Netsanet: ዜጎቻችንን በስደት አውሬና ውሃ እየበላቸው የሚገኘው በሃገራቸው ሰርቶ የመኖር ዋስትና ስለተነፈጉ ነው!! – ከአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) የተሰጠ መግለጫ

Freitag, 12. Dezember 2014

ዜጎቻችንን በስደት አውሬና ውሃ እየበላቸው የሚገኘው በሃገራቸው ሰርቶ የመኖር ዋስትና ስለተነፈጉ ነው!! – ከአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) የተሰጠ መግለጫ


UDJ-SEAL
ኢትዮጵያችን ከምትታወቅባቸው ዘርፈ ብዙ ገዥ- ወለድ ችግሮች መካከል ስደት አንዱ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ዜጎቻችን በሀገራቸው ላይ ሰርተው የመኖር ዋስትና በመነፈጋቸው፤ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው እናስተዳድራችኋለን በሚሉ ገዥዎች በመጨፍለቁ የተሸለ ነፃነትና ኑሮ ፍለጋ እግራቸው በመራቸው መሰደድ የተለመደ ሁኗል፡፡

ገዥው ፓርቲም ከራሱ የስልጣን ቆይታ በስተቀር ሀገራዊ አደጋ እየሆኑ የመጡና የዜጎችን ስነ-ልቡና የሚጎዱ ሁነቶችን እንደማንኛውም ዜጋ አድማጭ ከመሆን በዘለለ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ቁርጠኝነትም ፍላጎትም እንደሌለው በተደጋጋሚ ተስተውሏል፡፡ ዜጎች ሀገራቸውን ጥለው ለምን በአደገኛ ሁኔታ ስደትን እንደመረጡ ከመረዳትና ችግሩን ከስሩ ለመፍታት እንቅስቃሴ ከማድረግ ይልቅ አንደመፍትሄ የተወሰደው ህገ-ወጥ አዘዋዋሪ የተባሉት ላይ ብቻ በመሆኑ ችግሩ እልባት ሊያገኝ አልቻለም፡፡ ስለዚህ ዛሬም ጀሮአችን የወገኖቻችንን ሰቆቃ ከመስማትና እየደረሰባቸው ለውን ጉድ ከማየት አልታቀበም፡፡ ፓርቲያችን እንደሚያምነው ለዚህ ህዝባዊ ሰቆቃ ዋነኛ ተጠያቂ ዜጎች በሀገራቸው ተስፋ እንዲያጡና ሰርተው የሚኖሩበት ዕድል እንዳያገኙ ያደረገውን ደፍጣች ስርዓት የገነባው የኢህአዴግ መንግስት ነው፡፡

ሰሞኑን ከ70 የሚበልጡ ኢትዮጵያውያን በጀልባ የተለመደውን የተሻለ ነፃነትና ስራ ፍለጋ ወደ የመን ሲሻገሩ ሰምጠው መሞታቸው እየተዘገበ ነው፡፡ የኢህአዴግ መንግስት በሚመራት ሀገራችን እና እከተለዋለሁ በሚለው የልማታዊ መንግስት ፍልስፍና ዜጎች በሀገራቸው ሰርተው መኖር ስላልቻሉና ሰርክ የሚለፈፈው የ11 በመቶ እድገት ዜጎችን ከስደትና ከመከራ ሊታደጋቸው እንዳልቻለ የሚያሳይ ነው።

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ በእነዚህ ዜጎች በዚህ ሁኔታ መሞት የተሰማው ሀዘን እጅግ ጥልቅ ነው። ለወዳጅ ዘመዶቻቸውም መፅናናትን እንመኛለን፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አሳዛኝ ክስተት ሲፈጠር ደግሞ ይሄ የመጀመሪያው አይደለም። ከአሁን በፊትም በተመሳሳይ ሁኔታ ወደ ተለያዩ የዓረብ ሀገራትና ወደ አውሮፓ ደህንነቱ ባልተጠበቀ መንገድ በጀልባ ለመሻገር ሲሞክሩ ያለቁት ወገኖቻችን ቁጥር ቀላል አይደለም።

ገዥው ፓርቲም የፓርቲያችንን ሀገራዊ ጥሪ አዳምቶ ባያውቅም የዜጎች የኢኮኖሚ ዋስትና እንዲረጋገጥ፤ ደህንንነታቸው እንዲጠበቅና በሀገራቸው ሰርተው መኖር የሚችሉበት ሁኔታ እንዲፈጠር ከፕሮፓጋንዳ ባለፈ ጠንካራ ስራ መስራት አለበት ብለን እናምናለን።
ለዘላቂ መፍትሄ ግን ስደትና እልቂት ከዚህ የከፋ ጉዳት ከማድረሱ በፊት ህዝቡ ትኩረት ሰጥቶ እንዲከታተለውና ለስደት የዳረገውን ስርዓት በመታገል ህዝባዊ የሆነ መንግስት ማቋቋም እንደሚገባው እናምናለን፡፡ የተከበረው የኢትዮጵያ ህዝብ መፍትሄው ስደት ሳይሆን እዚሁ አላሰራ ያለውንና ነፃነት ነጣቂውን መንግስት በመፋለም ስር ነቀል ሀገራዊ ለውጥ እንዲመጣ መታገል ይኖርበታል፡፡

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት)
ታህሳስ 1 ቀን 2007 ዓ.ም
አዲስ አበባ

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen