Netsanet: ለዩኒቨርሲቲ መምህራን የሚሰጠው ስልጠና ተቃውሞ ገጠመው

Mittwoch, 1. Oktober 2014

ለዩኒቨርሲቲ መምህራን የሚሰጠው ስልጠና ተቃውሞ ገጠመው



• አዳዲስ ተማሪዎች ካልሰለጠናችሁ አትመዘገቡም ተብለዋል

ባለፉት ሳምንታት ለተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ሲሰጥ የነበረውን የ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ›› የማጥመቅ ስልጠና ከትናንት ጀምሮ ለ10 ቀናት ለዩኒቨርሲቲ መምህራን እየተሰጠ ሲሆን፣ ስልጠናው ከፍተኛ ተቃውሞ እንደገጠመው በጎንደርና ደብረማርቆስ ስልጠና ላይ የሚገኙ መምህራን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ስልጠናውን የሚሰጡት የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ተፈራ ደርበውና የቀድሞው የትምህርት ሚኒስትር ዶ/ር ስንታየሁ ወልደሚካኤል እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በሁለም ዩኒቨርሲቲዎች ስልጠና ላይ የሚገኙ መምህራን ፈታኝ ጥያቄዎችን እንዳነሱ የተገለጸ ሲሆን በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ‹‹የምንሰለጥንበት ሰነድ ለምሁራን የሚመጥን አይደለም፣ ጽንፈኛ ነው፣ ኒዮ ሌብራሊዝምን ጭራቅ አድርጎ ማቅረብ ተገቢ አይደለም፤ ሰነዱ ማጣቀሻ ስለሌለው እንደ ሰነድ ልናየው አንችልም፣ ይህ ስርቆት (ፕላጃሪዝም ነው)፣ ልማታዊ መንግስት ‹‹ዲፔንደንሲ ቲዮሪ›› ከተባለው የተወሰደ እንጂ የራሱ የሆነ ነገር የለውም፣ ነጸነት በሌለበት በነጻነት ተናገሩ አትበሉን፣ በነጻነት የተናገሩት እስር ቤት ገብተዋል፣ እኛ ምን ዋስትና አለን›› እና የመሳሰሉት አስተያየቶችና ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡

በተመሳሳይ በደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ሰነዱ፣ ‹‹ህወሓት ከተሰነጠቀ በኋላ መለስ የጻፈው ነው፣ የአንድ ሰው ሀሳብ ሊጫንብን አይገባም፣ ልማታዊ መንግስት ጥቂት የስርዓቱ ደጋፊዎችን ማበልጸግና አብዛኛውን ህዝብ ማደህየት ነው፣ ኢህአዴግ ድሃ ህዝብና ሀብታም ፓርቲ ለመፍጠር ነው የሚሰራው፣ ፌደራሊዝሙ ዋነኛ የግጭት ምንጭ ነው፣ የመሬት ፖሊሲው ዜጎችን ይከፋፍላል፣ 23 አመት ገዝታችኋል፣ ለቀጣይ 40 አመት እገዛለሁ ማለትም ተገቢ አይደለም›› የሚሉ ጥያቄዎችና አስተያየቶች መነሳታቸውን የነገረ ኢትዮጵያ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ለ10 ቀን የሚሰጠው ስልጠና በመጀመሪያ በሰፊ አዳራሽ ስልጠናው የሚሰጥ ሲሆን ከስልጠናው በኋላ መምህራን በየትምህርት ክፍላቸው ተከፋፍለው ጥያቄ እንዲጠይቁና እንዲወያዩ እንደሚደረጉ ሰልጣኞቹ አክለው ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል አብዛኛዎቹ ዩኒቨርሲቲዎች በኢቲቪ (ኢቢሲ) ለምዝገባ የጠሯቸውን የመጀመሪያ አመት ተማሪዎች ከምዝገባ በፊት ለ10 ቀን እንዲሰለጥኑ እያደረጉ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሊያስመዘግቡ የመጡ ወላጅ ልጃቸውን እንዲመዘግቡላቸው በጠየቁበት ወቅት ‹‹ከመመዝገባችሁ በፊት ስልጠና መውሰድ አለባችሁ፡፡ ከስልጠናው በፊት አንመዘግብም›› እንዳሏቸው ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ በተመሳሳይ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ለምዝገባ የጠራቸው ጀማሪ ተማሪዎች ለስልጠናው እንዳይዘገዩ አዲስ አበባ ድረስ መጥቶ በአውቶቡስ እየወሰደ እንደሚገኝ ምንጮች አክለው ገልጸዋል፡፡

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen