Netsanet: ሰማያዊ ፓርቲ የሚያዚያ 19ኙን ሰልፍ ለሌላ ቀን እንዲቀይር የአ.አ አስተዳደር ጠየቀ

Samstag, 19. April 2014

ሰማያዊ ፓርቲ የሚያዚያ 19ኙን ሰልፍ ለሌላ ቀን እንዲቀይር የአ.አ አስተዳደር ጠየቀ

April18/2014


የሰማያዊ ፓርቲ ሚያዚያ 19 ቀን ሰልፍ ለማድረግ ላሰገባዉ የማሳወቂያ ደብዳቤ ፣ ከአዲስ አበባ አስተዳደር ምላሽ እንዳገኝ ሰማያዊ ፓርቲ ገለጸ። የአስተዳደሩ ደብዳቤ፣ ሰልፉን በታሰበው ሚያዚያ 19 ቀን፣ ማድረግ እንደማይቻልና ለሌላ ቀን እንዲያስተላልፈው የሚጠይቅ ሲሆን፣ የሰማያዊ ፓርቲ ግን፣ ለሰልፉ መራዘም የቀረቡት ምክንያቶች በቂ አይደሉም በሚል፣ ቀኑን እንደማይለወጥ፣ ባስገባው ሁለተኛ ደብዳቤ ለአስተዳደሩ አሳዉቋል።
የሰማያዊ ፓርቲ በላከው ሁለተኛ ደብዳቤ፣ አስተዳደሩ ሰልፉ እንዲራዘም የተጠየቀበት ምክንያቶች እንዳሉ ቢጠቁምም፣ ምክንያቶቹ በቂ አይደሉም ከማለት ወጭ ፣ የቀረቡት ምክንያቶችን ግን በመግለጫዉ አልዘረዘረም። አስተዳደሩ ለፓርቲዉ የላከዉንም የቀኑን አራዝሙ ደብዳቤ ለማግኝት ያደረግነው ሙከራም አልተሳካም።
የአገሪቷ ሕግ «ሰላማዊ ሰልፉ ወይም ህዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባው በሌላ ጊዜ ወይም በሌላ ስፍራ ቢደረግ ይሻላል የሚል አስተያየት ካለውም ምክንያቱን በመግለፅ ይህንኑ ጥያቄው በደረሰው በ12 ሰዓት ውሳጥ በፅሁፍ ለአዘጋጁ የማሳወቅ ኃላፊነት አለበት ………ሆኖም የከተማው ወይም የአውራጃው አስተዳደር ፅ/ቤት ሰላማዊ ሰልፉ ወይም ህዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባው ምንጊዜም በየትኛውም ቦታ ሊካሄድ አይችልም ማለት አይችልም» ሲል የዜጎችን ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት የመንፈግ ስልጣን ማንም እንደሌለው የሚደነግግ መሆኑ ይታወቃል።
የአዲስ አበባ አስተዳደር ሚያዚያ 26 ቀን፣ አንድነት ፓርቲ ለጠራው ሰልፍ እውቅና እንደሰጠ መዘገቡ ይታወሳል። ምናልባትም ለሰማያዊ የሚያዚያ 19 ሰልፍ እውቅና አልሰጠም ያለው፣ ሰማያዊ ቀኑን ወደ ሚያዚያ 26 ቀን እንዲያዞርና፣ የሰማያዊም የአንድነትም ሰልፍ በአንድ ቀን ፣ ግን በተለያዩ ቦታዎች እንዲደረግ አስቦ ሊሆን እንደሚችል አንዳንዶች ይናገራሉ።
ሰማያዊ ለአስተዳደሩ ያስገባዉን ደብዳቤ ለማንበብ ከታች ይመልከቱ
========================================
ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር ከንቲባ ጽ/ቤት
የሰላማዊ ሰልፍና ሕዝባዊ ስብሰባ ማሳወቂያ ክፍል
ጉዳዩ፡- የሰላማዊ ሰልፍ ፕሮግራማችንን በድጋሚ ስለማሳወቅ
ፓርቲያችን ሚያዝያ 19/2006 ዓ.ም ለሚደረገው ሰላማዊ ሰልፍ መስተዳድሩ አስፈላጊውን ህጋዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ሚያዝያ 7/2006 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ ማሳወቃችን ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጅ የስብሰባና ሰላማዊ ሰልፍ ማሳወቂያ ክፍሉ ሚያዝያ 7/2006 ዓ.ም በጻፈው ደብዳቤ ‹‹የሰላማዊ ሰልፍ ጥያቄያችሁ ይመለከታል›› በሚል ያለ በቂ ምክንያት እቅዳችንን ለሌላ ጊዜ እንድናስተላልፍ ገልጾልናል፡፡
ነገር ግን በአዋጁ መሰረት ሰላማዊ ሰልፍ የጠራው አካል ሰልፉን በሌላ ጊዜ እንዲያስተላልፍ ማዘጋጃ ቤቱ መጠየቅ የሚችለው በጠየቀበት ቀን ከአቅም በላይ የሆነ አሳማኝ ምክንያት ሲኖር ብቻ ነው፡፡ በዚህም መሰረት በመስተዳድሩ በኩል የተገለጸልን አሳማኝ ምክንያት ስለሌለ ያቀድነውን ሰላማዊ ሰልፍ በያዝነው ፕሮግራም ማለትም ለማዘጋጃ ቤቱ በቁጥር ሰማ/180/06 በተጻፈ ደብዳቤ ባሳወቅነው መሰረት ሚያዝያ 19/2006 ዓ.ም የምናካሂድ መሆኑን እየገለጽን አስተዳደሩ በህግ የተጣለበትን ኃላፊነት እንዲወጣ በድጋሚ እናሳውቃለን፡፡
ከሠላምታ ጋር!

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen