Netsanet: ከታህሳስ 10 ቀን 2007 የአዲስ አበባና ባህርዳር አመጾች ምን እንማራለን?

Donnerstag, 25. Dezember 2014

ከታህሳስ 10 ቀን 2007 የአዲስ አበባና ባህርዳር አመጾች ምን እንማራለን?

ዓርብ ታህሳስ 10 ቀን 2007 ዓ.ም. አዲስ አበባ እና ባህርዳር በዓይነታቸው ልዩ የሆኑ ሕዝባዊ ተቃውሞዎችን አስተናግደዋል። በአዲስ አበባ ሙስሊም ወገኖቻችን ከህወሓት ሰላዮች እይታ ውጭ በተደራጀ መንገድ በኑር መስኪድ ያደረጉት ተቃውሞ ቢያንስ ሶስት ቁም ነገሮችን አስገንዝቧል። እነዚህ ሶስት ነገሮች፣ (1ኛ) ምላሽ እስካላገኘ ድረስ የመብት ማስከበር ትግል በአፈና ተዳፍኖ እንደማይጠፋ፣ (2ኛ) ጽናት ካለ የወያኔ አፈናን የሚቋቋም ድርጅትና ተግባቦት መፍጠር እንደሚቻል፣ እና (3ኛ) ሙስሊሙን በተመለከተ የህወሓት አንድ-ለአምስት አደረጃጀት መፍረሱ ናቸው። ይህ ድል የሙስሊም ኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆን ሙስሊም ያልሆኑ ኢትዮጵያዊያንም የሚጋሩት የጋራ ድል ነው። በተለይም የወያኔ አንድ-ለአምስት አደረጃጀት የሚናድ መሆኑ በተግባር ማሳየታቸው እና የህወሓት ሰላዮች ሳይሰሙ ተቃውሞዓቸውን አደራጅተው ተግባራዊ ማድረጋቸው የሚደነቅ ነው።
በዚሁ ዕለት በባህርዳር የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ከሕዝብ ጋር ሳይመክር በልማት ስም ያሻውን የሚያደርገውን እብሪተኛን ለመቃወም በአጭር ጊዜና በፍጥነት ተሰባስበው ቁጣቸው ማሰማት ችለዋል። በባህር ዳር ሕዝብ ልብ ውስጥ ለዓመታት ሲብሰለሰል የቆየውን የበደል ስሜት በዚህ አጋጣሚ ገንፍሎ ወጥቷል። በተለይም የወያኔ “ምርጥ ባርያ” መሆኑ የሚስፈነጥዘው ብአዴን በአማራ ሕዝብ ምን ያህል የተጠላና የተናቀ መሆኑ እንዲያውቅ ተደርጓል። ሆኖም ግን፣ ማናቸውንም ዓይነት ተቃውሞ የማያስተናዱት ህወሓትና ባርያው ብአዴን በባዶ እጁ ለተቃውሞ በወጣው ሕዝብ ላይ የጥይት ናዳ እንዲያወርድ ሠራዊታቸውን በማዘዛቸው እና ይህን ዘግኛኝ ትዕዛዝ የሚያስፈጽም ሠራዊት ያለ በመሆኑ ብዙ አዛውንት፣ ጎልማሶችና ወጣቶችን ለሞትና ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል። የህወሓትና የብአዴን ሠራዊት ከዱላና ከገዳይ ጥይት ሌላ አንዳችም የአድማ መበተን እውቀት የሌለው መሆኑን የሚያሳዝን ነው፤ በሰላማዊ ሕዝብ ላይ እንዲተኩስ ሲታዘዝ የሚተኩስ መሆኑም የሚያሳፍር ነው። በባህርዳር ከተፈፀመውም የኢትዮጵያ ሕዝብ (1ኛ) ሕዝባዊ አብዮት እንዲህ በደንብ ሳይታሰብበትም ሊቀሰቀስ የሚችል መሆኑ፣ (2ኛ)ህወሓት ሕዝብ አምርሮ ሲነሳበበት የሚደነግጥና የሚርበተበት ፈሪ መሆኑ፣ እና (3ኛ) በፈሪነቱ ምክንያትም በባዶ እጃቸው በወጡ አዛውንትና ህፃናት ጭምር የተኩስ እሩምታ ከመክፈት የማይመለስ መሆኑን አስተውሏል ብለን እናምናለን።
ህወሓትንና አገልጋዮቹን ከስልጣን ለማባረር በአዲስ አበባ እና ባህርዳር የተደረጉትን ማቀናጀት ግዴታ ነው። በሌላ አነጋገር የባህር ዳሩ ሕዝባዊ አመጽ አዲስ አበባ ኑር መስጊድ በታየው ዓይነት ብልሃት፣ ድርጅት እና ዲሲፕሊን ተመርቶ ቢሆን ኖሮ በባህር ዳር የተጫረው የነፃነት እሳት በመላው አገሪቷ ተቀጣጥሎ ዛሬ የምንገኝበት ሁኔታ ከታህሳስ 10 ከነበረው ፈጽሞ የተለየ በሆነ ነበር። ለወደፊቱም ማድረግ የሚኖርብን ይህ ነው። ሙስሊምና ክርስቲያኑ ተደጋግፎ አንዱ ዘንድ የጎደለው በሌላው አካክሶ የሁላችንም ጠላት የሆነውን ህወሓትን ከነ አገልጋዮቹ ከሥልጣን ማስወገድ የሁላችንም የጋራ ግዴታ ነው። ጠመንጃው የፍርሃቱ መሸሸጊያ ያደረገው ህወሓትም ጠመንጃውን የሚያስጥል መላ እና ዱላ መዘጋጀት ይኖርበታል። ህወሓትንና አጫፋሪዎቹን ከሥልጣን ለማባረር በጠንካራ ድርጅት፣ ዲሲፕሊንና ብልሃት የሚመራ ሕዝባዊ እምቢተኝነትና ሕዝባዊ አመጽ ቅንጅት ሊኖር እንደሚገባ የታህሳስ 10 ቀን 2007 ትልቁ ትምህርት ነው። በዚህ ዕለት የህወሓትን ወደ ጠመንጃ የመሮጥ ወራዳ ባህርይን የሚያስቆም ኃይል የማደራጀት አስፈላጊነትም ጉልህ ሆኖ ወጥቷል። ዓርብ ታህሳስ 10 ቀን 2007 ዓም አዲስ አበባና ባህርዳር የተፈፀሙትን አገናኝቶ ያነበበ ማንኛውም ሰው የሁለገብ ትግል ስልት ምንነትና አዋጭነት በገሃድ ይረዳል፤ ወደዚያ እያመራን መሆኑንም ይገነዛባል።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ዓርብ ታህሳስ 10 ቀን 2007 ዓ.ም. በባህርዳር ከተማ በርካታ ወገኖቻችን ሕይወታቸውን ያጡ በመሆናቸው የተሰማውን ጥልቅ ሀዘንና ቁጭትእየገለፀ ለቤተሰቦቻቸው መጽናናትን ይመኛል። እንደዚሁም በዚሁ ዕለት በህወሓትና ብአዴን ሠራዊቶች ጥይት ለቆሰላችሁና ለተደበደባችሁ ወገኖቻችን ሁሉ ህመማችሁ ህመማችን፤ በእናንንተ ላይ የደረሰው በደል በሁላችንም ላይ የደረሰ መሆኑን እንድትረዱልን እንፈልጋለን። እንዲህ ዓይነቱ በደል እንዲያበቃ ደግሞ ህወሓት፣ ብአዴን እና በየክልሉ ያሉት አጋፋሪዎቹ ከሥልጣን መወገድ እንዳለባቸው ያለጥርጥር እናምናለን። ህወሓት እና አጫፋሪዎቹን ከሥልጣን ለማባረር ደግሞ ሕዝባዊ እምቢተኝነት ከሕዝባዊ አመጽ ጋር ማዳቀል ስለሚኖርብን በሁሉም ረገድ ዝግጅቶቻችን አጠናቀን ለወሳኙ ፍልምያ እንነሳ።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen