Netsanet: "እጆቻችን ነሐሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም ማታ በካቴና የታሰርን የተፈታነው ታኅሳስ 17 ቀን 2009 ዓ.ም ነው፡፡" ነገረ ኢትዮጵያ / Negere Ethiopia

Samstag, 13. Mai 2017

"እጆቻችን ነሐሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም ማታ በካቴና የታሰርን የተፈታነው ታኅሳስ 17 ቀን 2009 ዓ.ም ነው፡፡" ነገረ ኢትዮጵያ / Negere Ethiopia

"እጆቻችን ነሐሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም ማታ በካቴና የታሰርን የተፈታነው ታኅሳስ 17 ቀን 2009 ዓ.ም ነው፡፡"

ነገረ ኢትዮጵያ / Negere Ethiopia

"ከጠዋቱ 3 ሰዓት አካባቢ ከሶስቱም ዞን በተመሳሳይ ሰዓት ከውጭ ወደ ታራሚው መጥሪያ በመትረየስ እና በክላሽ ከፍተኛ የሆነ ተኩስ ወደ ታራሚው ተተኮሰ፡፡" "እጆቻችን ነሐሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም ማታ በካቴና የታሰርን የተፈታነው ታኅሳስ 17 ቀን 2009 ዓ.ም ነው፡፡" "እኛ የደሀ ልጆች ፍትህ ፊቷን አዙራብን መንግስት ሁሉን አጠንክሮብን ስለኛ የሚሟገትልን አካል አጥተን አሁን ለብቻ በተሰራልን ቂ/ማ/ቤት ጠባብ ጊቢ ውስጥ ተስፋ በቆረጠ ኑሮ ውስጥ እንገኛለን፡፡" "የሐይማኖ አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች እና አባላት፣ የመንግስት ባለስልጣናት፣ የሲቪክ ማህበራት፣ ጋዜጠኞች እና የሟች ቤተሰቦች ዝም ማለታቸው እጅግ ልብ የሚሰብር ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ እና አለማቀፍ ማህበረሰቡን የሚመለከት የህሊናና የሰብዓዊነት ጉዳይ ነው፡፡" ግንቦት 01 ቀን 2009 ዓ.ም ግልፅ ደብዳቤ ለሚመለከታቸው ሁሉ ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ቂሊንጦ በቂሊንጦ ማ/ቤት ነሐሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም በደረሰው ድንገተኛ የእሳት አደጋ ምክንያት የ23 ሰዎች ህይወት መጥፋት እና የመንግስት እና የህዝብ ንብረት መውደሙ ይታወቃል፡፡ ይህንንም መነሻ በማድረግ በሸዋ ሮቢት ማ/ቤት በፖሊስ እና ደህንነቶች ታራሚዎች ላይ የተደረገው ምርመራ እውነቱን ወደ ጎን በመተው በማ/ቤት ውስጥ ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ እንደተንቀሳቀሰ እና ማ/ቤቱ ከመቃጠሉ በፊት ለረዥም ጊዜ የታቀደና ሲሰራበት የቆየ በማስመሰል ማ/ቤት በረዥም ጊዜ ዕቅድ እንደተቃጠለ አጣርቻለሁ ብሎ አቅርቧል፡፡ እውነቱ ግን የማ/ቤቱ አተት ገብቷል በሚል ምክንያት የቤተሰብ ምግብ አይገባም ብለው የለጠፉት ማስታወቂያ ምክንያት ታራሚዎች ኃላፊነት እንዲያነጋግሯቸው ሊጠይቁም የማ/ቤት አስተዳደር በወሰደው የኃይል እርምጃ ምክንያት የተፈጠረ በዕለት ግጭት የደረሰ አደጋ እንጂ ቀደም የታቀደ አይደለም እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ ግን የአደጋው ምክንያት የሆኑትን የማ/ቤቱ ኃላፊዎችን ከተጠያቂነት ለማዳን ሲባል እኛ ጠያቂ እና ተቆርቋሪ የሌለን የደሀ ልጆች መልስ ሆነናል፡፡ ይህም በቅርቡ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ለቀ/ማ/ቤት በደረሰው አጣርቻለሁ ብሎ ለህ/ተ/ም/ቤት ያቀረበው ሪፖርት እኛ የጉዳዩ ባለቤት የሆነውን ተከሳሾች ያለ ነገር እና የእኛ እምነት ያላካተተ ቢሆንም የሪፖርቱ ውጤት የሚያሳየው የተከሰስንበት የክስ ጭብጥ ጋር በጭራሽ የማይገናኝ እና የሚጣረስ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የሚያሳየው ፖሊስ በምርመራ ደረስኩበት ብሎ እኛን የከሰስንበት ሐሰት እና ያለውን የፖለቲካ ጫና ለመቀነስ የቀረበ የፖለቲካ መልስ መሆኑ ነው፡፡ ይህ ማረሚያ ቤት ከፌ/መ/ቤቶች አንዱ የሆነና ጠንካራ ጥበቃ እና ከፍተኛ የሆነ ፍተሻ የሚደረግበት ሲሆን ቤተሰቦቻችን ለጥየቃ በሚመጡበት ጊዜ በኤሌትሪክ ማሽን እና በእጅ ከፍተኛ ፍተሻ ይደረግባቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንኳ የማያደርገው እናቶቻችን እና ሴት እህቶቻችን ሞዴሳቸው ሳይቀር ከፍተኛ የሆነ አስነዋሪ ፍተሻ ይደረግባቸዋል፡፡ ፍ/ቤት ስንሄድ፣ ከጠበቃ ጋር ስንገናኝ እና ህክምና በምንወጣበት እና በምንገባበት ወቅት ከሁለት ጊዜ በላይ ጥብቅ ፍተሻ በሚደረግበት ታራሚው 1-10 በሚባል አደረጃጀት ተደራጅቶ ስለ ሀገሩ ስለፖለቲካ እና ሌሎችም ጉዳዮች እንዳያወራ እርስ በእርሱ በሚጠባበቁበት፣ ከ1-10 ውጭ በቡድን ሰው በማይቀመጥበት ከዚህ በላይ የተጠቀሱትን ተላልፎ የተገኘ ታራሚ ከፍተኛ የሆነ ድብደባ የሚፈፀምበት እና ጨለማ ቤት በሚወረወርበት፣ መኝታ ክፍላችን ቢያንስ በሳምንት 1 ጊዜ በሚፈተሽበት፣ ጠያቂ ቤተሰብ ለአንድ ታራሚ ከ200 ብር በላይ መስጠት በማይቻልበት፣ የማ/ቤት ኃላፊዎች በማ/ቤት ግቢ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ንግድ በሚያካሔዱበት፣ ኦዲት ተደርጎ የማያውቀው መ/ቤት ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር ችግር ያለበት ሲሆን ከፍተኛ ኢ-ሰብዓዊ እረገጣ የሚካሄድበት ፌ/ማ/ቤት ነው፡፡ እንደሚታወቀው ነሐሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም ማ/ቤቱ በመቃጠሉ ለ23 ሰው ሞት ለ15 ሰው በጥይት መቁሰል እና የንብረት ውድመት የተከሰተ ሲሆን የቃጠሎው መንስኤ ደግሞ የመልካም አስተዳደር እጦት ነው፡፡ ይኸውም ነሐሴ 26 ቀን 2008 ዓ.ም የማ/ቤቱ ኃላፊዎች የታራሚውን የየቤቱ አስተዳዳሪዎች በማስጠራት "በአተት በሽታ ምክንያት ከነሐሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ የቤተሰብ ምግብ የማይገባ መሆኑን ለታራሚው አሳውቁ" በማለት እነሱም/የታራሚ ተወካዮች/ "ለታራሚው እራሳችሁ ተናገሩ ታራሚውን አነጋግሩ" ቢሉም ኃላፊዎች "ለታራሚው ሔደን ከመንነግር አጥራችንን ብንጠብቅ ይሻለናል" በማለት ትዕዛዙን በዚህ መልኩ ካስተላለፈ በኋላ ነሀሴ 27 ቀን 2008 ዓ.ም ከነሐሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ ከቤተሰብ የሚመጣ ምግብ የማይገባ መሆኑን የሚገልፅ ማስታወቂያ በግቢው በር/ኮሪደር/ በመለጠፉ ታራሚው ለየዞን ተጠሪ ፖሊሶች "የቤተሰብ ምግብ ልንከለከል አይገባንም ኃላፊዎች መጥተው ያነጋግሩን" በማለት የጠየቀ ሲሆን በነሀሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም ጧት 12 ሰዓት ለቆጠራ ለመጡት ፖሊሶችም ታራሚው ይህንኑ ጥያቄ ሲያቀርብ ፖሊሶች ባልተለመደ ሁኔታ የግቢውን በር (ኮሪደር) ቆልፈው በመሄዳቸው ታራሚው እስከ 3 ሰዓት ድረስ በተስፋ ሲጠብቅ ቢቆይም ከጠዋቱ 3 ሰዓት አካባቢ ከሶስቱም ዞን በተመሳሳይ ሰዓት ከውጭ ወደ ታራሚው መጥሪያ በመትረየስ እና በክላሽ ከፍተኛ የሆነ ተኩስ ወደ ታራሚው ተተኮሰ፡፡ ታራሚውም እየተመታ ሲወድቅ ቀሪው ነብስ አውጭኝ በማለት ወደ መኝታ ክፍል በመግባት በሚሯሯጥበት ሰዓት የጭስ ቦንብ በከፍተኛ ሁኔታ ወደ ግቢው በመወርወሩ እና ግቢው በመቃጠሉ (ዞን 2 እና ዞን 3) ታራሚው በከፍተኛ ስቃይ ወደ ቅጥር ጊቢው ለመውጣት በምንታገልበት ጊዜ ወንድሞቻችን በጥይት ተመትተው ወደቁ፡፡ ወደ ቅጥር ጊቢው ከወጣን በኋላ እስከ ማታ እንድንውል ተደርጎ በማንነታችን በዘራችን ተጠርጥረን በገባንበት ክሳችን እናም በሐይማኖታችን በማ/ቤት ተለይተን 175 ሰዎች ከፍተኛ ድብደባ ተፈፅሞብን ወደ ሸዋሮቢት ማ/ቤት የተወሰድን ሲሆን በጠቅላላው ታራሚው ልብሱን የአንገት ሐብሉን (የወርቅ የብር) የጣት ቀለበት (የጋብቻ የጌጥ) መፅሐፍት ለመፅሐፍ ቅዱሱ ቁራን እና ሌሎችን ጨምሮ) በኪሱ የያዘውን ገንዘብ እና ጫማውን ከተዘረፉ በኋላ ወደ ሸዋሮቢት እና ዝዋይ ማ/ቤት ተጭነን እስከ መስከረም 19 ቀን 2009 ዓ.ም በማ/ቤት ፖሊሶች በየቀኑ ሽንት ቤት ስንጠቀም ምግብ ስንመገብ ለሁለት ለሁለት እንደታሰርን እንድንጠቀም ተደርጎ ከፍተኛ የሆነ ድብደባ ይፈፀምብን ነበር፡፡ ሽንት ቤት ለሁለት እንደታሰርን በተቀመጥንበትም ጭምር እየተደበደብን እጃችን ወደ ኋላ እየታሰርን ጭቃ ላይ እየተንከባለልን ውሃ እየተርከፈከፈብን ዘግናኝ ድብደባ የተፈፀመብን ቆይተናል፡፡ ያለ ጫማ ሽንት ቤት እንጠቀም ነበር፡፡ ከመስከረም 20 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ ከዝዋይ እና ከሸዋ ሮቢት የመረጡንን ታራሚዎች እና በወቅቱ ቃጠሎ ሲፈፀም በጨለማ ቤት የነበሩትን (ከግንቦት 2 ቀን 2008 ዓ.ም) ጀምሮ መ/አ/ ማስረሻ ሰጤ፣ አበበ ኡርጌሳ እና እስሜኤል በቀለን እንዲሁም ከእነሱ ጋር በጨለማ ቤት የነበረው ተፈርዶበት ወደ ዝዋይ ማ/ቤት ሄዶ የነበረው ፍቅረማርያም አስማማውን ቃጠሎውን የረዥም ጊዜ ዝግጅት በማስመሰል እነሱንም ወደ ሸዋ ሮቢት በማምጣት ኢትዮጵያ ተቀብላ ያፀደቀቻቸው አለማቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን እና ህገ መንግስታዊ መብታችን እንዲሁም አሁን በስልጣን ላይ ያለው የኢህአዴግ መሪዎች ደርግን አስወግደው ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲህ አይነት ሲቃይ(ቶርቸር) አይደገምም ብለው ሐውልት ያቆሙለትን ነገር እጅግ አሰቃቂ፣ አስነዋሪ እና ዘግናኝ በሆነ ሁኔታ "በተሰፋልህ ልክ ትለብሳለህ ወደድክም ጠላህም የፖለቲካ መልስ ትሆናለህ" እየተባልን፡- 1ኛ. ሁለት እጃችን በካቴና ታስሮ ወደ ጣራ በማንጠልጠል እግሮቻችን በአየር ላይ በየአቅጣጫው ከማገር ጋር እየወጠሩ፤ 2ኛ. የእጃችን አውራ ጣቶች በሲባጎ በአንድ ላይ ከታሰሩ በኋላ በእጃችን መሀል ጉልበታችን ታጥፎ እንዲገባ ከተደረገ በኋላ በጉልበታችን መሀል እንጨት ተደርጎ ተዘቅዝቀን ተሰቀለን ውስጥ እግራችን በከፍተኛ ሁኔታ ተደብድበናል፤ 3ኛ. በኤሌክትሪክ ሾክ ተደርገናል፤ 4ኛ. ብልታችን ላይ ሀይላንድ ውሃ ተንጠልጥሏል አሁን ማህን እንሁን አንሁን አናውቅም፤ 5ኛ. ጥፍራችን በፒንሳ ተነቅሏል፡፡ እጆቻችን ነሐሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም ማታ በካቴና የታሰርን የተፈታነው ታኅሳስ 17 ቀን 2009 ዓ.ም ነው፡፡ በአጠቃላይ መሬት እና ሰማይ ድብልቅልቅ እስከሚልብን ድረስ እየተደበደብንና እየተሰቃየን ዘግናኝ የሆነ ኢ-ሰብዓዊ ረገጣ ተፈፅሞብናል፡፡ አንዱን ተሰቃይ አደራጅ ሌላውን ተደራጅ በማስመሰል አማራ፣ ጉራጌ እና ደቡቡን የግንቦት 7 አደራጅ፤ ኦሮሞውን የኦነግ አደራጅ፤ በሐይማኖት ነፃነት ጥያቄ የገቡ ሙስሊሞችን የአልሸባብ አደራጆች፤ ድሃውን የአዲስ አበባ ወጣት ደግሞ ከላይ በተጠቀሱት ተደራጅ እና ሀገራቸውን በህክምና ሊያገለግሉ ከስዊድን አገር ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የአዲስ የልብ ህክምና ባለቤት የሆኑትን ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ እና በሙስና ተጠርጥሮ የታሰረው ሚስባህ ከድርን የገንዘብ ምንጭ (ደጋፊ) በማስመሰል በነሀሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም በቃጠሎው ዕለት ዶ/ር ፍቅሩ ባዘጋጁት 60 መኪኖች በጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል አካባቢ እንዲቆም ተደርጎ ከእስር ቤት አምልጠን በአምስት አቅጣጫ (በጎንደር በአሶሳ በሞያሌ በኢትዮጵያ ሶማሌ) አድርጋችሁ ወደ ኤርትራ በመሄድ ከአሸባሪ ድርጅቶች ጋር ልትገናኙ አስባችኋል፣ ቂ/ማ/ቤት አቃጥላችኋል (በዕለቱ ግን አንድም ታራሚ የተለየ እንቅስቃሴ አላደረገም/የሚል ሰነድ በማዘጋጀት የእኛ ያልሆነ በወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ 27/2 ቃል እንድንፈርም ተደርጎ ፅሁፉንም እያጠናን እንድንለማመድ ከተደረገ በኋላ ቪዲዮ የተቀረፅን ሲሆን እርስ በርስ ከስቃይ ብዛት እንድንገናኝ እያደረጉ "አደራጅቻለሁ፣ ገንዘብ ሰጥቻለሁ፣ ኤርትራ ልንሄድ ነበር፣ ከእስር ቤት ልናመልጥ ነበር" እንድንባባል አደረጉ፡፡ የቃጠሎውን መንስኤ እና እውነት ወደ ጎን በመተው የማናውቀውን እና የእኛ ያልሆነውን በተባለው መልኩም ያልተፈፀመውን ወንጀል የእኛ ለማስመሰል በእንዲህ አይነት ሁኔታ ከ1 ወር ከ15 ቀን በላይ (ለሁሉም ሰው የፈጀው ጊዜ ነው) የፈጣሪ ያለህ፣ የመንግስት ያለህ፣ በህግ አምላክ ግደሉን እናቴ አባቴ ወየው ስንል ሰሚ አጥተን አካላችን ጎሎ ሞራላችን ተነክቶ 38 ሰዎች 19ኛ ወ/ችሎት በሽብር አንቀፅ 3/11214/ እና 6 ተከፍቶብን በግፍ እስር ላይ እንገኛለን፡፡ ፍ/ቤት ቀርበን ህገ መንግስታዊ መብቶቻችን ተጥሰዋል፤ 1ኛ በግዳጅ የተገኘ ቃል በህገ መንግስቱ የተከለከለ መሆኑን አስረድተን በ27/2 መሰረት በሲቃይ ብዛት የሰጠነው ቃል ውድቅ ይደረግልን፤2ኛ ያሰቃዩንን እና ኢሰብዓዊ ድርጊት የፈፀሙብንን የመርማሪ ፖሊሶች የማ/ቤት አመራር እና ፖሊሶች መክሰስ እንድንችል ፖሊስ ቃላችን እንዲቀበለን፤ 3ኛ አካላችን ላይ የነበረው ጠባሳ (በአሁኑ ወቅት የአብዛኞቻችን ድኗል/ሽሯል) ፎቶ ግራፍ እንድንነሳ፤ 4ኛ የቂሊንጦ ቃጠሎ መንስኤውን ገለልተኛ ወገን እንዲያጣራው ፍ/ቤቱ እንዲያዝ እና ፍርደኞች ወደ ፍርድ ክልል (ቃሊቲ) እንዲሄዱ ተደርጎ ክሳችንን ከዚያ ሆነን እንድንከታተል ያቀረብነው አቤቱታ እና የህይወት ዋስትና እንዲሰጠን አቤቱታ ያቀረብን ቢሆንም ፍ/ቤቱ አንድም ነገር ሳይበይን ለግንቦት 14 ዓቃቢ ህግ በሃሰት ያደራጃቸውን ምሰክሮች ለመስማት ቀጥሮናል፡፡ ማ/ቤቱም ለምን አቤቱታ አቀረባችሁ በማለት 37 ሰዎችን 4 በ5 በሆነች ጠባብ ቤት ውስጥ ጨለማ ክፍል ከ2 ወር በላይ በመቆየት አሰቃይተውናል፡፡ ከዚሁ ቃጠሎ ጋር በተያያዘ 121 ሰዎች ልደታ 3ኛ ወ/ችሎት በአንድ መዝገብ የከሰሱ ሲሆን 8 ሰዎችን እያንዳንዳቸው እና የ539/1ሐ የወ/ህግን በመተላለፍ የከሰሳቸው ሲሆን ቀሪዎችን ደግሞ በከባድ ንብረት ማውደም እና ሁከት ሁለት ክስ ከፍቶባቸው አቤቱታ አንሰማም ተብለን እኛም ፍ/ቤቱን ሳይስማ ክሱ አይነበብም ብለን አሁን ለግንቦት 14 ቀን 2009 ዓ.ም ዐ/ህግ ክሱን 20/20 እያደረገ እንዲያደራጅ የቀጠረን ሲሆን ልደታ 3ኛ ወ/ችሎት እናቀርባለን፡፡አንደኛ በእስር ላይ የነበሩ ሰዎችን በቃሊቲ ማ/ቤት ዞን 8 አስቀምጠው በሐሰት እኛ ላይ ከመሰከሩ ከዚህ ቀደም ተከሰውበት የገቡበት ክስ እንደሚቋረጥላቸው (እንደሚፈቱ) ቃል ተገብቶላቸው በሀሰት ሊመሰክሩብን ተዘጋጅተዋል፡፡ እኛ የደሀ ልጆች ፍትህ ፊቷን አዙራብን መንግስት ሁሉን አጠንክሮብን ስለኛ የሚሟገትልን አካል አጥተን አሁን ለብቻ በተሰራልን ቂ/ማ/ቤት ጠባብ ጊቢ ውስጥ ተስፋ በቆረጠ ኑሮ ውስጥ እንገኛለን፡፡ ክሱን እንቆቅልሽ የሚያደርገው ደግሞ ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ አስገብተውላቸዋል በማለት የማ/ቤት 8 ፖሊሶች ነገሩን እውነት ለማስመሰል ወደ ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ወስደው ከመረመሯቸው በኋላ በዋስትና ለቀዋቸዋል፡፡ ይህም ከሽብር አዋጁ ጋር በተፃረረ መልኩ ሲሆን እኛ ግን ቀደም በገባንበት ክሳችን ነፃ ብንባልም (ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ እና ሚስባህ ከድርን ጨምሮ ብዙ ሰው ነፃ የተባለ አለ) እንዲሁም በቀደም ክሳችን ተፈርዶብን የተፈረደብንን ፍርድ ብንጨርስም በአሁኑ የሀሰት ክስ በግፍ እስር ላይ እንገኛለን፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ ስደተኞችን ለመቀበል በአለም 2ኛ ሆና እያለ በእኛ በዜጎች ላይ እንዲህ አይነት አረመናዊ ኢሰብዓዊ ድርጊት ሲፈፀም እውን በስልጣን ላይ ያሉ መሪዎች አያውቁምን? የሐይማኖ አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች እና አባላት፣ የመንግስት ባለስልጣናት፣ የሲቪክ ማህበራት፣ ጋዜጠኞች እና የሟች ቤተሰቦች ዝም ማለታቸው እጅግ ልብ የሚሰብር ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ እና አለማቀፍ ማህበረሰቡን የሚመለከት የህሊናና የሰብዓዊነት ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም በፖሊስ የተሰጠን የሐሰት ክስ ተቋርጦ በሰብዓዊ መብት ሪፖርት መሰረት እንደገና ምርመራ ተደርጎ እኛን ስለማይመለከተን ክሱ ለባለቤቱ እንዲሰጥ እያልን ከዚህ ደብዳቤ ጋር አባሪ አደረግን በሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሪፖርት የተነሱ እና ያልተነሱ በተጨማሪ በምርመራ የደረሰብንን አጠቃላይና ያለውን እውነት አያይዘን የላክን መሆኑን እንገልፃለን፡፡

https://netsanetlegna.wordpress.com/2017/05/13/%e1%8a%a5%e1%8c%86%e1%89%bb%e1%89%bd%e1%8a%95-%e1%8a%90%e1%88%90%e1%88%b4-28-%e1%89%80%e1%8a%95-2008-%e1%8b%93-%e1%88%9d-%e1%88%9b%e1%89%b3-%e1%89%a0%e1%8a%ab%e1%89%b4%e1%8a%93-%e1%8b%a8%e1%89%b3/
https://netsanetlegna.wordpress.com/2017/05/13/%e1%8a%a5%e1%8c%86%e1%89%bb%e1%89%bd%e1%8a%95-%e1%8a%90%e1%88%90%e1%88%b4-28-%e1%89%80%e1%8a%95-2008-%e1%8b%93-%e1%88%9d-%e1%88%9b%e1%89%b3-%e1%89%a0%e1%8a%ab%e1%89%b4%e1%8a%93-%e1%8b%a8%e1%89%b3/

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen