Netsanet: የኢትዮጵያዉያን አንድነት – ለወያኔ ግብዐተ መሬት (ይገረም አለሙ)

Samstag, 19. Dezember 2015

የኢትዮጵያዉያን አንድነት – ለወያኔ ግብዐተ መሬት (ይገረም አለሙ)

የኢትዮጵያዉያን አንድነት – ለወያኔ ግብዐተ መሬት (ይገረም አለሙ)

በኢትዮጵያ የነበሩት መንግስታት ዴሞክራሲያዊ አስተዳደርን ማስፈን ባይሆንላቸው ለሀገራቸው ቀናኢ ነበሩና ሱዳን ከኢትዮጵያ የምትመኘውን መሬት ለመወሰድ የነበራት የዘመናት ህልም ሳይሳካ ኖሯል፡፡ አሁን ግን በስም እንጂ በተግባር ኢትዮጵያ መንግሥት አልባ የሆነችበትን ይህን አጋጣሚ በመጠቀም የዘመናት ምኞቷን ለማሳካት ከወያኔ ጋር እየተሞዳመደች ነው፡፡ ይህን ድብቅ የአቶ መለስ ዜናዊ ሴራ የወያኔ ባለሥልጣኖች ለመደበቅ ቢጣጣሩም የሱዳን ጋዜጦች በደስታና በአሸናፊነት ስሜት እየዘገቡት ለማወቅ ተችሏል፡፡

ይህ የድብቅ ስምምነት ተግባራዊ ሆኖ ከኢትዮጵያ ሕዝብ እውቅናና ፍላጎት ውጪ ሱዳን መሬት ለመውሰድ ብትችል ሰላም የማታገኝበት ለትውልድም ግዜ እየጠበቀ የሚፈነዳ ፈንጂ ማቆየት መሆኑን በዋሽንግቶን ዲሲ በሚገኘው የሱዳን ኤንባሲ ሰላማዊ ሰልፍ የወጡ ኢትዮጵያውያን አስገንዝበዋል፡፡ የዚህ ሰልፍ ተካፋይ ለመሆን ከሌላ ከተማ የተገኙ የኦሮሞ ተወላጅ ኢትዮጵያውያን በቦታው ሲደርሱ መጣን ተቀበሉን ማለታቸውን ስሰማ የወያኔ የመቶ አመት የቤት ሴራ አበቃለት ይሆን! በማለት ሳላውቀው አይኔ በእንባ ተሞላ፡፡ ለካስ ከሀዘን ባላተናነሰ ደስታም ያስለቅሳል፡፡የአመታት ምኞት እውን ሲሆን ማየት አይንን አንባ ያስረግዛል!!

በዚሁ ስብሰባ ላይ የተገኙት አቶ ገመቹ የተባሉ ሰው እኛ የኦሮሞ ተወላጆች የወያኔን የከፋፍለህ ግዛ አጥር ሰብረን ስንመጣ እናንተ አማራና ቅማንት ተባብላችሁ ተከፋፍላችሁ ጠበቃችሁን፤በጣም አዝነናል ይህን የወያኔን ሴራ በጥሳችሁ በአንድ ኢትጵያዊነት መንፈስ እንድትቆሙ ጥሪ እናስተላልፋለን በማለት የገለጹት ወቅታዊ መልእክትም ልብ የሚነካ ነበር፡፡ መለያየት በቃ እንበል!

ተደጋግሞ እንደተገለጸው ወያኔ በስልጣን መቆየት የሚችለው ኢትዮጵያውያንን ሰበብ እየፈጠረ ማለያየት፤ እሳት እየጫረ ማገዳደል የሀሰት ወሬ እየነዛ በጥርጣሬ እንዲተያዩ ማድረግ እስከቻለ ብቻ ነው፡፡ የኢትዮጵያውያን አንድነት የወያኔ ግብአተ መሬት መሆኑን ከማንም በላይ ቁንጮዎቹ ወያኔዎች በሚገባ ያውቃሉ፡፡ ሰለሆነም እንቅልፍ አጥተው የሚያልሙትና የሚሰሩት እንዴት በምን መንገድና ስልት እንዲሁም መቼና የት ኢትዮጵያዉያንን በተለይ አማራና ኦሮሞን ርስ በርስ እንደሚያበጣብጡ ነው፡፡

ሀያ አራት አመት ሙሉ በጽሁፍ፤ በንግግር ፤ በዘፈን ወዘተ የተላለፉ መልእክቶች የወያኔን የመከፋፈል ሴራ አክሽፈው አንድነትን ሊያመጡ አልቻሉም ነበር፡፡ ሎሬት ጸጋየ ገብረ መድህን በአንድ ግጥሙ የሰው ልጅ ሀ ብሎ ከፊደል ወይንም ዋ ብሎ ከመከራ ይማራል እንዳለው እነሆ ዛሬ ህዝቡ ከመከራ ተምሮ ከፖለቲከኞቹም ቀድሞ ወደ አንድነት እየመጣ ነው፡፡

ከህዝቡ ቀድመው የወያኔን ሴራ ሊያከሽፉ፣አርአያ ሆነው አንድነትን ሊያጠናክሩ፣ግንባር ቀደም ሆነው ትግሉን ሊመሩ ይገባቸው የነበሩ ብዙዎቹ ፖለቲከኞች ከገቡበት ህልም ሳይነቁ ሕዝቡ ቀደማቸው፡፡ መምራቱ ባይሆንላቸውም የህዝቡ ተነሳሽነት እያናቃቸው፤ እየተከፈለ ያለው መስዋዕትነትም ከየግል ጠባብ አመለካከትና የሥልጣን ጥም ተላቀው ለህዝብ ትግል ቅድሚያ እንዲሰጡና ስለ አንድነት እንዲያስቡ እያደረጋቸው መሆኑን እያን እየሰማ ነው፡፡ እሰየው፣ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡

ሎሬት ጸጋየ ገብረ መድህን የአባቶቻችንን ጥረት ሳስታውሰው ትዝ ሲለኝ ከሞከርነው ነገር ይልቅ ያልሞከርነው ነው የሚቆጨኝ እንዳለው ትናንት፣ ትናንት በስትያ በሆነው ባደረግነው የምናዝን የምንቆጭና በዚሁም የምንወቃቀስ ሳይሆን ልናደርገው ሲቻለን ያላደረግነውን ልናውቀውና ልንሄድበት ሲገባን ያላወቅነውንና ያልሄድንበትን መንገድ ለይተን (ይህም አንድነት ነው) የተጀመረው ትግል ከውጤቱ መስዋእትነቱ የማይከፋበትንና ለድል የሚበቃበትን ስራ መስራት ወቅታዊና አንገብጋቢ ጉዳይ ነው፡፡

ለዚህ ደግሞ ቀዳሚውና ዋናው በየግል ከምትሰጡት መግለጫና ከምታደርጉት እንቅስቃሴ አልፋችሁ ድምጻዊ ቴዲ አፍሮ ገና በ 97 ምርጫ ዋዜማ ጃ ያስተሰርያል ብሎ ባዜመው ዘፈኑ እስቲ ተባበሩ ይያዝ እጃችሁ አለበለዚያማ በምን ያስታውቃል እኛን መውደዳችሁ ያለውን ዛሬ ከአስር አመት በኋላ ተግባራዊ ማድረግ ነው፡፡ የትናንት ልዩነቶችን ወደ ጎን ብሎ እጅ ለእጅ ተያይዞ መታየትና በተግባርም በጋራ መንቀሳቀስ ነው፡፡ ፖለቲከኞቻችን በዚህ መልክ ብትታዩ ከምንም በላይ የወያኔን የከፋፋይነት ሴራና ስራ ታከሽፋላችሁ ብቻ ሳይሆን የመቶ አመት የቤት ስራ የሚለውን ከምንጩ ታደርቃላችሁ፡፡ ለተጀመረው ትግልም ብርታትና ቀጣይነት ሀይል ትሰጣላችሁ፤ በተግባር ደግሞ ኢትዮጵያ ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርኣት የምታመራበትን ስልትና መንገድ በጋራ ትቀይሳላችሁ፤ድል ያለመስዋዕትነት ባይገኝም ከድሉ መስዋዕትነቱ እንዳይከፋ ማድረግ ትችላላችሁ፣ በጥቅሉ ድሉን ታቃርባላችሁ፡፡

በታላቁ መጽኃፍ ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ ተብሎ እንደተጻፈው ይህ ወቅት ኢትዮጵያ ከወያኔ አገዛዝ ተላቃ ዴሞክራሲያዊት ሀገር እንድትሆን የሚሹና የሚታገሉ፣ በተቃራኒው በስመ ተቀዋሚ እያጭበረበሩ የኖሩና አሁንም በዚሁ መንገድ መቀጠል ዓላማቸው የሆኑ ፖለቲከኞችና ፓርቲዎች የሚለዩበት ነው፡፡ እስካሁንም መለየት እየተቻለ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ህዝብ ነጻነት ለሀገሪቱም ዴሞክራሲያዊነት ነው የምንታለው የምትሉ ወገኖች ህዝቡ እያሳየ ያለውን አንድነት እናንተ ተግባራዊ ማድረግ ተስኖአችሁ ይህ ህዝብ ከባድ መስዋዕትነት እየከፈለበት የሚገኘው ትግል በዚሁ መልኩ ብቻ ቀጥሎ በወያኔ ቢጨፈለቅ ከወያኔ ባልተናነሰ በታሪክና በትውልድ ትጠየቃላችሁ፡፡

መስዋእትነቱ ሊከብድ የድሉ ወቅት ሊረዝም ይችል ይሆናል እንጂ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሆነ የትእግስቱን ያህል ሲያመር የሚያደርገውን ማወቅ የፈለገ ያውቀዋል፡፡ ሰሞኑን የሚታየውም ከበቂ በላይ ገላጭ ነው፡፡ ሕዝቡ ካመረረ መሪ ማጣት ለግዞት እንደማያንበረክከው የአምስት አመቱ የአርበኝነት ታሪኩም ያስረዳል፡፡ ዘር ሳይመነዝር የቋንቋም ሆነ የሀይማኖት ልዩነት ሳይፈጥር በአርበኞች እየተመራ እንዲያም ሲል ከመካከሉ የጎበዝ አለቆችን እየመረጠ በዱር በገደሉ ተዋግቶ ከፊሉም ከጣሊያን ጋር መስሎና ተመሳስሎ በውስጥ አርበኝነት ታግሎ ነው ለነጻነት የበቃው፡፡

በርካታ ፖለቲከኞችና የፖለቲካ ድርጅቶች ባሉበት በዚህ ዘመን ግን የህዝብ ትግል መሪ አጥቶ ወደ ጎበዝ አለቃ ምርጫ ሊደረስ አይታሰብም፡፡ እናም ለሥልጣኑ መቆየት ሲል ሕዝብ ቢያልቅ ሀገር ቢጠፋ ደንታ የሌለው ወያኔ ራሱም እየገደለ ርስ በርስም እያገዳደለ ዜጎች በየቀኑ እየሞቱ በመሆኑ ፖለቲከኞቻችን ሀላፊነታችሁ ከባድና ውስብስብ ነውና ፍጠኑ፤ እስከዛሬ የለበሳችሁትን ሱፍም ሆነ ገበርዲን አስቀምጡና ኢትዮጵያዊ ኩታ ለብሳችሁ ስለ ዴሞክራሲ እያዜማችሁ እጅ ለእጅ ተያይዛችሁ እናያችሁ፡፡ ፈጠናችሁ ሸንጎ ተቀመጡና ትግሉ ተጠናክሮና ሰፍቶ ስለሚቀጥልበት፤ መስዋእትነቱ ስለሚቀንስበትና ድሉ ስለሚቃረብበት ዘዴና መንገድ ተነጋገሩ አቅዱ ተንቀሳቀሱ፡፡

የኢትዮጵያውያን አንድነት ለወያኔ ግብዐተ መሬት ነው፡፡ በመሆኑም አንዱ የሌላውን ግብዣና ጥሪ መጠበቅና ይህን ላለመገናኘት ምክንያት ማድረግ አሁን ግዜው አልፎበታል፡፡ በዲሲው ሰልፍ ላይ ተገኝተው መጣን ተቀበሉን እንዳሉት የኦሮሞ ተወላጆች ሁሉም መጣን ተቀበሉን ማለት አንዱ ወደ ሌላው መሄድ ይኖርበታል፡፡ ርስ በርስ እየተጠራሩና አንዱ የሌላውን በር እያንኳኳ በአንድ መድረክ መገናኘትና መምከር ግዜ የሚሰጠው አይደለም፣ እናም ፍጠኑ፡፡ ይህን ማድረግ ደግሞ ህዝቡ እየከፈለው ካለው መስዋዕትነት አንጻር ሚዛን የሚደፋ አይደለም፡፡ታሪክ ለክብር ያጫቸው ኢትዮጵያዉያን የሚታዩበትም የሚፈተኑበትም ወቅት አሁን ነው፡፡

እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይጠብቅ

http://wp.me/p5L3EG-8B

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen