Netsanet: የ‹‹ሚዲያ ካውንስሉ›› ምስረታ አጨቃጫቂ ጉዳዮች ተነሱበት

Donnerstag, 9. Oktober 2014

የ‹‹ሚዲያ ካውንስሉ›› ምስረታ አጨቃጫቂ ጉዳዮች ተነሱበት



‹‹የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት የምክክር ጉባዔ›› በሚል የሚዲያ ካውንስ ለመመስረት እየተደረገ የሚገኘው ስብሰባ አጨቃጫቂ ጉዳዮች ተነሱበት፡፡ ለሁለት ቀን የሚቆየው ስብሰባ ዛሬ መስከረም 29/2007 ዓ.ም በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ የተጀመረ ሲሆን ‹‹የምክክር ጉባዔው››ን በሰብሳቢነት ወይዘሮ ሚሚ ስብሃቱ እንዲሁም በምክትል ሰብሳቢነት አቶ አማረ አረጋዊ መርተውታል፡፡ በጉባዔው በአብዛኛው ገዥውን ፓርቲ የሚደግፉ ሚዲያዎች፣ ማህበራትና ግለሰቦች ተገኝተዋል፡፡ 

የመተዳደሪያ ደንቡ ላይ ባተኮረው የዛሬው ውይይት ካውንስሉ ‹‹የትኞቹን ሚዲያዎች ይቀፍ?›› የሚለው ጥያቄ አጨቃጫቂ ከመሆኑም በተጨማሪ የ‹‹ሚዲያ ካውንስሉ›› በበጎ አድራጎት ድርጅትነት ወይንስ በንግድ ድርጅትነት ይቋቋም የሚለውም አጨቃጫቂና ውሳኔ ያልተሰጠበት ጉዳይ ሆኖ አልፏል፡፡ 

በስብሰባው ላይ መንግስት ለመረጃ ዝግ መሆኑንና ይህም በጋዜጠኞች ላይ ለሚደርሰው በደል እንደምክንያት የተነሳ ሲሆን የኮምኒኬሽን ሚኒስትር ድኤታው አቶ እውነቱ ገለታ ችግሩ እንዳለ አምነዋል፡፡ 

‹‹የምክክር መድረኩ›› አዘጋጆች ለቅድመ ጥናትና ለጉባዔው ከእንግሊዝ ኤምባሲ የገንዘብ እርዳታ እንዳገኙ ገልጸዋል፡፡

ሆኖም አሁንም ድረስ እውቅና የተነፈገው ‹‹የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ›› በምስረታው ወቅት ከእንግሊዝ ኤምባሲ ጋር ግንኙነት ባደረገበት ወቅት በመንግስት ድጋፍ የሚንቀሳቀሱት የጋዜጠኛ ማህበራት፣ በአሁኑ ወቅት የሚዲያ ካውንስሉን ለማቋቋም በግንባር ቀደምነት የሚንቀሳቀሱት ግለሰቦችና መንግስት ‹‹ከውጭ አካላት ጋር ግንኙነት እያደረገ ነው፡፡ ይህም የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ይጎዳል›› በሚል መግለጫ ከማውጣትም በተጨማሪ በመንግስትና በመንግስት ደጋፊ ሚዲያዎች ወቀሳ እንዳቀረቡበት ይታወሳል፡፡ 

በነገው ዕለት ስለጋዜጠኝነት ስነ ምግባር፣ ስለ ሚዲያዎች አሰራርና መሰል ጉዳዮች ውይይት ይቀርባል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ነገረ ኢትዮጵያ መረጃዎችን እየተከታተለች ለማቅረብ ትጥራለች፡፡

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen