Netsanet: ከሁሉ በፊት የሰባዊ መብት ጥበቃ እና የብሔራዊ እርቅ ያስፈልጋል!! ከመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) የተሰጠ መግለጫ

Montag, 12. Oktober 2015

ከሁሉ በፊት የሰባዊ መብት ጥበቃ እና የብሔራዊ እርቅ ያስፈልጋል!! ከመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) የተሰጠ መግለጫ

ከሁሉ በፊት የሰባዊ መብት ጥበቃ እና የብሔራዊ እርቅ ያስፈልጋል!!12144958_896631350421800_1641189443633199080_n12115783_896631343755134_7789333707150151204_n

ከመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) የተሰጠ መግለጫ
የኢህአዴግ መንግሥት ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት እተገብረዋለሁ በሚለው የእድገት እና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ላይ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ለማወያየት እንደፈለገ መስከረም 24 ቀን 2008 ዓ.ም በፃፈልን ደብዳቤ ገልጾልና፡፡ ይህ ሁኔታ መልካም ቢሆንም ቅሉ አንድ መንግሥት የሚነድፋችው እቅዶች ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉት ሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች አምነውበትና የኔ ብለው በሙሉ ልብ ሲቀበሉት እና ሙሉ ተሳትፎ ሲያደርጉበት መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው፡፡
ይሁን እንጂ ዛሬ አገራችን ኢትዮጵያ በተበጣጠሰ ሁኔታ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ እና የማህበራዊ ትስስሯ ፈጽሞ በላላበት ሁኔታ፣ የዘርና የጎሳ ፖለቲካ የፈጠረው ችግር ተጋብቶና ተዋልዶ አብሮ የኖረውን ሕዝብ ለያይቶና አራርቆ በጠላትነት እንዲተያይ አድርጐታል፡፡ ይህ በመሆኑም የጉልበት (Labor) እና የካፒታል (capital) ዝውውር ተገትቶ ባለበት ሁኔታ እና ዜጎች በአገራቸው ውስጥ ከቦታ ቦታ ተዘዋውረው እንዳይሰሩና ሀብት ንብረት እንዳያፈሩ ተገትተው እና ተገድበው ባለበት በአሁኑ ወቅት፣ የዚህን አካሄድ አስከፊነት የሚያመላክተን በየዮኒቨርስቲው የሚገኙ ተማሪዎች በአንድ ስሜትና በወንድማማችነት ለምርምርና ለፈጠራ ከመነሳት ይልቅ የጎሳ ጎራ ለይተው እየተንቆራቆሱ መገኘታቸው ለሀገሪቱ በሚጠቅም ጉዳና ላይ አለመሆናቸውን ያመላክታል፡፡
ኢህአዴግ የፈጠረውና ያጠናከረው ወገን የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በሞኖፖል ይዞ ሌላውና የገዥው ፓርቲ ደጋፊ ያልሆነው ክፍል ደግሞ ወደ ድህነት አዘቅት ውስጥ እንዲገባ ተደርጓል፡፡ ይህም የሚያሳየን እንደፖለቲካው ሁሉ ፍትሀዊ የሆነ የኢኮኖሚ ክፍፍል አለመኖሩን ነው፡፡ 
ዜጎች ከላይ እንደተጠቀሱት ያሉ ችግሮች እንዲስተካከሉ በሚናገሩበትና በሚጽፉበት ወቅት ሽብርተኛ እየተባሉ ህግን ባልተከተለ ሁኔታ ወደ እስር ቤት ይወረወራሉ፡፡ ፍትህም በወቅቱ አይሰጣቸውም፡፡ ለብዙ ጊዜ በዚያው ሲማቅቁ እንዲቆዮ ከተደረገ በኋላ ያለፍርድ ቤት ውሳኔና ትዕዛዝ ከእስር ቤት እንዲለቀቁ ይደረጋል፡፡ ይህ ሁኔታም ሠላምን ሳይሆን ጥላቻን፤ የሀገር መረጋጋትን ሳይሆን ብጥብጥን የሚፈጥር መሆኑን ገዢው ፓርቲም ቢሆን ቁልጭ አድርጎ የሚያውቀው ይመስለናል፡፡
የኢህአዴግ መንግሥት እንደነዚህ ያሉ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ከመፍታት ይልቅ ሕዝባችንን በሀብታም እና ደሀ፣ የኢህአዴግ ደጋፊና ጠላት በሚል ስለከፋፈለው፣ እርሱ የፈጠራቸው ሀብታሞች የሀገሪቱን ሀብት በሞኖፖል እንዲይዙ ሲደረግ ቀሪውና እውነትን በመፈለግ እርሱኑ ሲታገል የነበረው ሕዝብ ደግሞ ከሥራው ይፈናቀላል፣ ከንግድ ሥራው ከስሮ እንዲወጣ ይደረጋል፣ አርሶ አደር ከሆነም ከመሬቱ ይፈናቀላል፡፡ ይህ አካሄድም አንድነትን ሳይሆን መለያየትን፣ ወንድማማችነትን ሳይሆን ጠላትነትን፣ መደጋገፍን ሳይሆን በጠላለፍን የሚፈጥር መሆኑን በድጋሜ ለኢህአዴግ ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡
ከላይ እንደተጠቀሰው የኢኮኖሚው እንቅስቃስ በጥቂቶች ቁጥጥር ስር ስለዋለና ፍትሀዊ የሆነ የኢኮኖሚ ክፍፍል ስለጠፋ ከሕዝባችን 80 በመቶ የሚሆነው በከፍተኛ ችግር ውስጥ ወድቆ ይገኛል፡፡ የኢህአዴግ መንግሥትም ይህን የተጎዳ ክፍለ ሕዝብ ዞር ብሎ ከማየትና ከመደገፍ ይልቅ የራሱን ፖለቲካ ማጠናከርና ሁኔታዎችን በቁጥጥሩ ሥር ለማድረግ ጥረት ሲያደርግ ይታያል፡፡
የኢህአዴግን መንግሥት ለመምከርና ለማሳሰብ የምንወደው በሀገሪቱ ውሰጥ፡-
1. የልማት፣ የእድገትና ብልጽግና መሠረቱ ዲሞክራሲና የዜጎች መብት መጠበቅና መከበር ሆኖ ሳለ ዜጎች በፖለቲካ አመለካከታቸው ብቻ በየእስር ቤቱ በመሰቃየት ላይ ባሉበት፣ ሌሎች አባላትም በዚህ አመለካከታቸው የተነሳ እየተሳደዱ፣ እየተዋከቡና ንብረታቸውን እየተነጠቁ በአጠቃላይ የሰብአዊ መብታቸው ተገፎ ከፍተኛ በደል እየተፈፀመባቸው ባለበት በአሁኑ ወቀት፣
2. ከላይ እንደተጠቀሰው ሁሉ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ሕዝባችን ተጋብቶ፣ ተዋልዶና ሀብት አፍርቶ በሰላም ከሚኖርባቸው የተለያዩ አካባቢዎች “ክልልህ አይደለም ከክልላችን ውጣ” እየተባለ በገዢው ፓርቲ ካድሬዎችና ደጋፊዎች ሀብታቸው እየተነጠቀ፣ እየተቃጠለ፣ እየተቀማ፣ እነርሱም እየተደበደቡና እየታሰሩ በአሳዛኝ ሁኔታ ከነቤተሰባቸው እየተባረሩ ባሉበት በአሁኑ ወቅት ዜጎች በወጣው እቅድ ላይ በሙሉ ልብ ሊሳተፉ ይችላሉ ለማለት ያስቸግራል፡፡ 
3. እንደዚህ ያለውን ግዙፍ ብሔራዊ እቅድ ተግባራዊ ለማድረግ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በባለቤትነትና በእኔ ባይነት መሳተፍና ለተግባራዊነቱም በትጋት ይነሱ ዘንድ ከላይ የተጠቀሱት ከፍተኛ የሆኑ ችግሮች መፈታት አለባቸው ብለን እናምናለን፡፡
እንደነዚህ ባሉ ማነቆዎች እና ችግሮች ላይ እርምት ሳይደረግ የወጣውን እቅድ ሕዝባችን በአንድ ልብ ደግፎ በመረባረብ ከዳር ያደርሰዋል ብሎ ማሰቡ ብዙ እርምጃ ያስኬዳል የሚል እምነት የለንም፡፡ ስለዚህ የአህአዴግ መንግሥት ሁሉም ዜጎች በሀገሪቱ እንቅስቃሴዎች ላይ ሙሉ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ከፈለገ ከላይ የተጠቀሱ ችግሮች ሙሉ ለሙሉ በአስቸኳይ መፈታት አለባቸው የሚል ምክራችንን ልንለግስ እንወዳለን፡፡
በአጠቃላይ የኢህአዴግ መንግሥት በዚህ እቅድ ላይ ሕዝባችንን ለውይይት ከመጥራቱ በፊት መቅደም ያለባቸው አንገብጋቢ ጉዳዩች እንዳሉና በቅድሚያ መፈፀም እንዳለባቸው እያሳሰብን ሁሉም የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላትን ያካተተ ስብሰባ ተደርጎ ብሔራዊ ውይይት፣ እርቅና መግባባት የሚደረስበት ስብሰባ ኢህአዴግ መጥራት እንዳለበት እናሳስባለን፡፡
አንዲት ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ጥቅምት 01 ቀን 2008 ዓ.ም

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen