Netsanet: እሺ አሁንስ ባህር ዳር ላይ ደግሞ ወገኖቼን ለምን ገደላችሗቸው

Sonntag, 28. Dezember 2014

እሺ አሁንስ ባህር ዳር ላይ ደግሞ ወገኖቼን ለምን ገደላችሗቸው

December 27, 2014
ለዚህ ደርግ ኢሰፓ ዜጎችን አይደለም ዝነብ አይገልም

ዳዊት ዳባ

የባህር ዳር ህዝብ ይህን ቦታ እጅግ ለረጅም አመታት ለአምልኮ ስንጠቀምበት የነበረ ነው። ለባለ ሀብት መሰጠቱና ለሌላ አገልግሎት እንዲውል መወሰኑ ትክክል አይደለም ብሎ ቅሬታውን ሊያሰማ አደባባይ ወጣ። ይህ ለእምነቱ የሰናፍጭ ቅንጣት ታህል ቀናዊ የሆነ በአገሬ ጉዳይና በኑሮዬ እሚንት የምታህል መብት አለኝ ብሉ የሚያስብ የየትም አገር ዜጋ ሊያደረገው የሚችል ነው። በእውን ይህን ማድረግ የሚከለከል ወይ ማድረጉስ ወንጀል የሚደረግበት ህዘብ በአለም ላይ አለ ወይ?። እኔ እይመስለኝም።
Bahir Dar protest
በባህርዳር የተቃውሞ ሰልፍ በወያኔ ታጣቂዎች ድብደባ ከተፈጸመባቸው ውስጥ አንዱ
በዋናነት ቅሬታቸውን ሰልፍ ወጥተው ማሰማታቸው የህግ አግባብ ያለው ነው። ህዝብ ይህን ማድረጉ ተፈጥራዊም ህገ መንግስታዊም እምነታዊም መብት መሆኑ ደምቆ ይሰመረብት። ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ቅሬታቸውን ማቅረባቸውንም እንዲሁ።
ይህም ሆና በባህር ዳር ላይ የሆነው እጅግ እጅግ በጣም ቀላል ነገር ነበር። መገድል መደብደብ ማዋከብ ውስጥ ሳይገባ ይህን የህዝብ ቅሬታ ማስተናገድ በቀላሉ የሚቻልባቸው መንገዶች ነበሩ።የሚያዳምጥ አካል በመላክ ቅሬታውን ማዳመጥን ብቻ ነበር እኮ የሚፈልገው። የህዝቡ ቅሬታ እውነታ ከሌለው እውነታውን ማስረዳት። የህዝቡ ቅሬታ እውነትነት ኖሮት ቦታው ለሌላ አገልግሎት ተሰጥቶ ከሆነ ውሳኔው የተላለፈበትን አግባብና በልዋጭ ህዝብ አምልኮውን የሚፈፅምበት ቦታ ተዘጋጅቶ ከሆነ ይህንን መንገርና በቀላሉ ሰላማዊ ፍፃሜ መስራት ይቻል ነበር። ሌላ ሶስተኛ አካል ከጀርባ ህዝብን አሳስቷል። ነጭ የገዳዬች ምክንያት ነው። ካልሆነ ከጨፈጨፍክ በሗላ ሳይሆን እዛው ሰልፉ ላይ አሳስተዋችሁ ነው። የምታቀርቡት ቅሬታ ምንም መሰረት የሌለው ነው። በማለት የተፈጠረውን አለመግባባት ማጥራት አይቻልም ነበር ወይ?። ቅሬታው አግባብ ኖሮት ውሳኔው የተላለፈበትን አግባብ እዛው መንገሩ ጥሩ አይሆንም ተብሎ ከታሰበም። ቅሬታውን አድምጠናል።
መልሳችንን በዚህ ቀን በዚህ መንገድ እንሰጣለን ማለትንስ ማንን ገደለ። አዎ ይህን በማድረግ በሰለጠነው መንገድ መጨረስ ስትችሉ ፈጇችሗቸው።
