ማክሰኞ ህዳር 23/07 ዓ.ም ወደዚያች ንዳድ ወደሆነችው ዝዋይ ከተማ ስንደርስ ከረፋዱ 3፡00 ነበር፡፡ ያንን መከረኛ መንገድ እንደዋዛ አልፈን ወደ ግዞት ቤቱ ስንገባ በመመላለስ የተግባባናቸው ጠባቂዎች በፈገግታ ተቀበሉን፡፡ ሙሉ አድራሻችንን አስመዝግበን ያመጣነውን ስንቅ በማስፈተሽ ጠያቂና እስረኛ የሚገናኝበት ቦታ ላይ ስፍራችንን ያዝን፡፡ የዛሬው ቀን ግን ከሌላው ሳይለይ አይቀርም፡፡ ከተቀመጥን ደቂቃዎች ቢያልፉም ስለታሰረ ብቻም ሳይሆን አብረውት ቢያወሩ የሚናፍቁት ተመስገን አልመጣም፡፡ ከእንቅልፍ አልነቃ ይሆን? እንደምንመጣ ስለሚያውቅ ግን ይሄ ሊሆን አይችልም፡፡ ተመስገንን እንዲጠራልን የላክነው እስረኛ መልዕክቱን እንዳስተላለፈ ነግሮን አለፈ፡፡ ይህ ልጅ ታማኝ ከሚባሉት እስረኞች መካከል የሚጠቀስ ነው፡፡ እነዚህ ታማኝ እስረኞች ከመታመናቸው የተነሳ ከጊቢውም ወደ እየወጡ እንደሚመለሱ የከተማው ነዋሪ የሹክሹክታ ወሬ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ መቼም ከተማ የሚወጡት ከዝዋይ ሀይቅ አሳ ሊያጠምዱ እንዳልሆን ግልፅ ነው፡፡ የወታደሮቹ ሀላፊ መጥቶ ገርመም አድርጎን አለፈ፡፡ እሱን ተከትሎ ሌሎች ሁለት ወታደሮች በተመሳሳይ ሁኔታ አይተውን ተመለሱ፡፡ ነገረ ስራቸው አላማረንም፡፡ ይሄን መታገስ አልቻልንም፤ ድምፃችንን ከፍ አድርገን መናገር ጀመርን፡፡ ‹ተመስገን ሳይመጣ 40 ደቂቃ አለፈው፤ ኸረ የተመስገን ያለህ› ብንልም ሰሚ ግን አልነበረም፡፡ በቦታው ከተገኘን ከ55 ደቂቃ በኋላ ታማኙ እስረኛ ተመስገን ሲጠቀምባቸውን የነበረውን እቃዎች ወረቀት ከያዙ ወታደሮች ጋር ይዞ ሲመጣ የማደርገውን ነገር እስካጣ ድረስ ድንጋጤ ወረረኝ፡፡ እንዳልናገር ምላሴ ተያያዘ፤ ምን ማድረግ እንዳለብኝ ለማ፡፡ ከፊታችን ሊደርሱ ጥቂት የቀራቸውን ወታደሮች ‹‹ተመስገንስ? ተሜስ›› አልኳቸው፡፡ እነሱ ግድም አልሰጣቸው፡፡ የመጣሁትን ስንቅ ዕየደባበሱ ‹‹ተመስገን ትላንት አዲስ አበባ ሄዷል››፤ ‹‹የምን አዲስ አበባ ነው? መቼም ወደቤት አይሄድም?››፡፡ ወደ ቃሊቲ በለሊት መሄዱን አረዱን፡፡ አሁን ተናድድኩ፡፡ ‹‹ትላንት ከሰዓት ጠይቀነዋል፤ አንደሚሄድ እሱም አያወቅም ነበር፤ ለኛም አልንገራችሁን ሌላው ቢቀር ደውላችሁ ብትነግሩን ምን ነበረበት?›› መልስ ሳይሰጡን የራሳቸውን ወሬ ማውራት ጀመሩ፡፡ ያመጣሁት ምግብና ቡና እናታችን ዕረፍት አጥታ የሰራቸው ነው፡፡ ድካሟን ሳስበው አዘንኩላት፡፡ ምን ማድረግ ይቻላል? ምንም፡፡
ያመጣሁትን ምግብ ለክንፈሚካኤል (አበበ ቀስቶ) እንድሰጥ እንዲጠሩልኝ ብጠይቅም አልሆነም፤ ግን እናድርስላቹሁ የሚል ሀሳብ ከወታደሮቹ መጣ፡፡ አማራጭ ስለሌለን ቡናና ምግቡን ሰጥተን ተመሰገን ሲጠቀምባቸው የነበሩትን እቃዎች ይዘን ተመለስን፡፡ ተልዕኮአችን ሳይሳካ ጉዞ ወደ አዲስ አበባ፡፡
ቃሊቲ ዞን 3
እንግዲህ ተመስገን ለሚወዳት ሀገሩ ሲል ከቂሊንጦ ዝዋይ፤ ከዝዋይ ደግሞ ቃሊቲ መንከራተቱን ተያይዞታል፡፡ መከራውን የሚያብሰው ደግሞ ከቃሊቲ እስር ቤት እጅግ አስከፊ ወደሆነው ቦታ መዘዋወሩ ነው፡፡ ዞን 3 ይባላል፡፡ ዞኑ ምን እንደሚመስል ዛሬ ከሰማሁት ጥቂት ላካፍላችሁ፡፡ መግቢያው ላይ ‹በከፍተኛ ጥበቃ ስር የሚገኝ› ይላል፡፡ በዞን 3 የሚገኙት እስረኞች በጠቅላላ ማለት ይቻላል በተደጋገመ ስርቆት፣ ማጭበርበርና አስገዳጅ የሌብነት ወንጀል ሲፈፅሙ ተገኝተዋል የተባሉ እስረኞች የሚታጎሩበት ዞን ነው፡፡ ታዲያ ተመስገን ይህ ቦታ እንዲገባው የተፈረደበት ስለምንድን ነው? እኛ ሳናውቅ የዘረፈው ነገር ይኖር? ህዝብ ሳይሰማ በሌብነት ንብረት አካብቶ ይሆን? ሰብዕናው ይህ እንዳልሆነ ለመመስከር ከኔ በላይ የከሳሾቹም ልብ ያውቀዋል፡፡ የዕሰረኞቹ ማደሪያ መጋዘን በቆርቆሮ የተሰራና ጠባብ ሲሆን በውስጡ ሙሉ ቃሊቲ እንኳን የማይችላቸው 300 እስረኞች ታሽገውበታል፡፡ ዛሬ ተመስገን 301ኛ በመሆን ነባሮቹን ተቀላቅሏቸዋል፡፡ የእነዚህ እስረኞች የመኝታ ሁኔታ የአንዱ ራስ ከስር ያንዱ እግር ከላይ ሲሆን በተለምዶ አስመራ ድርድር የሚባለውን መልክ ይወክላል፡፡ በርግጥ ይህ ለተሜ ትንሹ መስዋዕትነት ነው፡፡ መንፈሱን ለማድቀቅ፣ ጥንካሬውን ለማራከስ የታሰበ ቢሆንም የታመነለትን ምክኒያት ሊሸርፉት እንደማይችሉ ግን ነብሴ ትመሰክራለች፡፡ የሐዋሪያው ጴጥሮስ ተዘቅዝቆ መሰቀል ላመነበትስ አይደል! ለእነዚህ 300 እስረኞች ያለው የሻዎር አቅርቦት 1 ብቻ መሆኑ ደግሞ ሌላው ትንግርት ነው፡፡ አንድ ሰው በሳምንትም የመታጠብ እድል ላይኖረውም ይችላል፡፡ የመጋዘኑ መታፈን ለተባዮች ምቹ መኖሪያ ሆኗቸዋል፡፡ ተሜ ከከፋ ግፍ ወደ ከፋ ሰቆቃ ቢዘዋወርም ‹‹ለሀገሬ ስል ጉዞዬ እስከ ቀራኒዮ ድረስ ነው›› ያለውን እያደረገ እንደሆነ ስመለከት በፅናቱና በብርታቱ እደነቃለሁ፡፡
Keine Kommentare:
Kommentar veröffentlichen