፣ ሁሉም ዘውጎች፡ ሁልም ማህበረሰቦች የእኔም ናት የሚልዋት፤ መገለል፣ መገፋት፣ መረገጥ ያከተሙባት፤ ህዝቧ የስልጣን ባለቤት፣  ዜጎቿ ነጻ የሆኑባት፣ ባይተዋር ያልሆኑባት፣ ባለቤት የሚሆኑባት፣ የበይ ተመልካች ያልሆኑባት፣ ፍትሃዊ የስልጣንና የሀብት ክፍፍል የሰፈነባት፣ ሁሉም ተጠቃሚ ሁሉም የአገሪቱን ጸጋዎች፣ እሴቶች ባለድርሻ የሚሆኑባት፣ ሁሉም ማህበረስቦች/ በጠቅሉም የኢትዮጵያ ህዝብ የስልጣን ባለቤትነቱ የተረጋገገጠበት ሀገረ መንግስት (state) ስንመሰርት  እና ይህ የሚገለጽበት ህገ-መንግስታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርአት እውን ማድረግ ስንችል ብቻ ነው። ይህን ሁኔታ በመፍጠር ብቻ ነው አገራችንን ከጥፋት ማዳን የሚቻለው።
የኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ነገዶች የቋንቋና የባህል ማህበርስቦች ሙሉ ክብርና እኩልነት የሚጎናጸፉባት ፣ ሀገራዊ ማነንታቸው ለዘመናት ሁለንተናዊ ግንኙነች የገነቡት ትስስርና ውርርስ እንዲጠናከር በባለቤትነት፣ በዜግነት መብቶቻቸው  ሀገራዊ የጋራ ብሄርተኝነት – ኢትዮጵያዊንትን የሚያዳብሩባት፡ በእኩልነት የሁሉም የሆነች ኢትዮጵያ – የአማራው የኦሮሞው ፣ ጉራጌው፣ የከምባታው፣  የአፋሩ፣ የሶማሌው፣የኣንዋኩ  ወዘተ የሆነች ኢትዮጵያ – የሰው ልጅ በዘውግ ማንነቱ ብቻ ሳይሆን በቀዳሚነት ሰው በሰውነቱ ፡ በስብእናው በተፈጥሮና በፈጣሪ የተሰጡት ሁለንተናዊ ነጻነቶችና መብቶች  ከፍተኛ ክብርና ሞገስ የሚጎናጸፍባት ኢትዮጵያ ፡ የሰው ልጅ፡ የማናቸውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ መብት፡ ነጻነትና  ክብር የነገሰባት፣ እንክባብካቤ የሚደረግባት፡የሚነገሱባት፡ የሚንስራፉባት ኢትዮጵያን እውን ስናደርግ ነው።
ኢትዮጵያዊነት የጋራ ብሄራዊ ማንነት  የሚጠናከረውና የሚያብበው የተገፉ፡ በታሪክ ሂደት  ተገቢ የስልጣን ውክልና ያልተጎናጸፉ  ማህበረሰቦች በእኩልነት  በፖለትካ ስርአቱ በፍትሀዊ የስልጣንና  የሀብት ክፍፍል ባለድርሻ የሚሆኑበት ስርዓት ሲዘረጋ ነው፣በዲሞክራሲያዊ ህገ-መንግስታዊ ስራአት የተረጋገጡ መብቶች ሲሟሉ ብቻ ነው። ያኔ ሁሉም የኔም ነው የሚለው  ከቨርዥን 1.0 ወደ ቨርዥን 2.0 ( የኮምፑተር ሶፍት ዋር አናሎጂ ለመጠቀም) የተሸጋገረ የሁሉም የጋራ ማንነት የሆነ ኢትዮጵያዊነት ያብባል። የሚያድጉ የሚዳብሩ እርምጃዎችንና ግንባታዎች በማድረግ የኢትዮጵያ ጸጋና ውበት የሆኑትን ልዩ ልዪ ባህሎችና ቋንቋዎች የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሀበቶች ጭምር መሆናቸውን ማረጋገጥ ይገባል። ይህ ሁሉ ዕውን የሚሆነው የ በዙሃን (pluralism in all its manifestations) ህብረ ቀለምን በአንድነት(unity with diversity) ማሰተናገድና ማቻቻል  የሚችል ዲሞክራሲያዊ የፖለካ ስራአት  ስንመሰርት ነው። ይህን የፖለቲካ መሰረት ስንጥል ነው በሙሉ ትኩረትና በሙሉ ጉልበት አገራችን ኢኮኖሚያዊ አድገትና የቴክኖሎጂ ምጥቀት ተጠቃሚ እንድትንሆን፡ እንዲሁም ሁለንተናዊ ልማትና የተፈጥሮ ሀብታችን እንክብካቤ  ላይ በማተኮር ከድህነትና ጠኔ ነጻ የወጣ ጤናማ ኩሩ ህዝብ ለመሆን  የምንችለው ።
ከማንም የአለም ሕዝቦች በላይ የኢትዮጵያ ህዝብና በውስጡ የሚገኙ ማህበርሰቦች  ጥንታውያን ናቸው። ጥንታዊ ግሪካዊያን የታሪክ ጸሀፊዎች  ኣንዱ የሆነው ሄሮዶተስ የታወቀውና ጥንታዊ ኢትዮጵያውያንን ኣስመልክቶ የሚጠቀሰው “the blameless Ethiopians where the Gods love to feast with” ኣማልክት ከኢትዮጵያውን ጋር ድግስ መብላት ይወዳሉ ብሎ ነበር የጻፈው። ነብዪ መሐመድ- ለአደጋ ተጋለጡ የእስልም ተከታዮችን  ፍትህ ወደ ማያጉዋድለው   ወደ ኢትዮጵያ ንጉስ ሂዱ በለው ነበር  የላኩዋቸው። ሌሎች በታሪክ የተመዘገቡና ኢትዮጵያን የሚያሳዩት በጥንት ዘመን  ብዙ ብጎ ምግባሮችና ጻጋዎች ማማ የነበረች ምድርም እንደነበረች ይገልጻሉ። አሁንም ኢትዮጵያዊያን የዚያን የሩቅ ዘመን ከፍተኛ ስብዕናና የፍትህ እሴቶች የሚበልጡ የፍትህ፡ እኩልነት፡ የሰው ልጆች  ነጻነት የነገሰባት ዘመናዊ ሀገር መገንባት የማንችልበት ምክንያት የለም።ለዘመናት የኖረውን ከኣለም ሀገሮች ብቸኛው ሀገራዊ ነጻነት የነበረን ህዝቦች የማህበርስቦች እኩልነት፣ የዚጎች ነጻነት የሰፈነባት ሀገር እንድትሆን ማሸጋገር ፡ስንችል ነው ኢትዮጵያዊነት ወደ ሚቀጥለው የእድገት ደረጃ የሚሸጋገረው። ሀገራዊ የነጻነት የዘመናዊ ታሪካችን በዜጎች ነጻነትና ፍትህ  መመንዘር፡ ለሁሉም ማህበሰቦች እኩልነትን ማሟላት ስንችል ነው።
ስለዚህ ትግላችን ይህን የጋራ ቤታችን የሆነችዋን ኢትዮጵያ አገራችንን የማዳን ትግል ነው፡፡ ትግላችን  ኢትዮጵያዊነትና የኢትዮጵያዊት ቤት የሆነችውን ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ማዳን ነው። ለኢትዩጵያዊነትና ለሁሉም ኢትዮጵያውያን መታገል የንቅናቄያችን መብትም በውዴታ የገባንበትም ግዴታ ነው። ከወያኔ ፋሽስታዊ የጨካኞች ስርአት ጋር የመረረ የከረረ ሁለገብ/ሁለንተናዊ ትግል ማድረግ ያለብንም ይህን የተሻለ የህዝብና የዜጎች መብቶችና ነጻነቶች የሚረጋገጡባት የፓለቲካ ስርአት እውን ለማድርግ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ሀገራዊ አንድነትና ኢትዮጵያዊነት ህልውና   አደጋ ውስጥ በመሆናቸውም ጭምር  ነው።
ይህንን ኢትዮጵያን  የማዳን ሀገር አድን ታላቅ ራዕይና ተልዕኮ ቃል ኪዳን የሚመጥን ቃልን ወደ ተግባር ፡ ዲስኩርን ወደ ተግባር የሚተረጉም እንቅስቃሴዎችን ከከፍተኛ አመራሮቹና  በሺ የሚቆጠሩ  አባላቱ እያደረገ ይገኛል። አመራሮቹ  ታጋዮቹ  ሆነው ሲገኙ፣ መስዋዕትነት ሲከፍሉ ሲያታግሉና ሲታገሉ ቆይተዋል።የአርበኞች ግንቦት 7 ሀገራዊ  ራዕይና ተልዕኮ ለትልቅ ሀገር ለመቶ ሚሊዮን ህዝባችንን የሚመጥነውን ዲሞክራሲዊ ስራአት እውን  ማድረግ ነው። ንቅናቄችን ብዙ መስዋትነት እየከፈለም ነው። ወድፊትም ይከፍላል። ኢትዮጵያዊነትና ኢትዮጵያን ለማዳን ለህዝብ ነጻነትና ለሁሉም ዜግጎች መሰረታዊ መብቶች ለሁልም ዘውጎችና ማህበረሰቦች እኩልነት መታገል ብሎም ምስዋዕትነት መክፈል አጅግ የምንኮራበት እንጂ የምናፍረብት፣ ግንባራችንንም የምናጥፍበት በፍጹም አይሆንም።
አርበኞች ግንቦት 7 ውስት የሚገኙ አባላት የተሰባሰቡት በኢትዮጵያዊነት ነጻነትና ፍትህ የጠማቸው ስለሆኑ እንጂ ዘር እየተቋጠሩ አይደለም። ንቅናቄያችን የልዩ ልዩ  ዘውጎችና ብሄሮች ተወላጅ የሆኑ አባላት ቢኖሩትም ራዕይው ሀገራዊ፣ ኢትዮጵያዊ ነው። የጋራቸው የሚያስተሳስራቸው ያሰባሰባቸው ለዘመናት የተገነባው  ከሁሉም ብሄሮች ማንነት በላይ  የሆነው ኢትዮጵያዊነታቸው ነው። የንቅናቄው አርማ የኢትዮጵያ አንድነት ነው። ኢትዮጵያዊነት ነው።  ግባችን ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ስርአት ነው።  ስለዚህም ነው አርበኛች ግንቦት 7 የወደፊትዋ ኢትዮጵያ በዜግነት እኩልነትና ነጻነት ላይ የተመሰረተ ሀቀኛ የዲሞክራሲያዊ ስርአት ለኢትዮጵያ አንድነትና በአገራችን ለሚገኙ ዘርፈ ብዙ ውስብስብ ችግሮች ብቸኛ አገር አድን የፓለቲካ መፍትሄ ነው ብሎ በጽኑ የሚያምነው የሚያቀነቅነው። መስዋእትነት በመክፈል  ላይ የሚገኘው።
ጥሪያችን ኢትዮጵዊነትና ኢትዮጵያ ሀገራችንን በትግችን ለማዳን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ቆርጦ ለተግባራዊ ትግልና ኣስተዋጻኦ እንዲነሳ ነው!!
ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት  ለዘላለም ይኖራሉ!! ፡በትግላችን መስዋእትነት  አንድነቱዋ የተጠብቀ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እውን እናደርጋለን!!
ኑው ዮርክ፡ ፊብሩዋሪ 17፡ 2017

Dienstag, 14. Februar 2017

የወያኔዋ ኢትዮጵያ — ደማቸውን ያፈሰሱላት የሚዋረዱባት፤ የሸጧት ግን የሚከበሩባት ምድር (አቻሜለህ ታምሩ)

የወያኔዋ ኢትዮጵያ — ደማቸውን ያፈሰሱላት  የሚዋረዱባት፤ የሸጧት ግን  የሚከበሩባት ምድር

የኢሉባቡር ጠቅላይ ግዛት አካል ከነበረው  ከጋምቤላ በ1894 ዓ.ም. በተደረገው የኢትዮጵያና የእንግሊዝ ስምምነት መሰረት፤ከሱዳን ተነስቶ በነጭ ዐባይ አድርጎ የሚመጣው የንግድ መርከብ የሚቆምበት ወደብና  የእንግሊዝ የቀረጥ አስተዳደር  መስሪያ ቤት የሚያርፍበት ቦታ የሚሆን  ከ2000 ሜትር ወይንም ከ40 ሄክታር የማይበልጥ መሬት፤ እንግሊዝ  ሱዳንን ለቅቃ ስትወጣ ግን  ወደ ኢትዮጵያ የሚመለስ የንግድ ማዕከል [Commercial Enclave]  እግሊዞች እንዲያስተዳድሩት ተሰጥቶ ነበር።

እንግሊዝ  ይህንን ቦታ እንደያዘች  አስተዳደሩን እንዲጠብቁ የራሷን ዜጎች ትሾም ነበር። በኢትዮጵያ መንግስት  በኩል  ደግሞ ጋምቤላን እንዲያስተዳድርና ወሰኑን እንዲጠብቅ የተሾመው ከጋምቤላ ባላባቶች አንዱ ነበሩ።  ኮሎኔል ጃክ ሞሪስ [Jack Maurice] የሚባለው እንግሊዛዊ  አስተዳደሩን በተረከበበት ጊዜ ጀምሮ የጋምቤላውን ባላባትና አስተዳዳሪ እያታለለና በገንዘቡ እየገዛ  በስምምነቱ ለእንግሊዝ ተለክቶ ከተሰጠው ወሰን እያለፈ ብዙ የጋምቤላን መሬት የሱዳን አካል ያደርግ ጀመር። ይህንን   ወረራና የጋምቤላ መሬት  ከኢትዮጵያ ተወስዶ ወደ ሱዳን መካለል  የወቅቱ  የኢትዮጵያ መሪ ልዑል  አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮነን  ይሰማሉ።

ዜናው እንደተሰማ  ከተቻለ በሰላም፤ ካልሆነ ግን በጦር ኃይል ድንበር ታልፎ ወደ ሱዳን የተወሰደውን የጋምቤላ መሬት እንዲያስመልስ፤ ወደፊትም ድንበሩን እንዲጠብቁ በደጃዝማች ብሩ ወልደገብርኤል [ኋላ ላይ ራስ] የሚመራ ጦር ወደ አካባቢው ይላካል። ደጃዝማች ብሩ ወልደገብርኤል  ወታደር አሰልፈው አካባቢው እንደደረሱ ጦርነት ከመክፈታቸው በፊት በዲፕሎማሲ መንገድ የጋምቤላው ባላባት የኢትዮጵያን ወሰን አልፈው ለሱዳን የሰጡትን መሬት እንግሊዝ እንዲለቅላቸው  ኮሎኔል ጃክ ሞሪስን ጠየቁ። ኮሎኔል ጃክ ሞሪስም ድሮውን ቦታውን የያዘው ስምምነቱን ተላልፎ አውቆ ኖሮ፤ ኢትዮጵያና እንግሊዝ ወደ ጦርነት ሳያመሩ ወሰን አልፎ ወደ ሱዳን ያካለለውን ብዙ መሬት በሰላም ለኢትዮጵያ ለማስረከብ ተስማማ።

ከዚህ ጊዜ ጀምሮ  ራስ ብሩን ተከትሎ ዳር ድንብር ለማስከበር  ከመሀል አገር ተነስቶ ወደ ጋምቤላ የዘመተው የኢትዮጵያ ወታደር በጋምቤላ በረሀ ያለውን በሽታ ችሎ  እስከ ጥሊያን  ወረራ ድረስ አንዲት ክንድ መሬት ሳያስወስድ እየጠበቀ ቆየ። ከጥሊያን ወረራም በኋላም የኢትዮጵያ ነጻነት ከተረጋገጠበው ዘመት ጀምሮ  ሱዳን ነጻ  እስክትወጣና  በ1894 ዓ.ም. በተደረገው የኢትዮጵያና የእንግሊዝ ስምምነት መሰረት ሙሉው የጋምቤላ መሬት ወደ ኢትዮጵያ እስኪመለስ ድረስ  ዳር ድንበር ሲጠብቅ እዚያው ኢሉባቦር ጠቅላይ ግዛት ጋምቤላ ኖሯል።

ሆኖም ግን  ባላባት ተብሎ አካባቢውን  እንዲያስተዳድርና ድንበሩን እንዲጠብቅ የተሾመው ፊት አውራሪ ጋምቤላ [ፊታውራሪ ጋምቤላ የአኙዋክ ተወላጅ ባላባት ናቸው] ለኮሎኔል ጃክ ሞሪስ እየተደለሉ የአስወሰዱትን መሬት ተዋግተው  ለማስመለስ፤ ከዚያም በኋላ ድንበሩ እንዳይደፈር ወሰኑን ለመጠበቅ ከዳጃች ብሩ ወልደ ገብርዔል  ጋር የዘመቱ ወታደሮች ልጆች  ወያኔና ኦነግ ስልጣን በያዙ ማግስት  «ነፍጠኛ»  ተብለው   ከኢሉባቦርና ጋምቤላ ተፈናቅለው አባቶቻቸው ደም ባፈሰሱበት ምድር  ስደተኛ እንዲሆን ተደርገዋል።

አቶ ዮሀንስ መሸሻ በ1989  ዓ.ም. ባሳተሙት «የማውቃት ኢትዮጵያ» መጽሀፋቸው በዚያው አመት  ከኢሉባቦር ጠቅላይ ግዛት  «ነፍጠኛ» ተብለው  «አገራችሁ ሂዱ!» በመባላቸው ተፈናቅለው አዲስ አበባ በስደት ሲንከራተቱ ካገጓቸው አማሮች መካከል  ከደጃዝማች ብሩ ወልደገብርኤል ጋር የጋምቤላው ባላባት ለእንግሊዝ የሸጡትን መሬት ለማመለስ ከዘመቱና ድንበሩን ሲጠብቁ ከኖሩት አርበኞች  የአንዱን አርበኛ የአገር ውስጥ  ስደተኛ ታሪክ አስፍረዋል። 

ኢትዮጵያ ደማቸውን ያፈሰሱላት  የሚዋረዱባት፤ የሸጧት ግን  የሚከበሩባት አገር ሆና  ነው  እንጂ እኒህ ነጻ ባወጡት ምድር የጦጣ ግንባር ያህል እንኳ የአንገት ማስገቢያ ተከልክለው  በአማራነታቸው ብቻ ነፍጠኛ ተብለው ከኢሉባቦር በአገር ሻጮች  እንዲፈናቀሉ የተደረጉት ኢትዮጵያዊ  ጀግና፤ የእንግሊዙ  ሞሪስ እያታለለ ወስዶ የሱዳን አካል አድርጎት  እሳቸው ግን  ባስመለሱት መሬት ላይ  በስማቸው ትምህርት ቤትና መንገድ፤ ከተማና ተቋማት የሚሰየምላቸው፤ ሀውልትም የሚቆምላቸው አርበኛ ነበሩ።

Samstag, 11. Februar 2017

ምጧ የተራዘመባት- ኢትዮጵያ! (ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ)

ምጧ የተራዘመባት- ኢትዮጵያ! (ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ)

ምጧ የተራዘመባት- ኢትዮጵያ! (ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ)
elias-gebru
ሀገረ ኢትዮጵያ፡- ከአገዛዝ፣ አገዛዝ ስትሻገር በጭቆና በትር ተቀጥቅጣ፤ ስትማቅቅ በርካታ ዓመታትን አስቆጥራለች፡፡ የህዝቦቿ መከራም ቅርፁን እየቀያየረ፤ ሲያሻውም እየተመላለሰ ትናንትን አቋርጦ ዛሬ ላይ ደርሷል፡፡ ለጭቆና በትሩ ተግባር ወለድ መፍትሔዎች ካልተበጀላቸው መከራው ነገም ይቀጥላል አገዛዙ አለና!
ሀገር በጉልበት ሲገዛ ፣ ወረቀት ላይ በደማቁ አምሮ የተጻፈ ሕግ በመርህ መተግበር ሲሳነው፤ ህዝብና ገዢ ኃይል የአይጥና የድመት ኑሮን ለመኖር ሲገደዱ፣ የነቃ፣ የተማረ በሚባለው የህብረተሰብ ክፍል ዘንድ የሀገርን ሳይሆን የግል ጥቅምን ማስቀደም እንደ አዋቂነት ሲቆጠር፣ ሲተገበር፣ ለቁስ መንሰፍሰፍና “ለእኔ ብቻ!” የሚል የስግብግበነት መንፈስ አይን አውጥቶ በገሃድ ሲታይ፤ የጤናማ ይሉኝታ ባህል ተሸርሽሮ ገደል ሲገባ፣ ሀገር በቀል ባህላዊ እሴቶችን ይዞ መኖር ኃላ ቀርነት ሲያስብለን፣ ፖለቲካ በሀሳብ ሙግት ሳይሆን በጥላቻ ፣ በጠልፎ መጣል፣ በጉልበትና በፍረጃ ሲሰራ፣ የእራስን ዜጋ ንቆ ፈረንጅን ማምለክ ዘመናዊነት ሲመስል፣ እውነትን መጋፋጥ ሞኝነት፣ በውሸት /በሀሰት/ ውስጥ መኖርና ማምለጥ እንደ ብልጠት ሲወሰድ፣ አድርባይነት፣ ሆድ አደርነትና ጥቅመኝነት የህብረተሱ ዋነኛ መገለጫ መሆናቸው ሲያመዝን ጉቦ፣ ሌብነትና ዘመናዊ ሙስና እንደክብር መግለጫ ሲቆጠሩ፣ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል!” ከሚል የመነጨ ጥልቅ የሥልጣን ጥም ሰፊውን ህዝብ ሲያሰቃይ፣ ባለሥልጣናት በየረገጡበት የውጭ ሀገራት ክብርን ሳይሆን ውርደትን ሲከናነቡ፣ ገዢ ኃይል፡- ሀገርን ወደፊት ማራመድ ሲሳነው ሀገር የቁልቆለት መንገድ ላይ መሆኗን በጥቂቱ ያመላክታል ብዬ አምናለሁ፡፡
ቀደምት ስልጡን ሀገር መሆኗ በታሪክ ተደጋግሞ የሚወሳላት ኢትዮጵያለ፡- በህወሃት/ኢህአዴግ የጉልበት የሥልጣን ዘመንም በርካታና ስፍር ቁጥር የሌላቸው ችግሮችን ፀንሳለች፣ መከራዎችንም አርግዛለች፣ ዛሬም በእነኚህ ችግሮችና መከራዎች እየዳከረች ነው፡፡
የህወሃት አገዛዝ፣ ከደርግ ውድቀት ማግስት በኃላ “ሰላምና መረጋጋት”፣ “ተሃድሶ” የሚሉ ሃሳቦችን ሲያቀነቅን ነበር፡፡ በተራዛሚ ሂደትም “ህዳሴ፣ ትራንስፎርሜሽን“ ሲል ከርሞ አሁን ደግሞ፡- “በጥልቀት መታደስ!” የሚል ወቅታዊ ነጠላ ዜማ በመልቀቅ የሀሰት ነጋሪት ጉሰማውን ተያይዞታል፡፡
ከሩብ ምዕተ ዓመት በላይ በሥልጣን ማማ ላይ ያሳለፈው ይህ አምባገነናዊ አገዛዝ፣ ብዙ ያወራላቸውና በፕሮፖጋንዳ ማሽኖችም ብዙ ያስነገረላቸው ተንኮል – ወለድ ዕቅዶቹ በሙሉ በክሽፈት አዙሪት ውስጥ የሚናውዙ ናቸው፡፡ ይህንን ለመረዳት ነገሮችን በአንክሮ መከታተልና ማጤን ወሳኝነቱ አሻሚ አይሆንም፤ እንደማሳያም ከላይ የጠቀስኳቸው ቃላቶች መካከል ሦስቱን በምሳሌነት ላስቀምጥ፡-
ህወሃት ኢህአዴግ የጉልበት ሥልጣንን “ሀ” ብሎ ሲጀምር በህዝቡ ዘንድ እንዲሰርፅለት የታተረው ቃል “ሰላምና መረጋጋት” የሚል ነበር፡፡ ለአንዲት ሀገር ህልውና፣ ለህዝቦቿ በአንድነት መኖር ሰላምና መረጋጋት ወሳኝ ኹነቶች ናቸው፡፡ በወቅቱም የሚፈለገው እውነተኛ ሠላም መኖርና መረጋጋት መስፈን/አለመሸፈት ሀቅን የመመርመር ህሊና ላላቸው ባለአዕምሮ ዜጎች ልተወውና ወደ ዛሬው እውነታ እንለፍ፡፡
ከ2008ዓ.ም የመጀመሪያ ወራት ጀምሮ “በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ ልዩ ዞኖች በአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ሥር ይካተቱ” የሚለውን የህወሃት/ኢህአዴግ እኩይ እቅድን በመቃወም በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች የተጀመረውን ህዝባዊ እምቢተኝነት ጠንካራና ተግባር ተኮር በመሆኑ የተነሳ አገዛዙን አንገዳግዶት ከባድ ስጋት ላይ ጥሎት እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፣ አንዱም የታሪካችን አካል ነው፡፡
ከተጠቀሰው አመት አጋማሽ በኃላም በአማራ ክልል የወልቃይት ጠገዴ የማንነት ጥያቄን ተከትሎ የተነሳው ህዝባዊ ተቃውሞና ትግል የአገዛዙን ህልውና በብርቱ መፈተኑም ይታወቃል፡፡ በያዝነው ዓመት መስከረም ወር በደብረዘይት/ቢሾፍቱ ከተማ በየዓመቱ የሚከበረው የእሬቻ በዓል ላይ የደረሰው እጅግ አሳዛኝና ዘግናኝ የሞት አደጋ አይረሳም፤ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ንፁሃን ወንድምና እህቶቻችንን አጥተናል!
ይህ ዘግናኝ ኹኔታ በተለይ በኦሮሚያ ክልል ዳግም ህዝባዊ ቁጣን ቀስቅሶ በርካታ ፋብሪካዎች፣ ተሽከርካሪዎች፣ ንብረቶች…… በእሳት ቃጠሎ መውደም ጀመሩ፡፡ ተቃውሞ አድራጊዎችና የአገዛዙ የፀጥታ ኃይሎች ፊት ለፊት ሲላተሙ የበርካቶች ህይወት አለፏል፡፡ ወዲያውም የሀገሪቱ ሰላምና ደኅንነት ከባድ አደጋ ላይ መውደቁን ገዢው ኃይል አመነና ይህ አሁንም ድረስ ያለንበት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለስድስት ወራት ታወጀ፡፡ ከእዚህ በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው ህወሃት/ኢህአዴግ ሥልጣን ከያዘ ጀምሮ አልፎ አልፎ አንጻራዊና ወቅታዊ ሰላምና መረጋጋትን በሀገሪቷ ከመፍጠር ባለፈ እውነተኛና ዘላቂነት ያለው ሰላምና ደኅንነትን እውን ማድረግ አለመቻሉን ነው፡፡ ከ25 ዓመታት በኃላም ሰላምና መረጋጋት በሀገሪቷ እና በዜጎቿ ዘንድ ሊረጋገጥ አልቻለም፡፡ ለእዚህ ደግሞ ዋናው ተጠያቂ “ሀገሪቷን እያስተዳደርኩ ነው” የሚለው ህወሃት/ኢህአዴግ ነው፡፡ የሀገርና የህዝብን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ አለመቻሉ የታላቅ ክሽፈቱ አንዱ ማሳያ ነው፡፡
በሌላ ረገድ ከኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ማግስት ጀምሮ ባሉ ጥቂት ዓመታት “ተሃድሶ” የሚለው ቃል በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በአሁኑ EBC በስፋት ይቀነቀን ነበር፡፡ የተሃድሶን ቃል ስንገልጠው “መታደስ” የሚል ፍቺን ይሰጠናል፡፡ መታደስ አንደ አዲስ መለወጥ ነው፡፡ በጎ ህሊና ያለው ሰው ተሃድሶን ይሻል፡፡ በመልካም መታደስ ለሰው ልጅ እፈላጊ ነውና ህወሃት/ኢህአዴግ፡- ሰፊው ህዝብና ሀገራችን በመታደስ ጎዳና ላይ ቢገኙ እጅግ ደስታና ሀሴት ነበር፡፡ ሆኖም፡- በ25ዓመታት ውስጥ “ተሃድሶን ውሃ በላት” በአገዛዙ በተግባር እውን ሊሆን አልቻለምና፤ ዛሬም “በጥልቀት” የሚል ተቀጽላ ቃል ተጨምሮባት በድጋሚ አፍአዊ ተግባር ላይ ውላለች፡፡ ‹‹ጥልቅ ተሃድሶ››ን በቃላት ማነብነብና በተግባር በጥልቀት ለየቅል ናቸው፡፡ ጥልቅ የሥልጣን ጥም ያለው ኃይል፣ በጥልቅ ሙስና የበሰበሰ አገዛዝ በጥልቅ ጥላቻ የገዛ ወንድምና እህቶቹን የሚያሰቃይ፣ የሚያስር፣ የሚያሳድድ፣ የሚገድል……. ቡድን በጥልቅ የገዛ ጥላውን ጭምር የሚፈራ ግለሰብ፣ ከቶ እንዴት በጥልቀትሊታደስ ይቻለዋልን???
ህወሃት/ኢህአዴግን ለ25 ዓመታት በአንክሮ ለተከታተለው፤ በጥልቀት ሊታደስ ቀርቶ በጥቂቱም ወደ መልካምነት ሊቀየር አለመቻሉን መረዳት ይቻላል፡፡ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓትን አፈራርሶ፣ የግል ሚዲያን አንቆ ገድሎ፣ ነፃና ገለልተኛ የሲቪክ ማኅበራትን አክስሞ፣ ዜጎችን በፍርሃት እስር ቤት ውስጥ ከርችሞ ጠባብነትና ትምክተኝነትን አስፋፍቶ፣ ዘረኝነትን አንግሶ፣ ጥቅመኝነትን ፈልፍሎ………. ወዘተ “በጥልቀት መታደስ” ማለት ቧልት ይሆናል፡፡ “ከድጡ ወደ ማጡ” ነውና ነገሩ፤ መታደስ አለመቻል ሌላኛው የአገዛዙ መገለጫ ነው፡፡
በ2002ዓ.ም የተደረገውን “ሀገር አቀፍ ምርጫ”ን ተከትሎ 99.6% “ድል” ወደ አገዛዙ ሄደ፡፡ ከምርጫው በኃላም በስፋትና በ“ጥልቀት” የምትቀነቀነው ቃል “ትራንስፎርሜሽን” ሆነች፡፡ የአምስት ዓመቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በሚል እጅግ የተለጠጠውና በአማላይ ቃላቶች የተንቦረቀቀው የዕቅዱን ዝርዝር መለስ ብሎ ማየት ይቻላል፡፡ ዕቅዱና አፈፃፀሙ በአልተገናኝቶ መስመር ሲነጉዱም አይተናል፡፡ እቅዱ 2ኛ ዙር ቢኖረውም ፍሬያማ አልነበረም፡፡ እቅዱ 3ኛ፣4ኛ ዙር ቢኖረው እንኳን ህወሃት/ኢህአዴግና ትራንስፎርሜሽን በተግባር የሚታዩ፣ የሚነካ፣ የሚዳሰስ፣ የሚቆነጠር፣ ህልውና አይኖራቸውም፡፡ ለምን? እውነተኛ ትራንስፎርሜሽን ከቅንነት፣ ከህዝባዊነት፣ ከአርቆ አላሚነት፣ ከድፍረት፣ ከእውቀት፣ ከትጋት፣ ከቁርጠኝነት…….ወዘተ የሚወለድ ሲኾን በአንጻሩ ጠባብነት፣ ትምክህተኝነት፣ ወገንተኘነት፣ ሙሰኝነት፣ ሴሰኝነት፣ የሥልጣን ጥመኝነትና ክፋት ባለበት ቦታ እውን አይሆንም፡፡ ሀገርን “ከአንድ ዝቅ ካለ ደረጃ ወደ ላቀው ሌላኛው ከፍታ አሸጋግራለሁ!” የሚል ኃይል በተቃራኒው የአዘቅት መንገድ ላይ አይገኝም ነበር፡፡ ግን ይህ በሀገራችን ሆነ! በመሆኑም አገዛዙ በብዙ ረገድ ሀገርን ወደ ከፍታ ሳይሆን ወደ አዘቅት ውስጥ ከቶታል፣ እየከተተም ይገኛል፡፡
…….“በ25 ዓመታት ውስጥ መታደስ አልቻልኩምና አሁን ገና በጥልቀት መታደስ አለብኝ!” የሚል ቡድን እንዴት የአንድን ሀገር የትራንስፎርሜሽን እቅድ እውን ሊያደርግስ ይቻለዋል?! ይህም ያልዘሩትን ዘር አዝመራ እንደማጨድ ይቆጠራልና ሌላኛውን የአገዛዙ ክሽፈት ነው፡፡
ከላይ በመግቢያዬ እንገለፅኩት፤ ኢትዮጵያ በዘመነ ህወሃት/ኢህአዴግ በርካታና ስፍር ቁጥር የሌላቸው ችግሮችን ፀንሳለች፤ መከራዎችንም አርግዛለች፤ እነኚህ ችግሮችና መከራዎች፡- ምጧ እንዲረዝም ስቃይዋም እንዲበረታ አደርገዋታል፡፡ ከምጧ እና ከስቃይዋም በሌላም መንገድ ለመገላገል በተፈጥሯዊ መንገድ አምጣ እውነተኛ ሰላምን፣ ነፃነትን፣ ዴሞክራሲን፣ ፍትህን፣ እኩልነትን፣……… መውለድ ይጠበቅባታል፡፡ አልያም የምጥ ማፍጠኛ መርፌ መውጋት ከቀላል እስከ ከፍተኛ የሚደርስ ቀዶ ጥገና ማድረግ የግዷ ሊሆን ነው፡፡ እኒዚህም ካልተሳኩ አሳዛኙን እውነታ መቀበል የዜጎቿ እጣ ፈንታ ይሆናል፡፡ ውስብስብና አስቸጋሪ ነገሮች ካልተፈጠሩ በቀር አንዲት እርጉዝ ሴት በተፈጥሯዊ መንገድ አምጣ ብትወልድ ጥሩ መሆኑን የዘርፉ የህክምና ባለሙያዎች እንደሚመክሩት ሁሉ፤ ሀገራችንም እውነተኛ ሰላምን፣ ነፃነትን፣ ዴሞክራሲን፣ ፍትህን፣ እኩልነትን፣…… በተፈጥሯዊ መንገድ አምጣ ብትወልድ ለዜጎቿም እፎይታ ነው፡፡ ይህ እውን እንዲሆን ግን ዴሞክራሲያዊ ለውጥን የሚሹ ዜጎች (በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ያሉ) ከመቼውም ጊዜ በላይ ስለሀገራቸው ቀጣይ ፖለቲካዊ እጣ ፈንታ በአንክሮና በስክነት ማሰብ፣ ማሰላሰል ይጠብቅባቸዋል፡፡ የሀሳብ ልዩነት የትም ቦታ አይጠፋምና ልዩነትን ችሎ አንድነት ላይ ግን ይበልጥ ጠንክሮ መቆም የውዴታ ግዴታቸው መሆኑን አሻሚ አይሆንም፡፡
የልዩነት መንገዶች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ለዓመታት መሰራቱ ወደታች ሲያወርዱን እንጂ ወደ ከፍታ ሲያወጡን በተግባር አልታየምና እያቃረንም፣ ውስጣችንን እየተፈታተነንም ቢሆን የልዩነት ድንበርን በድፍረት ተሻግረን ለተሻለ የሀገር ስሪትና ምስረታ አንድ እንሁን!
ለዴሞክራሲያዊ የለውጥ እንቅስቃሴ እንተባበር!

Donnerstag, 9. Februar 2017

የጎሳ ፖለቲካና የኢሳት ፈተና (ከአንተነህ መርዕድ) ከአንተነህ መርዕድ

የጎሳ ፖለቲካና የኢሳት ፈተና (ከአንተነህ መርዕድ)
ከአንተነህ መርዕድ
ከደርግ መውደቅ ማግስት የህዝብን ብሶትና የእለት ተእለት ውሎውን የሚዳስሱ በርካታ ጋዜጦችና መፅሄቶችን ከዳር ዳር ባይዳረሱም በአዲስ አበባና በትልልቅ ከተሞች ህዝቡ እየገዛና ከእጅ እጅ እየተቀባበለ በማንበብ ይከታተል ነበር። ወያኔዎች ገበናቸው እየተጋለጠ መግዛት እንደማይችሉ ሲገነዘቡ፤ ጋዜጠኞችን በማሰር፣ በማሰደድ፣ ብሎም በመግደል (አሰፋ ማሩና ተስፋዬ ታደሰን ሳንረሳ)፣ አዟሪዎችንም በመቀጥቀጥ የነፃ ሚድያን ህልውና እንዲያከትም አድርገዋል።
በዚህ የጨለመ ድባብና ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ነበር። ፀሃይ ከምስራቅ እንደምትወጣ ሁሉ ተስፋና ብርሃን ይዞ ኢሳት በአድማስ ላይ ብቅ ያለው። የኢሳት መፈጠር በጨለማ ማደግ ለሚመቻቸው እኩያን ሞት ስለሆነ ለማዳፈን ከየአቅጣጫው ሩጫ ተጀመረ። እውነቱን እያፍረጠረጠ ማውጣቱ መጥፊያቸው እንደሚሆን ያወቁት ወያኔዎች ብቻ ሳይሆኑ እውነተኛ ባህሪያቸውን ህዝብ እንዳያውቅባቸው የፈሩ የነገ መሳፍንት ጽንፈኞችም ሁሉንም ዓይነት ጦር ወርውረዋል። አሁንም ተስፋ ባለመቁረጥ የተቻላቸውን ያህል እያደረጉ ቢሆንም፤ ኢሳት ለህዝብ ነፃነት እውነት ላይ ተመስርቶ እስከሠራ ድረስ የሚያቆመው ኃይል አይኖርም። ለዚህም ነው ባለፉት ስድስት ዓመታት ውስጥ ከሁሉም አቅጣጫ የሚሰነዘርበትን ፈተና ተቋቁሞ እዚህ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰው። ወያኔ ኢሳትን ለማጥፋት ብዙ ሚሊዮን የህዝብ ገንዘብ አፍስሶ፣ የዲፕሎማሲና የስለላ ሥራ ሁሉ ሠርቶ ለስድስት ዓመት ያልተሳካለትን ተግባር በውክልና ይሁን በምቀኝነት በእውነት ፊት መቆም የማይችሉ ድንክ “ፖለቲከኞች” ወይም የፌስቡክ ጀግኖች የሚሰነዝሩት ብኩን ሃሳብ የበለጠ እያጋልጣቸው መሆኑን የተረዱ አይመስልም።
ኢሳት በጠንካራ የንዋይ መሰረትና በልምድ ፍፁም ብቃት ባላቸው ጋዜጠኞች የተገነባ ነው ማለት ከእውነት መራቅ ይሆናል። ጉልሁ እውነት ግን የወጣትነት እድሜአቸውን ለእውነተኛ አገራዊ ጉዳይ በሙያቸው ለማገዝ እየተሳሳቱም ቢሆን በቅንነት እየተማሩ ለመሥራት የቆረጡ ብዙ ተስፋ የሚጣልባቸው እንቁ ልጆች ያሉበት መሆኑ ነው። ሙያቸውን በሚገባ እያዳበሩ መሄዳቸውን ላለፉት ጥቂት ዓመታት ኢሳትን የተከታተለ ሁሉ ይገነዘበዋል። ኢትዮጵያ በሌለ አንጡራ ሃብቷ አስተምራ ዛሬ ከወደቀችበት የሚያነሳት ዜጋ በመብራት ስትፈልግ፤ በውጭም፣ በአገርም ውስጥ ያሉ አቅም ያላቸው ምሁራን ከፊሎችም በፍርሃት አንገታቸውን ደፍተው ህሊናቸውን ለድሎት ሲቸበችቡ፣ ጥቂቶችም ለሚያልሙት የነገ ስልጣን ሲሉ ጥልቅ ገደል እንድትገባ አንገቷ ላይ ደንጋይ ሲቋጥሩና በመንደር ሸንሽነው ተበተኝ ሲሏት በዚህ ማዕበል መሃል ትክክለኛ አቅጣጫ እንድትይዝ የኢሳት ጋዜጠኞች የሚያደርጉት መዋደቅ የተሸከሙትን የሃላፊነት ክብደት ያሳያል። የሚያሳዝነው ይህንን ብቸኛ ተቋምና ብርቅ የህዝብ ልጆች ኢላማ ያደረጉ እየተበራከቱ መምጣታቸው ነው። ቢሆንም የነዚህ እኩያን መንፈራገጥና መንጫጫት ኢሳት በትክክል እየሠራ ለመሆኑ አመላካች ቴርሞሜትር ነው። አንድ ዐይን ያለው በአፈር አይጫወትም የሚለው የአባቶቻችን አስተዋይ አባባል የተረሳን ይመስላል። አምባገነን ስርዓቶች እየተፈራረቁ ለአደቀቁት የኢትዮጵያ ህዝብ ለመከራው መወገድ ፈርቀዳጅ የሚሆን ተስፋ ሲፈነጥቅለት ያንን ተስፋውን እንደሾተላይ ደርሰው የሚቀጩ ልጆች ከአብራኩ ማፍራቱን አላቆመም።
ያለፉትን ስድስት ዓመታት በህሊናችን ስንቃኝ ኢሳት ያልዳሰሰው አገራዊ ጉዳይ፣ያላጋለጠው የዘረኝነት ተንኮልና ዘረፋ፣ ያልቃኘው ኢትዮጵያዊ የህብረተሰብ ክፍል፣ ያላመላከተው የነገ ብሩህ ተስፋ ቢኖር በጣም ትንሽ ነው። ዛሬ እየተቀጣጠለ ላለው ህዝባዊ አመፅና ለወያኔ መፍረክረክ ኢሳት ከፍተኛ ድርሻ አለው። ለአምባገነቡ ስርዓት ፍፃሜ የመጨረሻዋን የመቃብር ላይ ቢስማር የሚመታውም ኢሳት እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ። ከዚያም አልፎ በሚፈጠረው አዲስ ስርዓት ኢትዮጵያ ዳግም በአምባገነን ስርዓትና በዘረኝነት ማዕበል እንዳትመታ ጠባቂ መልዐኳ ከሚሆኑት ተቋማት ኢሳት አንዱ እንዲሆን ዜጎች ሁሉ ተግተው ሊሠሩ ይገባል።
ባለፉት አርባ ዓመታት ኢትዮጵያ ለምትዳክርበት የፖለቲካና የድህነት አረንቋ ድርሻ የነበራቸው ወገኖች እንዲሁም ለተሻለ ነገ ገንቢ ሃሳብ አለኝ ያሉትን ኢትዮጵያውያን እንደ ኢሳት መድረክ ሰጥቶ ይደመጡና ይታዩ ዘንድ እድል ያመቻቸ ማንም የለም። በኢትዮጵያ ሁኔታ ቀላል የማይባል ሚና ካላቸው ያለስኬት ካረጁት እስከ አዲሶቹ ፖለቲከኞች በኢሳት ተስተናግደዋል። መኢሶኖች፣ ኢህአፓዎች፣ ኢሰፓዎች፣ ሻዕብያዎች፣ ከፖለቲካው የተለዩትና አሁን ያሉት ወያኔዎች፣ ብአዴኖች፣ ኦህዴዶች፣ ኦነጎች (የተለያዩ አንጃዎች ሳይቀሩ)፣ የቅንጅት ሰዎች፣ የመድረክ አባላት፣ መኢአዶች፣አረናዎች፣ ሰማያዊዎች፣ኦጋዴኖች፣ ሲዳማዎች፣ ጋምቤላዎች፣ አፋሮች እንዲሁም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የፅንፉን ፖለቲካ ጠርዝና ጠርዝ ይዘው የሚጎትቱ የሞረሹ ተክሌ የሻውና ጁአር ሞሃመድ ሳይቀሩ ላንቃቸውን የከፈቱትና መታወቅን ያገኙት በኢሳት መድረክነት መሆኑን ቢክዱ እንታዘባቸዋለን። በነገራችን ላይ ኢሳት ቢጋብዛቸው እንኳ ሊቀርቡ የማይልፈጉት የትናንት ወንጀላቸውና የዛሬ ሸማቂ ልቦናቸው ውስጥስር የሰደደ ዘረኝነት ድፍረት የነፈጋቸው ገብሩ አስራት፣ ስዬ አብርሃ፣ ፍስሃ ደስታን፣ ሃሰን አሊን የመሳሰሉ ናቸው።
ከፖለቲካው ውጭ ከያኒያን፣ ፈላስፎች፣ የታሪክ ሰዎች፣ ሃኪሞች፣ ኢኮኖሚስቶች፣ ወታደራዊ ጠበብቶች፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፣ አክቲቢስቶች በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ያለምንም ገደብ ሃሳባቸውን ለህዝባቸው ያሰሙበት መድረክ ቢኖር በኢሳት ነው።
በጋምቤላዎች ላይ የተካሄደውን የዘር ፍጅት፣ በሳውዲ፣ በየመንና በሊብያ በኢትዮጵያውያን ላይ የተፈፀመን ሰቆቃ ከእስር ቤት ውስጥ ሳይቀር የሚሰማውን ጩኸት፣ የአማራውን ከየክልሉ እየተመነጠረ መገደል፣ መዘረፍና መፈናቀል፣ የወልቃይትን እልቂትና አፈና ከትናንት እስከዛሬ፣ የኦጋዴንን ፍጅት በቪድዮና በቃለመጠይቅ አስደግፎ አቅርቧል፤ የሙስሊሙን ድምፃችን ይሰማ እንቅስቃሴ፣ የኦሮሞን ህዝባዊ ትግል፣ የአማራውን ተጋድሎ በመረጃ እያስደገፈ ከባለሙያ ትንተና ጋር በማቅረብ ኢሳት የሄደበትን ርቀት የተከተለው ሚድያ የለም ለማለት ያስደፍራል። የዘር ደዌ የሚያሰቃያቸው ትንንሽ ህልመኛ መሳፍንት ሌት ተቀን አጥብቀው የሚፈሩትና በስውርና በግልፅ የሚተናኮሉት ኢሳትን መሆኑ አይገርምም። እንደ የዓመትባል በግ ሻጭ ነጋዴ ህዝብን ግንባሩ ላይ ከሌላው መለያ ቀለም እየቀቡ “አንተ የእኔ ነህ፣ ያኛው የእነከሌ ነው” የሚሉ የትርፍ ሰዓት ፖለቲከኖችና ነጋዴዎች ከቶውንም ኢሳትንና ጋዜጠኞቹን በአገር ጉዳይ ደፍረው መጋፈጥ አይችሉም። እንዴት ተብሎ? እንደሌላው መማር፣ ኑሮ ማደላደል፣ ውድ ጊዜአቸውን ከልጆቻቸውና ከቤተሰባቸው ጋር ማሳለፍ ሲችሉ፤ በለጋ እድሜአቸው፣ በሚያሳዝን የገቢ መጠን እየተዳደሩ ራሳቸውን ለአገር መስዋዕት ያቀረቡ የኢሳት ጋዜጠኞችን ማሽሟጠጥና ስም ጠርቶ መስደብ፣ ኢሳት ሊረዳ አይገባውም ብሎ በአደባባይ ከመፏለል የበለጠ ወያኔነት የለም።
ቆምንለት የሚሉትን ዘር መያዣነት (ሆስቴጅ) አድርገው በአንድ በረት ውስጥ እንደገባ ከብት ከሌላው እንዳይገናኝ “የእኔ ብቻ ነው”ን የሚያቅራሩ ጠባቦች በስደት በሚኖሩበት አገር ከወንድሞቻቸው ጋር ቡና መጠጣት ተስኗቸው “ግደለው፣ ፍጀው”ን በርቀት ሲያውጁ አገርቤት ህዝቡ በአንድነት ተቃቅፎ ሞትና መከራን እየተጋራ መኖሩን የሚያሳውቀውን ኢሳትን ቢጠሉ አያስገርምም። ከሁሉም የሚያስገርመው ኢሳትን የአንድ ዞግ (የአማራ ወይም የኦሮሞ) ብቻ አገልጋይ እንዲሆን እነሱ ትንሽ ሆነው ሊያሳንሱት ማለማቸው ነው።
የኦሮሞን ጉዳይ ለመሸፈን የተቋቋመው ኦ ኤም ኤን ስሙ እንደሚያመለክተው በኦሮሞ ጉድይ ላይ ብቻ አተኩሮ ቢሠራ የሚስደንቅ አይደለም። በእርግጥ የኦሮሞ ህዝብ ከቀሪው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ጭቆናን ለማስወገድ ሆነ በዘላቂ የጋራ የሆነች አገር ለመገንባት የሚያግዝ ሃሳቦች ቢስተናገዱበት ራሳችውን ለትልቅ አላማ ማሰለፋቸውን ያረጋግጣሉ። ነገር ግን ፅንፈኛውን ሃሳብ የያዙ ብዙ ሰዎች ለኦሮሞውም ሆነ ለሌላው የማይጠቅም ሃሳባቸውን ያለምንም ገደብ ሲረጩ ይስተዋላል። ቀስ በቀስ የህዝቡ ፍላጎትና ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ወደሰከነና ወደተሻለ አቅጣጫ ያመጣቸዋል ብለው ተስፋ ከሚያደርጉት አንዱ ነኝ።
በቅርብ ጊዜ ደግሞ የአማራ ድምፅ የሚል ሬድዮ ተቋቁሞ ፕሮግራሞቹን እያሰራጨ ነው። እንደ ኦ ኤም ኤን ሁሉ አማራውን በተመለከት ለመዘገብ አላማ እንዳለው ስሙ ይናገራል። የአማራውን ሰቆቃና ስቃይ በዜና በቃለ መጠይቅና በልዩ ልዩ ፕሮግራሞች በእውነት ላይ ተመስርቶ ከሰራ ጥቅሙ ከፍተኛ ይሆናል። ነገር ግን ብዙውን ጊዜ ኦ ኤም ኤን ላይ እንደሚታየው ሌላ ፅንፍ የረገጡ ለአማራውም ሆነ ለቀሪው የኢትዮጵያ ህዝብ የማይጠቅም ሃሳቦችን የሚረጩ ወገኖች ያለገደብ ከፏለሉበት ትልቅ አደጋ ይሆናል። እነዚህ ሁለቱ ተቋማት ቆምንለት ለሚሉት ህዝብ ከልባቸው በቅንነት ከሠሩ ትልቅ አማራጭና የዴሞራሲ ዋስትና ይሆናሉ። ወደሚፈለገው አቅጣጫም እንዲያድጉ ድጋፍ መቸር የሚገባ ሲሆን ሲሳሳቱም ገንቢ የሆነ ትችት ሊቀርብባቸው ይገባል።
ኢሳት የኢትዮጵያ ህዝብ ዐይን፣ ጀሮና አንደበት ነኝ ብሎ ከማወጁ አልፎ ለየትኛውም ሳይወግን ሁሉንም ህዝብ ያማከለ ሥራ በመስራት ላይ መሆኑን አስመስክሯል። ከሁሉም ኢትዮጵያውያን ድጋፍና አድናቆትም እያገኘ ነው። ኢሳትን ካለመበትና ቃል ከገባለት ኢትዮጵያዊ ሥራ ለማደናቀፍ የሚፈልጉ ወገኖች ከላይ ያየናቸውን ተቋማት እየተጠቀሙ የሚያደርጉት ዘመቻ ሁሉም በአንክሮ እየተመለከትነው ነው። ለዴሞክራሲ በመደጋገፍ መስራት ለድል ያበቃልና እነዚህን ተቋማት የሚያንቀሳቅሱና የሚደግፉ ወገኖች ሊያስቡት የሚገባ ጉዳይ ይመስለኛል። እርስ በእርስ በመጠላለፍ ተቃዋሚዎች ሽባ ሆነው እንደቀሩት ሁሉ በሽታው የሚድያ ተቋማት ላይ እንዳይገባ ያሳስበኛል። በኦህዴዶችና በብአዴኖች አማካኝነት ህወሃት እጁን እያስገባ እንድሆነ ያልታያችሁ ካላችሁ ዐይናችሁን ግለጡ እላለሁ። ኢሳት አማራውን አላገለገለም እያሉ በባዶ ጩኸት አየሩን የሚበክሉ ያሉትን ያህል የኦሮሞውን ጉዳይ ጉዳዩ አላደረገም የሚሉ ከሌላው ጎን አቧራ ያስነሳሉ። የሁለቱም ወገን መልዕክት ኢሳት በነሱ ደረጃ ወርዶና ጠብቦ የአንድ ወገን አቀንቃኝ እንዲሆን በመፈለጋቸው እንጂ እንደ ኢሳት ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል አማክሎ በሚዛናዊነት የሚሰራ ተቋም እስካሁን አልገነባንም።
በመንደርተኝነት ኢትዮጵያዊነትን መሸፈን አይቻልም። ጠባብና አጥፊ ነውና።
ሌላውን በመጥላትና በወገንተኝነት አገር እንደማይገነባ ሩቅ ሳንሄድ ከወያኔ ዘረኛ ስርዓት ተምረናል።
በትናንት አስከፊ ታሪካችን የዛሬ ህይወታችንና የነገ ተስፋችን ሊጨልም አይገባም። አገር የሚገነባው ከትናንት ተመክሮ ተነስቶ ወደ ፊት በማየት እንደሆነ ደቡብ አፍሪካ አስተምራናለች።
የትናንት ታሪካችን ሳይሸፋፈን እየተፈተሸ እውነቱ ቢወጣ መማርያችን እንጂ ለሸማቂና ሸፍጠኛ ፖለቲከኞች ሰለባ ሊያደርገን አይገባም። በመካሄድ ላይ ላለው ህዝባዊ ትግል መጠናከርና ለድል መብቃት ኢሳትና ሌሎችም ሚድያዎች የሚጫወቱት በጎ ሚና መበረታታት አለበት። መቶ ሚሊዮን ለተጠጋው የኢትዮጵያ ህዝብ ከአስር በላይ ኢሳትን የመሰሉ ጠንካራ ተቋማት ያስፈልጉታል። ማድረግ ያለብንም ይህንን እንጂ አንድና ብቸኛ ኢሳትን ማዳከም አይደለም።
ይህንን እንድፅፍ ወደ አስገደደኝ ጉዳይ ልመለስ። ሰሞኑን ኢሳት ከፕሮፌሰር ኃይሌ ላሬቦ ጋር ባደረገው ቃለመጠይቅ ምክንያት የተነሳው ጫጫታና ኢሳት ላይ ያነጣጠረው ዘመቻ ከሁሉም የፅንፍ ኃይሎች መሆኑ የአላማቸውን አንድነት የሚያመለክት ሆኗል። ኢሳት እንደሚድያ ተቋም ባለፉት ስድስት ዓመታት ከላይ በከፊል ለማሳየት የሞከርሁትን ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳይ ሁሉ ሽፋን ሲሰጥ ኖሯል። በተመሳሳይ ሁኔታ ከወዳጅም ድጋፍ፣ ከተቆርቋሪም እርማት፣ እንደጠላት ከሚቆጥሩትም ዘለፋና ጥቃት ደርሶበታል። ጋዜጠኛ ወንድማገኝ ጋሹ ከለንደን ፕሮፌሰር ኃይሌ ላሬቦን ከአቀረበ በኋላ በፕሮፌሰሩ፣ በኢሳትና በወንድማገኝ ላይ ከጽንፈኛ ወገኖች የተከፈተው ዘመቻ ስህተት ካለ በቀናነት እንዲታረም የሚጋብዝ እንቅስቃሴ ሳይሆን ፀጥ ለመሰኝት የታለመ ፀረ ዴሞክራሲ እንቅስቃሴ እንደሆነ ጎልቶ እየታየ ነው። ይህ አስተያየቴ በቅንነት ስህተቶች ኢንዲታረሙ የሚተጉ ኢትዮጵያውያንን አይመለከትም። እንዲያውም ሊበረታቱ ይገባል። ኃይሌ ላሬቦ ያቀረቧቸው ጭብጦች እውነትነት ከሌላቸው ሃሳባቸውን በሃሳብ ለመርታት ተዘጋጅቶ መቅረብ የእውነተኛ ምሁራን ስራ ይሆናል። ኢሳትም ለእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ መድረኩን ክፍት አድርጎ ማስተናገድ የሚዲይው ስነምግባርና አገራዊ ኃላፊነቱ ያስገድደዋል። ከዚያ በዘለለ ኃይሌ ላሬቦን የመሰሉትን ምሁራንና ኢሳትን ዝም ለማሰኘት አልሞ መንቀሳቀስ ትልቅ ወንጀል ብቻ ሳይሆን የቡድኑን ተሸናፊነት የሚያሳይ ነው። ክሽፈትን።
ይህ እውነትን ለማፈን የሚደረግ እሩጫ፣ ጠባብና አደገኛ አካሄድ ዛሬ አልተጀመረም። ከአስራ ስምንት አመት በፊት በጦብያ መፅሄት ላይ ጽሁፉን እንድናወጣለት ከአውሮፓ ዛሬ ስሙን የረሳሁት ሰው ላከልን። ኢዲቶርያል ቦርዱ ለሳምንት ተወያየንበት። የኦሮሞን ጉዳይ ለፖለቲካ ዓላማ የሚጠቀሙ በርካታ ወገኖች ስለአሉ በተገቢውና ሚዛናዊ በሆነ መልክ ማስተናገድ የምንችል መሆኑን መገምገም ነበረብን። ከሰውየው የተለየ ሃሳብ ያላቸው ካሉ በተለይም ከኦሮሞዎች መካከል ስንጠይቅ ዶክተር መረራ ጉዲና ፈቃደኛ ሆኑ። የሰውየውን መጣጥፍ ለህትመት ካበቃነው በኋላ ከራሱ ከፀሃፊውና ከዘር ፖለቲካ አራማጆች ሳይቀር ድጋፉ ጎረፈልን። በቀጥዩ ወር የዶክተር መረራን ፅሁፍ ስናወጣ ድጋፉ ከሌሎች እንደቀጠለ ሆኖ በኦነግ ዙርያ ያሉና ሌሎችም የዘር ፖለቲካ አቀንቃኞች ዛሬ በፕሮፌሰር ኃይሌና በኢሳት ላይ እንደተከፈተው ዓይነት ዘመቻ አየሩን ሞሉት። ኃይሌ ላሬቦ ከስራቸው እንዲወጡ ፔቲሽን እንደተፈረመው ለጦቢያ ባልደረቦች በተለይም በጊዜው አዘጋጁ ለነበርሁት “እንገድልሃለን” ማስጠንቀቅያ በስልክ ሁለት ሳምንት ሙሉ ደርሶናል። “መግደል የፈሪና የተሸናፊ ስልት ነው፣ የተለየ እውነት ካላችሁ መድረኩ ክፍት ነው። ተጠቀሙበት። መሞት የሚገባን ከሆነ ደግሞ ወያኔም ለመግደል እያስፈራራንና እያሰረን ስለሆነ ለሙያውና ለአገራችን የምንከፍለው ክብር ያለው መስዋዕት ይሆናል” እያልን መልሰንላቸዋል። አንዳቸውም ደፍረው አልመጡም። ይልቁንስ ይመቸናል ባሉት ኡርጂ ጋዜጣ ይዘልፉን ነበር። መረራ ላይ የደረሰባቸውን ራሳቸው ቢናገሩት ይሻላል። የመረራ ትችት ግን ጊዜውን የጠበቀ በመሆኑ ብዙ ኢትዮጵያውያንን በተለይም ብዥታ የነበረባቸውን ጭፍን የኦነግ ደጋፊዎችን ሳይቀር አስተምሯል። ኦነግም እንደወትሮው በአባሎቹ ሆነ በሌላው ስሜት ላይ መጋለብ ሳይችል ቀረና ራሱን እንዲመረምር ተገደደ።
በፕሮፌሰር ኃይሌ ላሬቦ፣ በወንድማገኝ ጋሹና ኢሳት ላይ የሚደረገው ዘመቻ ዝም ለማሰኘት ከሆነ የከሸፈ የደካሞች መንገድ ነው። ኃይሌ ላሬቦ ባቀረቡት ኢንተርቪው የተሳሳተ መልዕክት ካለ ለማረም የሙያ ግዴታ አለባቸው። ሆነ ብለው የማይገባ ስህተት ተናግረው ከሆነ የኦሮሞውን ህብረተሰብ ሳይሆን ራሳቸውን ነው የሚጎዳው። ታሪክን የመሰለ የሰው ልጅ ትልቅ ሃብት ግለሰብ ሆነ ቡድን በባለቤትነት ሊይዘው አይችልምና። እውነቱን አደባባይ ማውጣት የሁሉም ግዴታ እንጂ የተወሰኑ ሰዎች ወይም ቡድኖች ብቻ ሃላፊነት አይደለም። ጋዜጠኛ ወንድማገኝና ኢሳት ድክመታቸውን እያረሙ የኢትዮጵያን ህዝብ ለማገልገል ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው። ያንን ሃላፊነት ሲያጕድሉ የሚቀጣቸው ህዝቡ እንጂ ራሳቸውን የኮፈሱ ጋንጎች አይደሉም። ኢሳት ለኦሮሞ ህዝብ ትልቅ ከበሬታ እንዳለው በሥራው እያሳየ መሄዱ ያንገበገባቸው መንደርተኞች ጫጫታ ጊዜአዊ ነው። በርካታ የኦሮሞ ምሁራንና ፖለቲከኞች ከዚህ በፊት ኢትዮጵያዊ አግኝቷቸው በማያውቀው ደረጃ ሃሳባቸውን እንዲያካፍሉ በመደረጉ ትልቁ ብዥታ እየጠራ ኢትዮጵያን በጋራ የመገምባቱ ሃሳብ መሰረት እየጣለ መሄድ ላይ መሆኑ በጣም ፅንፈኛ ለሆኑና ለወያኔዎች አልተመቸም ስለሆነም ዘመቻው በጋራ የሚያደርጉት እየመሰለ ሄዷል። ፕሮፌሰር ህዝቅኤል ጋቢሳ የኢሳት ቤተኛ እንድሆኑ ደጋግመን አይተናቸዋል። በሚያቀርቡት የሳሳባቸው ግልፅነትና ድፍረት የማደንቃቸው ናቸው። የተሳሳተ ታሪክ ተነግሯል ካሉ እውነተኛ ታሪኩ ብለው የሚያውቁትን በመረጃ አስደግፈው ለመናገር ሙያውም ይፈቅድላቸዋል። ታሪኩ ባልተነገረበት ኦሮሞ ሚድያ ኔትወርክ ላይ አንድ አይነት ሃሳብ ካላቸው ሰዎች ጋር ብቻ ሄደው ያደረጉት ውይይት ዓላማውን የሳተ ይመስለኛል። ኢንተርቪውን የተከታተለው የኢሳት ታዳሚ እስከሆነ ድረስ ማስተባበል ሆነ ማሳረም የሚቻለው ከኢሳት የተከታተለውን ህብረተሰብ ነው። ሌላ አድማጭና ተመልካች ተፈልጎ የተሄደ ከሆነ ይህ ምሁራዊና ሙያዊ አካሄድ ሳይሆን ፕሮፓጋናዳ ነው የሚሆነው። ኢሳት መድረኩን ነፍጓቸው ከሆነ እንወቀውና ከስነምግባር አንፃር እንሞግተው። በዚህ ወቅት ኢሳት ላይ መቅረቡን የሸሹት “ኮሚኒቲያቸውን” ፈርተው ከሆነ ህዝብ የሚያከብራቸውና የሙያቸውን ስንምግባር የሚያስጠብቁት እውነትን ይዞ በመጋፈጥ መሆኑን መንገር ግድ ይለናል። ጦቢያ ላይ ለተስተናገደ ጉዳይ ኡርጂ ላይ እንደመሸገው ወንድማችን የኦሮሞ ሚድያ ኔትወክን ፈልጎ መሄድ እውነትን በእውቀት መሞገት አይደለም።
አንዳንድ የዋህ ወዳጆቼ ኢሳት ይህንን ለመዘገብ ጊዜው አይደለም ይላሉ። መቼ ነው ጊዜው? የሚዘራው እኩይ ፕሮፓጋንዳ ፍሬ እስኪያፈራና ዘረኞች እንደወያኔ በህዝብ ራስ ላይ ወጥተው እስኪጋልቡ ነው? ኢሳት ሆነ ሌላው ሚድያ ለነገ የሚያስቀምጡው እውነት ሊኖር አይገባም። በተለይም አገርንና ህዝብን በተመለከተ ጓዳ ውስጥ የሚውጠነጠንን ሁሉ አደባባይ ማውጣትና ማሳወቅ የሚድያ ትልቁና ዋና ሥራ ነው።
ኢትዮጵያን የመሰለች የረጂም ጊዜና ውስብስብ ታሪክ ያላት አገር ይቅርና በቅርቡ ብቅ ያሉ አገራት ባለፈ ታሪካቸው ይህ ነው ብለው የሚቋጩት፣ ያለቀ፣ ከስህተት ተፀዳ፣ ፍፁም የሆነ ታሪክ የላቸውም። በየጊዜው በምርምር የሚገኘውን እየፈተሹ እያዳበሩ አገር በመገንባት ላይ ነው የሚያተኮሩት።
የኛ የፖለቲካ ጋንግስተሮች ታሪክ ለጠባብ ፖለቲካ አላማቸው እስካልጠቀመ ድረስ ደንታ የላቸውም። ለመሆኑ የኢትዮጵያ ታሪክ ከምኒልክ ይጀምራል ያላቸው ማን ነው? እነሱ ተቀበሉትም አልተቀበሉት ኢትዮጵያ እንደበርካታ የዓለም ሃገራት ስትወድቅ ስትነሳ፤ ስትሰፋና ስትጠብብ፤ በዚህም ህልውናዋ ህዝቧ ሲጣላ ሲፋቀር፣ ሲጋባ ሲዋለድ፣ ሲፈልስና ሲዋሃድ የኖረ የብዙ ሺስ ዘመን ውጤት ነው። የሩቁን እንተውና ከክርስቶች ልደት ወዲህ ያለውን ብንመለከተው ንጉሥ ኢዛና ኑብያና መርዌ ድረስ ሲዘምትና ሲያስገብር እዚያ ደረጃ ያደረሰውን አቅም ያጎለበተው ዛሬ በየጎጡ ካለንበት ከተገኙ አባቶቻችን ጉልበትና ንብረት መሆኑን ማገናዘብ እንዴት ያቅተናል? ካሌብ ቀይባህርን ተሻግሮ የመን ድረስ ሲገዛ አፋር፣ ሶማሌ፣ ሲዳሞ፣ ጠቅላላ ደቡቡና ሰሜኑ ከእጁ አልነበሩም ብሎ የሚሞግት ሰው አለ? የአክሱምን ኃያልነት የተፈታተኑት የዮአዲት፣ የአገዎችና የሌሎችም ዘመቻዎች የህዝቡን ከታች ወደላይ፣ ከላይም ወደታች መቀላቀል እንዴት ያግደዋል? አምደፅዮን ዘርዐ ያዕቆብ ሶማሌን ይፋትን ደዋሮን ባሌ ድረስ ዘልቀው ግዛት ሊያሰፉ የዘመቱት የመደራቸውን ሰዎች ብቻ ይዘው ነው እንላለን? በኢትዮጵያ ጠረፍ ያሉት አሚሮች፣ ሱልጣኖች፣ አዳሎችና ሶማሌዎች ሲደክሙ በመገበር ሲጠነክሩ ደግሞ በመጋፋት መሃል ገብተው ሲያስገብሩና ሲቀላቀሉ የሚካሄደው የህዝብ ፍልሰትና ውህደት አይታየንም? ማንም ሊክደው የማይቻለው የአህመድ ኢቭን ኢብራሂም ኤል ቃዚ (የግራኝ መሃመድ) ዘመቻ መላ ኢትዮጵያን ሲያዳርስ የተፈፀመውን የህዝብ ውህደት እንዴት ነው የምናየው?
በግራኝ መሃመድ ዘመቻ የተዳከመውን ማዕከላዊ አስተዳደር ክፍተት በመጠቀም ከደቡብ የተንቀሳቀሰው የኦሮሞ ህዝብ ፍልሰትና መዋሃድ መላ ኢትዮጵያን አላዳረሰም ብሎ ማን ይክዳል? በዚህ ከባሌ ተነስቶ በተደረገ መስፋፋት ወቅት ደቡብ ውስጥ የነበሩት በርካታ ማህበረሰቦች ሲዳማ፣ወላይታ፣ ከምባታ፣ ሃድያ፣ ጉራጌ፣ ጃንጂሮ፣ ወዘተ ሳይዳጡ፤ ሰሜን ደግሞ ሸዋ ወለጋ፣ ጎጃም፣ ወሎ፣ ጎንደርና ትግራይ ዘልቆ የኦሮሞ ህዝብ ሲደርስ አማራው፣ አገው፣ ሽናሻው፣ ጉምዙ፣ ጋፋቱና ትግሬው ሳይጨፈለቅ፣ ሳይገደል፣ሳይገብርና ማንነቱን እንዲቀይር ሳይገደድ የተደረገ ዘመቻ ነው ብሎ ሊነግረን የሚደፍር ማን ነው? በዘመነ መሳፍንት ጊዜስ እያንዳንዱ መስፍን አቅሙ በፈቀደው ግዛቱን ሲያሰፋና ሲያጠብ ህዝብ ከቀየው አልተፋለሰም? አልሞተም? የነበረው እንዳልነበረ አልሆነም? የምኒልክ አያትና አባት ሳህለስላሴና ሃይለመለኮት በሁሉም አቅጣጫ ግዛታቸውን ለማስፋት እስከተቻላቸው ተግተዋል። ዘመነ መሳፍንት እንዲያከትም ፈር የቀደዱት አፄ ቴዎድሮስ ትግሬን ወሎን ጎጃምንና ሸዋን ያስገበሩት ሰይፍ ይዘው፣ እየቆረጡም፣ እየገደሉም፣ እየሞቱም ነው። አፄ ዮሃንስ ከአፄ ቴዎድሮስ የተለየ አላደረጉም። ንጉሥ ተክለሃይማኖት እስከ ከፋ ግዛቴ ነው ሲሉ፤ አፄ ምኒልክ ቀደምቶቻቸው የጀመሩትን ግዛት ያውም አፍሪካን ለመቀራመት ከዘመቱ የምዕራባውያን ወራሪ ኃይል ጋር እየተናነቁ፣ ሲጋፉ በታሪካችን እንዳሳለፍነው የጦርነት፣ የፍጅት ዘመቻ አድርገው አገር አቀኑ እንጂ ከአባቶቻቸው ተለይተው በዴሞክራሲ ገዙ ብሎ የሚሞግት አንድም ኢትዮጵያዊ የለም። በዘመነ ኃይለስላሴም በጣልያን ወረራና በተፈጥሮ አደጋ ሰፊ የህዝብ መፍለስ ተፈፅሟል። የትግራይና የወሎ ህዝብ በተደጋጋሚ ድርቅ ምክንያት ቀየውን ለቆ ጎጃም፣ ወለጋና ደቡብ በመስፈር ህይወቱን አትርፏል። በደርግ ጊዜ በሶማሌ ወረራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከሶስት መቶ ሺህ የበለጠ ገበሬ ከመላ አገሪቱ ተመልምሎ ሰልጥኖ ሲዘምት፣ ለበርካታ ዐመታትም በኤርትራና በትግራይም ሰፍሮ በጦርነቱ የተፈጠረውን ህዝባዊ ፍልሰትና መዋሃድ በዐይነ ህሊና ልንቃኝ ይገባል። በድርቁም የተጠቁትን የትግራይ፣ የወሎና የከምባታን ህዝብ በጎጃም ፓዌ በወለጋ በጋምቤላና በሌላም ለም መሬቶች አስፍሯል። በወያኔ ደግሞ ሰው በዘሩ እየተመነጠረ አማራ የተባለ ሁሉ ከበርካታ አካባቢዎች ሃብቱ እየተዘረፈና እየተገደለ እንዲፈናቀል ሲያደርግ ትግሬው ደግሞ ከተሞችንና ለም መሬቶችን እንዲቆጣጠር በሰፊው ተሰርቷል። ወልቃይት፣ ጋምቤላ፣ ደቡብ፣ ቤንሻንጉል፣ አዲስ አበባና ሌሎችም ቦታዎች የሚካሄደውን ወረራና ዘረፋ በየቀኑ የምንሰማው ነው።
ለብዙ ሺህ ዓመታት ነፋስ እንደሚገፋው ማዕበል ህዝቡ ከምስራቅ ወደ ምዕራብ፣ ከደቡብ ወደ ሰሜን፤ ከሰሜንም ወደ ደቡብና ምስራቅ በጦርነትና በሰላም ሲገማሸር፣ ሲቀላቀል፣ ሲዳዳጥና ሲጨፈላለቅ ብሎም ሲዋሃድ መኖሩ ይታወቃል። ከታሪካችን እንደምናስተውለው የኢዛናን፣ የካሌብን፣ የዮዲትን፣ የአምደፅዮንን፣ የግራኝን፣ የኦሮሞን መስፋፋት፣ የቴዎድሮስን፣ የዮሃንስን፣ የምኒልክን የኃይለስላሴን ኃይል እየተከተሉ በየቦታው የተዛነቁትን አያቶቻችንን ታሪክ ወደ ኋላ ብንቃኝ ማን በየትኛው ጊዜ ግፍ ፈፃሚ እንደነበር በትክክል ለማየት ከዘረኝነትና ከጠባብ የፖለቲካ ጥቅም ፀድቶ መገምገምን ይጠይቃል።
የገደለው ባልሽ
የሞተው ወንድምሽ፤
ሃዘንሽ ቅጥ አጣ
ከቤትሽም አልወጣ።
እንደተባለላት የአለፈ ታሪካችን ላይ ሲፈፀም የኖረው በጎና ክፉ ነገር የጋራችን መሆኑን መቀበልና ወደፊት መራመድን ይጠይቃል። ከዚያም፤
የተሻረው ባሌ ተሿሚው ወንድሜ፤
ምን እናገራለሁ ከዚህ መሃል ቁሜ።
እንዳለችው አልቃሽ ያለፈ ታሪክ ውጤታችንን በፀጋ ተቀብለን የቀደም ስህተቶች እንዳይደገሙ ተግቶ መሥራት መፍትሄ ይሆናል። ያለፈውን ታሪክ እዳ በቦታውና በጊዜው ያልነበረ ትውልድ እንዲከፍል በመጠየቅ የምናባክነውን ወርቃማ ጊዜና አቅማችንን አገርን ከአምባገነን ስርዓት ለማስወገድና ዴሞክራሲ ለማስፈን ብናውለው ይበጀናል።
“በሴት አያቶቻችን በር ማን እንዳለፈ እነሱ ብቻ ናቸው የሚያውቁት” የሚለውን እውነት ማን እንደተናገረ ረሳሁ። በየአንዳንዳችን ደም ሥር ውስጥ የብዙ ኢትዮጵያውያን ነገዶችን ዲ ኤን ኤ የያዘ ደም ነው በመላ ሰውነታችን የሚመላለሰው። ኢትዮጵያዊነት ብዝሃነትን በአንድነት ያካተተ ውበት ነው። ቋንቋ ዘርን እንደማያመለክት በስደት ዓለሙ ያላችሁ ቋንቋችሁን የማይችሉ ልጆቻችሁን ያሳደጋችሁ ሁሉ ጥሩ ምስክሬ ናችሁ። ለዚህም ይመስለኛል መጽሃፍ ቅዱስ በትንቢተ ኤርምያስ 13፡ 23 ላይ “በውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን ወይስ ነብር ዝንጉርጉርነትን ይለውጥ ዘንድ ይችላልን?” ያለው። አዎ የኢትዮጵያውያንን የዘር ብዝሃነት ክደው ስለዘር ንፅህና የሚሰብኩን እንደሂትለር ለክፉ ዓላማ ለማዋል እንጂ እናውቅለታለን ለሚሉት ህዝብ ደህንነት አለመሆኑ ግልፅ ነው።
በሶሻል ሚድያና በአየር ላይ አካፋና አዷማ ይዘው ታሪክ የሚቆፍሩ መናኛዎችን መምከር ካለብን ያለፉት አባቶቻችን በጊዜአቸው በመሰላቸው ኑረው አልፈዋል። ከሞቱበት አትቀስቅሷቸው። ልጆቻቸውን የሚገድል ስርዓት እንዲኖር እየደገፋቸሁ ለሞቱት አባቶቻችን ታሪክ ትቆረቆራላችሁ ብለን አናምንም። ራሳችሁ ከሞታችሁበትና ከገባችሁበት የዘረኝት አረንቋ ውጡና ዓለምን ተመልከቱ፣ ቤተሰቦቻችሁን ጠይቁ፣ የሚፈልጉት ፍትህ ነው፣ ሰላም ነው፣ ከጎረቤትና ከሃገሩ በሰላም በፍቀር መኖርን ነው። እያደቀቃቸው ያለው የዘረኝነት ጫማ ጥርሱ አልቆ ሊወገድ ትንሽ ሲቀረው የእናንተን አዲስ አንጓው የበዛ የዘረኝነት ጫማ ተክቶ እንዲረግጣቸው አይፈልጉም። ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና እንዳሉት የታሪክ ሂሳብ ማወራረድ ይቅር። ማንም አትራፊ አይሆንም። አሁን ላለንበት ውድቀት የሁላችንም ድርሻ አለበት። ታሪክን ለታሪክ ነቱ ትተን ህዝባችንና አገራችንን ወደፊት እናራምድ።
ከሁሉም በላይ ለሚደረገው ህዝባዊ ትግል ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ የሚገኙ የመገናኛ ብዙሃንን በተለይም ኢሳትን ኢላማ ያደረጉትን ኃይሎች መቋቋም ያስፈልጋል። ማንም ኢትዮጵያዊ ሃሳቡን በነፃነት በመግለፁ ጥቃት ሊደርስበት አይገባም። ምሁራንም በግላቸው ዘለፋ ይደርስብናል ብለው ለአገርና ለወገን የሚጠቅም እውቀታቸውን ከማካፈል ወደኋላ ማለት የለባቸውም። ሚድያዎችም ለህዝብ፣ ለአገርና ለእውነት መታመን እንጂ ለጠባብ ቡድኖች መጠቀሚያ እንዳይሆኑ ሁለንተናዊ ድጋፋችን አይለያቸው።

Montag, 6. Februar 2017

ወያኔ የመጨረሻውን እርሾ በመጋገር ላይ ነው (መስቀሉ አየለ)

ወያኔ የመጨረሻውን እርሾ በመጋገር ላይ ነው
መስቀሉ አየለ
ወያኔ እንደ አንድ የፖለቲካ ሃይል የፖለቲካ ሞቶዋል።ኢህአዴግ የተባለው የማደንጋሪያ ጭንብል ወልቆ ከወደቆ ሰንብቶዋል። የቀረው ነገር የግዜ ጉዳይ እንደሆነ የገዛ ሰውነቱ ነግሮታል። በየቦታው የሚታየው መተራመስ ሁሉ ሌላ ምክንያት የለውም። በዚህ ሂደት ውስጥ ወያኔ የቀረው አንድ ያልተሞከረ ነገር ቢኖር በራሱ ላይ መፈንቅለ መንግስት አድርጎና ጃኬቱን ቀይሮ በአዲስ መልክ መቅረብ መሆኑን ካሁን በፊት ባቀረብኩት አንድ የዳሰሳ ጥናት ላይ ለመግለጥ ሞክሬ ነበር። ይኽ መላምት እውነት እንደሆነ ከመቸው ግዜ በላይ አሁን ግልጥ ሆኖዋል።
የሃይል አሰላለፉ ምን ይመስላል።
በሶስት አንጃ ተከፍሎ የነበረው የህወሃት የሃይል አሰላለፍ አሁን ወደ ሁለት የወረደ መሆኑን ልብ ማለት ይገባል።ይኸውም፤
፩ የባለፈውን ሰሞን ህዝባዊ አመጽና አሁን በአመዛኙ ጎንደርና ጎጃምን ያካለለውን ህዝባዊ ተጋድሎ ትከትሎ በአስቸኩዋይ አውጁ ስም ስልጣኑን እያጠናከረ የመጣው በሳሞራ የሚመራው የመከላከያ ሃይልና የወታደራዊ ደህንነቱ ክፍል ነው። አባይ ወልዱና የትግራዩ ሚሊሻ ሙሉ ለሙሉ ለዚሁ አንጃ እጅ የሰጠ ሲሆን ይኽ ሓይል ከግዜ ወደ ግዜ ጡንቻው እየፈረጠመና አድማሱን እያሰፋ መስመሩንም ወደታች እየዘረጋ በመሆኑ ከፖለቲካው አመራር ጋር ከፍተኛ ፍጥጫ ውስጥ መግባቱ በደንብ የተስተዋለ ነገር ነው።
፪ የህወሃት የፖለቲካ ልሂቃን ብለው እራሳቸውን የሰየሙት የነአባይ ጸሃየ ደብረ ጾዮን የመሳሰሉት አከላት ደግሞ ሙሉ ለሙሉ በሙባል ደረጃ አሰላለፋቸውን የሴኪዩሪቲውን ሃይል ከሚዘውረው ከጌታቸው አሰፋ ጋር ያደረጉ ሲሆን የቀድሞዎቹ አፈንጋጮች የተባሉት እና ውስጥ ውስጡን እግራቸውን ለመዘርጋት የማርያም መንገድ ሲፈልጉ የኖሩት እነ ጻድቃን፣ ሰዬ አብራሃ፣ ስብሃትና አበበ ተክለሃይማኖት የመሳሰሉትም ከዚሁ ከጌታቸው አሰፋ ጋር መጠለያ ማግኘታው ሲታወቅ ይህ ቡድን በዋናነት የውጭ መንግስታት በተለይም የአሜሪካና የእንግሊዝ መንግስታትን የፖለቲካ ድጋፍ ያገኘ ነው።
በጥቅሉ ይኽ ለሁለት የተከፈለው የህወሃት አሰላለፍ መሃላቸውን ያለውን ልዩነት ለማጠብብ የሚያስችል አማካኝ መንገድ ሊገኝ ስላልቻለ ቅራኔው ከግዜ ወደ ግዜ እየሰፋና ሊታረቅ ወደ ማይችልበት ቀውስ ውስጥ እያመራ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ችግሩ ወዲህ ነው። እነዚህ ሁለት አካላት ያላባቸው ቅራኔ ሊፈታ እንደ ማይችል ግልጽ በሆነበት በዚህ ሰዓት የሳሞራ አንጃ በኮማንድ ፖስቱ ሽፋን መዋቅሩን ወደታች ለመዘርጋት የሚያደርገው ሙከራ የፖለቲካውንና የደህንነቱን መዋቅር ሙሉ በሙሉ በማንሳፈፍ ለመፈንቅለ መንግስት እያመቻቻቸው እንደሆነ እራሳቸው እነ አባይ ጸሃይ አያጡትም። ነገር ግን መፈንቅለ መንግስቱ ቢካሄድ በቀጣዩ ምን ሊከስት ይችላል የሚለውን ነገር ግን ከግምት በላይ መሄድ ይቻላል።
ይኽውም መፈንቅለ መንግስት ለማካሄድ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ማእከላዊነት ያለው (በአንድ ኮማንድ ሴንተር የሚመራ) አንጻራዊ በሆነ መልኩ ተቁዋማዊ ቅርጽ ያለው የወታደራዊ እና የፖለቲካ አድርጃጀት ሊኖር ግድ ይላል። ነገር ግን ዘረኝት እንደጋንግሪን ውስጥ ውስጡን በልቶ የጨረሰውና በዘረፋ ቅሌት በስብሶ እርስ በራሱ ለመበላላት ተፋጦ የቆመ ሃይል ባለበት፣ አገሪቱን ለመምራት ይጥቀምበት የነበረው የዘር ፖለቲካ ውልቅልቁ ወጥቶ ህዝባዊ ማእበሉ እንደ አሬራ ሊንጠው በተቃረበበት ፣ የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የሃይል አሰላለፍ መልኩን ቀይሮ ከሰሜን ሶማሊያ እስከ ደቡብ ሱዳን የግብጽ ወታደራዊ ሃይል መሰረት እየጣለ በመጣበት ሰዓት፣ እስከ ዛሬ ድረስ ተንጠልጥሎ የቆየባቸው አሜሪካና እንድሊዝ በትራምፕ ወደ ስልጣን መውጣትና የእንግሊዝን ከአውሮፓ ህብረት መውጣት የራሳቸውን ፖለቲካ መስቀለኛ መንገድ ላይ በቆመበት ሰዓት የሚካሄድ መፈንቅለ መንግስት የትግራዩ ገዥ ጉጅሌ መጨረሻው እንደ ዳይኖስረስ እራሱን በራሱ እንዲበላ በር ከመክፈት ውጭ ሌላ ፋይዳ የለውም። በጣም አስገራሚው ነገር ግን ይኽም ሁሉ ችግር እያለ ወያኔ ግን ከውጩ ይልቅ የውስጥ ቅራኔውን ማስታረቅ የሚችልበት ግዜም, ጉልበትም, ጥበብም, አደረጃጀትም ስለሌለው ይኽን በደም ጎርፍ የሚጠናቀቅ መፈንቅለ መንግስት ላለማድረግ መብትም አቅምም የለውም።

Mittwoch, 1. Februar 2017

በእስር ላይ የሚገኙት ጋዜጠኞቹ ኤልያስ ገብሩ እና አናኒያ ሶሪ በዛሬው እለት ካሉበት ቦታ ይህን መልእክት ልከዋል።

በእስር ላይ የሚገኙት ጋዜጠኞቹ ኤልያስ ገብሩ እና አናኒያ ሶሪ በዛሬው እለት ካሉበት ቦታ ይህን መልእክት ልከዋል።
ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ፡- ባንኪ ሙን [Antonio Guterres]
በአፍሪካ ህብረት የአሜሪካ አምባሳደር ፡- ……………………
በአንድ ሉአላዊ ሀገር ውስጥ፣ ሕዝብና መንግሥት የሚግባቡበት ጤናማ ግንኙነት እንዲኖራቸው የህግ እና ህገ-መንግሥታዊ ሥርዓት መኖሩ ቀዳሚው መሠረት መሆኑ ይታመናል፡፡ በህግ አግባብ ሥርዓትን ተከትላ የምትተዳደር ሀገርም ወደ እድገትና ብልፅግና በሂደት መሸጋገሯ አይቀርም፡፡ ከእዚህ በተቃራኒው የሚጓዙ ሀገራት ደግሞ ችግርና መከራዎቻቸው ተዘርዝረው አያልቁም፡፡
መስከረም 28 ቀን 2009ዓ.ም በሀገራችን ኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለስድስት ወራት ‹‹እንደ አስፈላጊነቱ ተፈፃሚ ይሆናል፡፡›› በሚል ‹‹በአፌድሪ መንግሥት መውጣቱ ይታወቃል›› የአዋጁ መውጣትም የሀገሪቱ ሰላምና ደህንነት ተናግቶ አደገኛ ደረጃ ላይ መድረሱን እንደሚያሳይ መንግሥት በወቅቱ ገልፆ ነበር፡፡ ነገር ግን አዋጁ ከመሠረታዊ የሰብዓዊ መብቶችና ከህገ-መንግሥታዊ ድንጋጌዎች ጋር ይጋጫል፡፡ በተለይም የመረጃ ልውውጥን ፣ በነጻነት የማሰብ ተፈጥሮአዊ እና ህገ-መንግሥታዊ መብቶችንና የመረጃ ምንጮችን የመከታል መብቶችን ሙሉ በሙሉ ይጨፈልቃል፡፡ ከሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችም ጋር በግልፅ ይጻረራል፡፡
በኢፌድሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 29 ላይ ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ተደንግጓል፡፡ ይህንን ህግ በአግባቡ እና ኃላፊነት በተሞላበት መልኩ በመጠቀም እኛ ስማችን ከታች የተገለፀው ኢትዮጵያዊያን የነፃ ሀሳብ አራማጅ ጋዜጠኞች፤ ላለፉት ከ6-8 ዓመታት ለሚሆን ጊዜ በነፃው የህትመት ሚዲያው ዘርፍ፣ ለበርካታ ጋዜጠኞችና መጽሔቶች ላይ በምናከብረው ሙያችን ሥንሰራ ነበር፡፡ ዘርፉ በበርካታ ችግሮችና ተግዳሮቶች የታጠረ መሆኑ ሳይዘነጋ! 

ከጥቅምት ወር 2008ዓ.ም ጀምሮ ‹‹ በአዲስ አበባ ዙሪያ በኦሮሚያ ክልል ያሉ ልዩ ዞኖች በአዲስ አበባ ከተማ ማስተር ፕላን ሥር ይካተቱ›› የሚለው የመንግሥት ዕቅድ በኦሮሚያ ክልል ታላቅ ህዝባዊ ተቃውሞን ማስነሳቱ የሚታወስ ነው›› እኛም ይህን ህዝባዊ ተቃውሞ በወቅቱ ተጋግዘን እናዘጋጅበት በነበረው ‹‹አዲስ ገጽ›› መጽሔት www.addisgetsh.com
 ላይ በተለያየ የአቀራረብ ሙያዊ ዘዴ፤ በተከታታይ ሰፊ ሽፋን በመስጠት ለንባብ ስናበቃ ነበር፡፡ ከኦሮሚያ ተቃውሞ ጋር በማያያዝ በአሁኑ ወቅት በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው ከታሰሩ በኃላ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የክስ ሂደታቸው በመከታተል ላይ የሚገኙት ታዋቂው እና የተከበሩ ፖለቲከኛ አቶ በቀለ ገርባ የመጨረሻውን ሰፊ ቃለ ምልልስ አደርገው የነበረው በአዲስ ገጽ መጽሔት ላይ ነው፡፡
እኚህ ፖለቲከኛ በተቃውሞውና በማስተር ፕላኑ ዙሪያ የሰጡት የመጀመሪያ ክፍል በመጽሔቷ ላይ ታትሞ ከወጣ ከ10 ቀናት በኃላ በፖሊስ ቆጥጥር ስር ውለዋል፡፡ ለችግሮች መፍትሔ ያሉትም ታዋቂው የኦሮሞ ህዝብ መብት ተሟጋች የሆኑት በአዲስ ገጽ መጽሔት ታትሞ ወጥቷል፡፡
በእዚህና በተያያዥ ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያም በወቅቱ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መ/ቤት ሚኒስትር የነበሩት አቶ ጌታቸው ረዳ ጋር ሞጋች ቃለ-ምልልስ አድርገን በመጽሔቱ ላይ በሁለት ክፍል ያለገደብ ተስተናግዷል፡፡ ይህ በተግባር የሚያሳየው መጽሔቱ ሚዛናዊና ሁሉን አሳታፊ የጋዜጠኝነት ሙያ መርህ እንደምንከተል ነው፡፡ በተጨማሪም ለረዥም ዓመታት ሲጠየቅ የነበረና እስካሁን ድረስ ምላሽ ማግኘት ያልቻለውን የወልቃይት-ጠገዴ የማንነት ጥያቄ በተመለከተም በመጽሔቷ ሽፋን ስንሰጥ ነበር፡፡ ጥያቄዎቻቸውንም ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕጋዊ መንገድ ያቀርቡ የነበሩ የወልቃይት-ጠገዴ የማንነት ጉዳይን በዋነኝነት ተወክለው ይከታተሉ የነበሩትን የኮሚቴ አባላት ቃለ-ምልልስም አድርገንላቸው ነበር፡፡ ይህ ከሆነ ከጥቂት ወራቶች በኃላም በመጽሔቷ ላይ በደረሰው ግልጽና ስውር ደባ የተነሳ ከህትመት ውጪ ሆኗለች፡፡ ሆኖም ይህ እውነትና ሀቅን መዘገብ የጋዜጠኝነት መርህ ከገዢው ኃይል ጋር እንድንላተም አድርገናል፡፡ በሂደትም መንግሥት መንግሥት በእኛ ላይ ጥርስ እንዲነክስብን ሆኗል ብለን እናምናለን፡፡
በመፅሔቷ ላይ የተለያዩ አንኳር ሀገራዊ ጉዳዮችን አንስተን ገዢውን መንግሥት ሞግተናል። ይሄ ቀውስ ከመምጣቱ በፊትም በጠረንጴዛ ዙርያ ነፃ የሃሳብ ውይይት እንዲደረግና ብሔራዊ እርቅ እንዲፈጠር እኛም ለአመታት ለለመድነው ለግሉ ፕሬስ አፈና ተግዳሮት እጅ ሳንሰጥ የኢንተርኔት ሚዲያን በመጠቀም የሃገራችንን፡- የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ፣ የፍትህ ጉዳዮች ላይ ሰፋፊ ዘገባዎችን፣ ትንትታኔዎችን፣ ሂሶችን እና ሃሳቦችን እንዲሁም አጀንዳዎችን ያለማቋረጥ ስናቀርብ ነበር። የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ከታወጀም በኃላም በሀገር ውስጥ ያሉ ጥቂት የግል ህትመት ሚዲያዎች እንኳን ነባራዊ እውነታን ለመዘገብና ለህዝብ ይፋ ለማድረግ በፍርሃት ቆፈን ውስጥ ሲያዙ፤ እኛ ግን በቻልነው መጠን የየግል ማህበራዊ ሚዲያዎችን (Facebook) በመጠቀም በድፍረት የሀገራችን ጉዳይ ያገባናል በማለት ዜናዎችንና የግል ሃሳቦቻችንን ስናቀርብ ቆይተናል።
ህዳር 8 ቀን 2009 ዓ.ም ሁለታችንንም (አብሮን የታሰረውን ፖለቲከኛውን አቶ ዳንኤል ሽበሺን ጨምሮ) በደኅንነት ኃይሎች ታፍነን ስንያዝ፤ አያያዛችን ሰብዓዊ መብታችንን የጠበቀ አልነበረም። እስካሁንም በታሰርንባቸው ሁለት የፖሊስ ጣቢያ እስር ቤቶች ውስጥ ሰብዓዊ መብቶቻችን በአግባቡ አልተጠበቁልንም። ለሶስት ቀናት ያህል ለየብቻ ( በባዶ ቤት ጭምር) ታስረን ነበር። በእነዚህ ቀናት በቤተሰብ እንኳን እንድንጎበኝ አልተፈቀደም። አሁን ወደምንገኝበት እስር ቤት ከተዘዋወርን በኃላ ደግሞ የተለያዩ የመብት ጥሰቶች ደርሰውብናል። ለምሳሌ ያህል ተገቢውን ህክምና በወቅቱና በአግባቡ አለማግኘት፣ መፅሃፍና ጋዜጦችን ማንበብ መከልከል፣ በጠባብ ክፍል ውስጥ ከ50 በላይ እስረኞች ጋር፣ ከአእምሮ ህሙማን ጋር ፣ ያለ ፍትህ በፍርድ ቤት ሳንቀርብ መታሰር ከብዙ በጥቂቱ ይጠቀሳሉ። ተጠርጥረን የተያዝንበትም ምክንያት ከግንቦት ሰባት እና ኦነግ ጋር መረጃዎችን በኢንተርኔትና በስልክ በመለዋወጥ ህገ-መንግሥዊ ስርዓቱን በኃይል ለመናድ የሚል መሆኑን መርማሪ ፖሊሳችን ገልፆልን፤ ድርጊቱን አለመፈፀማችንን ቃል ሰጥተናል።
ከእዚህ ውጭ እስካሁን እንዲሁ በግፍ ታስሮ ከመቀመጥ ውጪ ምንም የተባልነው ነገር የለም። ከታሰርን ሁለት ወራት ቢያልፍም እስከአሁን ፍርድ ቤት አልቀረብንም። የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ቀድሞም በሞት አፋፍ ላይ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ነፃ ፕሬስ ክፉኛ ያሽመደመደው ሲሆን ገዥ ሃይሉንም ወደ ጠቅላይ አምባገነናዊ ስርአት የከተተ ነው ብለን እናምናለን። የፖለቲካ ንግግርና ተግባቦት ከመቼውም በላይ አስፈላጊ በሆነበት በዚህ ወቅት ሰዎችን ማፈንና ማሰር የባሰ ሀገሪቷን ወደ ውድቀት ይመራታል። ሚዲያም በዚህ ወሳኝ ወቅት ወሳኝ ሚና ሊኖረው በተገባ ነበር። ያም ባለመሆኑ ሀገራችን ይበልጥ ወደከፋ አደጋ ውስጥ እየገባች መሆኑ ይሰማናል። እንደ ኢትዮጵያዊ ዜጋም ያሳስበናል። እኛም ብንሆን የዚህ አደገኛ ኹነት ሰለባ ነን። እንዲህም ሆኖ ባገኘነው እጅግ የጠበበ መንገድ ተጠቅመንም ቢሆን ነፃ ሃሳቦቻችንን በድፍረት ከመግለፅ አልተገታንም።
በአሁኑ ወቅት ሀገራችን ለገባችበት ቀውስ መውጫ መንገዱ የነፃ ሃሳብ ክርክር መሆኑን በፅኑ እናምናለን። የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ የጣሰው የሀገሪቷን ህገ-መንግሥታዊ ድንጋጌ ብቻ ሳይሆን የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ አንቀፅ 19ን ጭምር ነው። አዋጁ በተግባር ተፈፃሚ መሆን ከጀመረ አንስቶ የቂም በቀል መወጣጫ መሆኑን በተግባር ማየት ችለናል:: እኛ በታሰርንበት የቦሌ ክ/ከተማ ፖሊስ መምርያም ይህንን ለመረዳት ችለናል::
ዜጐች ነፃ መረጃዎችን በማግኘት በነፃ የሃሳብ ሙግት መድረክ ሀሳባቸውን አንሸራሽረው አሸናፊ ሆኖ የወጣ ሀሳብ ገዥ እንዲሆን ማድረግ ይገባል:: የሀገሪቷ ኢኮኖሚም ቢሆን በአዋጁ ሳቢያ እየተሽመደመደ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ አዋጁና አፈፃፀሙ በሀገሪቷ፡- ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አለው ቀድሞም ስር የሰደደው ሙስናም ይበልጥ ጨምሮ እየተስፋፋ ነው:: የሰውን ሥነ ልቦና በማሸማቀቅ ፍርሃትን እያነገሰ የሚገኘው ይህ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፤ ከሠላማዊ የፖለቲካ ትግል ይልቅ ሠዎች ወደ ሚስጢራዊና የታጠቀ የፖለቲካ ትግል ይበልጥ እንዲገቡ በር ይከፍትላቸዋል::
በተጨማሪም በአገሪቱ ላይ ከፍተኛ ያለመረጋጋት ሁኔታን በመፍጠር ለኢንቨስትመንቶች እንዳትሆን እና ከዓለም አቀፍ ማህበረሰብ እንድትገለል ያደርጋል::
‹‹በመሆኑም አዋጁ ይነሳ! እኛም በግፍ ያለወንጀላችን ታስረናል፣እንፈታ!›› እንላለን::
www.addisgetsh.com

ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ
ጋዜጠኛ አናንያ ሶሪ