ሁላችንም ማወቅ ያለብን እንደሁሌው ይህ እጅግ ቀላል ነግር በዚህ አይነት አሳዛኝ ሁኔታ የተፈፀመው አምጠንም ሰበብ ልንወልድልት በማይቻለን ስልጣን ላይ ያሉት የትግሬ ወያኔዎች በመሆናቸው ነው። አንድነት፤ ሰማያዊ፤ አዎ ኢሰፓም ብቻ የትኛውም አካል ስልጣን ላይ ቢሆን ኖሮ የሚያደርገው ካላይ ያልኩትን ነበር።
በእርግጠኛነት የምናገረው ለዚህ ቀላል ነግር የሰው ልጅ ለዛውም ዜጋ አይደለም ዝንብ አይሞትም ነበር። እናንተ ግን በምታውቁትና ሁሌም የዚህ አይነት የህዝብ ቅሬታን በምታስተናግዱበት መፍጀት በእድሜ የጠገቡ አሮጊቶችንና ለአካለ ስንኩላን እንኳ ሳትራሩ ዘግናኝ ወንጀል በድጋሚ ፈፀማችሁ። ግን ለምን?። ለምን ለሰው ለጅ ለዛውም ለወገናችሁ ሂወት የምትሰጡት ክብር እዚህ ደረጃ ወረደ?። ህዝብን ማሸበር እንዴት ነው እንደዚህ ደስታን እየሰጣችሁ ያለው?። ጎበዝ ግርም የሚል ነገር እኮ ነው የገጠመን።
ይህ በመፍጀት የሚነሱ የመብት ጥያቄዎችንና ቀላል ቅሬታዎችን ሁሉ መፍታት ለሀያ ሶስት አመት ሙሉ በተደጋጋሚ ሲፈፀሙ የነበረ መሆኑን ልብ እንበል። ሚሊዬኖችን ቀጥቅጠውበታል። በመቶ ሺዎች ገድለውበታል። በመቶ ሺ ዎች በየማጎርያው የመከራ ሂወት እንዲገፉበት አድርገዋል። ሚሊዬኖችን አሰድደዋል። ብዙዎችን ያለወላጅ አስቀርተዋል። ይህ ግፍ የተፈፀመባቸው ብዙዎቹ ይህን አይነቱን በሽታ ዝም ስለተባለ ማቆሚያ የሌለው መሆኑን በጠዋቱ አውቀው አቁሙ ስላሉ መሆኑን ደግሞ አንዘንጋ።
ዛሬም የሆነ አይነት “መንግስት” አድራጋችሗቸው ህግና ስርአትን ከማስከበር አኳያ፤ እንዲሁም በአደባባይ ስሜትን ለመግለፅ ከማሳወቅ በሉት ከማስፈቀድ የህግ አግባብ አኳያ እያያችሁ ትርጉም እንዲሰጣችሁ እየጣራችሁ ያላችሁ ትኖራላችሁ። እውነት እውነት እላችሗለው በጣሙን ተሳስታችሗል። እሩቅ ቦታ ሳልሄድ ሀዘን ደስታ ንዴት የስሜት ጉዳዬች ናቸው። ሁሌ በቀጠሮ የምናደርጋቸው አይደሉም። የሄን ደግሞ እኔ ስላልኩ አይደለም። ወያኔዎችም ያውቃሉ። ብሄራዊ ቡድናች ሌላ ጊዜ ደግሞ እሯጮቻችን አሸነፉ ብሎ ይህው ህዝብ በብዙ ቁጥር በደስታ ስሜት ብዙ ጊዜ ሳያስፈቅድ አደባባይ ወጥቷል። ገደሉት?። አልገደሉትም። ጦርነት አሸነፍን ባድሜ ለኛ ተወሰነ ብሎ ደስታውን ለመግለፅ ህዝብ አደባባይ በብዙ ቁጥር ወጥቶ ነበር። ፈጅት ፈፀሙበት?። አልፈፅሙም። መለስ ሞተ ብለው ሀዘኑን ሊገለፅ ነው ብለው ያለ ምንም ፍቃድ አሁንም አደባባይ ያወጡትን ህዝብ ፈጁት?። አልፈጁትም። እነሱ ደስታቸውን፤ ዝክራቸውንና ስኬታቸውን ሊነግሩን የበዛውን ጊዜ አደባባዩን የሚጠቀሙና ሲሰበሰቡ የሚውሉ ናቸው። እያስፈቀዱ ስለመሆኑ የምታውቁት ነገር አለ?። አስፈቀዱ ወይ ተከለከሉስ ሲባል ሰምታችሁ ታውቃላችሁ?። ወይ እዚህ ቦታ መሰብሰብ ወይ መሰለፍ አትችሉም ተባሉስ ሲባልስ?። ሲቀሰቅሱ አባላት ታሰሩባቸውስ ሲባል ሰምታችሗል?። አውቃለው ጥያቄዬ የሞኝ እንደሚመስል። የማነሳው ግን ህጋዊነት ላይ ጠንካራ እምነት አለችሁና እነሱ ከህግ በላይ ናቸው እንደማትሉ ገምቼ ነው።
ወያኔንና ወንጀሎቹንና ጥፋቶቹን በሚመለከት ተሳስታችሗል ስላልኩ አይክፋችሁ። ይህን ለጉድ የገነነብንን ድርጅት በሚመለከት ማንም ሁሌ በሁሉ ነገር ትክክል ሆኖ አያውቅም። ሁሌ ትክክል መሆንም ለማንም ቀላል አልሆነም። በዙ ጊዜ የህዝብ ስህተተኛነት ከጨዋነትና አርቆ ከማሰብም እንደሚመጣም አሳምሬ አውቃለው። ደጋፊዎቹን እንተዋቸውና ወያኔዎችን በብዙ ድምር ምክንያቶች መሰረት አድርጎ በጭራሽ የማይፈይድና ጎጂ ቡድን ነው። ለመልካም በቶሎ መጥፋት አለበት ብለን ያሰመርን ብዙዎች አለን። በሌላ ወገን ደግሞ በእምነቱ ለመቆየት የሚያያቸውንና የሚሰማቸውን አስገራሚ፤ዘግናኝ ጥፋቶችና ወንጀሎችን በሙሉ በሚቻለው ሁሉ አመክንዮ ሊሰራባቸው፤ትርጉም እንዲሰጡት ሲጥር ሲጥር የሚኖር አለ። ምክንያታዊ ለመሆን ከእለት እለት እየከበደውና እጅጉኑ እየተቸገረ ያለ ቢሆንም ተስፋው ፈፅሞ ያለተሟጠጠ ወይ እንዳይሟጠጥ እየጣረ ነው። ይህ ክፍል ብዛቱ ቀላል የማይባል እንደሆነም ይታወቃል። ወያኔዎችን በሚመለከት ሁላችንም በሁሉ ነገር ሁሌ ትክክል ለመሆን ይከብደናል ስል ግን በሁሉም ወገን ያለነው ስህተት ስለምንሰራ ነው። የኔን በሰሞኑ የተገለፀልኝን ደደብ የነበረ ስህተት ልንገራችሁ።
በጠኔ ለሚሰቃይና ልጆቹን መመገብ ለቸገረው ብዙ ሚሊዬን ህዝብ እርቦናል ሲላቸው ጠግበሀል ብለው ሲከራከሩት እሰማለው። አንዷለም እስክንድርና፤ ዞን ዘጠኞችን አሸባሪ ስለሆኑ ነው ብለው ሲከራከሩ እሰማለው። ቦንብ አፈንድተው ገድለው እነንትና ናቸው ብለው ሲከራከሩን እሰማለው። ቤተሰቦቻችንን ሰብስበው ልጆቻችሁን አሁን እንገላለን ወይ ልንገላቸው አምሮናል ሲሉና ሲደነፉ እሰማለው። እነዚህ እንደው ለምሳሌ ነው ያቀረብኳቸው። ሁሌና ሁሉ ነገራቸው አስገራሚ ድርቅና ያለበት፤ አሳማኝና አግባብ ያለው እንዲመስል እንኳ ቅንጣት ታክል የማይጨነቁበት እንደሆነ አውቃለው። የበዛ ድፍረትም አይባልም ጥጋብ ያለበቻው መሆኑን አውቃለው። በዚህ ደረጃ ነው እየተረዳሗቸው ነው እንግዲህ። እንደዚህ የሚያደርጉት ለምንድን ነው?። ለሚለው ጥያቄ መልስ ለመስጠት ስሞክር የተሳሳትኩት።
የሚመስለኝ የነበረው ከጠቅላላ የመሀበረባችን ግንዛቤ፤ የድህነቱ ደረጃ፤ የበዛው ዜጋ ከነሱ ወገን የሚቀርበውን መረጃ ብቻ ስለሚያገኝ፤ ያልቆረጠለትና እንዲቆርጥለት የማይፈልገው ዜጋ ገና ብዙ ቁጥር ያለው ስለሆነ። ምንም ብንለው ሀሳቡን የገዛዋል ከሚል ነው አይነት ምክንያቶችን እደረድር ነበር። የሚመስለኝ የነበረው እነዚህንና የመሳሰሉ ነገሮች በጥልቅ አስበው፤ አይተውትና አስልተው፤ ሌሎች መንገዶች መኖራቸውን ቢያውቁም ላሁን መፍጀቱ መቀጥቀጡና ማሰሩ ይሻላል፤ ያዋጣልም፤ ሰርቷልም ብለው በማወቅ የሚያደርጉት ነበር የሚመስለኝ። ስህተቴን ያሳየኝ በሰሞኑ በስዊድን ዜጎች ላይ ያደረጉት የመግደል ሙከራና እንግሊዛዊ ዜግነት ያለውን ግለሰብ መግደላቸው ነው። ለምን የነዚህ አገር ዜጎች እንደተመረጡ ማወቁ አልከበደኝም። ለምን መግደሉን መረጡ ለሚለው ጥያቄ ግን ከዚህ በፊት የምደረደርው ምክንያቶች አንዳቸውም በጭራሽ እንደማይሆኑ ተረዳው። እስከዛሬም ስህተቴ አለማወቅ ብቻ ሳይሆን እውነቱን ለማመን አለመፈለግ [Denial] እንደነበረበትም አወኩ። ምን ላድርግ ስልጣን ላይ ያለን አካል በዚህ ደረጃ ለማወቅ የሚያስፈራ ነገር አለው።
ለማንኛውም ይህን በሽታ ዝም ብለን እንዲቀጥል አናድርገው። በጭራሽ አይቆምም። በአንክሮ ላጤነው በፈጠነ ሁኔታ እየጨመረ እየባሰበት እየሄደ ነው። ብዙ ልናደርጋቸው የምንችላቸው ነገሮች አሉ። ልናደርግ የምንችለውን የምር አድርገን ልናስብበት ግን እንጀምር። ላሁኑ የተቃውሞ ሰልፎች ታቅደዋል እንቀላቀል።
ሁላችንም ልናደረገው የምንችላቸው ቀላል የሆኑ ነገሮች ደግሞ ብዙ አሉ። እነዚህን አንዳኗም ሳናስቀር ሁላችንም ዛሬ ማድረግ እንጀምር። አሁን ለምሳሌ እድሜያችሁ ለመምረጥ የደረሳችሁ በሙሉ ማድረግ የምንችለው ስለሆነ እባካችሁ ሄደን የመምርጫ ካርዳችንን አሁኑኑ እንውሰድ። የተለያየ አመለካካት ምርጫው ላይ ሊኖረን ይችላል። ቅንጦት ቢኖርበትም ይህ ችግር አይደለም። ልዩነቱ ላይ መጨቃጨቁ ይቀጥል። ማወቅ ያለብን አገዛዙ ምርጫ አለ፡፤ ውጡና ምረጡ ብሎን ይህን ማድረጋችን ደግሞ የሚረብሸውና የሚያስጨንቀው መሆኑን ነው። ደግሞ ፍራቻው ምክንያታዊም ትክክልም ነው። ሁላችንም ከተመዘገብን ምርጫ የሚባለው ነገር እራሱ ቀርቷል ሊሉ ወይ ካርድ ሊያወጣ የተሰለፈ ህዘብ ላይ ደግሞ ልተወው። ብቻ ትግል ብለን ካደረግነው ትግል የማይሆን ምንም እስከጭራሹ ምንም ነገር የለም። እስቲ ነገ ፖሊሱንም፤ ወታደሩንም፤ ደህንነቱንና ካድሬዎችን በተለየ ሁኔታ ሞቅ አድረገን ፈገግታ መስጠትና ሰላም ማለት ሁላችንም እንጀምር። ድርጊታችንን ትግል ነው እንበለው። በእርግጠኛነት በነጋታው መሳቅ ከአሸባሪነት ጋር ተያይዞ በኢቲሺ ሲተነትኑበት ትሰማላችሁ። ቆያይቶ ደግሞ ማግጠጥ ይባልና ህገ መንግስትን በመናድ የሚል ህግ ተጠቅሶበት እስር ቤት የሚገባ ይኖራል። ብቻ ዝም አንበል። በሆነ መንገድ በግፍ ለገደሏቸው ወገኖቻችን መቆርቆራችንን እናሳይ። ላሁኑ እንጠራራ፤ እንሰባሰብ፤እንቀሳቀስ ሄደን ከርዳችንን በእጃችን እናስገባ። የተቃውሞ ሰልፎችን በገፍ ወጥተን እንቀላቀል።
የሞቱትን ነብስ ይማር። መፅናናቱንና ጥንካሬውን ለሁላችንም ይስጠን።

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen