Netsanet: የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር ሁለተኛ ዙር መርሓ ግብሩን በቅርቡ እንደሚጀመር አስታወቀ

Sonntag, 14. Dezember 2014

የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር ሁለተኛ ዙር መርሓ ግብሩን በቅርቡ እንደሚጀመር አስታወቀ

• ‹‹ገዥው ፓርቲ ከፍርኃት ተላቆ ለህዝብ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት አለበት!››
ከህዳር ወር 2007 ዓ.ም ጀምሮ የአንድ ወር መርሓ ግብር ነድፎ ሲንቀሳቀስ የቆየው የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር በዛሬው ዕለት ታህሳስ 5/2007 ዓ.ም ‹‹በአፈና፣ በኃይል እርምጃና በውንብድና መብታችንን ለድርድር አናቀርብም!›› በሚል ባወጣው መግለጫ ሁለተኛ መርሓ ግብሩን በቅርብ ቀን ይፋ እንደሚያደርግ ገልጾአል፡፡
መግለጫው ለህዳር 7/2007 ዓ.ም ታቅዶ የነበረው ህዝባዊ አደባባይ ስብሰባ፣ እንዲሁም ለህዳር 27/28 2007 ዓ.ም ታቅዶ የነበረው የአዳር ሰልፍ በገዥው ፓርቲ የፖሊስና የደህንነት ኃይሎች እንደተበተነ የሚታወቅ ሲሆን ትብብሩ መርሓ ግብሮቹን ለማስፈጸም ህጋዊ መንገድ ቢከተልም በወቅቱ ስርዓቱ የወሰደውን ህገ ወጥ እርምጃ በዝርዝር አስቀምጧል፡፡
ትብብሩ በመግለጫው በአንዱ ወር መርሓ ግብር ወቅት ስርዓቱ አፋኝ እርምጃዎችን ቢወስድም ገዢው ፓርቲ በዘመናት በማለማመድ ፈቃጅ ሆኖ ለመታየት ያደረገውን ጥረት ሰብሮ ዕውቅና ከመስጠት ያለፈ ህጋዊ ሥልጣን የሌለው መሆኑን እንዲያውቅ ማድረጉን፣ በማስፈራራት ትግሉን መግታት እንደማይቻልና ለዚህም ለነጻነታቸውና ክብራቸው የቱንም መስዋዕትነት ለመክፈል የተዘጋጁ ታጋዮች በተለይም ወጣቶች መኖራቸውን እንዳሳየበት ገልጾአል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የህዝቡ የለውጥ ፍላጎት የደረሰበትን ደረጃና የንቃተ ኅሊና መዳበር፣ ህዝቡ ለፈጠራ ወንጀሎች እንዳይፈራና ይልቁንም በመንግሥት አሠራርና አመራር ላይ ያለው እምነት ከጥያቄ እንዲወድቅ፣ ፖሊስንና ፍርድ ቤቶችን ጨምሮ አስፈጻሚ አካላት ያለባቸውን ተጠያቂነት እንዲረዱና ራሳቸውን እንዲጠይቁ የሚያስችል ስሜት ፈጥሬበታለሁ ብሏል፡፡
‹‹የገዢውን ፓርቲ እየባሰ የመጣውን አምባገነናዊ ባህሪይ አጋልጠን፣ ኢትዮጵያዊያን ለተባበረ የጋራ ትግል ያላቸውን ድጋፍ በተግባር ተመልክተን፣ የጀመርነው የ‹‹ነጻነት ለፍትሃዊ ምርጫ›› ፕሮግራማችንን ትክክለኛለትና ተቀባይነት ለክተን ትግሉ ወደማይቀለበስበት የላቀ ደረጃ መሸጋገሩን አረጋግጠናል፡፡›› ያለው ትብብሩ የጋራ ትግሉን በበለጠ ጽናትና የኃላፊነት መንፈስ በመምራት የሁለተኛ ዙር እቅዱን በቅርብ ቀን ይፋ እንደሚያደርግ ገልጾአል፡፡
ትብብሩ በአንድ ወሩ መርሓ ግብር ወቅት በአገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ላደረጉለት ሁለንተናዊ ድጋድ፣ በስርዓቱ እርምጃ በመቃወም በሰልፍ፣ በመግለጫ፣ በታሰርንበት አስፈላጊውን በማቅረብና በመጠየቅ ላደረጉት ትብብር ምስጋናውን አቅርቧል፡፡ በተመሳሳይ የወሩ መርሓ ግብር ከተጀመረ አንስቶ ጉዳዩን ለህዝብ ለማሳወቅ የጣሩትን በአገር ቤትና በውጪ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን፤ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ በማመስገን በቀጣዩ ፕሮግራም ከጎኑ እንዲቆሙ ጥሪ አስተላልፏል፡፡
በሌላ በኩል ገዥው ፓርቲ ‹‹ለማንም የማይበጅ አካሄድ መርምሮና የህዝቡን የለውጥ ፍላጎት ተረድቶ ቆም ብሎ ራሱን እንዲፈትሽ፣ ከገባበት ፍርኃትና ሥጋት ተላቆ ለህዝብ ጥያቄዎች ተገቢውን ወቅታዊ ምላሽ በመስጠት ህገ መንግሥቱን አክብሮ እንዲያስከብር›› ሲል ጥሪ አቅርቧል፡፡

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen