Netsanet: አቡነ ማቲያስ ማህበረ ቅዱሳንን ለጅብ ሊያስበሉት ነው፤ “…አሸባሪ የመሆን ዕድሉ የሰፋ ነው” አሉት

Donnerstag, 9. Oktober 2014

አቡነ ማቲያስ ማህበረ ቅዱሳንን ለጅብ ሊያስበሉት ነው፤ “…አሸባሪ የመሆን ዕድሉ የሰፋ ነው” አሉት

‹‹ሕግና ሥርዓት የማይቆጣጠረው ማኅበር ጽንፈኛና አሸባሪ የመሆን ዕድሉ የሰፋ ነው›› አቡነ ማቲያስ

ከገዳማትና ከአድባራት የተወከሉ አስተዳዳሪዎችና ጸሐፊዎች ግን ሕንፃውን ጭምር እየገለጹ ማኅበረ ቅዱሳን መሆኑን በመጥቀስ ዕርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀዋል

በአድባራትና ገዳማት የመልካም አስተዳደር እጦት መንገሡ ተገለጸ ባለፉት አሥርት ዓመታት የምዕመናን ቁጥር ቀንሷል ተብሏል


ቤተ ክርስቲያን ግልጽ የሆነ መዋቅር ያላት ቢሆንም በቤተ ክርስቲያን ስም የሚደራጁ ማኅበራት፣ ከመዋቅራዊ ቁጥጥር ውጭ በመንቀሳቀስ ሀብትና ንብረት ያከማቹና እያከማቹ በመሆናቸው፣ ሕግና ሥርዓት የማይቆጣጠራቸው ከሆነ አሸባሪ የመሆን ዕድላቸው የሰፋ መሆኑን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ አስታወቁ፡፡
ፓትርያርኩ ይህንን ያስታወቁት ‹‹የቤተ ክርስቲያንን አስተዳደራዊ አስተሳሰብ ማበልፀግ›› በሚል መሪ ቃል ከመስከረም 27 እስከ መስከረም 28 ቀን 2007 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት መስብሰቢያ አዳራሽ የተጀመረውን ጉባዔ በከፈቱበት ወቅት ነው፡፡
H_E_Abune_Matiyas_Archbishop_of_Jerusalem_Misa
በቤተ ክርስቲያን ስም የሚንቀሳቀሱ ማኅበራት ብቻ ሳይሆኑ ሌሎችም ከቤተ ክርስቲያን መዋቅራዊ ቁጥጥር ውጭ የሚንቀሳቀስ ሀብትና ንብረት ማካበት የተከለከለና በከባድ ወንጀል የሚያስጠይቅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ይህ ድርጊት እየተስፋፋ መሆኑን የጠቆሙት ፓትርያርኩ፣ እየታየ ያለው የማኅበራት ዝንባሌ ሀብት ማካበት፣ ለቤተ ክርስቲያን ብቻ የተፈቀደውን ‹‹አሥራት በኩራት›› ለራሳቸው መሰብሰብ፣ ከቤተ ክርስቲያን ዕውቅና ውጪ የአገር ውስጥና የውጭ ሥራዎችን በሌላቸው ሥልጣን እየሠሩ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ፓትርያርኩ እንዳብራሩት፣ ማኅበራቱ በሰበሰቡት ሕገወጥ ሀብት አባቶችን ይከፋፍላሉ፡፡ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችን ያሾማሉ፣ ያሽራሉ፡፡ እነሱ የሚፈልጉትን የማይፈጽሙትን እያስፈራሩ በመሆናቸው፣ አካሄዳቸው ለቤተ ክርስቲያኗ ጥንካሬና ህልውና ፍጹም አደጋ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በቤተ ክርስቲያን ስም ያለአግባብ ሀብትና ንብረት ያካበተ ማንኛውም ኃይል ባስፈለገ ጊዜ እንቢተኛ በመሆን ቤተ ክርስቲያንን ሊከፋፍል ስለሚችልና በዓለም ላይ ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ ንፁኃንን እየጎዳ ያለውን ትዕይንት ሊያስከትል ስለሚችል፣ ሁሉም የሃይማኖቱ መሪና ተከታይ መታገልና መቃወም እንዳለበት ፓትርያርኩ አሳስበዋል፡፡
ሌላው ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ያነሱት ነጥብ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች ቁጥር ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ መቀነሱን ነው፡፡ ለምሳሌ ያህልም በአዲስ አበባ ሰባት በመቶ፣ በኦሮሚያ አሥር በመቶና በደቡብ 7.8 በመቶ የቀነሰ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ የተጠቀሰው ቁጥር እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አለመሆኑን የገለጹት ፓትርያርኩ፣ የምዕመናኑ ቁጥር መቀነስ በአሉታዊ ጎኑ ሃይማኖታዊና ማኅበራዊ ለውጥ እንደሚያስከትል ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ሃይማኖታዊ ተልዕኮአችንን መሠረት አድርገን ብንመለከት ወደ መንግሥተ እግዚአብሔር የምናቀርበው ሕዝብ እያጣን መሆኑን ያሳያል፤›› ብለዋል፡፡ ምዕመናን ሲቀንሱ የቤተ ክርስቲያን ሀብት እየቀነሰ ስለሚሄድም፣ የሚዘጉ አብያተ ቤተ ክርስቲያናትም እየበዙ እንደሚሃዱ አክለዋል፡፡
የቤተ ክርስቲያንና ጥንታዊ እሴቶችም በአገር ደረጃ የነበራቸው ጠቀሜታ እየቀነሰ ከሄደ፣ የሃይማኖቱና የአገሪቱ መሠረታዊና ማኅበራዊ እሴቶች እንደሚጎዱ የጠቆሙት ፓትርያርኩ ባህሉ ከተጎዳ ጭካኔ፣ ስግብግብነት፣ ስንፍናና ወንጀል እንደሚበዙ ገልጸዋል፡፡ ፈሪኃ እግዚአብሔር ከመቀነሱና ከመጥፋቱም በተጨማሪ የትውልዱ ሥነ ምግባር ተጎድቶ የተለየ አደጋ እንደሚያስከትልም አክለዋል፡፡
አንዳንድ ሰዎች ችግሮችን ግልጽ በማድረግ ውይይት ለማድረግ ሲጠየቁ፣ ‹‹ሌሎች ሃይማኖቶች በእኛ ላይ ሊዘባበቱ ይችላሉና ዝም ይሻላል ብለው ይመክራሉ፤›› ያሉት ፓትርያርኩ፣ ዝም ማለት በመመካከር ሊገኝ የሚችለውን መፍትሔ እንደሚያሳጣ፣ ለምዕመናንና ለሕዝብ የሚሰጠው የተሻሻለ አገልግሎት እንዳይኖር እንደሚያደርግ፣ የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደራዊ ሥራ በዘመኑ ሥልት እንዳይመራና ሃይማኖቱ እንዳይስፋፋ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡ በማከልም በዚህ ዘመን ማናቸውም የሚደረግ ነገር ሁሉ ለሕዝብ ያልተደበቀና ምዕመናን በየቀኑ እያዩት ያለ ጉዳይ በመሆኑ፣ ‹‹ዝም እንድንል የሚመክሩን የቤተ ክርስቲያኗን መሻሻልና መጠናከር የማይፈልጉ ወይም የችግሩን አሳሳቢነት ያልተረዱ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡
በአድባራት፣ በገዳማትና በቤተ ክህነት ጭምር ብልሹ አሠራር መስፈኑን የሚያሳይ በሁለት ሳምንት ብቻ ከአምስት በላይ ከሚሆኑ አድባራትና ገዳማት የተውጣጡ ምዕመናንና ካህናት በሠልፍ ወደሳቸው መምጣታቸው ማሳያ መሆናቸውን የተናገሩት ፓትርያርኩ፣ መደለያ (ጉቦ) በመስጠት ፍትሕ እንዲጓደል ማድረግ፣ በዘር፣ በአካባቢ በመደራጀት ንፁኃንን መበደልና ያልደከሙበትን ሀብት ያለአግባብ ማባከን ትምህርተ ወንጌልን የሚፃረር ተግባር መፈጸም በመሆኑ፣ ሁሉም ሊዋጋው የሚገባ ተግባር መሆኑን አሳስበዋል፡፡
በቤተ ክርስቲያን የተሰጣቸውን ኃላፊነት ተጠቅመው ለራሳቸው ጥቅም የሚሯሯጡ አንዳንድ ሰዎች መኖራቸውን የገለጹት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ በአንዳንድ ቦታ ብቻ ሳይሆን በመዋቅር ውስጥ እንደ ሰንሰለት ተያይዘው ለራሳቸው ጥቅም የሚሠሩ ግለሰቦች መበራከታቸው፣ የላቀ መንፈሳዊ ተግባር ለሚጠብቁ ምዕመናን ክፉኛ የመንፈስ ስብራት እየደረሰባቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ይህንንና ሌሎች ችግሮችንም ከምዕመናኑ ጋር በመተባበር በተለይ ከቤተ ክርስቲያኗ አገልጋዮች ጋር ዓመቱን ሙሉ በሚኖረው ውይይትና ምክክር ችግሩ ሊፈታ እንደሚችል ያላቸውን እምነት ተናግረዋል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ስለማኅበራት በጎ ያልሆነ አሠራርን ሲናገሩ ‹‹ማኅበራት›› እያሉ በወል ስም ከመጥራት ባለፈ ሙሉ ስም ባይጠቅሱም፣ ከገዳማትና ከአድባራት የተወከሉ አስተዳዳሪዎችና ጸሐፊዎች ግን ሕንፃውን ጭምር እየገለጹ ማኅበረ ቅዱሳን መሆኑን በመጥቀስ ዕርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያኗ ማንኛውም ገቢ እንደ ገንዘብ ሚኒስቴር በአንድ ቋት ሆኖ በቅዱስ ሲኖዶስ ኃላፊነት እንዲመራ ጠይቀዋል፡፡ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ይቅርታ ጠይቀው ወደ ቀድሞ ቤታቸው እንዲመለሱም እንዲሁ ጠይቀዋል፡፡
ምንጭ፡ ሪፖርተር ጋዜጣ

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen