‹‹(ጠባብ) ብሄርተኝነት ልክ እንደ ርካሽ መጠጥ ነው፡፡ መጀመሪያ እንድትጠጣው ይገፋህና ያሰክርሃል፡፡ ቀጥሎ አይንህን ያውርሃል፡፡ ከዛም ይገድልሃል፡፡›› ዳን ፍሪድ
በጌታቸው ሺፈራው
(የግል አስተያየት)
ጃዋር መሃመድ ከአመታት በፊት ከማደንቃቸው ኢትዮጵያዊ አክቲቪስቶች መካከል አንዱ ነበር፡፡ በተለይ ይህ ወጣት ከጥቂት አመታት በፊት እነ በረከት ስምኦንን አልጀዚራ ላይ ሲያፋጥጣቸው ሳይ አድናቆቴ ከፍ ብሎ ነበር፡፡ በዚህ ወቅት ጃዋር ወደ ሶማሊያ ዘው ብሎ ስለገባው ሰራዊት፣ ቋንቋ ሳይለይ በየትኛውም ኢትዮጵያዊ ላይ የሚደርሰውን በደል ሽንጡን ገትሮ መከራከሩ ይታወሳል፡፡ ግን ምን ያደርጋል ይህ አቋሙ እንደተጠበቀው ሊዘልቅ አልቻለም፡፡ መሃል ላይ የ‹‹እኛ እና እነሱ›› ብልሹ ፖለቲካ ሰለባ ሆነ፡፡
በተለይ በአንድ ወቅት አልጀዚራ ላይ ቀርቦ ‹‹በቅድሚያ ኦሮሞ ነኝ›› ካለ በኋላ የፖለቲካ አቋሙ እየተንሸራተተ ሜንጫን እንደ ህጋዊ ነገር ማንሳት ውስጥ ገባ፡፡ አንዴ ‹‹ኢትዮጵያዊ ሙስሊም›› ሆኖ የኦሮሞ ሙስሊሞች ነጻነት ለሌላው ኢትዮጵያዊ ሙስሊም ነጻነትም ወሳኝ ነው ሲል፣ በሌላ በኩል ደግሞ ክርስቲያኑን ኦሮሞ በሜንጫ አንገቱን ስለመቅላት ይሰብካል፡፡ (ይህን መረጃ የተቀነባበረ ነው የሚል መረጃ ያቅርብ)፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ክርስቲያኑን ኦሮምኛ ተናጋሪም ጭምር ወክሎ ‹‹ቅድሙያ ኦሮሞ ነኝ›› አለ፡፡
ከዚህ ውጣ ውረድ በኋላ ጃዋር በቅርቡ ከ‹‹ኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ›› ጋር ቃለ መጠይቅ አድርጓል፡፡ በቃለ መጠይቁ እስካሁን አሉ የሚላቸውን ብዥታዎች ለማጥራትና አቋሞቹንም ለማስረገጥ በሚመስል መልኩ የቀረበ ይመስላል፡፡ በዚህ ቃለ መጠይቅ ጃዋር ከዛ በፊት እንዳደረጋቸው አነጋጋሪ ነገሮች ባይኖሩትም ቃለ መጠይቁ በሙሉ ‹‹ምክንያታዊ ናቸው›› በሚላቸው ምክንያት አልባ የማምታታት ክርክሮች የተሞሉ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ፡፡
በቃለ መጠይቁ አልጀዚራ ላይ ‹‹መጀመሪያ ኦሮሞ ነኝ›› ያለበትን አቋሙን የሚያጠናክርበት ነው፡፡ ‹‹በልጅነቴ ነው በፖለቲካው ተጠምቄ ያደኩት›› የሚለው ጃዋር ‹‹ከተወለድኩበት ጊዜ ጀምሮ እስከምሞትበት ጊዜ ድረስ ከምንም ከማን በላይ ራሴን እንደ ኦሮሞ ነው የማያው፡፡›› ሲል በ‹‹ማንነቱ›› ሁኔታ ላይ ይደመድማል፡፡ ግን በዚሁ ቃለ መጠይቅም ቢሆን ከአንድ አቋም ወደ ሌላ አቋም ሲዘል ታይቷል፡፡
ጋዜጠኛው ‹‹ኦሮሞ ፈርስት›› የሚለው ጉዳይ ከመነሳቱ በፊት ኢትዮጵያዊ በሆኑ አጀንዳዎች ይሳተፍ እንደነበር በመግለጽ ከዛ በኋላ አቋም መቀየር አለመቀየሩን ሲጠይቀው ‹‹አልቀየርኩም›› ይላል፡፡ መልሶ ደግሞ ‹‹አየህ! ከ2008፣ 2009 በኋላ ‹ኮንሸስ› የሆነ ምርጫ አድርጌያለሁ፡፡ በተለይ ከአማራ ልሂቃን ጋር በመገናኘት ለእነሱ ስለ ኦሮሞ ህዝብ ትግል በማስረዳት ከእነሱ ጋር አብሮ ለመስራት ይቻላል የሚል እምነት ነበረኝ፡፡ የአማራ ልሂቃን በኦሮሞ ትግል ላይ ያላቸው አመለካከት በጣም የሚያስደነግጥና በጣም የሚያስፈራ ነበር፡፡ በትምህርት ጥናቴም ሆነ ባለኝ ቀረቤት ችግሩ ምንድን ነው ብየ ሳስበው ምን አልባት ካለማወቅ (ኢግኖራስን) የመነጨ ነው የሚል ነበር፡፡ ሁለቱንም አካል ወደ መሃል በማምጣል አብሮ መስራት ይቻላል በሚል አምስት አመት ያህል ነው የሰራሁት፡፡ ነገር ግን ያለው ችግር የግዝብተኝነት (አሮጋንስ) ችግር እንዳለ ተረዳሁ፡፡ ኦሮሞ ፈርስት የሚለው ከመምጣቱ በፊት ስርቤይ አድርጌ ነበር፡፡ ...27 ያህል ሰዎችን ደውየ 1 ወይም 2 ብቻ ናቸው የተቀበሉት፡፡ እንዲሁም የኦሮሞ ትግል እየተዳከመ በመጣ ቁጥር ያላቸው ንቀት እየተጠናረ ሄደ›› በሚል አቋሙን መቼ እንደቀየረ ለማስገንዘብ ሲጥር ‹‹ከተወለድኩ ጀምሮ እስከሞት ድረስ ኦሮሞ ነኝ›› የሚለው የ‹‹አሁኑ›› አቋሙንም ራሱ መልሶ ይከራከረዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ሌላ አቋሙን የቀየረበት ምክንያት እንዳለው ጃዋር እንዲህ ያስረዳል፡፡ ‹‹...በግብጽ የሚገኙ የኦሮሞ ስደተኞች በአባይ ጉዳይ ላይ ኢትዮጵያና ግብጽ ባለባቸው ችግር ጥቃት ሲደርስባቸው ‹‹እኛ ኦሮሞዎች ነን፡፡ ከኢትጵያ መንግስት ጋር ምንም ትስስር የለንም ሲሉ እንዴት አባታችሁ ኦሮሞዎች ነን ትላላችሁ የሚል በጣም አጸያፊ የሆነ የሚዲያ ዘመቻ ተጀመረባቸው፡፡ ያ ለእኔ ቀይ መስመሩን ያለፉበት እንደሆነና ...…በዚህም በማንነታችን ላይ የተነጣጠረ ጥቃት ነው ወደሚል ገባሁ›› ይለናል፡፡ እንደ ጃዋር ከሆነ ግብጽ ውስጥ አማርኛ፣ ትግርኛ፣ ሲዳምኛ..... ተናጋሪዎች የሉም፡፡ አሊያም ጥቃት አልደረሰባቸውም፡፡ ወይንም ደግሞ ነገ ጃዋር ቆሜለታለሁ በሚለው ኦሮሞነታቸው ግብጾች ጥቃት የሚያደርሱባቸው ሲሆን ‹‹እኛ ኦሮሞዎች አይደለንም፣ ከኦሮሞ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የለንም፡፡›› ቢሉ ትክክል ናቸው እንደማለት ነው፡፡
በዚህ ቃለ መጠይቅ ጃዋር ተራ የሀሳብና የአመክኖ ማምታታት ብቻ አይደለም የሚታይበት፡፡ አንዴ መለስ ዜናዊ፣ ሌላ ጊዜ ኦነግ፣ አሊያም ኦህዴድ የያዙትን አቋም አቋሙ አድር ሲከራከርበት፣ ‹‹እኛ›› እያለ ሲገልጽ ተስተውሏል፡፡
ለአብነት ያህል 27 ያህል የ‹‹አማራ ልሂቃንን›› አነጋግሬ አገኘሁት የሚለውን መደምደሚያ ሲገልጽ ነፍጠናውን አከርካሪው ሰብረነዋል የሚለውን አቶ መለስ አቋም በግልጽ እንደተጋራ ይታያል፡፡ ጃዋር ‹‹ይህን አሮጋንስ ማስተካከል የሚቻለው ... ቀኝ ዘመሙን የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት አከርካሪውን በመስበር እጅ ማሰጠት ነው፡፡ ያ ፖለቲካ እንደማይሰራ ወደ ‹ኮምፕሊት ፖለቲካል ባንክራፕሲ› ማስገባት ግዴታ ነው በሚለው መደምደሚያ ደርሼ ነበር፡፡›› ይላል፡፡ ይህኔ ጃዋር መለስን መለስን ነው የሚመስለው፡፡
ኦህዴድ ከገዥው ቡድን ጋር ተባብሮ የኦሮሞን ህዝብ እየበደለ ስለመሆኑ ለተነሳለት ጥያቄ ጃዋር ኦህዴድን ምንም አቅም የሌለው አድርጎ ይገልጸዋል፡፡ መልሶ ደግሞ ለህወሓት ፈታኙ ኦህዴድ ነው እያለ ያምታታል፡፡ ጃዋር መጀመሪያ ‹‹ለእኔ የኦህዴድ አመራሮችም ሆነ አባላት በአንድ ፋብሪካ የሚሰሩ የፋብሪካ ዩኒየን ያህል ጉልበት የሌላቸውና የማይፈቀድላቸው ሰዎች ናቸው፡፡ ከተፈጠረበት ጊዜ ድረስ እስካሁን ድረስ ምንም አይነት ድርጅታዊ ስብዕና የሌለው ድርጅት ነው፡፡›› በማለት ከምንም የማይገባ፣ ለምንም የማይሆን አቅመ ቢስ ያደርገዋል፡፡
ምንም አቅም የላቸውም ያለውን ተመልሶ ‹‹..ህወሓት እንደፈለገው ኦህዴድ ቡችላ የሚሆንለት አይደለም፡፡ ምክንያቱም ብዙ ያልነቁት በእድሜ እየገፉ በሄዱ ቁጥር፣ ከኦነግ ጋርም ለመሻማት የተማሩትን ወደ ድርጅቱ እየከተተ በሄደ ቁጥር፣ ኦህዴድ እንደ ድርጅት ባይጠናከርም ግለሰቦች በተቻለ መጠን የህዝቡን መብት ለማስጠበቅ እየተንቀሳቀሱ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ እንዲያውም በአሁኑ ወቅት ለህወሓት ከማንም በላይ አስፈሪው ኦህዴድ ሆኖ ያለበትና ባለፉት ሁለት አመታት የምናየው ዳይናሚክስ ከፍተኛ አደጋ እየፈጠሩበት እንዳለ ነው የምናየው፡፡›› በማለት በቅጽበት ኦህዴድን ከአነስተኛ ፋብሪካ ዩኒየንነት ወደ ግዙፍና አስፈሪ ፓርቲነት ያሳድገዋል፡፡
ጃዋር መጀመሪያ ‹‹እንደ ድርጅት አልቆጥረውም፤ አቅመ ቢስ ነው፡፡›› ስላለው ኦህዴድ ይቀጥላል፡፡ ‹‹ያ ብቻ አይደለም የተማሩ ኦሮሞዎችን በግዳጅ ወደ ቢሮክራሲው አስገብቷል፡፡ እነዚህ ግለሰቦች ቢያንስ ከስርዓቱ ጋር እምብይ ማለት ቢያቅታቸው ‹አክቲቭሊ› ህዝቡን መበደል እያደረሱ አይደለም፡፡ .....ከዚህም የተነሳ በኦነግ የተጀመሩ ብዙ ፕሮጀክቶችን ወደማጠናቀቀ እየደረሱ ነው ያለው›› በማለት ኦህዴድን የኦነግ ‹‹ራዕይ አስቀጣይ›› ያደርገዋል፡፡ ይፈጽማል ከሚባለው ኃጥያት ነጻ ሊያወጣው ይሞክራል፡፡
ጃዋር ከአንድ የፋብሪካ ማህበር አይሻሉም የሚላቸውን ኦህዴዶች እንደገና ሲያማካሻቸው ጋዜጠኛው ‹‹ስለዚህ የኦህዴድ መኖር አስፈላጊ ነው?›› ብሎ ይጠይቃል፡፡ ጃዋር ግን አሁንም ያምታታል፡፡ ‹‹አይደለም!›› ይላል፡፡ ግን ደግሞ ስለ ኦህዴድ አስፈላጊነት እንዲህ ይገልጻል፡፡ ‹‹በአሁኑ ወቅት ወደ 90 በመቶ የሚሆነው የኦሮሞ ልሂቃን ኦህዴድ ውስጥ ነው ያለው፡፡ ስለዚህ ቀጣዩ የኦሮሚያ እጣ ፈንታ በእነሱ እጅ ነው ያለው፡፡›› በማለት መኖሩ አስለላጊ አይደለም የተባለው ኦህዴድ የኦሮሚያ እጣ ፈንታ ሆኖት ያርፋል፡፡ ጃዋሪዝም እንዲህ በደቂቃዎች አቋምን የመቀየር፣ የመቀያየር፣ የማምታታት ፖለቲካ ነው!
ይህ እንግዲህ ጃዋር ነው፣ ፖለቲካው ደግሞ ጃዋሪዝም፡፡ ስለዚህ አሁንም ማምታታቱን ይቀጥላል፡፡ እናም በአዲስ አበባ ‹‹መሪ እቅድ ወይም ማስተር ፕላን›› ላይ ለተነሳው ተቃውሞ ኦህዴዶች አሉበት እንደሚባል ጋዜጠኛው ሲያስታውሰው ‹‹ማንኛውም ኦሮሞ ኦህዴድም ሆነ ኦነግ ‹‹ማንነት፣ ኦሮሞ የሚባል ነገርና አዲስ አበባ ጉዳይ አንድ ናቸው›› በማለት ኦህዴድን ከማህበር ወደ ለህዝብ እንደሚያስብና አላማ ያለው የፖለቲካ ድርጅት ያደርገዋል፡፡ በአብዛኛው የቃለ መጠይቅ ክፍል መጀመሪያ ላይ ‹‹የዩኒየን አቅም ያህል የሌላቸው›› ያላቸውን ኦህዴዶች ያሞገሰበት ነው፡፡ ‹‹የዛሬ 9 አመት አካባቢ ዋና ከተማው ወደ አዳማ ሲዛወር ኦህዴድ ከፍተኛ ተቃውሞ ማድረጉን፤ ወደ ዋና ከተማውን አዲስ አበባ ማስመለሳቸውን በመግለጽ ‹‹የዩኒየን ያህል አቅም የላቸውም፣ የፖለቲካ ድርጅትም አይደሉም ስላላቸው መወድስ ያቀርባል፡፡
አሁን በአዲስ አበባ በተፈጠረው ችግር ደግሞ ‹‹በኢህዴድ ውስጥ አንድም ልዩነት ሳይፈጠር በአመራሩ በአንድ አቋም የተቃወሙበት ነበር፡፡ በግልጽ የህወሓትን ሰዎች ተቃውመዋቸዋል፡፡ በህወሓትና በኦህዴድ ጉዳይ ላይ በዚህ ጉዳይ ላይ የነበረውን ልዩነት ከአሁን ቀደም ኖሮ አያውቅም፡፡ ከዚያ አልፎ ያን ተቃውሞ ህዝቡ እንዲያውቀው በቴሊቪዝን አስተላልፈዋል፡፡ ይህን በማድረጋቸው ብዙ ሰዎች ለስራቸውም፣ ለህይወታቸውም ለቤተሰቦቻቸውም ራሳቸውን አደጋ ላይ አጋልጠዋል፡፡ ወጣቱም እነሱን ተከትሎ ነው ወደ ትግል የገባው›› በሚል የትግሉ አንቀሳቃሽ ሞተሮች፣ ነጻ አውጭዎች ያደርጋቸዋል፡፡
‹‹በኦህዴድ ውስጥ እከሌን እናጥቃ እከሌን እንግደል ቢሉ የባሰ ችግር ውስጥ ስለሚገቡ እስካሁን እየተፋጠጡ፣ በተቻለ መጠን ኢህዴዶችን በሁለት ከፍለው እያጋጩ ለማዳከም ሙከራ እያደረጉ ነው ያሉት፡፡ ባለፈው ሳምንት ሁለት፤ ሶስት ስብሰባ ተደርጎ ኦህዴዶች በአንድ አቋም ነው ተስማምተው የወጡት፡፡ እናም (ህወሓቶች) የተሳካላቸው አይመስለኝም፡፡›› በማለት ከጠንካራው ኦህዴድ ጎን ሆኖ ህወሓት አቅመ ቢስ እንደሆነ ያወራል፡፡ መቸም መጀመሪያ ላይ ‹‹የዩኒየንን ያህል አቅም የለውም የተባለው ድርጅትና ይህኛው ኦህዴድ በአንድ ሰው፣ ደግሞም በአንድ ቃለ መጠይቅ ላይ፣ በሴኮንድና ደቂቃዎች ልዩነት የተነሳ መከራከሪያ ነው ብሎ ለማመን ይከብዳል፡፡ ግን የሆነው ይህ ነው፡፡ ምክንያቱም ፖለቲካው ማምታታት ነው፡፡ ጃዋሪዝም!
ጃዋር መጀመሪያ ላይ ‹‹አሽከር›› አድርጎ የሚያቀርባቸው ኦህዴዶች ወደ መጨረሻ አናብስት ይሆናሉ፡፡ እነዚህን ‹‹አናብስቶች›› የእራሱ አድርጎ ስለሚቆጥራቸው ኦህዴድን ሰራው የሚለውን ሁሉ ‹‹እኛ እንዲህ አድርገን›› እያለ ይገልጸዋል፡፡ ኦህዴድን እቃወማለሁ እያለ ኦህዴድ ሆኖ (እኛ እያለ) ኦህዴድ ስኬቴ ስለሚለው ‹‹ስኬት›› ይናገራል፡፡ ኦህዴድ አሰራኋቸው የሚላቸውን መሰረተ ልማቶች ‹‹የእኛ›› ሲል አፍለኛ የኦህዴድ ካድሬ ይመስላል፡፡ እንዲህ! ‹‹በተጨባጭ ያሳየነውም ይህንኑ ነው፡፡…….ህወሓት እምብይ እያለ የኦሮሞ ልሂቃን፣ የኦሮሞ ትምህርት ቢሮ በኦሮሚያ ውስጥ ያሉ አማሮችና ሌሎችም በቋንቋቸው መማር መብታቸው ነው ብለው ነው የደነገገሩት፡፡ ምክንያቱም የቋንቋ ጭቆና ምን እንደሆነ ስለምናውቀው በሌላ ጭቆና ማድረግ አንፈልግም፡፡›› ኦነግንም፣ ኦህዴድንም በዓላማ አስተሳስሮ ‹‹የኦነግ የፖለቲካ አላማ እና የአሁኑ የክልላዊ ህገ መንግስት ስታየው በኦሮሚያ ያሉ ዜጎች በሙሉ ኦሮሚያዊ ናቸው ነው የሚለው፡፡›› በሚል አንድም፣ ሁለትም፣ ሶስትም ነን ባይ ነው፡፡
‹‹ኢትዮጵያዊነት የተጫነብን ብልኮ ነው›› የሚለው ጃዋር ሌሎችን ‹‹ስትፈልግ ኢትዮጵያዊ ነኝ በል! ስትፈልግ አማራ ነኝ በል! ስትፈልግ ጎንደሬ ነኝ በል! ስትፈልግ የፈለገህን በል! በእኔ ላይ ግን የአንተን ማንነት ለመጫን አትሞክር....›› ብሎ በኃይለ ቃል ያስጠነቅቃል፡፡ በእርግጥም ምንም ሆነ ምን የእኔን ማንነት አሊያም እኔ የፈረጅኩትን ማንነት ተቀበል ማለት አግባብ አይደለም፡፡ ግን ጃዋር እንዲህ አስጠንቅቆ ሳይጨርስ እሱም ሌሎች ላይ የማፈልጉትን ብልኮ ይደርባል፣ እነሱ ነኝ በማይሉት ማንነት ይፈርጃቸዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ በቀዳሚነት የሚነሱት ስለ አገር አንድነት የሚያነሱትን ወገኖች ‹‹አማራ›› የሚል ብልኮ የሚጭንባቸው መሆኑ ነው፡፡ በስልክ ደውሎ ከአነጋገራቸው በኋላ አቋሙን እንዳስቀየሩት የሚናገርላቸው ‹‹የአማራ ልሂቃንም›› እንዲህ ብልኮ የተደረበባቸው ናቸው፡፡ ስለ አንድነት ያነሳ እሱ ባያምንበትም በጃዋር መመዘኛ ግን ‹‹አማራ›› ነው፡፡
ጃዋር በአንድ በኩል ‹‹አማራ›› የሚላቸው ልሂቃን የያዙት አቋም የሰፊው የአማራ ህዝብ አቋም አይደለም ይላል፡፡ ተመልሶ ደግሞ ‹‹ኦሮሚያ ውስጥ ያደጉት የነፍጠኛ ልጆች የአማራው ህዝብ የተሳሳተ አመለካከት እንዲይዝ አድርገውታል፡፡ ኦሮሞ ገና ቃሉ ሲነሳ አገር አፍራሽ፣ ጠበኛ የሚል አመለካከት በህዝቡ ውስጥ እንዲመጣ አደርገዋል፡፡ ከአሁን በፊት የነበሩት የአማራ ገዥዎችም ህዝቡ የተሳሳተ አመለካከት እንዲይዝ አድርገውታል፡፡›› በማለት የ‹‹አማራ ህዝብ የአማራ ልሂቃንን አስተሳሰብ እንደያዘ›› በገደምዳሜው ይከሳል፡፡ መጀመሪያ ላይ ‹‹የአማራ ልሂቃን አስተሳሰብ የሰፊው የአማራ ህዝብ አስተሳሰብ አይደለም፡፡›› ያለውን ወርድ ብሎ ‹‹ህዝቡን የተሳሳተ አመለካከት እንዲይዝ እድርገውታል›› ይለናል፡፡
ጃዋር ለወቅቱ አቋሙ ምክንያት አድርጎ የሚወስደው አንድም ደውሎ ያናገራቸው የ‹‹አማራ›› ልሂቃን አስተሳሰብ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ግብጽ ውስጥ ‹‹ኢትዮጵያዊ አይደለንም›› ብለው ግን ‹‹በቀኝ ዘመሙ›› የፖለቲካ ኃይል (ሚዲያ) ዘመቻ ተከፍቶባቸዋል በሚሉት ኦሮምኛ ወጣቶች ምክንያት ነው፡፡ በመሆኑም ይህ ጥቃት ቀዳሚ ትኩረት ማግኘት እንዳለበትና የአማራ ልሂቃን አስተሳሰብ አከርካሪውን መመታት እንዳለበት በመግለጽ ይህን የፖለቲካ ቡድን ቀዳሚ ጠላት አድርጎ ያቀርበዋል፡፡ ወደኋላ ላይ ደግሞ ጋዜጠኛ በፈቃዱ ሞረዳ ‹‹የኦሮሞ ህዝብ ጠላት ማን ነው?›› የሚል ጥያቄ ሲያቀርብለት ‹‹የኦሮሞ ህዝብ በራሱ ላይ ነው ማተኮር ያለበት›› በሚል ጠላት የሚባል ነገር ላይ ትኩረት እንደማያደርግ ይገልጻል፡፡ ግን ፖለቲካው ጃዋሪዝም ነውና አሁንም ማምታታቱን ይቀጥላል፡፡ በዚህ ወቅትም ህወሓት ቀዳሚው ጠላት ይሆናል፡፡ ቀደም ሲል ያላቸውን ጣል እርግፍ አድርጎም ‹‹አሁን ባለው ሁኔታ ‹‹አክቲቭ ኢነሚ›› ብለን የምንጠራው ህወሓትን ነው፡፡ ምንም ምንም ጭቅጭቅ የለውም፡፡›› እያለ ይቀጥላል፡፡ በደቂቃዎች ውስጥ የኦሮሞ ህዝብ ሶስትና ከዛ በላይ ጠላቶችና ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡት ግቦች ይቀመጡለታል፡፡ ‹‹የአንድነት ኃይሉን (አማራ ይለዋል) አከርካሪውን ከመምታት፣ በራሱ ላይ ትኩረት ማድረግ፣ ስርዓቱ (ህወሓት!) ላይ ‹‹ፎከስ›› ማድረግ..... ››
አብሮ ስለመስራትም ጃዋሪዝም ያው ማምታታት ነው፡፡ መጀመሪያ ላይ በደወለላቸው የ‹‹አማራ›› ልሂቃን መሰረት የኦሮሞ ህዝብ ራሱን ችሎ መስራት አለበት የሚል መደምደሚያ እንደደረሰ የሚናገረው ጃዋር ‹‹የእኛ እርሻ ላይ ዝናብ እየዘነበ ማንም ጋ አንሄድም፡፡›› ይላል፡፡ ትንሽ ቆይቶም ‹‹አብሮ ለመስራት መቼም ቢሆን ክፍት ነን፡፡›› በማለት ይህ ባህል ከድሮ የመጣ መሆኑን ያስረግጣል፡፡ ደግሞም እንደገና ‹‹ከሜጫና ቱለማ፣ እስከ መኢሶን፣ እስከ ኦነግ መሪዎች ለሁሉም የሚሆን መካከለኛ መንገድ ለመፍጠር ስርተዋል፣ መስዋትነትም ከፍለዋል፣ ያ መስዋትነታቸው ግን ሰሚ አላገኘም፡፡ እንዲናቁ ነው መንገድ የከፈተው፡፡›› በሚል ወደ መካከለኛ መንገድ ለመምጣት የሚደረገው ፖለቲካ መስዋዕትነት የሚያስከፍልና የማያወጣ አይነት እንደሆነ በገደምዳሜው ይገልጻል፡፡ አብረን መስራት አለብን፡፡ ዝግ አይደለንም እንዳላለ ‹‹እኛ ስንጎዳ ያ ጉዳት ዳግመኛ እንዳይደገም እርምጃ መውሰድ ያለብን እኛ ብቻ ነን፡፡›› በሚል ‹‹ብቻችን እንወጣዋለን!›› የሚል አቋሙን እንደገና ሊያጠናክር ይሞክራል፡፡
የ‹‹ብሄር/የእኛ እና እንሱ›› ፖለቲካ ስስ የሆነውን ጉዳይ በማጋጋል እውቅናን ማግኘት፣ ጥላቻ በመስበክ ደጋፊ ማሰባሰብ፣ ማምታታት ነው፡፡ ‹‹የእኛ እና እነሱ ፖለቲካ›› አመክኖ ሳይሆን የማነጻጸር አባዜ የተጠናወተው የማምታታት ፖለቲካ ነው፡፡ ይህ መነጻጸር የማይገባውን ነገር የማነጻጸር አባዜ የጃዋሪዝም ዋነኛ መገለጫ ነው፡፡
ምክንያታዊ ለሚባል ሰው፤ ሰው ምንም ይሁን ምን በህገ ወጥነት መታሰር የለበትም፡፡ አማርኛ ተናገረ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ ተናገረ፣ሶማልኛ አሊያም ሌላ ቋንቋ በህገ ወጥ መንገድ መታሰር የለበትም፡፡ የግድ ሶስት ወይንም አራት ኦሮምኛ ተናጋሪ በህገ ወጥ መንገድ ከታሰረ ይህን ህገ ወጥነት መቃወም እየተቻለ፤ አምስት ወይንም ስድስት አማርኛ ወይንም ትግርኛ አሊያም ሌላ ቋንቋ ተናጋሪ ዜጋ መታሰር ነበረበት የሚል የስካር፣ ‹‹ጠባብ ብሄርተኝነት›› ያወረው ክርክር ሊቀርብ አይገባም፡፡
ለጃዋሪዝም ግን ይህ ሰብአዊም ሆነ ህጋዊ አመክኖ አይሰራም፡፡ ጃዋር ‹‹ዛሬ እስር ቤት ብትገባ ምርጥ የኦሮሞ ልጆችን እስር ቤት ውስጥ ነው የምታገኛቸው፡፡ አንድ የአማራ እስረኛ ካለ 90 የኦሮሞ እስረኛ አለ፡፡›› በሚል በኦሮምኛ ተናጋሪዎች ላይ እየደረሰ ያለውን በደል ‹‹አልተበደለም!›› ከሚለው ‹‹አማራ›› ጋር በማነጻጸር ‹‹ለመከራከር›› ይጥራል፡፡ እንደ ጃዋር የበርካታ ኦሮምኛ ተናጋሪዎች መታሰር ምክንያታዊ ሊሆን የሚችለው ሌሎች በህገ ወጥ መንገድም ቢሆን ከታሰሩ ብቻ ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ ልክ ርካሽ መጠጥ እንደሚያመጣው ‹‹ጠባብ ብሄርተኝነት›› የሚያመጣው ጭፍንና የማምታታት ፖለቲካ ነው፡፡
የአዲስ አበባ ‹‹ማስተር ፕላን›› ለ‹‹ኦሮሞ ህዝብ ቆመናል›› የሚሉት አካላት አመክናዊ እንዳልሆኑ ካሳዩናቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው፡፡ ‹‹ፊንፊኔ የኦሮሚያ ናት›› ይሉ እንዳልነበር በሌላ በኩል ደግሞ ‹‹አዲስ አበባ የኦሮሚያን መሬት እየወሰደች ነው፡፡›› የሚል የጃዋሪዝም ፖለቲካ ውስጥ ገቡ፡፡ በሂደት ስርዓቱ ‹‹ማስተር ፕላኑን›› የተቃወሙ ወጣቶችን በጠራራ ፀኃይ ጨፈጨፋቸው፡፡ በወቅቱ በተፈጠረው ችግር ሌላ ቋንቋ ተናጋሪዎችም ‹‹ከኦሮሚያ ውጡ ተብለው ተደብድበዋል፣ ተገድለዋል፡፡›› በተለይ ስለ ኢትዮጵያ አንድነት የሚያቀነቅኑ የፖለቲካ አካላት ጉዳዩን በግልጽ ለመደገፍ አልቻሉም፡፡ ምን ያህል ሰርተውበታል የሚለው እንዳለ ሆኖ ግድያውን ተቃውመው ሰልማዊ ሰልፍ ወጥተዋል፣ ሻማ አብርተው ጭፍጨፋውን ተቃውመዋል፣ መግለጫ አውጥተዋል፡፡ ይህም ቢሆን በቂ ላይሆን ይችላል፡፡ ጃዋር ተቃዋሚዎች ያደረጉትን ትንሽም ነገር ቢሆን በቂ አይደለም ከማለት ይልቅ ማብጠልጠሉን ነው የመረጠው፡፡
በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ ትንሽም ቢሆን የሰሩትን ተቃዋሚዎች እያብጠለጠለ ለህወሓት መሳሪያ ሆኖ ተማሪዎቹን ያስጨፈጨፈውን ኦህዴድን በ‹‹ማስተር ፕላኑ›› ዙሪያ ለህወሓት ፈተና፣ በ‹‹ፊንፊኔ›› ጉዳይ ከህዝብ አሊያም ለ‹‹ኦሮሚያ›› ከቆሙ ሌሎች ኃይሎች ጋር ተመሳሳይ አቋም እንዳለው፣ ትግሉንም በማቀጣጠል ለወጣቱ አርዕያ አድርጎ ማወደሱ ነው፡፡ ግድያውን የተቃወሙት ተቃዋሚዎች በጃዋር የተብጠለጠሉት ግን በተማሪዎቹ ላይ የተፈጸመውን ግድያ በሚገባ አልተቃወሙም በሚል አይደለም፡፡ ጃዋር አሁንም ያነሳው ለመከራከሪያነት የማይበቃ ‹‹የጠባብ ብሄርተኝነት›› ማነጻጸሪያ ነው፡፡ ጃዋር የፖለቲካ ቡድኖቹ ለኦሮምኛ ተናጋሪ ተማሪዎች ላይ የተደረገውን ግድያ አልተቃወሙም ለማለት ያነሳው የዞን ዘጠኝ ጦማሪያንን ነው፡፡ በኦሮሚያ ተማሪዎች በተፈጸመው ግድያ በቂ ምላሽ አልተሰጠም ብሎ ለመከራከር የዞን ዘጠኞች ላይ የተፈጸመው ህገ ወጥ እስር ተቃዋሚዎች ያሰሙት ተቃውሞ ተጋንኗል በሚል በመከራከሪያነት አቅርቦታል፡፡ ይህ ጃዋሪዝም ነው፡፡ የማይነጻጸረውን ማነጻጸር፣ በቅጽበት የተቃወሙትን መደገፍ፣ የደገፉትን መቃወም፣ አመክኖ ሲጠፋ ማምታታት!
Keine Kommentare:
Kommentar veröffentlichen