ከ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር የተሰጠ መግለጫ
የ‹‹ታዛቢዎች›› ምርጫ የገዥው ፓርቲንና የምርጫ ቦርድን አንድነት ይበልጡን ያረጋገጠ ነው!
የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር ‹‹ነጻነት ለፍትሓዊ ምርጫ›› በሚል ዘመቻ የተዘጋውን የምርጫ ምህዳር ለማስከፈት እየታገለ ይገኛል፡፡ ይህን ትግል የጀመርነው ገዥው ፓርቲ በአምባገነንነት ተቀናቃኞቹን ለማጥፋት ከሚወስደው እርምጃ ባሻገር ፍትሀዊ ምርጫ እንዲያስፈጽም የተቋቋመው ምርጫ ቦርድ ከገዥው ፓርቲ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ እየሰራ በመሆኑ ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት ምርጫ ቦርድ ራሱን ከገዥው ፓርቲ ወገንተኝነት ነጻ በማድረግ ሌሎች ተቀናቃኝ ፓርቲዎችንና ገዥውን ፓርቲ በእኩል አይን በማየት ተግባሩን በገለልተኝነት እንዲወጣና የገዥው ፓርቲ መሳሪያ መሆኑን እንዲያቆም በተደጋጋሚ ተቃውሟችንን አሰምተናል፡፡
ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ እንዳልሆነ ቅሬታችንን ስናቀርብ፣ ምህዳሩን ለማስከፈት ስንታገል ምርጫ ቦርድ የገዥው ፓርቲ መሳሪያ ስለመሆኑ የሚያሳዩ ተጨባጭ መረጃዎችን በማቅረብ ነው፡፡ እሁድ ታህሳስ 12/2007 ዓ.ም የህዝብ ታዛቢዎችን ለማስመረጥ በየ ቀበሌው በጠሩት ስብሰባዎች ተገኝተን በተጨባጭ ያረጋገጥነው ይህን የምርጫ ቦርድና የኢህአዴግን አንድነት ነው፡፡
የህዝብ ታዛቢዎች፣ የፖለቲካ ድርጅትና የግል እጩ ወኪሎች አሰራር መመሪያ ቁጥር 3/2001 አንቀጽ 9/3/ሀ መሰረት የምርጫ ጣቢያው ሀላፊ ለምርጫ ጣቢው ህዝብ ይፋ የስብሰባ ጥሪ እንደሚያደርግ ቢደነግግም ይህ ተግባራዊ ካለመደረጉም በላይ የገዢው ፓርቲ ካድሬዎች በየቀጠናው የመረጧቸው የወጣትና ሴት ሊግ አባላት ብቻ በስብሰባው እንዲሳተፉ ተደርገዋል፡፡ በተጨማሪም በዚሁ መመሪያ አንቀፅ 7/3 የህዝብ ታዛቢዎች በሚመረጡበት ጊዜ ተወዳዳሪ የፖለቲካ ድርጅቶች በፅሁፍ መጋበዝ እንዳለባቸው ያትታል፡፡ ሆኖም ከኢህአዴግ ተወካዮች ውጭ የትኛውም የተቃዋሚ ድርጅት ተወካይ በጽሁፍ አልተጋበዘም፡፡ በራሳችን ተነሳሽነት ጉዳዩን ለመከታተል ተወካዮቻችን ብንልክም ‹‹ልትበጠብጡ ነው የመጣችሁት›› እየተባለ እስከመታሰርና መባረር ደርሰዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ድምጻቸው እንዳይሰማ ተደርገዋል፡፡ የመኢአድና የአንድነት ተወካዮች ሂደቱን እንዳይሳተፉ ተደርገዋል፡፡
በዚሁ መመሪያ አንቀጽ 9/4 መ የምርጫ ጣቢያውን አምስት የህዝብ ታዛቢዎች ለመምረጥ 10 ሰው በእጩነት መጠቆም እንደለበት ቢደነገግም ከዚሁ ምርጫ ቦርድ ከማያከብረው ህግና ደንብ ውጭ ኢህአዴግ 99.6 አሸነፍኩት በሚልበትና ልምድ ባላቸው ታዛቢ ተቋማት በስፋት ማጭበርበር እንደተከሰተበት በተረጋገጠው ምርጫ 2002 ዓ.ም ‹‹ታዛቢ›› የነበሩ ሰዎች ያለ ተወዳዳሪ መጭውን ምርጫ እንዲታዘቡ ተደርጓል፡፡ በዚሁ ንዑስ አንቀጽ ሠ ታዛቢዎቹ በድምጽ ብልጫ መመረጥ እንዳለባቸው ቢደነገግም የ2002 ዓ.ም ‹‹ታዛቢዎች›› ያለ ተወዳዳሪ የኢህአዴግ አመራሮች በሆኑት አስመራጮች መልካም ፈቃድ ታዛቢ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡
በመሆኑም ለቀጣዩ ምርጫ የ‹‹ህዝብ ታዛቢዎች›› ያስመረጡት የገዥው ፓርቲ አመራሮች ከመሆናቸው በተጨማሪ የ‹‹ህዝብ ታዛቢዎች›› ተብለው የተቀመጡት ሰዎች መካከል የአልጋ ቁራኛ የሆኑ፣ ማንበብና መጻፍ የማይችሉ፣ በወጉ ተንቀሳቅሰው መታዘብ የማይችሉ አዛውንቶችና ባልና ሚስትም ጭምር ይገኙበታል፡፡ እነዚህም በ2002 ዓ.ም ‹‹ታዛቢዎች›› ተብለው ቀርበው ተግባራቸውን ሳይወጡ ከመቅረታቸውም ባሻገር ህጉ በማይፈቅደው መንገድ አሁንም ምርጫ እንዲያስፈጽሙ በገዥው ፓርቲ መወሰኑ፣ እንዲሁም በመታመማቸው፣ ማንበብና መጻፍ የማይችሉ በመሆናቸው መታዘብ እንደማይችሉ ቅሬታ ቢቀርብም ምርጫን በማስመሰያነት የሚጠቀመው ኢህአዴግና ለገዥው ወገንተኛ የሆነው ምርጫ ቦርድ በማን አለብኝነት አጽድቀውታል፡፡
ምርጫ ቦርድ በዚህ ብቻ ሳያበቃ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ከሂደቱ ባገለለ መልኩ የምርጫ ታዛቢዎችን መርጦ መሰየሙ ለገዢው ፓርቲ መገልገያ ከመሆኑም ባሻገር ባጠቃላይ ምርጫው የኢህአዲግ የማምታቻ ፖለቲካ እንደሆነ ያረጋገጠ ነው፡፡ ከኢህአዴግ በስተቀር ፓርቲዎች በደብዳቤ የህዝብ ታዛቢዎችን ምርጫ እንዲከታተሉ ያለመጠራታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በተለይም የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ፓርቲ (መኢአድ) እና አንድነት ለፍትህና ዴሞክራሲ ፓርቲ (አንድነት) በሂደቱ እንዳይሳተፉ ኃላፊነት በጎደለው የተበላሸ ቢሮክራሲ ማስተጓጎሉም ፍፁም ተቀባይነት የሌለው ነው፡፡ ችግሮች ቢኖሩ እንኳን በወቅቱ መፍታት እና መስተናገድ ሲኖርባቸው እና ምርጫ ቦርድ በአዋጅ የተጣለበትን ኃላፊነት ሳይወጣ ምርጫውን እመራለሁ ማለቱ በራሱ ተቋሙ በራሱ የቆመና በአግባቡ የሚሰራ አለመሆኑን አመላካች ጭምር ነው፡፡
ይህ የ‹‹ታዛቢዎች›› ምርጫ ከአሁን ቀደምም ተጨባጭ መረጃዎችን በማቅረብ ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ አለመሆኑን በመግለጽ ከገዥው ፓርቲ መሳሪያነት ወጥቶ ተግባሩን እንዲፈጽም የጀመርነው ትግል ትክክለኛነት ያረጋገጠልን ነው፡፡ ይህ በገዥው ፓርቲና ተግባሩን መወጣት ባቃተው ምርጫ ቦርድ የተከናወነው ድራማ የ‹‹ታዛቢዎች›› ምርጫ የኢህአዴግንና የምርጫ ቦርድን አንድነት ይበልጡን ያረጋገጠ ነው!
Keine Kommentare:
Kommentar veröffentlichen