Netsanet: አየር ሃይል እየታመሰ መሆኑን ምንጮች ገለጹ

Dienstag, 23. Dezember 2014

አየር ሃይል እየታመሰ መሆኑን ምንጮች ገለጹ


ታኀሳስ ፲፬(አስራ አራትቀን ፳፻፯ / ኢሳት ዜና :-የአየር ሃይል ባልደረባ የሆኑት ሻምበል ሳሙኤል ግደይ፣ መቶ አለቃ ቢልልኝ ደሳለኝ ከበረራ ቴክኒሻኑ ጸጋ ብርሃን ግደይ ጋር በጋራ በመሆን የሚያበሩትን ሄሊኮፕተር ይዘው ከጠፉ በሁዋላ የአየር ሃይል አዛዦች አስቸኳይ ግምገማ ከተጠሩ በሁዋላ እርስ በርስ እየተገማገሙና ከእነዚህ ሰዎች ጋር ግንኙነት አላቸው ብለው የሚያስቡትን የአየር ሃይል አባላት ለማሰር እንቅስቃሴ መጀመራቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል። በተለይም የትግራይ ተወላጅ ከሆኑት ሻምበል ሳሙኤል ግዴይና ቴክኒሻኑ ጸጋ ብርሃን ጋር የቅርብ ግንኙነት አላቻው የተባሉ ሰዎች እየተጠሩ በመጠየቅ ላይ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሎአል። የመከላከያ ሚኒስትር ሻምበል ሳሙኤል ግደይን ከሃዲ ሲል ሲፈርጀው፣ መቶ አለቃ በልልኝ ደሳለኝንና ቴኒኪሻን ጸጋ ብርሃንን ደግሞ ተገደው መብረራቸውን ገልጿል።

የኢሳት ታማኝ ምንጮች እንደገለጹት ከፍተኛ የበረራ ልምድ ያላቸው ሻምበል ሳሙኤል የህወሃት ባለስልጣናት በኢትዮጵያ አየር ሃይል ላይ የሚያደርሱትን ጥፋት ከሚቃወሙት የትግራይ ተወላጆች መካከል አንዱ ነው። መቶ አለቃ ቢልልኝ ደግሞ በአየር ሃይል ውስጥ የተስፋፋውን ዘረኝነት ከሚኮንኑ አብራሪዎች መካከል መሆኑ ታውቋል። በ2 ሺ ዓም አየር ሃይልን የተቃለቀለው መቶ አለቃ ቢልልኝ ሱዳን ውስጥና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ሄሊኮፕተር በማብረር ብቻውን የተለያዩ ግዳጆችን መወጣቱን ምንጮች ገልጸዋል። ሁሉም ስርዓቱን በመቃወም ጥለው የጠፉ እንጅ፣ መንግስት እንዳለው አንዱ  ሌላውን አስገድዶ እንዲጠፋ አለማድረጉን ጉዳዩን በቅርብ የሚያውቁት ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል።
በሌላ በኩል መንግስት አብራሪዎቹ ሄሊኮፕተሩን ኤርትራ አሳርፈውታል የሚል መግለጫ ቢሰጥም፣ የኤርትራ መንግስት ምንም መግለጫ አልሰጠም። ኢሳት ሄሊኮፕተሩ የት እንዳረፈ ለማወቅ ያደረገው ሙከራም እስካሁን አልተሳካለትም። በአየር ሃይል አዛዦች ውስጥ የተፈጠረውን ትርምስ ተከትሎ ኮሎኔል አበበ ተካና በብርጋዴር ጄኔራል ማሾ ሃጎስ እርስ በርስ መወነጃጀል ጀምረዋል።
ኮሎኔል አበባ ተካ በህወሃት መሪዎች ዘንድ የሚወደዱ በመሆናቸው አየር ሃይልን ከጀርባ ሆነው እስካሁን ሲመሩት ቆይተዋል። አለቃቸው ብርጋዴር ጄኔራል ማሾ ሃጎስ ደግሞ ከህወሃት ባለስልጣናት ጋር በሚፈጥሩት አለመግባባት የተነሳ  ስልጣን ሳይኖራቸው  በስም ብቻ ተንሳፈው የሚኖሩ ናቸው። ብርጋዴር ጄኔራል ማሾ ቀደም ብሎ ከአየር ሃይል አዛዡ ሞላ ሃይለማርያም ጋር ከፍተኛ ጸብ ውስጥ ገብተው የነበር ሲሆን፣ ከኢታማጆር ሹሙ ሳሞራ የኑስ ጋርም ያላቸው ልዩነት እየሰፋ ሄዶ እርስ በርስ ማውራት ማቆማቸው ይነጋራል። ከጄ/ል ማሾ ጋር በእኩል ደረጃ የነበሩ ወታደራዊ  አዛዦች ቀድመዋቸው የጄኔራልነት ማእረግ ሲሰጣቸው እርሳቸው ግን ከሁለት ጊዜ በላይ እንደታለፉና  በቅርቡ በተደጋጋሚ ባሰሙት ቅሬታና ህወሃትን ከመከፋፈል ለማዳን በሚል ምክንያት የብርጋዴር ጄኔራልነት ማእረግ እንዲሰጣቸው ተደርጓል።
ጄ/ል ማሾ በሲነየርቲ ከፍተኛ የማእረግ ደረጃ ላይ መድረስ የነበረብኝ ቢሆንም፣ ከጓደኞቹ እንዳንስ ያደረገኝ ጄ/ል ሳሞራ በሚያደርስብኝ በደል ነው በሚል በተደጋጋሚ ቅሬታ እንደሚያሰሙና ከስራቸው እየቀሩ በተለያዩ ሱሶች ተጠምደው እንደሚውሉ የቅርብ ምንጮች ይገልጻሉ። ጄ/ል ማሾ ቦታውን በስም ብቻ እንዲይዙ ተደርጎ ዋናውን የበረራ ስምሪት የሚያካሂዱት ኮ/ል አበበ መሆናቸው ፣ ኮሎኔል አበበን በሚደግፉት በእነ ሳሞራ እና በጄ/ል ማሾ መካከል ያለው ውዝግብ እንዲሰፋ ተጨማሪ ምክንያት ሆኗል።
ኮ/ል አበባ ተካ አየር ሃይልን በተለይም የድሬዳዋን አየር ምድብ ማዘዝ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ አየር ሃይሉን ጥለው የሚጠፉ አብራሪዎች ተበራክተዋል። ባለፉት 6 ወራት ብቻ 11  አብራሪዎች አየር ሃይልን ጥለው በመጥፋት ግንቦት7ትና አርበኞች ግንባርን  ተቀላቅለዋል። አብዛኞቹ ለመጥፋታቸው ከሚሰጡዋቸው ምክንያቶች መካከል ዘረኝነት፣  የተበላሸ አስተዳደራዊ አሰራር መኖርና በአገሪቱ የሚታየው የመብት አፈና  የሚሉት ናቸው።
የአየር ሃይል ምንጮች እንደሚሉት ኮ/ል አበበ ተካ የውቅሮ ተወላጅ ሲሆኑ፣ በድሬዳዋ ምድብ ውስጥ ያሉ የሃላፊነት ቦታዎችን በውቅሮ ልጆች ብቻ እንዲሞሉ አድርገዋል። ቀደም ብሎ የአየር ሃይል አዛዥ የነበሩት አበበ ተክለሃይማኖት በተመሳሳይ የውቅሮ ልጅ ሲሆኑ፣ ኮ/ል አበበን አሁን ላሉበት ደረጃ ያደረሱዋቸው እርሳቸው መሆናቸውንም ምንጮች ይገልጻሉ። ኮ/ል አበበ አየር ሃይል እንዲዳከም ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውን የተለያዩ አብራሪዎች ቢናገሩም፣ እስካሁን ድረስ ማንም ደፍሮ እርምጃ አልወሰደባቸውም። እርሳቸው ሃላፊ ሆነው ከተሾሙ ወዲህ በ2001 ዓም ሃምሌ ወር ላይ 2 ኤፍ ኤፍ 260 የመሰረታዊ በረራ ማስተማሪያ ሄሊኮፕተሮች ተጋጭተዋል። እርሳቸው በሰጡት የተሳሳተ አመራር  2 ኤም አይ 35 ሄሊኮፕተሮች በአየር ላይ ተጋጭተው 6 አብራሪዎች አልቀዋል። አንድ ኤፍ ኤፍ ሄሊኮፕተር ደግሞ ሁርሶ ላይ ሞተር ጦፍቶበት የወደቀ ሲሆን፣ አብረራዎቹ እንደ እድል ተርፈዋል። እነዚህ ሁሉ ችግሮች የኮ/ል አበበ የአመራር አሰጣጥ ድክመት የፈጠራቸው መሆናቸው ቢታመንም፣ ለረጅም ጊዜ ጄ/ል ሞላ እንዳይገመገሙ አድርገዋቸው እንደቆዩ ጄ/ል ሞላ ሃላፊነቱን ከለቀቁ በሁዋላ ደግሞ ጄ/ል ሳሞራ እየተከላከሉላቸው ይገኛሉ።
ኮሎኔሉ አበበ በጦር ሄሊኮፕተሮች የኮንትሮባንድ እቃዎችን ወደ ድሬዳዋ እየጫኑ ከጄ/ል ሞላ ሃይለማርያም ጋር በመሆን ሲነግዱ እንደቆዩና ከፍተኛ የሆነ ሃብት እንዳከማቹ የቅርብ ምንጮች ይገልጻሉ። በድሬዳዋ፣ አዲስ አበባና መቀሌ ሰፋፊ ቦታዎችና በአዲስ አበባም አንድ ትልቅ ፎቅ አሰርተዋል በማከራየት ላይ ናቸው። እነዚህ ሁሉ ቸግሮች ጄ/ል ማሾ ኮሎኔል አበበን ለመክሰስ በቂ ምክንያቶች ቢሆኑላቸውም፣ ከላይ ባሉ ባለስልጣናት ድጋፍ በማጣታቸው እስካሁን ውጤታማ ሊሆኑ አልቻሉም። ሰሞኑን የጠፉትን አብራሪዎች ከጄ/ል ማሾ ጋር ለማያያዝ የእነ ኮ/ል አበበ ደጋፊዎች ጥረት እያደረጉ ሲሆን፣ ከጄ/ል ማሾ ጋር ግንኙነት አላቸው ወይም አላማቸውን ይደግፋሉ ያሉዋቸውን ሁሉ ለመምታት እየተንቀሳቀሱ ነው።
ኮ/ል አበበ ኢሳት ሊያነጋግራቸው ቢሞክርም ፈቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸው ይታወቃል። ብርጋዴር ጄነራል ማሾን ለማነጋገር ተደጋጋሚ ሙከራ ብናደርግም አልተሳካልንም።

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen