Netsanet: የአዲስ አበባ መስተዳድር የሰማያዊ ፓርቲን የሰላማዊ ሰልፍ የእውቅና ደብዳቤ ተቀበለ

Donnerstag, 17. April 2014

የአዲስ አበባ መስተዳድር የሰማያዊ ፓርቲን የሰላማዊ ሰልፍ የእውቅና ደብዳቤ ተቀበለ

April 17/2014
የአዲስ አበባ መስተዳድር የሰማያዊ ፓርቲን የሰላማዊ ሰልፍ የእውቅና ደብዳቤ ተቀበለ


ሰማያዊ ፓርቲ ትናንት ሚያዚያ 7/2006 ዓ.ም ለአዲስ አበባ መስተዳድር ከንቲባ ጽ/ቤት ሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ ማሳወቂያ ክፍል ሚያዝያ 19/2006 ዓ.ም ለሚያደርገው ሰላማዊ ሰልፍ የእውቅና ደብዳቤ አስገብቶ የነበር ሲሆን በወቅቱ ሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ ማሳወቂያ ክፍሉ ‹‹በተጠየቀው ዕለት ሌሎች ፕሮግራሞች አሉብኝ!›› በሚል አሳማኝ ያልሆነ ምክንያት የቀን ለውጥ እንዲያደርጉ በደብዳቤ ገልጾ ነበር፡፡ 

ነገር ግን ሰማያዊ ፓርቲ ጽ/ቤቱ የቀን ለውጥ እንዲደረግ ያቀረበው ምክንያት አሳማኝ ያልሆነና ጽ/ቤቱ በህግ የተሰጠውን ኃላፊነት ያላገናዘበ መሆኑን ጠቅሶ ሰልፉን በታቀደው ቀንና ሰዓት እንደሚያደርግ በድጋሚ ዛሬ ሚያዝያ 8/2006 ዓ.ም በደብዳቤ አሳውቋል፡፡ ሆኖም የጽ/ቤቱ ኃላፊ አቶ ማርቆስ በዛብህ ‹‹ደብዳቤውን አልቀበልም፡፡ እንደለመዳችሁት ውጡና ተደብደቡ›› የሚል ምላሸ ሰጥተው እንደነበር የሰልፉ አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ብርሃኑ ተክለያሬድ ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጅ አስተባባሪዎቹ ደብዳቤውን የመቀበል ግዴታ እንዳለባቸው በመግለጽ፤ ደብዳቤውን ካልተቀበሏቸው ከቢሮው እንደማይወጡ በማሳወቃቸው ኃላፊው የእውቅና ደብዳቤውን ፈርመው መቀበላቸው ታውቋል፡፡ 
በየ ክፍለ ከተማው የሰላማዊ ሰልፍ አስተባባሪ ኮሚቴ አቋቁሞ ሲንቀሳቀስ የቆየው ሰማያዊ ፓርቲ ቅስቀሳውን አጠናክሮ እንደቀጠለና በቀጣይ ቀናትም የመኪና ላይና የቤት ለቤት ቅስቀሳ እንደሚደረግ አስተባባሪ ኮሚቴው አስታውቋል፡፡

በድጋሚ የቀረበውን ደብዳቤ ከዚህ በታች ይመልከቱ፡-

ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር ከንቲባ ጽ/ቤት 

የሰላማዊ ሰልፍና ሕዝባዊ ስብሰባ ማሳወቂያ ክፍል

ጉዳዩ፡- የሰላማዊ ሰልፍ ፕሮግራማችንን በድጋሚ ስለማሳወቅ 

ፓርቲያችን ሚያዝያ 19/2006 ዓ.ም ለሚደረገው ሰላማዊ ሰልፍ መስተዳድሩ አስፈላጊውን ህጋዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ሚያዝያ 7/2006 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ ማሳወቃችን ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጅ የስብሰባና ሰላማዊ ሰልፍ ማሳወቂያ ክፍሉ ሚያዝያ 7/2006 ዓ.ም በጻፈው ደብዳቤ ‹‹የሰላማዊ ሰልፍ ጥያቄያችሁ ይመለከታል›› በሚል ያለ በቂ ምክንያት እቅዳችንን ለሌላ ጊዜ እንድናስተላልፍ ገልጾልናል፡፡ 
ነገር ግን በአዋጁ መሰረት ሰላማዊ ሰልፍ የጠራው አካል ሰልፉን በሌላ ጊዜ እንዲያስተላልፍ ማዘጋጃ ቤቱ መጠየቅ የሚችለው በጠየቀበት ቀን ከአቅም በላይ የሆነ አሳማኝ ምክንያት ሲኖር ብቻ ነው፡፡ በዚህም መሰረት በመስተዳድሩ በኩል የተገለጸልን አሳማኝ ምክንያት ስለሌለ ያቀድነውን ሰላማዊ ሰልፍ በያዝነው ፕሮግራም ማለትም ለማዘጋጃ ቤቱ በቁጥር ሰማ/180/06 በተጻፈ ደብዳቤ ባሳወቅነው መሰረት ሚያዝያ 19/2006 ዓ.ም የምናካሂድ መሆኑን እየገለጽን አስተዳደሩ በህግ የተጣለበትን ኃላፊነት እንዲወጣ በድጋሚ እናሳውቃለን፡፡

ከሠላምታ ጋር!

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen