Netsanet: የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ትብብር የመግባቢያ ስምምነት ሠነድ

Dienstag, 21. Oktober 2014

የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ትብብር የመግባቢያ ስምምነት ሠነድ

I.መግቢያ፡-

1.1. ጥቅምት 15 ቀን 2005 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በምርጫ 2005 የጊዜ ሰሌዳ ላይ ከፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ለመምከር በአዳማ በጠራው ስብሰባ ከተሳተፍን ድርጅቶች 41ዱ ‘’ ከምርጫ ሰሌዳው በፊት በምርጫ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ እንነጋገር‘’ በማለት ላቀረቡት ኃሳብ ምርጫ ቦርድ ’’ መጀመሪያ የጊዜ ሰሌዳ አጽድቀን ካልሆነ‘’ብሎ ባቀረበው ኃሳብ ባለመስማማት ፔቲሽን ከፈረሙ 33ት የፖለቲካ ፓርቲዎች ሃያ አራታችን(24) ግንኙነታችንን በመቀጠል በጉዳዩ ላይ በጋራ እየመከርን ቆይተን በሂደት የጋራ ስምምነት መፈራረማችን ይታወሳል፡፡ ከምርጫ ጋር የተገናኙ ጥያቄዎችን ለምርጫ ቦርድ፣ለመንግስት አካላትና ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብና ለጋሽ አገራት ተወካዮች አቅርበን የነበረ ቢሆንም የጉዳዩ ቀዳሚና ዋነኛ ባለቤት ከሆነው ምርጫ ቦርድ ያገኘነው ምላሽ ጥያቄዎቻችን ሙሉ በሙሉ ውድቅ ከማድረግ አልፎ በማጣመም ለፕሮፖጋንዳ ፍጆታ በማዋል የገዢው ፓርቲ ጉዳይ ፈጻሚነቱን ያረጋገጠበት በመሆኑ፤ 

1.2. ባለፉት 23 ዓመታት አገራችን በአንድ ፈላጭ ቆራጭ አምባገነናዊ ፓርቲ አገዛዝ ሥር ወድቃ ድህነት እየተንሰራፋ፣የኑሮ ውድነቱ እያሻቀበ፣ማህበራዊ ቀውስ( ሥራ አጥነት፣መፈናቀል፣የማህበራዊ አገልግሎት አቅርቦትና ጥራት ማሻቆልቆል፣ ሰርቶ የመኖር ዋስትና ማጣት…) እየተባባሰ ፣መልካም አስተዳደር እየተደፈጠጠ፣ሙስና እየነገሰ፣በአጠቃላይም ህገመንግስቱ እየተሸራረፈና የዜጎች ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች እየተጣሱ በመሆናቸው የተቃውሞው ጎራ የተባበረ ትግል ጊዜ የማይሰጠው መሆኑን እኛም ሆንን መላው የሀገራችን ህዝብ ያረጋገጡት በመሆኑ፣ 

1.3. ዛሬም ገዢው ፓርቲና መንግሥት ባልተለያዩበት ሥርዓት ውስጥ በመሆናችን የሰብአዊና ዲሞክራሲ መብቶች ይከበሩ፣የህግ የበላይነት ይስፈን፣ በነጻ የመደራጀትና ኃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብቶች ይከበሩ… ጥያቄዎችን የሚያነሱ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችን፣ጋዜጠኞችን፣የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን በአጠቃላይም ከገዢው ፓርቲ ዓላማ፣ፍላጎትና ኃሳብ በተለየ መንቀሳቀስ ቀርቶ ማሰብ በካድሬ እርምጃና በፈጠራ ወንጀሎች ለእስራት፣ስደት፣መፈናቀል፣ ጎዳና ተዳዳሪነት፣ ስቃይና እንግልት፣…የሚዳርግ መሆኑን በመረዳት፤በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ገዢው ፓርቲ/መንግስት ከምርጫ 97 በኋላ ያወጣቸውን አፋኝ ህጎች ተከትሎ እየወሰደ ያለው እርምጃ እየከፋ መጥቶ በ2005 ዓ.ም ምርጫ ወቅት ‹‹የፖለቲካ ምህዳሩ ጠቧል›› ካልነው ደረጃ አልፎ ‹‹የፖለቲካ ምህዳሩ ተዘግቷል›› ወደሚያስብል ደረጃ መሸጋገሩንየእምነት ነጻነት ጠያቂዎች፣ጋዜጠኞች፣ጦማሪያን፣የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፣ ለእስር የተዳረጉበት፣የነጻውን ፕሬስ የተዘጉበትን እውነታ በማጤን

1..4 የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ከወረቀት እንዳያልፍ በተደረገበትና ለዚህም ገዢው ፓርቲ/መንግሥት ሃቀኛ ዲሞክራቲክ ሠላማዊ ኃይሎችን ለማቀጨጭ ከሚያደርገው ህገ ወጥ አካሄድ ጎን ለጎን ዜጎችን በማስገደድ ጭምር ከመመልመል አልፎ << አማራጭ >> የምርጫ ተፎካካሪዎችን በዳረጎት እያዘጋጀ መሆኑን በጋራ ለባለድርሻ አካላት የማሳወቅ አስፈላጊነትንና ወቅታዊነት በመረዳት፤ 

1.4. የጋራ እንቅስቃሴአችን በምናደርገው ሰላማዊ ትግል ብቸኛው የሥርዓት ለውጥ ማምጫ መንገድ ነጻ፣ፍትሃዊ፣ተኣማኒ፣…ምርጫ በመሆኑና በምርጫው ዙሪ በየወቅቱ ያነሳናቸው ጥያቄዎች ደግሞ የህገመንግስትና የዲሞክራሲና ሰብአዊ መብቶች መከበር ጥያቄዎች እንደመሆናቸው በምርጫ ሰሞን ብቻ የሚከናወኑ ሣይሆን በዘላቂነት ህዝብን የማደራጀት፣የማነቃነቅና የማታገል ቀጣይነት ያላቸው ተግባራት መሆናቸውን በማጤን፣ለትብብራችን ቀጣይነትና ዘላቂነት በመተማማንና በመተባበር መንሳቀስን አስፈላጊነት አጽንኦት በመስጠት፤

በትብብር የሠላማዊ ትግል ስልቶችን በመጠቀም የተቀናጀ የጋራ ትግል ለማድረግ ይህን የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ዛሬ ጥቅምት 11 ቀን 2007 ዓ.ም. ተፈራርመናል፡፡

II የትብብሩ አስፈላጊነትና ወቅታዊነት ላይ የተደረሰ የጋራ ግንዛቤ፡-
2.1. ነጻ፣ፍትሃዊ፣ተኣማኒ …ምርጫን በሚመለከት፡-

2.1.1. በሀገራችን የመድብለ ፓርቲ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታን በትክክል ተግባራዊ ለማድረግ ነጻ፣ፍትሃዊ፣ተኣማኒ …ምርጫ የማይታለፍ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ በቀጣዩ ዓመት 5ኛው አገራዊ ምርጫ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይሁንእንጂ ምርጫውን ነጻ፣ፍትሃዊ፣ተኣማኒ ለማድረግ በገዢው ፓርቲና በተቃዋሚዎች መካከል ሊደረግ የሚገባው ውይይት ፣ድርድርና ስምምነት በገዢው ፓርቲ እምብተኝነት አልተሳካም፡፡ ከዚህ ቀደም በ‹‹33ቱ›› ባደረግነው ግምገማ የደረስንበትን አጠቃለን ያቀረብናቸው ጥያቄዎች እስካሁን ተገቢው መልስ አልተሰጣቸውም፡፡ በግምገማ የደረስንበት ‹‹አሁን ላለንበት ተጨባጭ ሁኔታ የሚመጥን መፍትሄ የሚሰጥ ገዢውን ፓርቲ ጨምሮ አንድም የፖለቲካ ፓርቲ የለም ›› የሚለው መደምደሚያ ቢኖርም ‹‹አለሁ›› የሚል ሠላማዊ የትግል ስልት የሚከተል ፓርቲ ከኖረም ወደ ሥልጣን ለመምጣት ብቸኛው መንገድ ምርጫ ነው፡፡ መጪው ምርጫ በአገራችን ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚደረገውን ሠላማዊ የፖለቲካ ትግል ወደ ወሳኝ ምዕራፍ የሚያሸጋግር እንደሚሆን ከፍተኛ ግምት አለ ፡፡ በመሆኑም ለመጪው ምርጫ ከፊታችን ያሉት አማራጮች ሁለት ናቸው፡፡ አንድም በመንግሥትና ህዝብ (ባለድርሻ አካላት በሙሉ) መካከል የመተማመን ስሜት በመፍጠር በፍትሃዊ፣ ነጻና ተኣማኒ ምርጫ በአገሪቱ ዲሞክራሲዊ ሥርዓት ለመገንባት የሚያስችል መሰረት የሚጣልበትና ወደ ቀጣይና ዘላቂ ሠላም ፣ልማትና መድብለ ፓርቲ ዲሞክራሲ የምንሸጋገርበት ፣ ያሊያም ህወኃት/ኢህአዴግ በያዘው የ‹‹በመቃብሬ ላይ›› አቋሙ ጸንቶ በጀመረው የጥፋት መንገድ ገፍቶ በህዝብና መንግሥት መካከል የሚኖረው ግንኙነት የበለጠ የሚበላሽበትና አገሪቱን ወደ ፍጹም አምባገነናዊ ሥርዓት የሚያሸጋግርበትና የከፋ አዘቅት የሚያወርድበት ነው፡፡

2.1.2. በአገሪቱ ያለን ዲሞክራቲክ የሠላማዊ ትግል ኃይሎች የተመሰረትነውም ሆነ የምንታገለው ሁለተኛውን አማራጭ ለመቀልበስ፣የመጀመሪያውን ተግባራዊ ለማድረግ ነውና ለዚህ የምንበቃበት ብቸኛው መንገድ ሠላማዊ የትግል ስልቶችን በመተግበር አልፎ በፍትሃዊ፣ ነጻና ተኣማኒ ምርጫ የሚወሰነው ትግል እንደመሆኑ የየፓርቲ ፕሮግራማችንም ሆነ አደረጃጀታችን …. የተለያየ ቢሆንም ባለንበት ተጨባጭ ሁኔታ ማናችንም ለዓላማችን እውን መሆንና ከግባችን ለመድረስ የምርጫ ሜዳውን ለማስተካከል የድርሻችንን ማበርከት የግድ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ከምርጫው ጋር የምናነሳቸው ጥያቄዎች እንዲመለሱና የምርጫው አደረጃጀት፤ አወቃቀርና አስተዳደር ነጻና ገለልተኛ መሆኑ እንዲረጋገጥ ማድረግ ወቅታዊ ስለሆነ ለዚህ በጋራ መቆምና መታገል ይኖርብናል ፡፡ 

2.2. የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት በሚመለከት፡-
2.2.1. የሁላችንም የጋራ የሆነ ብቸኛ መንገድ ለሆነው ምርጫ ጋሬጣዎችንና እንቅፋቶችን በጋራ በመጥረግና ማስተካከል ላይ አንዳችም ልዩነት የለንም፡፡ የዜጎች የፈለጉትን የፖለቲካ ኃሳብ በመቀበል በፖለቲካ ፓርቲዎች አባል ሆነው የመንቀሳቀስ፣ወይም የመደገፍ፣እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች ህዝቡን አደራጅተው በህዝቡ ውስጥ በነጻነት ተንቀሳቅሰው ዓላማቸውን፣ፕሮግራማቸውንና ፖሊሲዎቻቸውን የማሰራጨት… እንዳይችሉ ገዢው ፓርቲና መንግስትን መለየት አስቸጋሪ በሆነ መልኩ በሚያሳድሩት ተጽዕኖ በሚወጡ ህገ መንግስቱን በሚጻረሩና ዲሞክራሲን በሚጋፉ አዋጆች፣ደንቦችና መመሪያዎች የፖለቲካ ተሳትፎ መብቶቻቸው ተገድበዋል፡፡ ነጻ የሙያም ሆነ የማኅበረሰብ የሲቪክ ተቋማት እንቅስቃሴም በተመሳሳይ ታፍነዋል፡፡ በተቃራኒው ገዢው ፓርቲ/ መንግሥት ዜጎችን በማስገደድ ጭምር በአባልነት እየመዘገበ የፖለቲካ ምህዳሩን በማጥበብ በሜዳው ላይ ብቻውን እየፈነጨበት የሚገኝበትን ሁኔታ እንመለከታለን፡፡ 

2.2.2. ስለዚህ በዚህ ጉዳይ ላይ በጋራ ቆመን በኅብረት የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋና የተናጠልና የጋራ ነጻ እንቅስቃሴኣችን ላይ በገዢው ፓርቲ እየተፈጠሩ ያሉት ችግሮች እንዲስተካከሉ፣የነጻ የማኅበረሰብና ሙያ ማህበራት እንቅስቃሴም ከአፈና እንዲላቀቅ መወያየት፣ መጠየቅ፣ ተጽዕኖ ማሳደርና ለተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በነጻነት የፖለቲካ ሥራቸውን እንዲሰሩ በጋራ ለመንቀሳቀስ በምርጫ 2005 በ‹‹33ቱ›› የጀመርነውን ይዘን ባለመቀጠላችንና ዘገዬን ብለን ከመቆጨት ያለፈ የአስፈላጊነት ጥያቄ የለም፡፡ ባለፈው ላይ መጠበብ አይቻልም፣ ቁጭቱም መፍትሄ አማጭ/አዋላጅ ሊሆን ይገባዋልና በቀጣዩ ጊዜ በጋራ ምን እናድርግ? የሚለው ላይ በጋራ በመወያየት በሚደረስ ስምምነት መሰረት አቅምን አስተባብሮ በጋራ መንቀሳቀስ ጊዜ የሚሰጠው አይደለም፡፡ በዚህ መሰረት ገዢውን ፓርቲ ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት መካከል ብሄራዊ መግባባት መፍጠር የሚቻልበት የውይይትና ዕርቅ መድረክ ለማመቻቸት በጋራ መንቀሳቀስ የማይታለፍ ወቅታዊ ተግባራችን ነው፡፡ 

2.3. የዜጎችን ሰብዐዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች በሚመለከት፡- 
2.3.1. ሰብዐዊና ዲሞክርሲያዊ መብቶች ባልተከበሩበት የዜጎችን ነጻ ፖለቲካዊ ተሳትፎና ለመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ የሚኖራቸውን አስተዋጽኦ ውስን ያደርገዋል፡፡ የዜጎች ነጻ ፖለቲካዊ ተሳትፎ በሌለበት የዲሞክራሲ ተቋማት፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣የፕሬስ ተቋማት …በነጻነትና ገለልተኝነት ሊንቀሳቀሱ አይችሉም፡፡ ጠንካራ ተቃዋሚነት በጠላትነት በሚያስፈርጅበትና ለእስራት፣ ስደት፣በፈናቀል፣ሥቃይና ሞት በሚዳርግበት፣ ኃሳብና ተቃውሞን የመግለጽ ነጻነትንመጠየቅም ሆነ ተግባራዊ ማድረግ በሚያስወነጅልበትና የቱንም አደጋ ሊያስከትል በሚችልበት፣…ሁኔታ ውስጥ ለዜጎች አማራጭ የምርጫ ኃሳቦችና ፖሊሲዎችን በነጻነት የማቅረብ፣ የዜጎችም የመጠቀም ዕድል ጠባብ ይሆናል፡፡ ዜጎች ሰብዐዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን ለመጠቀም -ስለፖለቲካዊ ተሳትፎኣቸውና የፖለቲካ ሥልጣን ባለቤትነታቸውና ምንጭነታቸውን ባልተረዱበት ወይም መብታቸውን ካለፍራቻና መሸማቀቅ በማይጠቀሙበት ነጻ፣ፍትሃዊ፣ ተኣማኒ … ምርጫ እውን አይሆንም፤ዜጎች ልዩ ልዩ መብቶቻቸውንና ጥቅሞቻቸውን አቻችለው ለመኖርየሚስችላቸውን ነጻነት ተግባራዊ ማድረግ አይችሉም ፡፡ 

2.3.2. ስለሆነም የዜጎች ሰብዐዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ፣የህግ የበላይነት ተረጋግጦ ገዢው ፓርቲ በዜጎች ላይ የሚፈጽማቸውን የመብት ጥሰቶች በጋራ መቃወም፣ እንዳይፈጸሙ መከላከልና እንዲከበሩ በአንድነት መቆምና መንቀሳቀስ ከላይ የደረስንባቸው የጋራ ግንዛቤዎች ጋር የማይነጣጠል/የተቆራኘ ነው፡፡

III. ½FÐpoü¿ YHHŒ| WŒÆ ëRGû°… ¨?G!' 

ምርጫ 2007 በህገ መንግስቱ ላይ በተቀመጡ ዲሞክራሲያዊ መብቶች መሰረት ለመድብለ ፓርቲ ዲሞክራሲዊ ሥርዓት ግንባታ መሰረት መጣል በሚያስችል መንገድ ለማከናወን በልምድና ተሞክሮ የታዩ ችግሮች እንዲስተካከሉና በሁለቱ ተቀናቃኝ/ተፎካካሪ ኃይሎች ማለትም በገዢው ፓርቲና በሠላማዊ ዲሞክራቲክ ኃይሎች መካከል መተማመን እንዲፈጠር እንዲሁም የህዝብ የመምረጥ መብትና ነጻነት ተከብሮ (ፍትሃዊ፣ ነጻና ተኣማኒ ሆኖ) የአገሩና የሥልጣን ባለቤትነቱ እንዲረጋገጥ በጋራ መታገል ፤
በዚህ መሠረት ትብብሩ በሁለት ዋና ዓላማዎች ላይ ቆሟል፤እነዚህም

3.1.የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋትና የምርጫ ሜዳውን በማስተካከል የፖለቲካ ተወዳዳሪዎች በህዝቡ ውስጥ ያለአድልኦ በህግ መሰረት የምንቀሳቀሱበትና የሚወዳደሩበትን ሁኔታ ለማመቻቸት በጋራ ለመታገል፣ 

3.2. በአገሪቱ ውስጥ የሚታየው በሁለት ጠርዝ ላይ የቆመ ፖለቲካና የተካረረ በጥላቻ፣ በቀል፣ ሴራ፣ …. የታጀበ ያለመተማመን/ጥርጣሬ መንፈስ ለማስወገድ ገዢውን ፓርቲ ጨምሮ ሁሉን ባለድርሻ አካላት የሚያሳትፍ የብሄራዊ ውይይትና ዕርቅ መድረክ የሚፈጠርበትን ሁኔታ ለማመቻቸት በጋራ መንቀሳቀስ፤

Iv- o|qqP oÏR ½Gû»ና¬Œú wÐpR|
4.1. የዋና ዓላማዎች ማስፈጸሚያ የጋራ ተግባራት፡-
4.1.1. የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋትና የምርጫ ሜዳውን በማስተካከል የፖለቲካ ተወዳዳሪዎች በህዝቡ ውስጥ ያለአድልኦ በህግ መሰረት የምንቀሳቀሱበትና የሚወዳደሩበትን ሁኔታ ለማመቻቸት በጋራ መታገል፣ 
4.1.1.1. የመንግስትና የገዢ ፓርቲ መዋቅሮች የሚለዩበት፣ለምርጫ ተወዳዳሪዎች በእኩል የተመቻቸ የመወዳደሪያ የፖለቲካ ሜዳ እንዲፈጠር በጋራ መታገል፤
4.1.1.2. በምርጫ ተዋናዮች የሚታመን የምርጫ አስፈጻሚ አካል/መዋቅርና ተቀባይነት ያለው የምርጫ ሥርዓት እንዲኖር በጋራ መታገል፤
4.1.1.3. ከምርጫ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው የዲሞክራሲና አማራጭ ኃሳብ የሚያቀርቡ የሚዲያ ተቋማት በዓላማቸው መሠረት ለህዝብ መረጃና ዕውቀት የሚያስተላልፉበት ሁኔታ እንዲመቻች በጋራ መታገል፤
4.1.1.4. በህገ መንግስቱና በህግ ከተቀመጡት ውጪ እነዚህን ሁኔታዎች በሚገድብ መንገድ በመንግስትና ገዢው ፓርቲ የሚደረጉ ህገወጥ ተግባራት እንዲቆሙ፣ ከህገመንግስቱ የሚቃረኑና እነዚህን መብቶች የሚገድቡ አዋጆች ፣መመሪያዎችና ደንቦች እንዲታረሙ/እንዲስተካከሉ ወይም እንዲሰረዙ/፣ ካልታረሙም በጋራ ዕውቅና ለመንፈግ በጋራ መቆም፤
4.1.2. በአገሪቱ ውስጥ የሚታየው በሁለት ጠርዝ ላይ የቆመ ፖለቲካና የተካረረ በጥላቻ፣ በቀል፣ ሴራ፣ …. የታጀበ ያለመተማመን/ጥርጣሬ መንፈስ ለማስወገድ ገዢውን ፓርቲ ጨምሮ ሁሉን ባለድርሻ አካላት የሚያሳትፍ የብሄራዊ ውይይትና ዕርቅ መድረክ የሚፈጠርበትን ሁኔታ ለማመቻቸት በጋራ መንቀሳቀስ፤
4.1.2.1. በህገ መንግስቱ መሠረት የመንግስት መዋቅሮች ከገዢው ፓርቲ ተጽዕኖና ቁጥጥር ነጻ እንዲወጡ በጋራ መታገል፣
4.1.2.2. በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ ቦታዎች በዜጎች ላይ ለተፈጸሙ ህገወጥ እርምጃዎች አስፈላጊው ማጣራት እንዲደረግ፣ለተጎጂዎች ካሳ እንዲከፈል…ወዘተ፣መንግስት ይቅርታ እንዲጠይቅ፣…በጋራ መታገል
4.1.2.3. ለዘላቂ ሠላም፣ ጤናማ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት፣በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ዘላቂ አንድነት መሰረት የሚጣልበት ሥርዓት ለመፍጠር በጋራ መታገል፤
4.1.2.4. ይህን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የገዢው ፓርቲ አባላትን ከሥጋት ነጻ የሚያወጣ፣በህዝብና መንግስት መካከል ጤናማ ግንኙነት/መተማመን/የሚፈጥር ፣ በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የአንድነት፣እኩልነት፣መተማመንና አብሮነት፣ መንፈስ ... እንዲፈጠር ሁሉን አቀፍ ብሄራዊ የዕርቅና መግባባት ጉባኤ ለማካሄድ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት በጋራ መንቀሳቀስ፣ 
4.1.2..5.በህዝብ ሃብት የምንቀሳቀሱ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ከገዢው ፓርቲ ተጽዕኖ ተላቀው የህዝብና የተቃዋሚ ፓርቲዎችን በሚዛናዊነት የሚያገለግሉበት ሁኔታ እንዲፈጠር በጋራ መታገል፤
4.2. የትብብሩ የጋራ ዋና ዋና ተግባራት፤

4.2.1. መንግሥት በሚወስዳቸው የሀገርና የሕዝብ ዘላቂ ጥቅሞችን የሚጎዱ እርምጃዎች ላይ ተወያይቶ የጋራ አቋም መያዝ፣የአገርና ህዝብ ጥቅም ለማስጠበቅ በጋራ መሥራት፤
4.2.2. ይህንን የመግባቢያ ሰነድ በፈረሙ ፓርቲዎች ወይንም አባሎቻቸው ላይ መንግሥት ወይንም ገዥው ፓርቲ ሕገ-ወጥ እርምጃ በሚወስድበት ጊዜ ሁሉም ፓርቲዎች እርምጃውን በመቃወም በጋራና በአንድነት መቆም፣
4.2.3. የመግባቢያውን ሰነድ ከፈረሙ ፓርቲዎች አንድ ወይንም ከአንድ በላይ ሆነው ሰላማዊ የተቃውሞ እርምጃ ለመውሰድ ተስማምተው ሲንቀሳቀሱ በሃሳቡ ላይ በመወያየት ተገቢ ድጋፍ መስጠት፣
4.2.4. ፓርቲዎች በሚያደርጉት ዲኘሎማሲያዊ ጥረቶች በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ወጥነት ያለው አቋም በመያዝ ትግላቸውን በማቀናጀት መንቀሳቀስ፣
4.2.5. ምርጫን በተመለከተ የጋራ ስልት መቀየስ፣ ለተግባራዊነቱ በጋራ መስራት፤ 
4.2.6. በሃቀኛ ተቃዋሚነት የተሰለፉ ሌሎች ፓርቲዎች ሁሉ የዚህ ትብብር አካል እንዲሆኑ በጋራ ስምምነት ጥሪ ማድረግ፣
4.2.7. ትብብሩ በእቅድ ለሚያከናውናቸው ተግባራት ማስፈጸሚያ የሚውል የፋይናንስና ማቴሪያል ድጋፍ በጋራ ማሰባሰብ፣ አስተዋጽኦ ማድረግ፣
4.2.8. በተቃዋሚዎች መካከል ጤናማ ግንኙነትና የትግል አጋርነት መንፈስ እንዲጠበቅ ጥረት ማድረግ" በተቃዋሚዎች ላይ የሚሰነዘሩ የማጥላላት" የማንኳሰስና የመከፋፈል አፍራሽ እንቅስቃሴዎችን መከታተልና መከላከል፤
4.2.9. የትብብሩ አቅም እንዲጎለብት እንዳስፈላጊነቱ ከፓርቲ ፖሊሲ፣ ፕሮግራምና አይዶሎጂ ውጪ ባሉ የሁሉንም አባል ፓርቲዎችና የትብብሩን አቅም በሚያጎለብቱ በስምምነት በሚመረጡ ርዕሶች የተለያዩ ወረክሾፖች" ዐውደ ጥናቶችና የውይይት መድረኮች ማዘጋጀት፤ 
4.2.10. በዲሞክራሲ ግንባታ ሂደት ባለድርሻ ከሆኑ አካሎች ጋር መልካም የሥራ ግንኙነት መፍጠር! መረጃ መለዋወጥ" የጋራ በሆኑ ጉዳዮች በትብብር የመሥራት ሁኔታ ማመቻቸት፤
4.2.11. የሕዝቡን የአንድነት መንፈስ የሚያጎለብቱ እርምጃዎችን በጋራ መውሰድ "አፍራሽ የመከፋፈልና የማጋጨት አዝማሚያዎችን በጋራ መከላከል፤
4.2.12. መላው ሕዝብ ለዲሞክራሲያዊ ለውጥ በባለቤትነትና በቁርጠኝነት በጋራ እንዲቆም የተለያዩ ስልቶችን በመጠቀም ተከታታይ ቅስቀሳ ማድረግ " ትምህርት መስጠት የሚያስችል ስልት መቀየስና መተግበር፤
V- ልዩ ልዩ ኮሚቴዎችን ስለማቋቋም
ይህንን ትብብር ለማጠናከርና ከፍ ብሎ የተመለከቱትን ተግባራት በአጥጋቢ መንገድ ለማከናወን ትብብሩ የተለያዩ ቋሚና ጊዚያዊ ኮሚቴዎችን ያቋቁማል፡፡ እነዚህም ከሰነዱ ፈራሚ ፓርቲዎች የበላይ አመራር ሁለት ተወካዮች ያሉበት የትብብሩን እንቅስቃሴ በበላይነት የሚያስተባብርና የሚመራ የኢትዪጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አስተባባሪ ኮሚቴ ፣እንዲሁም የአስተባባሪ ኮሚቴውን ውሳኔዎችና የትብብሩን ዕቅድ የሚያስፈጽም ሴክሬታሪት በቋሚነተት ይቋቋማል፡፡ እንዳስፈላጊነቱ ሌሎች ንዑሳና ኮሚቴዎችና ጊዚያዊ ኮሚቴዎች ይቋቋማሉ፡፡
5.1. የኢትዮጵያ wcዋሚ ፓርቲዎች አስተባባሪ ኮሚቴ ተግባርና ኃላፊነት፡- 
አስተባባሪ ኮሚቴው ከትብብሩ አባል ድርጅቶች በጽሁፍ የሚወከሉ አንድ ቋሚ አባልና አንድ ተለዋጭ አባል በድምሩ ሁለት አባላት ያካተተ የትብብሩ ከፍተኛው የግንኙነት አካል ሆኖ የሚከተሉት ተግባርና ኃላፊነት ይኖረዋል፡፡

5.1.1. የትብብሩን እንቅስቃሴዎች የሚያቅዱና የሚያስፈጽሙ ሴክሬታሪያት አባላትን ከመካከሉ ይመርጣል ይሽራል፤
5.1.2. የሴክሬታሪያቱን ዕቅዶች የትብብሩ አባል የፖለቲካ ድርጅቶችን ፍላጐት /ኢንተረስት ጠብቀው መዘጋጀታቸውን ማረጋገጥና ማጽደቅ፤
5.1.3. የሴክሬታሪያቱን የሥራ እንቅስቃሴ መከታተል፣ መገምገምና ሪፖርቱን አድምጦ ውሳኔና የሥራ መመሪያ መስጠት፤ ስምምነት የተደረሰባቸው የጋራ ተግባራት በእቅድ መሠረት መከናወናቸውን ይከታተላል፤ 
5.1.4. በአስተባባሪ ኮሚቴው ተለይተው በሚወሰኑ ጉዳዮች ከሦስተኛ ወገኖች ጋር በሚደረግ ግንኙነትና ድርድር ከአባል ድርጅቶች መሪዎች መካከል ብቃትና ልምድ ያላቸውን በምርጫ ይወክላል፤ ውክልና ያነሳል፤
5.1.5. ለሥራ ማስፈጸሚያ በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው የሚዘጋጁ የአሰራር ሥርዓት፣ደንቦችና መመሪያዎች ይመረምራል፣ያጸድቃል፤
5.1.6. የአዲስ ፓርቲዎችን የአባልነት ማመልከቻ ከሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ሲቀርብለት በደንቡ መሠረት መርምሮ ውሳኔ ይሰጣል፤
5.1.7. የትብብሩን በጀት ያፀድቃል፤ ተግባራዊነቱን ይቆጣጠራል፡፡ 
5.1.8. የሥምምነት ሰነዱን ያሻሽላል፤
5.1.9. ሌሎች ተግባራትን ለሴክሬታሪያቱ ይሰጣል፡፡

5.2. የትብብሩ ሴክሬታሪያት ተግባርና ኃላፊነት
ተጠሪነቱ ለዐቢይ ኮሚቴ የሆነ የትብብሩን እንቅስቃሴ የሚያቅድና የሚያስፈጽም አምስት /5/ አባላት ያሉት ሴክሬታሪያት ይመረጣል፡፡ ሴክሬታሪያቱ የሚከተሉት ተግባራት ይኖሩታል፡፡
5.2.1. በጋራ የሚከናወኑ ተግባራት ዕቅድ ያወጣል፤ በአስተባባሪ ኮሚቴው ሲፀድቅ ተግባራዊ ያደርጋል፡፡
5.2.2. ለዕቅዱ ተግባራዊነት አስፈላጊ የሆኑ ንዑስ ኮሚቴዎችን ያቋቁማል፤የዕቅዶችን ተፈጻሚነት ያስተባብራል! ያስፈጽማል፤
5.2.3. ስለትብብሩ እንቅስቃሴ ለአስተባባሪ ኮሚቴው ወቅታዋ ዘገባ /ሪፖርት ያቀርባል፡፡
5.2.4. የአስተባባሪ ኮሚቴ ስብሰባ ይጠራል፡፡
5.2.5. በዕቅዱ የተያዙ ተግባራትን ለማስፈጸም አስተባባሪ ኮሚቴው« ወክሎ ከሦስተኛ ወገኖች ጋር ይገናኛል፣ መግለጫ ይሰጣል $
5.2.6. ለትብብሩ የሥራ እንቅስቃሴ በጀት ያዘጋጃል፡፡ በአስተባባሪ ኮሚቴ ሲፀድቅ ተግባራዊ ያደርጋል፡፡ 
5.2.7. የሴክሬታሪያቱ ጽ/ቤት ከአባል ድርጅቶች ጽ/ቤት አመቺ በሆነው ውስጥ ወይም እንዳስፈላጊነቱ የራሱን ጽ/ቤት ያቋቁማል፡፡
5.2.8. ለትብብሩ አስፈላጊ የሆኑ የአሠራር ሥርዓቶችን ደንቦችና መመሪያዎች ረቂቅ አዘጋጅቶ ለአስተባባሪ ኮሚቴ ያቀርባል፣ሲጸድቅ ተግባራዊ ያደርጋል፡፡
5.2.9. ሌሎች በአስተባባሪ ኮሚቴ የሚሰጡትን wግባራት ያከናውናል፡፡

5.3. ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች

5.3.1. የትብብሩ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት የአገልግሎት ጊዜ አንድ ዓመት ይሆናል፡፡
5.3.2. የትብብሩ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ከ2 ጊዜ በላይ በተከታታይ ሊመረጡ አይችሉም፣ምርጫው ከቀድሞ ኮሚቴ አባላት ቢያንስ ሲሶው በቀጣይ ኮሚቴ መቀጠላቸውን ያገናዘበ ይሆናል፡፡ 
5.3.3. የትብብሩ አስተባባሪ ኮሚቴ አንድ ሰብሳቢና አንድ ም/ሰብሳቢ፣ ፀሐፊና ም/ፀሐፊ ይኖረዋል፡፡ ሰብሳቢው እና ፀሃፊው በማይገኙበት ጊዜ ምክትሎች ተክተው ይሠራሉ፡፡
5.3.4. ስለትብብሩ የሥራ እንቅስቃሴ በትብብሩ ስም ለሚዲያ መግለጫ መስጠት የሚችሉት ሰብሳቢው እና ፀሐፊው ብቻ ይሆናሉ፡፡ እንደአስፈላጊነቱ ሌሎች የአስተባባሪ ኮሚቴ አባላትን ሊወክሉ ይችላሉ፡፡ 
5.3.5. ሰብሳቢው የአስተባባሪ ኮሚቴንና የዐቢይ ኮሚቴን መደበኛና አስቸኳይ ስብሰባ ይመራል፡፡
5.3.6. የትብብሩ ዐቢይ ኮሚቴ መደበኛና አስቸኳይ ስብሰባዎች እንዳመቺነቱ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ባሉዋቸው አባል የፖለቲካ ድርጅቶች ጽ/ቤት ውስጥ በዙር ይካሄዳሉ፡፡
5.3.7. የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መደበኛና አስቸኳይ ስብሰባዎች በኮሚቴው የወቅቱ ሰብሳቢ ጽ/ቤት ወይም በትብብሩ ጽ/ቤት ይካሄዳሉ፡፡
5.3.8. በትብብሩ የተፈጸመው ግንኙነትና የተደረሰበት ስምምነት እያንዳንዱ አባል ፓርቲ ከሌሎች ጋር በየትኛውም ከፍተኛ ደረጃ (ግንባርና ውህደት) በሚያደርገው የአብሮ መሥራት ግንኙነት ላይ ተጽዕኖ አያሳድርም፤ 
5.3.9. በዚህ ሰነድ ውስጥ ከተካተተው ዓላማና በዓላማው ሥር (3.1. እና 3.2) ሥር ከተቀመጡት ዝርዝር ተግባራት ሥር ሌላ/ሌሎች የጋራ ጉዳዮችን ማካተት ቢያስፈልግ በዐቢይ ኮሚቴው በሚደረግ ውይይትና በሚደረስ ውሳኔ መሰረት ይሆናል፡፡ 
የፖለቲካ ፓርቲ የፓርቲ መሪ/ተወካይ ስም፣ ፊርማና - Gኅተም

1.
2.
3.
4.
5.
6.
7.
8.
9.
10.
11.
12.
13.
14.
ጥቅምት 11 ቀን 2007 ዓ.ም ፤አዲስ አበባ

(ነገረ ኢትዮጵያ በትብብሩ ጉዳይ ቀጣይ መረጃዎችን እየተከታተለች ለማሳወቅ ትጥራለች)

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen