በምርጫ አለመሳተፍ መብት ነው !በኢትዮጵያ ያለው ጭላንጭል የፖለቲካ ምኅዳር ሲታይ፣ይህ ውሳኔ የሕግ፣የፖለቲካ እና የሞራል ድጋፍ አለው፡፡ሆኖም ግን በምርጫ ያለመሳተፍ መብት በራሱ-የራሱ የሆነ ተግዳሮቶች አሉትና፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የትርፍ-ኪሳራ ሥሌት የግላቸው ነው የሚሆነው፡፡
ይድነቃቸው ከበደ
ይህ ጹሑፍ በምርጫ አለመሳተፍ መብት መሆኑን ከህግ አንፃር ለማየት እንጂ፣ የሚጪው አገረ አቀፍ ምርጫን አስመልክቶ “ኢሕአዴግ ለመርጫ አልተዘጋጀም !” እና “የ24 ሰዓት ተቃውሞ በአዲስ አበባ !” በሚል ዕርሶች ከዚህ በፌት በፃፍኳቸው ፁሑፍ የ2007 አገር አቀፍ ምርጫ፣ ገዥው መንግስት ለነፃ እና ፍትሃዊ ምርጫ እራሱን አዘጋጅቶ፣ ውጤታማ ምርጫ ማካሄድ እንደማይቻል የግል እምነቴን ገልጫለው፡፡
ወደተነሳሁበት ዕርስ ስገባ፡- ማንኛውም ሰው በፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ እንዲሳተፉ አይገደድም፣ባለመሳተፉ ግን ተቃውሞን የመግለፅ እና ደግፋ የመስጠት መብት ይነፈጋል ማለት አይደለም ፡፡ይህም በመሆኑ የትኛውም የዲሞክራሲ ሥርዓት የተሟላ ተሳትፎ በህብረተሰብ ካልተደረገበት ውጤታማነቱ ደካማ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡የዲሞክራሲ ሥርዓት ማሳያ መስታዎት ከሆኑት ውስጥ አንዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በነፃነት መንቀሳቀስ ነው፡፡ ማንኛውም ሰው ያለምንም ፍርሃት በፈለገው ወይም በፈለገችው ፓርቲ ውስጥ አባል የመሆን ዕድልና አማራጭ ማግኘት የግለሰብ መብት ነው፡፡ግለሰቦች በፈለጉት የፖለቲካ ፓርቲ የመደራጀት እና የመሳተፍ ነፃነት ሲኖራቸው ለዲሞክራሲ መሠረት ይሆናል፡፡
ይህ አይነቱ የዲሞክራሲ ሥርዓት በአገራችን ምን ያኸል ተፈፃሚ ነው ? ተብሎ ቢጠየቅ ምላሹን ለማወቅ ብዙም አድካሚ አይደለም፡፡ውጤቱ አሉታዊ ነው፡፡እርግጥ ነው በሕገ መንግስት አንቀፅ 31 ማንኛውም ሰው ለማንኛውም ዓለማ በህግ “የመደራጀት” መብት እንዳለው በግልፅ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ይሄን መነሻ በማድረግ በአገር አቀፍ እና በክልል ደረጃ የተቋቋሙ የፖለቲካ ፓርቲዎች መኖራቸው የሚታወቅ ነው፡፡የእነዚህ ፓርቲዎች መብት እና ግዴታ እንዲሁም ሊከተሏቸው የሚገባ መርህዎች፣ በሕገ መንግስቱ፣በፓለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ አዋጁች እዲሁም በመተዳደሪያ ደንብቻው ብቻ ነው፡፡
በዚህም መሠረት ተቋቁመው እየተንቀሳቀሱ ያሉ የተቃዋሚ ፓርቲዎች በአገራችን ቁጥራቸው በርካታ ቢሆንም፣ ቢሚፈለገው ሁኔታ እየተንቀሳቀሱ ያሉ ግን በቁጥር አነስተኛ ፓርቲዎች ሲሆን፣ የተቀሩት የምርጫ መጣ ወይም የመግለጫ አሯሯጮች pacemaker መሆናቸው በግልፅ የሚታወቅ ነው፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ዋንኛ ዓላማ በመርጫ ተወዳድረው በማሸነፍ የፓለቲካ ሥልጣን በመያዝ የቆሙለት ዓላማ በስልጣን ዘመን ተግባራዊ ማድረግ ነው፡፡
ምርጫ በዲሞክራሳዊ አካሄድ ለሚወከል መንግስት የጥንካሬ መለኪያ ነው፡፡ይህን ለማለት የሚያስችለው ተመራጮች መብታቸው እና ግዴታቸውን ሙሉ በሙሉ ከመራጩ ሕዝብ ስለሚያገኙት ነው፡፡እንዲ አይነቱ በሕዝብ ተሳትፎ ሥልጣን የሚቀየርበት ዋናው መንገድ ነፃና ሚዛናዊ የሆነ ምርጫ ሲደረግ ብቻ ነው፡፡ በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ በኢሕአዲግ/ በህወሐት መንግሰት የ24 ዓመት የስልጣን ዘመን በተደረጉ ምርጫዎች ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለመሆን አልቻለም፡፡ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ በዋነኛነት የሥርዓቱ አስከፊ ድርጊት ቢሆንም፣ በተጨማሪ ጠንካራ የሆኑ በመላው ኢትዮጵያ የሕዝብ ድጋፍ ያለው የተቃዋሚ ፓርቲ አለመኖሩም ጭምር ነው፡፡ እርግጥ ነው በ1997 ዓ.ም በቅንጅት የታየው የተቃዋሚ ፓርቲዎች መነቃቃት፣ በአገራችን የዲሞክራሲ በዓል አንድ እርምጃ ወደፊት ከነበረበት ያንቀሳቀሰው ቢሆንም፣ በገዥው ሥርዓት ቀጥተኛ ተፅኖ፣ እንዲሁም በቅንጅት ፓርቲ ውስጥ በታየው ድክመት እና የስልጣን ሽኩቻ የለውጥ እንቅስቃሴውን ገትቶታል፡፡
አሁን ላይ በአገራችን የሚንቀሳቀሱ የተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ከበፊቱ “በቆምክበት እርገጥ” አይነት የተቃውሞ እንቅስቃሴ ተላቀው ምን ያህል “ወደፊት” እየሄዱ ነው የሚለውን ምላሽ ይህን ጹሑፍ ለሚያነቡ እና ለጉዳዩ ቅርብ ነኝ ለሚሉ ወገኖች የምተወው ሃሳብ ነው፡፡ ሆኖም ግን በአገር ውስጥ የሚንቀሣቀሱ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ከ6 ወር በኋላ አገር አቀፍ ምርጫ ይጠብቃቸዋል፡፡ፓርቲዎች የምርጫ ፓርቲ ቢሆኑም ፣በምርጫ አለመሳተፍ መብታቸው በሕግ የተጠበቀ መሆኑን አውቀው ግራ ቀኛቸውን ቢመለከቱ፣ዝም ብሎ ገዥውን ፓርቲ በምርጫ ከማጀብ ይላቀቃሉ፤አሊያም በእኩል ተሳትፎ ወደ ምርጫው የሚገቡበትን መንገድ ተገዳድረው ማመቻቸት ይቻላል፡፡
የተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች የምዝገባ አዋጅ ቁ .573/2000 አንቀፅ 39 ቁ.2 ሐ.“ የፖለቲካ ፓርቲ ለሁለት ተከታታይ የምርጫ ዘመን የጠቅላላ ወይም የአካባቢ ምርጫ ወድድርን ሳይሳተፍ የቀረ እንደሆነ ” ምርጫ ቦርድ በአዋጁ መሠረት ውሳኔ በማስተላለፍ ከመዝገብ ሊሰርዝ ይችላል፡፡የሚል የህግ ድንጋጌ አለ፣ይህን ድንጋጌ ከተነሳንበት ዓላማ ጋር በማገናኘት ምክንያት እና ውጤቱን መመልከት ተገቢ ነው፡፡
በመሠረቱ የፓርቲ ነፃነት በእንዲ መልኩ መገደብ አጠቃላይ የአዋጁ ችግር ዋንኛ ማሳያ ነው፡፡የትኛውም ፓርቲ በምርጫ የመሳተፍ ወይም ያለመሳተፍ መብት ካለጊዜ ገደብ ለራሱ ለፓርቲ የሚተው ስራ እንጂ ፣በህግ ገደብ የተጣለበት መሆን የለበትም፡፡ይህን ለማለት የሚያስደፍረው የግል እንዲሁም የጋራ መብት የሚጋፋ በመሆኑ ነው፡፡ለዚህም ማሳያ የመምረጥ እና ያለመምረጥ መብት የተጠበቀ ነው፡፡ ለምሳሌ እኔ በመጪው ምርጫ አልመርጥም ፣አልመረጥም ይህ በህግ ክልከላ ተደርጎብኝ ሳይሆን የእኔ መብት በመሆኑ ነው፡፡ልክ እንደኔ የግል መብት ያላቸው ሰዎች ተሰባበስበን የጋራ መብታችን ለማቋቋም በምንቀሳቀስበት ወቅት በግሌ ማድረግ የምችለውን በጋራ እንደማጣት ይቆጠራል፡፡ከዚህ አንፃር ይህ ድንጋጌ በእኔ እይታ ተገቢ መስሎ አይታየኝም፡፡
አሁን ባለው ነባራዊ ሃቅ በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች የሚተዳደሩት በዚህ አዋጅ ነው፡፡በመሆኑም አዋጆን መሠረት በማድገረግ በምርጫ አለመሳተፍ ገደብ ቢኖረውም ለፓርቲዎች የተሰጠ መብት አለ፡፡ ማንኛው ፓርቲ ለሁለት ተከታታይ የምርጫ ዘመን ሳይሳተፍ የቀረ እንደሆነ ይሰረዛል፡-ይህ ማላት፣በ2002 አገር አቀፍ ምርጫ በማንኛውም ምክንያት በምርጫ ያልተሳተፈ “ሀ” የተባለ ፓርቲ በ2007 የማይሳተፍ ከሆነ ይሰረዛል ማለት ነው፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ ይሄ “ሀ” የተባለው ፓርቲ በ1997 ምርጫ አልተሳተፈም ብንል ፣በ2002 ተሳትፏል ካልን በ2007 ምርጫ አለመሳተፍ የ”ሀ”ፓርቲ መብት ነው፡፡ይህም በማድረጉ ከምርጫ ቦርድ ምን አይነት ጥያቄ ለዚህ ፓርቲ አይቀርብም፡፡በዚህ መሠረት ፓርቲዎች ለሁለት ተከታታይ የምርጫ ዘመን በምርጫ ካተሳተፉ የመሰረዝ እጣቸው በእጃቸው ነው፡፡ሆኖም ግን የምርጫ ዘሙኑ ተከታታይነት ሳይኖረው በምርጫ አለመሳተፍ በአዋጁ መሠረት የሚያስከትለው ውጤት አይኖረውም፡፡
ይህ ከላይ የቀረበው ማሣያ፣ ለአገር አቀፍ እንዲሁም ለአካባቢ ምርጫ የሚያገለግል ነው፡፡በአሁን ወቅት ሁለቱ ምርጫዎች በተመሳሳይ የምርጫ ዘምን ባለመካሄዳቸው እረሳቸውን ችለው የሚቆጠሩ የምርጫ ዘመን ነው፡፡በኢትዮጵያ አሁን ባለው የምርጫ ስርዓት ፣የአንድ የምርጫ ዘመን አምስት ዓመት ነው፡፡ስለዚህም በአገር አቀፍ እና በአካባቢ የምርጫ ዘመን የ2 ዓመት ልዩነት አለ ማለት ነው፡፡በመሆኑም በዘንድሮ የአገር አቀፍ ምርጫ ዘመን ከባለፈው ሁለት ዓመት ከተካሄደው የአካባቢ ምርጫ ዘመን ፈፅሞ የሚገኛኝ አይደለም፡፡
በሕገ መንግሥት አንቀፅ 38 ቁ.1 ሐ.“ በማናቸውም ደረጃ በሚካሄዱ ምርጫ፣የመምረጥ እና የመመረጥ ፣ምርጫው ሁሉ አቀፍ፣በእኩልነት ላይ የተመሰረት እና መራጩ ፈቃዱን በነጻነት የሚገልፅበት ዋስትና የሚሰጥ መሆን አለበት፡፡”በማለት የህጎች ሁሉ የበላይ ሕግ በሆነው ሕገ መንግሰት በግልፅ ተቀምጧል፡፡
ሆኖም በአገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ሕገ መንግስቱን መሰረት ያደረገ ምርጫ ስለመካሄዱ አጠራጣሪለው የሚል ፓርቲ፣እንዲሁም ምርጫው ከመካሄዱ በፌት በምርጫው ሄደት ላይ ቅደመ ሁኔታ እስካልሟላለት ድረስ የታሰበው ምርጫ ነጻ፣ፍትሃዊ፣ ተኣማኒና አሳታፊ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ አይደለም በማለት ከበቂ ምክንያቶች ጋር በማዛመድ ከላይ በተገለፀው የተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች የምዝገባ አዋጅ መሰረት፣ በምርጫ ያለመሳተፍ መብት በሕግ ድጋፍ ያላው መብት ነው፡፡
ይህ መብት ከሕገ መንግሰቱ እና ከላይ በተገለፀው አዋጅ የመነጨ ሲሆን፣ ከዚህ ውጪ ያሉ ማናቸውም አሰራሮች፣ልማዳች እንዲሁም መመሪያ ይህን መብት የሚጋፉ መሆን እንደሌለባቸው የታወቀ ነው፡፡እናም ፓርቲዎች ሁሌም የፖለቲካ ምኅዳሩ ተዘግቷል፣ሰላማዊ ሰልፍ ማካሄድ አልቻልንም፣መሰብሰቢያ አዳራሽ ተከለከልን……..ወዘተ እያሉ ከሚናገሩ፣ምኅዳሩ እንዲሰፋ ከገዥው ፓርቲ ጋር በመነጋገር ማስተካከል ካልተቻለ፣በጊዜ ከምርጫው ታቅበው ገዥው ፓርቲ እራሱ ደግሶ እራሱ ለብቻው ይስተናገድበት ዘንድ በመተው እውነታውን ለህዝብና ለዓለም ቁልጭ አድርጎ ማሳየት ነው፡፡እስከ መቼ በምርጫ መጭበርበር !
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር !
Keine Kommentare:
Kommentar veröffentlichen