Netsanet: አገር እንደዋዛ፤ ስትደርቅ እንደጤዛ (አቢቹ ነጋ)

Mittwoch, 23. Dezember 2015

አገር እንደዋዛ፤ ስትደርቅ እንደጤዛ (አቢቹ ነጋ)

አገር እንደዋዛ፤ ስትደርቅ እንደጤዛ (አቢቹ ነጋ)

አቢቹ ነጋ

ሁለት ሚሊዮን የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን ተሰደው ይገኛሉ። የስደታቸው ምክንያት ብዙና የተለያየ ስለሆነ መዘርዘር አያስፈልግም። ሁሉንም አንድ የሚአደርግ ነገር ግን አለ። ስደትን ደስ ብሎት የተቀበለ የለም። አንድ ቀን ወደ ሃገር ተመልሶ ሃገሩንና ሕዝቡን መርዳት ሁሉም ይፈለጋል።

ኢትዮጵያዊያኖች በየቀኑ በሚባል ደረጃ ይገናኛሉ። የግንኙነታቸው አድማስ በምንገድና በገበያ አዳራሽ ብቻ የተወሰን ሳይሆን በጸሎት ቤት፤ በድግስ፤ በበዓላት፤ በሐዘን፤ በግልና በመሳሰለው ይገናኛሉ። በምንም መድረክ ይገናኙ ስለሃገራቸው፤ ስለወገናቸው፤ ስለታሪካቸው፤ ባሕላቸው፤ ቀያቸው፤ የሃገራቸው መልካ ምድር፤ ሃይማኖታቸው፤ ኑሯቸው፤ የሃገር ናፍቆታቸው፤ ፖለቲካቸው መነጋገርን ያዘወትራሉ።

አንዳንዴ ብዙ ውይይቶች ጫፍ ደርሰው ሊበጠሱ የደረሱ እስኪመስል ድረስ ይጨቃጨቃሉ። ሁሉም ተወያይ በማንኛውም ጉዳይ ላይ ባለሙያ መስሎ ይታያል። ውይይታቸው ፊት ለፊት ብቻ ሳይወሰን ዘመኑ በወለደው የመገናኛ ብዙሃን፤ ማህበራዊ ድረ ገጾች፤ ቴሌ ኮንፈረንሶችን በመጠቀም ይደረጋል። አንዱ ሌላውን ግልሰበ ሲአብጠለጥል፤ አንዱ ቡድን ሌላውን ሲኮንንና ሲአወግዝ መስማትና ማየት ልምድና በሐሪ ሆኗል። ብዙውን ጊዜ እነዚህ ውይይቶችና ክርክሮች ለችግሩ መፍቴሄ ሳይሰጡ ጥፋትን፤ ስህተትንና ውግዘትን አጉልተው ይቋጫሉ።

ብዙዎች ይህ የኢትዮጵያዊያን መገለጫ የሆነውን ባሕሪ ያወግዛሉ። እንደዚህ ጸሐፊ እይታ ከሆነ እርር ትክን ያለ፤ እስከ መጣላት የሚአደርስ ውይይት የሚአደርጉት ሃገራቸውንና ሕዝባቸውን ከመውደዳቸው የተነሳ ብቻ ሳይሆን ጤናማና አዋቂነትም ነው ይላል። ሃገርን ከማፍቀር የተነሳ ለሕዝቧ ይበጃል የሚሉትን ሐሳብ መሰንዘራቸው ሊአስወግዛቸው አይገባም። አለመንጋገርና አለመወያየት ግን የጤናማ በሐሪ ምልክት አይደለም ሊሆንም አይችልም። መነጋገርና መወያየት ካለ ለችግሮች መፍትሔ ማግኘት ይቻላል።

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ማስተር ፕላንን በመቃውም በተነሳው ሕዝባዊ ተቃውሞ ኢትዮጵያ እየታመሰች ትገኛለች። በሃገር ቤት በተከሰተው የፖለቲካ ቀውስ ዳያስፖራ ኢትዮጵያዊያን ልባቸው ተሰብሯል፤ ደንግጠዋል፤ ተጨንቀዋል፤ ሱባኤ ገብተዋል። አምላክ በቅዱስ እጁ ሃገራቸውን እንዲባርካትና እንዲቃኛት ፈጣሪያቸውን ተማጽነዋል። ምክንያቱ ግልጽ ነው-ቀውሱ ከቀጠለ የሚወዷት ሃገራችው ልትፈርስና ብትንትንዋ ሊወጣ በመሆኑ ሰግተዋል። ብዙዎችም የሚፈራው እንዳይሆን ምንመደረግ አለበት ብለው ሌት ተቀን ሲለፉ ይታያል። አገሪቱ ከፈረሰች መግቢያ ሊጠፋ ነው። በሶማሊያ፤ በሶሪያ፤ በአፈግሃኒስታን፤ በኢራክ፤ በሩዋንዳ፤ በሊቢያ፤ በማሊ ወዘት ከወደቁት አገሮች (Failed States) ጎራ ልትመደብ ነው የሚል ስጋት አላቸው። ይህ ከሆነ ደግሞ ባለሶስት ቀለሙ፤ ባለ ወርካው ፣ ባለመዶሻው ፣ የአማራው፣ የኦጋዴኑ፣ የደቡቡ፣ የጉራጌው፣ የቤንሻንጉሉ፣ የጋሞው፣ የቅማንቱ (ስንቱ ተዘርዝሮ ያልቃል) ባንዲራ የሚውለበለብበት መሬትና ወጋግራ አይኖርም። ያለ ሃገር የጎሳ ጥያቄ አይኖርም። ማፍረስና ማውደም ለሁሉም ቀላል ስራ ሲሆን መልሶ መግጠም ግን ይቸግራል። በዛ ጊዜ ቄሱም፤ ሸሁም፤ ፓስተሩም ዝም መጽሃፉም ጎሳውም ዝም ይሆናል።

ሁል ጊዜ እናቶቻችን እንዲህ ሲሉ ይመክራሉ-አይሆንምን ትቶ ይሆናልን ማሰብ ይላሉ። ይህም የቅድሚያ ዝግጅት (Contingency Planning) ያስፈልጋል እንደማለት ይሆናል። ዕውነት አላቸው- ማሰባቸው ተገቢ የመስላል።

የኢትዮጵያዊያን ስጋትም እንዲሁ በአየር ላይ የተፈበረከ፤ መሰረተቢስ፤ ተራ መላምትና የናፋቂነት አስተሳሰብ አይደለም። የኢትዮጵያን ፖለቲካያዊ፤ ኢኮኖሚያዊ፤ ማሕበራዊ፤ አስተዳደራዊ፤ ሕጋዊ መስፈርቶች (Indicators) ለሚከታተልና ሰክን ብሎ ለሚአስብ ሰው ብዙ ጉዳዮች ዓይናቸውን ያፈጠጡ እውነታዎች ናቸው። ከወደቁት አገሮች ጋር ሊአስመድባት ወይም ወደዚያ እያንደረደሯት ያሉ ምልክቶች በገሃድ ይታያሉ። አሁን እዚህ ደረጃ አልደረስንም። ጉዞው ግን ፈጥኗል። እሩቅ አይደለም። ስለሆነም ለብዙዎቻችን ሁሉም ነገር ጨልሟል።

ጨለማውን ወደ ብርሃን መቀየር ይቻላል። አዎ እንችላለን (YES WE CAN) ብለን በአንድነት ከተነሳን ይቻላል። መፍትሔው በየአንዳንዳችን ቤትና ቡድን እጅ ይገኛል። ሩቅ መሄድ አይኖርብንም። ለብዙ ዓመታት ብዙ ተከራክረናል። ክርክሩ ይብቃ። መፍትሄው ላይ እንስራ። በእጃችን የሚገኝ መፍትሔ አለ። መፍትሔው ከየአንዳንዳችን የሚጠበቅበት ጊዜ ትላንት ወይም ነገ ሳይሆን ዛሬ ነው። በየለቅሶ ቤቱ፤ ጸሎት ቤቱ፤ በግብዣው፣ በአደባባይና በመንገድ ስናወጣና ስናወርዳት የነበረችውን ኢትዮጵያ በተግባር የምንታደግበት አስራ አንደኛው ስዓት ላይ ደርሰናል። ወደድንም ጠላንም የመጣንበት ጎሳ ሳይሆን የመጣንበት ሃገር ገላጫችን እንደሆነ አንዘንጋ።

ከሰሞኑ የሚታየው የሕዝብ እንቅስቃሴ ሁሉን አቀፍ መሆኑ ያስደስታል። ቀድሞ ነጻ አውጪ ነን እያሉ ይሰብኩ የነበሩት እንደ ሌንጮ ለታ ዓይነቶች በኢትዮጵያ ጥላ ስር ለመስራትና ለእርቀ ሰላም ጥሪ ሲአቀርቡ ማየትና መስማትን የመሰለ ትልቅ ተስፍ ሰጪ ነገር የለም። በእጃችን ያለው መፍትሔ የሚባለው ምሳሌም ይህ ነው። ሌሎችም ይህን ፈለግ ሊከተሉ ይገባል። በስልጣን ላይ ያለው መንግሥትም ከሕዝብ ጋር ለመነጋገር ዝግጁነቱን በአስቸኳይ ለሕዝብ ማብሰር አለበት። ይህን ካላደረገ ኪሳራው ይበልጥ የሚጎዳው እራሱን ነው።

በየስርቻወ ነጻ አውጪ እየመሰረቱ መናቆር ለማንም የሚበጅ አይሆንም። መገንጠልና ነፃነት መፍትሔ ቢሆን ኖሮ በኤርትራ፤ በደቡብ ሱዳን፤ በፓኪስታን ወዘተ ያለው ሁኔታ ባልታየ። ይህን የሚፈልግ ኢትዮጵያዊ ይኖርላ ብሎ ለማመን ይቸግራል። ካለም የሚወክለው ጥፋትን ነው። ስለዚህ ዓማራ፤ ኦረሞ፤ ትግሬ፤ ጉራጌ፤ ደቡብ ሕዝቦች፤ ኦጋዴን፤ አፋር፤ ቤንሻንጉል፤ ጉራጌ ወዘት ሳይባል መነሳት ያስፈልጋል። ለነገሩ ብዙዎቻችን የነጻ አውጪ መሪዎችን ጨምሮ የጎሶችን ክልል እንኳን ጠንቅቀን አናውቅም።

ይሀን ካላደረግን አገር አንደዋዛ ትጠፋና መጨረሻችን እንደ ጤዛ ተኖ በወጡበት መቅረት ይሆናል። በአገር ቤትም ሆነ በውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ መንቃት አለበት። ቢረፍድም አልዘገየምና አገራችንን ከውድመት እንታደጋት። ሳይኖራት አስተምራ፤ አብልታና አጠጥታ አሳድጋናለች። ዓማረ አረጋዊ ‘መንግሥት እራሱን ይፈትሽ’፤ የሻቢያው ተስፋዬ ገብረአብ ‘ጎዳናው የት ያደርሳል’ ብለው ያስነበቡን መጣጥፎች’ ምክሮች ለሁላችንም የሚመቹ ናቸው። እናዳምጣቸው። አንዳንዴ ከምናምኑም የርግብ እንቁላል መጠበቅ ክፋት የለውም። መርዝም መድሐኒት ይሆናልና። መሬቱ ሰፊ አየሩ ምቹና ለሁላችንም በቂ ስለሆነ እንወቅበት። አመሰግናለሁ።
አቢቹ ነጋ (aneganega2013@gmail.com)

ታሕሳስ 12, 2008

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen