Netsanet: የደብረ ዘይት የአየር ሃይል ባልደረባ ፓይለት አዲሱ አገኘሁ የግፍ አገዛዙን በመቃወም የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባርን ተቀላቀለ።

Samstag, 13. Dezember 2014

የደብረ ዘይት የአየር ሃይል ባልደረባ ፓይለት አዲሱ አገኘሁ የግፍ አገዛዙን በመቃወም የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባርን ተቀላቀለ።


ሕዳር 30/2007 ዓ.ም ወደ አርበኞች ግንባር የትግል ጎራ የተቀላቀለው ፓይለት አዲሱ አገኘሁ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ፓዊ ወረዳ ውስጥ ተወልዶ ያደገ መሆኑ ሲታወቅ በደብረ ዘይት አየር ሃይል ውስጥ ለስድስት/6/ ዓመት ያህል በአውሮፕላን አብራርነት ሙያ ላይ ተመድቦ ሲሰራ መቆየቱ ታውቋል።
ፓይለት አዲሱ አገኘሁ የመጀመሪያውን በረራ ያደረገው S.F 260 በሚባለው አውሮፕላን መሆኑ ሲታወቅ፦ በአየር ሃይል የቆይታ ጊዜያቶቹም የተለያዩ ስልጠናዎችን የተከታተለ መሆኑን ፓይለት አዲሱ አገኘሁ ገልፆ ከተከታተላቸው ኮርሶች መካከል በኬሚካል ኢንጅነሪንግ ለ3 ዓመት ያህል ስልጠና የወሰደ ሲሆን፦ በግራውንድ ቶሪ ስልጠና በተመሳሳይ ለ3 ዓመት ያህል ሲከታተል ቆይቶ ከአሰልጣኞቹ ጋር ባለመግባባቱ ምክንያት ስልጠናውን ለማቋረጥ እንደተገደደ ፓይለት አዲሱ አገኘሁ አክሎ ገልጿል።
ሰሞኑን የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባርን የተቀላቀለው ፓይለት አዲሱ አገኘሁ ጨምሮ እንደገለፀው፦ በኬሚካል ኢንጅነሪንግ ተቋም ውስጥ በተማሪዎች የምግብ በጀት ላይ የተቋሙ አስተዳዳሪዎች እየፈፀሙት ያለው የሙስና ወንጀልና እንዲሁም በአየር ሃይል አባላት ላይ እየተሰራ ያለው የዘር መድሎ ልዩነት የተነሳ አገዛዙን ለመክዳትና የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባርን ለመቀላቀል እንደቻለ ፓይለት አዲሱ አገኘሁ ጨምሮ ገልጿል ።
የደብረ ዘይት የአየር ሃይል አባላት በግፍ አገዛዙ በመማረር ከፊሉ ሃገር ጥለው እየኮበለሉ መሆናቸው ሲታወቅ፦ ከፊሉ ደግሞ ፀረ-ወያኔ የነፃነት ትግሉን በመቀላቀል ላይ ይገኛሉ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፓይለት አዲሱ አገኘሁን ጨምሮ አምስት/5/ የአየር ሃይል ባልደረቦች የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባርን መቀላቀላቸው የሚታወስ ነው።
በተያያዘ ዜና፦ ብዛት ያላቸው የጎንደር ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባርን ተቀላቀሉ። 
ሕዳር 30/2007 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባርን ከተቀላቀሉት የጎንደር ዩኒቨርስቲ የB.A ተመራቂ ከሆኑት ተማሪዎች መካከል ተማሪ ቻላቸው ተክሉ ወ/ማሪያም ፣ ተማሪ ተስፋሁን ፈንታ እና እንዲሁም የጎንደር የቴክኒክ ማሰልጠኛ የ2ኛ ዓመት ተማሪዎች የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባርን ተቀላቅለዋል።
እኒሁ በቡድን ሆነው ግንባሩን የተቀላቀሉት የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች በሰጡት የጋራ አስተያየት የመንግስት ሥራን ለመያዝ መስፈርቱ የፓለቲካ አመለካከት ወይም ወያኔያዊ አስተሳሰብ ላይ የተመሰረተ የፓለቲካ ምዘና በመሆኑ በአሁኑ ጊዜ አፍቃሪ ወያኔ ያለሆነ የሐገሪቱ የተማረ ዜጋ እንኳንስ የመንግስት ሰራተኛ ሆኖ ራሱን፣ ቤተሰቡንና ሃገሩን ሊያገለግል ቀርቶ በሥራ አጥነት እየባዘነ በሰላም ለመኖር ከማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል በማለት በአገዛዙ ላይ ያላቸውን ጥላቻ ተማሪዎቹ በቁጭት አስተያየታቸውን በጋራ ሰንዝረዋል።

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen