Netsanet: ብሄራዊ ብድር የዕድገታችን ምንጭ እንጂ የደኅንነታችን ስጋት ሊሆን አይገባም

Samstag, 13. Dezember 2014

ብሄራዊ ብድር የዕድገታችን ምንጭ እንጂ የደኅንነታችን ስጋት ሊሆን አይገባም

እኛ ሰዎች ሁሌም ከምንፈራዉና ከምንጠላዉ አንዴ ከገባንበት ደግሞ የቱንም ያክል ብንጠላዉና ብንፈራዉ እየደጋገምን የምንዘፈቅበትና በቀላሉ የማንወጣዉ አዘቅት ቢኖር ብድር ወይም የብድር ልጅ የሆነዉ ዕዳ ነዉ። ብድር ግለሰቦች ብቻ ሳይሆኑ የንግድ ድርጅቶች፤ ማዘጋጃ ቤቶች፤ ትላልቅ ኮርፓሬሺኖችና አገሮች በአጭርና በሪጂም ግዜ የሚያጋጥማቸዉን የገንዘብ እጥረት የሚሸፍኑበት መንገድ ነዉ። ወይም ቀለል ባለ አማርኛ ብድር ወደፊት በምናገኘዉ ገቢ ዛሬን መኖር ማለት ነዉ። ብድር ግለሰቦች፤ ድርጅቶች ወይም አገሮች የመከፈል አቅማቸዉን እያዩ ቢበደሩና የተበደሩትን ገንዝብ ዉጤታማ በሆነ መንገድ ከተጠቀሙበት የእድገትና የብልጽግና መንገድ የሚከፍት አለዚያም የምንበደረዉ ብድር ከአቅም በላይ ከሆነና ዉጤታማ ባልሆነ መልኩ ከተጠቀምንበት ደግሞ በቀላሉ የማንወጣዉ መቀመቅ ዉስጥ ይዞን የሚገባና ጫናዉ ከትዉልድ ወደ ትዉልድ የሚተላለፍ ዕዳ ነዉ። ዕዳ ደግሞ በተለይ አገሮች የሚገቡበት ዕዳ ተከፍሎ ካላለቀ ወይም በምህረት ካልተሻረ በቀር ወለዱ ወለድ እየወለደ በተበዳሪ አገሮች የኤኮኖሚ እድገት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያደርግ የዕድገትና የብልፅግና ጠላት ነዉ። ዛሬ ሰፋ አድርገን የምንመለከተዉ ብድርና ዕዳን ቢሆንም ዋናዉ ትኩረታችን ግን አገራችን ኢትዮጵያን ጨምሮ በታዳጊ አገሮች የኤኮኖሚ ዕድገት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ የሚያደርገዉን ብሄራዊ ብድርና ዕዳ ነዉ። ሁላችንም እንደምናዉቀዉ አገራችን ኢትዮጵያ ባለፉት ሃያ አመታት በብድር ላይ ብድር እየተበደረች አንዱንም ሳትከፍል በድጋሚ እየተበደረች ከድጡ ወደማጡ እየገባች ነዉ።
የኢትዮጵያ መንግስት መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ የዉጭ አገር ምንጮች ብድር መበደር ከጀመረ ብዙ አመታት ተቆጥረዋል።ከቀዳማዊ ሚኒልክ በኋላ ኢትዮጵያን ለረጂም አመታት የመሩት ሦስቱ መንግስታት የብድር ጥማት ከፍተኛ ቢሆንም በብድር መጠኑም ሆነ በተከማቸ የዕዳ መጠኑ ዛሬ በስልጣን ላይ አንዳለዉ እንደ ወያኔ አገዛዝ የአገራችንን ብሄራዊ ደህንነት ለአደጋ ባጋለጠ መልኩ ብድር የተበደረና ዕዳ ዉስጥ የተዘፈቀ አገዛዝ ኢትዮጵያ አይታ አታዉቅም። የወያኔ አገዛዝ አገር ዉስጥ ቦንድ እየሸጠና ብሔራዊ ባንክን እያስገደ በተለያየ መልኩ የሚወስደዉ ብድር ከአለም ባንክ፤ ከአለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት፤ ከዉጭ አገር ባንኮችና አበዳሪ አገሮች በየአመቱ ከሚበደረዉ ብድር ጋር ተደምሮ የዛሬዉን ኢትዮጵያዊ ብቻ ሳይሆን የዛሬዉን ኢትዮጵያዊ የልጅ ልጆች ጭምር ባለዕዳ አድርጓቸዋል።
የወያኔ አገዛዝ ለህዳሴዉ ግድብና ለእድገትና ትራንስፎርሜሺን ዕቅድ ማስፈጸሚያ በሚል የአገሪቱን አመታዊ ገቢና የመክፈል አቅም በላገናዘበ መልኩ እጅግ በጣም ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ገንዝብ ከተለያዩ የአገር ዉስጥና የዉጭ አገር ምንጮች እየተበደረ ነዉ። ይህ መጠነ ሰፊ ብድር በረጂም አመት የሚከፈልና ከፍተኛ ወለድ የተሸከመ ሲሆን ወያኔ ይህ ብዙ ኢትዮጵያዉያንን ያሰጨነቀ ብሄራዊ ዕዳ አልበቃ ብሎት ከአቅም ዉጭ የጀመራቸዉን ፕሮጀክቶች ለማስጨረስ ነዉ በሚል ሰበብ አሁንም አገራችን ኢትዮጵያን ከዕዳ ወደ ዕዳ እየከተታት ይገኛል። በተለይ ወያኔ አበዳሪ አገሮች፤ የአለም ባንክና ወዳጆቹ የሆኑ መንግስታት ጭምር ተዉ ይቅርብህ ብለዉ እየመከሩት አልሰማ ብሎ በዚህ አመት ለመሸጥ ያሰበዉ ሉዓላዊ ቦንድ ወይም ፈረንጆቹ ሶቨርን ቦንድ ብለዉ የሚጠሩት ቦንድ ሽያጭ የጉዳዩ አሳሳቢነት የገባቸዉን ኢትዮጵያዉያንንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ከወዲሁ እያሰጨነቀ ነዉ። በእርግጥም ሉዓላዊ ቦንድ ሽያጭ የሚያስጨንቅ ብቻ ሳይሆን አንደ ኢትዮጵያ አይነቶቹን ቀድሞዉኑም ዕዳ ዉስጥ የተዘፈቁ ደሃ አገሮች ህልዉና አደጋ ዉስጥ የሚከት የኤኮኖሚ ዕድገትን ብቻ ሳይሆን የአገር ደህንነትን ጭምር የሚፈታተን አደገኛ ጅምር ነዉ። ለመሆኑ ሉዓላዊ ቦንድ ምንድነዉ? አደገኛነቱስ ምኑ ላይ ነዉ?
ሉዓላዊ ቦንድ አገራቸዉ ዉስጥ ዝቅተኛ ቁጠባ የሚታይባቸዉ ብሔራዊ መንግስታት አገራቸዉ ዉስጥ ከአቅማቸዉ በላይ የሆነ የገንዘብ እጥረት ሲያጋጥማቸዉ የሽያጭ ዋጋዉ በአገራቸዉ ገንዘብ ሳይሆን ያወጣናል ብለዉ በሚያምኑት በሌላ አገር ገንዘብ ለምሳሌ በዶላር ወይም በዩሮ የተተመነ ቦንድ እየሸጡ ገንዝብ የሚበደሩበት መንገድ ነዉ። የየአገሩ መንግስታት ቦንድ አየሸጡ ገንዘብ መበደራቸዉ አዲስ ክስተት አይደለም፤ ሆኖም መንግስታት በተለይ የታዳጊ አገሮች መንግስታት ቦንድ የሚሸጡት አገራቸዉ ዉስጥ በአገራቸዉ ገንዘብ ነዉ። ሉዓላዊ ቦንድን ልዩ የሚያደርገዉ ቦንዱ የሚሸጠዉ በአለም አቀፍ ደረጃ ሆኖ ሽያጩ የሚከናወነዉ ደግሞ በዉጭ ምንዛሪ መሆኑ ነዉ። ሉዓላዊ ቦንድ ሽያጭን ከመደበኛ ቦንድ ሽያጭ የሚለዩት ብዙ ነገሮች አሉ።
ሉዓላዊ ቦንድ ከሌሎች መደበኛ ቦንዶች ጋር ሲነፃፀር ብዙ ዉስብስብ ችግሮች አሉበት። ለምሳሌ ሉዓላዊ ቦንድ የሚገዙ አገሮች ወይም ድርጅቶች ቦንዱን የሚገዙት በዉጭ ምንዛሪ ነዉ፤ ሁለተኛ ሻጩ አገር ለቦንዱ የሚከፍለዉ ወለድ እጅግ በጣም ከፍተኛ ነዉ። በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ብዙዉን ግዜ ሉዓላዊ ቦንድ የሚሸጥ አገር ከቦንዱ ሽያጭ የሚያገኘዉ ገንዘብ ወለዱ የተቀነሰለት ገንዝብ ነዉ። ለምሳሌ በ10 በመቶ ወለድ የአንድ መቶ ሚሊዮን ዶላር ሉዓላዊ ቦንድ የሚሸጥ አገር እጁ ላይ የሚገባዉ ዘጠና ሚሊዮን ዶላር ሲሆን ብድሩን መልሶ ሲከፍል የሚከፍለዉ ደግሞ አንድ መቶ ሚሊዮን ዶላር ነዉ። ይህ ማለት ደግሞ ቦንድ ሻጩ አገር ወለዱን የሚከፍለዉ በተበደረዉ ገንዝብ ተጠቅሞበት ሳይሆን የተበደረዉ ገንዘብ ገና እጁ ላይ ሳይገባ ነዉ ወለዱን የሚከፍለዉ። ለሉዓላዊ ቦንድ የሚከፈለዉ ወለድ እጅግ በጣም ከፍተኛ ስለሆን ብዙ አገሮች በተለይ ታዳጊ አገሮች ሉዓላዊ ቦንድ መሸጥ የማይፈልጉት ይህንኑ ለብድሩ የሚከፈለዉን ከፍተኛ ወለድ ሰለሚፈሩ ነዉ።
የወያኔ አገዛዝ እንደተራ ወረቀት እየፈበረከ ገበያ ዉስጥ የሚበትነዉ ገንዘብና ከአገር ዉስጥ ባንኮች ከአቅሙ በላይ የሚበደረዉ ገንዝብ ኢትዮጵያ ዉስጥ የዋጋ ንረቱን ምን ያህል ሰማይ ላይ እንደሰቀለዉና የኢትዮጵያን ህዝብ ምን ያክል እንዳደኸየ ሁላችንም በግልጽ የምናዉቀዉ ሀቅ ነዉ። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ የአገራችን ገበሬና ሠራተኛ የወያኔ ብልሹ የኤኮኖሚ ፖሊሲ ለአመታት ከፈጠረዉ የዋጋ ንረት በሽታ ሳይድን ነዉ ሌላ ሉዓላዊ ቦንድ የሚባል በቀላሉ የማይድን አደገኛ በሽታ ፊቱ ላይ የተደቀነበት።
ሉዓላዊ ቦንድ ደሃ አገሮች የሚሸጡትና ኃብታም አገሮች የሚሸጡት እየተባለ በሁለት ይከፈላል። ኃብታም አገሮች የሚሸጡትን ቦንድ ከነወለዱ ከፍለዉ ይጨርሳሉ ተብሎ በቦንድ ገዢ አገሮችና ድርጅቶችና ስለሚታመን እነዚህ አገሮች ለሚሸጡት ሉዓላዊ ቦንድ የሚከፍሉት ወለድ ዝቅተኛ ነዉ። ኢትዮጵያን መሰል ደሃ አገሮች ግን ብድር የመክፈል ችሎታቸዉ አስተማማኝ ስላልሆነ ሉዓላዊ ቦንድ ሲሸጡ ለቦንድ ገዢዉ የሚከፍሉት ወለድ እጅግ በጣም ከፍተኛ ነዉ። ስለሆነም ደሃ አገሮች በተለይም እንደ ኢትዮጵያ አይነቶቹ ለመጀመሪያ ግዜ ሉዓላዊ ቦንድ ለሚሸጡ አገሮች ቦንድ ለመሸጥ ከመወሰናቸዉ በፊት ማስተካከል ያለባቸዉ ብዙ ነገሮች አሉ። በነገራችን ላይ ሉዓላዊ ቦንድ መሸጥ በራሱ ምንም ጥፋት የለበትም። እንዲያዉም ህዝባዊና አገራዊ ሃላፊነት የሚሰማቸዉ መንግስታት ሉዓላዊ ቦንድ በመሸጥ የፋይናንስ ጉድለታቸዉን በመሸፈን የአገራቸዉን እድገት አቅጣጫ ቀይሰዉ ጠንካራ ኤኮኖሚ የመገንባት አቅም ማግኘት ይችላሉ። በኛም አገር ዘረኞቹ የወያኔ መሪዎቸ አንደኛ አገራዊ ሃላፊነት ቢሰማቸዉ፤ ሁለተኛ በአቅማቸዉ ቢኖሩ፤ ሦስተኛ በአገር ስም የተበደሩትን ገንዘብ መዝረፍ አቁመዉ ሁሉንም ለአገር ጥቅም ቢያዉሉትና ተበድረዉ በሚሰሯቸዉ ፕሮጀክቶች ሁሉም ኢትዮጵያዊ እኩል ተጠቃሚ ቢሆን አገራችን መደበኛ ቦንድም ሆነ ሉዓላዊ ቦንድ በመሸጥ የምትበደረዉ ገንዘብ ብሄራዊ አቅም ስለሚገነባ ዕዳዉ ብዙም አያስፈራንም። ችግሩ ያለዉ ሉዓላዊ ቦንድ መሸጡ ላይ ሳይሆን እዚህ ዉሳኔ ላይ ከመደረሱ በፊት መወሰድ ያለባቸዉን እርምጃዎች በጥንቃቄ መዉሰዱ ላይ ነዉ። የወያኔም ትልቁ ችግር ያለዉ እዚህ ላይ ነዉ። የቦንዱ ሽያጭ ይዞት የሚመጣዉን ጣጣና ፈንጣጣ ግምት ዉስጥ ሳያስገባ ነዉ ሉዓላዊ ቦንድ እሸጣለሁ ብሎ ያወጀዉ።
የወያኔ አገዛዝ የበጀት ዲሲፕሊን የሌለዉ፤ በአቅሙ የማይኖር፤ እመራዋለሁ የሚለዉን አገር ኃብት የሚዘርፍና በሚያደርጋቸዉ ነገሮች ሁሉ ኢትዮጵያን የማያስቀድም የአገርና የህዘብ ጠንቅ የሆነ ክፉ አገዛዝ ነዉ።ኢትዮጵያን ጨምሮ በመላዉ አለም የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን የወያኔ ፓርላማ የሉዓላዊ ቦንድ ሽያጭ ረቂቅ ህግ አፀደቀ ሲባል ቀልባቸዉ የረገፈዉ ከላይ የተጠቀሱትን የወያኔ ጠባዮች በሚገባ ሰለሚያዉቁ ነዉ። ወያኔ ከአገር ዉስጥም ሆነ ከአገር ዉጭ የብድር ምንጮች በሚበደረዉ ገንዘብ መንገድ፤ ህንፃና ግድብ ሊሰራ ይችላል። እነዚህ ነገሮች በመሰራታቸዉ የሚከፋ ኢትዮጵያዊ ያለ አይመስለንም። ብዙ ኢትዮጵያዉያንን የሚከፋቸዉ ወያኔ በነሱ ስም በተበደረዉ ብድር በጀመራቸዉ ፕሮጀክቶች ሁሉ መጠቀም አለመቻላቸዉና በገዛ አገራቸዉ የበይ ተመልካች መሆናቸዉ ነዉ። እዚህ ላይ የህዳሴዉን ግድብ አንደ ምሳሌ ወስደን መመልከት እንችላለን። የህዳሴዉን ግድብ የእንጂኔሪንግ ኮንትራት ያለምንም ጨረታ አሸንፎ ከፍተኛ ትርፍ የሚያጋብሰዉ መስፍን ኢንጂኔሪንግ የተባለ የወያኔ ድርጅት ነዉ። ለህዳሴዉ ግድብ ማሰሪያ ሲሚንቶ የሚያቀርበዉ የወያኔዉ መሶብ ሲሚንቶ ፋብሪካ ነዉ። ለግድቡ ፕሮጀክት የትራንስፖርትና ማጓጓዣ አገልግሎት የሚሰጡት የአዜብ መስፍን ዘመዶች ናቸዉ;፡ ለህዳሴዉ ግድብ ሰራተኞች የምግብ አገልግሎት የሚሰጡት የወያኔ ኩባንያዎች ናቸዉ። የህዳሴዉን ግድብ እንደምሳሌ ወሰድነዉ እንጂ ኢትዮጵያ ዉስጥ በብድርም ሆነ በእርዳታ ገንዘብ በሚሰሩ ፕሮጀክቶች ሁሉ ተጠቃሚዉ ወያኔና ባለ ሟሎቹ ናቸዉ። ወያኔ እንደ ተራራ የቆለለዉን ብድር እስከነወለዱ የሚከፍለዉ ግን የኢትዮጵያ ህዝብ ነዉ።
የአለም ባንክንና አለም አቀፉን የገንዝብ ድርጅት ጨምሮ ብዙ የኤኮኖሚ ሳይንስ ጠበብቶች አገሮች በተለይ የዉጭ ዕርዳታ ጥገኛ የሆኑ ደሃ አገሮች ሉዓላዊ ቦንድን አገር ዉስጥ ለሚያጋጥማቸዉ የገንዘብ ጉድለት ማሟያ አድረገዉ እንዳይጠቀሙ በተከታታይ ያስጠነቅቃሉ። የወያኔ አገዛዝም ይህ ማስጠንቀቂያ በተከታታይ ከደረሳቸዉ መንግስታት አንዱ ነዉ። ሆኖም የማንንም ምክር የማይሰማዉ ወያኔ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ ሉዓላዊ ቦንድ በመሸጥ መዘዙ ከትዉልድ ወደ ትዉልድ የሚተላለፍ ክፉ በሽታ እየዘራ ይገኛል። ወያኔ እስከዛሬ የተበደረዉ ብድር ምኑም ሳይከፈል ሉዓላዊ ቦንድ ከጀመረ በእናት አገራችን ላይ እንደ ትልቅ ተራራ የሚቆለለዉን ብሄራዊ ዕዳ የምንከፍለዉ እኛ የዚህ ዘመን ኢትዮጵያዉያን ብቻ ሳንሆን ገና ያልተወለዱ የልጅ ልጆቻችን ጭምር ናቸዉ።
ኢትዮጵያ ኤኮኖሚዋ ያልዳበረ ደሃ አገር በመሆኗ አበዳሪ አገሮችን ብድር ሰርዙልኝ ብላ ሳትወተዉት፤ የብድር ክፊያ ግዜዋን ሳታራዝም፤ ወይም የብድር ዉል ማሻሻያ ጥያቄ ሳታቀርብ እስከዛሬ የተበደረችዉንና ለወደፊትም የምትበደረዉን የዉጭና የአገር ዉስጥ ብድር የመክፈል ሃላፊነቷን ጤናማ በሆነ መልኩ መወጣት የምትል አገር አይደለችም። እንደዚህ የምንለዉ ደግሞ ወያኔንና ዘረኛ ስርዐቱን ስለምንጠላ ሳይሆን በሚከተሉት ማስረጃዎች ላይ ተንተርስሰን ነዉ። 1ኛ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ዕዳና አጠቃላይ አገራዊ ምርት (GDP) መጧኔ ቁጥሩ ከፍተኛ ነዉ።
ይህ ማለት ኢትዮጵያ የተቆለለባት ዕዳና ቤሄራዊ ገቢዋ ይቀራረባሉ፤ እኩል ናቸዉ ወይም ዕዳዋ ከገቢዋ ይበልጣል ማለት ነዉ። 2ኛ የአገራችን የዉጭ ብድርና የዉጭ ንግድ ገቢ መጣኔ እጅግ በጣም ከፍተኛ ነዉ። ይህ ማለት ደግሞ ምርታችንን ለአለም ገበያ አቅርበን የምናገኘዉ የዉጭ ምንዛሪ ከዉጭ አገር ዕቃ ሊገዛልን ቀርቶ የተበደርነዉን ብድር ወለዱንም መክፈል አይችልም ማለት ነዉ። 3ኛ የወያኔ አገዛዝ የብድር ዕዳና አገዛዙ አገር ዉስጥ በግብር መልክ የሚሰበስበዉ ገቢ መጣኔ እጅግ በጣም ከፍተኛ ነዉ። ቀለል ባለ አማርኛ የወያኔ አገዛዝ ሁሉንም ነገር ትቶ በሚሰበስበዉ ገንዘብ ዕዳዉን ብቻ ቢከፍል ከእዳዉ ለመላቀቅ ብዙ አመታት ይፈጅበታል።
ለእናት አገራቸዉ ለኢትዮጵያ የሚጨነቁ ኢትዮጵጵያዉያን የወያኔ ፓርላማ በቅርቡ ያፀደቀዉን የሉዐላዊ ቦንድ ሽያጭ ህግ አጥብቀዉ የሚቃወሙት እነዚህን ሁሉ ገሃድ የወጡ የአገራችንን ችግሮች በሚገባ ስለሚያዉቁ ነዉ። ለኢትዮጵያና ለህዝቧ እንጨነቃለን ስንል ደግሞ እንደ ወያኔ “እኔ ከሞትኩ ሠርዶ አይብቀል” በሚል የንፉጎች አባባል ተዉጠን አይደለም። ለትናንትናዋ ኢትዮጵያ እንደተጨነቅን ሁሉ ለዛሬዋ፤ ለነገዋና እኛ ካለፍን በኋላ ለሚመጣዉ ኢትዮጵያዊ ትዉልድም እኩል እንጨነቃለን። ለዚህም ነዉ የሉዓላዊ ቦንድ ሽያጩን ብቻ ሳይሆን ወያኔ ያመጣብንን መዐት ሁሉ ለማስቆምና አገራችንን በትክከለኛ የእድገትና የዲሞክራሲ መሠረቶች ላይ ለማስቀመጥ ወያኔ መወገድ አለበት ብለን የሞት የሽረት ትግል የጀመርነዉ።

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen