በቃለ ዐዋዲው ደንብ መሠረት፣ በካህናት እና ምእመናን አንድነት በየደረጃው የተዋቀረውና የቤተ ክርስቲያናችንን አስተዳደር ለመምራት ከፍተኛ የሥራ አስፈጻሚነት ሥልጣን የተሰጠው አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ፣ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ደረጃ ያካሔደውን ፴፫ኛ ሀገር አቀፍ ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ ጥቅምት ፰ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ቀትር ላይ የአቋም መግለጫ በማውጣትና የውሳኔ ሐሳብ በማቅረብ አጠናቅቋል፡፡
የ፴፫ኛው የመ/ፓ/አጠ/ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዓመታዊ ስብሰባ ተሳታፊ የመምሪያ ዋና ሓላፊዎች
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን መዋቅር ባለባቸው አህጉረ ስብከት ኹሉ በበጀት ዓመቱ የተከናወኑ ሃይማኖታዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅሰቃሴዎች የሚንጸባረቁበት ይኸው የአጠቃላይ ጉባኤው ቃለ ጉባኤ÷ የአቋም መግለጫ እና የውሳኔ ሐሳብ ዛሬ፣ ጥቅምት ፲፪ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ለተጀመረው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የመጀመሪያ ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባበግብዐትነት ቀርቦ ከጸደቀ በኋላ ለኹሉም አህጉረ ስብከት እንደሚላክ ተገልጧል፡፡
በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ አጠቃላይ ሪፖርት መግቢያ እንደተነገረው፣ ቤተ ክርስቲያናችን በኹለንተናዊ መልኩ ላስመዘገበችውና ለምታስመዘግበው ውጤት ‹‹ወደር የማይገኝለት ተግባራት የሚያከናውነውን›› ከፍተኛ የሥራ አስፈጻሚዎች ጉባኤ – አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ – ዓመታዊ ስብሰባ ቃለ ጉባኤ የአቋም መግለጫና የውሳኔ ሐሳብ ዋና ዋና ሐሳቦች በማጠቃለል የዳሰስንበት ዘገባ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
ከኃምሳ አህጉረ ስብከት የተወከሉ ከ800 ልኡካን በላይ የተሳተፉበትና ከጥቅምት ፭ – ፰ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. የዘለቀው ይኸው ሀገር አቀፍ ዓመታዊ ስብሰባ አብዛኛውን ጊዜውን የወሰደው÷ ከብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ፣ ከአህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች፣ ከመምሪያዎችና ድርጅቶች ዋና ሓላፊዎች የቀረቡትን የበጀት ዓመቱን የሥራ አፈጻጸም ዘገባዎች በማዳመጥ ነበር፡፡ በበጀት ዓመቱ በኹሉም አህጉረ ስብከት ከፍተኛ የገቢ ዕድገት እንደተመዘገበ በሪፖርቶቹ የተጠቀሰ ሲኾን የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩንና የብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ሐዋርያዊ ጉዞዎች ጨምሮ በመልካም አስተዳደር የማሻሻያ ርምጃዎችና በራስ አገዝ የልማት እንቅስቃሴዎች የበለጠ ሊጠናከሩና ሊስፋፉ የሚገባቸው ተጠቃሽ ተሞክሮዎችበየአህጉረ ስብከቱ እንዳሉ ተመልክቷል፡፡
….በየዓመቱ በጥቅምት ወር መጀመሪያ የአጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በዋናነት አህጉረ ስብከት የሥራ ፍሬአቸውን የሚያቀርቡበት፣ እርስ በርስ ልምድ የሚለዋወጡበት ዐቢይ ጉባኤ ነው፡፡ ከአህጉረ ስብከት የሥራ ፍሬዎች መካከል አንዱ በዓመቱ ከምእመናን አስተዋፅኦ እና ከልዩ ልዩ ገቢዎች የሰበሰቡትን ገንዘብ በሕጉ መሠረት ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሚያስገቡበት ነው፡፡ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤትም ከኹሉም አህጉረ ስብከት ያሰባሰበውን በበጀት ቀምሮ ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በማቅረብ ሲወሰንለት ለልዩ ልዩ ሥራዎች ያውለዋል፡፡ ለምሳሌ በ፳፻፮ ዓ.ም. ለገዳማትና ለአብነት ት/ቤቶች በሚልዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ድጋፍ ተደርጓል፡፡ ኻያ ስድስት አህጉረ ስብከት ራሳቸውን ባለመቻላቸው በበጀት ተደጉመዋል፡፡ በሰበካ ጉባኤ ፍሬ ልዩ ልዩ ልማቶች ለምተዋል፤ አኹንም በመልማት ላይ ናቸው፡፡ በ፳፻፮ ዓ.ም. የበጀት ዓመት በኹሉም አህጉረ ስብከት የተሻለ ሥራ እየተሠራ እንደኾነ ከደረሱን ሪፖርቶች ለመረዳት ችለናል፡፡ አህጉረ ስብከት ከምእመናን የሚገኘውን አስተዋፅኦ መሰብሰብ ብቻ ሳይኾን የቤተ ክርስቲያናችን ምጣኔ ሀብት በዓለት ላይ የተመሠረተ ይኾን ዘንድ ልዩ ልዩ የልማት ሥራዎችን በመሥራት ላይ ናቸው፡፡ ልማቱ የቤተ ክርስቲያናችንን ገቢ ከማሳደጉም በላይ ለብዙ ዜጎችም የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡ አዲስ አበባን ሳይጨምር ሌሎች አርባ ዘጠኙም አህጉረ ስብከት ባደረጉት ከፍተኛ የሥራ እንቅስቃሴና የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያም እነርሱን ለመደገፍ በትምህርታዊ ሴሚናር በማጠናከሩ መምሪያው ዐቅዶት ከነበረው በላይ በዚኽ ዓመት ከፍተኛ የኾነ የፐርሰንት ገቢ ተገኝቷል፡፡ የበጀት ዓመቱን አጠቃላይ ገቢ /95,430,500.6/ ካለፈው ዓመት ጋራ ስናነጻጽር በ10,458,155.10 ብልጫ አሳይቷል፡፡ ይህ ከፍተኛ ዕድገት ሊገኝ የቻለው ብፁዓን አባቶች የአህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች እና በሥራቸው ያሉ ልዩ ልዩ ሠራተኞች ተግተው በመሥራታቸው ነው፡፡ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ገቢ የዚኽን ያኽል ካደገ የአህጉረ ስብከትና የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ገቢም ከዚኽ የበለጠ እንደኾነ እንረዳለን፡፡ በተለይም ከዚኽ በፊት ጎልቶ ይታይ ያልነበረው ከኢትዮጵያ ውጭ ያሉ አህጉረ ስብከትም ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ገቢ ማድረግ ያለባቸውን እያስገቡ ይገኛሉ፡፡ ….የገንዘብ ገቢን በማሳደግ በኩል በትጋት የተሠራ ቢኾንም ምእመናንን በመጠበቅና በማትረፉ በኩል ብዙ ይቀረናል፡፡ ምእመናንን ከነጣቂ ተኩላ በመጠበቅና ሃይማኖታቸውን እንዲያውቁ ዐውቀውም ራሳቸውን እንዲጠብቁ ለማድረግ በንቃት ልንሠራ ይገባናል፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን ቅዳሴው፣ ማሕሌቱ፣ ስብሐተ ነግሁ፣ ጸሎተ ፍትሐቱ እና ሌሎችም በቤተ ክርስቲያናችን አገልግሎት ላይ ያሉ ስብከቶቻችን ኾነው ለምእመናን ትምህርት ሊሰጥባቸው ይገባል፡፡ አኹን እየታየ ያለውን ዕድገት የበለጠ አጠናክሮ ማስቀጠል ይቻል ዘንድ ምእመናንን በማትረፍ በኩል ትጉህ ዘኢይነውም ኾነን መሥራት አለብን፡፡ በአጠቃላይ በአጠቃላይ በ፳፻፮ ዓ.ም. ለተገኘው ኹለንተናዊ ዕድገት ደከመን ሰለቸን ሳይሉ ሌሊት እና ቀን የሠሩት ኹሉም ብፁዓን አባቶች እና በሥራቸው ያሉ ካህናትና ምእመናን ምስጋናና ክብር ሰላምም ይገባቸዋል፡፡ /ሊቀ ማእምራን ፋንታኹን ሙጨ፤ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ዋና ሓላፊ/
ስብከተ ወንጌልን በማጠናከርና በማስፋፋት የምእመናንን ፍልሰት በማስቆምና የምእመናንን ቁጥር በመጨመር፤ የቃለ ዐዋዲውን ድንጋጌ በማስፈጸም ሰበካ ጉባኤን በማጠናከር፤ በሥልጣነ ክህነት አሰጣጥ፣ በንብረትና ቅርስ አጠባበቅ፤ ሕገ ወጥ አጥማቂዎችንና ፈቃድ የሌላቸው ሰባክያንን እንዲኹም የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ድብቅ ሤራ በመከላከልና በማጋለጥ ረገድ የታዩ ድክመቶችን፤ የሕንፃ ቤተ ክርስቲያን መሥሪያና የመቃብር ቦታ ለማግኘት ቤተ ክርስቲያን ጥያቄ ስታቀርብ የበታች ባለሥልጣናት ከሌሎች እምነቶች በተለየ አድልዎ መፈጸማቸውና የተፋጠነ ምላሽ አለመስጠታቸው አልበቃ ብሏቸው መብታቸውን የጠየቁ ካህናትንና ምእመናንን በጥፋተኝነት እየወነጀሉ ለእስርና እንግልት መዳረጋቸውና ያለጥፋታቸው የታሰሩትን ለማስፈታት ለበላይ አካል ጥያቄ ቢቀርብም መፍትሔ አለመገኘቱካጋጠሙ ችግሮች ዋነኞቹ እንደኾኑ ከቀረቡት ዘገባዎች ለመረዳት ተችሏል፡፡
በአሳሳቢነት የተጠቀሰውን የምእመናን ፍልሰት ለመግታትና የተሐድሶ መናፍቃንን እንቅስቃሴ ለመቋቋም ዐይነተኛው መፍትሔ÷ የችግሩን ደረጃ በሚመጥን ዝግጅት ስብከተ ወንጌልን በማስፋፋት ምእመናን በእምነታቸው ማጽናት፣ በትምህርተ ወንጌል አዲስ አማንያንን ለማፍራት መፋጠን፤ ቅዱስ ሲኖዶስ ስብከተ ወንጌልን በተመለከተ በተደጋጋሚ ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች መፈጸምና ማስፈጸም፤ የመልካም አስተዳደር ማሻሻያዎችን አጠናክሮ መቀጠል መኾኑን ጉባኤው በአቋም መግለጫው አሥምሮበታል፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግር የቤተ ክርስቲያንን ህልውና የሚፈታተንና የምእመናንን ፍልሰት የሚያባብስ እንደኾነ መገንዘቡን ጉባኤው ጠቅሶ፣ ሥርዐትና ትውፊትን በጠበቀ አኳኋን የመልካም አስተዳደር መርሖዎችን ለመተግበር ለኹሉም ሠራተኞች በየደረጃው የአስተሳሰብ ለውጥንና የአቅም ግንባታን መሠረት ባደረገ ሥልጠና ቤተ ክርስቲያን ልትደርስ ወደሚገባት በማድረስ ክብሯንና ልዕልናዋን ለመጠበቅ ቁርጠኝነቱን አረጋግጧል፡፡
ሥልጣነ ክህነትና ምንኵስና የሌላቸው አንዳንድ ግለሰቦች ወደማይታወቁበት ሀገረ ስብከት በመሔድ ‹‹ሥልጣነ ክህነት ተቀብለናል፤ መንኵሰናል›› በማለት በየቦታው ለሚፈጥሩት ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ለሚፃረር ችግር የመቆጣጠር፣ የማረምና የማስተማር ሓላፊነቱን እንደሚወጣ አስታውቋል፡፡ በማእከል ይኹን በአህጉረ ስብከት ደረጃ በሊቃውንት ጉባኤ ያልተመረመሩና ፈቃድ ያላገኙ የግለሰቦችና የቡድኖች የጽሑፍ፣ የድምፅ፣ የምስል ወድምፅ ኅትመት ውጤቶች በምእመናን አእምሮ ስሕተት እየዘሩ መኾኑን ከቀረቡት ዘገባዎች መረዳቱን ጠቅሶ፣ ኹኔታው ተባብሶ ከቀጠለ ትምህርተ ሃይማኖትንና ትውፊትን፣ ቀኖናንና ሥርዐትን ሊለውጥ ስለሚችል በአህጉረ ስብከት የተጠናከረ ቁጥጥርና ክትትል እንዲደረግ፣ በማእከል ደረጃ ደግሞ የሊቃውንት ጉባኤ የምእመኑን ጥያቄዎች ሊመልስ በሚችል መልኩ እያደራጀ ታትመው እንዲሰራጩ እንዲደረግ አስገንዝቧል፡፡ በዚኽ ረገድ ቅዱስ ሲኖዶስ ከአኹን በፊት በተደጋጋሚ የወሰናቸው ውሳኔዎች በተግባር እንዲውሉ ተግቼ እንቀሳቀሳለኹ ብሏል አጠቃላይ ጉባኤው – በአቋም መግለጫው፡፡
የቃለ ዐዋዲ ደንቡ ከሀገሪቱ ሕጎችና ደንቦች ጋራ ያጋጠሙትን የመጣጣም ችግሮች በመፍታት የቤተ ክርስቲያንን የአስተዳደር ሥራዎች በአግባቡ ለመምራት ሕገ ቤተ ክርስቲያኑንና ቃለ ዐዋዲውን የማሻሻል ሥራው በፍጥነት ተጠናቅቆና በቅዱስ ሲኖዶስ ጸድቆ መታተም እንዳለበት ያሳሰበው ጉባኤው፣ ይህ እስኪኾን ድረስ ባለው ቃለ ዐዋዲ ሰበካ ጉባኤን የማደራጀቱንና የማጠናከሩን ሥራ ተግተን እንሠራለን ብሏል፡፡
አጠቃላይ ጉባኤው አብነት ት/ቤቶችን ለመጠበቅ፣ ለማሳደግና ለማስፋፋት በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ በመንበረ ፓትርያርኩ የተመደበው አምስት ከመቶ በጀት ለአብነት መምህራንና ተማሪዎች መድረሱ የበለጠ እንዲረጋገጥ፤ በፓትርያርኩና በብፁዓን አባቶች አካላዊ ጉብኝት የሚደረገው ሞራላዊ ማበረታቻ ተጠብቆ እንዲቀጥልም ጠይቋል፡፡
ዘመኑ የሚጠይቀውን የተማረ የሰው ኃይል ለማፍራት የቤተ ክርስቲያናችን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የደቀ መዛሙርት ምልመላና ቅበላ እንዲኹም የትምህርት ዝግጅት በከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲከናወን ያሳሰበው አጠቃላይ ጉባኤው፣ ትምህርቱና ልማቱ ለልዩ ልዩ ቋንቋ ተናጋሪ የአገራችን ሕዝብ ይደርስ ዘንድ፣ የትምህርት ተቋማቱን አቅም በፈቀደ መጠን በሌሎች ቦታዎች ለማስፋፋት በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ የተደረሰበትን አቋም ለማሳካት ተግቶ እንደሚሠራ አስታውቋል፡፡
በትምህርተ ሃይማኖትና በሥነ ምግባር የታነፀ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለማፍራት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረጉ ያሉት የሰንበት ት/ቤቶች አገልግሎት በሀገር አቀፍ ደረጃ በወጣ ስትራተጂያዊ ዕቅድ እንዲመሩ መደረጉን አጠቃላይ ጉባኤው በጠንካራ ጎኑ ጠቅሷል፡፡ የበለጠ ውጤታማ እንዲኾኑም የምእመናንን የቋንቋ ብዙኅነት ከግምት በማስገባት ወጣቶች እንደ ዕድሜአቸው መጠን ሊማሩ የሚችሉበት ሥርዐተ ትምህርት በብሔራዊ ደረጃ እንዲቀረፅ፣ ማስተማርያ መጻሕፍትም እንዲዘጋጁና በማእከል በሊቃውንት ጉባኤ እየተመረመሩ እንዲሠራጩ ጉባኤው አሳስቦ፣ የማደራጃ መምሪያውና አህጉረ ስብከት በጋራ ለሚሠሩት ሥራ የበኩላችንን እንወጣለን ብሏል፡፡
‹‹ቅርሶቻችን የሃይማኖታችን አገልግሎት መፈጸሚያዎች፣ ብሔራውያትና ዓለም አቀፍ ሀብቶቻችን ናቸው፤›› ያለው አጠቃላይ ጉባኤው፣ በየጊዜው የሚደርስባቸው የዘረፋ፣ የቃጠሎ፣ የብልሽት ችግሮች አኹንም ያልቀረ በመኾኑ ከማስተማርና ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ ዘራፊዎችን በሕግ የመጠየቅና የማስቀጣት፣ ቅርሶችን የማስመለስና በቦታቸው በጥንቃቄ እንዲያዙ በማድረግ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ቅርስ ጥበቃ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን የተቀናጀ ሥራ ለመሥራት እንደሚተጋ፤ ነባር ቅርሶችንና ንዋያተ ቅድሳትን ከመጠበቅም በተጨማሪ በአኹኑ ወቅት እየተዘጋጁ ያሉት አልባሳትና ንዋያተ ቅድሳት የቤተ ክርስቲያንን ትውፊት ጠብቀው በማእከል ማምረቻና ማከፋፈያ ድርጅቶች እንዲደራጁና እንዲጠናከሩ ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ እንዲሰጥበት ጠይቋል፡፡
‹‹የኻያ አንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን ገባሬ ተኣምር›› የተባለው ሰበካ ጉባኤ ክፍያ በ፶ ሳንቲም አስተዋፅኦ መጀመሩን ያስታወሰው አጠቃላይ ጉባኤው፣ ዛሬ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚልዮን የሚቆጠር ገንዘብ መሰብሰብ መቻሉ የራስን አገልግሎትና የልማት ዕቅዶች በራስ አቅም የመፈጸም ጥረት በማሳደጉ እንዳስደሰተው ገልጧል፡፡ ገንዘብ መሰብሰብ ብቻ ሳይኾን የተገኘውን የእግዚአብሔር ገንዘብበተገቢው የሒሳብ አያያዝ ሥርዐት በጥንቃቄ በመያዝ፣ ሥራን በዕቅድ በመምራትና አፈጻጸሙን በወቅቱ በመገምገም ለሚገባው አገልግሎት ለማዋል፣ የቤተ ክርስቲያንን የፋይናንስ አቅም በቀጣይነት በማሳደግ በምእመናንዋ ልማት ላይ የተመሠረተ ሉዓላዊ ክብሯን ለመጠበቅ ተግቶ እንደሚሠራ በአጽንዖት ገልጧል፡፡
ግማሽ ሚልዮን የተማረ ኃይል ይዞ የሚንቀሳቀስን ማኅበር እንዴት በጥበብ እንይዘዋለን ብሎ ማሰብ ይገባል፡፡ ከሺሻና ከጫት ቤት ያሉ ወጣቶቻችንን መልሶ፣ በግቢ ጉባኤያት ያሉትን አስተምሮ ሰንበት ት/ቤት እንዲቋቋም፣ ሰበካ ጉባኤ እንዲደራጅ፣ ስብከተ ወንጌል እንዲስፋፋ እያደረገ ነው ያለው፡፡ ይልቅስ እንደ ማኅበረ ቅዱሳን አንሠራም? እንደነሱ አንሠራም?!
የሠሩ ሰዎች የሠሩትን ሥራ እንሰማለን፤ እናያለን፤ እናነባለን፤ ልጆቻችን ናቸው፤ ማበረታታት ሲገባ እነርሱን አስወጥቶ ሌላ ክርስቲያን መፈለግ ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ያጠፉት ጥፋት ካለ በማስረጃ ይቅረብ፡፡ የቅዱስ አባታችን ንግግር የእርሳቸውን አቋም ተከትለን እንድንሔድ ነው፤ ነገር ግን ለውሳኔ የሚረዳው ማስረጃ ነው፤ የሚያሸንፈው እውነት ነው፤ ስሕተት ካለ ማረም መገሠጽ ይገባል፤ የምንወስነው ውሳኔ እግዚአብሔር ያየዋል ብለን ማመን አለብን፡፡ ምናልባት የእነርሱ[የማኅበሩ] መኖር የሚጎዳው ሰው ካለ እኔ አላውቅም፤ አለዚያ መርዝ መርጨት ነው፡፡/የጅግጅጋ/ሶማሌ/ ሀገረ ስብከት ልኡክ/
የ፴፫ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዓመታዊ ስብሰባው፣ ከቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ አግኝተውም ኾነ ፈቃድ ሳይኖራቸው በተለያየ መልኩ ተደራጅተው በማገልገል ላይ ያሉ ማኅበራት፣ ለቤተ ክርስቲያን ዕድገትና ለስብከተ ወንጌል መስፋፋት የራሳቸው ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳላቸው በአቋም መግለጫው አስገንዝቧል፡፡
በተለይም ማኅበረ ቅዱሳን በቅዱስ ሲኖዶስ በጸደቀለትና እየተመራበት በሚገኘው መተዳደርያ ደንቡ መሠረት በየአህጉረ ስብከቱ በዘረጋቸው መዋቅሮች የፈጸማቸው ኹለንተናዊ የድጋፍ ተግባራት፣ በብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁና በአብዛኛዎቹ የአህጉረ ስብከት ሪፖርቶች ተካተው አጠቃላይ ጉባኤው አድምጧቸዋል፡፡ በሥራ አፈጻጸም ዘገባዎቹ እንደተዘረዘረውማኅበረ ቅዱሳን÷ ለገዳማትና አድባራት፣ ለአብነት ት/ቤቶች የሕንፃ ፕላን ሥራ፣ የፕሮጀክት ዝግጅት፣ የሥልጠና፣ በሕግ የማማከር አገልግሎት እና የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል፤ ልዩ ልዩ የብዙኃን መገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የትምህርተ ወንጌል አገልግሎት ሰጥቷል፡፡
ከማኅበራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ጋራ በተያያዘ የሚፈጠሩ የሰላም መደፍረስ ችግሮችን ቅዱስ ሲኖዶስ በጥልቀት መርምሮ አስፈላጊ ውሳኔ እንዲሰጥበት ጉባኤው ጠይቋል፤ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔንም በኹሉም የቤተ ክርስቲያን መዋቅሮች ውስጥ ለማስፈጸም ዝግጁ መኾኑን አረጋግጧል፡፡
Keine Kommentare:
Kommentar veröffentlichen